በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምንከተላቸው የሥነ ምግባር ደንቦች

የምንከተላቸው የሥነ ምግባር ደንቦች

የምንከተላቸው የሥነ ምግባር ደንቦች

በሥነ ምግባር ረገድ ያለው አመለካከት በአስገራሚ ሁኔታ መለወጡ በወጣቶች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የይሖዋ ምሥክሮች ያምናሉ። እንደምታውቁት አዲስ ሥነ ምግባር የተባለው የሥነ ምግባር አመለካከት ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ተስፋፍቷል። የዚህ አዲስ ሥነ ምግባር የመጀመሪያ ደጋፊዎች ከነበሩት አንዱ እንግሊዛዊው የውልዊች ጳጳስ እንዲህ ብለዋል:- “በራሱ ‘መጥፎ’ ሊሆን የሚችል ምንም ነገር የለም።” ከዚህ አባባል ጋር አንስማማም። ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ አመለካከት ካላቸው ጋር መከራከር እንደማንፈልግ ግልጽ ማድረግ እንፈልጋለን። ፍላጎታችን የምንከተላቸውን የሥነ ምግባር ሥርዓቶችና እነዚህን ሥርዓቶች የምንከተልባቸውን ምክንያቶች ለመግለጽ ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ የታወቁ የቲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆሴፍ ፍሌቸር ስለ አዲሱ ሥነ ምግባር እንዲህ ብለዋል:- “በዚህ ሥነ ምግባር መሠረት ከጋብቻ ውጭ የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት የሚቃወም ነገር የለም። እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ጥሩ ሊሆን ይችላል።” በዩናይትድ ስቴትስ የሃይማኖት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ፍሬዴሪክ ሲ ውድ ለተማሪዎች እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “የወሲብ ድርጊቶችን የሚገዙ ሕጎች የሉም። እደግመዋለሁ፣ ምንም ዓይነት ሕግ የለም። ማድረግ አለባችሁ ወይም ማድረግ የለባችሁም የሚባል ምንም ነገር የለም።” ቲዮሎጂ ቱደይ ጥቅምት 1965 ገጽ 396

እነዚህን የመሰሉ የሥነ ምግባር አመለካከቶች በሰፊው የታወቁ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ግን እነዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጩና ተገቢ እንዳልሆኑ ያምናሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ይህ አቋማችን በ1976 በታተመውና ጠባያችን በሥነ ምግባር ሥርዓቶች እንዴት እንደሚነካ በሚገልጸው ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት በተባለው መጽሐፍ ላይ ተንጸባርቋል። አንድ ተመራማሪ ከ12 እስከ 19 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 100 ተማሪዎች እንዲያነቡት ካደረገ በኋላ የተናገረው ሊጠቀስ የሚገባው ነው:- “በመጽሐፋችሁ ላይ የገለጻችሁት ዓይነት የሥነ ምግባር ደንብ ተግባራዊ ሊሆን የቻለበት ዘመን ይኖር ይሆናል። አሁን ግን መሥራቱን እጠራጠራለሁ። ይህ ትውልድ ከቀደሙት ትውልዶች ሁሉ ይበልጥ የሠለጠነ ነው።”

ይሁን እንጂ አዲሱን የሥነ ምግባር ደረጃ መያዝ ወጣቶችን ‘ይበልጥ የሰለጠኑ’ ያደረጋቸው መስሎ አይታየንም። በቅርቡ ከ13 እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ከ160,000 የሚበልጡ ወጣቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከወንዶቹ 41 በመቶና ከልጃገረዶቹ ደግሞ 21 በመቶ የሚሆኑት የፆታ ግንኙነት ፈጽመዋል። ከ16 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ የሆኑት ደግሞ ከአራቱ እጅ ወደ ሦስቱ እጅ የሚጠጉት ወንዶችና ከሴቶች ደግሞ ግማሽ የሚሆኑት የፆታ ግንኙነት ፈጽመዋል። ይሁን እንጂ ውጤቱ ምን ሆነ?

በኮረዳነት ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና እንደ ወረርሽኝ ተዛምቷል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ወጣት ሴቶች መካከል ከአሥሩ አንዷ ታረግዛለች። በዓመት 1,250,000 ወጣት ሴቶች ማለት ነው። ከእነዚህ ውስጥ 600,000 የሚያክሉት ሲወልዱ የቀሩት ያስወርዳሉ። እንደዚሁም በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በየዓመቱ አስፈሪ የሆነውን ኸርፐስ ጨምሮ በተለያየ የአባላዘር በሽታ ይለከፋሉ። ስለዚህ እነዚህን ማህበራዊ ሁኔታዎች ‘የመሠልጠን’ ውጤቶች እንደሆኑ አድርገን የማንመለከትበት ጥሩ ምክንያት አለ ብለን እናምናለን።

ጤናማ የሥነ ምግባር ደንቦች

ለወጣቶች ምን ዓይነት የሥነ ምግባር ደንቦች ማስተማር እንደሚገባ ብዙ አደናጋሪና የተዘበራረቀ አስተሳሰብ አለ። በዚህ ረገድ ግልጽ የሆነ ጠንካራ እምነት ባለመኖሩ መምህራን ያዝናሉ። አንዳንድ መምህራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ጤናማ የሥነ ምግባር ደንቦች ለተማሪዎቻቸው እንዲያስተምሩ የበለጠ ነፃነት ቢኖራቸው እንደሚመኙ እንገነዘባለን። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን ሥነ ምግባርን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው ትምህርቶች በእውነት ጤናማ ውጤት እንደሚያስገኙ እናምናለን።

ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ለወጣት ልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች ማስተማር የሚጀምሩት ቀደም ብለው ነው። ብዙውን ጊዜም ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት በሚለው መጽሐፍ ይጠቀማሉ። ከፈለጋችሁ ምሥክሮች የሆኑ ተማሪዎቻችሁ የዚህን መጽሐፍ ቅጂ ሊያመጡላችሁ ይችላሉ። ቀጥለው ከተዘረዘሩት የምንከተላቸው የሥነ ምግባር ደንቦች ጋር ያስተዋውቋችኋል።

ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነት:- ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነት ሁሉ ዝሙት በመሆኑ ፍጹም ስህተት እንደሆነ እናምናለን። ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” (1 ቆሮንቶስ 6:18) ‘ከዝሙት ራቁ’ በማለት ይናገራል። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የፆታ ግንኙነት አምላክን በመቃወም የሚሠራ ከባድ ወንጀል እንደሆነ እናምናለን። ቅዱሳን ጽሑፎች “አመንዝሮችን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” ይላሉ።​—ዕብራውያን 13:4፤ ራእይ 21:8

ግብረ ሰዶ:- ግብረ ሰዶም ትክክል ያልሆነ ምግባር እንደሆነ እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወንድና ሴት ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች የሚናገረውን አስተውሉ:- “እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ። እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ። ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ”​—ሮሜ 1:26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11

የአልኮል መጠጦች:- የአልኮል መጠጦች ምግብ ናቸው። ስለዚህ ተገቢ ቦታ ከተሰጣቸው ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። (መዝሙር 104:14, 15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚደረገው ሰዎች ያለ አግባብ ይጠቀሙባቸዋል። እኛም መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ እንደሚያሳስበው ለአልኮል መጠጦች ተገዥ መሆን ከባድ ሥነ ምግባራዊ ስህተት መሆኑን እናምናለን። (ምሳሌ 20:1፤ 23:29–35፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ባለ ሥልጣኖች ወጣቶች የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ በመከልከል ባንዳንድ አገሮች ያወጡትን ሕግ እናከብራለን። ከእነዚህም ሕጐች ጋር እንተባበራለን።

ዕፆች:- ለደስታ ተብለው የሚወሰዱ እንደ ሐሺሽ፣ ማሪዋና፣ ሄሮይን፣ ኮኬይን፣ ጫትና ትንባሆ የመሰሉትን አንወስድም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በማለት አጥብቆ ስለሚያሳስብ የይሖዋ ምሥክሮች የስሜት ደስታ ለማግኘት ብለው ሱስ በሚያሲዙ ወይም አእምሮ በሚያቃውሱ ነገሮች በመጠቀም ሰውነታቸውን ማበላሸት ስህተት መሆኑን ያምናሉ።​—2 ቆሮንቶስ 7:1

ጸያፍ አነጋገር:- ጸያፍ ንግግር ተገቢ እንዳልሆነ እናምናለን። ጸያፍ ንግግር “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ። የሚያሳፍር ነገርም፣ የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ ጋር አይስማማም።​—ኤፌሶን 5:3, 4

ባለ ሥልጣኖችን ማክበር:- ወጣቶቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ጋር በመስማማት የትምህርት ቤት ባለ ሥልጣኖችንና መምህራንን እንዲያከብሩ እንጠብቅባቸዋለን። (ሮሜ 13:1–7፤ 1 ጴጥሮስ 2:13–17) ወጣቶቻችንን በጥልቅ እንዲያከብሩት ያስተማርናቸው ይሖዋ አምላክ ታማኞች፣ እውነተኞችና ለሌሎች አሳቢዎች እንድንሆን ይነግረናል።​—ዕብራውያን 13:18፤ ቆላስይስ 3:9፤ ኤፌሶን 4:25፤ ማቴዎስ 7:12

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ጠቀሜታ

የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሥርዓቶች መከተል የአባሎቻችንን ሕይወት በጣም እንዳሻሻለው አይተናል። ችግሮች የሚያጋጥሙንና ልጆቻችንም ፍጹማን ባይሆኑም በአብዛኛው እንደ ስርቆት፣ ውሸት፣ ማታለልና ሌሎችን እንደ መጉዳት ከመሳሰሉ መጥፎ ድርጊቶች ተላቅቀናል። እኛና ልጆቻችን የአምላክን ሕግ በታዘዝን መጠን እንደ ወረርሽኝ በተስፋፉት የአባለዘር በሽታዎች፣ ለጋብቻ ከመድረሳቸው በፊት ዲቃላ በሚወልዱ እናቶች፣ በዲቃላ ልጆችና ውርጃዎች ከመሠቃየትና በኅሊና መረበሽና በሐዘን ከመጨነቅ ነፃ ሆነናል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆን አዳምስ መጽሐፍ ቅዱስን “በዓለም ካሉት መጽሐፎች ሁሉ የበለጠ መጽሐፍ” ማለታቸው ትክክል ነው ብለን እናምናለን። ፕሬዘዳንት አብርሃም ሊንከንም መጽሐፍ ቅዱስን ከተቀበልክ “ይበልጥ ደስተኛና የተሻልክ ሰው ሆነህ ለመኖርና ለመሞት ትችላለህ” ማለታቸው ትክክል ነበር ብለን እናምናለን።

ሆኖም እንደምታውቁት ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ አታድርጉ ብሎ የሚከለክለውን እንዲያደርጉ ማለትም “ወደ መዳራት ብዛት እንዲሮጡ” እኩዮቻቸው ተጽዕኖ ያደርጉባቸዋል። አንዳንዶች በተጽዕኖው ለመሸነፍ እምቢተኞች ሲሆኑ እኩዮቻቸው “እየተሳደቡ ይደነቃሉ።” (1 ጴጥሮስ 4:4) ወጣቶቻችን ከጋብቻ በፊት በሚደረግ የፆታ ግንኙነት ወይም በመሳሰሉት ተግባሮች ስለማይካፈሉ አንዳንድ ጊዜ ይሾፍባቸዋል። እንዲያውም ይሳቅባቸዋል። ስለዚህ መምህራን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ደንቦች አክብረው ለመኖር ለሚጥሩት ወጣቶቻችን ማበረታቻ በመስጠት የልጆቻችንን ጥረት ሲደግፉ ደስ ይለናል።

የወጣቶቻችን ምግባር በመጽሐፍ ቅዱስ የተገደበ በመሆኑ ምክንያት የቀረባቸው ነገር እንዳለ ሆኖ እንደማይሰማቸው ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። እንዲያውም አንድ ወጣት የራሱን ሕይወት ከሌሎች የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሕይወት ጋር በማወዳደር “የቀረብኝ ነገር ቢኖር ብዙ ችግር ብቻ ነው” ብሏል። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ያወጣቸው ሕጎችና ደንቦች እኛን ከመጥፎ ነገር ለመጠበቅ የተሰጡ ስለሆኑ ብንታዘዛቸው ብዙ ጥቅም እንደምናገኝ እናምናለን።​—መዝሙር 19:7–11

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘መጽሐፍ ቅዱስን በመቀበል ይበልጥ ደስተኛና የታሻልክ ሰው ሆነህ ለመኖርና ለመሞት ትችላለህ።’​—አብርሃም ሊንከን

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጠባያችን በሥነ ምግባር ደንቦች እንዴት እንደሚነካ የሚገልጽ መጽሐፍ። ምሥክሮች የሆኑ ወላጆች ይህንን መጽሐፍ ልጆቻቸውን ለማስተማር ይጠቀሙበታል።