ድምፅን ማሻሻልና የድምፅ ማጉያ አጠቃቀም
ጥናት 13
ድምፅን ማሻሻልና የድምፅ ማጉያ አጠቃቀም
1–3. በድምፅ ጥራት ረገድ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ድክመቶች ምንድን ናቸው? የየራሳችንን ድክመት ለመመርመር የሚያስችለን ምንድን ነው?
1 ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ “የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው?” ሲል ሙሴን ጠይቆት ነበር። (ዘጸ. 4:10, 11) እኛም በዚህ ጥያቄ ላይ ሰው እንዲናገር ያስቻሉትን አስደናቂ የሆኑ የሰውነት ክፍሎች በሙሉ የሠራ ማን ነው? የሚል ጥያቄ ልንጨምር እንችላለን። ሙሴ ‘አንደበቱ ኮልታፋና አጥርቶ መናገር የማይችል’ ቢሆንም አምላክ የንግግር ችሎታውን እንዲያሻሽል ሊረዳው እንደሚችልና እንደረዳውም ለማወቅ ችሏል። ነቢዩ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጥሩ ንግግር ለማድረግ ችሏል።
2 ዛሬም የንግግር ድክመት እንዳላቸው የሚገነዘቡ ብዙ የአምላክ አገልጋዮች አሉ። አንዳንዶች ድምፃቸው ደካማ ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ ሰላላ የአንዳንዶቹም ጎርናና ወይም ሸካራ ነው። ስልል ያለ፣ የሚነፋነፍ ወይም ጎርናና ድምፅ መስማት አያስደስትም። ሕያው ያልሆነና ከፍና ዝቅ የማይል ድምፅ ደግሞ የማንንም መንፈስ አያነሳሳም። ድምፅህ ከእነዚህ ድክመቶች አንዱ የሚታይበት ቢሆን አይዞህ፣ ሊሻሻል ወይም ሊስተካከል እንደማይችል ነገር ተቀብለህ ዝም ማለት አይኖርብህም።
3 እርግጥ አንድ ሰው እንዲሻሻል ከተፈለገ ማሻሻል የሚኖርበትን ድክመት አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል። የአገልግሎት ትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ጠቃሚ የሆኑ ምክሮች የሚሰጥበት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጠቃሚ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው። ያለህን የድምፅ ጉድለት ለመመርመርና ለማወቅ ያስችልሃል። በተጨማሪም የራስህን ድምፅ በቴፕ ቀድተህ ብታዳምጥ ጥሩ ይሆናል። እስካሁን ድረስ ድምፅህን ሰምተህ አታውቅ ከነበረ አሁን ስትሰማ በጣም ትደነቃለህ። በምትናገርበት ጊዜ የሚሰማህ በጭንቅላትህ ውስጥ ያሉት አጥንቶች እርግብግቢት ሲሆን ወፈር ያለ ድምፅ ይኖረዋል። የቴፕ መቅጃ የሚያሰማህ ግን ለሌሎች የሚሰማውን የራስህን ድምፅ ነው። ድምፅ ለማሻሻል ስለሚቻልባቸው መንገዶች ለመነጋገር እንዲቻል አስቀድመን ልብ ሳንል የምናወጣው ድምፅ እንዴት እንደሚፈጠር በአጭሩ ብንመለከት ጥሩ ይሆናል።
4–6. ድምፅ የሚፈጠረው እንዴት ነው?
4 ድምፅ እንዴት እንደሚፈጠር። ለማንኛውም ድምፅ መፈጠር ዋነኛ ምክንያት የሚሆነው እንደወናፍ ሆኖ ከሚያገለግለው ሳንባችን የሚወጣው አየር ነው። ይህ አየር በጉሮሮ በኩል አልፎ ማንቁርት ውስጥ ይገባል። ማንቁርት በጉሮሮህ መካከለኛ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ብዙ ጊዜ የድምፅ ሳጥን ተብሎ ይጠራል። በድምፅ ሳጥንህ ውስጥ የድምፅ አውታሮች የሚባሉ ሁለት የተጣጠፉ ትናንሽ ጡንቻዎች አሉ። ዋነኞቹ ድምፅ አመንጪዎች እነዚህ ናቸው። እነዚህ “የድምፅ አውታሮች” በድምፅ ሳጥንህ ግድግዳ ላይ እንደተንቀሳቃሽ መደርደሪያዎች ሆነው ተለጥፈዋል። ዋናው ተግባራቸው አየር ለመውጣትና ለመግባት እንዲችል መከፈትና መዘጋት እንዲሁም ያልተፈለገ ነገር ወደ ሳንባ እንዳይገባ መከላከል ነው። አውታሮቹን የሚያንቀሳቅሳቸው ከሳንባህ የሚወጣው ትንፋሽ ነው። ስለዚህ አየር አልፏቸው ሲሄድ በሚያደርጉት እርግብግቢት ድምፅ ይፈጥራሉ። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ፊኛ ነፍተህ የፊኛውን አንገት ያዝ አድርገህ ትንፋሹ እንዲወጣ ብታደርግ የፊኛው አፍ እየተርገበገበ ድምፅ ይፈጥራል። ስለዚህ በምትናገርበት ጊዜ በማንቁርትህ ውስጥ ያሉት የድምፅ አውታሮች እርስበርሳቸው ይጣበቃሉ። በመካከላቸው የሚገኘው
የV ቅርጽ ያለው ክፍተት ይዘጋል። እነዚህ አውታሮች በጣም ጠብቀው ሲወጠሩ የእርግብግቢታቸው ፍጥነት ስለሚጨምር የሚፈጥሩት ድምፅ ቀጠን ያለ ይሆናል። ረገብ ወይም ዘና ሲሉ ደግሞ የሚፈጥሩት ድምፅ ወፈር ያለ ይሆናል።5 የአየሩ ሞገድ ከማንቁርትህ ከወጣ በኋላ ላንቃ ወደሚባለው ላይኛው የጉሮሮ ክፍል ይገባል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ አፍህና ወደ አፍንጫህ ቀዳዳ ይሄዳል። እዚህም ዋነኛውን የድምፅ ቃና የሚያዳብሩ ቃናዎች ይጨመራሉ። እነዚህ ተጨማሪ የድምፅ ቃናዎች ድምፁን ያሻሽሉታል፣ ጮክ ያደርጉታል ወይም ያጠናክሩታል። ትናጋ፣ ምላስ፣ ጥርስ፣ ድድ፣ መንጋጋና ከንፈር ደግሞ የሚርገበገበውን የድምፅ ሞገድ እየቆራረጡ አናባቢና ተነባቢ ሆሄያትን ይፈጥራሉ። በዚህ መልክ ድምፁ ትርጉም ያለው ንግግር ሆኖ ይወጣል ማለት ነው።
6 በእርግጥም የሰው ድምፅ በጣም አስደናቂ ነገር ነው። በአገልግሎቱ ስፋትና ዓይነት ማንኛውም ዓይነት ሰው ሠራሽ መሣሪያ ሊወዳደረው አይችልም። ከሐዘኔታና ከፍቅር እስከ ቁጣና ጥላቻ የሚለያዩ ስሜቶችን የመግለጽ ችሎታ አለው። የሰው ድምፅ ፍጽምና በጎደለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ በሦስት ደረጃዎች ስምንት ስምንት የተለያዩ ኖታዎችን ማሰማት ይችላል። በተገቢ ሁኔታ ሲሠለጥንና ሲዳብር ደግሞ ውብ የሆኑ የሙዚቃ ዜማዎችን ብቻ ሳይሆን ልብን የሚቀሰቅስ ንግግርም ሊፈጥር ይችላል። ቀጥለን እንደምንመለከተው ሁለት ነገሮች ድምፅን ለማሻሻል ያስፈልጋሉ።
7–10. የትንፋሽን አወጣጥ መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው? ለምንስ?
7 የትንፋሽን አወጣጥ መቆጣጠር። አንድ ተናጋሪ ጥሩ ድምፅ ለማውጣት ከፈለገ ሳንባው ውስጥ በቂ አየር ሊኖረውና አተነፋፈሱን ለመቆጣጠር መቻል ይኖርበታል። ብዙ ሰዎች በሚናገሩበት ጊዜ እንዴት ትንፋሽ ማስወጣትና ማስገባት እንደሚኖርባቸው አያውቁም። በዚህም ምክንያት በላይኛው የሳንባቸው ክፍል ብቻ ስለሚጠቀሙ ፈጠን ብለው በሚናገሩበት ጊዜ ትንፋሽ ያጥራቸዋል። ብዙውን ጊዜ እንደሚታሰበው ትልቁ የሳንባ ክፍል የሚገኘው በላይኛው የደረት ክፍል አይደለም። ይህ ክፍል ትልቅ መስሎ የሚታየው በትከሻህ አጥንት ምክንያት ነው። ትልቅ ስፋት ያለው የሳንባ ክፍል ዳያፍረም ከሚባለው የአካል ክፍል በላይ ያለው ነው። ይህ ዳያፍረም የተባለ ጡንቻ ጠንካራና የደጋን ቅርጽ ያለው ሲሆን እንደወናፍ በማገልገል ሳንባህ ትኩስ አየር እንዲያስገባና የተቃጠለውን አየር እንዲያስወጣ ይረዳዋል። ዳያፍረም ከጎድን አጥንቶች ጋር የተያያዘ ሲሆን ደረትን ከሆድ ዕቃ ይለያል። ትንፋሽ በምናስወጣበትና በምናስገባበት ጊዜ የምንጠቀመው በዚህ የደጋን ቅርጽ ባለው ጡንቻ ነው። ደጋን የሚመስለው የዳያፍረም ቅርጽ ወደላይ በሚገፋበት ጊዜ በሳንባህ ውስጥ የሚገኘውን አየር ወደውጭ ገፍቶ ያወጣዋል። ወደታች በሚወርድበት ጊዜ ደግሞ አየር ወደ ሳንባህ ይገባል።
8 ድምፅህን ለማሻሻል ከምታደርገው ነገሮች የመጀመሪያው
አተነፋፈስህን መቆጣጠርን ማወቅ ነው። ለመናገር አስበህ ወደ ውስጥ በምትተነፍስበት ጊዜ ጠባብ የሆነው ላይኛው የሳንባህ ክፍል እንዳይለጠጥ ለማድረግ ጥረት አድርግ። የሳንባህ ታችኛው ክፍል እንዲለጠጥ አድርግ። ከዚያ በኋላ በሆድ ዕቃ ጡንቻዎች ረዳትነት ዳያፍረምህ መጠነኛ ግፊት ብቻ እያደረገ የተነፈስከው አየር ቀስ በቀስ እንዲወጣ አድርግ። ይህም የተነፈስከው አየር በፍጥነት እንዳያፈተልክ ያስችላል። ተናጋሪው የትንፋሹን አወጣጥ ካልተቆጣጠረ ወዲያው ትንፋሹ ያልቅና ድምፁ የተቆራረጠና የተሰባበረ ይሆናል።9 ብዙዎች የትንፋሻቸውን አወጣጥ ለመቆጣጠር የሚሞክሩት ጉሮሮአቸውን በመወጠር ነው። ይህን ማድረጋቸው ግን ድምፃቸውን ከማዳከምና ከማጎርነን በስተቀር ምንም ፋይዳ አይኖረውም። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይፈጠር የጉሮሮህን ጡንቻዎች ዘና ለማድረግ ሞክር።
10 አንድ ሯጭ ለውድድር ራሱን ማሠልጠን እንደሚኖርበት ሁሉ አንድ ተናጋሪም አተነፋፈሱን በዳያፍረሙ አማካኝነት ለመቆጣጠር ራሱን ማሠልጠን ይኖርበታል። ቀጥ ብሎ ቆሞ ዘለግ ያለ ትንፋሽ ሊስብና ቀስ ብሎ ትንፋሹን እያወጣ በአንድ ትንፋሽ የተቻለውን ያህል ብዙ ፊደላትን ወይም ቁጥሮችን እየጠራ ሊለማመድ ይችላል። ጮክ ብሎ እያነበበም ሊለማመድ ይችላል።
11–15. የጡንቻዎች መወጠር ከድምፅ መቅጠን፣ ከመነፋነፍና ከማልጎምጎም ጋር ዝምድና የሚኖረው በምን መንገድ ነው?
11 የተወጠሩ ጡንቻዎችን ማዝናናት። አብዛኞቹን የድምፅ ችግሮች ለማሸነፍ የሚያስችል ቀላል ዘዴ ራስን ማዝናናት ነው። አንድ ሰው ራሱን እንዴት እንደሚያዝናና ካላወቀ ድምፁን እንዲያሻሽል ለመርዳት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ዘና ስትል በጣም ከፍተኛ የሆነ መሻሻል ልታደርግ ትችላለህ። የአእምሮ መወጠር ጡንቻዎችም እንዲወጠሩ ስለሚያደርግ አእምሮም ሆነ መላው አካል መዝናናት ይኖርበታል። ስለ አድማጮችህ ትክክለኛ የሆነ አመለካከት በመያዝ የአእምሮህን ውጥረት አስወግድ። አብዛኛውን ጊዜ አድማጮችህ የሚሆኑት የይሖዋ ሕዝቦች ናቸው። ወዳጆችህ የሆኑት ሰዎች በረድፍ ስለተቀመጡ ብቻ ጠላቶችህ ይሆናሉን? አይሆኑም። የእኛን አድማጮች የመሰሉ የወዳጅነትና የፍቅር መንፈስ ያላቸው አድማጮች ሊያገኝ የሚችል ሰው በመላው ምድር አይገኝም።
12 በመጀመሪያ ላይ የተለየ ትኩረት አድርገህ ራስህን ማዝናናት ሊኖርብህ ይችላል። መናገር ከመጀመርህ በፊት ፍርሃት ስለተሰማህ ትንፋሽህ እንደተቆራረጠና አጭር እንደሆነ ትገነዘብ ይሆናል። ይህን ሁኔታ ለማስተካከል ሆን ብሎ በረዥሙና በዝግታ በመተንፈስ የጉሮሮህን ጡንቻዎች ማዝናናት ትችላለህ።
13 ቀደም ሲል እንደተማርነው የድምፅ አውታሮች እንዲወጠሩ ማድረግ ድምፃችንን ያቀጥነዋል። ስለዚህ የድምፅ አውታሮችን በወጠርካቸው መጠን ከአንተ የሚወጣው ድምፅ በጣም ጮክ ያለ ይሆናል። ቀጭንና ውጥረት እንዳለብህ የሚያሳይ ድምፅ ስለሚወጣህ አድማጮችህም
ውጥረት ይሰማቸዋል። ይህን ሁኔታ ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል? የድምፅ አውታሮችህ የሚርገበገቡት አልፎአቸው በሚሄደው አየር እንደሆነ ታስታውሳለህ። ከአንድ ክራር የሚወጣ ድምፅ ቃና በክሩ መጥበቅና መላላት እንደሚለዋወጥ ሁሉ የእነዚህም የድምፅ አውታሮች መጥበቅና መላላት ከእነርሱ የሚወጣውን ድምፅ ቃና ይለውጠዋል። የድምፅ አውታሮች ዘና በሚሉበት ወይም በሚረግቡበት ጊዜ ከእነርሱ የሚወጣው ድምፅ ወፈር ያለ ይሆናል። ስለዚህ ማድረግ የሚኖርብህ ነገር የጉሮሮ ጡንቻዎችህን ማዝናናት ነው። በተጨማሪም በውጥረት ምክንያት ምግብ ለመዋጥ የሚያገለግሉት ጡንቻዎች የድምፅ አውታሮችን የሚቆጣጠሩትን ጡንቻዎች ሊቃወሙ ይችላሉ። ይህም ድምፅህን ያሻክረዋል። ልዩ ትኩረት አድርገህ እነዚህን ጡንቻዎች በምታዝናናበት ጊዜ ድምፅህ ይሻሻላል።14 አንዳንድ ጊዜ የጉሮሮና የአፍ ጡንቻዎች ሲወጠሩ የአፍንጫ ቀዳዳ ስለሚዘጋ አየር በአፍንጫ በኩል መተላለፍ ያቅተዋል። ይህም መነፋነፍን ያስከትላል። እንዲህ ያለውንም ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስፈልገው መዝናናት ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በአፍንጫ ቀዳዳ መዘጋት ምክንያት እንዲህ ያለ ችግር ሊያጋጥም ይችላል።
15 በተጨማሪም መንጋጋዎችን ማዝናናት ያስፈልጋል። መንጋጋዎች ውጥረት ካላቸው አፍ በደንብ ሊከፈት ስለማይችል ድምፅ በጥርሶች መካከል ለመውጣት ይገደዳል። በዚህም ምክንያት ግልጽ ያልሆነና የሚልጎመጎም ድምፅ ይሰማል። መንጋጋዎችን ማዝናናት ሲባል ግን በንግግር ልማዳችን ረገድ ንዝህላሎች እንሁን ማለት አይደለም። ቃሎችን አጥርቶ ለመናገር እንዲቻል ከሚፈጠረው ድምፅ ጋር በሚመጣጠን መጠን መቆጣጠር ይኖርብናል ማለት ነው።
16, 17. የድምፅን የማስተጋባት ኃይል እንዴት ማሻሻል ይቻላል? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ጠቅላላውን የጡንቻዎች ውጥረት ማዝናናት ድምፃችን የሚያስተጋባ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል። ግልጽ የሆነ ድምፅ ዘና ካለ ጉሮሮ ከወጣ በኋላ ድምፁ ርቆ ለመሄድ እንዲችል የማስተጋባት ኃይልና ባሕርይ ሊኖረው ያስፈልጋል። ድምፅ የማስተጋባት ባሕርይ የሚኖረው መላው ሰውነት ድምፅ የማውጣትና የመርገብገብ ባሕርይ ሲኖረው ነው። ውጥረት ከኖረው ግን ለመርገብገብና ድምፅ ለማውጣት አይችልም። ከማንቁርት የሚወጣው ድምፅ በአፍንጫ ቀዳዳዎች ብቻ ሳይሆን በደረት አጥንቶች፣ በጥርሶች፣ በላንቃና በአፍንጫ ላይ ያስተጋባል። እነዚህ ሁሉ የአካል ክፍሎች ለድምፁ የማስተጋባት ችሎታ አስተዋጽኦ ለማድረግ ይችላሉ። ድምፅ እንዲጎላ በሚያደርገው በቆዳ በተሸፈነው የመሰንቆ ሣጥን ላይ አንድ ነገር ቢቀመጥ ከመሰንቆው የሚወጣው ድምፅ በጣም ደካማ ይሆናል። ነፃ ሆኖ መርገብገብ ይኖርበታል። በጡንቻዎች የተያያዙት አጥንቶቻችንም ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ድምፅህ የማስተጋባት ችሎታ ካለው አለብዙ ድካምና አለ ብዙ ጭንቀት ለብዙ አድማጮች ማሰማት ትችላለህ። ድምፅህ የማስተጋባት ባሕርይ ከጎደለው
ድምፅህ የተለያየ ቅላጼ እንዲኖረውና የተለያዩ ስሜቶችን እንዲገልጽ ለማድረግ ያስቸግርሃል።17 ድምፅ የማስተጋባት ኃይል የሰውነት ክፍሎችን አዝናንቶ እም . . . የሚል የማያቋርጥ ድምፅ እያወጡ በመለማመድ ሊሻሻል ይችላል። ከንፈር በትንሹ መነካካት አለበት እንጂ ሙሉ በሙሉ መገጠም የለበትም። ከንፈር ጠብቆ ካልተገጠመ የድምፁ እርግብግቢት ጥብቅ በሆኑ ጡንቻዎች አይታፈንም ወይም በአፍንጫ በኩል እንዲወጣ አይገደድም። አንዳንድ ቃላትን መደጋገምና የኘ፣ የመ፣ የነ እና የለ ቤተሰብ የሆኑትን ሆሄያት ድምፆች ረዘም አድርጎ በማውጣት መለማመድ በጣም ጠቃሚ ነው። የድምፅን ጥራት ለማሻሻል ጠቃሚ የሆነ ሌላ ልምምድ ደግሞ አፍ ከፍቶና መንጋጋዎችን ዘና አድርጎ ፊደላትን ጫን ብሎ ማንበብ ነው።
18–22. በድምፅ ማጉያ መሣሪያ በአግባብ በመጠቀም ረገድ የትኛውን ምክር ልብ ማለት ይኖርብናል?
18 በድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች በአግባብ መጠቀም። ትላልቅ በሆኑ የመሰብሰቢያ ቦታዎች የተናጋሪውን ጫና ቀለል ለማድረግና አድማጮች ደስ የሚል ድምፅ እንዲሰሙ ለማስቻል ሲባል የኤሌክትሮኒክ የድምፅ ማጉያ መጠቀም ግድ ይሆናል። የድምፅ ማጉያ ሲኖር ተናጋሪው ድምፁን ከፍ ለማድረግ ብዙ አይደክምም፣ አድማጮችም የሚነገረውን ለማዳመጥ ብለው ጆሮቻቸውን አያስጨንቁም። በብዙ ጉባኤዎች መድረክ ላይ ወጥተው የሚናገሩት ብቻ ሳይሆኑ በአድማጮች መካከል ሆነው ሐሳብ የሚሰጡትም በድምፅ ማጉያ ይጠቀማሉ። የሚሰጡት ሐሳቦች በሙሉ ለሁሉም የሚሰሙ መሆን አለባቸው። በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ስብሰባዎች የድምፅ ማጉያ መሣሪያ ባይኖርም እንኳ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በድምፅ ማጉያ መጠቀም አስፈላጊ ይሆናል። ስለዚህ በድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች እንዴት በአግባብ መጠቀም እንደምንችል ማወቅ ያስፈልገናል።
19 አፍህ ወደ ድምፅ ማጉያው ምን ያህል መቅረብ ይኖርበታል? አብዛኛውን ጊዜ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ሴንቲ ሜትር ራቅ ማለት አለበት። በድምፅ ማጉያ አጠቃቀም ረገድ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው ችግር ተናጋሪው ከድምፅ ማጉያው በጣም መራቁ ነው። ስለዚህ በአፍህና በድምፅ ማጉያው መካከል ያለውን ርቀት በጥንቃቄ ተቆጣጠር። በተጨማሪም ድምፅህ በቀጥታ ወደ ድምፅ ማጉያው እንዲሄድ አድርግ። እንዲህ ካላደረግህ የድምፅ ማጉያ መሣሪያው ተቆጣጣሪ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጎ ጥሩና ግልጽ የሆነ ድምፅ ወደ አድማጮች እንዲደርስ ለማድረግ ይቸገራል። ወደ ድምፅ ማጉያው ተጠግቶ መሳል፣ ማስነጠስ ወይም ጉሮሮ መጥረግ መደረግ የሌለበት ነገር ነው።
20 በድምፅ ማጉያ በምትጠቀምበት ጊዜ ከድምፅ ማጉያው የሚወጣው የራስህ ድምፅ እንዴት ሆኖ እንደሚሰማህ አዳምጥ። የድምፅህን መጠን ካስተዋልክ በኋላ አስፈላጊ ከሆነ ከድምፅ ማጉያው ያለህን ርቀት ለማስተካከል ትችላለህ። ወደ ድምፅ ማጉያው ጠጋ በማለት ወይም ከድምፅ
ማጉያው ትንሽ ራቅ በማለት አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይቻላል። አንዳንድ ተናጋሪዎች ድምፃቸው በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ምክንያት የድምፃቸው ጥራት ከመዛባቱም በላይ አድማጮችን የሚያስቸግርና የሚያስጨንቅ ስለሚሆን ዝቅ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ለንግግርህ ጥሩ ጣዕም ለመስጠት ፈልገህ አልፎ አልፎ ድምፅህን ዝቅ ለማድረግ ብትፈልግ ዘመናዊው የድምፅ ማጉያ መሣሪያ በሹክሹክታ የሚነገረውን እንኳን ሊያሰማ የሚችል መሆኑን አስታውስ።21 በድምፅ ማጉያ አጠቃቀም ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆንበት ሌላ ነገርም አለ። “ፐ” የሚለው ድምፅ ተደጋግሞ የሚሰማበት ጊዜ እንዳለ አስተውለሃልን? ይህ የሚሆነው ተናጋሪው ወደ ድምፅ ማጉያው በጣም ተጠግቶ በሚናገርበት ጊዜ ነው። “ሰ” የሚለው ድምፅም ችግር የሚፈጥርበት ጊዜ አለ። የድምፅ ማጉያው በጣም ከፍ አድርጎ እንደፉጨት ሆኖ እንዲሰማ ስለሚያደርግ እንደዚህ ያለውን ድምፅ በምታሰማበት ጊዜ ላላ ማድረግ ያስፈልጋል። ችግሩን እንዴት እንደምታስወግድ ካወቅህ ለማስወገድ አስቸጋሪ አይሆንብህም።
22 የድምፃችን አወጣጥ በጣም አስደናቂ የሆነ የፈጣሪ ስጦታ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም የመፈልሰፍ ችሎታ ያለው አእምሮአችን የፈጣሪ ስጦታዎች ናቸው። በድምፅ ማጉያ መሣሪያዎች መናገር የተቻለው እነዚህን ስጦታዎች በማግኘታችን ነው። በድምፅ ማጉያም ሆነ አለድምፅ ማጉያ፣ በድምፃችን በምንጠቀምበት ጊዜ ሁሉ የንግግር ፈጣሪ የሆነውን አምላክ በሚያስከብር መንገድ እንጠቀምበት።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]