በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግለትና ፍቅራዊ ስሜት ማሳየት

ግለትና ፍቅራዊ ስሜት ማሳየት

ጥናት 33

ግለትና ፍቅራዊ ስሜት ማሳየት

1. ግለትህን የሚቀሰቅሰው ምንድን ነው?

1 ግለት የንግግር ሕይወት ነው። ስሜትህ በነገሩ ተነክቶ ግለት ካላሳየህ አድማጮችህም እንደማያሳዩ የተረጋገጠ ነው። ትምህርቱ አንተን ካልቀሰቀሰህ እነርሱንም አይቀሰቅስም። ይሁን እንጂ እንደ አንድ ተናጋሪ መጠን እውነተኛ ግለት እንድታሳይ ከተፈለገ ለመናገር ያዘጋጀኸው ሐሳብ ለአድማጮችህ በእርግጥ ያስፈልጋል የሚል ጽኑ እምነት ሊኖርህ ይገባል። ይህም ማለት ዝግጅት በምታደርግበት ጊዜ እነርሱን ግምት ውስጥ አስገብተሃል፤ በጣም የሚጠቅማቸውን ነጥቦች መርጠህላቸዋል፤ እንዲሁም አድማጮችህ የትምህርቱ ዋጋማነት ወዲያው እንዲታያቸው በሚያስችል መንገድ አቀነባብረህላቸዋል ማለት ነው። ይህንን አድርገህ ከሆነ ከልብ ለመናገር ትገፋፋለህ፤ አድማጮችህም ተመሳሳይ ስሜት በማሳየት አጸፋውን ይመልሳሉ።

2–5. ሞቅ ባለ ስሜት የቀረበ ንግግር የግለት መግለጫ የሚሆነው እንዴት ነው?

2 ሞቅ ባለ ስሜት በመናገር ግለትን ማሳየት። ግለትህን ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ግልጽ የሚያደርገው ሞቅ ያለ አነጋገርህ ነው። ቀዝቀዝ ያለ ስሜት ለማሳየት ወይም ፍዝዝ ብለህ ለመናገር አትችልም። ፊትህ፣ የድምፅህ ቃና እና አነጋገርህ ሕያው መሆን አለባቸው። ይህም በሚያነቃቃ ብርቱ ስሜት መናገር አለብህ ማለት ነው። ጭፍን አቋም አክራሪ ሳትመስል የምትናገረውን እንደምታምንበት ሆነህ መናገር አለብህ። በግለት መናገር አለብህ፤ ሆኖም ከመሥመሩ እንዳትወጣ ራስህን መግታት ይኖርብሃል። ራስህን መቆጣጠር ከተሳነህ አድማጮችህን ታጣለህ።

3 ግለት ተላላፊ ነው። ንግግርህን በግለት ብታቀርብ አድማጮችህም ያው ግለት ይጋባባቸዋል። ከአድማጮች ጋር ጥሩ ግንኙነት በማድረግ የእነርሱ ግለት ተመልሶ ወደ አንተ ይንፀባረቅና የራስህን ግለት ሕያው ሆኖ እንዲዘልቅ ያደርገዋል። በሌላው በኩል ግን ስሜትህ ከሞተ የአድማጮችህም ስሜት አብሮ ይሞታል።

4 ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ ብሎናል። አንተም እንደዚሁ ከሆንህ ሞቅ ያለው ንግግርህ የአምላክ መንፈስ በአድማጮች ላይ እንዲፈስ ያደርጋል፤ እርምጃ እንዲወስዱም ያነሳሳቸዋል። አጵሎስ ንግግር በሚሰጥበት ወቅት ይህን የመሰለ መንፈስ አሳይቶአል፤ ጥሩ ተናጋሪ ተብሎም ተጠርቷል። — ሮሜ 12:11፤ ሥራ 18:25፤ ኢዮብ 32:18–20፤ ኤር. 20:9

5 ስለምትሰጠው ንግግር የጋለ ስሜት እንዲያድርብህ ከተፈለገ ሊደመጥ የሚገባ ጥሩ ትምህርት እንዳዘጋጀህ ራስህን ለማሳመን መቻል ይኖርብሃል። የምታቀርበው ትምህርት በመጀመሪያ አንተን ተናጋሪውን ማነቃቃት እንደሚችል አድርገህ በደንብ አዘጋጀው። ትምህርቱ አዲስ ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም አቀራረብህ ወይም ለነገሮች ያለህ አመለካከት አዲስ ሊሆን ይችላል። አድማጮችህን በአምልኮታቸው የሚያጠናክራቸውና የተሻሉ አገልጋዮች ወይም የተሻሉ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ትምህርት እንዳዘጋጀህላቸው ከውስጥ ከተሰማህ ንግግርህን በጋለ ስሜት ለማቅረብ ጥሩ ምክንያት አለህ። ደግሞም በዚሁ መንገድ እንደምታቀርበው አያጠራጥርም።

6–9. በአንድ ንግግር ውስጥ የተካተቱት ሐሳቦች ግለትን ለማሳየት ምን ድርሻ ይኖራቸዋል?

6 ለትምህርቱ የሚስማማ ግለት። ንግግርህ የተለያየ ጣዕም እንዲኖረውና አድማጮችህም እንዲጠቀሙ ንግግሩ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በከፍተኛ የግለት ስሜት መቅረብ የለበትም። አለበለዚያ አድማጮች በንግግሩ ተነክተው እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ይዳከማሉ። ይህም ድምፅህን መለዋወጥ እንድትችል ትምህርቱ ልዩ ልዩ ገጽታዎችን ያካተተ መሆን አለበት የሚለውን ቀደም ብሎ የተሰጠውን ምክር በድጋሚ ያጠናክረዋል። ይህም ማለት ለአድማጮችህ የምታብራራቸው አንዳንድ ሐሳቦች ከሌሎች ነጥቦች በበለጠ ግለት መቅረብ አለባቸው ማለት ነው። ይህም በመሆኑ እንደነዚህ ያሉ ነጥቦች በንግግሩ ውስጥ በየስፍራው በጥሩ ዘዴ ተሰባጥረው መገኘት አለባቸው ማለት ነው።

7 በተለይ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በግለት መቅረብ አለባቸው። በንግግርህ ውስጥ ሲዘረዘሩ የቆዩ ነጥቦችን የምትቋጭባቸው ማሳረጊያዎች መኖር አለባቸው። እነዚህ የንግግርህ ከፍተኛ ነጥቦች በመሆናቸው አድማጮችህን እንዲያነሳሱ፣ የንግግሩን ፍሬ ነገርና ምክንያቶችህን ወይም ምክርህን እንዲያስጨብጡ የታቀዱት እነዚሁ ነጥቦች ይሆናሉ። ቀደም ሲል አድማጮችህን አሳምነሃቸዋል፤ አሁን ደግሞ ቅስቀሳ ማድረግ፤ እንዲሁም ንግግሩ ያስገነዘባቸው መደምደሚያዎች የሚያስገኙዋቸውን ጥቅሞች፤ አድማጮች ንግግሩን ከሰሙ በኋላ የተቀበሏቸውን ወይም ያመኑባቸውን ነገሮች ቢከታተሉ ይህ የሚያመጣላቸውን ልዩ ልዩ ደስታና መብት ሕያው አድርገህ ማሳየት ያስፈልግሃል። ይህም የጋለ አነጋገርን ይጠይቃል።

8 እንደዚህም ሲባል በሌሎች ጊዜያት ስሜትህ ቀዝቀዝ ይበል ማለት አይደለም። ስላዘጋጀኸው ርዕሰ ጉዳይ ከውስጥ የሚሰማህ ግለት ፈጽሞ መቀነስ የለበትም። ምንም ዓይነት የስሜት መቀዝቀዝ ማሳየት የለብህም። ገለል ባለ ስፍራ ላይ ሣር በመብላት ላይ ያለች ሚዳቋን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ምንም እንኳን የተዝናናች መስላ ብትታይም ትንሽ አደጋ ስታይ ተስፈንጥራ ሩጫ ለመጀመርና በከፍተኛ ዝላይ እየተወረወረች ለማምለጥ የሚያስችል ብርቱ ኃይል በቀጫጭኖቹ እግሮቿ ውስጥ ተቀምጧል። ተዝናንታ ብትበላም ሁልጊዜ ንቁ ናት። አንተም ሁልጊዜ በሙሉ ግለት ባትናገርም ልክ እንደ ሚዳቋዋ ለመሆን ትችላለህ።

9 ታዲያ ይህ ሁሉ ምን ማለት ነው? ግለት በግድ፣ ራስን አስጨንቆ የሚመጣ ነገር አይደለም ማለት ነው። ግለት ከውስጥ ፈንቅሎ እንዲወጣ የሚያደርገው ቆስቋሽ ነገር መኖር አለበት። ይህ ቆስቋሽ ነገር አንተ ያዘጋጀኸው ትምህርት መሆን ይኖርበታል። ግለትህ ለትምህርቱ የሚስማማ መሆን አለመሆኑን ምክር ሰጪህ ይከታተላል። በዝቷል? ወይስ አንሷል? ወይስ አለቦታው ነበር? እርግጥ የግል የተፈጥሮ ባሕርይህን ግምት ውስጥ ያስገባል። ዓይነ አፋር ወይም ዝምተኛ ከሆንህ በዚህ በኩል እንድታሻሽል ያበረታታሃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስሜትህ በትንሽ ነገር ሰማይ የሚደርስ ከሆነ ስለ አደጋው ያስጠነቅቅሃል። እንግዲያው ግለትህ ለትምህርቱ የሚስማማ ይሁን፤ እንደዚሁም የትምህርቱ አዘገጃጀት በንግግሩ ወቅት አለፍ አለፍ እያልህ በግለት ለመናገር የሚያስችል መሆን ይኖርበታል።

**********

10–12. ፍቅራዊ ስሜት ሲባል ምን ማለት ነው?

10 ግለት ከፍቅራዊ ስሜት ጋር የቅርብ ተዛማጅነት አለው። ለነዚህ ባሕርያት መነሻ የሚሆኑት ስሜቶች የተለያዩ ናቸው። በሰው ላይ የሚያመጡትም ለውጥ የተለያየ ነው። ተናጋሪ ሆነህ በሰው ፊት ስትቀርብ ብዙ ጊዜ ግለት የሚሰማህ በትምህርቱ ምክንያት ነው፤ ፍቅራዊ ስሜት የሚያድርብህ ግን ከአድማጮችህ አንፃር ይኸውም እነርሱን የመርዳት ምኞት ሲያድርብህ ነው። በንግግር ምክር መስጫ ቅጽ ላይ የሰፈረው “ፍቅራዊ ስሜት” የሚለው የንግግር ባሕርይ በጥንቃቄ ሊታሰብበት የሚገባ ነው።

11 ፍቅራዊ ስሜት ካለህ አድማጮችህ ፍቅር፣ ደግነትና ርኅራኄ የምታሳይ ሰው እንደሆንህ ይሰማቸዋል። በብርድ ምሽት እሳት ለመሞቅ ሰው እንደሚሰበሰብ ሁሉ አድማጮችህም ወደ አንተ ይሳባሉ። የጋለ አነጋገር ቀስቃሽ ነው፤ ሆኖም የርኅራኄ ስሜትም ያስፈልጋል። አእምሮን ማሳመኑ ሁልጊዜ በቂ አይሆንም፤ ልብንም ጭምር መገፋፋት አለብህ።

12 ለምሳሌ ያህል ከገላትያ 5:22, 23 ስለ ፍቅር፣ ስለ ትዕግሥት፣ ስለ ደግነትና ስለ የዋህነት በምታነብበት ጊዜ እነዚያን ጠባዮች በአነባበብህ ሁኔታ ሳታንጸባርቅ ብታነብ ተስማሚ ወይም ተገቢ ይሆናልን? በተጨማሪም በ1 ተሰሎንቄ 2:7, 8 ላይ ያሉትን የጳውሎስን የርኅራኄ ቃላት ልብ በል። እነዚህ ቃላት በፍቅራዊ ስሜት ማንበብን የሚጠይቁ ናቸው። ታዲያ ይህን ባሕርይ እንዴት ማሳየት ይገባሃል?

13, 14. ፍቅራዊ ስሜት ፊት ላይ ሊነበብ የሚችለው እንዴት ነው?

13 ፍቅራዊ ስሜት ፊት ላይ ይነበባል። በውስጥህ ለአድማጮችህ ፍቅራዊ አመለካከት ካለህ ፊትህ ላይ መታየት አለበት። ይህ ካልሆነ ግን አድማጮችህ በውስጡ ለእኛ ፍቅራዊ ስሜት አለው ብሎ ማመኑ ሊያዳግታቸው ይችላል። ሆኖም ለአድማጮችህ ያለህ ፍቅራዊ ስሜት ልባዊ መሆን ይኖርበታል። ከላይ እንደ ሽፋን አድርገህ ልትለብሰው አትችልም። በሌላው በኩል ግን ፍቅራዊ ስሜት ሲባል ልበ ቡቡ መሆን ወይም ቅጥ የሌለው ስሜታዊ መሆን ማለት እንደሆነ አድርገን በማሰብ እንዳንሳሳት መጠንቀቅ አለብን። ፊት ላይ የሚነበብ የደግነት ስሜት ልባዊነትንና ቅንነትን ያሳያል።

14 አብዛኛውን ጊዜ ንግግር የምታቀርበው ወዳጃዊ ስሜት ለሚያሳዩ አድማጮች ነው። ስለሆነም አድማጮችህን በምትመለከታቸው ጊዜ ስለ እነርሱ ፍቅራዊ ስሜት ይሰማሃል። ትዝናናለህ፣ ለወዳጆችህ እየተናገርህ እንዳለህም ይሰማሃል። ከአድማጮችህ መካከል ወዳጃዊ ፊት የሚያሳይ አንድ ሰው ምረጥ። ለጥቂት ጊዜያት እሱን እየተመለከትህ ተናገር። ከዚያም ሌላ ምረጥና አሁንም በዚያው መንገድ ለእርሱ ተናገር። ይህ ከአድማጮች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርህ ከመርዳቱም በላይ ከአድማጮችህ ጋር ያቀራርብሃል። ለአድማጮችህ የምታሳየው ብሩህ ፊትም አድማጮችህን ወደ አንተ ይስባቸዋል።

15–19. የአንድን ተናጋሪ ድምፅ ፍቅራዊ ስሜትን እንዲያንጸባርቅ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ግለጽ።

15 ፍቅራዊ ስሜትን በድምፅ ቃና ማሳየት። እንስሳትም እንኳን በድምፅ ቃና ሰውዬው በውስጡ ምን ስሜት እንዳለው ሊገባቸው እንደሚችል በደንብ የተረጋገጠ ሐቅ ነው። እንግዲያው አድማጮች ፍቅራዊ ስሜትን በሚያንፀባርቅ የድምፅ ቃና የቱን ያህል ይሳባሉ!

16 ልብህ ከአድማጮችህ ጋር ካልሆነ፤ ማለትም አድማጮችህ ለንግግርህ ስለሚሰጡት ምላሽ ሳይሆን ስለምትናገራቸው ቃላት በይበልጥ የምታስብ ከሆነ ይህን ሁኔታ ንቁ ከሆኑ አድማጮች መሰወር ያስቸግራል። ለምትናገራቸው ሰዎች ልባዊ ስሜት ካለህና ልክ አንተ እንደምታስበው አድርገው ማሰብ ይችሉ ዘንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ወደ እነርሱ ለማስተላለፍ አጥብቀህ የምትመኝ ከሆነ ግን ይህ ስሜትህ በድምፅህ ቃና ይንጸባረቃል።

17 ሆኖም ይህ ከልብ የመነጨ ስሜት መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። የይምሰል ግለት ማሳየት እንደማንችል ሁሉ እውነተኛ የሆነ ፍቅራዊ ስሜትም ማስመሰያ ሊሆን አይችልም። ተናጋሪው በግብዝነት ወለላ ቃላት የሚናገር እንዳይመስል መጠንቀቅ አለበት። በተጨማሪም ፍቅራዊ ስሜት ከደካማ ስሜታዊነት ወይም አልባሌው ስሜታዊ ሰው ከሚያሳየው ቅልስልስነት ጋር ሊማታብን አይገባም።

18 ኃይለኛ ወይም ሸካራ ድምፅ ካለህ በአነጋገርህ ፍቅራዊ ስሜትን ማሳየት ሊያስቸግርህ ይችላል። ማንኛውንም እንዲህ ያለ ችግር ለማስወገድ በንቃትና በትጋት መጣር ይኖርብሃል። ችግሩ ያለው ድምፅህ ላይ ስለሆነ ይህን ለማሻሻል ጊዜ ያስፈልጋል። ሆኖም በተገቢ ትኩረትና ጥረት ድምፅህን በማሻሻል ፍቅራዊ ስሜት እንዲያስተላልፍ ልታደርገው ትችላለህ።

19 ፈጠን ፈጠን እያሉ መናገር ወይም ቃላትን መዋጥ ንግግርን ከባድ እንደሚያደርጉት ማስታወስ ያስፈልጋል። ስለዚህ ቃላትን ሳብ እያደረግህ መናገርን ተማር። ይህም እነዚያን ቃላት ለስለስ ያደርጋቸዋል። የድምፅህ ቃናም ሞቅ ያለ ስሜት የሚያስተላልፍ ይሆናል።

20, 21. በንግግሩ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች ፍቅራዊ ስሜትን ለማሳየት የሚረዱት እንዴት ነው?

20 ለትምህርቱ የሚስማማ ፍቅራዊ ስሜት። እንደ ግለት ሁሉ በንግግርህ ላይ ፍቅራዊ ስሜትን ማሳየትህ በአብዛኛው በምትናገረው ሐሳብ ላይ የተመካ ነው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን እንዳወገዘ የሚገልጸው በማቴዎስ 23 ላይ የሚገኘው ዘገባ ነው። ኢየሱስ እነዚህን ኃይለኛ የውግዘት ቃላት ቅዝቅዝ ባለ ስሜት አቅርቧቸዋል የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮአችን አይመጣም። ሆኖም በዚህ የቁጣ አነጋገር መካከል ጣልቃ የገባ ፍቅራዊ ስሜትን የተሞላ የኢየሱስን ርኅራኄ የሚያንፀባርቅ ቃል አለ። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።” እዚህ ላይ የርኅራኄ ስሜት በግልጽ ይታያል። ሆኖም ቀጥሎ ያለውን አባባል ተመልከተው:- “እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።” ይህ አባባል ከላይ ከተገለጸው ጋር አንድ ዓይነት ስሜት አያስተላልፍም። ያለመቀበልን ወይም የመጥላትን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው።

21 ታዲያ ፍቅራዊ ስሜት ትክክለኛ ቦታው የት ላይ ነው? በመስክ አገልግሎት ላይ ወይም በተማሪ ንግግርህ ላይ የምትናገራቸው አብዛኞቹ ነገሮች ይህንን ለመግለጽ አጋጣሚ ይከፍታሉ። ሆኖም አንድን ሰው ለማሳመን ስታነጋግር፣ ስታበረታታ፣ ስትመክር፣ ሐዘኔታን ስትገልጽና በመሳሰሉት ጊዜያት እነዚህን ስሜቶች ማሳየት ትችላለህ። ፍቅራዊ ስሜት ማሳየትን መዘንጋት የለብህም፤ ሆኖም ተስማሚ ሆኖ ስታገኘው ግለትንም ማሳየት እንዳለብህ አስታውስ። በሁሉም ነገሮች ሚዛናዊ ሁን። ይሁን እንጂ የምትናገረውን ነገር ሁሉ እስከተቻለ ድረስ ከሙሉ ስሜቱ ጋር ግለጸው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]