በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥቅሶችን ማንበብና ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ

ጥቅሶችን ማንበብና ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ

ጥናት 25

ጥቅሶችን ማንበብና ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ

1–3. ንግግር ስንሰጥ ጥቅሶችን እንዴት አድርገን ማንበብ ይኖርብናል?

1 በግል በሚደረግ ውይይትም ይሁን በመድረክ ላይ ቆመህ በብዙ ሰዎች ፊት ስለ አምላክ ዓላማዎች በምትናገርበት ጊዜ የምትሰጠው ማብራሪያ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያወጣህ በምታነባቸው ጥቅሶች ላይ ያተኮረ ነው። ስለሆነም እነዚያ ጥቅሶች በደንብ መነበብ ይኖርባቸዋል። እንደ ነገሩ መነበብ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ጥቅስ የማንበብህ ዓላማ ግቡን እንዲመታ ከተፈለገ አነባበብህ የምታቀርበውን ትምህርት ይበልጥ ቀስቃሽ ሊያደርገው ይገባል። በዚህ ምክንያት የንግግር ምክር መስጫው ቅጽ ጥሩ ችሎታ ያለው የወንጌል አገልጋይ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውን “ጥቅስ ሲነበብ ተፈላጊዎቹን ቃላት ማጉላት” የሚለውን ነጥብ በዝርዝሩ ውስጥ ጨምሯል።

2 ጥቅሶች በስሜት መነበብ ይኖርባቸዋል፤ ይሁን እንጂ ከመጠን በላይ እንደዚያ ማድረግ አያስፈልግም። ጥቅሱን ምን ያህል ማጉላት እንደሚያስፈልግ የሚወስነው የጥቅሱ ዓይነትና በንግግሩ ውስጥ ጥቅሱ ያለው አገባብ ነው። ጥቅሱ እያብራራህ ላለኸው ነጥብ መቋጫ መሆን አለበት። ትኩረት መሳብ ያለበት የአነባበቡ ሁኔታ መሆን የለበትም።

3 ከዚህም በላይ ንባብህ ለነጥቡ ድጋፍ በሚሆኑት የጥቅሱ ክፍሎች ላይ የሚያተኩር መሆን ይኖርበታል። አነባበብህ ነጥቡን በማስጨበጥ አድማጮችን ማሳመን ይኖርበታል። በዚህ መንገድ የጥቅሶችን ተፈላጊ ቃላት እያጎሉ ማንበብ መተማመንን ያሳድራል። ለንባቡም ኃይል ይሰጠዋል።

4, 5. “ትክክለኛ ቃላትን ማጉላት” ሲባል ምን ማለት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

4 ትክክለኛ ቃላትን ማጉላት። ምን መጥበቅ እንዳለበት የሚወስነው ጥቅሱ የተነበበት ምክንያት ነው። በጥቅሱ ውስጥ ያለው ሐሳብ ሁሉ እኩል ከጠበቀ ጎላ ብሎ የሚታይ ምንም ነገር አይኖርም። ስለዚህ ለማስረዳት ያሰብከው ነጥብ ተድበስብሶ ይቀራል። እንግዲያው በዋነኛነት መጉላት ያለባቸው ጥቅሱ የተጠቀሰበትን ዓላማ ግልጽ የሚያደርጉት ቃላት መሆን ይኖርባቸዋል።

5 ለምሳሌ ያህል ኃጢአት ወደ ዘላለማዊ ሥቃይ ሳይሆን ወደ ሞት የሚመራ መሆኑን ለማስረዳት በሕዝቅኤል 18:4 ብትጠቀም ጥቅሱን በሚከተለው መንገድ ታነበዋለህ:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” ጋደል ባሉ ፊደላት የተጻፈውን ቃል ለየት አድርገህ ታጠብቃለህ። ነገር ግን የሚሞተው አካሉ ብቻ ሳይሆን ነፍሱም ጭምር እንደሆነ ለማስረዳት ብትፈልግ የምታጠብቅበትን ቦታ ትቀይራለህ። እንደሚከተለው በማለት ታነባለህ:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።” የቱን ማጉላት እንዳለብህ የሚወስነው ጥቅሱን የጠቀስክበት ምክንያት ወይም ዓላማ ነው።

6–12. በአንድ ጥቅስ ውስጥ የምንፈልገውን ሐሳብ የያዙትን ቃላት ልናጎላ የምንችለው በምን መንገድ ነው?

6 ውጤታማ በሆነ የማጉላት ዘዴ መጠቀም። ጎላ ብለው እንዲታዩ የምትፈልጋቸውን ቃላት በተለያዩ መንገዶች ማጉላት ይቻላል። የምትጠቀምበት ዘዴ ግን ከጥቅሱና ጥቅሱ በንግግሩ ውስጥ ካለው አገባብ ጋር የሚጣጣም መሆን ይኖርበታል።

7 “ጥቅስ ሲነበብ ተፈላጊዎቹን ቃላት ማጉላት” ስለሚለው የንግግር ባሕርይ የቀረበው ይህ ማብራሪያ በንግግር ጊዜ መጠቀም የምንችልባቸውን ለማጉላት የሚያስችሉ ዘዴዎች በሙሉ ለመዘርዘር የታቀደ አይደለም። “ማጥበቅ” በሚለው የንግግር ባሕርይ ላይ ስትደርስ እነዚህ ዘዴዎች በተሟላ መልኩ ተዘርዝረው ታገኛቸዋለህ። ሆኖም ጥቅሶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማንበብ ይረዱህ ዘንድ ጥቂት ዘዴዎች እዚህ ላይ ቀርበዋል።

8 በድምፅ ነጥቡን ማጉላት። ይህ ዘዴ ሐሳቡን ግልጽ የሚያደርጉት ቃላት ከቀረው ዓረፍተ ነገር ጎላ ብለው እንዲታዩ የሚያደርግ በድምፅ ላይ የሚደረገውን ማንኛውንም ለውጥ፤ ይኸውም የድምፁን ቃና፣ ፍጥነት ወይም ኃይል መለዋወጥን ይመለከታል።

9 ቆም ማለት። ተፈላጊ ከሆነው የጥቅሱ ክፍል በፊት ወይም በኋላ አለዚያም በሁለቱም ቦታዎች ላይ በዚህ ዘዴ መጠቀም ይቻላል። ልክ ዋናው ሐሳብ ላይ ስትደርስ ቆም ማለትህ አእምሮ ያንን ሐሳብ ለመቀበል እንዲሰናዳ ያደርገዋል። ከሐሳቡ በኋላ ቆም ማለትህ ሐሳቡ አእምሮን ሰርስሮ እንዲገባ ያደርጋል።

10 መደጋገም። አንድ ልዩ ነጥብ ላይ ስትደርስ ንባብህን በመግታት ያንን ቃል ወይም ሐረግ ደግመህ በማንበብ ጐላ ልታደርገው ትችላለህ። ይህንን ዘዴ መጠቀም የሚገባው ሳይበዛ ነው።

11 የሰውነት እንቅስቃሴዎች። የሰውነት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ፊት ላይ የሚነበብ ስሜት ብዙውን ጊዜ አንድ ቃል ወይም ሐረግ ከሌላው ለየት ብሎ እንዲታይ ሊያደርጉ ይችላሉ።

12 የድምፅ ቃና። አንዳንድ ጊዜ ቃላት ሲነበቡ የሚሰማው ቃና ትርጉሙን ሊለውጠውና እነዚያን ቃላት ከሌሎች ለየት ሊያደርጋቸው ይችላል። እዚህም ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤ በተለይም ምጸት አዘል ቃላትን ስናነብ።

13, 14. ጥቅሱን ባለቤቱ ካነበበው ተፈላጊ የሆኑትን ቃላት እንዴት አድርገን ልናጎላ እንችላለን?

13 ባለቤቱ የሚያነባቸው ጥቅሶች። ጥቅሱን ባለቤቱ በሚያነብበት ጊዜ መጥበቅ የሌለባቸውን ቃላት ጎላ አድርጎ ሊያነብ ወይም የትኛውንም ቃል ሳያጎላ ሊያነብ ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ለማድረግ ትችላለህ? ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲያጋጥም ጥቅሱን ከነጥቡ ጋር በምታያይዝበት ጊዜ የተፈለገውን ቃል ማጉላቱ አብዛኛውን ጊዜ የተሻለ ነው። ጥቅሱ ተነቦ ሲያልቅ ተፈላጊዎቹን ቃላት በመድገም ወይም ጥያቄዎች በመጠየቅ ባለቤቱ በእነዚያ ቃላት ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ትችላለህ።

14 ሌላም ነገር ማድረግ ይቻላል። ይሁን እንጂ ይኸኛው ዘዴ ጥንቃቄና ጥበብ ይጠይቃል። ባለቤቱ እያነበበ ሳለ ተፈላጊው ነጥብ ላይ ሲደርስ ይቅርታ ጠይቀህ ልታቋርጠውና እንዲጐላ በፈለግከው ቃል ወይም ሐረግ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ትችላለህ። እንደዚህ ማድረግህ ሰውዬውን የማያሳፍረው ወይም የማያስቆጣው ከሆነ ይህ ዘዴ በጣም ውጤታማ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሳይበዛ ሊሠራበት ይገባል።

**********

15–17. ጥቅሱ ከጉዳዩ ጋር እንዴት እንደሚገናዘብ ግልጽ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ጥቅስ ሲነበብ ተፈላጊዎቹን ቃላት ማጉላትህ ብቻውን ዓላማህን ለማሳካት በቂ አይሆንም። እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ጥቅሱ ራሱ ለማስረዳት የፈለግከውን ነጥብ በቀጥታ ያስቀምጥ ይሆናል። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ሐሳቡን የያዙትን ቃላት ትኩረት እንዲደረግባቸው ማድረግና ለማስረዳት ከፈለግከው ነጥብ ጋር ማያያዝ ያስፈልግሃል። የንግግር ምክር መስጫው ቅጽ “ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ማገናዘብ” ሲል ስለዚህ ጉዳይ መናገሩ ነው። ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ትውውቅ እንደሌላቸው አስታውስ። በዚህም ምክንያት ጥቅሱን ስላነበብክላቸው ብቻ ነጥቡን ማግኘት አይችሉም። ተፈላጊ የሆኑትን ቃላት በድጋሚ ማንበብና ከተፈለገው ነጥብ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ ማብራራቱ ሐሳቡ በአእምሮአቸው ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ያደርጋል።

16 አንድን ጥቅስ ከጉዳዩ ጋር ለማገናዘብ የምትችለው ለጉዳዩ የሚስማማ ከሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም በትክክል እንድታስተዋውቀው ያስፈልጋል። ከዚያም ዋናው ዓላማህ ማስተማር መሆኑን በማስታወስ የጥቅሱን ሐሳብ በተቻለህ መጠን ቀለል አድርገህ መግለጽ አለብህ።

17 ከዚህም በተጨማሪ አንተ ራስህ ጥቅሱ ግልጽ ሆኖ እንዲገባህ ያስፈልጋል። ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ለማገናዘብ የምትሰጠው ማብራሪያም ትክክለኛ መሆን ይኖርበታል። አስፈላጊ ከሆነ ከጥቅሱ ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች፣ በጥቅሱ ውስጥ የተገለጹትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ወይም ሰዎች እየጠቀስክ ልታብራራ ትችላለህ። የትኛውንም ጥቅስ ቢሆን ጸሐፊው በአእምሮው ይዞት ከነበረው ዓላማ ውጭ ፈጽሞ አትጠቀምበት። ጥቅሱ ለነጥቡ እንዴት እንደሚሠራ ስታብራራ የማኅበሩን ጽሑፎች በጥንቃቄ ተከተል።

18. ከጉዳዩ ጋር ለማያያዝ የምንፈልጋቸውን የጥቅሱን ቁልፍ ቃላት ውጤት ባለው መንገድ ልናጎላቸው የምንችለው እንዴት ነው?

18 ለማያያዝ የምትጠቀምባቸውን የጥቅሱን ቃላት መለየት። አንድን ጥቅስ ከጉዳዩ ጋር ለማያያዝ ማብራሪያ ከመስጠትህ በፊት ወይም በመስጠት ላይ እያለህ ተፈላጊዎቹን ቃላት በድጋሚ ጠቅሰህ ማጉላትህ ብዙውን ጊዜ አስፈላጊ ነው። ይህ የሚደረግበት ምክንያት ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው በጥቅሱ ውስጥ ያሉት ሌሎች ሐሳቦች ደብዘዝ እንዲሉ ወይም ሁለተኛ ደረጃ እንዲይዙ ለማድረግ ነው። በአጠቃላይ ለዚህ የምንጠቀምበት ዘዴ እንዲጠብቁ የተፈለጉትን ቃላት በድጋሚ መናገር ቢሆንም ሁልጊዜ እንደዚያ ማድረጉ አስፈላጊ አይደለም። ከሌሎች ቃላት ለየት ያደረግካቸውን ከጉዳዩ ጋር የሚገናዘቡ ቃላት አንዳንድ ጊዜ በሌሎችም ዘዴዎች በደንብ እንዲተኰርባቸው ለማድረግ ትችላለህ። አንደኛው ዘዴ ያንኑ ሐሳብ በሌሎች ተመሳሳይ ቃላት ደግሞ መናገር ነው። ሌላው ዘዴ ደግሞ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው። ትምህርቱን የምታቀርበው ለአንድ ባለቤት ከሆነ ተፈላጊዎቹን ሐሳቦች ሰውዬው በድጋሚ እንዲናገራቸው የሚያደርግ ጥያቄ ለማዘጋጀት ትችላለህ።

19–22. “ጥቅሱን ስታስተዋውቅ የጠቀስካቸውን ነገሮች አለመርሳት” ሲባል ምን በማድረግ መደምደምን መዘንጋት የለብንም ማለት ነው?

19 ጥቅሱን ስታስተዋውቅ የጠቀስካቸውን ነገሮች አለመርሳት። በቀላል አነጋገር ይህ ማለት ጥቅሱን የጠቀስክበትን ዓላማ አድማጭህ በግልጽ እንዲገባው ማድረግ አለብህ ማለት ነው። በሆነ ምክንያት ጥቅሱን በቅድሚያ ማስተዋወቁ አስፈላጊ ወይም የተሻለ ሆኖ አላገኘኸው ይሆናል። ቢሆንም የጥቅሱን ሐሳብ ከተፈለገው ነጥብ ጋር ማገናዘብ አያስፈልግም ማለት አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ጥቅሱን ከማንበብህ በፊት ለማስረዳት ስለፈለግከው ነጥብ አድማጮችህን በትንሹም ቢሆን በቅድሚያ ማዘጋጀትህ አይቀርም። አሁን ደግሞ ጥቅሱን በጥሩ ሁኔታ ለመደምደም ከፊተኛው ሐሳብ ጋር ማገናዘብ አለብህ።

20 ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ለማገናዘብ ምን ያህል ማብራሪያ መስጠት እንዳለብህ የሚወስነው የአድማጮችህ ሁኔታና ያ ነጥብ ከአጠቃላዩ ትምህርት አንጻር ሲታይ የሚኖረው ክብደት ነው። አብዛኛውን ጊዜ ጥቅሱን ተንትኖ ማብራራቱ ብቻ አይበቃም። በጥቅሱ ውስጥ ያሉትን እንዲጐሉ የተደረጉትን ሐሳቦች ጥቅሱን ስታስተዋውቅ ካቀረብከው ነጥብ ጋር ማገናዘብ ይኖርብሃል። ጥቅሱንና ነጥቡን የሚያገናኛቸው ድልድይ ምን እንደሆነ ግልጽ ማድረግ አለብህ።

21 ግብህን ማሳካት እስከቻልክ ድረስ ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር በቀላል መንገድ ብታያይዝ የተሻለ ነው። ማብራሪያህ ምንም ግንኙነት ከሌላቸው ዝርዝር ጉዳዮች ነፃ መሆን አለበት። ይህን ለማድረግ የምትችለው ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች በተቻለ መጠን ጥቂት በማድረግና ከዚያም እነርሱን ግልጽ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ቁም ነገሮችን ብቻ በመጨመር ነው። በጥቅሱ ማስተዋወቂያ ላይ ተጠቅሶ ገና መልስ ያላገኘ ጉዳይ ካለ ጥቅሱን ከጉዳዩ ጋር ለማገናዘብ የምትሰጠው ገለጻ መልሱን ማስቀመጥ ይኖርበታል።

22 በንግግር ማሰልጠኛ ፕሮግራም ውስጥ በዚህ የዕድገት ደረጃ ላይ ስትደርስ ቀላልና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማስረዳትን ግብህ ማድረግ ይኖርብሃል። እዚህ ግብ ላይ ከደረስክ ጥቅስ አንብበህ በርሱ ላይ የምትሰጠው ገለጻ ጥሩ የማስተማር ጥበብ ያለው ሰው የሚኖረውን ዓይነት ችሎታ የሚያሳይ ይሆናል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]