በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወታችን ዓላማ

የሕይወታችን ዓላማ

የሕይወታችን ዓላማ

በመጀመሪያ የይሖዋ ምሥክሮችን ማንነትና የሕይወታችንን ዓላማ በአጭሩ መግለጽ ጠቃሚ ይሆናል። እኛ በመላው ዓለም በ231 አገሮች የምንገኝ ዓለም አቀፍ ክርስቲያናዊ ቡድን ነን። አምላክን የምናመልክበት መንገድ ጠቅላላውን የሕይወት አመለካከታችንንና አኗኗራችንን ይነካል።

አምላክ በተወሰነ ቦታ የሚኖር ሕያው አካል መሆኑን ስለምናምን ከሱ ጋር የአባትና የልጅነት መቀራረብና ዝምድና እንዲኖረን ማድረግ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ እናምናለን። (ማቴዎስ 6:9) ይህን ዝምድና ለማግኘት ከሚያስችሉን ነገሮች አንዱ እሱን በግል ስሙ ማወቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 83:18 ላይ እንዲህ ይላል:- “ስምህ ይሖዋ የሆንከው አንተ ብቻ በምድር ላይ የሁሉ የበላይ እንደሆንህ አሕዛብ ይወቁ።”—አዓት

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሕይወታችን በሙሉ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን አርዓያ ለመከተል እንፈልጋለን። ኢየሱስ ከፍተኛ ትምህርት የነበረው ሰው መሆኑን ያስተማራቸው ትምህርቶች ጥበብ የተሞላባቸው ከመሆናቸው ለመገንዘብ እንችላለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እውቀቱን የተጠቀመበት ሌሎችን ለመጥቀም እንጂ ከፍተኛ ሀብት ወይም ትልቅ ማዕረግ ለማግኘት አልነበረም። በሕይወቱ የመጀመሪያውን ትልቅ ቦታ የሰጠው ለአምላክ አገልግሎት ነበር። “የእኔስ ምግብ የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል።—ዮሐንስ 4:34

እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ ይሰማናል። በመላው ዓለም የሚኖሩ ምሥክሮች ይህን ፍላጎታቸውን ለመፈጸም ስለሚያስችላቸው ለትምህርት ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ። ወጣቶቻችን ስለ አካባቢያቸውና ስለ ሕይወታቸው እንዲሁም ስለ ሕይወት ምንነት ግንዛቤና እውቀት አግኝተው የእውቀት አድማሳቸውን እንዲያሰፉ እናበረታታለን። በዚህም ምክንያት ብዙ የሰብዓዊ እውቀት መስኮችን የሚዳስሰውን ንቁ! የተባለውን መጽሔታችንን አዘውትረው ያነባሉ። ለትምህርት ቤት ሥራቸውም ይጠቀሙበታል። አንዳንድ መምህራንም የሚሰጡትን ትምህርት ሲያዘጋጁ በዚህ መጽሔት ይጠቀማሉ።

ልጆቻችን የሚያገኙት የትምህርት ማሠልጠኛ አብዛኞቻቸው የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። ዘ ጆርናል ኦቭ ፐርሰናሊቲ የተሰኘው መጽሔት በ12 ዓመት ልጆች የ“ፈጠራ ችሎታ” ላይ በአውስትራሊያ ስለተደረገ ጥናት ሲዘግብ እንዲህ ብሏል:- “በተለይ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ብዛት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ልጆች ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ እንዳላቸው መገንዘብ ተችሏል።” ይህ ሊሆን የቻለው የምሥክሮቹ ሃይማኖት የማሰብ ችሎታቸውን እንዲጠቀሙ ስለሚያበረታታ ነው።

ወጣት ምሥክሮች ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም ትምህርት የሚከታተሉት ክብር ወይም ታዋቂነት ለማግኘት በማሰብ አይደለም። የሕይወታቸው ዋና ግብ ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት ውጤታማና ፍሬያማ መሆን ነው። ለዚህም ከትምህርት ቤት የሚያገኙት ሥልጠና ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ይገነዘባሉ። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ የሚመርጡት በዘመናዊው ዓለም ራሳቸውን ለመቻል የሚያበቋቸውን የትምህርት ዓይነቶች ነው። በዚህ የተነሣ አብዛኞቹ ሙያ ነክ ትምህርቶችን ሊወስዱ ወይም በሙያ ትምህርት ቤቶች ገብተው ሊማሩ ይችላሉ። ትምህርት ሲጨርሱም ዋነኛ ሥራቸው በሆነው በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ላይ ለማተኮር የሚያስችላቸው ዓይነት ሥራ ለማግኘት ይፈልጋሉ።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት

ከላይ ከተባለው ለመረዳት እንደምትችሉት የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ብዙ ሃይማኖተኞች ይበልጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ይመለከቱታል። “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ” መሆኑን ያምናሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት

ከእነዚያ ቃላት ጋር በመስማማትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው ነገር ሁሉ ትክክል እንደሆነና አንድን ክርስቲያን በሕይወቱ ሊመራው እንደሚገባ እናምናለን። በመሆኑም አንድ ወጣት ምሥክር ለአንዳንድ የትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች ያለው አመለካከት ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ግድየለሽ የሆነ ተማሪ ካለው አመለካከት በጣም የተለየ ሊሆን ይችላል። ይህ ብሮሹር እነዚህን እንቅስቃሴዎችና የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ረገድ ያላቸውን አቋም ለምን እንደወሰዱ እንድትገነዘቡ ሊረዳችሁ ይሞክራል።

እንደምታውቁት መጽሐፍ ቅዱስ ተወዳዳሪ የሌለው የትንቢት መጽሐፍ ስለሆነ ምሥክሮቹ በእነዚህ ትንቢቶች ማመናቸው ለትምህርት ቤት ባላቸው አመለካከት ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ከግምት ውስጥ እንድታስገቡት ልንጠይቃችሁ እንወዳለን።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመላው ዓለም የሚኖሩ ምሥክሮች ለትምህርት ከፍተኛ ግምት ይሰጣሉ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ዕለታዊ መመሪያ ይጠቀሙበታል