በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመዘጋጀት አስፈላጊነት

የመዘጋጀት አስፈላጊነት

ጥናት 8

የመዘጋጀት አስፈላጊነት

1–5. ዝግጅት በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለማን ነው? ለምንስ?

1 የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ የአገልግሎት ባልደረባው የነበረውን ቲቶን ክርስቲያኖች ሁሉ “መልካም ሥራን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁዎች እንዲሆኑ” እንዲመክራቸው አሳስቦት ነበር። (ቲቶ 3:1 የ1980 ትርጉም ) ይህም ማለት ወደፊት ለሚሠሩት ሥራ በአእምሮአቸውም ሆነ በዝንባሌያቸው መዘጋጀት ነበረባቸው ማለት ነው።

2 በማንኛውም ዓይነት ቲኦክራሲያዊ ሥራ ዝግጅት አስፈላጊ ነው። እርግጥ አንድን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትሠራ ሥራው ሙሉ በሙሉ አዲስ ስለሚሆንብህ ተጨማሪ ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ ይሆንብሃል። የእውቀትህ ክምችት አያደገ ሲሄድ ግን ቀድሞ ከተማርካቸው ነገሮችና ካገኘኸው ተሞክሮ መጠቀም ትችላለህ። ቢሆንም አንድን ዓይነት ሥራ ለምንም ያህል ጊዜ ስትሠራ ብትቆይ ዝግጅት ማድረግ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ።

3 የንግግር ክፍል የተሰጣቸው ብቻ ሳይሆኑ ጥሩ ብቃት ያለው የምሥራቹ አስፋፊ ሊሆን የሚፈልግ ማንኛውም ክርስቲያን መዘጋጀት ይኖርበታል። ለበርካታ ወራት ወይም ዓመታት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል የቆየህ ከሆንክ ወደ አገልግሎት ከመሄድህ በፊት እንደ መጀመሪያው ረዘም ላለ ጊዜ መዘጋጀት ላያስፈልግህ ይችላል። ተዘጋጅተህ ብትሄድ ግን የበለጠ ውጤት ልታገኝ ትችላለህ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜም ቢሆን እንዲሁ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመራህበት ጊዜ ብዙ ዝግጅት ማድረግ አስፈልጎህ ነበር። ይሁን እንጂ አንድን መጽሐፍ ምንም ያህል ጊዜ ደጋግመህ ብታስጠና የተማሪህን ሁኔታ እያሰብክ ብትከልሰው ጥናቱን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት ትችላለህ። መድረክ ላይ ወጥተህ ንግግር በምትሰጥበት ጊዜም ቢሆን እንዲሁ ነው። ባለፉት ዓመታት ያገኘኸው ተሞክሮ በጣም ሊጠቅምህ ይችላል። ቢሆንም ንግግር እንደምትሰጥ አስቀድሞ ከተነገረህ በቂ ዝግጅት ሳታደርግ ንግግሩን ለመስጠት አትሞክር።

4 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም ቢሆን መዘጋጀት ለሁላችን በጣም አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ተማሪ የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ስላለው በአንድ የተወሰነ ቀን የሚሸፈኑትን ትምህርቶችና የሚቀርበውን ትምህርትና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከፕሮግራሙ ላይ ማግኘት ይችላል። ከትምህርት ቤቱ የምታገኘው ጥቅም በምታደርገው ዝግጅት መጠን ላይ የተመካ ነው። በቅድሚያ የመዘጋጀትን አስፈላጊነት ችላ የምትል ከሆነ ብዙ ጥቅሞች ሊያመልጡህ ይችላሉ።

5 ለመዘጋጀት ጊዜ ያስፈልጋል። ቢሆንም ከዝግጅቱ የሚገኘው ጥቅም ከማንኛውም ዓይነት ጥረት ያመዝናል። መዘጋጀታችን በክለሳዎች ላይ ጠቃሚ ተሳትፎ እንድናደርግ ከማስቻሉም በላይ የይሖዋን አስተሳሰብ እንድንገነዘብና ስለ እውነት “ንጹሕ ልሳን” ያለን እውቀት እንዲሻሻል ያደርጋል። (ሶፎ. 3:9) ለትምህርት ቤቱ በቅድሚያ የመዘጋጀት ልማድ እንዲኖርህ ከቤተሰብህ አባሎች ጋር ወይም ከሌሎች ወዳጆችህ ጋር ለማንበብና ለማጥናት ዝግጅት አድርግ። እርግጥ በዚህ ትምህርት ቤት የተመዘገበ ሁሉ ንግግር የመስጠት አጋጣሚ ስለሚኖረው እንዴት ንግግሩን ለመዘጋጀት እንደሚችል አንዳንድ ሐሳብ መስጠት ጠቃሚ ይሆናል።

6. በአገልግሎት ትምህርት ቤት የንባብ ክፍል ሲሰጠን እንዴት መዘጋጀት ይኖርብናል?

6 የንባብ ክፍል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ላይ በየጊዜው የንባብ ክፍል ይቀርባል። ይህንን ክፍል ለማቅረብ ስትዘጋጅ መጀመሪያ የሚነበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጥንቃቄ አንብብ። ከስሞችና አስቸጋሪ ከሆኑ ቃላት አነባበብ ጋር ተዋወቅ። አለቦታው ሳትቆምና ሳትገድፍ በውይይት መልክ ለማንበብ እንድትችል ጮክ ብለህ እያነበብህ ተለማመድ። ትምህርቱ በተመደበለት ጊዜ ውስጥ ሊያልቅ የሚችል መሆኑን በጥንቃቄ አረጋግጥ።

7–11. ከአንድ ጽሑፍ ንግግር በምናዘጋጅበት ጊዜ የምንጠቀምባቸውን ነጥቦች ለመምረጥ የሚረዳን ስለምን ነገሮች ማሰብ ነው?

7 ከታተመ ጽሑፍ ንግግር ማዘጋጀት። እንዲህ ላለው ንግግር ለመዘጋጀት መደረግ የሚገባው የመጀመሪያ ነገር የተመደበውን ጽሑፍ በጥንቃቄ ማንበብ ነው። ከዋና ዋና ነጥቦች ግርጌ አስምር ወይም በወረቀት ላይ ዋና ዋና ነጥቦቹን በአጭሩ ጻፍ። የተብራሩትን ዋና ዋና ሐሳቦች በግልጽ ለመረዳት ሞክር። አሁን በተመደበው ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ትምህርት ልትሸፍን ስለማትችል የምታቀርባቸውን ነጥቦች ምረጥ። በነጥቦቹ አመራረጥ ረገድ ሊመሩህ የሚችሉ ነገሮች አሉ:- (1) አድማጮችህና የትዕይንቱ ዓይነት። ትምህርቱ እንዴት ተግባራዊ በሆነ መንገድ ሊሠራበት እንደሚችል ለመግለጽ ትዕይንቱ ይረዳልን? (2) የንግግሩ መልእክትና ለማሳየት የምትፈልገው የትምህርቱ ተግባራዊ ጥቅም።

8 የአድማጮችህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገባ። አድማጮችን የሚማርክና የሚጠቅም ነጥቦችን መምረጥ ይኖርብሃል። በጽሑፉ ላይ ከተገለጹት ነጥቦች አንዳንዶቹ ለአድማጮቹ ከባድ ከሆኑ በሌሎቹ አንቀጾች ላይ የበለጠ ትኩረት አድርግ። በተጨማሪም የምትናገረውን ሐሳብ በይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉልህን ጥቂት ጥቅሶች ለመምረጥ ትችላለህ። አድማጮችህን ግምት ውስጥ የምታስገባ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ትምህርት ለመሸፈን አትሞክርም። ትምህርቱን ለመጨረስ ከተጣደፍክ ከንግግሩ መገኘት የነበረበት ብዙ ጥቅም ይታጣል። ስለዚህ ጥቂት ነጥቦችን መርጦ በደንብ ማብራራት የተሻለ ይሆናል።

9 የተማሪ ንግግር በምታቀርብበት ጊዜ ለመልእክትህ አንድ ዓይነት ትዕይንት ብትመርጥ ጠቃሚ ይሆናል። ትዕይንትህ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ያገኘኸውን ሰው ስታነጋግር ወይም ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ጊዜ የቀረበልህን ጥያቄ ስትመልስ ወይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት ስትሰጥ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ለልጅህ እንደምታስረዳ የሚያሳይ ትዕይንትም ልትጠቀም ትችላለህ። ከእነዚህም ሌላ ብዙ ዓይነት አቀራረቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ትዕይንት በምትመርጥበት ጊዜ ዋናው አስፈላጊ ነገር በተቻለ መጠን ሊያጋጥም የሚችል እውነተኛ ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑ ነው። ስለዚህ ስለ ትዕይንት በጥንቃቄ አስብ። ሌሎች አስፋፊዎችም ጥሩ ሐሳብ ሊሰጡህ ስለሚችሉ አማክራቸው።

10 የመረጥከው መልእክት ምንድን ነው? ትምህርቱንስ ምን ነገር ለማስረዳት ልትጠቀምበት አስበሃል? እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ከታተመው ጽሑፍ ውስጥ የሚያስፈልጉህን ነጥቦች ምረጥ። ለንግግርህ መልዕክትና ዓላማ እምብዛም አስተዋጽኦ የማያደርጉትን ነጥቦች አውጣ። አብዛኛውን ጊዜ መብራራት የሚኖርባቸው ነጥቦች በተመደበልህ ጽሑፍ ውስጥ ስለሚኖሩ ብዙ ሐሳቦችን ከሌላ ጽሑፎች ለመሰብሰብ ከመሞከር ይልቅ በእነዚህ ላይ ብቻ ማተኮር በቂ ይሆናል። እርግጥ እንዲህ ሲባል ተስማሚ የሆነ ምሳሌ ማዘጋጀት ወይም አድማጮችህ የምትሰጠውን ትምህርት ጠቃሚነት በይበልጥ እንዲገነዘቡ የሚያስችል ሌላ ነጥብ መጨመር አይቻልም ማለት አይደለም። የሚቻል ሆኖ ሲገኝ አድማጮችህ ከንግግርህ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እንዲችሉ ትምህርቱ እንዴት በሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል አመልክት።

11 የንግግሩን መልእክትና ትዕይንቱን ከመረጥክ በኋላ በጽሑፉ ላይ ከሰፈሩት አንቀጾች አንዳንዶቹ ለንግግሩ የማይስማሙ እንደሆኑ ትገነዘብ ይሆናል። በእያንዳንዱ አንቀጽ የሰፈረውን ሐሳብ የመጠቀም ግዴታ የለብህም። ከዚህ ይልቅ በጽሑፉ ላይ ከተገለጹት ሐሳቦች በዛ ያለውን ክፍል ለመሸፈን የሚያስችልህን መልእክትና ትዕይንት ምረጥ።

12. በዝርዝር ከቀረቡ ጥቅሶች ንግግር ለማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

12 በዝርዝር ከቀረቡ ጥቅሶች ንግግር ማዘጋጀት። ከአንድ የጥቅሶች ዝርዝር ምናልባት በቋንቋህ የሚገኙ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት ከተባለው ቡክሌት ወይም ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ላይ ከተዘረዘሩት ጥቅሶች ክፍል እንድታቀርብ ትጠየቅ ይሆናል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ዓላማህ እነዚህን ጥቅሶች መሠረት በማድረግ ንግግር ወይም በመስክ አገልግሎት የሚቀርበውን የመሰለ መልእክት ማቅረብ ነው። በተመደበልህ ጊዜ ውስጥ አብራርተህ ልትጨርስ የማትችላቸው ብዙ ጥቅሶች ተዘርዝረው ከሆነ የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች ምረጥ። በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ልትሸፍን በምትችላቸው ጥቅሶች ብቻ ብትጠቀም የተሻለ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ልትጠቀምባቸው ያሰብካቸውን ጥቅሶች መርምር። እነዚህን ጥቅሶች ለመጠቀም የፈለግክበትን ምክንያት ወስን። ትምህርቱን ስታዘጋጅ ስለ እያንዳንዱ ጥቅስ የምትሰጠው ገለጻ ጥቅሱን የተጠቀምክበትን ምክንያት ግልጽ ለማድረግ የሚያስችል ይሁን። በተጨማሪም የጥቅሱ አነባበብ ቁልፍ የሆኑትን ቃላት የሚያጎላ መሆን ይኖርበታል። በመጨረሻም ለጥቅሱ የምትሰጠው ማብራሪያ ዋናውን ነጥብ ያስገነዝባል።

13–15.ንግግሩ የሚዘጋጅበት የተወሰነ ጽሑፍ ሳይሰጥ በአንድ የተወሰነ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ንግግር ለማዘጋጀት በሚፈለግበት ጊዜ እንዴት ያሉ እርምጃዎችን መከተል ይቻላል?

13 ርዕሱ ብቻ በሚሰጥበት ጊዜ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም ሆነ በአገልግሎት ስብሰባ ወይም በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ የንግግሩ ርዕስ ብቻ ተሰጥቶህ ንግግር እንድታዘጋጅ የምትጠየቅበት ጊዜ ይኖራል። መልእክቱን የምታቀርብበት የተወሰነ ጽሑፍ ላይሰጥህ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚያጋጥምህ ጊዜ እንደሚከተለው ማድረግ ትችላለህ። ምን ዓይነት ነጥቦችን ማብራራት እንደሚኖርብህ በአእምሮህ አሰላስልና ነጥቦቹን ወረቀት ላይ በአጭሩ ጻፍ። ይህ የመጀመሪያ እርምጃ በጣም አስፈላጊ ነው። ንግግርህ ትኩስ ሐሳብ የያዘ ወይም ሌሎች የተናገሩት ሐሳብ ጭማቂ ብቻ መሆኑ የሚወሰነው በዚህ የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የምርምርህ አድማስ በጥቂት ነጥቦች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ስለሚያደርግ ዓላማ ከሌለው ብዙ ምርምር ያድንሃል። ከዚህም በላይ ለራስህ ባሕርይ ባዕድ በሆነ አነጋገር ከመጠቀም ይልቅ ከራስህ የአነጋገርና የአቀራረብ ስልት ጋር የሚስማማ ትምህርት ለማቅረብ ያስችልሃል። በተጨማሪም ንግግር ስለምትሰጥበት ርዕሰ ጉዳይ ከጎለመሱ ሰዎች ጋር ብትነጋገር ጥሩ ይሆናል። ንግግሩ ሊዘጋጅና ሊዳብር ስለሚችልበት መንገድ ጠቃሚ ሐሳብ ሊሰጡህ ይችላሉ።

14 ከዚህ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ማውጫና (በኮንኮርዳንስ) በማኅበሩ ማውጫዎች (ኢንዴክሶች) ረዳትነት በመጽሐፍ ቅዱስና በሌሎች ጽሑፎች ላይ ምርምር በማድረግ ከራስህ አእምሮ ባመነጨኸው ትምህርት ላይ ተጨማሪ መረጃ ትጨምራለህ። አብዛኛውን ጊዜ ምርምር የምታደርግበትን ጽሑፍ የአርዕስት ማውጫ አስቀድመህ ብትመለከት ብዙ ልትጠቀም ትችላለህ። ከዚያም በጣም የሚጠቅምህን ፍሬ ነገር የት ለማግኘት እንደምትችል ለማወቅ ኢንዴክስ ተመልከት። በጣም የሚያስፈልጉህን ፍሬ ነገሮች ብቻ መምረጥ ብዙ ጊዜ ሊቆጥብልህ ይችላል። በምታነብበት ጊዜ አሁን ለምትዘጋጅበት የንግግር መልእክት ጠቃሚ ባልሆኑ ሐሳቦች ልትመሰጥ ትችላለህ። ጽሑፉን ከቃኘህ በኋላ የሚጠቅምህን ክፍል ብቻ ምልክት ብታደርግ እንዲህ ካለው አደጋ ትድናለህ። አብዛኛውን ጊዜ የሚያስፈልግህ የእያንዳንዱ አንቀጽ ፍሬ ሐሳብ የተገለጸበትን አረፍተ ነገር ልብ ማለትና ጠቃሚ መስሎ የታየህን አንቀጽ ብቻ ማንበብ ነው።

15 ከተለያዩ ጽሑፎች የቃረምካቸውን ሐሳቦች በራስህ ሐሳቦች ላይ ከጨመርክ በኋላ በተመደበልህ ጊዜ ውስጥ ልታቀርብ የምትችላቸውን ምርጥ ሐሳቦች ለመምረጥ ትዘጋጃለህ። ከሰበሰብካቸው በርካታ ነጥቦች መካከል አስፈላጊዎቹን ሐሳቦች ለመምረጥ እንዲረዳህ ተግባራዊ መሆን የሚችል ሐሳብ ነውን? ማራኪ ሐሳብ ነውን? የንግግሩን መልእክት የሚያጎላ ነውን? እንደሚሉት ያሉትን ጥያቄዎች ለራስህ አቅርብ።

16, 17. ማስታወሻ በመያዝ ረገድ ምን ሐሳብ ተሰጥቶአል?

16 ማስታወሻ መያዝ። ማንኛውንም ዓይነት ንግግር ለማቅረብ ተጠይቀህ ዝግጅት ስታደርግና ከልዩ ልዩ ጽሑፎች ሐሳብ በምታፈላልግበት ጊዜ ለማንኛውም ንግግር ያገኘሃቸውን ነጥቦች መዝግበህ የምትይዝበት አንድ ዓይነት ዘዴ አስፈላጊ ይሆናል። አንዳንድ ተማሪዎች በትናንሽ ካርዶች ወይም ወረቀቶች ላይ ለንግግሩ የሚጠቀሙባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለየብቻ መጻፍ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።

17 የሚጻፈው ነገር በጣም አጭርና ሐሳቡን የሚያስታውስህ ብቻ ሊሆን ይችላል። የማስታወሻው አጭር መሆን ከሌላ ምንጭ የተዋስከውን አነጋገር ወይም አረፍተ ነገር ከመከተል ይልቅ በራስህ አገላለጽ ለመናገር ያስችልሃል። ሐሳብህን ያገኘህበትን የጽሑፍ ምንጭ ጻፍ። ይህም ባስፈለገ ጊዜ ገጹንና አንቀጹን ለማግኘት ያስችልሃል። ለሐሳቡ ድጋፍ የሚሰጡ ቁልፍ ጥቅሶች በሙሉ መጻፍ አለባቸው። በካርዶች ወይም በቁራጭ ወረቀቶች መጠቀም የሚያስገኘው ሌላ ጥቅም ንግግሩን በምትዘጋጅበት ጊዜ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማስወጣትና አዳዲስ ሐሳቦችን ለመጨመር በምትፈልግበት ጊዜ አስተዋጽኦውን በሙሉ መገልበጥ ሳያስፈልግህ መጨመር ወይም ማውጣት ማስቻሉ ነው።

18. የተዘጋጀ ሕዝብ ለመሆን የምንፈልገው ለምንድን ነው?

18 የተዘጋጀ ሕዝብ። ማንኛውም ቲኦክራሲያዊ ሥራ ሲሰጥህ በቂ ዝግጅት ለማድረግ ችላ የማለት አዝማሚያ ካለህ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ መዘጋጀት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ብታስተውል ጥሩ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አጥማቂው ዮሐንስ “የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ” የማሰናዳት ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር። (ሉቃስ 1:17) “የተዘጋጁት” እስራኤላውያን ይሖዋ እንዲሠሩለት ያሰበውን ሥራ ለመሥራት እንዲችሉ በይሖዋ አሠራር ራሳቸውን ለመለወጥና ለማስተካከል ፈቅደው ነበር። ለእኛም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ በመጠቀምና ለሚሰጠን ክፍልና ሥራ ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ይሖዋ በሰጠን በዚህ የትምህርት ፕሮግራም አማካኝነት ለመለወጥና ለመስተካከል ፈቃደኛ መሆናችንን እናሳያለን። በዚህም መንገድ ውጤታማ የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን የሚያስችለንን ብቃት እናገኛለን።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]