አዲስ ነገር የሚያሳውቅ፤ ግልጽ፣ የሚጨበጥ
ጥናት 21
አዲስ ነገር የሚያሳውቅ፤ ግልጽ፣ የሚጨበጥ
1–3. ንግግሩ አዲስ ነገር የሚያሳውቅ እንዲሆን በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሐሳቦችን ማቅረብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 ጥሩ ንግግር የሚጀምረው በትጋት በሚደረግ ዝግጅት ነው። ይህም ጊዜንና ጥረትን ይጠይቃል። ሆኖም ጥረቱ እንዴት የሚክስ ነው! የትክክለኛ እውቀት ክምችትህን ትገነባለህ፤ እንዲሁም ለአድማጮችህ የምታካፍላቸው ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ይኖሩሃል። በደፈናው ወይም በአጠቃላይ ከመናገር ይልቅ ለአድማጮችህ የምታቀርባቸው የእውቀት ብርሃን የሚጨምሩ ዝርዝር ሐሳቦች ይኖሩሃል፤ የምትናገረው ነገር ትክክለኛ እንደሆነም ታውቃለህ። ይህም አድማጮችህ ስለ አምላክ ቃል ያላቸውን ግንዛቤና አድናቆት ይገነባል፤ ይሖዋንም ያስከብራል። አዲስ ነገር የሚያሳውቅ ስንል ንግግርህ ምን ቁም ነገሮችን ይዟል ማለታችን ነው። በአጭሩ የጉዳዩን የተለያዩ ዘርፎች ከዚህ በታች ተመልከት። በንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ነጥብ ይህ ነው።
2 በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ነጥቦች። አጠቃላይ ጉዳዮችን የሚዳስስ ንግግር ክብደትና ኃይል አይኖረውም። የተድበሰበሰ ንግግር ይሆናል። ነጥቡ ምን እንደሆነ አድማጮች እርግጠኞች አይሆኑም። ትምህርቱን አድማጮች እንዲያስታውሱ ከተፈለገ የተወሰኑ ነጥቦችን የሚያስጨብጥ መሆን ይኖርበታል። ይህም ከልዩ ልዩ ጽሑፎች መረጃዎችን እንዳፈላለግንና ስለ ርዕሰ ጉዳዩ እውቀት እንዳለን ያሳያል።
3 በዝግጅት ጊዜ ለምን? መቼ? የት? እና የመሳሰሉትን በመጠየቅ ይህን የንግግር ባሕርይ ማዳበር ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ነገር እንደተፈጸመ መናገሩ ብቻ በቂ አይደለም። የቦታዎችን ስም፣ ጊዜውን፣ ምናልባትም ምክንያቶቹን ጨምረህ ግለጽ። አንዳንድ እውነቶችን መናገሩ ብቻ አይበቃም። ለምን እውነት እንደሆኑ፤ እነዚህን ማወቁም ለምን ጠቃሚ እንደሆነ ግለጽ። ማሠልጠኛ ትምህርት እየሰጠህ ከሆነ አንድን
ነገር እንዴት መሥራት እንደሚቻል አስረዳ። አድማጮችህ በነገሩ ላይ ቀደም ሲል ያላቸው እውቀት ትምህርቱን ምን ያህል ማስፋፋት እንዳለብህ ይወስናል። ስለዚህ የትኞቹን ዝርዝር ነጥቦች መጨመር እንዳለብህ ለመወሰን የአድማጮችን እውቀት ገምግም።4–6. ንግግርህ በተለይ ለእነዚያ አድማጮች አዲስ ነገር የሚያሳውቅ እንዲሆን በአእምሮህ ልትይዛቸው የሚገቡት ነገሮች ምንድን ናቸው?
4 ለአድማጮችህ አዲስ ነገር የሚያሳውቅ። በአንድ ቦታ ለተሰበሰቡ አድማጮች አዲስ ነገር የሚያሳውቅ ንግግር ለሌሎች አድማጮች ምንም ላይጨምርላቸው ይችላል፤ ወይም ደግሞ ከነጭራሹ አእምሮአቸውን የሚያጨልም ሊሆንባቸው ይችላል። እንግዲያው ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ትምህርቱ ለእነዚያ አድማጮች የሚስማማ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ወይም ራሱን ለይሖዋ ለመወሰን በመዘጋጀት ላይ ላለ ግለሰብ አለዚያም ዓለማውያን ለተሰበሰቡበት ቡድን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እንዴት እንደሚካሄድ የሚያስረዳ ንግግር ማቅረብ ቢኖርብን አቀራረቡ እንደ ሰዎቹ ሁኔታ ፈጽሞ የተለያየ ይሆናል።
5 እነዚህ ሁኔታዎች በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በምንወስዳቸው የተለያዩ ክፍሎች ላይ ሊታሰብባቸው ይገባል። በማንኛውም ንግግር ላይ የሚቀርበው ትምህርት ከአድማጮች፣ ከትዕይንቱና ከንግግሩ ዓላማ አንጻር ሊታሰብበት ይገባል። እነዚህ ሁኔታዎች እንደ ንግግሩ ዓይነትና ተናጋሪው እንዳዘጋጀው ትዕይንት (ሴቲንግ) ሊለያዩ ይችላሉ። እርግጥ የመምሪያ ንግግሩ ለጉባኤው የሚቀርብ ንግግር ሆኖ ይዘጋጃል። ሌሎች ንግግሮች ግን ከዚህ የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። የአድማጮቹ ዓይነትና የንግግሩ ዓላማ ከትዕይንቱ ሊታወቅ ይችላል። በማንኛውም ሁኔታ ተማሪውም ሆነ ምክር ሰጪው ራሳቸውን እንዲህ እያሉ ሊጠይቁ ይችላሉ:- ትምህርቱ ለእነዚህ አድማጮች እንደሚስማማ ተደርጎ ቀርቧልን? አድማጮች እውቀትና በሕይወታቸው ውስጥ መመሪያ ሊሆናቸው የሚችል ትምህርት ሊያገኙበት ይችላሉን?
6 በምትዘጋጅበት ጊዜ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- በዚህ ንግግር አማካኝነት ላከናውነው የፈለግኩት ነገር ምንድን ነው? ልናገረው ከፈለግሁት ውስጥ ምን ያህሉን ይህ ሰው ወይም ቡድን ያውቀዋል? እነዚህ ነጥቦች ግልጽ እንዲሆኑ በመጀመሪያ ምን መሠረት መጣል አለብኝ? ይህን ንግግር የምሰጠው ከዚህ ፈጽሞ ለተለየ ቡድን ቢሆን ኖሮ በምን የተለየ መንገድ አቀርበው ነበር? አቀራረባችንን በዚህ መንገድ ከተለያየ አቅጣጫ ማየቱ ስለ አንድ ነገር ያለንን ግንዛቤ ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል። አድማጮችን በግምት ውስጥ ስታስገባ የሚኖረውን ልዩነት ለመረዳትና ለእነዚያ አድማጮች አዲስ ነገር የሚያሳውቅ ትምህርት በምታዘጋጅበት ጊዜ በተለያዩ ቡድኖች ፊት ሊኖርህ የሚችለውን የተለያየ አቀራረብ ተለማመድ።
7, 8. ንግግሮቻችንን ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ልናደርጋቸው የምንችለው እንዴት ነው?
7 ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው ትምህርት። ልንማራቸው የምንችል ብዙ ነገሮች አሉ። ሆኖም ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉት ሁሉም አይደሉም። ለእኛ አዲስ ነገር የሚያሳውቅ ንግግር ስለ ክርስቲያናዊ
አኗኗራችንና ስለ አገልግሎታችን ማወቅ የሚያስፈልጉንን ነገሮች የሚያሳውቀን ንግግር ነው። የቀሰምነውን እውቀት እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንችል ለማወቅ እንፈልጋለን።8 ተማሪው ሲዘጋጅ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካችም ምክር ሲሰጥ ይህን ነጥብ እንዲህ ብለው በመጠየቅ ሊያስቡበት ይችላሉ:- በንግግሩ ውስጥ የተግባር መመሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ምን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይገኛሉ? ትምህርቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ ሊያገለግል ይችላልን? የቀረበውን ትምህርት ትንሽ ለወጥ በማድረግ በመስክ አገልግሎት ሊሠራበት ይቻላልን? የአምላክን ቃል ከፍ ከፍ የሚያደርግና ወደ ዓላማው የሚያመለክት ነውን? ይህን ሁሉ ነገር ማካተት የሚችሉት ንግግሮች በጣም ጥቂት ናቸው፤ ሆኖም የቀረበው ትምህርት ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ከተፈለገ አድማጮች በሆነ መንገድ ጥቅም የሚያገኙበት መሆን ይኖርበታል።
9–11. ትክክለኛ ነገር መናገር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 ትክክለኛ ነገር መናገር። የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን የሚናገር ድርጅት ናቸው። እውነትን የምንናገርና በምንሰጣቸው ጥቃቅን ማብራሪያዎች ጭምር ቃላችን ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛ መሆን አለበት። ይህም መሠረተ ትምህርትን በተመለከተ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የተናገሩትን ጠቅሰን ስንናገር፣ ስለ ሌሎች የምንናገረው ቃልና ስለ ማንነታቸው የምንሰጠው መግለጫ እንዲሁም ሳይንሳዊ መረጃን ወይም ዜናዎችን በተመለከተ የምንናገረውንም የሚጨምር መሆን ይኖርበታል።
10 ለአድማጮች የተነገረ የተሳሳተ መልዕክት እየተባዛና ስህተቱም እየጎላ ሊሄድ ይችላል። አድማጮች ትክክለኛ ያልሆነ ነገር ከሰሙ ተናጋሪው በሌሎችም ነጥቦች አስተማማኝ ስለመሆኑ ጥያቄዎችን ያስነሳል፤ አልፎ ተርፎም ተናጋሪው የሚያቀርበው መልዕክት ራሱ ትክክለኛ ስለመሆኑ ጥያቄ ያስነሳል። ፍላጎት ያሳየ አዲስ ግለሰብ እንዲህ ያለ ሐሳብ ሰምቶ በሌላ አጋጣሚ ደግሞ የተለየ አስተያየት ቢሰማ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሐሳብ አንድነት የለም ወደሚል ድምዳሜ ሊደርስና ምክንያቱን እንኳ ሳይገልጽ የነበረውን ግንኙነት ሊያቋርጥ ይችላል።
11 በተለይ ተማሪው አዲስና በአምላክ ቃል ጥልቅ እውነቶች ሙሉ በሙሉ ያልደረጀ ከሆነ ምክር ሰጪው እያንዳንዱን ቃል መሰነጣጠቅ አይገባውም። ከዚህ ይልቅ ተማሪው አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል በዘዴ ሊረዳውና ቀደም ብሎ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት በማድረግ ትክክለኛ ነገር በመናገር በኩል እንዴት ማሻሻል እንደሚችል ሊያሳየው ይችላል።
12, 13. ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ማቅረቡ ምን ጥቅም አለው?
12 ተጨማሪ ማብራሪያዎች። ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ በማሰላሰልና ልዩ ልዩ ጽሑፎችን በመመልከት ያሰባሰብናቸው ሐሳቦች ንግግሩን ሊያዳብሩና አድማጮች ቀደም ብለው የሚያውቁትን በመደጋገም አዲስ እውቀት የማይሰጥ ትምህርት ከማቅረብ ያድናሉ። ይህም አቀራረቡን አዲስ ያደርገዋል፣ የአድማጮችን ስሜት ሕያው ያደርጋል፣ በአድማጮች ዘንድ በጣም የታወቀውንም ርዕሰ ጉዳይ እንኳ አስደሳች ሊያደርገው ይችላል።
በተጨማሪም ተናጋሪው በልበ ሙሉነት እንዲናገር ያስችለዋል። ለአድማጮች የሚያቀርበው ትንሽ ለወጥ ያለ ሐሳብ እንዳለው በማወቁ ንግግሩን ገና ከማቅረቡ በፊት ግለት ይኖረዋል።13 ከራስ የመነጨ ግምታዊ ሐሳብ መስጠት ልንሸሸው የሚገባ አደጋ ነው። የማኅበሩን ጽሑፎች ልትመለከትና ለምትሰጣቸው ሐሳቦች መሠረት ልታደርጋቸው ይገባል። የማኅበሩን ማውጫዎችና (ኢንዴክስ) የጥቅሶችን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት። የምትናገረው ሁሉ ነገሮችን በተሳሳተ መልክ የሚያቀርብ ሳይሆን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጥ።
**********
14–16. ሁኔታዎችን በቀላል አነጋገር ለመግለጽ በዝግጅት ጊዜ ምን መደረግ አለበት?
14 ክፍልህን በምትዘጋጅበት ጊዜ ልትናገር ያሰብከውን እንዴት ማቅረብ እንደሚገባ ማወቁም ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። የንግግር ምክር መስጫው ቅጽ “ግልጽ፣ የሚጨበጥ” የሚለው ይህንን ነው። ለዚህ ጉዳይ በቂ ትኩረት አለመስጠቱ ያሰብከውን መልእክት ለአድማጮችህ እንዳታስተላልፍ ወይም እነርሱ የሰሙትን በአእምሮአቸው እንዳይዙት እንቅፋት ሊሆን ይችላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሊተኮርባቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ።
15 በቀላል አገላለጽ የቀረበ። ይህ ማለት የምንናገራቸውን ሐረጎች በቅድሚያ አስበን ማዘጋጀት ያስፈልገናል ማለት አይደለም። ነገር ግን የምናቀርባቸውን ሐሳቦች አንድ በአንድ ልንመረምራቸውና አንዳንድ ወሳኝ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ልናስገባ ይገባል። ይህም አብዛኛውን ጊዜ አንድ ወጥ የሆነ ንግግር ለመስጠትና ሐሳቦችን በቀላል አነጋገር ለመግለጽ ያስችላል። በተናጋሪው አእምሮ ውስጥ የተዘበራረቀ ርዕሰ ጉዳይ ለአድማጮችም የተዘበራረቀ ሆኖ ይቀርባል።
16 ሰዓት ሲደርስ የሚደረግ የሩጫ ዝግጅት መወገድ ይኖርበታል። እያንዳንዱ የንግግሩ ነጥብ ለተናጋሪው ቀላልና ግልጽ እስኪሆንለት ድረስ ሐሳቡን ማብላላት ይኖርበታል። በዝግጅት ጊዜ እነዚህን ነጥቦች መላልሶ ማየቱ በአእምሮው ውስጥ ቁልጭ ብለው እንዲታዩት ስለሚያደርግ በንግግር ጊዜ በቀላሉ እየተንቆረቆሩ ይወጣሉ፤ በተናጋሪው አእምሮ ውስጥ የሚጨበጡ ሆነው እንደሚታዩ ሁሉ ለአድማጮችም እንዲሁ የሚጨበጡ ይሆናሉ።
17, 18. ያልተለመዱ ቃላት ትርጉማቸው መብራራት ያለበት ለምንድን ነው?
17 ያልተለመዱ ቃላትን መግለጽ። ቅዱሳን ጽሑፎችንና የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ጽሑፎች ማጥናታችን ከሥራችን ጋር ለማይተዋወቁ ሰዎች ጆሮ በጣም እንግዳ የሚሆኑ ብዙ መነጋገሪያ ቃላትን አስገኝቶልናል። ለአንዳንድ አድማጮች እንዲህ ዓይነቶችን ቃላት እየተናገርን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስረዳት ብንሞክር ከምንናገረው ውስጥ ብዙው መና ሆኖ ይቀራል፤ አለዚያም ጠቅላላው ንግግራችን የማይጨበጥ ይሆንባቸዋል።
18 የአድማጮችህን ሁኔታ ገምግም። የመረዳት ደረጃቸው የቱን ያህል ነው? ከሥራችን ጋር ምን ያህል ይተዋወቃሉ? ከእነዚህ ቃላት ውስጥ
ልክ እንደ ተናጋሪው አድርገው በቀላሉ የሚረዷቸው ስንቶቹን ነው? እንደ “ቲኦክራሲ፣” “ቀሪዎች፣” “ሌሎች በጎች፣” “አርማጌዶን” እና “መንግሥት” የመሳሰሉት ቃላት በአድማጭ አእምሮ ውስጥ የተሳሳተ ሐሳብ ሊቀርጹ አለዚያም ምንም ዓይነት ሐሳብ ላያስተላልፉ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ አድማጩ ከሥራችን ጋር የማይተዋወቅ ከሆነ እንደ “ነፍስ” “ሲኦል” እና “አለመሞት” የመሳሰሉት ቃላት ትርጉማቸው እንዲብራራለት ያስፈልገዋል። ንግግሩ የሚቀርበው ለጉባኤው ከሆነ ግን እንደነዚህ ያሉት ቃላት መብራራት አያስፈልጋቸውም። ስለዚህ ትምህርቱ ለማን እንደሚቀርብ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።19, 20. ሐሳብ ከማብዛት ልንቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ሐሳብ አለማብዛት። አንድ ንግግር በጣም ብዙ ነጥቦችን ያካተተ በመሆኑ የአድማጮች አእምሮ በሐሳቦች ጎርፍ ሊጥለቀለቅ ይችላል። በዚህም ምክንያት የመረዳት ችሎታቸው ሊደክም ብሎም ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል። የንግግሩ ዓላማ ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ በግልጽ ሊብራሩ የማይችሉ ብዙ ነጥቦችን በመግቢያው ላይ ማስተዋወቅ አያስፈልግም። የአድማጮች አእምሮ ሊቀበለው ከሚችለው በላይ ብዙ ሐሳብ መዥጐድጐድ የለበትም። ከዚህም በተጨማሪ ለእንግዳ ወይም ፍላጎት ላሳየ አዲስ ሰው የሚቀርበው ትምህርት በዚያው ርዕሰ ጉዳይ ለጉባኤው ከሚቀርበው ንግግር ጋር ሲነጻጸር በቀለለ መልኩ ሊቀርብ ይገባዋል። እዚህም ላይ ቢሆን ተናጋሪው ትምህርቱን የሚያቀርበው ለማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ምክር ሰጪው ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።
20 አንድ ተማሪ በንግግሩ ውስጥ ምን ያህል ሐሳብ መጨመር እንዳለበት እንዴት ለማወቅ ይችላል? በዝግጅት ወቅት ነገሮችን ከተለያየ አንፃር ማየቱ ይረዳዋል። የምታቀርበውን ትምህርት አንድ በአንድ መርምረው። ከእነዚህ ሐሳቦች ውስጥ ቢያንስ በከፊል እንኳ በአድማጮች ዘንድ የሚታወቁት ምን ያህል ናቸው? ፈጽሞ አዲስ ሊሆኑ የሚችሉትስ ምን ያህል ናቸው? አድማጮቹ ቀደም ሲል ሰፊ የእውቀት መሠረት ካላቸው በተወሰነው ጊዜ ውስጥ በዚያ ላይ ብዙ መገንባት ይቻላል። አድማጮች ንግግር ስለሚሰጥበት ርዕሰ ጉዳይ ምንም ነገር የማያውቁ ከሆነ ግን ተናጋሪው ምን ያህል ነጥቦችን ማቅረብ እንዳለበትና አድማጮች ሙሉ በሙሉ እንዲገባቸው እነዚህን ነጥቦች ለማብራራት ምን ያህል ጊዜ ማጥፋት እንደሚኖርበት ሲወስን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]