በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የድምፅ መጠንና ቆም እያሉ መናገር

የድምፅ መጠንና ቆም እያሉ መናገር

ጥናት 23

የድምፅ መጠንና ቆም እያሉ መናገር

1, 2. ስንናገር የድምፃችን መጠን በቂ መሆን ያለበት ለምንድን ነው?

1 የተናገርከውን ነገር ሌሎች በቀላሉ ሊሰሙት ካልቻሉ የንግግርህ ጥቅም በከንቱ ይቀራል። በሌላው በኩል ግን ከመጠን በላይ እየጮህክ ብትናገር አድማጮችህ ሊረበሹና ያዘጋጀሃቸውን ጥሩ ሐሳቦች መከታተል ሊያቅታቸው ይችላል። በብዙ የመንግሥት አዳራሾች ላይ የሚታየው ሁኔታ የተመጣጠነ ድምፅ አስፈላጊነት ለምን እንደሚያሳስበን ግልጽ ያደርግልናል። በአዳራሹ ውስጥ ከፊት የተቀመጡት ሰዎች የሚሰጡትን ሐሳብ ከኋላ ያሉት ብዙውን ጊዜ ሊሰሙት አይችሉም። አንዳንድ ጊዜ መድረኩ ላይ ቆሞ የሚናገረው ተናጋሪ ድምፁ ደካማ ይሆንና አድማጮችን መቀስቀስ ሳይችል ይቀራል። በመስክ አገልግሎትም መስማት የሚያስቸግራቸው ሰዎች ያጋጥሙናል። በተጨማሪም ወደ ቤት ገብተን ስንመሰክር በቤቱ ውስጥም ሆነ ከቤቱ ውጭ እኛን የሚረብሽ ድምፅ ሊያጋጥመን ይችላል። ይህ ሁሉ ትክክለኛ የድምፅ መጠንን በጥንቃቄ እንድናስብበት ያስገድደናል።

2 ያለ ችግር እንዲሰሙን በቂ ድምፅ ማሰማት። ድምፃችን ምን ያህል መጉላት እንዳለበት ለማመዛዘን በመጀመሪያ ሊታሰብበት የሚገባው በቂ ኃይል ያለው ድምፅ ለማሰማት ጥረት ተደርጓልን? የሚለው ጥያቄ ነው። በሌላ አነጋገር ድምፅህ ከፊት ያሉትን ሳያደነቁር ከኋላ ያሉት ሊሰሙት ችለዋልን? ለጀማሪ ተናጋሪዎች ይህ መለኪያ በቂ ሊሆን ይችላል፤ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች ግን ቀጥሎ ያሉትን ሁኔታዎች ለማሟላት መጣር አለባቸው። እያንዳንዱ ተማሪ በዚህ የንግግር ባሕርይ ረገድ እስከምን ድረስ መታረም እንዳለበት የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ይወስናል።

3–10. ድምፃችንን በትክክል ለመመጠን የትኞቹ ሁኔታዎች ይረዱናል?

3 ሁኔታዎችን ለመቋቋም የምናሰማው የድምፅ መጠን። አንድ ተናጋሪ እየተናገረ ሳለ የተለያዩ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ማወቅ ይኖርበታል። ይህን ማወቁ የማስተዋል አድማሱን ስለሚያሰፋለት አቀራረቡን እንደ ሁኔታው እንዲለዋውጥና አድማጮቹ የሚናገረውን ቃል ሰምተው እንዲከታተሉት ለማድረግ ያስችለዋል።

4 ሁኔታዎች ከአዳራሽ ወደ አዳራሽ እንዲሁም እንደ ተሰብሳቢዎቹ ብዛት ይለያያሉ። ሁኔታዎችን በቁጥጥርህ ሥር ለማድረግ የድምፅህን መጠን መቆጣጠር ይኖርብሃል። ፍላጎት ባሳየ ሰው ቤት ውስጥ ስትሆን ከምታሰማው ድምፅ ይልቅ በመንግሥት አዳራሽ የምታሰማው ድምፅ ጐላ ማለት አለበት። ከዚህም ሌላ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከፊት ባሉት ወንበሮች ላይ ሰብሰብ ብሎ የተቀመጠ አነስተኛ ቡድን (ለምሳሌ በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ጊዜ) አዳራሹ በሰው በሚሞላበት ጊዜ (ለምሳሌ በአገልግሎት ስብሰባ ጊዜ) ከሚጠይቀው ያነሰ ድምፅ ያስፈልገዋል።

5 ነገር ግን እነዚህም ሁኔታዎች ቢሆኑ ቋሚ አይደሉም። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥና ከዚያ ውጭ የሚረብሽ ድምፅ በድንገት ሊሰማ ይችላል። መኪና ወይም ባቡር ሲያልፍ፣ የእንስሳት ጩኸት፣ የልጆች ለቅሶ፣ አርፋጆች እነዚህ ሁሉ የድምፅህን መጠን እንድትለዋውጥ ያስገድዱሃል። እነዚህ ሁኔታዎች ሲከሰቱ አለመንቃቱና አስፈላጊውን ለውጥ አለማድረጉ አድማጮች አንድ በጣም አስፈላጊ ነጥብ እንዲያመልጣቸው ሊያደርግ ይችላል።

6 ብዙ ጉባኤዎች የድምፅ ማጉያ መሣሪያ አላቸው። ሆኖም በአጠቃቀማቸው ላይ ጥንቃቄ ካልተደረገና የድምፁ መጠን አለቅጥ ከፍና ዝቅ የሚል ከሆነ ተማሪው እነዚህን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ምክር እንዲሰጠው ያስፈልጋል። (ስለ ድምፅ ማጉያ አጠቃቀም ጥናት ቁጥር 13⁠ን ተመልከት።)

7 አንዳንድ ጊዜ አንድ ተናጋሪ ይህንን የድምፅ መጠን በደንብ እንዳያሳይ የራሱ የድምፅ ዓይነት ዕንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። ይህ ችግር ካለብህና ድምፅህ መሐል ላይ እየሞተ የሚሄድ ወይም የሚቆራረጥ ከሆነ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ይህንን ግምት ውስጥ ያስገባዋል። ኃይል ያለው ጥሩ ድምፅ እንዲኖርህ የሚያስችል የልምምድ ፕሮግራም እንድታወጣ ሐሳብ ያቀርብልህ ይሆናል። ሆኖም ድምፅን መለዋወጡ ሌላ የንግግር ባሕርይ ስለሆነ የድምፅን መጠን በተመለከተ ጠበቅ አናደርገውም።

8 ሊፈጠሩ የሚችሉትን ሁኔታዎች ሁሉ በአንድ ንግግር ላይ ማየትና መፍረድ አይቻልም። ምክር መሰጠት ያለበት አሁን ከተሰጠው ንግግር አንፃር እንጂ በሌላ ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን በመጥቀስ አይደለም። እርግጥ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ተማሪው አሁን ስላቀረበው ንግግር ቢያመሰግነውና በምክር መስጫ ቅጹ ላይ “ጥ” የሚል ምልክት ቢሰጠውም አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነበት ለየት ባሉ ሁኔታዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሊጠቅስለት ይችላል።

9 አንድ ተማሪ የድምፁ መጠን በቂ መሆኑን እንዴት ለማመዛዘን ይችላል? ከዋና ዋናዎቹ መለኪያዎች አንዱ አድማጮች የሚያሳዩት ስሜት ነው። ልምድ ያለው ተናጋሪ መግቢያውን እያቀረበ በአዳራሹ ውስጥ ከኋላ የተቀመጡትን ሰዎች ፊትና አጠቃላይ ሁኔታቸውን በጥንቃቄ በማስተዋል ያለ ምንም ችግር እየሰሙት መሆን አለመሆናቸውን ሊገመግም ይችላል። ድምፁንም እንዳስፈላጊነቱ ከፍ ወይም ዝቅ ያደርጋል። የአዳራሹን “ሁኔታ” በደንብ ካረጋገጠ በኋላ ምንም ችግር አይኖረውም።

10 ሌላው ዘዴ በዚያው ፕሮግራም ላይ ክፍል ያላቸውን ሌሎች ተናጋሪዎች ማየት ነው። የሚናገሩት በቀላሉ ይሰማልን? የድምፃቸው መጠን ምን ያህል ነው? ይህን ሁሉ ከገመገምህ በኋላ ድምፅህን እንዳስፈላጊነቱ አስተካክል።

11, 12. የድምፃችን መጠን ከትምህርቱ ጋር የግድ መጣጣም ያለበት ለምንድን ነው?

11 ለትምህርቱ የሚስማማ የድምፅ መጠን። ስለ ድምፅ መጠን አሁን የምናደርገው ውይይት በሌላ ቦታ ላይ ድምፅን ከፍና ዝቅ ስለማድረግ ከተሰጠው ሐሳብ ጋር እንዳይደነጋገርብን መጠንቀቅ ያስፈልገናል። አሁን እዚህ ላይ ለመናገር የፈለግነው የድምፃችን መጠን ከምናቀርበው ትምህርት ጋር የሚጣጣም መሆን እንደሚያስፈልገው ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ተማሪ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎችን የሚያወግዝ ቃል እያነበበ ቢሆን በወንድሞች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር ምክር የሚሰጠውን ቃል ቢያነብ ከሚያሰማው ለየት ያለ የድምፅ መጠን እንደሚጠቀም ግልጽ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ 36:11⁠ን ከቁጥር 12ና 13 ጋር በማወዳደር እነዚህ ቃሎች በተለያየ የድምፅ መጠን ቀርበው መሆን እንዳለባቸው ልብ በል። የድምፁ መጠን ከሚቀርበው ትምህርት ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት፤ ሆኖም ከልክ በላይ እንደዚህ ማድረግ አያስፈልግም።

12 የድምፅህ መጠን እንዴት መሆን እንዳለበት ለመወሰን የትምህርቱን ዓይነትና ዓላማህን አንድ በአንድ መርምር። የአድማጮችህን አስተሳሰብ የመለወጥ ዓላማ ካለህ ከመጠን በላይ ጮክ ብለህ በመናገር አታሽሻቸው። ለሥራ ሞቅ ባለ መንፈስ እንዲነሳሱ ለመቀስቀስ ከፈለግህ ግን የድምፅህ ኃይል ምናልባት ከፍ ማለት ሊኖርበት ይችላል። ትምህርቱ ጠንከር ባለ ድምፅ መቅረብ ካለበት በለስላሳ ድምፅ አታዳክመው።

**********

13–16. ቆም ማለት ምን ጥቅም እንዳለው ግለጽ።

13 ንግግር ስታቀርብ በተገቢ ቦታዎች ላይ ቆም እያልክ መናገርህ በቂ ድምፅ የማሰማትን ያህል አስፈላጊ ነው ለማለት ይቻላል። ይህን ካላደረግህ የምትናገራቸው የአንዳንድ ነገሮች ትርጉም በቀላሉ ይሰወራል፤ አድማጮችህ ሊያስታውሷቸው የሚገቡት ዋና ዋና ነጥቦችም በአእምሮ ውስጥ ለዘለቄታው ሳይቀረጹ ይቀራሉ። በየቦታው ቆም ማለትህ ተማምነህና ተረጋግተህ ለመናገር፣ አተነፋፈስህን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠርና በንግግሩ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ትንሽ አረፍ እያልክ ሚዛንህን ለማስተካከል ያስችልሃል። ቆም እያልክ መናገርህ ሁኔታዎች ከቁጥጥርህ ውጭ እንዳልሆኑ፣ የማያስፈልግ ፍርሃት እንዳላስጨነቀህ፣ አድማጮችህን እንዳልረሳሃቸውና እነርሱ ሊሰሙትና ሊያስታውሱት የሚገባ ትምህርት ልታቀርብላቸው እንደምትፈልግ ያሳያቸዋል።

14 ጀማሪ ተናጋሪ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ውጤታማ በሆነ መንገድ ቆም ማለትን መለማመድ አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ ለማቅረብ ያዘጋጀኸው ትምህርት በጣም አስፈላጊ እንደሆነና አድማጮችህ እንዲያስታውሱት እንደምትፈልግ ራስህን ማሳመን ይኖርብሃል። አንዳንድ ጊዜ አንዲት እናት ልጅዋን ለመገሰጽ ስትፈልግ በመጀመሪያ ትኩረቱን ለመሳብ የሆነ ነገር ትናገራለች። ልጅዋ ሙሉ ትኩረቱን ወደ እርሷ እስኪያደርግ ድረስ ሌላ ቃል አትናገርም። ከዚያ በኋላ ያሰበችውን ትናገራለች። ልጁ ቃሏን ቸል እንዳይል፤ ከዚህ ይልቅ በሌላም ጊዜ እንዲያስታውሰው ትፈልጋለች።

15 አንዳንድ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በየዕለቱ ከሰው ጋር ሲያወሩም እንኳ ቆም አይሉም። ይህ ችግር ካለብህ የመስክ አገልግሎትህን ውጤታማነት ለማሻሻል ይህን የንግግር ባሕርይ ለመኰትኰት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። በመስክ አገልግሎት ላይ ስንሆን ንግግራችን የውይይት መልክ ይኖረዋል። የቤቱ ባለቤት ጣልቃ ገብቶ መናገር እንዲጀምር በሚጋብዝ ሳይሆን እንዲያዳምጥህና በትዕግሥት እንዲያስጨርስህ በሚያደርግ ሁኔታ ቆም ለማለት ትክክለኛውን ዘዴ ተጠቅሞ ቆም ማለት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ከሰው ጋር ስንወያይም ይሁን ወደ መድረክ ወጥተን ስንናገር ቆም እያሉ በመናገር በኩል ጥሩ ችሎታንና ብቃትን ማሳየታችን በሁለቱም ሁኔታዎች ላይ አስፈላጊነቱም ሆነ በአጸፋው የሚገኘው አስደሳች ውጤት ያው ነው።

16 ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ በትክክለኛው ቦታ ላይ ቆም ማለትን አዳጋች የሚያደርገው አንዱ ችግር ብዙ ሐሳብ ማዘጋጀት ነው። እጅግ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ባስፈላጊው ቦታ ላይ ቆም ለማለት በቂ ጊዜ ይኑርህ።

17–21. ሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም ማለት የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ግለጽ።

17 ሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም ማለት። ባጭሩ ሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም የምንልበት ዓላማ ሐሳቡን ግልጽ ለማድረግ፣ ተዛማጅ ሐሳቦችን ከሌሎች ለመለየት፣ እንዲሁም ሐረጎችን፣ የዓረፍተ ነገርንና የአንቀጽን መጨረሻ ለማመልከት ነው። ብዙ ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን ለውጦች በድምፅ ወይም በአነጋገር ለውጥ ማመልከት ይቻላል፤ ሆኖም ቆም ማለትም የሥርዓተ ነጥቡን ቦታ በማመልከት በኩል ውጤታማ ነው። ነጠላ ሰረዝና ድርብ ሰረዝ በዓረፍተ ነገር አከፋፈል ላይ የተለያየ ትርጉም እንዳላቸው ሁሉ ቆም ማለትም እንደ አጠቃቀሙ ሁኔታ መለያየት ይኖርበታል።

18 አለቦታው ቆም ማለት የአንድን ዓረፍተ ነገር ትርጉም ፈጽሞ ሊለውጠው ይችላል። በሉቃስ 23:43 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ለዚህ ማስረጃ ይሆኑናል። ኢየሱስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ በገነት ውስጥ ከእኔ ጋር ትሆናለህ” ብሏል። [አዓት] ነጠላ ሰረዙ “እልሃለሁ” እና “ዛሬ” በሚሉት ቃላት መካከል ቢሆን ኖሮ ሐሳቡን ፈጽሞ ይለውጠው ነበር። ለጥቅሱ በብዙዎች ዘንድ የሚሰጠው የተሳሳተ አተረጓጐም ለዚህ ማስረጃ ነው። እንግዲያው ሐሳቡን በትክክል ለማስተላለፍ በተገቢ ስፍራ ላይ ቆም ማለቱ የግድ አስፈላጊ ነው።

19 ጽሑፍ ስታነብ በሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም ማለትን ዘወትር በመለማመድ አስተዋጽኦ ይዘህ በራስህ አገላለጽ ንግግር ስትሰጥ እንዴት ቆም ማለት እንደምትችል ተማር። አንዳንዴ በንባብ ጊዜ ቸል ሊባል የሚችለው ሥርዓተ ነጥብ ነጠላ ሰረዝ ብቻ ነው። ነጠላ ሰረዝ ላይ ቆም ማለቱና አለማለቱ ብዙውን ጊዜ የምርጫ ጉዳይ ነው። ድርብ ሰረዝ፣ አራት ነጥብ፣ ትእምርተ ጥቅስና አዲስ አንቀጽ ግን ሁሉም የግድ ቆም ማለትን ይጠይቃሉ።

20 በንባብ መልክ ለጉባኤው እንድታቀርበው የተዘጋጀ ጽሑፍ ካለ ወይም አንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በንባብ መልክ የምታቀርብ ቢሆን የት ላይ ቆም ማለት እንዳለብህ ጽሑፉ ላይ ምልክት ማድረጉ ሊረዳህ ይችላል። በሐረግና በሐረግ መካከል አጭር ቆምታ የምታደርግባቸውን ስፍራዎች በአንድ ቋሚ መሥመር ምልክት ልታደርግባቸው ትችላለህ። ትንሽ ረዘም ያለ ቆምታ የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ ሁለት ቋሚ መሥመሮችን ወይም “X” ምልክት ልታደርግባቸው ትችላለህ።

21 በሌላው በኩል ግን ልምምድ ስታደርግ አንዳንድ ዓረፍተ ነገሮች ለንባብ አስቸጋሪ በመሆናቸው ደጋግመህ በተሳሳተ ቦታ ላይ የምትቆም ከሆነ በእርሳስ በመጠቀም በአንድ ሐረግ ውስጥ የተካተቱ ቃላትን የሚያጣምር መሥመር ለማድረግ ትችላለህ። ይህን ካደረግህ በኋላ በምታነብበት ጊዜ በእርሳስ አንድ ላይ የተጣመሩት ቃላት እስኪያልቁ ድረስ አትቁም። ልምድ ያላቸው ብዙ ተናጋሪዎች ይህን ያደርጋሉ።

22–24. የሐሳብ ለውጥ ሲደረግ ቆም ማለት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

22 የሐሳብ ለውጥ ለማድረግ ቆም ማለት። ከአንዱ ዋና ነጥብ ወደ ሌላው በምትሻገርበት ጊዜ ቆም ማለትህ አድማጮች ነጥቦቹን ወደኋላ መለስ ብለው እንዲያብላሏቸው አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ከዚህም ሌላ አድማጮች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወስዱ ይረዳቸዋል። አእምሮም ቢሆን ለመሰባሰብ ጊዜ ያገኛል፤ እንዲሁም የአቅጣጫ ለውጡን ለማስተናገድና ቀጥሎ የሚቀርበውን ማብራሪያ መከታተል ይችል ዘንድ ራሱን ለማዘጋጀት አጋጣሚ ይኖረዋል። መኪና የሚነዳ ሰው አቅጣጫ ለመለወጥ ሲል በመጀመሪያ ትንሽ ቆም እንደሚል ሁሉ አንድ ተናጋሪም የሐሳብ ለውጥ ከማድረጉ በፊት ትንሽ ቆም ማለቱ በጣም አስፈላጊ ነው።

23 አስተዋጽኦ ይዞ በራስ አገላለጽ ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ ትምህርቱ በዋና ዋና ነጥቦች መካከል ቆም ለማለት እንደሚያስችል ተደርጎ መዘጋጀት ይኖርበታል። በዚህ ምክንያት ንግግሩ የተቆራረጠ ወይም ወጥነት የጐደለው ይሆናል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሐሳቦቹ አዘገጃጀት አንድን ነጥብ ለማስፋፋትና ለማሳረግ፤ በኋላም ትንሽ ቆም በማለት ወደ ሌላ ሐሳብ ለመሄድ የሚያስችል መሆን ይኖርበታል ማለት ነው። አስፈላጊ ከሆነ ለማስታወስ ያህል እንደነዚህ ያሉትን ማሳረጊያዎችና ለውጦች ምልክት ልታደርግባቸው ትችላለህ።

24 ከሥርዓተ ነጥብ ይልቅ ለሐሳብ ለውጥ የሚደረገው ቆምታ ረዘም ያለ ነው። ይሁን እንጂ ረጅም ቆምታዎች መብዛት የለባቸውም፤ አለዚያ ንግግሩ ይንዛዛል። ከዚህም በላይ ችክ ሊል ይችላል።

25–28. ቆም ማለት አንድን ነጥብ ለማጉላትና ድንገት የሚፈጠሩ ረብሻዎችን ለመቋቋም እንዴት እንደሚጠቅመን አስረዳ።

25 ለማጉላት ቆም ማለት። ለማጉላት በማሰብ የሚደረገው ቆምታ ብዙውን ጊዜ ድንገተኛና ነቃ የሚያደርግ ነው። ምን ሊናገር ይሆን የሚል ጉጉት ይቀሰቅሳል፤ አድማጮች ወደኋላ ተመልሰው በነጥቦቹ ላይ እንዲያስቡም ይረዳል።

26 ከአንድ ትልቅ ነጥብ በፊት ቆም ማለት አድማጮች አንድ ነገር ለመስማት እንዲጓጉ በማድረግ አእምሮአቸውን ያዘጋጀዋል። ከዚያ ነጥብ በኋላ ቆም ማለት ደግሞ ያ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ጠልቆ እንዲገባ ጊዜ ይሰጣል። እነዚህ ሁለት የቆምታ ዘዴዎች አገልግሎታቸው አንድ ዓይነት አይደለም። ስለዚህ የት ቦታ ላይ በየትኛው ዘዴ መጠቀሙ እንደሚሻል ወይም በሁለቱም ዘዴዎች መጠቀም ተስማሚ እንደሆነ አመዛዝነህ መወሰን አለብህ።

27 ለማጉላት ሲባል የሚደረግ ቆምታ ከፍተኛ ትርጉም ላላቸው ነጥቦች ብቻ መወሰን አለበት፤ አለዚያ ቆምታው ዋጋ አይኖረውም።

28 በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቆም ማለት። ንግግሩ እንዲቋረጥ የሚያደርጉ አንዳንድ ሁኔታዎች ብዙውን ጊዜ ተናጋሪው ለትንሽ ጊዜ ቆም እንዲል ያስገድዱታል። ረብሻው ብዙም የጐላ ካልሆነና ድምፅህን ከፍ በማድረግ ልትቋቋመው የምትችል ከሆነም የተሻለ ነው። ነገር ግን የተፈጠረው ረብሻ ንግግሩን ፈጽሞ እስከማቆም የሚያደርስ ከሆነ ቆም ማለት ይኖርብሃል። ስለ አሳቢነትህ አድማጮችህ ደስ ይላቸዋል። ልናገር ብትልም ብዙውን ጊዜ አይሰሙህም፤ ምክንያቱም ጊዜያዊው ረብሻ ሐሳባቸውን ወስዶታል። እንግዲያው አድማጮችህ አንተ ካዘጋጀህላቸው መልካም ነገሮች ሙሉ ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ቆም የማለትን ዘዴ ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቀምበት።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]