በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ መጪው ጊዜ ያለን አመለካከት

ስለ መጪው ጊዜ ያለን አመለካከት

ስለ መጪው ጊዜ ያለን አመለካከት

ለሕይወት ያለንን አመለካከት በጥልቅ የሚነካ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በራእይ 21:3, 4 ላይ ይገኛል። እንዲህ ይነበባል:- “እግዚአብሔር እሱ ራሱ ከእነርሱ [ከሰዎች] ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል። እንባዎችንም ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ስለሚፈጥረው የተሻለ ዓለም በተደጋጋሚ ይገልጻል:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”—2 ጴጥሮስ 3:13፤ መዝሙር 37:9–11, 29፤ ኢሳይያስ 11:6–9፤ 35:5, 6

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ባስተማራቸው ጊዜ እንዳመለከተው የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ የዚህ ተስፋ ፍጻሜ እንደሆነ ያምናሉ። (ማቴዎስ 6:10) የአምላክ መንግሥት እውነተኛ መስተዳድር እንደሆነች እናምናለን። (ኢሳይያስ 9:6, 7) የሰውን ልጆች የሚያስጨንቁትን ሁኔታዎች በሙሉ ከምድር ላይ አጥፍታ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የምትችል ብቸኛ መንግሥት ነች።

የአምላክ መንግሥት መምጣት በአሁኑ ጊዜ ባሉት መንግሥታት ላይ ምን ውጤት እንደሚያስከትል በሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ ተገልጿል:- “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል. . . እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች። ታጠፋቸውማለች። ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44

ይህ ለውጥ በጣም እንደቀረበ ስለምናምን ወጣቶቻችን የአምላክ መንግሥት እውነተኛ መስተዳድር ስለመሆኗ ካለን እምነት ጋር ለሚስማማ የዕድሜ ልክ ሥራ መዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ያምናሉ። ዋነኛ ዓላማችን በፊታችን ስላለው ብሩህ ተስፋ ለሰዎች መናገር ነው። በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ኀዘኖችና ችግሮች አልፈን አምላክ ለሚያገለግሉት ያዘጋጃቸውን በረከቶች የምናገኝበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት እንጠብቃለን። እርግጠኛ የሆነው የአምላክ ተስፋ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ይላል። 1 ዮሐንስ 2:17

ከዓለም መለየት

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጪው ጊዜ ያላቸው ይህ አመለካከት በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ላይም ትልቅ ውጤት አስከትሎ እንደነበረ መገመት አያስቸግርም። ከዓለም የተለዩ ሰዎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ታሪክ ጸሐፊው ኢ ጂ ሃርዲ ክርስቲያኒቲ ኤንድ ዘ ሮማን ገቨርንመንት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት “ክርስቲያኖቹ በዙሪያቸው በነበረው ዓለም እንግዶችና መጻተኞች ነበሩ። ዜግነታቸው በሰማይ ነበር። የሚጠብቋት መንግሥት የዚህ ዓለም አልነበረችም። ስለዚህ ከመጀመሪያ ጀምሮ በሕዝባዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት አለመፈለግ የክርስትና ግልጽ ገጽታ ሆነ።”

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ተለይተው ከሚታወቁባቸው ዋነኛ ባሕርያት አንዱ ከዓለም መለየታቸው እንደሆነ ገልጿል። “ከዓለም አይደሉም” ብሏል። (ዮሐንስ 17:16፤ 15:19) የይሖዋ ምሥክሮችም ከዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በመስማማት “የዓለም ክፍል” ላለመሆን ይጥራሉ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ሲባል ራሳችንን ከዓለም ሰውረን ባህታውያን እንሆናለን ማለት አይደለም። በምንኖርበት ማኅበረሰብና በትምህርት ቤት ስላሉት ሰዎች ደህንነት ከልብ እናስባለን። ወጣቶቻችንም ለትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች ጠቃሚ አስተዋጽኦ ለማበርከት ይፈልጋሉ።

ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር አብረን “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደተያዘ” መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚናገር እናምናለን። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ዮሐንስ 12:31፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4) በመሆኑም የዓለም ተጽዕኖ በልጆቻችን ላይ ስለሚኖረው ጐጂ ውጤት እናስባለን። ብዙውን ጊዜ እኛ ከጥሩ ሥነ ምግባር ውጭ እንደሆነ የምናምነውን አኗኗር ዓለም አስውቦ ያቀርበዋል። ትምህርት ቤቶችም በዚህ ይነካሉ። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በተቻለ መጠን ልጆቻቸው እነዚህን ከመሰሉት ጐጂ ተጽዕኖዎች እንዲርቁ ይፈልጋሉ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ዓለምም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል”​—1 ዮሐንስ 2:17