በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከትምህርት ቤቱ ሥርዓት ጋር መተባበር

ከትምህርት ቤቱ ሥርዓት ጋር መተባበር

ከትምህርት ቤቱ ሥርዓት ጋር መተባበር

የይሖዋ ምሥክሮች ለልጆቻቸው ሊያስተላልፏቸው ከሚችሉት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ቅርሶች አንዱ ጥሩ ትምህርት እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ልጆቹ ለሚያገኙት ትምህርት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው? በትምህርት ቤት የሚያስተምሯቸው መምህራን ብቻ ናቸውን?

የመጀመሪያ ደረጃ ኃላፊነት የሚወድቀው በመምህራን ላይ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ልጆች የተገኙት ከወላጆች እንደመሆኑ መጠን የቤተሰብ ክፍል ናቸው። የመንግሥት ወይም የማንኛውም አስተዳደራዊ ተቋም ንብረቶች አይደሉም። ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ሊማሩ እንደሚገባ የመወሰን ከአምላክ የተሰጠ ኃላፊነት አለባቸው።

ሆኖም የትምህርት ቤት መምህራን በጣም የሚደነቅና ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ያበረክታሉ። በዚህ ሥርዓት በተጓደለበት ዘመን የሚያከናውኑት ሥራ በጣም ከባድ እንደሚሆንባቸው እንገነዘባለን። ወላጆች ከመምህራን ጋር ለመተባበር ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

የወላጆች ትብብር

በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆች ከልጆቻቸው መምህራን ጋር መተዋወቃቸው፣ ከእነርሱ ጋር ለመገናኘትና ለመነጋገር ዝግጅት ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። ከመምህራኑ ጋር የሚገናኙት ፊት ለፊት ለመፋጠጥ ሳይሆን በልጁ እድገት ረገድ ወላጆችና መምህራን እንዴት ሊተባበሩ እንደሚችሉ ለመነጋገር ነው። ወላጆች መምህሩ የሚናገረውን ለመስማትና ልጆቻቸው እንዲደረግላቸው ስለሚፈልጉት ነገር በግልጽ ለመናገር ደስተኞች ናቸው።

ምሥክር የሆነው አባት ወይም እናት ከመምህሩ ጋር ተገናኝቶ በሚነጋገርበት ጊዜ ልጆቹ ተገቢ የሆነ ክርስቲያናዊ ጠባይ እንዲያሳዩ እንደሚጠብቁባቸውና መጥፎ ነገር አድርገው ቢገኙ እንዲነገረው እንደሚፈልግ ለመምህሩ ማሳወቅ ይኖርበታል። መምህሩ ምክንያታዊ ቅጣት በሚሰጥበት ጊዜም ወላጆች እንደሚደግፉት እንዲያውም ቅጣቱን በቤትም ጭምር እንደሚያጠናክሩለት ሊያረጋግጡለት ይገባል።

ወላጆች ሊረዱ ከሚችሉባቸው ሌሎች መንገዶች አንዱ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ጥሩ ቁርስ መብላታቸውን ማረጋገጥ ነው። የቤት ሥራቸውን አሟልተው መሥራታቸውንና መጽሐፎቻቸውን በሙሉ መያዛቸውን አረጋግጡ። ሁልጊዜ ለትምህርት ቤቱ ደንቦች አክብሮት አሳዩ። ልጆቹም እንዲያከብሩ አሳስቡአቸው። ልጆቹ ስለ ትምህርት ቤትና በትምህርት ቤት ስላጋጠማቸው ማንኛውም ዓይነት ችግር እንዲናገሩ አድርጓቸው።

የዩናይትድ ስቴትስ የጤና፣ የትምህርትና የበጐ አድራጎት ክፍል ኸልፒንግ ችልድረን ሜክ ካርየር ፕላንስ: ቲፕስ ፎር ፓረንትስ በተባለው ጽሑፉ ላይ ልጆቻቸው እንዴት በጥሩ ሁኔታ እንዲማሩ ሊያነሳሷቸው እንደሚችሉ ለወላጆች እንዲህ በማለት ይነግራቸዋል:- “ልጃችሁ በትምህርት ቤት የሚማረውና የሚያጠናው ነገር ወደፊት ሥራ በሚይዝበት ጊዜ ምን ያህል እንደሚጠቅመው እንዲገነዘብ እርዱት። እንደ ንባብ፣ እንደ ሒሳብና እንደ ንግግር ችሎታ ያሉት ትምህርቶች ለማንኛውም የሥራ ዓይነቶች በጣም የሚያገለግሉ መሆናቸውን አስረዱት። በአጭሩ ትምህርት ቤት የሚሄዱት እንዲሁ መሄድ ስላለባቸው ብቻ ሳይሆን በጣም አስፈላጊ ምክንያት ስላለ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዷቸው።”

በዚህ ብሮሹር ላይ የተገለጸው ሁሉ በትምህርት ቤት ባለ ሥልጣኖችና በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች መካከል አስደሳች መተባበር እንዲኖር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ እናደርጋለን።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ልጆችን በማስተማር ረገድ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆች ናቸው።