በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ወጥ ሆኖ የተቀነባበረ ንግግር

አንድ ወጥ ሆኖ የተቀነባበረ ንግግር

ጥናት 30

አንድ ወጥ ሆኖ የተቀነባበረ ንግግር

1–3. በአንድ ንግግር ውስጥ የነጥቦቹ በቅደም ተከተል መቀነባበር ምን ሚና ይኖረዋል? ንግግሩን በደንብ ማቀነባበር የሚቻለውስ እንዴት ነው?

1 አንድ ወጥ የሆነ ንግግር አድማጮች በቀላሉ መከታተል የሚችሉት ንግግር ነው። በሌላው በኩል ግን ንግግሩ አንድ ወጥነት ከሌለው አድማጮች ሐሳባቸው ወዲያው መበታተን ይጀምራል። እንግዲያው ይህን ጉዳይ ንግግርህን በምትዘጋጅበት ጊዜ በጥሞና ልታስብበት እንደሚገባ ግልጽ ነው። ይህም በመሆኑ በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ “በማያያዣዎች ማገጣጠም” የሚለው ነጥብ ሰፍሯል።

2 ማገጣጠም ሲባል የተለያዩ ክፍሎች እርስ በርስ ተሰካክተው፣ ተጣብቀውና እንደ ሰንሰለት ተያይዘው አንድ መልክ ያዙ ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ይህ የሚከናወነው ልዩ ልዩ ክፍሎቹን በቅደም ተከተል በማቀነባበር ነው። ለአብዛኞቹ ንግግሮች ግን ነጥቦች በቅደም ተከተል መቀነባበራቸው አይበቃም። እርስ በርስ መያያዝ የሚያስፈልጋቸው ክፍሎች አሉ። እንዲህ በመሳሰሉት ጊዜያት የንግግሩን ወጥነት ለመጠበቅ ከአንድ ነጥብ ወደ ሌላው የሚያሸጋግር ድልድይ ያስፈልጋል። አዲሶቹን ሐሳቦች ቀደም ሲል ከቀረቡት ሐሳቦች ጋር ለማያያዝ በቃላት ወይም በሐረጎች እንጠቀማለን። ነጥቦቹ የቀረቡበት ጊዜ በመራራቁና የማብራሪያው አቅጣጫ ከመቀየሩ የተነሣ የተፈጠረው ክፍተት በዚህ መንገድ ይደፈናል። በማያያዣዎች ማገጣጠም ማለት ይኸው ነው።

3 ለምሳሌ ያህል የንግግርህ መግቢያ፣ ሐተታና መደምደሚያ ራሳቸውን የቻሉ የተለያዩ የንግግሩ ክፍሎች ናቸው። ቢሆንም በመሸጋገሪያ ድልድዮች አማካኝነት በደንብ መገጣጠም ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በተለይም በሐሳብ ይዘታቸው ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ነጥቦች እርስ በርስ እንደ ሰንሰለት መያያዝ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜም ማያያዣ የሚያስፈልጋቸው ዓረፍተ ነገሮች ወይም አንቀጾች ሊሆኑ ይችላሉ።

4–7. መሸጋገሪያ ቃላት መጠቀም ማለት ምን ማለት ነው?

4 በመሸጋገሪያ ቃላት መጠቀም። ብዙ ጊዜ ማያያዣ በሆኑ ቃላት ወይም ሐረጎች በመጠቀም ብቻ በሐሳቦች መካከል ድልድይ መዘርጋት ይቻላል። ከእነዚህ ቃላት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- በተጨማሪም፣ ከዚህም በላይ፣ ብሎም፣ ከዚህም በተጨማሪ፣ እንደዚሁም፣ በተመሳሳይም፣ ይህም በመሆኑ፣ በዚህ መንገድ፣ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ፣ እንግዲህ፣ ከላይ ያለውን ስንመለከት፣ ስለሆነም፣ እንግዲያው፣ ከዚያም በኋላ፣ ይሁን እንጂ፣ በሌላውም በኩል፣ በተቃራኒው ግን፣ በአንጻሩም፣ ቀደም ሲል፣ ከእንግዲህ ወዲያ፣ ወዘተ . . . እንደነዚህ ያሉት ቃላት ዓረፍተ ነገሮችንና አንቀጾችን ጥሩ አድርገው ያያይዛሉ።

5 ይሁን እንጂ ይኸኛው የንግግር ባሕርይ ብዙ ጊዜ ከእነዚህ ቀላል ማያያዣዎች የበለጡ ነገሮችን ይጠይቃል። አንድ ቃል ወይም ሐረግ ለማያያዝ በቂ በማይሆንበት ጊዜ በመካከላቸው ክፍተት ያለባቸውን ሁለት የተለያዩ ዐበይት ነጥቦች የሚያገናኝ ድልድይ መዘርጋት ይኖርበታል። ይህ ድልድይ ሙሉ ዓረፍተ ነገር ወይም የተሟላ መሸጋገሪያ ሐሳብ ሊሆን ይችላል።

6 ክፍተቱን መድፈን የሚቻልበት አንዱ መንገድ የፊተኛውን ነጥብ አንዳንድ ሐሳቦች ከኋለኛው ነጥብ መግቢያ ጋር በማሰባጠር ሁለቱን ለማያያዝ መሞከር ነው። ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ብዙ ጊዜ በዚህ ዘዴ እንጠቀማለን።

7 ከዚህም በላይ እርስ በርስ መገጣጠም ያለባቸው ተከታታይ ነጥቦች ብቻ አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ በንግግሩ ውስጥ በተራራቀ ጊዜ ላይ የተጠቀሱ ነጥቦችም መያያዝ አለባቸው። ለምሳሌ ያህል የንግግሩ መደምደሚያ ከመግቢያው ጋር መያያዝ ይኖርበታል። ምናልባት በንግግሩ መክፈቻ የተጠቀሰ ሐሳብ ወይም ምሳሌ በመደምደሚያው ላይ አድማጮችን ለማነሳሳት ወይም ያንን ነጥብ ወይም ምሳሌ ከንግግሩ ዓላማ ጋር የሚዛመድበትን መንገድ በድጋሚ ለማሳየት በሆነ መንገድ አያይዞ መናገር ይቻል ይሆናል። የዚያን ምሳሌ ወይም ሐሳብ አንዳንድ ገጽታዎች በዚህ መንገድ በድጋሚ መጥቀሱ አያያዥ ሆኖ ያገለግላል። ለንግግሩ ወጥነትም አስተዋጽኦ ያበረክታል።

8. ንግግሩን አንድ ወጥ ለማድረግ ምን ዓይነት መሸጋገሪያ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ የአድማጮቹ ሁኔታ የሚወስነው እንዴት ነው?

8 የንግግሩ መያያዝ ለአድማጮችህ አቅም በቂ መሆን አለበት። የሐሳብ ማያያዣዎች ምን ያህል ሰፊ መሆን እንዳለባቸው በከፊል በአድማጮችህ ሁኔታ ይወሰናል። ይህም ሲባል ማያያዣ የማያስፈልጋቸው አድማጮች አሉ ማለት ሳይሆን አንዳንድ አድማጮች እርስ በርስ መያያዝ ከሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ጋር ብዙም ትውውቅ ስለማይኖራቸው ማያያዣውን በይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አሁኑ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ የሚናገረውን ጥቅስ ስለ መንግሥቱ ከሚናገር ሌላ ጥቅስ ጋር ለማያያዝ ምንም አይቸገሩም። ነገር ግን መንግሥቲቱ የአእምሮ ሁኔታ ወይም በልብ ውስጥ ያለች ነገር እንደሆነች አድርጎ የሚመለከት ሰው በሁለቱ ጥቅሶች መካከል ያለውን ግንኙነት በቀላሉ መረዳት አይችልም። ያንን ግንኙነት ግልጽ ለማድረግ አንድ ዓይነት አያያዥ ሐሳብ ማቅረብ ያስፈልጋል። ከበር ወደ በር በምናደርገው የምሥክርነት ሥራ ዘወትር እንደዚህ ያለ ማስተካከያ ለማድረግ እንገደዳለን።

**********

9–13. የተቀነባበረ ንግግር ምንድን ነው? አንድን የተሳሳተ የሰዎች አባባል ማፍረስ የሚቻልባቸው ሁለት መሠረታዊ መንገዶችስ ምንድን ናቸው?

9 ከዚህ ጋር የቅርብ ትስስር ያለው የንግግር ባሕርይ “የተቀነባበረ፣ አንድ ወጥ የሆነ” የተባለው ሲሆን ይህም በምክር መስጫው ቅጽ ላይ ከተጨመሩት አንዱ ነው። ሰዎችን ለማግባባት መሠረታዊ የሆነ ስልት ነው።

10 “ሎጂክ” ምንድን ነው? እዚህ ላይ ለምንፈልገው ዓላማ እንዲያገለግለን “ሎጂክ” መልክ ያለው ወይም ምክንያታዊ የሆነ አስተሳሰብን የሚመለከት ሳይንስ ነው ለማለት እንችላለን። ሎጂክ አንድ ርዕሰ ጉዳይ እርስ በርስ የሚያያዙት ክፍሎቹ ተቀነባብረው የሚቀርቡበት አንዱ መንገድ ስለሆነ ጉዳዩ በቀላሉ የሚጨበጥ ይሆናል። “ሎጂክ” እነዚያ ክፍሎች ለምን አንድ ላይ እንደሚሄዱና እንደሚዛመዱ ይገልጻል። የሚቀርቡት ማብራሪያ ሐሳቦች አንድ በአንድ እየተሰካኩ ከሄዱና በአንድ መሥመር ከወጡ ንግግሩ የተቀነባበረ ይሆናል። (“የተቀነባበረ” የሚለው ቃል “ሎጂካል ዲቨሎፕመንት” የሚለውን የእንግሊዝኛ ሐረግ ለመተርጎም የገባ ነው።) ለንግግር ቅንብር ጥቂት ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል ነገሮችን እንደ አስፈላጊነታቸው በቅደም ተከተል በማስቀመጥ፣ ታሪክን ከኋላ ጀምሮ በመተንተን ወይም አንድ ዓይነት ችግር ጠቅሶ ወደ መፍትሄው በመሄድ የተቀነባበረና አንድ ወጥ የሆነ ትምህርት ማዘጋጀት ይቻላል።

11 አንድን የተሳሳተ የሰዎች አባባል ለማፍረስ ልንከተላቸው የምንችል ሁለት መሠረታዊ ዘዴዎች አሉ። (1) እውነቱን ለአድማጮች በቀጥታ መንገር፤ ከዚያም ድጋፍ የሚሆኑ ማስረጃዎችን ማቅረብ። (2) በተሳሳተው አባባል ላይ ጥቃት መሰንዘር፤ ያ አባባል ከፈረሰ እውነቱ ራሱ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ከዚያ በኋላ የሚቀረው ነገር የተብራሩትን እውነቶች ከአድማጮቹ አስተሳሰብ ጋር ማገናዘብ ይሆናል።

12 ሁለት ተናጋሪዎች ፍጹም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ሊኖራቸው አይችልም። አንድን ርዕሰ ጉዳይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት እንደሚቻል ለማስረዳት ፍጹም ምሳሌ የሚሆነን የአራቱ ወንጌሎች አጻጻፍ ነው። አራት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የእርሱን አገልግሎት አስመልክተው የየራሳቸውን ዘገባ ጽፈዋል። እያንዳንዱ ዘገባ የተለያየ ነው፤ ሆኖም እያንዳንዱ ጸሐፊ የተቀነባበረ መልእክት ጽፏል። እያንዳንዱ ጸሐፊ አንድ የተወሰነ ዓላማ ለማከናወን በሚያስችል መንገድ ዘገባውን አቅርቧል፤ እያንዳንዱም ዓላማው ሰምሮለታል።

13 በዚህ ረገድ ምክር የሚሰጥህ ወንድም የንግግርህን ዓላማ ለይቶ ማወቅና ያ ዓላማ መሳካት አለመሳካቱን ተመልክቶ የሐሳቦቹን ቅደም ተከተል ለመገምገም መጣር ይኖርበታል። አንተም በተለይ ለትምህርቱ በምትሰጠው መግቢያና መግቢያውን ከመደምደሚያው ጋር በማያያዝ ዓላማህን ግልጽ ብታደርግ እርሱንም ሆነ አድማጮችህን ለመርዳት ትችላለህ።

14, 15. ነጥቦቹን በደንብ አቀነባብሮ ማቅረቡ በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት አስረዳ።

14 ምክንያታዊ የነጥቦች ቅደም ተከተል። ትምህርቱን ወይም አስተዋጽኦውን በምታቀነባብርበት ጊዜ ከሁሉ በፊት መሠረት ያልተጣለለትን ሐሳብ ወይም ነጥብ አለማስገባትህን እርግጠኛ ሁን። ደጋግመህ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቅ:- ተፈጥሮአዊ ቅደም ተከተሉን በመጠበቅ ቀጥሎ መቅረብ ያለበት ነገር ምንድን ነው? እዚህ ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላ ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለው ምክንያታዊ ጥያቄ ምንድን ነው? ያ ጥያቄ ምን ሊሆን እንደሚችል ካረጋገጥህ በኋላ በቀላሉ መልሱን ስጥ። ምን ጊዜም ቢሆን አድማጮችህ ቀደም ሲል በተገለጸው ሐሳብ መሠረት “አሁን የተነገረው ነጥብ ትክክል መሆኑን መረዳት እንችላለን” ለማለት መቻል ይኖርባቸዋል። ቀደም ሲል መሠረት ጥለህለት ካልነበረ ነጥቡ ከሌሎቹ ነጥቦች መሥመር ውጭ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። አንድ የቀረው ነገር አለ።

15 ትምህርቱን በምታቀነባብርበት ጊዜ እርስ በርስ ተደጋጋፊ የሆኑትን ክፍሎች መለየት አለብህ። የእነዚህን ክፍሎች ተዛማጅነት ለማየትና በዚሁ መሠረት ለማቀነባበር መጣር ይኖርብሃል። ነገሩ ቤት እንደ መሥራት ነው። መሠረቱን ሳይጥል ግንቡን ለማውጣት የሚሞክር ግንበኛ የለም። ወይም ደግሞ ልስኑን ከጨረሰ በኋላ የቧንቧ ሥራውን ለመትከል አይሞክርም። የአንድ ንግግር ግንባታም ልክ እንደዚሁ ነው። እያንዳንዱ ክፍል የተቀነባበረ ንግግር ለመገንባት የራሱን ድርሻ ማበርከት፤ ይህንንም ድርሻ በቅደም ተከተል ማቅረብ፤ የሚቀርበውም ሐሳብ ፊተኛውን ነጥብ የሚያዳብርና ለሚቀጥለው ነጥብ መንገድ የሚጠርግ መሆን ይኖርበታል። በንግግርህ ውስጥ ነጥቦችህን በዚያ ቅደም ተከተል ለማቅረብ ምን ጊዜም ምክንያት ሊኖርህ ያስፈልጋል።

16–20. አንድ ሰው በንግግሩ ውስጥ አግባብነት ያላቸውን ነጥቦች ብቻ እንዳስገባ እንዴት እርግጠኛ ለመሆን ይችላል?

16 አግባብነት ያላቸውን ነጥቦች ብቻ መጠቀም። የምትጠቀምበት እያንዳንዱ ነጥብ በንግግሩ ውስጥ ከሌላ ነጥብ ጋር ለመሰካካት መቻል ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን ከሌሎች ነጥቦች ጋር ግንኙነት የሌለው ወይም የማይገጥም መስሎ ይታያል። አግባብነት የሌለው ነጥብ ነው። ቅንብሩን የሚያበላሽ ወይም ከሌላ ነገር ጋር የማይያያዝ ነጥብ ነው።

17 ይሁን እንጂ አንተ የጠቀስከው አንድ ነጥብ ከሌሎች ነጥቦች ጋር በደንብ እስከተሳሰረ ድረስ ከውጭ ዝምድና የሌለው መስሎ ስለታየ ብቻ ምክር ሰጪህ አግባብነት የለውም በማለት በዘፈቀደ አይወስንም። እንዲህ ያለውን ነጥብ የመረጥከው ለአንድ ዓላማ ሊሆን ይችላል። ከንግግሩ አርዕስት ጋር የሚሄድ ከሆነ፣ የንግግሩ አንድ ክፍል ከተደረገና ቦታውን ጠብቆ ከገባ ምክር ሰጪህ ይቀበለዋል።

18 ንግግሩን በምትዘጋጅበት ጊዜ አግባብነት የሌለውን ነጥብ ቶሎ ብለህና በቀላሉ ለመለየት የምትችለው እንዴት ነው? አርዕስታዊ አስተዋጽኦ ጥሩ አገልግሎት የሚሰጠው እዚህ ላይ ነው። ያሰባሰብካቸውን መረጃዎች በመልክ በመልካቸው ለመመደብ ይረዳሃል። በልዩ ልዩ ካርዶች ወይም በተመሳሳይ ነገሮች ለመጠቀም ሞክር። በእያንዳንዱ ካርድ ላይ አንድ ላይ የሚሄዱ ተዛማጅ ነጥቦችን አስቀምጥ። ከዚያም ነጥቦቹ የመቀነባበር መልክ እንዲኖራቸው በምን ቅደም ተከተል መቅረብ እንዳለባቸው በማመዛዘን ካርዶቹን በተርታ አስቀምጥ። ይህን ማድረግህ ርዕሰ ጉዳዩን ከምን አቅጣጫ ማብራራት እንዳለብህ ለመወሰን ከመርዳቱም በላይ ለንግግሩ አርዕስት አግባብነት የሌላቸውን ነጥቦች ቶሎ ለመለየት ያስችልሃል። ቅደም ተከተል የሚያፋልሱ ነጥቦች ካሉ፤ ነገር ግን እነዚህ ነጥቦች ትምህርቱን አሳማኝ ለማድረግ አስፈላጊ ከሆኑ እንደገና አስተካክሎ ማስገባት ይቻላል። አስፈላጊ ካልሆኑ ግን ለንግግሩ አርዕስት አግባብነት እንደሌላቸው ተቆጥረው መወገድ ይኖርባቸዋል።

19 አድማጮችህንና ለማከናወን ያሰብከውን ዓላማ ግምት ውስጥ በማስገባት የመረጥከው አርዕስት አንድ ነጥብ አግባብነት ያለው መሆን አለመሆኑን ለመወሰን እንደሚረዳ ከዚህ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ አንዱ ነጥብ ላሰብከው ዓላማ በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይህም በአድማጮችህ እውቀትና ሁኔታ ላይ የተመካ ነው። ለሌሎች አድማጮች ወይም ለሌላ አርዕስት ግን የማያስፈልግ ወይም እምኑም ውስጥ የማይገባ ነጥብ ሊሆን ይችላል።

20 በዚህ መሠረት ክፍል እንድታዘጋጅበት የተመደበልህን ጽሑፍ የቱን ያህል መሸፈን አለብህ? በተመደበው ጽሑፍ ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ነጥብ ለመሸፈን ስትል ጥሩ ቅንብርንና ወጥ የሆነ አቀራረብን መሠዋት የለብህም። ይሁንና የተማሪ ንግግር የትምህርት ቤቱ ዝግጅት አንዱ እውቀት ገንቢ ክፍል በመሆኑ ተግባራዊ ሆኖ ካገኘኸው ብዙ ነጥብ ለማካተት የሚያስችል ትዕይንት ብትመርጥ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ አርዕስቱን ለማዳበር የግድ አስፈላጊ የሆኑት ቁልፍ ነጥቦች ሊቀሩ አይችሉም።

21. ቁልፍ የሆነ አንድም ሐሳብ መቅረት የሌለበት ለምንድን ነው?

21 ቁልፍ ሐሳቦችን አለማስቀረት። አንድ ሐሳብ ቁልፍ ሐሳብ መሆኑንና አለመሆኑን እንዴት ለማወቅ ትችላለህ? ያ ነጥብ ቢቀር የንግግርህ ዓላማ ግቡን የማይመታ ከሆነ ያ ነጥብ የግድ አስፈላጊ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይ ለተቀነባበረና ወጥ ለሆነ አቀራረብ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ የሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ሁለት ፎቅ ቤት ቢሠራልህና ፎቆቹን የሚያገናኝ ደረጃ ሳይሠራ ቢቀር ምን ማድረግ ትችላለህ? በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦች የጐደሉት ንግግርም ልክ እንደዚሁ ነው። የተቀነባበረና ወጥ የሆነ አቀራረብ ሊኖረው አይችልም። አንድ የቀረ ነገር አለ። ከአድማጮችህም መካከል አንዳንዶቹ ሐሳባቸው ወደ ሌላ ይሄዳል። ንግግሩ በደንብ የተቀነባበረና ምክንያታዊ የነጥቦች አደራደር ካለው ግን ይህ ችግር አይፈጠርም።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]