ጥሩ አዳማጭ ሁን
ጥናት 5
ጥሩ አዳማጭ ሁን
1–5. ማዳመጥ ማለት ምን ማለት ነው? በተለይ በጉባኤ ስብሰባዎች ማዳመጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 የይሖዋ አገልጋይ በመሆንህ የምታሳየው እድገት የተመካው በአብዛኛው ጥሩ አዳማጭ በመሆንህ ላይ ነው። በሕይወት ዘመንህ በሙሉ ማዳመጥ ትምህርት በማግኘት ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው። የሚነገረውን ነገር ምሳሌ 1:5 እንደሚለው “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል።”
በትኩረት የምትሰማ ከሆነ በማዳመጥ ላይ ነህ ማለት ነው። በሚነገረው ነገር ላይ ትኩረት ካላደረግክ ግን ቃሎቹ የሚወድቁት በደነቆረ ጆሮ ላይ ይሆናል። በከፊል ብቻ ከሚያዳምጡህ ሰዎች ጋር ተነጋግረህ እንደምታውቅ የታወቀ ነው። የቱንም ያህል ጊዜ በተናገርከው እንደተስማሙ ቢገልጹም ቁምነገሩን እንዳልተረዱና ከምትናገረው ነገር ምንም ዓይነት ጥቅም እንዳላገኙ ታውቃለህ። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ፣ በተለይ ደግሞ መለኮታዊ ትምህርት በምንከታተልበት ጊዜ ጥሩ አዳማጮች ለመሆን በጣም መጠንቀቅ አይኖርብንምን?2 የጉባኤ ስብሰባዎች በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት የሚዘጋጅልን የትምህርት ፕሮግራም ክፍል ናቸው። በትኩረት በማዳመጥ ለይሖዋና እርሱ እኛን ለማስተማር ላደረገው ዝግጅት አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። ይሁን እንጂ አምላክ አፈጣጠራችንን ስለሚያውቅና አንዳንድ ጊዜ ትኩረታችን ሊበታተንብን እንደሚችል ስለሚገነዘብ ከመንፈሣዊ ማዕዱ እንድንመገብ ሲጋብዘን “በጥሞና አዳምጡኝ፣ ጥሩውንም ብሉ። . . . ጆሮአችሁን ወደ እኔ አዘንብሉና ወደ እኔ ኑ። አድምጡኝ፣ ነፍሳችሁም በሕይወት ትኖራለች” በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ኢሳ. 55:2, 3 አዓት) የዘላለም ሕይወት ለማግኘትና ሌሎች ሰዎችም የዘላለም ሕይወትን ሽልማት እንዲያገኙ ለመርዳት ከፈለግን በጥሞና ማዳመጥና የአምላክን ሐሳብ መረዳት ያስፈልገናል። — ዕብ. 1:1, 2፤ 2:1
3 በተጨማሪም በትኩረትና በጥሞና ማዳመጥ ትሕትና እንዳለን ያሳያል። ማናችንም ብንሆን ትሑቶች የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን። ማናችንም ብንሆን ከሌላው ሰው የምናገኘው ትምህርት ይኖራል። ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ሰው ፈጽሞ የለም። ተናጋሪው የአነጋገር ቅልጥፍና ቢጎድለው ወይም ጥሩ ችሎታ ያለው ተናጋሪ ባይሆንም እንኳ ልባዊ የሆነ የትሕትና ባሕርይ ከኖረን የሚናገረውን ነገር በትኩረት በማዳመጥና በንግግሩ መነካታችንን በማሳየት ልንረዳውና ልናበረታታው ይገባል። ምናልባትም ከዚህ በፊት ያላስተዋልነውን ሐሳብ ወይም ነጥብ ይጠቅስ ይሆናል። ይሖዋ በመንፈሣዊ አነጋገር ሕፃናት ከሆኑት አፍ ትምህርት እንዲፈልቅ ሊያደርግ ይችላል። — ማቴ. 11:25
4 በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በትኩረት ማዳመጥ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በስብሰባዎቹ ላይ የምንማራቸው ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ በተግባር ልናውላቸው የሚገቡትን ነገሮች ነው። አዲሱን ሰው ለመልበስ የምንችለው “ትክክለኛ እውቀት” ስናገኝ ብቻ ነው። (ቆላ. 3:9, 10 አዓት) በጥንቃቄ ካላዳመጥንና ለዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት ካልሰጠን ግን በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ለመገንዘብ ስለማንችል መንፈሣዊ ዕድገታችን ሊገታ ይችላል። በተጨማሪም የቃል ወይም የጽሑፍ ክለሳዎች በሚደረጉበት ጊዜ ትክክለኛውን መልስ ለመስጠት መቻል አስፈላጊ ነው። ከዚህ ይበልጥ ግን በመስክ አገልግሎታችን ላይ ስለ ታላቁ ተስፋችን ምክንያት ለሚጠይቁን ሁሉ ተገቢ መልስ ለመስጠት መቻላችን እንዴት በጣም አስፈላጊ ነው!
5 የሚነገሩትን ነገሮች በትኩረት የማዳመጥን ልማድ ስትኮተኩት የምታዳምጣቸውን ነገሮች የማስታወስ ችሎታህ ይዳብራል።
6–8. ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ ሐሳብህ እንዳይባዝን ለማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
6 እንዴት ማዳመጥ ይቻላል? በስብሰባዎች ጊዜ ትኩረታችን በሌሎች ነገሮች በቀላሉ ሊወሰድብን ይችላል። ሐሳባችን በሙሉ በቀኑ ባጋጠመን ሁኔታ ወይም ነገ ልንሠራ ባሰብነው ጉዳይ ሊዋጥ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የሚነገረውን ነገር በትኩረት የማያዳምጥ ከሆነ ስብሰባው ቦታ ላይ መቀመጡ ምን ትርጉም አለው? ስለዚህ ማንም ቢሆን ራሱን መገሰጽና ሐሳቡ ወደፈለገበት እንዳይሄድ ልጓም ማበጀት ያስፈልገዋል። አእምሮ ወደፈለገበት እንዳይባዝንና በጊዜው የሚደረገውን ውይይት በጥሞና እንዲያዳምጥ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋል። በጊዜው ውይይት ለሚደረግበት ጉዳይ ባዕድ የሆኑትን ጉዳዮች በሙሉ በአእምሮ መጋረጃ መዝጋት ይገባል። ሐሳብን መሰብሰብ የሚባለውም ይህ ነው።
7 ሐሳብህ እንዳይበታተን ወይም ትኩረትህ እንዳይወሰድ የሚረዳ ጥሩ ዘዴ ተናጋሪው የጠቀሳቸውን ነጥቦችና ጥቅሶች በማስታወሻ ላይ መጻፍ ነው። የምትጽፈው ማስታወሻ የተንዛዛ ከሆነ ሐሳብህን መሰብሰብ ስለሚያስቸግርህ አጠር ያለ ማስታወሻ ያዝ። ይህ ማስታወሻ በሌላ ጊዜ ሊጠቅምህ ይችል ይሆናል። ወደፊት የማትጠቀምበት ቢሆንም እንኳ ሐሳብህ በሙሉ በሚነገረው ነገር ላይ እንዲያተኩር ይረዳሃል። ውይይት የሚደረግበትን ርዕሰ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ስለምትከታተል ተናጋሪው ያቀረባቸውን ነጥቦችና ምክንያቶች ለይተህ ለማመልከት ትችላለህ።
8 ከሰው ጋር በምትነጋገርበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች እያቀረበ ቢከታተልህ በደንብ እያዳመጠህ መሆኑን ያሳያል። በተመሳሳይም አንድ ንግግር በምታዳምጥበት ጊዜ አእምሮህ ገንቢ የሆኑ ጥያቄዎችን እየጠየቀ መልሱን ለማግኘት የሚጠባበቅ ከሆነ በትኩረት የምታዳምጥ መሆንህን የሚያመለክት ጥሩ ማስረጃ ነው። ከሚመጡልህ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የቀረበውን ትምህርት እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ? የሚል ሊሆን ይችላል።
9. አንድን ንግግር በምናዳምጥበት ጊዜ የማሰብ ፍጥነታችንን በጥሩ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
9 የአንድ ሰው የማሰብ ፍጥነት ከተናጋሪው የመናገር ፍጥነት ስለሚበልጥ ውጪያዊ የሆኑ ሐሳቦች ወደ አእምሮ ለመግባት በቂ ጊዜ ሊያገኙ ይችላሉ። አማካዩ የማሰብ ፍጥነት 400 ቃላት በደቂቃ ሊደርስ እንደሚችል ሲገመት አማካዩ የመናገር ፍጥነት ግን በደቂቃ 125 ቃላት ያህል ነው። ይሁን እንጂ የሚሰጠውን ትምህርት ፍሬ ነገር በሐሳባችን ጠቅለል አድርገን ለማየት ብንሞክርና ብንከልስ አእምሮ ያለውን ይህን የማሰብ ፍጥነት ለጥቅማችን ልናውለው እንችላለን። በዚህም መንገድ ትምህርቱ በአእምሮአችን ውስጥ ጠልቆ ይቀረጻል።
10, 11. ጥሩ የልብ ዝንባሌ ጥሩ አዳማጭ ለመሆን ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
10 ተናጋሪው የሚጠቅሳቸውን ጠቃሚ ነጥቦች ለመያዝ የሚያስችለን ሌላው ጠቃሚ ዘዴ ደግሞ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ይዞ ማዳመጥ ነው። የምናዳምጥበት ዓላማ የተናጋሪውን አቀራረብና ትምህርት ለመተቸት ወይም ለማረም አይደለም። የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሆነ እርማት የመስጠት ኃላፊነት ያለበት የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ነው። ስለዚህ ሌሎቻችን ተናጋሪው በሚናገራቸው ጠቃሚ ሐሳቦች ላይ ልናተኩር እንችላለን።
11 የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ለተማሪ ተናጋሪዎች እርማት በሚሰጥበት ጊዜም ሌላው ተማሪ ከተሰጠው እርማት ጋር ይስማማና አይስማማ እንደሆነ ማሰቡ ምንም ጥቅም ሊያስገኝለት አይችልም። እርሱን የሚጠቅመው የተሰጠው ምክር እርሱንም የሚመለከተው እንደሆነና እንዳልሆነ ማሰብና ከተሰጠው ምክር ምን ዓይነት ጥቅም ሊያገኝ እንደሚችል ማሰላሰል ነው። ይህን ካደረገ ራሱ ንግግር እንዲሰጥ በሚመደብበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በስብሰባው ላይ ከሚቀርበው ከእያንዳንዱ ንግግር እድገትና መሻሻል እንዲያገኝ የሚያስችለው ሐሳብ ለማግኘት ይችላል።
12. ልጆች ጥሩ አዳማጭ መሆንን ሊማሩ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
12 ወጣቶችና ትናንሽ ልጆችም በትኩረት እንዲያዳምጡ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል። ወላጆቻቸው ሊመለከቱአቸው በሚችሉበት ቦታ ቢቀመጡ ጥሩ ነው። ማንበብ የሚችሉ ከሆነ የራሳቸው የሆነ የሚጠናው ጽሑፍ ቅጂ ቢኖራቸው ይበረታታሉ። በአጠቃላይ አነጋገር ከፕሮግራሙ ጋር ዝምድና በሌላቸው ነገሮች እንዲጠመዱ ማድረግ ጥበብ አይደለም። እቤታቸው ሲመለሱ ያዳመጡአቸውን ነገሮች መልሰው እንዲናገሩ እንደሚጠየቁ ቢነገራቸው በትኩረት እንዲያዳምጡ ሊገፋፉ ይችላሉ። በስብሰባው ላይ የተነገሩትን ነገሮች አስታውሰው ከተናገሩ ምሥጋና ሊሰጣቸው ይገባል። — ዘዳ. 31:12
13, 14. የአመጋገብ ልማዳችን የማዳመጥ ችሎታችንን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
13 ከስብሰባ በፊት ከበድ ያለ ምግብ መብላት እንቅልፍ ስለሚያስመጣ ሐሳብን ሰብሰብ አድርጎ መከታተል አስቸጋሪ ይሆናል። ይህም የሚሆነው የሰውነታችን ኃይል በሙሉ የበላነውን ምግብ በመፍጨትና በማዋሃድ ላይ ስለሚውልና የማሰብ ችሎታን የሚያንቀሳቅስ በቂ ኃይል ስለማይኖር ነው። የአእምሮ ሐሳብ የመቀበል ችሎታ በዚህ መንገድ ሲደነዝዝ አድማጩ በቂ ንቃት ሳይኖረው ፍዝዝ ብሎ ያዳምጣል ወይም እንቅልፍ እንቅልፍ ይለዋል።
14 ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ዘወትር በስብሰባዎች ላይ ተገኝተህ የሚቀርቡትን ፕሮግራሞች ለማዳመጥ እንድትችል ጉዳዮችህን ማስተካከልህ ነው። በብዙ ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች ከክፍል ይቀሩና የተሰጠውን ትምህርት ብቻቸውን ለመከለስ ሙከራ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ ትምህርቱ ሲሰጥ ራስህ ካልሰማኸው ከትምህርቱ በቂ ጥቅም ለማግኘት አትችልም። ቤተሰቦችህ ወይም ወዳጆችህ ከስብሰባ ሊያስቀሩህ አይገባም። ከአምላክ ቃል የሚቀርቡትን
እውነቶች ለማዳመጥ ሕይወትን ለማቆም በሚያስችል አዘውታሪነት በስብሰባዎች ተገኝ።15, 16. በስብሰባዎች ላይ የማዳመጥ ችሎታችንን እንዴት ልንፈትንና ልናሻሽል እንደምንችል ግለጽ።
15 የማዳመጥ ችሎታህን መፈተን። በየሳምንቱ አምስት ሰዓት የሚያክል ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች እናሳልፋለን። በዚህ ጊዜ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው በማዳመጥና በመማር ነው። ከዚህ ጊዜ የተቻለውን ብዙ ጥቅም ለማግኘት ትጥራለህን? በየሳምንቱ በሚቀርቡት የሕዝብ ንግግሮች ላይ ከሚሰጡት ነጥቦች ስንቶቹን ታስታውሳለህ? በቲኦክራሲያዊው የአገልግሎት ትምህርት ቤት ወይም በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ከተገኘህ በኋላ የእያንዳንዱን ንግግር ዋና ዋና ሐሳቦች በራስህ አነጋገር ልትገልጽ ትችላለህ ወይስ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በፕሮግራሙ ላይ የተካፈሉት እነማን እንደነበሩ እንኳን ማስታወስ ያቅትሃል? ሐሳብህን ሰብሰብ አድርገህ በትኩረት ለማዳመጥ የበለጠ ጥረት በማድረግና ምናልባትም ማስታወሻ በመያዝ የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ትችል ይሆንን? ሞክረው። ከስብሰባው በኋላም ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ከሌሎች ጋር በመወያየት ከልስ።
16 በብዙዎቹ ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ ጥያቄዎች እየተጠየቁ አድማጮች ሐሳብ እንዲሰጡባቸው ይጋበዛሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጡት ሐሳቦች ብዙ ሰዓት በፈጀ የግል ጥናት ወይም በብዙ ዓመታት ተሞክሮ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሌሎች ሐሳብ በሚሰጡበት ጊዜ የሚናገሩትን ከልብህ ታዳምጣለህን? ተናግረው ከጨረሱ በኋላ የተናገሩትን ሐሳብ በራስህ አነጋገር ባጭሩ ደግመህ ለመናገር እስከሚያስችልህ ድረስ በጥሞና ታዳምጣለህን? እንዲህ ለማድረግ ሞክር። ምን ያህል ብዙ ነገሮችን ለማዳመጥ እንደምትችል ስትገነዘብ በጣም ትደነቃለህ።
17. አንቀጾች በሚነበቡበት ጊዜ በትኩረት እንድናዳምጥ የሚረዳን ምንድን ነው?
17 በተጨማሪም በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ብዙ ነገሮች ይነበባሉ። በመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በመጽሐፍ ጥናት ላይ የሚጠኑት ጽሑፎች አንቀጽ በአንቀጽ ይነበባሉ። የሚነበበውን ነገር በጥሞና ታዳምጣለህ ወይስ ሐሳብህ ወደ ሌላ ነገር እንዲሄድ ትፈቅዳለህ? በሚነበቡት አንቀጾች ውስጥ በቃል ቢዘረዘሩ በቂ ጊዜ የማይገኝላቸው በጣም ብዙ ትምህርቶች ይገኛሉ። ከንባቡ በኋላ ሐሳብ በሚሰጡ ወንድሞች ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በድጋሚ መጠቀሳቸው በአእምሮአችን ውስጥ እንዲቀረጹ ያደርጋቸዋል። በስብሰባዎች ላይ የሚነበቡትን ሁሉ ስናዳምጥ ብዙ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። ዓይንህ በጽሑፉ ላይ እንዲያተኩር ብታደርግና ብታዳምጥ በትኩረት ለመስማት ትችላለህ።
18–20. በጉጉት የሚያዳምጡ ሰዎች ለጥረታቸው ጥሩ ዋጋ የሚያገኙት እንዴት ነው?
18 በጉጉት የሚያዳምጡ ሁሉ ተገቢ ዋጋ ያገኛሉ። በጉጉት የሚያዳምጡ ሁሉ መማር የሚኖርባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይገነዘባሉ። የተቻላቸውን ያህል ብዙ ትምህርት ለማግኘትም ይጓጓሉ። የምሳሌ 2:3, 4ን ምክር ይከተላሉ። ‘ረቂቅ እውቀትን ጥራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን አንሳ፣ እርስዋንም እንደ ብር ፈልጋት።’ ይህንንም ሲያደርጉ ይሖዋ ይባርካቸዋል፤ ምክንያቱም የሚከተለውን ቃል ገብቶላቸዋል:- “የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ። የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።” — ምሳሌ 2:5, 9
19 ጥሩ አዳማጮች ለመሆን ከፈለግን ራሳችንን መገሠጽ እንደሚያስፈልገን አይካድም። ይሁን እንጂ በአጸፋው የሚገኘው ጥቅም እንዴት ብዙ ነው! መንፈሣዊ ዕድገታችን ግልጽ ሆኖ መታየት ይጀምራል። በሕይወታችን ውስጥ ጠቃሚ ለውጦች እናደርጋለን። ምሥራቹን ከመድረክም ሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ ለሌሎች የማሳወቅ ችሎታችንም ይሻሻላል።
20 በግል ጥናት የምናሳልፈው ጊዜ በጣም አነስተኛ ሊሆን ይችላል። በጉባኤ ስብሰባዎች ግን ብዙ ለማዳመጥ እንችላለን። ስለዚህ የአደማመጣችን ሁኔታ ጥሩ እንዲሆን በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ነው። የምናዳምጣቸው ነገሮች ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎትና የዘላለም ሕይወታችንን የሚነኩ ስለሆኑ ኢየሱስ ‘እንዴት እንደምታዳምጡ ተጠበቁ’ ሲል የሰጠው ምክር እንዴት ትክክለኛ ነው! — ሉቃስ 8:18
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]