በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስተዋጽኦ ማዘጋጀት

አስተዋጽኦ ማዘጋጀት

ጥናት 9

አስተዋጽኦ ማዘጋጀት

1–4. የአንድ ንግግር መልእክትና ዋና ዋና ነጥቦች ምን መሆን እንዳለባቸው እንዴት መወሰን ይቻላል?

1 የወንጌል ጸሐፊ የነበረው ሉቃስ ለወዳጁ ለቴዎፍሎስ “እኔ ከመጀመሪያው አንሥቼ ሁሉን ነገር በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ ታሪኩን በቅደም ተከተል እጽፍልህ ዘንድ መልካም ሆኖ ታየኝ” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 1:3 የ1980 ትርጉም ) ስለዚህ በቂ ጥናትና በልዩ ልዩ ጽሑፎች ላይ ምርምር ካደረገና ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን መረጃዎች በሙሉ ከሰበሰበ በኋላ ቅደም ተከተሉን ለመረዳት በሚቀል መንገድ ማደራጀት ጀመረ። እኛም ንግግራችንን ስንዘጋጅ ይህንኑ ልማድ ብንከተል በጣም እንጠቀማለን። አስተዋጽኦ ማዘጋጀት ይኖርብናል ማለት ነው።

2 ዋና ዋና ሐሳቦችን መምረጥ። የምንናገረው፣ በተለይም ስለ አምላክ ቃል ከሰዎች ጋር ውይይት የምናደርገው ሐሳቦችን ወደ ሌላ ሰው አእምሮ ለማስተላለፍ ስለሆነ ልናስተላልፍ የፈለግነው ሐሳብ በቅድሚያ በራሳችን አእምሮ ውስጥ ግልጽ መሆንና በትክክል መቀረጽ ይኖርበታል። ለንግግርህ የሚያስፈልጉትን መረጃዎች በሙሉ ከሰበሰብህ በኋላ አድማጮችህ ምን ነገር በአእምሮአቸው ይዘው እንዲሄዱ እንደምትፈልግ ለመወሰን ትችላለህ። ይህን ልታስተላልፍ የምትፈልገውን መልእክት በአንድ አረፍተ ነገር ለማስቀመጥ ሞክር። ይህ አረፍተ ነገር የንግግርህን ፍሬ ሐሳብ አጠቃልሎ የሚገልጽ ከሆነ ወይም አድማጮችህ እንዲያስታውሱ የምትፈልገውን ዋነኛ ቁም ነገር በሚገባ የሚያስረዳ ከሆነ የንግግርህ መልእክት ሆኖ ሊያገለግልህ ይችላል። በምትዘጋጅበት ጊዜ ሁሉ መለስ እያልክ ለማየት እንድትችል ይህን መልእክት ብትጽፈው ጥሩ ይሆናል።

3 አሁን ከሰበሰብከውና ካደራጀኸው መረጃ ውስጥ ይህን ዋና መልእክት ለማስተላለፍ የሚያስፈልጉትን ዋና ዋና ሐሳቦች ምረጥ። እነዚህ ሐሳቦች የንግግሩ ዋና ዋና ነጥቦች ሆነው ያገለግላሉ። ትምህርቱን ያዘጋጀኸው በተለያዩ ካርዶች ላይ ከሆነ እነዚህን ካርዶች ጠረጴዛህ ላይ በቅደም ተከተል አስቀምጣቸው። አሁን ደግሞ እነዚህን ዋና ዋና ነጥቦች ለመደገፍ የሚያስፈልጉ ሌሎች ነጥቦችን ምረጥና ከሚደግፉአቸው ዋና ዋና ነጥቦች አስከትለህ በየቦታቸው አስቀምጥ። የሰበሰብካቸውን ዋና ዋና ነጥቦችና በእነርሱ ሥር ያሉትን ሐሳቦች በአስተዋጽኦው ውስጥ በየቦታቸው በምታስቀምጥበት ጊዜ አንዳንዶቹ ነጥቦች የንግግርህን መልዕክት ለማስፋፋት የማያስፈልጉ እንደሆኑ ትገነዘብ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉትን ነጥቦች ለማስወጣት አታመንታ። ንግግርህን አግባብነት በሌላቸውና በማያስፈልጉ ነጥቦች ከምታጨናንቅ እነዚህን ነጥቦች ብታስቀር የተሻለ ይሆናል። በተጨማሪም ትምህርትህ ሊገባ በሚችል ቅደም ተከተል የተቀነባበረ መሆኑን አረጋግጥ። እዚህ ላይ በተሰጠው ሐሳብ መሠረት የምትዘጋጅ ከሆነ የሐሳብ መቆራረጥ ወይም የቅደም ተከተል መዛባት በሚኖርበት ጊዜ ከአስተዋጽኦው በቀላሉ ለማስተዋልና ለማስተካከል ትችላለህ። እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ከፊቱ ካለው ዋና ነጥብ ጋር የተያያዘና የንግግሩን መልእክት ለማዳበር የሚጠቅም መሆኑን ለማረጋገጥ ትችላለህ። በተጨማሪም በእነዚህ ዋና ዋና ርዕሶች ሥር የሰፈሩት ነጥቦች ተገቢውን ድጋፍ ስለሚሰጡ ንግግሩ ቅደም ተከተሉ የተጠበቀና ለመረዳት የማያዳግት ሐሳብ ለማስተላለፍ ይችላል።

4 እስከ አሁን ያቀናበርካቸው ነጥቦች በንግግርህ አካል ውስጥ መካተት የሚኖርባቸው ናቸው። አሁን ደግሞ መግቢያና መደምደሚያ ያስፈልግሃል። ለንግግርህ ካዘጋጀኸው መልእክት ጋር የሚጣጣም መክፈቻና አድማጮችህ ከንግግርህ ዓላማ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያነሳሳ መደምደሚያ ምረጥ። አሁን ይህን ያቀናበርከውን አስተዋጽኦ ለመጨረሻ ጊዜ በአንድ ወረቀት ላይ ለመጻፍ ዝግጁ ሆነሃል። ይህንንም በተለያዩ መንገዶች ለማድረግ ትችላለህ።

5, 6. የአርዕስት አስተዋጽኦ ምንድን ነው? የዓረፍተ ነገር አስተዋጽኦስ?

5 የአስተዋጽኦ ዓይነቶች። በጣም የተለመዱት የአስተዋጽኦ ዓይነቶች ሁለት ናቸው። እነርሱም አርዕስታዊ እና በአረፍተ ነገር መልክ የሚዘጋጁ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ሁለቱም ዘዴዎች አንድ ላይ ተጣምረው ይሠራባቸዋል። አርዕስታዊ አስተዋጽኦ ለማዘጋጀት በገጹ አናት ላይ የንግግርህን መልእክት ጻፍ። ከዚያም ዋና ዋና ነጥቦቹን ከንግግሩ መልእክት ግርጌ አሳጥረህ ጻፍ። እያንዳንዱ ዋና ነጥብ በገጹ የግራ ኅዳግ ጀምሮ ይጻፋል። ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ነጥቦች ከሚደግፉአቸው ዋና ዋና ነጥቦች ግርጌ ወደ ቀኝ ገባ ብለው ይጻፋሉ። ሁለተኛ ደረጃ ለተሰጣቸው ለእነዚህ ነጥቦች ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሰጡ ነጥቦች ካሉ በሦስተኛ ደረጃ ገባ ብለው ሊጻፉ ይችላሉ። አሁን ወረቀትህን ትንሽ በመመልከት ብቻ አድማጮችህ እንዲረዱ የምትፈልገውን ዋና ሐሳብ የሚያብራሩት ዋና ዋና ነጥቦች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ትችላለህ። ይህም ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ በጣም ይጠቅምሃል፤ ምክንያቱም እያንዳንዱን ዋና ሐሳብ የሚያብራሩትን ቁልፍ ቃላት በመደጋገም ጠበቅ ለማድረግና በአድማጮች አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጹ ለማድረግ ትችላለህ። እያንዳንዱን ዋና ነጥብ በምታብራራበት ጊዜ በዚሁ ዓይነት ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ጠበቅ አድርግ። በዚህ ዓይነቱ አስተዋጽኦ ትኩረት የሚደረገው ሐሳቡን በአጭሩ ለመግለጹ ጉዳይ ነው።

6 ሌላው የተለመደው የአስተዋጽኦ ዓይነት በአረፍተ ነገር መልክ የሚዘጋጅ አስተዋጽኦ ነው። በዚህ ዓይነቱ አስተዋጽኦ እያንዳንዱ ሐሳብ በተሟላ አረፍተ ነገር ይገለጻል። ቢሆንም እያንዳንዱ አረፍተ ነገር የአንድን የንግግር አንቀጽ ፍሬ ሐሳብ አጠቃልሎ የሚይዝ መሆን ይኖርበታል። እርግጥ፣ የንግግሩ ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ አንደኛው አረፍተ ነገር ከሌላው ገባ ብሎ ሊጻፍ ይችላል። ንግግሩ በሚሰጥበት ጊዜ ተናጋሪው አረፍተ ነገሩን በቀጥታ ሊያነብና በኋላም በቃሉ ሊያብራራ ይችላል። ሁለቱም የአስተዋጽኦ ዓይነቶች የየራሳቸው ጥቅም አላቸው። በአረፍተ ነገር አስተዋጽኦ ሐሳቡ ሙሉ በሙሉ ስለሚገለጽ ብዙ ሳምንታት ቀደም ብሎ ለሚዘጋጁ ወይም በተራራቀ የጊዜ ርዝመት ተደጋግመው ለሚሰጡ እንደ ሕዝብ ንግግር ላሉ ንግግሮች ጥሩ ነው።

7, 8. ንግግሩን በምትሰጥበት ጊዜ አስተዋጽኦህን ምን ልታደርግ ትችላለህ?

7 ከዋናው አስተዋጽኦ በፊት የተዘጋጀው ረቂቅ ከሁለቱ የአስተዋጽኦ ዓይነቶች አንዱን ማለትም የአረፍተ ነገር መልክ ያለው ወይም አርዕስታዊ አስተዋጽኦ ልትጠቀም ትችላለህ። ሐሳብህንም እንደፈለግህ አብራርተህ ልትጽፍ ትችላለህ። በዚህ መንገድ አድማጮችህ እንዲያገኙ የምትፈልገውን ትንንሽ ነጥብ በሙሉ ለመጨመርህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ንግግሩን በምትሰጥበት ጊዜ ግን አጠር ያለ አስተዋጽኦ ቢኖርህ ተመራጭ ይሆናል። ንግግርህን በምትዘጋጅበት ጊዜ የመጀመሪያውን ረቂቅና ዋናውን አስተዋጽኦ ሁለቱንም ከፊትህ ልታስቀምጥ ትችላለህ። አጠር ብሎ የተዘጋጀውን አስተዋጽኦ እየተመለከትክ በረቂቁ ላይ የተገለጹትን ሰፋ ያሉ ነጥቦች በሙሉ ለማስታወስ እስክትችል ድረስ ተለማመድ። አጠር ብሎ የተዘጋጀውን አስተዋጽኦ በመመልከት ብቻ ዘርዘር ያሉትን ነጥቦች ለማስታወስ ስትችል ንግግርህን ለመስጠት ተዘጋጅተሃል ማለት ነው።

8 አስተዋጽኦ ለማዘጋጀት አስፈላጊ የሆኑት ዋና ዋና ነጥቦች በአጭሩ እነዚህ ናቸው። አሁን ደግሞ ሦስቱን የንግግር ክፍሎች ሰፋ አድርገን ብንመረምር ጥሩ ይሆናል።

9–12. (ሀ) የአንድ ንግግር መግቢያ ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) የአንድ ዓይነት መግቢያ ምሳሌ ጥቀስ።

9 መግቢያ። በንግግር መክፈቻ ላይ የሚነገረው ቃል ዓላማ የአድማጮችን ፍላጎት መቀስቀስ ነው። በመክፈቻ ላይ የሚነገሩት አረፍተ ነገሮች አድማጮች ለርዕሰ ጉዳዩ ጉጉት እንዲያድርባቸው የሚያደርጉና ትምህርቱ ለእነርሱ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት የሚያስገነዝቧቸው መሆን ይኖርባቸዋል። በተለይ የመጀመሪያው አረፍተ ነገር በጥንቃቄ ሊታሰብበት ይገባል። ከአድማጮች ጋር አስደሳች የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያስችል እንጂ ጥላቻ የሚያነሳሳ ወይም በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ቀኖናዊ አስተሳሰብ የሚያስተላልፍ መሆን የለበትም።

10 ብዙ ዓይነት መግቢያዎች አሉ። አንድ ዓይነት ምሳሌ መጠቀም ወይም በአድማጮች ዘንድ በሚገባ የታወቀ አነጋገር መጥቀስ ይቻላል። መፍትሔ የሚያስፈልገው አስቸጋሪ ሁኔታ መጥቀስ ትችላለህ። ከርዕሰ ጉዳዩ በስተጀርባ የተፈጸመ ታሪካዊ ሁኔታም መግቢያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። የተለያዩ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይቻላል። የምትሸፍናቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በአጭሩ መዘርዘርም ትችላለህ።

11 መግቢያው ከንግግሩ ጋር በሚገባ የሚስማማ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ጉልህ የሆነ ምሳሌ በተለይ ተናጋሪው በንግግሩ በሙሉ ደጋግሞ የሚጠቅሰው ከሆነ በጣም ጥሩ መግቢያ ሊሆን ይችላል። በጥንቃቄ የተመረጠ ምሳሌ ከሆነ ንግግሩ አስደሳችና ለመከታተልም ሆነ ለማስታወስ ቀላል እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ አንድ ወጥ የሆነ ንግግር ለማቅረብ ያስችላል።

12 የመግቢያው አቀራረብ አድማጮች ለንግግሩ በሚኖራቸው ፍላጎት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ተናጋሪው ግራ ሳይጋባና ሳይንተባተብ በእርግጠኝነትና በጸና መንፈስ ንግግሩን መጀመር ይኖርበታል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ተናጋሪዎች ንግግራቸውን በጥሩ ሁኔታ ለመጀመር እንዲችሉ በመጀመሪያ የሚናገሩትን አንድ ወይም ሁለት አረፍተ ነገር መጻፍ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተዋል።

13–16. (ሀ) የአንድ ንግግር ሐተታ እንዴት ሊስፋፋ እንደሚችል ግለጽ። (ለ) ለአንድ ንግግር የተመደበው ጊዜ የንግግሩን ሐተታ አዘገጃጀት የሚነካው እንዴት ነው?

13 የንግግሩ ሐተታ። የንግግርህ ሐተታ በብዙ መንገዶች ሊስፋፋ ይችላል። አስፈላጊነታቸው አነስተኛ በሆኑ ነጥቦች ጀምረህ ደረጃ በደረጃ ጠንካራና ከፍተኛ ወደሆነው ነጥብ ለመድረስ ትችላለህ። በተጨማሪም ትምህርቱን በሥራ 7:2–53 ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው ታሪክ በአፈጻጸሙ የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ማቅረብ ይቻላል። የንግግርህ መልእክት በሚስፋፋባቸው ዋና ዋና ነጥቦች መሠረት ከፋፍሎ ማቅረብም ሌላው ጥሩ መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል የንግግሩ መልእክት “ከሞት መቤዠት” ከሆነ “ሞት እንዴት መጣ”፣ “የሰው ልጅ ቤዛ ለማስገኘት አልቻለም”፣ “ቤዛ ሊሰጥ የሚችለው ማን ብቻ ነው? ለምንስ?”፣ “ከቤዛው የሚገኙ በረከቶች” በሚሉ ዋና ዋና ነጥቦች ከፋፍለህ ማስፋፋት ትችላለህ።

14 ንግግርህ የተፈጥሮ ሁኔታዎችን መሠረት በማድረግ ቢከፋፈል ጥሩ እንደሚሆን ልትገነዘብ የምትችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ መጀመሪያ ለመላው ጉባኤ፣ ቀጥሎ ለሚስቶች፣ ከዚያም ለባሎችና ለልጆች መመሪያ ሰጥቶአል። (ኤፌሶን ምዕራፍ 5⁠ን እና 6⁠ን ተመልከት።) አለበለዚያም ንግግርህ ውጤትንና ምክንያትን በሚያገናዝብ ወይም ችግሮችን ከገለጸ በኋላ መፍትሔውን በሚያብራራ መንገድ ሊቀርብ የሚችል ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ዘዴዎችን በአንድ ላይ ለማጣመር የሚቻልበት ጊዜም ሊኖር ይችላል።

15 ቀኖችንና ዓመታትን ሳይጠቅሱ የሁኔታዎችን አፈጻጸም መተረክም የተለመደ የንግግር አቀራረብ ዘዴ ነው። ገላጭ ሐሳቦችን መጨመርም ንግግሩን በጥሩ ሁኔታ ያዳብረዋል። አንገብጋቢ የሆኑ የጊዜውን ጥያቄዎች አንስቶ ደጋፊና ተቃዋሚ ሐሳቦችን ጎን ለጎን በማስቀመጥ ሊቀርቡ የሚችሉ ንግግሮችም አሉ።

16 ከጊዜህ ጋር ተመጣጣኝ ያልሆኑ ብዙ ሐሳቦችን በአስተዋጽኦህ ውስጥ አጨናንቀህ አትጨምር። ጥሩው ትምህርት በቂ ጊዜ ተሰጥቶት ካልተብራራ ጠቃሚነቱን ያጣል። ከዚህም በላይ ማንም ሰው ስለ አንድ ጉዳይ የሚያውቀውን ነገር በሙሉ በአንድ ቀን እንዲናገር አይፈለግበትም። ምናልባት በሌላ ጊዜ ይህንኑ ርዕሰ ጉዳይ ከሌላ አቅጣጫ ማብራራት ይቻል ይሆናል። ለእያንዳንዱ የንግግርህ ዋና ነጥብ በቂ ጊዜ ከመደብህ በኋላ ከተወሰነው ጊዜ ጋር የሚመጣጠን ሐሳብ አቅርብ። ወሳኙ ነገር የተሸፈነው ትምህርት ብዛት ሳይሆን ጥራቱ ነው።

17–20. መደምደሚያ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? እንዴትስ ሊቀነባበር ይችላል?

17 መደምደሚያ። የማንኛውም ንግግር የመዝጊያ ክፍል በጥንቃቄ ታስቦበት ሊዘጋጅ የሚገባው ነው። በንግግሩ ሐተታ ውስጥ የተብራሩትን ሐሳቦች በሙሉ የሚያጠቃልልና አድማጮች ከሰሙትና ከተማሩት ነገር ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያነሳሳ መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም ነጥቡን የሚያስጨብጥ መሆን አለበት።

18 ከንግግሩ መልእክት ጋር የሚስማማ መደምደሚያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ብዙ ዓይነት መደምደሚያዎች አሉ። የንግግሩን ዋና ዋና ነጥቦች አጠቃልለህ በአጭሩ ከገለጽህ በኋላ ወደቀጣዩ ምክንያታዊ መደምደሚያ ልትሸጋገር ትችላለህ። ወይም የቀረበው ትምህርት አድማጩን እንዴት በግል እንደሚመለከተውና በቀረበው ትምህርት መሠረት ምን ማድረግ እንደሚችል በመግለጽ ትምህርቱ እንዴት በሥራ ላይ እንደሚውል የሚያመለክት መደምደሚያ ማቅረብ ይቻላል። በአንዳንድ ንግግሮች በተለይም ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ በምናቀርበው የስብከት መልእክት ቀስቃሽ የሆነ መደምደሚያ ማቅረብ በጣም የተሻለ ይሆናል። የቤቱ ባለቤት ጽሑፍ እንዲወስድ ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ፈቃደኛ እንዲሆን ሊገፋፋው ይችላል።

19 በተጨማሪም መደምደሚያው ደረጃ በደረጃ ሲገነቡ የቆዩ ሐሳቦችን በመቋጨት በአድማጩ አእምሮ ውስጥ ተቀርጾ መቅረት የሚገባውን ቁልፍ ነጥብ አጉልቶ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። ንግግሩን በጥሩ ሁኔታ ለማጠቃለል በመግቢያው ውስጥ ከተጠቀሰው ሐሳብ ጋር ማያያዝ ተገቢ ነው። በመግቢያው ላይ ቀርቦ የነበረውን ምሳሌ ወይም ጥቅስ መለስ ብሎ መጥቀስ ይቻላል። ብዙ ጊዜ ውሳኔ ላይ ደርሶ ያንን ውሳኔ መከተል አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑ በመደምደሚያው ላይ ይገለጻል። በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ኢያሱ ከመሞቱ በፊት የሰጠውን የመሰነባበቻ ንግግር የደመደመበት ሁኔታ ነው። — ኢያሱ 24:14, 15

20 ስለዚህ ጥሩ አስተዋጽኦ የወጣለት ንግግር ትኩረት የሚስብ መግቢያ ሊኖረው እንደሚገባ ተገንዝበናል። በጥንቃቄ የተመረጡና የንግግሩን መልእክት የሚደግፉ ቁልፍ ነጥቦች ምክንያታዊ በሆነ ቅደም ተከተል የሚብራሩበት መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም አድማጮች ከቀረበው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ጋር የሚስማማ እርምጃ እንዲወስዱ የሚቀሰቅስ መደምደሚያ ሊኖረው ያስፈልጋል። አስተዋጽኦው በሚዘጋጅበት ጊዜ እነዚህን ሁሉ አብሮ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በጥሩ ችሎታ የተዘጋጀ የንግግር አስተዋጽኦ ብዙ ጊዜ ሊቆጥብልህ ይችላል። በተጨማሪም ንግግርህ ትርጉም ያለው፣ በሚያዳምጡት ሰዎች አእምሮ ውስጥ ጠቃሚ የሆነ መመሪያ ተቀርጾ እንዲኖር የሚያደርግ እንዲሆን ያደርጋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]