አድማጮችህን አሳምን፣ ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ እርዳ
ጥናት 31
አድማጮችህን አሳምን፣ ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ እርዳ
1, 2. አሳማኝ ነጥብ ሲባል ምን ማለት ነው?
1 ንግግር ስትሰጥ አድማጮችህ ይሰሙኛል ብለህ ትጠብቃለህ፤ ይህም ብቻ አይደለም። እነርሱን ለማሳመን የምታቀርብላቸውን ነጥቦች እንዲቀበሉና ተግባራዊ እንዲያደርጓቸው ትፈልጋለህ። ይህን ማድረግ የሚችሉት ግን አንተ የምትናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት ካሳመንካቸውና ልባቸው ቅን ከሆነ ነው። ማሳመን ሲባል አእምሮን የሚያረኩ ማስረጃዎች ማቅረብ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ማስረጃዎቹ ብቻቸውን ሁልጊዜ በቂ አይሆኑም። ብዙ ጊዜ ለማስረጃዎቹ ድጋፍ የሚሆኑ ማሳመኛ ነጥቦችን ማከልም አስፈላጊ ነው። ይህም በመሆኑ አንድን ነገር በመደገፍ ወይም በመቃወም የሚደረገው
ውይይት ሦስት መሠረታዊ ሁኔታዎችን ያካተተ ነው:- አንደኛ ማስረጃዎቹ ራሳቸው፤ ሁለተኛ ማስረጃዎቹ የሚቀርቡበት ቅደም ተከተል፤ ሦስተኛ ማስረጃዎቹ የቀረቡበት ሁኔታ ወይም ዘዴ። በንግግር ምክር መስጫ ቅጽህ ላይ ስላለው “አሳማኝ ነጥቦች” ስለሚለው ጉዳይ አሁን በሚቀርበው ማብራሪያ ላይ ማስረጃው እንዴት መቅረብ እንዳለበት ሳይሆን ምን መናገር ወይም ምን ማስረጃ ማቅረብ እንዳለብህ እንወያያለን።2 አሳማኝ ነጥቦች ጠንካራ በሆኑ መሠረታዊ ምክንያቶች የተደገፉ ናቸው። ምክር ሰጪህም ነገሩን የሚመለከተው ከዚሁ አንጻር ነው። የምታቀርባቸው ነጥቦች ከአንድ ጽሑፍ በቀዝቃዛ ስሜትም እንኳ ቢነበቡ የሚያሳምኑ መሆን ይኖርባቸዋል። የነጥቦችህ አሳማኝነት አንድን ሐሳብ ለማስጨበጥ በምታቀርባቸው ቁም ነገሮች ላይ ሳይሆን በንግግሩ አቀራረብ ላይ የተመካ ከሆነ ግን የምታቀርባቸው ነጥቦች ጽኑና ሕያው እንዲሆኑ ይህንን የንግግር ባሕርይ የበለጠ ማዳበር ይኖርብሃል።
3–6. ለምን መሠረት መጣል እንደሚያስፈልግ ግለጽ።
3 መሠረት መጣል። መከራከሪያ ነጥብ ከማቅረብህ በፊት ትክክለኛ መሠረት መጣሉ አስፈላጊ ነው። ውይይት የሚደረግበት ነጥብ ምን እንደሆነ በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርብሃል። ከአድማጮችህ ጋር የምትተማመኑባቸውንና ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ነገሮች ጠንከር አድርገህ በመግለጽ መነሻ የሚሆን የጋራ መሠረት መጣሉ ጥቅም አለው።
4 የአንዳንድ ቃላትን ትርጉም ግልጽ ማድረግ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ከጉዳዩ ጋር አግባብነት የሌላቸው ነገሮች ሁሉ ተበጥረው መውጣት ይኖርባቸዋል። መሠረቱን በጥድፊያ አትገንባ። ጥብቅ ሆኖ ይውጣ። ሆኖም ጠቅላላው ሕንጻ እሱ የሆነ ይመስል በመሠረቱ ላይ ጊዜህን ሁሉ አታጥፋ። ሰዎች የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ሐሳብ ለማፍረስ በምትዘጋጅበት ጊዜ የዚያን ክርክር ደካማ ጎኖች ለማግኘትና ውይይቱ ምን አቅጣጫ መያዝ እንዳለበት ለመወሰን፤ ብሎም ወደ ጉዳዩ ሥረ መሠረት ለመግባት በመጀመሪያ ሰዎች የሚያቀርቧቸውን መከራከሪያ ሐሳቦች አንድ በአንድ መርምር።
5 ንግግር በምታዘጋጅበት ጊዜ አድማጮች ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ምን ያህል እንደሚያውቁ በቅድሚያ ለመገምገም መሞከር አለብህ። ይህን ማድረግህ ማሳመኛ ነጥቦችህን ከማቅረብህ በፊት የቱን ያህል መሠረት መጣል እንደሚኖርብህ ለመወሰን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርግልሃል።
6 ምንም እንኳን እዚህ ላይ እየተነጋገርን ያለነው ነጥብ ይህ ባይሆንም በአነጋገርህ ዘዴኛ መሆንህና ክርስቲያናዊ ሥነ ሥርዓታማነትን ማሳየትህ ደግነትና አሳቢነት ባለው ሁኔታ እንድትናገር ያስገድድሃል። ምን ጊዜም ስለ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለህን እውቀት እዚህ ላይ አሟልተህ ጥቅም ላይ በማዋል የአድማጮችህን ልብና አእምሮ ለመክፈት መጣር ይኖርብሃል።
7–13. “ጠንካራ ማስረጃ ማቅረብ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስረዳ።
7 ጠንካራ ማስረጃ ማቅረብ። ተናጋሪ በመሆንህ አንድ ነገር አንተ ስላመንክበት ወይም ስለተናገርከው ብቻ ነገሩ “በማስረጃ ተረጋገጠ” ማለት አይደለም። አድማጮችህ “ይህ ነገር እውነት የሆነው ለምንድን ነው?”
ወይም “ለምን እንደዚያ ብለህ ለመናገር ቻልህ?” ብለው ቢጠይቁ ትክክል ናቸው። አንተም ተናጋሪ እንደመሆንህ “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የመቻል ግዴታ አለብህ።8 “እንዴት?” “ማን?” “የት?” “መቼ?” “ምን?” የሚሉት ጥያቄዎች ቁም ነገሮችን ወይም ሁኔታዎችን ያሳውቃሉ። “ለምን?” የሚለው ጥያቄ ግን ምክንያቶችን ያስገኛል። በዚህ ረገድ ብቸኛ የሆነና ቁም ነገሮችን በመግለጽ ብቻ መልስ የማያገኝ ጥያቄ ነው። የማሰብ ችሎታህን በኃይል የሚያሠራ ጥያቄ ነው። ይህም በመሆኑ ንግግርህን በምትዘጋጅበት ጊዜ “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ ደጋግመህ ጠይቅ። ከዚያም የጥያቄውን መልሶች ማግኘትህን እርግጠኛ ሁን።
9 ማስረጃ ለማቅረብ እንደ ባለ ሥልጣን ተደርጎ የሚታይ አካል የተናገረውን መጥቀስ ትችላለህ። በቀላል አነጋገር ያ አካል ከተናገረ እውነት መሆን አለበት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ስለ ጉዳዩ የሚያውቅ እርሱ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ይህ ብቻውን ነገሩን ለማመን በቂ ምክንያት ይሆናል። በዚህ መስክ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ይሖዋ አምላክ ነው። ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሚሆነንን አንድ ጥቅስ ማቅረቡ ያንን ነጥብ ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ ይሆናል። ይህም “የምሥክርነት” ማስረጃ ይባላል፤ ምክ ንያቱም ተቀባይነት ካለው ምሥክር “ምሥክርነት” ማቅረብን ይጠይቃል።
10 የምሥክርነት ማስረጃ ስታቀርብ ያ ምሥክር በአድማጮችህ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። ሰብአዊ ባለ ሥልጣኖችን እንደ ምሥክር አድርገህ የምትጠቅስ ከሆነ ስለ ማንነታቸውና በአድማጮች ዘንድ እንዴት እንደሚታዩ እርግጠኛ ሁን። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን እንዳለው መለኮታዊ መመሪያ አድርገው ይቀበሉታል፤ ሆኖም የሰው ሥራ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱትም አሉ። ስለሆነም የመጨረሻው ባለ ሥልጣን አድርገው አይቀበሉትም። በዚህ ዓይነቱ ጊዜ ሌላ ዓይነት ማስረጃዎችን ማቅረብ ይኖርብሃል፤ ወይም በመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለብህ።
11 አንድ ልትጠነቀቅበት የሚገባ ነገር አለ። ምንም ዓይነት ማስረጃ ብትጠቅስ ሳታዛባ በሐቅ ማቅረብ ይኖርብሃል። አንድ ሰው የተናገረውን አለቦታው መጥቀስ አይገባህም። አንድን ባለ ሥልጣን ጠቅሰህ ስትናገር ሐሳብህ እርሱ በአእምሮው ይዞት ከነበረው ሐሳብ ጋር አንድ መሆኑን አረጋግጥ። የተጠቀሰው ሐሳብ የት እንደሚገኝ ለይተህ ግለጽ። ስታትስቲካዊ መረጃዎችን ስታቀርብም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። አላግባብ ከተጠቀምክባቸው ነገሩ ባንተ ላይ ይዞርና የተናገርከውን ሁሉ ሊንደው ይችላል። በአማካይ አንድ ሜትር ያህል ጥልቀት ባለው ወራጅ ውኃ ላይ ሰጥሞ የሞተውን አንድ ዋና የማይችል ሰው አስታውስ። ሰውዬው መሐል ላይ የውኃው ጥልቀት ሦስት ሜትር ያህል እንደሚደርስ ዘንግቶት ነበር።
12 የሁኔታዎች ማስረጃ የተባለው ደግሞ ሰብአዊ ምሥክርነትን ወይም
መለኮታዊ ሥልጣንን መሠረት በማድረግ ከሚቀርበው ማስረጃ ውጪ ያለው ነው። የምሥክሮችን ቃል በመጥቀስ ሳይሆን ተጨባጭ ሐቆች የሚጠቁሙትን መሠረት በማድረግ የሚቀርብ ማስረጃ ነው። ተጨባጭ ሐቆችን መሠረት በማድረግ የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎች ለማጠናከርና የሁኔታዎች ማስረጃዎችን አሳማኝ ለማድረግ ለዚያ ድምዳሜ ድጋፍ የሚሰጡ ተጨባጭ ነገሮችን ወይም ምክንያቶችን መደርደር ያስፈልጋል።13 ያቀረብካቸው ማስረጃዎች (በቅደም ተከተል ላይሆን ይችላል) ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ ንግግሩን ለምታቀርብላቸው አድማጮች አጥጋቢ ከሆኑ ምክር ሰጪህም አጥጋቢ ናቸው ብሎ ይቀበላቸዋል። ምክር ሰጪው ራሱን በአድማጮች ቦታ በማስቀመጥ “አሳምኖኛልን?” በማለት ራሱን ይጠይቃል። እንዳሳመንከው ከተሰማው ስላቀረብከው ትምህርት ያመሰግንሃል።
14. ውጤታማ ማጠቃለያ ምንድን ነው?
14 ውጤታማ ማጠቃለያ። አሳማኝ ነጥቦችን ካቀረብህ በኋላ አንድ ዓይነት ማጠቃለያ መስጠቱ የግድ አስፈላጊ ነው። አእምሮን ለማሳመን የሚደረገው የመጨረሻው ጥረት ይህ ነው። ላቀረብካቸው አሳማኝ ነጥቦችም የአድማጮችህን አድናቆት ከፍ ያደርጋል። ምንም እንኳን ማጠቃለያ ሲባል በመሠረቱ “ይህ እንደዚህ ስለሆነ፤ ያም እንደዚያ በመሆኑ እንዲህ ብሎ መደምደም ይቻላል” የሚል ይዘት ቢኖረውም ቀደም ሲል አንድ በአንድ የቀረቡትን ቁም ነገሮች የግድ መዘርዘር ያስፈልጋል ማለት አይደለም። የማጠቃለያው ዓላማ ነጥቦቹን አንድ ላይ ለማሰርና ወደ መደምደሚያው እንዲያመሩ ለማድረግ ነው። የቀረቡትን ነጥቦች አንድ ላይ በማሰር አድማጮቹን እንዲያምኑ የሚያደርገው ብዙ ጊዜ ውጤታማው ማጠቃለያ ነው።
**********
15, 16. አድማጮች ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ መርዳት ያለብን ለምንድን ነው?
15 በአንድ ንግግር ውስጥ የምታቀርባቸው አሳማኝ ነጥቦች ጠንካራ ቢሆኑም እነዚያን ተጨባጭ ሁኔታዎች መናገሩ ብቻ አይበቃም። አድማጮችህ ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ ይኸውም እንዲገቧቸውና አንተ ወደደረስክበት ድምዳሜ እንዲደርሱ መርዳት በሚያስችል መንገድ ነጥቦችህን ማቅረብ ይኖርብሃል። የንግግር ምክር መስጫው ቅጽ “ነጥቦቹን እንዲያገናዝቡ መርዳት” ሲል የሚጠቅሰው ይህንን ነው።
16 ይህ የንግግር ባሕርይ እንዲኖርህ ልትመኘው የሚገባህ ነው፤ ምክንያቱም አምላክም ነገሮችን እንድናገናዝብ ያደርጋል። በተጨማሪም ኢየሱስ የምሳሌዎቹን ትርጉም ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸውና እነዚሁኑ እውነቶች ለሌሎች ማስተማር እንደሚችሉ አድርጎ ያስታጥቃቸው ነበር። እንግዲያው አድማጮችህ ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ መርዳት ሲባል ያቀረብካቸው ነጥቦች እንዲገቧቸው፣ አንተ ወደደረስክበት ድምዳሜ እንዲመጡና ባቀረብካቸው ማስረጃዎች ተጠቅመው ሌሎች ሰዎችን ማስተማር እንደሚችሉ አድርጎ ለማስታጠቅ በሚያስችሉ ዘዴዎች መጠቀም ማለት ነው።
17, 18. የጋራ አቋም ሳይለቁ መቀጠል የሚቻለው እንዴት ነው?
17 የጋራ አቋምን አለመልቀቅ። በንግግርህ መክፈቻ ላይ አንድ የጋራ
መነሻ ወይም መሠረት ለመጣል የሚረዱት በጣም ወሳኝ የሆኑት ነገሮች የምትናገረው ቃልና አነጋገርህ ናቸው። ይሁን እንጂ በንግግሩ ሂደትም ላይ ይህን የጋራ አቋም መልቀቅ የለብህም፤ አለዚያ አድማጮችህን ጭምር ታጣለህ። የአድማጮችህን አእምሮ መማረክ እንደሚችሉ አድርገህ አሳማኝ ነጥቦችን ማቅረብህን መቀጠል ይኖርብሃል። ይህም እያብራራህ ስላለኸው ርዕሰ ጉዳይ ያላቸውን አመለካከት ዘወትር ማስታወስና በዚህ እውቀት ተጠቅመህ የነጥቦቹ ምክንያታዊነት እንዲታያቸው መርዳት አለብህ ማለት ነው።18 አንድ የጋራ አቋም መሥርቶ ያንን እስከ መጨረሻው ይዞ በመቀጠል፤ ወይም በሌላ አነጋገር፣ አድማጮች ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ በመርዳት በኩል ሊጠቀስ የሚችል አንድ ጥንታዊ ምሳሌ በሥራ 17:22–31 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐዋርያው ጳውሎስ አድማጮቹን ለማሳመን ያቀረበው ንግግር ነው። ገና በንግግሩ መክፈቻ ላይ የጋራ አቋም እንዴት እንደመሠረተና ጠቅላላው ንግግር እስኪያልቅ ድረስ በዘዴ ያን መሠረት እንደጠበቀ ልብ በል። ንግግሩን ሲደመድም አንድን ዳኛ ጨምሮ አንዳንድ አድማጮቹን ይህ እውነት ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። — ሥራ 17:33, 34
19–23. ነጥቦች በበቂ ሁኔታ መብራራት የሚችሉባቸውን አንዳንድ ዘዴዎች ጠቁም።
19 ነጥቦቹን በበቂ መጠን ማብራራት። አድማጮች ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ የሚቀርቡትን ነጥቦች ከዚያ ጉዳይ ጋር እንዲያገናዝቡ ከተፈለገ ነጥቦቹ ሙሉ በሙሉ ስላልገቧቸው ብቻ አንቀበልም እንዳይሉ ለማገናዘብ የሚያስችለው በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። እንግዲህ እነርሱን መርዳቱ የአንተው ፋንታ ነው።
20 ይህንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ከፈለግህ ከመጠን በላይ ብዙ ነጥቦችን ለመሸፈን ከመሞከር መቆጠብ አለብህ። ንግግርህ በጥድፊያ ከቀረበ ትምህርቱ ሊሰጥ ይችል የነበረው ጥሩ ነገር ሊቀር ይችላል። ነጥቦችህን አድማጮች እንዲሰሟቸው ብቻ ሳይሆን እንዲገቧቸውም ጭምር ጊዜ ወስደህ በደንብ አብራራቸው። አንድ በጣም አስፈላጊ ሐሳብ ካመጣህ ጊዜ ወስደህ አስፋፋው። ለምን? ማን? እንዴት? ምን? መቼ? የት? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በንግግርህ ላይ ለመመለስ ሞክር። ይህን ካደረግህ አድማጮችህ ሐሳቡ በተሟላ መልኩ እንዲጨበጥላቸው ትረዳቸዋለህ። አንዳንድ ጊዜ ስለ አንድ ጉዳይ የድጋፍ ወይም የማፍረሻ ነጥቦች በማምጣት የአቋምህን ምክንያታዊነት በይበልጥ ለማጠናከር ትችላለህ። በተመሳሳይም አንድ መሠረታዊ ሥርዓት ከተናገርህ በኋላ አድማጮችህ ይህ እንዴት ሊሠራ እንደሚችል ለማየት እንዲችሉ ምሳሌ ሰጥተህ ማስረዳቱ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። እርግጥ ይህን እያመዛዘንህ ሳታበዛ ማድረግ ይኖርብሃል። አንድ ነጥብ እስከ ምን ድረስ በስፋት መብራራት እንዳለበት ለመወሰን ምን ያህል ጊዜ እንዳለህና ነጥቡ እየተብራራ ላለው ርዕሰ ጉዳይ የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማመዛዘን አለብህ።
21 አድማጮች ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እንዲያገናዝቡ በመርዳት በኩል ጥያቄዎች ምን ጊዜም ዓይነተኛ መሣሪያ ናቸው። አድማጮች መልስ
እንዲሰጡ የማይጠበቁባቸውን ጥያቄዎች ማቅረብም በትክክለኛ ቦታ ላይ ቆም ማለት ሲታከልባቸው አእምሮን ለማመራመር ይረዳሉ። በመስክ አገልግሎት ላይ እንደሚያጋጥመው ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዎች እየተናገርህ ከሆነ በጥያቄዎች አማካኝነት ሐሳባቸውን እንዲገልጡ እያደረግህ ለመቀጠል ትችላለህ። በዚህ መንገድ እያቀረብክላቸው ያሉትን ሐሳቦች እየጨበጡና እየተቀበሉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ትችላለህ።22 የአድማጮችህን አእምሮ ወደ አንድ አቅጣጫ ለመምራት ስለምትፈልግ አድማጮችህ በራሳቸው ተሞክሮም ይሁን ቀደም ብለህ ባቀረብካቸው ማብራሪያዎች ምክንያት ከሰበሰቡት እውቀት በመነሳት በዚያ ላይ መገንባት ይኖርብሃል። እንግዲያው አንዳንድ ነጥቦችን በበቂ ሁኔታ ማስፋፋትህን ለመገምገም አድማጮችህ ስለ ጉዳዩ ቀደም ሲል ያላቸውን እውቀት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል።
23 አድማጮችህ እየተከታተሉህ መሆኑን ለማረጋገጥ አንድ ነገር ስትናገር ምን ስሜት እንደሚያሳዩ መከታተሉ ምን ጊዜም ጥሩ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ስታገኘው የሚቀጥለውን ነጥብ ለማቅረብ ከመሞከርህ በፊት ወደኋላ ተመልሰህ አንዳንድ ነጥቦችን ግልጽ አድርግላቸው። ነጥቦቹን ከጉዳዩ ጋር እያገናዘቡ እንዲሄዱ ለማድረግ ጥንቃቄ ካላደረግህ መሐል ላይ የንግግሩ መሥመር ሊጠፋባቸው ይችላል።
24. ነጥቡ ከዋናው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው ለአድማጮችህ ማስረዳት ለምን ዓላማ ያገለግላል?
24 ነጥቡን ከአድማጮች አስተሳሰብ ጋር አገናዝበው። ማንኛውንም ነጥብ ስታቀርብ ይህ ነጥብ ውይይት ከተደረገበት ጉዳይ ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው በግልጽ ማስረዳትህን አረጋግጥ። በተጨማሪም ለንግግርህ ቀስቃሽነትን ጨምርበት። አድማጮችህ ከቀረቡላቸው ተጨባጭ ነገሮች አንፃር እርምጃ እንዲወስዱ አጥብቀህ አሳስባቸው። ያቀረብከው ትምህርት በእርግጥ ካሳመናቸው ያንን ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ይሆናሉ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]