በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓላትን ማክበር

በዓላትን ማክበር

በዓላትን ማክበር

የይሖዋ ምሥክሮች በአብዛኞቹ ዓመት በዓሎችና ሌሎች ክብረ በዓሎች አለመካፈላቸው አንድን መምህር ግራ ሊያጋባው ይችላል። የሚከተለው ማብራሪያ ይህን ጉዳይ ለምን አክብደን እንደምንመለከት ለመረዳት እንደሚያስችላችሁ ተስፋ እናደርጋለን።

ብዙዎቹ ዓመት በዓሎችና በበዓሎቹ ላይ የሚፈጸሙት ልማዶች ከምታስቡት በላይ ከክርስትና የተለየ ሃይማኖታዊ መሠረት እንዳላቸው ተገንዝባችሁ ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮችም እነዚህን በዓላት የማያከብሩት በዚህ ምክንያት ነው። የሚከተለውን ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን ሥርዓት ለመከተል እንጥራለን:-

“ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለው? ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? . . . ስለዚህ ይሖዋ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ . . . ይላል።”—2 ቆሮንቶስ 6:14–17

ስለዚህ በዓሉ በሆነ መንገድ ከሐሰት አማልክት ጋር የተያያዘ ከሆነ ወይም በዓሉን ማክበር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ካለን ግንዛቤ ጋር የሚጋጭ ከሆነ በአከባበሩ አንካፈልም።

የልደት ቀኖች:- እርግጥ ድግስ መደገስና መገባበዝ ወይም ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ስጦታ መለዋወጥ ስህተት አይደለም። (ሉቃስ 15:22–25፤ ሥራ 20:35) የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን ዓመት ስጦታ በመሰጣጣትና እርስበርስ በመገባበዝ ይደሰታሉ። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተከበሩ የተነገረላቸው የልደት ቀኖች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነርሱም እውነተኛ አማኞች ባልነበሩ ሰዎች የተከበሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የግብፁ ፈርዖንና ሄሮድስ አንቲጳስ የተባለው ሮማዊ ገዥ ሲሆኑ የሁለቱም የልደት ቀን መከበር ለሰዎች መገደል ምክንያት ሆኗል። (ዘፍጥረት 40:18–22፤ ማርቆስ 6:21–28) ስለዚህ የሚከተሉትን የጥንት ክርስቲያኖች ስለ ልደት በዓል ያላቸውን ዝንባሌ የሚገልጹ የታሪክ መረጃዎች ማንበባችን እንግዳ ነገር አይሆንብንም።

“በዚህ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች በአጠቃላይ የልደት ቀናቸውን የማክበር ሐሳብ ፈጽሞ አልነበራቸውም።” ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ሪሊጅን ኤንድ ቸርች፣ ዲዩሪንግ ዘ ስሪ ፈርስት ሴንቸሪስ (ኒው ዮርክ 1848) በአውግስቶስ ኒያንደር የተጻፈ (በሄንሪ ጆን ሮዝ የተተረጐመ) ገጽ 190

“በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ከተጠቀሱት ቅዱሳን መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ በልደት ቀናቸው ድግስ እንደ ደገሱ ወይም በጣም ትልቅ ግብዣ እንዳዘጋጁ ተጽፎ አናገኝም። ወደዚህ ወደ ታችኛው ዓለም ተወልደው የመጡበትን ቀን በታላቅ ደስታ ያከበሩት (እንደ ፈርዖንና ሄሮድስ የመሳሰሉ) ኃጢያተኞች ብቻ ናቸው።” የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ (ኒው ዮርክ 1911) ጥራዝ 10, ገጽ 709 (የሦስተኛው መቶ ዘመኑን ኦሪገን አዳማንቲየስ ጠቅሶ የጻፈው)

በተጨማሪም የልደት ቀን ክብረ በዓሎች በዓሉ ለሚከበርለት ግለሰብ ከልክ ያለፈ ክብር ወደ መስጠት ያዘነብላሉ። የቀድሞ ክርስቲያኖች ከዚህ እንዲርቁ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነበር። (መክብብ 7:1) ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በልደት ቀን በዓላት ላይ በሚደረጉ ነገሮች (ግብዣዎች፣ መዝሙሮች፣ ስጦታ መስጠትና በመሳሰሉት) የማይካፈሉት በዚህ ምክንያት ነው።

ገና:- ታኅሣሥ 25 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ ታህሣሥ 29) ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቀን አለመሆኑን ሳታውቁ አትቀሩም። የሚፈለገው ድርጊቱ መፈጸሙ ነው እንጂ ቀኑ ልዩነት አያመጣም የሚል ስሜት ይኖራችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ የገና በዓል አመጣጥ ቀኑ ከዚህ የበለጠ ትርጉም እንዳለው ያመለክታል። የሚከተሉት ኢንሳይክሎፔድያዎች እንዲህ በማለት ያስረዳሉ:-

“የገናን በዓል ማክበር በመለኰታዊ ትዕዛዝ የተጀመረ ወይም ከአዲስ ኪዳን የተገኘ ልማድ አይደለም። የክርስቶስን የልደት ቀን ከአዲስ ኪዳን አረጋግጦ ማወቅ አይቻልም። እንደ እውነቱ ከሆነ ከማንኛውም ሌላ ምንጭ ሊረጋገጥ አይችልም። የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት አባቶች ስለ ምንም ዓይነት የገና በዓል አከባበር አይናገሩም።” ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል ቲዮሎጂካል ኤንድ ኤክሌሲያስቲካል ሊትሬቸር (ግራንድ ራፒድስ፣ ሚችጋን 1981 እንደ ገና የታተመ) በጆን ማክሊንቶክ እና ጀምስ ስትሮንግ ጥራዝ 11 ገጽ 276

“በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ተስፋፍተው የሚገኙት ወይም ቀደም ባሉት ዘመናት ተመዝግበው የምናገኛቸው የገና በዓል ልማዶች የክርስትና እውነተኛ ልማዶች ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸው ወይም ያልተቃወመቻቸው አረማዊ ልማዶች ናቸው። በሮም ይከበር የነበረው ሳተርናሊያ ገና በሚከበርበት ወቅት ለሚፈጸሙት ለአብዛኞቹ ፈንጠዝያዎች ሞዴል ሆኗል።” ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ (ኤዲንበርግ 1911) በጄምስ ሃስቲንግስ የተዘጋጀ ጥራዝ 3 ገጽ 608, 609

ገና በጥንት ዘመን የክርስቶስ ልደት የሚከበርበት ቀን እንዳልነበረ በሰፊው ይታወቃል። የታኅሣሥ 1981 ዩ ኤስ ካቶሊክ ገጽ 32 “ገናን ከአረማዊ አመጣጡ መነጠል ፈጽሞ አይቻልም” ይላል። መጽሔቱ እንደሚከተለው በማለት ያብራራል:-

“በሮማውያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው በዓል ታኅሣሥ 17 ጀምሮ ‘ድል ያልተደረገው የፀሐይ ልደት ቀን’ (ናታሊስ ሶሊስ ኢንቪክቲ) በሆነው ታኅሣሥ 25 ያበቃ ነበር። በአራተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የሮም ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች ታኅሣሥ 25 ‘የጽድቅን ፀሐይ’ የልደት ቀን ለማክበር ምቹ ይሆናል ብለው ወሰኑ። የገና በዓል ተወለደ።”

አንዳንዶች ስለ ገና እነዚህን ሐቆች ሲያውቁ ምን አድርገዋል? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ (1982) የገና በዓል በሚለው ርዕስ ሥር እንዲህ ይላል:- “በ1600ዎቹ ዓመታት  . . . የገና በዓል በእንግሊዝና በአሜሪካ በነበሩ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች በሕግ ተከልክሎ ነበር። የጥንት ሕዝቦች ገና ከአረማውያን የመጣ ነው ብለው እንዳላከበሩት ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች የገናን በዓል የማያከብሩበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። ለገና በዓል በሚደረጉ ድግሶች፣ ጨዋታዎች፣ መዝሙሮች፣ የስጦታ ልውውጥና በሌሎች ከገና በዓል ጋር ዝምድና ባላቸው ልማዶች አንካፈልም።

የይሖዋ ምሥክሮች በተመሳሳይ በትምህርቱ ዓመት ውስጥ በሚከበሩት ሌሎች ሃይማኖታዊ ወይም ከፊል ሃይማኖታዊ በዓሎች አከባበር አይካፈሉም። ምክንያቱም እነዚህ ዓመት በዓሎችም ክርስቲያን ካልሆኑ አምልኰቶች ጋር ስለሚያያዙ ነው። እንዲያውም በክብረ በዓሎቹ ላይ ጐልተው የሚታዩት የእንደዚህ ዓይነቶቹ ክርስቲያን ያልሆኑ አምልኰቶች አንዳንድ ገጽታዎች ናቸው። የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከቱ:-

ፋሲካ:- ይህ ዓመት በዓል የሚከበረው የክርስቶስን ትንሣኤ ለማስታወስ ነው ቢባልም አንዳንድ ዓለማዊ የጽሑፍ ማስረጃዎች ስለዚህ በዓል ምን እንዳሉ አስተውሉ:-

“ፋሲካ፣ ጥንት በአንግሎ ሳክሶኖች ኢስትር ይባል የነበረና የቲውቶናውያን የብርሃንና የፀደይ አምላክ የምትከበርበት የፀደይ በዓል ነበር። ስሙ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማክበር ይደረግ ለነበረው በዓል የተሰጠው ገና በ8ኛው መቶ ዘመን በአንግሎ ሳክስኖች ነበር።”—ዘ ዌስትሚኒስተር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል (ፊላደልፊያ 1944) በጆን ዲ ዴቪስ ገጽ 145

“የትም ቦታ የፋሲካ ጥንቸል ያመጣችውን ባለ ብዙ ቀለም የፋሲካ እንቁላል ይፈልጋሉ። ይህ ተራ የሆነ የሕፃን ጨዋታ ሳይሆን የመዋለድ አምልኮ ሥርዓት ርዝራዥ ነው። እንቁላሉና ጥንቸሏ ሁለቱም የሚያመለክቱት መዋለድን ነበር።” የፉንክና የዋግናልዝ ስታንደርድ ዲክሽነሪ ኦቭ ፎክሎር ሚቶሎጂ ኤንድ ሌጀንድ (ኒው ዮርክ 1949) ጥራዝ 1 ገጽ 335

የዘመን መለወጫ ቀን:- “በጥንቷ ሮማ የዓመቱ የመጀመሪያው ቀን የደጆችና የበሮች እንዲሁም የመጀመሪያዎችና የፍጻሜዎች አምላክ ተብሎ ይመለክ የነበረው ጣዖት ጃነስ የሚከበርበት ቀን ነበር። የዘመን መለወጫ ቀን የክርስትና በዓል ሆኖ በቤተ ክርስቲያን መከበር የጀመረው በ487 ነበር።”—ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔዲያ (1982) ጥራዝ 14 ገጽ 237

የእናት ቀን:- “ከጥንቷ ግሪክ የእናት አምልኮ ልማድ የመጣ በዓል ነው። ታላቋ የአማልክት እናት ተብላ ትመለክ ለነበረችው ለሲቤሌ ወይም ለሪያ በሚቀርብ የአምልኮ ሥርዓት ይከበር የነበረው የእናት አምልኮ በመላይቱ ታናሽቱ እስያ የሚፈጸመው በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።”—ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ (1959) ጥራዝ 15 ገጽ 849

እነዚህ በሰፊው ከሚከበሩት ዓመት በዓሎች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ተማሪዎችም አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ በዓሎች በሚከበሩባቸው ቀናት አንዳንድ ነገር በማድረግ በአከባበሩ እንዲካፈሉ ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች በኅሊናቸው ምክንያት መዝሙር በመዘመር፣ ሙዚቃ በመጫወት፣ በጭውውቶች በመካፈል፣ የሰልፍ ጉዞ በማድረግ፣ ሥዕል በመሳል፣ በድግሶች በመካፈል ወይም በመብላትና በመጠጣት እነዚህን በዓላት ለማክበር በሚፈጸሙ በማናቸውም ድርጊቶች አይካፈሉም። ሆኖም እነዚህ ዓመት በዓሎች እንዳይከበሩ አንቃወምም ወይም አከባበሩን ለማሰናከል ጥረት አናደርግም። ልጆቻችን በእነኚህ በዓላት አከባበር እንዳይካፈሉ በደግነት የሚፈቅዱትን መምህራን ከልብ እናመሰግናቸዋለን።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንት ክርስቲያኖች የልደት በዓላቸውን አላከበሩም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የይሖዋ ምሥክሮች በኅሊናቸው ምክንያት ዓመት በዓሎችን ለማክበር በሚፈጸሙ በማናቸውም ድርጊቶች አይካፈሉም