በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የማስታወሻ አጠቃቀም

ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የማስታወሻ አጠቃቀም

ጥናት 28

ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የማስታወሻ አጠቃቀም

1. ከአድማጮች ጋር ግንኙነት የመፍጠርና በዚህ ረገድ በማስታወሻ የመጠቀሙን አስፈላጊነት ግለጽ።

1 ከአድማጮችህ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠርህ ለማስተማር ከፍተኛ እገዛ ያደርግልሃል። የእነርሱን አክብሮት ለማትረፍና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር ያስችልሃል። ከአድማጮችህ ጋር ያለህ ግንኙነት እንደ አንድ ተናጋሪ ሆነህ ስትመለከታቸው እነርሱ የሚያሳዩትን እያንዳንዱን የስሜት ለውጥ እንዲሰማህ እስኪያደርግ ድረስ በጣም ሊያቀራርባችሁ ይገባል። የማስታወሻ አጠቃቀምህ ከአድማጮችህ ጋር ይህን የመሰለ ግንኙነት እንዲኖር በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል። ብዙ ሐሳብ የተጻፈበት ማስታወሻ ከአድማጮችህ ጋር የሚኖርህን ግንኙነት ሊያደናቅፍ ይችላል። ሆኖም በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከወትሮው ሰፋ ያለ ማስታወሻ ማዘጋጀት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ማስታወሻውን በጥሩ ዘዴ እስከተጠቀምክበት ድረስ የሚያውክ አይሆንም። ይህ የሆነበት ምክንያት ጥሩ ችሎታ ያዳበረ ተናጋሪ ማስታወሻውን ማየትን ስለማያበዛ ወይም በማይገባው ጊዜ ላይ ስለማይመለከት ነው። ስለሆነም ከአድማጮች ጋር ያለው ግንኙነት አይቋረጥበትም። በምክር መስጫ ቅጽህ ላይ ይህ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል። “ከአድማጭ ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ የማስታወሻ አጠቃቀም” ተብሎ ተጠቅሶአል።

2–5. ከአድማጮች ጋር ውጤታማ የእይታ ግንኙነት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

2 ከአድማጮች ጋር የእይታ ግንኙነት መፍጠር። የእይታ ግንኙነት አድማጮችህን ማየት ማለት ነው። አድማጮችህን ጠቅለል አድርገህ ማየት ማለት ሳይሆን በአድማጮች መካከል የሚገኙትን ግለሰቦች መመልከት ማለት ነው። ፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት ማየትና በዚያው መሠረት አስፈላጊውን ነገር ማድረግ ማለት ነው።

3 አድማጮችን ማየት ማለት ግራና ቀኝ እየተገላመጡ ሁሉንም ማዳረስ ማለት አይደለም። ከአድማጮች አንዱን እያየህ አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር ለዚያ ግለሰብ ተናገር። ከዚያም ፊትህን ወደ ሌላ ግለሰብ በማዞር ጥቂት ዓረፍተ ነገሮችን ለእርሱ ተናገር። ማንኛውንም ግለሰብ ለረዥም ጊዜ ፍጥጥ ብለህ በማየት እንዲያፍር አታድርግ። ከጠቅላላው አድማጮች ውስጥ በጥቂቶች ላይ ብቻ አታተኩር። ይህን ዘዴ በመቀጠል ፊትህን እያዘዋወርክ አድማጮችህን ተመልከት። ፊትህን ወደ አንድ ሰው አቅንተህ ስትናገር ወደ ሌላ ሰው ከመዞርህ በፊት በእርግጥ ለዚያ ሰው መናገርና እርሱ የሚያሳየውን የስሜት ለውጥ መከታተል አለብህ። ማስታወሻህን በአትራኖሱ ላይ ማኖር ወይም በእጅህ መያዝ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማስቀመጥ አለብህ። በዚህ መንገድ ዓይንህን አንድ ጊዜ መለስ በማድረግ ብቻ አየት ልታደርገው ትችላለህ። ማስታወሻህን ለማየት ራስህ የግድ መዞር ካለበት ከአድማጮችህ ጋር የሚኖርህ ግንኙነት ይቀንሳል።

4 ምክር ሰጪህ ማስታወሻህን ምን ያህል ጊዜ ደጋግመህ እንደምታየው ብቻ ሳይሆን በየትኛው ጊዜ ላይ እንደምታየው ጭምር ይከታተላል። የአንድ ነጥብ ማሳረጊያ ላይ ስትደርስ ማስታወሻህን ብትመለከት የአድማጮችህን ስሜት ለማየት አትችልም። ቶሎ ቶሎ ማስታወሻህን የምትመለከት ከሆነ ከአድማጮች ጋር ያለህ ግንኙነት ይዳከማል። ይህም በአጠቃላይ የመደናገጥ ልማድ እንዳለብህ ወይም ንግግሩን ለማቅረብ በቂ ዝግጅት እንዳላደረግህ ያመለክታል።

5 ብዙ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች ጠቅላላውን ንግግር በንባብ መልክ እንዲያቀርቡ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ይህም ከአድማጮች ጋር የሚኖራቸውን የእይታ ግንኙነት ውስን ያደርግባቸዋል። ነገር ግን ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ከትምህርቱ ጋር በደንብ ቢተዋወቁ አለፍ አለፍ እያሉ ቦታቸውን ሳይስቱ አድማጮችን ሊመለከቱ ይችላሉ። ይህም ስሜትን በሚገልጽ መንገድ ለማንበብ ያነቃቃቸዋል።

6–9. ከአድማጮች ጋር ግንኙነት ለማድረግ የሚረዳውን ሌላ ዘዴና በዚህ በኩል የሚያጋጥሙትን አደጋዎች ግለጽ።

6 በአነጋገርህ ግንኙነት መፍጠር። ይህም እንደ እይታ ግንኙነት ሁሉ የግድ አስፈላጊ ነው። አነጋገር ሲባል የምትጠቀምባቸውን ቃላት ይመለ ከታል።

7 ከአንድ ሰው ጋር በግል ስታወራ “አንተ” “የአንተ” ወይም “እኛ” “የእኛ” በማለት በቀጥታ ታነጋግረዋለህ። ተስማሚ ሆኖ ካገኘኸው ብዙ ቁጥር ላላቸው አድማጮችም በዚሁ መንገድ መናገር ትችላለህ። ንግግርህን ከአንድ ወይም ከሁለት ሰዎች ጋር በመካሄድ ላይ እንዳለ ውይይት አድርገህ ለማየት ሞክር። አድማጮችህን በደንብ ብትከታተላቸው ልክ ለአንተ አንድ ቃል እንደተናገሩህ ያህል ይሰማህና ምላሽ ለመስጠት ትችላለህ። ይህም ትምህርቱን ስታቀርብ ከአንድ ሰው ጋር እየተነጋገርክ እንዳለህ እንዲሰማህ ያደርጋል።

8 ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚያስፈልግ ነገር አለ። ከአድማጮችህ ጋር በጣም የተዝናና ቅርርብ እንዳለህ በሚያስመስል መንገድ አትናገር። በመስክ አገልግሎት ላይ ከአንድ ወይም ከሁለት ሰው ጋር ክብር ባለው መንገድ ስትነጋገር በጣም የሚያቀራርብ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደማታደርግ ሁሉ እዚህም ላይ ጥንቃቄ አድርግ። ሆኖም ለእነዚያ ሰዎች በቀጥታ እንደምትናገር ሁሉ ንግግር በምትሰጥበትም ጊዜ ልክ እንደዚያው ቀጥተኛ መሆን ትችላለህ፤ ይገባሃልም።

9 ሌላም አደጋ አለ። በተውላጠ ስም ስትጠቀም አድማጮችህ መጥፎ እንደሠሩ በሚያስመስል መንገድ እንዳትናገር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል ስለ ዓመፀኝነት ንግግር የምትሰጥ ብትሆን አድማጮችህ ዓመፀኞች እንደሆኑ የሚያስመስል ቃል አትናገርም። ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ዝቅተኛ ሰዓት ስለመመለስ ትምህርት እየሰጠህ ቢሆን ሁልጊዜ “እናንተ” ከማለት ይልቅ “እኛ” በማለት ራስህንም ለመጨመር ትችላለህ። ስለ ሌሎች ሰዎች ስሜት የሚኖርህ አሳቢነትና ጥሩ ግምት በዚህ ዓይነቱ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ ይጠብቅሃል።

**********

10, 11. ከአስተዋጽኦ መናገርን እንድንማር ሊያበረታታን የሚገባው ምንድን ነው?

10 ከአስተዋጽኦ መናገር። የመጀመሪያ ንግግራቸውን ከአስተዋጽኦ የሚያቀርቡ አዲስ ተናጋሪዎች እምብዛም አይኖሩም። አብዛኞቹ ንግግሩን በወረቀት ላይ ጽፈው በቀጥታ ያነቡታል፤ አለዚያም ይሸመድዱትና በንግግር ያቀርቡታል። ምክር ሰጪህ በመጀመሪያው ላይ ይህን ያልፈዋል፤ ነገር ግን በንግግር ምክር መስጫ ቅጽህ ውስጥ “ከአስተዋጽኦ መናገር” ወደሚለው ነጥብ ስትደርስ በማስታወሻ ተጠቅመህ ንግግር እንድትሰጥ ያበረታታሃል። በማስታወሻ ተጠቅሞ መናገርን በደንብ ስትችል ወደ ሕዝብ ተናጋሪነት ለመሸጋገር ከፍተኛ እርምጃ ማድረግህን ያመለክታል።

11 ሌላው ቀርቶ ትንንሽ ልጆችና ማንበብ የማይችሉ ትልልቅ ሰዎችም እንኳ በሥዕል ተጠቅመው ሐሳብ ለማስተላለፍ ይሞክራሉ። አንተም በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ አጫጭር ንግግሮች እንዴት እንደተዘጋጁ ተመልክተህ ለንግግርህ ቀላል አስተዋጽኦ ማዘጋጀት ትችላለህ። በመስክ አገልግሎት ላይ ዘወትር ስትሰማራ ለሰዎች የምትመሰክረው ጽሑፍ እያነበብክ አይደለም። ቆርጠህ ከተነሣህበት በትምህርት ቤቱም ልክ እንደዚያው ማድረግ ትችላለህ።

12, 13. አስተዋጽኦ ለማዘጋጀት የሚረዱ አንዳንድ ሐሳቦችን ስጥ።

12 ከአስተዋጽኦ መናገርን መማርህ ንግግሩን ስትዘጋጅም ይሁን ስታቀርብ በንባብ መልክ ማዘጋጀትንና ማቅረብን እንድትተው ስለሚረዳህ ንግግሩን አትሸምድድ። አለዚያ የዚህኛው ጥናት ዓላማ ይከሽፋል።

13 በንግግርህ ላይ ጥቅሶችን የምትጠቀም ከሆነ እንዴት? ማን? መቼ? የት? እና የመሳሰሉትን የተውሳከ ግሥ ጥያቄዎች እየጠየቅህ አስተዋጽኦ ልታዘጋጅ ትችላለህ። ከዚያም ላዘጋጀኸው ትምህርት የሚስማሙ ሆነው ስታገኛቸው እነዚህን ነጥቦች የማስታወሻህ ክፍል አድርገህ ተጠቀምባቸው። ንግግር በምታቀርብበት ጊዜ ተስማሚ ሆኖ ስታገኘው እነዚህን ጥያቄዎች ለራስህ ወይም ለቤቱ ባለቤት እያቀረብህ መልሳቸውን ስጥ። ነገሩ ይህን ያህል ቀላል ነው።

14, 15. ምን ሁኔታዎች ተስፋ ሊያስቆርጡን አይገባም?

14 ጀማሪዎች ብዙ ጊዜ ‘አንድ ነጥብ ብዘልስ?’ እያሉ ይጨነቃሉ። ይሁን እንጂ ንግግርህ በደንብ ተቀነባብሮ ከቀረበ ማንም ሰው ነጥብ ማስቀረትህን ልብ ለማለት አይችልም። ደግሞም እዚህ ደረጃ ላይ ዋናው አሳሳቢ ነገር ነጥቦቹ ሁሉ የመሸፈናቸው ጉዳይ አይደለም። አሁን ለአንተ ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው በአስተዋጽኦ ተጠቅሞ ንግግር መስጠትን መማሩ ነው።

15 ይህን ንግግር ስታቀርብ ከአሁን በፊት ያዳበርካቸውን በርካታ የንግግር ባሕርያት ልትረሳ ትችል ይሆናል። በዚህ አትሸበር። ተመልሰው ይመጣሉ። እንዲያውም ክፍልህን በንባብ መልክ ማቅረብን ስትተው እነዚያን ባሕርያት በተሻለ ሁኔታ ታሳያለህ።

16, 17. የማስታወሻ ነጥቦችን በምንጽፍበት ጊዜ ምን ማስታወስ ይገባናል?

16 በአገልግሎት ትምህርት ቤቱ ላይ ለምትሰጣቸው ንግግሮች የምታዘጋጀውን ማስታወሻ በተመለከተ አንድ ምክር እናክልልህ። ማስታወሻህ ሐሳቦችን ለማስታወስ እንጂ እዚያ ላይ የሰፈሩትን ሐሳቦች ቃል በቃል ለመድገም ማገልገል የለበትም። ማስታወሻው ነጥቦችን አጠር አጠር አድርጎ የሚያስቀምጥ መሆን አለበት። በተጨማሪም ንጹሕ፣ በሥርዓት የተያዘና ጽሑፉ የሚነበብ መሆን ይኖርበታል። ትዕይንትህ ተመላልሶ መጠየቅ ከሆነ ማስታወሻህ በግልጽ የሚታይ መሆን የለበትም። ምናልባት በመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ ልታስቀምጠው ትችላለህ። ንግግሩን ከመድረክ የምታቀርብ ከሆነ በአትራኖስ እንደምትጠቀም ስለምታውቅ የማስታወሻ አጠቃቀም ጉዳይ ችግር አይሆንም። ነገር ግን እርግጠኛ ካልሆንህ ለማንኛውም ሁኔታ ተዘጋጅ።

17 ሌላው የሚረዳህ ነገር በማስታወሻህ አናት ላይ የንግግሩን መልዕክት መጻፉ ነው። ዋና ዋና ነጥቦችም ለዓይን ጉልህ ሆነው መታየት ይኖርባቸዋል። ጎላ ባሉ ፊደላት ለመጻፍ ሞክር አለዚያም አስምርባቸው።

18, 19. ከአስተዋጽኦ መናገርን ለመለማመድ የምንችለው እንዴት ነው?

18 በማስታወሻህ ላይ ጥቂት ነጥቦችን በመጻፍ ንግግር መስጠት አለብህ ሲባል እንደ ነገሩ አድርገህ መዘጋጀት ትችላለህ ማለት አይደለም። በመጀመሪያ ንግግሩን በዝርዝር አዘጋጅ። የምትፈልጋቸውን ያህል ብዙ ሐሳቦች ጻፍ። ከዚያም በጣም አጠር ያለ ሁለተኛ አስተዋጽኦ አዘጋጅ። ንግግርህን በምትሰጥበት ጊዜ የምትጠቀምበት አስተዋጽኦ ይኸኛው ይሆናል።

19 አሁን ሁለቱን አስተዋጽኦዎች ከፊትህ አስቀምጠህ አጠር ብሎ የተዘጋጀውን አስተዋጽኦ ብቻ እየተመለከትህ የቻልከውን ያህል በመጀመሪያው ዋና ነጥብ ሥር የተካተቱትን ሐሳቦች ተናገር። ቀጥለህ ሰፋ ያለውን አስተዋጽኦ ተመልክተህ ምን ሐሳቦችን እንደዘለልክ አረጋግጥ። አጠር ብሎ በተዘጋጀው አስተዋጽኦ ውስጥ ወዳለው ሁለተኛ ዋና ነጥብ በመሄድ ልክ እንደዚያው አድርግ። ከጊዜ በኋላ ከአጭሩ አስተዋጽኦ ጋር በጣም ስለምትተዋወቅ በሰፊው አስተዋጽኦ ውስጥ ያሉትን ነጥቦች በሙሉ ማስታወስ ወደምትችልበት ደረጃ ትደርሳለህ። በልምምድና በተሞክሮ ብዛት አስተዋጽኦ ይዘህ በራስህ አገላለጽ ንግግር መስጠት ያለውን ጥቅም ይበልጥ እያደነቅህ ትሄዳለህ። በንባብ መልክ ንግግር የምትሰጠው የግድ እንደዚያ ማድረግ ሲኖርብህ ብቻ ይሆናል። በይበልጥ ተዝናንተህ ትናገራለህ፤ አድማጮችህም በበለጠ አክብሮት ያዳምጡሃል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]