በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥናት ብዙ ጥቅም ያስገኛል

ጥናት ብዙ ጥቅም ያስገኛል

ጥናት 7

ጥናት ብዙ ጥቅም ያስገኛል

1. ጥናት ለምን ነገር ያዘጋጀናል?

1 እምነትህ ሲያድግ ለአምላክ ያለህ ፍቅር እየጠነከረ ሲሄድ፣ የማስተዋል ችሎታህ ሲዳብርና ከአገልግሎትህ የምታገኘው ደስታና ፍሬ ሲጨምር ለማየት ትፈልጋለህን? በእነዚህ መስኮች ሁሉ የምታደርገው እድገት በአብዛኛው የተመካው በግልና በቤተሰብ ጥናትህ ላይ ነው። የግልና የቤተሰብ ጥናት ሊቀር የማይችል የክርስቲያናዊ ሕይወታችን ክፍል ነው። በአሁኑ ጊዜ አምላክን ለማገልገል የሚያስፈልገንን ብቃት የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ በአምላክ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለምናገኘው ሕይወት ከምናደርጋቸው ዝግጅቶች አንዱ ክፍል ነው። የሚገባህን ያህል ታጠናለህን? — ማቴ. 4:4

2, 3. ለጥናት የሚሆን ጊዜ እንዴት ለማግኘት ይቻላል?

2 ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው ችግር ለጥናት የሚያስፈልገውን በቂ ጊዜ ማግኘት ነው። ሆኖም ችግሩ መፍትሔ የሌለው አይደለም። የጥናት ፕሮግራምህ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ከተገነዘብህ በሳምንቱ ውስጥ የምትሠራቸውን ነገሮች አንድ በአንድ መርምር። ምንም ነገር የማታደርግበት ብዙ ነፃ ጊዜ አታገኝ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጉዳዮች ላይ ‘ጊዜ እንድንዋጅ’ ይመክረናል። (ኤፌ. 5:15–17) ቴሌቪዥን ካለህ በሳምንቱ ውስጥ ቴሌቪዥን በመመልከት የምታሳልፈው ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ለምን አትመዘግብም? ምን ያህል ብዙ ጊዜ በዚያ ላይ እንደምታሳልፍ ስትገነዘብ በጣም ትደነቅ ይሆናል። “ተራ ወሬ” በስልክ በማውራት፣ ጎረቤቶችን በመጠየቅ፣ ዓለማዊ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን በማንበብ ምን ያህል ጊዜ ታባክናለህ? በዚህ መንገድ ከምታሳልፈው ጊዜ ከፊሉን ዘላቂ ጥቅም ለሚያስገኝልህ ጥናት ልትጠቀምበት ትችላለህን? ይህን ዓይነቱን ጥናት በቀኑ ጊዜ ውስጥ፣ ማታ ላይ ወይም አመቺ በሆነልህ በማንኛውም ሰዓት ማድረግ ትችላለህ። ማንኛውም ሰው አብዛኛውን ጊዜ በጣም ለሚያስፈልገው ነገር ጊዜ ማግኘት አያስቸግረውም። ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ውድ አድርጎ ለሚመለከት ሰው ደግሞ የአምላክን ቃል ከማጥናት የበለጠ ‘አስፈላጊ ነገር’ ሊኖር አይችልም። — ፊልጵ. 1:9–11፤ ምሳሌ 2:1–5

3 በመጀመሪያ ጊዜ ሐሳብህን ሰብሰብ አድርገህ በጥናትህ ላይ ማተኮር አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን ቀላልና አስደሳች ይሆንልሃል። ይሁን እንጂ የአምላክን ቃል ማጥናት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ፣ የማይቋረጥ ጥናት የምታደርግበትን ጊዜ መወሰንና ልባዊ ጥረት ማድረግ ያስፈልግሃል።

4, 5. ጥናት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? ጥናቱን በጸሎት መጀመር ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?

4 ጥናት የሚደረግበት ዓላማ የተጠናውን ትምህርት በሌላ ጊዜ ለማስታወስና ለሌሎች ሰዎች በግልጽ ለማስረዳት መሆን ይኖርበታል። የተለየ ትኩረት ሳናደርግ ላይ ላዩን የምናነብበት ጊዜ ሊኖር ቢችልም ላይ ላዩን ማንበብ ጥናት ነው ሊባል አይችልም። ጥናት ልዩ ልዩ ጽሑፍ እየተመለከቱ ምርምር ማድረግን፣ በጥልቅ ማሰብንና የተጠናው ትምህርት እንዴት በሥራ ላይ እንደሚውል ማሰላሰልን ይጠይቃል። በተገቢ ሁኔታ አጥንተህ ልትጨርስ ከምትችለው በላይ ብዙ ገጽ ለመሸፈን አትሞክር። እንዲህ ብታደርግ ጥናትህ ጥልቀት የሌለውና ጥቅም የማያስገኝልህ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን እየተመለከትህ ምርምር ለማድረግና ለማሰላሰል በቂ ጊዜ መድብ። ቢሆንም ከጥናትህ ውጤት በማግኘት ላይ መሆንህን ለመገንዘብ እንድትችል በቂ መጠን ያለው ትምህርት ለመሸፈን እቅድ አውጣ።

5 አንድ ክርስቲያን ተማሪ የአምላክን እውቀት ጥልቅ ነገሮች ለመረዳት በራሱ ችሎታ አይመካም። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ፣ የአምላክ ውስን አገልጋዮች ድርጅትና የአምላክ ቃል እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያውቃል። ጥናት በሚደረግበት ጊዜ የአምላክን በረከት በጸሎት መጠየቅ ተገቢ የሚሆነውም በዚህ ምክንያት ነው። — ያዕ. 1:5፤ ሉቃስ 11:9–13

6, 7. ከቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ተፈላጊውን ጥቅም ለማግኘት የትኞቹን ጠቃሚ ሐሳቦች መሞከር ይቻላል?

6 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም ላይ በየሣምንቱ የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይመደባል። አብዛኛውን ጊዜ መላው ቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው በየምሽቱ አንድ ወይም ሁለት ምዕራፍ በማንበብ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሊሸፍኑት ይችላሉ። ከዚህ ንባብ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት እያንዳንዱ አንቀጽ ከተነበበ በኋላ አንቀጹን ያነበበው ሰው ወይም ከቤተሰቡ መካከል አንዱ በአንቀጹ ቁልፍ ነጥብ ላይ ሐሳብ ቢሰጥ ጥሩ ይሆናል። ብቻህን ለራስህ የምታነብ ከሆነም ጥቂት ጊዜ ወስደህ በተገለጸው ሐሳብ ላይ አሰላስል። አንቀጹ ከቀረው የምዕራፉ ክፍል ጋር እንዴት እንደሚስማማና አንተን በግልህ እንዴት እንደሚነካህ አስብ።

7 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ከጨረስክ በኋላ ግልጽ ያልሆኑልህ ነጥቦች ካሉ ተጨማሪ ጊዜ ወስደህ በሌሎች ጽሑፎች ላይ ምርምር ብታደርግ ጥሩ ይሆናል። የአንድ የተለየ ጥቅስ ሐሳብ ወይም ስሜት ግልጽ አልሆነልህ ይሆናል። ስለዚያ ጥቅስ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ጥቅሱ የተብራራበትን ጽሑፍ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ውስጥ የሚገኘውን የጥቅሶች ማውጫ ለመመልከት ትችላለህ። ጥያቄህ እንደ “ቅድስና” ወይም እንደ “ታላቂቱ ባቢሎን” ያሉትን የተለዩ ቃላት ወይም አነጋገሮች የሚመለከት ከሆነ በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ውስጥ የሚገኘውን የርዕሰ ጉዳዮች ማውጫ አውጥተህ ማየት ትችላለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሰ ሰው ወይም ቦታ በይበልጥ ለማወቅ በምትፈልግበት ጊዜም ቢሆን ይህንኑ የመሰለ ዘዴ ልትጠቀም ትችላለህ። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው መጽሐፍ ላይ ወይም በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስህ በስተጀርባ የሚገኘውን የጥቅስ ማውጫ አውጥተህ የተዘረዘሩትን ጥቅሶች በማየት ብቻ ስለ ሰዎችና ቦታዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትችላለህ።

8, 9. ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች እንዴት መልስ ለማግኘት ይቻላል? ከመልሶቹ በተጨማሪ ምን ነገር ለማግኘት መጣር ይኖርብናል?

8 መልስ ለማግኘት በልዩ ልዩ ጽሑፎች ላይ ምርምር ማድረግ። ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወይም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምትመራበት ጊዜ መልሱን በእርግጠኝነት የማታውቀው ጥያቄ ሊያጋጥምህ ይችላል። በጥናትህ ጊዜ እንደነዚህ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ከልዩ ልዩ ጽሑፎች ምርምር ለማድረግ ትችላለህ። በቂ ጥናት አድርገህ መልስ ስትሰጥ ‘የእውነትን ቃል እንደሚገባ ስለመያዝህ’ እርግጠኛ ለመሆን ትችላለህ። (2 ጢሞ. 2:15) መጠነኛ ጥረት ካደረግህ አብዛኛውን ጊዜ አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ትችላለህ። የምትፈልገው ስለ አንድ ጥቅስ የሚያብራራ ሐሳብ ለማግኘት ከሆነ በጥቅሱ አካባቢ ያሉትን ሐሳቦች አንብብ። ከጥቅሱ ላይና ታች ያለው ሐሳብ የሚያብራራው ስለ ምን ነገር ነው? በዚህስ መሠረት አሁን ውይይት የሚደረግበት ጥቅስ ሐሳብ ምንድን ነው? ይህን ካረጋገጥክ በኋላ ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ላይ የጥቅስ ማውጫ የሚለውን ክፍል አውጥተህ ለመመልከት ትችላለህ። ጥያቄው መሠረተ ትምህርት ወይም ትንቢትን የሚመለከት ነው ወይስ ተማሪው በሕይወቱ ውስጥ ሊሠራበት የሚያስፈልገውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓት የሚመለከት? በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ውስጥ የሚገኙት የርዕሰ ጉዳዮችና የጥቅሶች ማውጫ ክፍሎች የሚያስፈልግህን መረጃ ለማግኘት ይረዱሃል።

9 የምትፈልገውን መልስ እንዳገኘህ እርግጠኛ ስትሆን ለመልሱ ምን ማስረጃ አግኝቼአለሁ ብለህ ራስህን ጠይቅ። መልሱ ለምትነግረው ሰው በቂ በሆነ ማስረጃ ላይ ያልተመሠረተና ቀኖናዊ ሐሳብ መስሎ ይታያልን? ወይስ በማኅበሩ ጽሑፎች ላይ ለቀረቡት መደምደሚያዎች የተሰጡት ምክንያቶች ይታዩሃልን? የቀረበው ማስረጃ ግልጽ ሆኖልሃልን? እውነት መሆኑን በተጨባጭ መንገድ ለማስረዳት ትችላለህን? የምታነጋግረው ሰው እንደዚያ ብለህ ለመደምደም ያበቁህን ምክንያቶች እንድታቀርብ ወይም የጥቅስ ድጋፍ እንድትሰጠው ሊጠይቅህ ይችላል። ፍሬ ሐሳቡን በምሳሌ ለማስረዳት ትችላለህን? ተማሪው ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ የሚረዱህን መሪ ጥያቄዎች አስበህ አዘጋጅተሃልን? በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያደረግኸው ጥናት መልሱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ይረዳሃል።

10, 11. ለመጠበቂያ ግንብ ጥናትና ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እንዴት መዘጋጀት እንደሚቻል ሐሳብ ስጥ።

10 “ለመጠበቂያ ግንብ” ጥናት መዘጋጀት። በአንዳንድ አገሮች የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ተቃውሞ ስለሚደርስበት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ዘወትር አይገኝም። እንደነዚህ ባሉት አገሮች ወንድሞች ቀደም ብለው ያጠኗቸውን መጽሔቶች ይከልሳሉ ወይም በአእምሮአቸው የሚያስታውሱትን ይወያያሉ። በቅርቡ ያጠናኸውን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ዋና ዋና ነጥቦች ታስታውሳለህን? በምናጠናበት ጊዜ ዓላማችን የተማርነውን እውቀት በሌላ ጊዜ አስታውሰን በግል ሕይወታችን ወይም በመስክ አገልግሎታችን ለመጠቀም መሆን ይኖርበታል።

11 መጽሔቱ እንደደረሰን ወዲያውኑ ከዳር እስከ ዳር አንብበን ብንጨርሰው ጥሩ ይሆናል። በዚህ መንገድ ስለ ጽሑፉ አጠቃላይ የሆነ እውቀት ይኖረናል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጽሑፉ በጉባኤ ላይ ከመጠናቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት በግላችን እንከልሰዋለን ወይም ከቤተሰባችን ጋር እንወያይበታለን። በዚህ ጊዜ መጀመሪያ የርዕሰ ትምህርቱን አርዕስት፣ ትምህርቱ የተመሠረተበትን ጥቅስና ደመቅ ብለው የተጻፉትን ሁሉንም ንዑስ አርዕስት ልብ በል። ይህም ስለ ትምህርቱ አጠቃላይ የሆነ ሐሳብ እንድታገኝና በእያንዳንዱ አንቀጽ ውስጥ የሰፈረው ዝርዝር ሐሳብ ከዋናው ርዕሰ ጉዳይ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለመገንዘብ ይረዳሃል። አሁን መላውን ትምህርት አንቀጽ በአንቀጽ አንብብ። በዚህ ጊዜ የጥያቄዎቹን መልሶች እየፈለግህ አግኝ፤ ቁልፍ ነጥቦቹን በሌላ ጊዜ እንድትመለከታቸው አስምርባቸው። አንዱን አንቀጽ አንብበህ ከጨረስክ በኋላ የጥያቄውን መልስ በራስህ ቃላት ለመናገር ካልቻልክ አንቀጹን ደጋግመህ አንብብ። ለተሰጡት መልሶች የቀረቡትን የጥቅስ ማስረጃዎች ልብ በል። ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጻፉትን ጥቅሶች አውጥተህ ተመልከት። በስብሰባው ላይ ሐሳብ ልትሰጥበት የምትፈልገውን ጥቅስ ምልክት አድርግበት። በአንድ ንዑስ ርዕስ ሥር የሰፈሩትን አንቀጾች በሙሉ ስትጨርስ ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለህ ያጠናኸው ክፍል አጠቃላዩን ርዕሰ ጉዳይ በማብራራት ረገድ ምን ድርሻ እንዳበረከተ አሰላስል። ሙሉውን ርዕሰ ትምህርት ስትጨርስም እንዲሁ አድርግ። የተማርከውን እውቀት የት ልትሠራበት እንደምትችል፣ የግል ሕይወትህን እንዴት እንደሚነካው፣ እንዴት ለሌላ ሰው ልታስረዳ እንደምትችል አሰላስል። እንዲህ ካደረግህ መልሶችን ብቻ ምልክት ከማድረግ አልፈህ ጥበብና ማስተዋል ለማግኘት ትችላለህ። (ምሳሌ 4:7) በጉባኤ ስብሰባ ላይ ከሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናትም ብዙ ደስታ ታገኛለህ። ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናትም በተመሳሳይ መንገድ መዘጋጀት ይቻላል።

12–14. የቤተሰብ ጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዴት ያሉ ጽሑፎችስ ሊጠኑ ይችላሉ?

12 የቤተሰብ ጥናት። ከሁሉም በላይ ለጥናት የምታወጣው ዝግጅት የቤተሰብህን አባሎች በሙሉ የሚያቅፍ መሆን ይኖርበታል። ይህ ከተደረገ እያንዳንዳቸው የተሟላ ጥቅም ያገኛሉ። አንድ የቤተሰብ ራስ በጥንቃቄ እያጠና ሚስቱና ልጆቹ በመንፈሳዊ ቢራቡ ትክክል ይሆናልን? የቤተሰቡ ራስ ‘የራሱ ለሆኑት፣ ይልቁንም ለቤተሰቦቹ የሚያስፈልጋቸውን’ በማቅረብ ረገድ የተጣለበት ኃላፊነት ሥጋዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ማቅረብንም ይጨምራል። (1 ጢሞ. 5:8) ለልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጠና መስጠት ትልቅ ጥበብ መሆኑ በምሳሌ 22:6 ላይ በተሰጠው ምክር ተገልጿል። “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።” ልጄ በጣም ትንሽ ስለሆነ ጥናቱ ምንም ሊጠቅመው አይችልም ብለህ አታስብ። ልጆች መማር የሚጀምሩት ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ነው። (2 ጢሞ. 3:15) በጣም ፈጣን እድገት የሚያሳዩ ቤተሰቦች አብዛኛውን ጊዜ የቤተሰብ ንባብና ጥናት ፕሮግራም ያላቸው ቤተሰቦች ናቸው። ፕሮግራሙ እንዳይቋረጥ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

13 የቤተሰብህ አባሎች ሐሳብ እንዲሰጡ በማድረግና በሚገባ መረዳታቸውን ለማረጋገጥ ጥያቄዎችን በመጠየቅ የዕለቱን ጥቅስ አብረሃቸው ትወያያለህን? እንዲህ ማድረግህ ለቤተሰብህ ብዙ መንፈሳዊ ምግብ ሊያስገኝላቸው ይችላል። ብዙ ቤተሰቦች የዕለቱን ጥቅስ የሚወያዩት ምግብ በሚበሉበት ጊዜ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሳምንቱ ውስጥ ሰፋ ያለ የቤተሰብ ጥናት የሚደረግበት ጊዜ መመደብ ይኖርበታል። ጥናቱን በአንድ ምሽት ወይም አመቺ በሆነ ሌላ ጊዜ ማድረግ ይቻላል። ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን ለመረዳት፣ ከተለያየ አቅጣጫ ነገሩን ለማየትና ሐሳቦቹ በልብ ውስጥ እንዲቀረጹ ለማድረግ በቂ ጊዜ መመደብ ያስፈልጋል። ዘወትር የሚደረግ የቤተሰብ ጥናት ሁላችሁም ከጥናት ከሚገኘው ጥቅም ተካፋይ እንድትሆኑ ያስችላችኋል። እንዲህ ያለ የቤተሰብ ጥናት ፕሮግራም አላችሁን? በቤትህ ውስጥ ያልተዘወተረ ነገር ከሆነ ለምን ዛሬውኑ ከቤተሰብህ ጋር ተወያይተህ የቤተሰብ ጥናት የቤተሰብህ ሕይወት ክፍል እንዲሆን የሚያስችል እርምጃ አትወስድም? — ኤፌ. 6:4፤ ዘዳ. 6:4–7

14 ልጆች በጣም ትንንሾች ከሆኑ ሊገባቸው የሚችልና የሚጠቅማቸው ትምህርት በጥናቱ ላይ ቢጨመር ጥሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጣም ከባድ የሆነ ትምህርት በሚጠናበት ጊዜም እንኳ ሊገባቸው በሚችል ነጥብ ላይ ቀላል ጥያቄ በመጠየቅ ማሳተፍ ይቻላል። ብዙ ቤተሰቦች በቤተሰብ ጥናታቸው ጊዜ ለመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ይዘጋጃሉ። ቢሆንም ለቤተሰቡ አስፈላጊ የሆነ ማንኛውም ዓይነት ጽሑፍ ሊጠና ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና ጠንካራ የሆነ የቤተሰብ መተሳሰርና መንፈሳዊ አድናቆት ያስገኛል።

15–17. አዘውትሮ ከሚደረግ ጥናት ምን ጥቅም ሊገኝ ይችላል?

15 የትጋት ዋጋ። ለጥናት መትጋት ከሚከፍለው ዋጋ አንዱ ለአእምሮአችን በቂ ልምምድና ማነቃቂያ በመስጠት የማስታወስ ችሎታችን እንዲዳብር ማድረጉ ነው። ቀደም ሲል ያጠናነውን ትምህርት በመስክ አገልግሎትም ሆነ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለማስታወስና ሐሳብ ለመስጠት ቀላል ይሆንልናል። ፍላጎት ያላቸው አዳዲስ ሰዎች ጥያቄ ሲጠይቁን ጽሑፎችን ማገላበጥ ሳያስፈልገን ከአእምሮአችን ብቻ መልስ ለመስጠት እንችላለን። ለሐሳባችን ድጋፍ የሚሰጡ ጥቅሶችን በቀላሉ ለማውጣት እንችላለን። ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጠው ጥቅም ግን ስለ አምላክ ቃል የተሟላና የዳበረ እውቀት እንዲኖረን ማስቻሉ ነው። እምነታችንን ያጠነክርልናል፤ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በይበልጥ እንድናስተውል ያስችለናል፤ ከይሖዋ አገልግሎት የምናገኘውን ደስታ ያበዛልናል። — ዕብ. 5:14

16 ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች መንፈሳዊነታቸውን ለሚመለከቱ ጉዳዮች ቅድሚያ ይሰጣሉ። ጊዜ ከታጣ አነስተኛ ግምት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ሊቀሩ ይችላሉ። የሕይወትን ቃል ማጥናት ግን ሊቀር የማይችል ጉዳይ ነው። ይሖዋ ‘ታገኘኛለህ’ ሲል የገባውን ቃል የሚፈጽመው እንደዚህ ያለ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ነው። (1 ዜና 28:9) በተለይ የምታጠናው የጭንቅላት እውቀት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ልብህን ለመመገብ ከሆነ ይህ እውነት ይሆናል። ቃሉን በማጥናት ለይሖዋና አስደናቂ ለሆኑት ሥራዎቹ ያለህ አድናቆትና ፍቅር ይደግ።

17 የአምላክ አገልጋዮች የአምላክን ቃል የሚያጠኑበት ትክክለኛ ዓላማ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ 1:9, 10 ላይ በጻፈው ቃል ተገልጿል:- “በመንፈሳዊ ጥበብና በማስተዋል ሁሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምትገነዘቡበት ሙሉ ዕውቀት እንዲኖራችሁ . . . እንዲህም ከሆነ እንደ ጌታ ፈቃድ በመኖር በሁሉ ነገር ጌታን ታስደስታላችሁ፤ የመልካም ሥራ ፍሬም ሊገኝባችሁና እግዚአብሔርንም በማወቅ ልታድጉ ትችላላችሁ።” — የ1980 ትርጉም

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]