በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሚያንጽ ውይይት

የሚያንጽ ውይይት

ጥናት 16

የሚያንጽ ውይይት

1, 2. ከሰዎች ጋር የምናደርገው ውይይት ምን ዓይነት መሆን ይገባዋል?

1 በየዕለቱ ከሰዎች ጋር በምናደርጋቸው ውይይቶች አምላክን ለማስከበር የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ “ቀኑን ሙሉ ለአምላክ ውዳሴ እናቀርባለን፣ እስከ ዘላለምም ስምህን ከፍ ከፍ እናደርጋለን” ሲል ጽፏል። ታዲያ ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ ይሖዋን የሚያመልኩ በሙሉ ሊኖራቸው የሚገባ የሚያስመሰግን ዝንባሌ አይደለምን? ከንፈራችንን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ያሳስበናል። — መዝ. 44:8 አዓት

2 ይህ ዓይነቱ ቁርጥ ውሳኔ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ሌሎችን የሚገነባ ነገር ከመናገር ይልቅ የሚያፈርሳቸውን የመናገር ዝንባሌ ሊኖረን ይችላል። (ያዕ. 3:8–12) ስለዚህ “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል” ብቻ እንድንናገር የሚያበረታታንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ዘወትር ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። — ኤፌ. 4:29

3, 4. ውይይት ከመናገር ሌላ ምን ነገርን ይጨምራል? ይህንንስ የት ለመለማመድ እንችላለን?

3 እርግጥ ነው፣ ውይይት የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ እንደመሆኑ መጠን ማዳመጥንም እንደሚጨምር መታወስ ይኖርበታል። ሰዎችን የሚያንጽ ነገር ብቻ ተናገር። ይሁን እንጂ ሌሎችም ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል። የሚናገረው ሰው ሐሳቡን እንዲገልጽ ለማድረግ ተስማሚ የሆኑ ጥያቄዎችን የመጠየቅን ልማድ አዳብር። ከጠየቅህም በኋላ ሰውዬው ተናግሮ እስኪጨርስ ድረስ ያለውን ጊዜ ቀጥለህ ምን እንደምትናገር ለማሰብ ከመጠቀም ይልቅ የሚናገረውን ነገር በጥሞናና በጉጉት አዳምጥ። የሌሎችን ሐሳብ ለማወቅ ይህን የመሰለ ፍላጎት ማሳየትህ ብቻውን ሊያንጻቸው ይችላል።

4 የሚያንጽ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉን ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ እቤትህ ከራስህ ቤተሰብ ጋር በምትሆንበት ጊዜ፤ ከሥራ ወይም ከትምህርት ቤት ጓደኞችህ ጋር በምትሆንበት ጊዜ፤ ከእምነት ባልደረቦችህ ጋር በምትገናኝበት ጊዜ የሚያንጽ ጭውውት ለማድረግ ትችላለህ። በአገልግሎት ትምህርት ቤት የምንሰጣቸው ብዙ ንግግሮች ጥሩ ውይይት የማድረግ ችሎታችንን እንድናዳብር ያስችሉናል።

5–7. በቤተሰባችን መካከል የሚደረገውን ውይይት ለማሻሻል፣ በተለይ በምግብ ጊዜያት ምን ለማድረግ እንደምንችል ሐሳብ ስጥ።

5 በቤት ውስጥ። በቤት ውስጥ የምናደርገው ጭውውት ለቤተሰቡ ደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ስለዚህ በዚህ ረገድ ያለንን ችሎታ ለማዳበር አስፈላጊውን ጥረት ማድረጋችን ተገቢ ነው። ባሎችም ሆኑ ሚስቶች የትዳር ጓደኞቻቸው የሚናገሩትን ነገር በጥሞና ሲያዳምጡአቸው ደስ ይላቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው የሚናገሩትን ሲሰሙና ልባዊ አሳቢነት ሲያሳዩአቸው ይደሰታሉ። ሌላ ሰው ሲያነጋግርህ ብታቋርጠው ወይም መጽሔት ማገላበጥ ብትጀምር ወይም በማንኛውም ሌላ መንገድ ለማዳመጥ ፍላጎት የሌለህ መሆኑን ብታሳይ በቤተሰብህ መካከል የሚኖረው የመወያየት መንፈስ ፈጥኖ ይበላሻል። ማንም ሰው ቢሆን የሚናገረውን መስማት ለማይፈልግ ሰው ማውራት ደስ አይለውም።

6 የምግብ ጊዜያት የሚያንጽ የቤተሰብ ጭውውት ለማድረግ የሚቻልባቸው ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው። በየቀኑ በአንደኛው የምግብ ጊዜ የሚደረገው ውይይት ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ በሚገኘው በዕለቱ ጥቅስ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይችላል። በሌሎቹ የምግብ ጊዜያት ደግሞ በቅርቡ በተነበበ የመጠበቂያ ግንብ ወይም የንቁ! መጽሔት ላይ የተመሠረተ ጠቃሚና የሚያንጽ ውይይት ማድረግ ይቻላል። ይሁን እንጂ በምግብ ጊዜያት የሚደረገው ውይይት ድርቅ ያለ ሥርዓት የተከተለ፣ ከልብ የመነጨ ነፃ ሐሳብ ለመስጠትና በተዝናና መንፈስ ለመመገብ የማያስችል መሆን የለበትም።

7 እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በምግብ ጊዜ የሚያንጽ ውይይት እንዲኖር አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል። የምግብ ጊዜ የመወቃቀሻ ጊዜ አይደለም። ይህ ዓይነቱ ነገር የተበላው ምግብ በተገቢ ሁኔታ እንዳይፈጭ እክል ይሆናል። አንድ ሰው በቀኑ ውስጥ ትምህርት ሰጪ የሆነ ወይም የሚያስቅ ነገር መስማቱ አይቀርም። በመስክ አገልግሎትም አስደሳች ተሞክሮ ሊያጋጥመው ይችላል። አለበለዚያም ቤተሰቡ ሊሰማው የሚገባ ነገር በጋዜጣ ላይ አንብቦ ወይም በሬዲዮ ሰምቶ ይሆናል። ምግብ በሚበሉበት ጊዜ አስታውሶ ለቤተሰቡ ሊያካፍለው ይችላል። እንዲህ ካደረጋችሁ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቶሎ በልታችሁ ለመነሳት ከመጣደፍ ይልቅ እርስ በርሳችሁ ለመጨዋወት ትናፍቃላችሁ።

8–10. በወላጆችና በልጆች መካከል የሚደረግ የግል ውይይት በተለይ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ልጆቹስ እንዴት ከወላጆቻቸው ማበረታቻ ሊያገኙ ይችላሉ?

8 በተጨማሪም ወላጆች ከእያንዳንዱ ልጅ ጋር ሌሎቹ የቤተሰብ አባሎች በማይኖሩበት በግል መጨዋወት ያስፈልጋቸዋል። እቤታቸው እንዳሉ ይሁን መንገድ ለመንገድ እየሄዱ፣ በተዝናና መንፈስ ቢጨዋወቱ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ይችላሉ። እንዲህ ያለው ጭውውት ወጣቱ በሚያድግበት ጊዜ ለሚያጋጥሙት አካላዊ ለውጦች ሊያዘጋጀው ይችላል። በተጨማሪም እንደነዚህ ያሉት ውይይቶች በልጁ ልብ ውስጥ ምን እንዳለ፣ እውነተኛ ፍላጎቱ ምን እንደሆነና የሕይወቱ ግብና ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችላሉ። ፍላጎቱንና ዓላማውን ለመቅረጽና ለማስተካከልም ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣሉ።

9 በጭውውታችሁ ወቅት ልጃችሁ ችግር አጋጥሞት እንደነበረ ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር አድርጎ እንደነበረ ቢነግርህ ወዲያው ልትቆጣ ብትጀምር ውይይቱ በአጭሩ ተቀጭቶ ይቀራል። ለወደፊቱም ቢሆን በዚህ ጊዜ ያጋጠመውን ሁኔታ ስለሚያስታውስ ሁለተኛ እንዲህ ያለ ነገር አያነሳም። አብዛኛውን ጊዜ በጥሞና ብታዳምጠውና ሁኔታውን እንደምትረዳለት የሚያሳዩ ጥያቄዎችን ብትጠይቀው የተሻለ ይሆናል። ከዚያም በደግነትና ጥብቅ አቋም በማሳየት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የራቀውን አካሄዱን እንዲያስተካክል ልትረዳው ትችላለህ።

10 ጭውውት ለቤተሰብ ደስታ አስፈላጊ ቢሆንም ሁልጊዜ መናገር አስፈላጊ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም የራስህን አሳብ የምታሰላስልበትና ፀጥ ብለህ ሁኔታዎችን የምታመዛዝንበት ጊዜ ቢኖርህ ጥሩ ነው። ስለዚህ የቤተሰብ አባሎች ፀጥታ እንዲኖር የሚፈልጉበት ጊዜ ይኖራል።

11, 12. ከመደበኛው የመስክ አገልግሎት በተጨማሪ ለመመስከር የሚያስችሉ እንዴት ያሉ አጋጣሚዎች አሉ?

11 ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር። የአንድ ሰው አገልግሎት ጥሩ ንግግር ለመጀመር ባለው ችሎታ የሚነካው እንዴት ነው? አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ለምን ሁልጊዜ ጥሩ ተሞክሮ እንደሚያጋጥማቸው አስባችሁ ታውቃላችሁ? ራሳቸው ቀዳሚ ሆነው ውይይት ስለሚጀምሩ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱሳዊው ምሳሌ “የጠቢባን ከንፈር እውቀትን ትዘራለች” ይላል። — ምሳሌ 15:7

12 ከመደበኛው የመስክ አገልግሎት ውጭ እንኳን ከሰዎች ጋር ውይይት ለመጀመርና ስለ ይሖዋ ለመናገር የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን የቤት እመቤቶች ለጎረቤቶች ወይም እቤታቸው ዕቃ ለመሸጥ ለሚመጡ ሰዎች ሊመሰክሩ ይችላሉ። ልጆች ወደ ትምህርት ቤት በሚጓዙበት ጊዜ ወይም አንደኛው ክፍለ ጊዜ አልቆ የሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ መምህር ከመግባቱ በፊት ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር ውይይት ሊጀምሩና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊናገሩ ይችላሉ። ከቤታቸው ውጭ የሚሠሩ ደግሞ በሥራ ቦታቸው፣ ምናልባትም በምሣ ሰዓት ሊመሰክሩ ይችላሉ። በመናፈሻ ቦታዎች በምትዘዋወርበት፣ ዕቃ ለመግዛት በምትሰለፍበትና አውቶቡስ በምትጠብቅበት ጊዜም እንኳ ከሌሎች ጋር የሚያንጽ ውይይት ለመጀመር ትችላለህ። የመንግሥቱ ስብከት በታገደባቸው አገሮች የስብከቱ ሥራ በአብዛኛው የሚከናወነው መደበኛ ባልሆነ መንገድ ውይይት በመጀመር ነው። ይህ የስብከት ዘዴ ፍሬያማ መሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በእነዚህ አገሮች የአምላክ አገልጋዮች ቁጥር በፍጥነት በማደጉ ታይቷል።

13–16. ምሥክርነት ለመስጠት መንገድ የሚከፍት ውይይት ለመጀመር እንዴት ባሉ ዘዴዎች መጠቀም ይቻላል?

13 በተለያዩ ሁኔታዎች ተጠቅመን ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስፈልገን ውይይቱን ለመክፈት የወዳጅነት ቃል መናገር ብቻ ሊሆን ይችላል። ከዚያ በኋላ ጭውውቱ ሊቀጥል ይችላል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። አንድ ቀን ቀትር ላይ በሰማርያ በሚገኝ አንድ ጉድጓድ አጠገብ ለማረፍ በተቀመጠ ጊዜ ውኃ ልትቀዳ የመጣች አንዲት ሴት ውኃ እንድታጠጣው ጠየቃት። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ስለማይነጋገሩ ይህ ጥያቄው ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ያላትን ፍላጎት ቀሰቀሰው። አንድ ጥያቄ ጠየቀችው። ኢየሱስም የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ እንዳለው በመናገር የማወቅ ጉጉቷን በይበልጥ አነሳሳው። በዚህም ምክንያት የመመስከር አጋጣሚ አገኘ። ወዲያው ምሥክርነት መስጠት እንዳልጀመረ ልብ ማለት ይገባል። ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችለውን መንገድ ለማዘጋጀት በወዳጃዊ ንግግር ተጠቀመ። — ዮሐ 4:5–42

14 አንተም ይህን የመሰለ የሚያንጽ ንግግር ለመጀመር ትችላለህ። አውቶቡስ በምትጠብቅበት ጊዜ አጠገብህ ለሚገኘው ሰው ስለ አየር መበከል ወይም ስለ ጦርነት ወይም ተመሳሳይ ስለሆኑ ሌሎች ችግሮች የሚገልጽ መጽሔት ወይም ጋዜጣ ልታሳየው ትችላለህ። ከዚያም “እነዚህ ሁኔታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም የተባባሱት ለምን ይመስልዎታል? መላዋ ምድር ለመኖር የምታስደስት ሥፍራ የምትሆንበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ?” ብሎ መጠየቅ ይቻላል። በተጨማሪም በወቅቱ በአካባቢው ስለተከሰተ ችግር መናገርና “ታዲያ መፍትሔው ምን ይመስልዎታል?” ብሎ መጠየቅ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ታይቶአል። ይህም እውነተኛ መፍትሔ ስለሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት ወደ መወያየት ይመራል። እርግጥ፣ አስተዋይ መሆን ያስፈልጋል። ሰዎችን ለማነጋገር ሞክረህ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ በግድ ውይይቱን መቀጠል አስፈላጊ አይደለም። ቢሆንም በውኃ ጉድጓድ አጠገብ እንደነበረችው ሳምራዊት ሴት በደስታ የሚያደምጡ ሰዎች መኖራቸው አይቀርም።

15 ስለ አምላክ ቃል ለመነጋገር የሚያስችል አጋጣሚ መፍጠር የሚቻልበት ሌላ መንገድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቀላሉ ሊታዩ በሚችሉባቸው ቦታዎች ማስቀመጥ ነው። ጽሑፎች እቤት ውስጥ ሊታዩ በሚችሉባቸው ቦታዎች ሲቀመጡ አብዛኛውን ጊዜ ሊጠይቁን የሚመጡ ሰዎች ስለ ጽሑፎቹ መናገር ይጀምራሉ። ይህም ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል መንገድ ይከፍታል። በትምህርት ላይ የምትገኝ ከሆንክ በጠረጴዛህ ላይ መጽሐፍ ወይም መጽሔት ብታስቀምጥ ስለ ጽሑፉ ምንነት የሚጠይቅህ ሰው እንደሚኖር የታወቀ ነው። በዚህ ጊዜ ስለ ጽሑፉ ምንነት በመናገር ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ ታገኛለህ። በምሳ ሰዓት ወይም በሕዝብ መጓጓዣ ውስጥ ሆነህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ብታነብ የማወቅ ጉጉት ላላቸው ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የመናገር አጋጣሚ ሊከፍትልህ ይችላል።

16 ከምታውቃቸው ሰዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ወደ መነጋገር ሊያመራ ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ የሚተዋወቁ ሰዎች የሚጨዋወቱት ምን እንዳደረጉ፣ የት ሄደው እንደነበረ፣ ምን አይተውና ሰምተው እንደነበረ ወይም ምን ለማድረግ እንደሚያቅዱ ነው። ስለዚህ ከሌሎች ጋር የመነጋገር አጋጣሚ ስታገኝ ምን ስታደርግ እንደነበርክ ለምን አትነግራቸውም? በክልል ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ከነበረ ለሥራ ባልደረባህ ወይም ለጎረቤትህ የት ሄደህ እንደነበረና የስብሰባው ዋነኛ ንግግር ርዕስ ምን እንደነበረ ተናገር። ስለ ንግግሩ ጥያቄ ይጠይቅህ ይሆናል። በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔት ምን እንዳነበብህ ለሰዎች ተናገር። የመስማት ፍላጎታቸውን ካነሳሳህ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ይጠይቁሃል። አሁን ተጨማሪ ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚ አገኘህ ማለት ነው። እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ወደ አምላክ ዓላማ ለመምራት የታቀዱ ውይይቶች የሚያንጹ እንደሆኑ አያጠራጥርም።

17–20. ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር ስንሆን የሚያንጽ ውይይት ልናደርግ ስለሚያስችሉን ርዕሰ ጉዳዮች ሐሳብ ስጥ።

17 ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር ስንሆን። ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜም የምናደርገው ንግግር ከፍተኛ ደረጃ ያለውና ለምሥራቹ አገልጋዮች የሚገባ መሆን ይኖርበታል። የመነጋገሩ ዓላማ ጊዜ ለማሳለፍ ብቻ ሳይሆን ለመተናነጽ መሆን ይኖርበታል።

18 በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ የሚያንጽ ጭውውት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ይገኛል። ስብሰባው እንዳለቀ ወዲያው ተጣድፎ የመውጣት ልማድ አይኑርህ። በዚህ ጊዜ ለምን ተሞክሮ ካላቸውና ሸምገል ካሉ ወንድሞች፣ እንዲሁም ዓይነ አፋርና ገለልተኛ የመሆን ባሕርይ ካላቸው ወንድሞች ጋር አትጨዋወትም? ብዙ የምንነጋገርባቸው ጉዳዮች አሉ። በቅርቡ በመጣ መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ስለወጣና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ስለሚገባ ትምህርት መነጋገር ይቻላል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስለተሰጠህ ክፍል ልትነጋገሩ ትችላላችሁ። በንግግርህ ልትጠቀምበት ስለምትችለው አዲስ ሐሳብ ሊነግሩህ የሚችሉ ሊኖሩ ይችላሉ። አለበለዚያም አንተ ራስህ ሌሎች ክፍላቸውን እንዲያቀርቡ የሚረዳቸው ሐሳብ ልትሰጣቸው ትችላለህ። በመስክ አገልግሎት ስለተገኙ ተሞክሮዎችም መነጋገር ይቻላል። አለበለዚያም በዚያ ቀን በተደረገው ስብሰባ በጣም ስላሰደሰቱህ ክፍሎች መናገር ትችላለህ። እንደነዚህ ያሉት ውይይቶች ሌሎችን እንደሚያንጹ የታወቀ ነው።

19 በትላልቅ ስብሰባዎች ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመነጋገር አጋጣሚ ይገኛል። ብዙ ምሥክሮች ለምግብ በሚሰለፉበት ጊዜ ወይም ወደ ስብሰባው ቦታ በሚሄዱበትና በሚመለሱበት ጊዜ በአጠገባቸው ካገኙአቸው ጋር መነጋገር ይጀምራሉ። ንግግር ለመጀመር ከሚያስችሉህ ጥሩ መንገዶች አንዱ ላገኘኸው ወንድም ወይም እህት ስምህን መናገርና የእርሱን ስም መጠየቅ ነው። እንዴት የይሖዋ ምሥክር ሊሆን እንደቻለ ጠይቀው። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያለው ጥያቄ አስደሳች ወደሆነና ወደሚያንጽ ውይይት ይመራል።

20 በመስክ አገልግሎት ለመካፈል በምትሄድበት ጊዜም መንገድ ላይ እያለህ ጠቃሚ የሆነ ውይይት ለማድረግ ትችላለህ። ምንም ዓይነት ቁም ነገር ስለሌላቸው ጉዳዮች ከመናገር ይልቅ ለምን በዚያ አካባቢ የሚኖሩትን ሰዎች ስለምታነጋግርበት ዘዴ ወይም ርዕሰ ጉዳዮች አትወያይም? በተጨማሪም ሊነሱ የሚችሉትን የተቃውሞ መልሶች እንዴት ማብረድ እንደምትችል ብትወያይ በጣም ጥሩ ይሆናል። እንደነዚህ ባሉት ጊዜያት ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች መነጋገርና ማሰብ ተገቢ ከመሆኑም በላይ መንፈሳችንን ያድሳል። — ፊልጵ. 4:8, 9

21–24. ውይይቱ የሚያንጽ ካልሆነ እኛ በግላችን ምን ለማድረግ እንችላለን?

21 በወንድሞችና በእህቶች መካከል በምትሆንበት ጊዜ ጭውውቱ ዓላማ ቢስ ወይም የማያንጽ ከሆነ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ጭውውቱን ይበልጥ ጠቃሚ ወደሆነ አቅጣጫ ዞር ሊያደርግ የሚችል ጥያቄ ለመጠየቅ ሞክር። አንድ የተለየ ርዕሰ ጉዳይ አንስተህ ጥያቄ አቅርብ። እንዲህ ባለው ውይይት የሚካፈሉት ሁሉ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ዕድል ቢያገኙ ይበልጥ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

22 ውይይቱ ስለ ሌሎቸ የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች ከሆነ የሚያንጽ ውይይት ከመሆን ይልቅ እነርሱን የሚያዋርድ ወይም የሚተች እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በቦታው ካሉት መካከል አንዱ ስለሌላ ወንድም ድክመት መናገር ቢጀምር ውይይቱን ወደሚያንጽ መሥመር ዘወር ለማድረግ የሚያስችል ድፍረት ይኖርሃልን? ለይሖዋ ድርጅት በታማኝነት በመቆም ከአባላቱ አንዱ ጥቃት እንዳይደርስበት ትከላከልለታለህን? ይህ ቀላል ጉዳይ ነው የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በአምላክ ውስን አገልጋዮች ላይ ስህተት መለቃቀም በአምላክ ዝግጅት ላይ ወደማጉረምረም ሊመራ እንደሚችል ካስታወስን ጉዳዩን እንደቀላል ነገር አንቆጥረውም። — ያዕ. 5:9፤ 2 ቆሮ. 10:5

23 ጭውውቱ ሁሉንም የሚያዝናናና አስቂኝ ቀልዶች የሚነገሩበት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለው ጭውውትም ቢሆን አዝናኝና ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ጭውውቱ ደረጃውን ቀንሶ ለክርስቲያን አገልጋዮች የማይገባ ነገር የሚነገርበት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ልብ ማለት ያስፈልጋል:- “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፣ ይልቁን ምስጋና እንጂ።” — ኤፌ. 5:3, 4

24 ስለዚህ የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ዘወትር ከሌሎች ጋር የምናደርገው ውይይት ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ይሁን። እንዲህ ካደረግን ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ” በማለት የጻፈውን ግሩም ምክር ሥራ ላይ አዋልን ማለት ነው። — ሮሜ 15:2

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]