በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመደበኛ ትምህርት ውጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች

ከመደበኛ ትምህርት ውጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች

ከመደበኛ ትምህርት ውጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች

የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት በጥናትና በሥራ ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደሌለበት ያምናሉ። በትምህርት ቤት ሰዓቶች አንዳንድ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግና መዝናናት አእምሮ ያድሳል። ሆኖም ብዙ ወጣት ምሥክሮች ትምህርት ቤቶች በሚያካሂዷቸው ከመደበኛ ትምህርት ውጭ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንደማይሳተፉ አስተውላችሁ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳይ ጥቂት ብንገልጽላችሁ አመለካከታችንን እንድትገነዘቡ ሊረዳችሁ ይችላል።

የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ቤተሰቦች በአምልኰታቸው ላይ የተመሠረቱ እንቅስቃሴዎችና ፕሮግራሞች አሏቸው። ወላጆችም በዚህ የቤተሰብ ፕሮግራም ውስጥ መዝናኛዎችን እንዲጨምሩ ይበረታታሉ። ወላጆች መዝናኛዎችን ሲያዘጋጁና ሲቆጣጠሩ፣ አብዛኛውን ጊዜም ከልጆቹ ጋር አብረው ሲዝናኑ አስፈላጊውን ቁጥጥር ለማድረግ ይችላሉ።

አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ጥቂት ቤተሰቦች አንድ ላይ ተሰባስበው ሊዝናኑ ይችላሉ። በየዓመቱም የክልል ስብሰባና የወረዳ ስብሰባ ተብለው በሚጠሩ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ረዘም ያለ ጉዞ ያደርጋሉ። እነዚህ ጉዞዎች ቤተ መዘክሮችን፣ ታሪካዊ ቦታዎችንና ሌሎች ባሕላዊ ማዕከሎችን ለመጐብኘት የሚያስችል አጋጣሚ ያስገኙላቸዋል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ወጣት ምሥክሮች ከሌሎቹ የአገሩ ክፍሎች ከመጡና እንደ እነርሱ ይሖዋ አምላካቸውን የማገልገል ግብ ካላቸው ሌሎች ብዙ ወጣቶች ጋር በመገናኘትና በመጨዋወት ይደሰታሉ።

በተለይ የማኅበረሰቡ የሥነ ምግባር ደረጃ እየተበላሸ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ወጣቶቻችን ይህን የመሰለ ጤናማ ባልንጀርነት ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እናስባለን። የይሖዋ ምሥክሮች “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ለሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠንቀቂያ ትልቅ ክብደት ይሰጣሉ። ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ኢየሱስ “ከዓለም አይደላችሁም” በማለት ለተከታዮቹ ከተናገረው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር እንጥራለን። (1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ዮሐንስ 15:19) ምሥክሮች የሆኑ ቤተሰቦች ከመደበኛ ትምህርት ውጭ ለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች፣ ቀጥሎ ለተገለጹት ጭምር፣ ያላቸውን አመለካከት የሚወስኑት እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው።

ስፖርት:- በስፖርት የምናገኘው ዓይነት የሰውነት ማሠልጠኛ ይጠቅመናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ትክክለኛውን አመለካከት ይገልጻል:- “እግዚአብሔርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ። ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁኑና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል።” (1 ጢሞቴዎስ 4:7, 8) የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ምክር ጋር በመስማማት በትምህርት ሰዓት የሚሰጡት የአካል ማጐልመሻ ትምህርቶች ጠቃሚ መሆናቸውን ያውቃሉ።

ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ብዙውን ጊዜ ትምህርት ቤቶች ለስፖርት ከሚገባው የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጡ ይሰማቸዋል። ስለዚህም ልጆቻቸውን በሚያሠለጥኑበት ጊዜ ለአትሌቲክ ውጤታቸው ልከኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ ይጥራሉ። ልጆቻቸው በሚያድጉበት ጊዜ ታዋቂ ስፖርተኞች ሳይሆን ጥሩ የአምላክ አገልጋዮች የመሆንን ግብ እንዲከታተሉ ተስፋ ያደርጋሉ። ስለዚህ ልጆቻቸው ከትምህርት ውጭ ያላቸውን ጊዜ በአንድ ዓይነት ስፖርት ልቀው ለመገኘት ሳይሆን መንፈሣዊ ጉዳዮችን ለመከታተል እንዲጠቀሙበት ተስፋ ያደርጋሉ። ስለዚህ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት በኋላ ያለውን ሰዓታቸውን በአንዳንድ የስፖርት ዓይነቶች ብልጫ ለማግኘት ሳይሆን በይበልጥ መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለመከታተል እንዲጠቀሙበት ያበረታቷቸዋል።

በተደራጁ ስፖርቶች መሳተፍ ምሥክር የሆኑ ወጣቶችን ጤናማ ላልሆነ ባልንጀርነት ያጋልጣቸዋል ብለን እናምናለን። በተጨማሪም በዘመናዊ ስፖርት የሚታየው የውድድር መንፈስ ማለትም ‘ማሸነፍ ሁሉም ነገር ሳይሆን ብቸኛው አማራጭ ነው’ የሚለው አስተሳሰብ ጐጂ ውጤት እንደሚያስከትል ይሰማናል። ስለዚህ ወጣት ምሥክሮች ተጨማሪ መዝናኛ ካስፈለጋቸው ከእምነት መሰሎቻቸው፣ አዎን፣ “ጌታን በንጹሕ ልብ ከሚጠሩት ጋር” እንዲያደርጉት ወላጆቻቸው ያበረታቷቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:22

የትምህርት ቤት ጭፈራዎች:- ጭፈራም ልክ እንደ ስፖርት ጤናማና ጠቃሚ ሊሆን ይችላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አባካኙ ልጅ በሰጠው ምሳሌ ላይ ዘፈን የደስታ መግለጫ ሆኖ እንዳገለገለ ስለጠቀሰ ዘፈንን ወይም ጭፈራን እንዳልተቃወመ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 15:25) ይሁን እንጂ ምሥክር ወጣቶች ትምህርት ቤቶች በሚያካሂዷቸው ዘፈኖችና ጭፈራዎች እንደማይካፈሉ አስተውላችሁ ይሆናል። የማይካፈሉበት ምክንያት ምንድን ነው?

ዋናው ምክንያት የትምህርት ቤት ዘፈኖችና ጭፈራዎች በሚደረጉባቸው ቦታዎች የሚኖረው መጥፎ ሁኔታ ነው። ማጨስ፣ ከመጠን በላይ መጠጣት፣ ዕጽ መውሰድ፣ አሳፋሪ የሆኑ ወሲባዊ ባሕርያት መኖራቸው የተለመደ ነው። ስለዚህ በእነዚህ ዘፈኖች ወይም ጭፈራዎች ላይ የሚገኝ ሰው ጥሩ ካልሆኑ ባልንጀሮች ጋር አብሮ መዋሉ የማይቀር ነው። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች “ጌታን በንጹሕ ልብ ከሚጠሩ ጋር” እንዲተባበሩ ከተሰጠው ምክር ጋር በመስማማት ከትምህርት ቤት ዘፈኖችና ጭፈራዎች ይርቃሉ።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር መቀጣጣር:- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መቀጣጠር በብዙ አካባቢዎች የተለመደ የመዝናኛ ዓይነት ሆኗል። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጆችና ወጣቶች እንኳን ይቀጣጠራሉ። በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲዞሩ፣ ሲሳሳሙ፣ እንዲያውም ከዚያም ያለፈ ነገር ሲያደርጉ ይታያሉ። ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ለጋብቻ ያልደረሱ ለጋ ልጆቻቸው ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ጓደኞቻቸው ጋር ብቻቸውን ሆነው ወንድና ሴት ወጣቶች በሚቀጣጠሩበት ጊዜ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ማድረጋቸው ትክክል እንዳልሆነ ያምናሉ።

የትምህርት ቤት ክበቦች:- ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ይህን ፍላጎታቸውን በትምህርት ቤት ውስጥ በሚቋቋም ክበብ ውስጥ ገብተው እርስ በርስ ለመካፈል ይፈልጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ክበቦች የሚሰጡት ጥቅም ከማኅበራዊ አገልግሎት አያልፍም። እንደነዚህ ባሉት እንቅስቃሴዎች ከተወሰኑ ተማሪዎች ጋር መካፈል አብዛኛውን ጊዜ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ወደ መፈጸም እንዳመራ ታይቷል። እንዲህ ያለ አጋጣሚ ሊከሰት ስለሚችል የአንድ የትምህርት ቤት ክበብ አባል ከመሆን በፊት በጥንቃቄ ማመዛዘን እንደሚያስፈልግ ይሰማናል።

ምሥክር ወጣቶችና ወላጆቻቸው የሚያስቡባቸው አስፈላጊ ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው:- የክበቡ ሥራዎች የሚከናወኑት በትምህርት ሰዓት ነውን? ትምህርት ቤቱ በቅርብ ይቆጣጠራቸዋልን? የክበቡ አባል መሆን ለቤተሰብ ወይም ለጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሊውል የሚገባውን ከትምህርት ሰዓት ውጭ ያለ ጊዜ ይሻማልን? በመጨረሻም ልጆቻቸው ክበብ ውስጥ መግባት ካለባቸው በምን ዓይነት ክበቦች ወይም የትምህርት ቤት ድርጅቶች እንዲገቡ የመፍቀድ ኃላፊነት ያላቸው የምሥክሮቹ ወላጆች ናቸው።

የትምህርት ቤት ቲያትሮች:- የይሖዋ ምሥክሮች ተዋናይ መሆንን ራሱን አይቃወሙም። የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎች የወረዳ ስብሰባዎቻችን ፕሮግራም ጉልህ ክፍል ናቸው። ሆኖም ምሥክር ወላጆች ልጆቻቸው በትምህርት ቤት ቲያትሮች እንዲሳተፉ ለመፍቀድም ሆነ ለመከልከል ከመወሰናቸው በፊት የሚያጤኗቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ያህል ቲያትሩ የሚያስተላልፈው መልእክት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይስማማልን? ምሥክር ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸውን የሥነ ምግባር ደረጃዎች በሚፈቅዱ ቲያትሮች አይሳተፉም። በተጨማሪም በቲያትሩ ልምምድ የሚባክነው ጊዜና ጤናማ ያልሆነ ባልንጀርነት ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ስለዚህ ወላጆች ምሥክር ወጣቶች በቲያትር መሳተፍ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው በሚወስኑበት ጊዜ እነዚህን ጉዳዮች ያጤናሉ።

ደምና ሌሎች ስጦታዎች:- በብዙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በየጊዜው ለተለያየ ዓላማ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። አንዳንዴም ለሌላ ሰው የሚሰጥ ደም እንዲለግሱ ይጠየቃሉ። ይሁን እንጂ “ከደም ራቁ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ ደም እንዳይበላ ወይም ለማንኛውም ሌላ አገልግሎት እንዳይውል የሚያዝዝ እንደሆነ እንገነዘባለን። ስለዚህ በኅሊና ምክንያት ደም አንሰጥም ወይም አንቀበልም።—ዘፍጥረት 9:4–6፤ ዘሌዋውያን 17:10–14፤ ሥራ 15:19, 20, 28, 29

በዚህ ብሮሹር ላይ ቀደም ብለን በተወያየንባቸው ምክንያቶች ለፖለቲካ ጉዳዮች ወይም ለሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ወይም ዓመት በዓል ለማደራጀት ተብለው ለሚጠየቁ የገንዘብ መዋጮዎች የይሖዋ ምሥክሮች አያዋጡም። በተጨማሪም በሎተሪ፣ በቁማር፣ ወይም በማንኛውም ይህን የሚመስል ጨዋታ አንካፈልም። ይሁን እንጂ እንደሁኔታው መዋጮ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የግል ውሳኔ የሚሰጥባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ የአካል ጉዳት የደረሰበት ወይም የታመመ የትምህርት ቤት ጓደኛ ካለን አበባ ወይም ሌላ ዓይነት ስጦታ ለመግዛት ገንዘብ ቢሰበሰብ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ለማዋጣት ደስተኞች ናቸው።—ሥራ 20:35

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል”—1 ቆሮንቶስ 15:33