በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክፍል ትምህርት

የክፍል ትምህርት

የክፍል ትምህርት

የይሖዋ ምሥክሮች አመለካከት በትምህርታቸው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ሌላው መስክ ሥርዓተ ትምህርቱ ነው። ስለዚህ ልጆቻቸው ምን መማር እንዳለባቸው የመምረጥ ኃላፊነት ያላቸው ወላጆች ናቸው ብለን ስለምናምን እዚህ ላይ የቀረበው ማብራሪያ በመምህራንና ምሥክሮች በሆኑ ወላጆች መካከል መግባባትና ጥሩ ትብብር እንዲኖር ለመርዳት ታስቦ የቀረበ ነው።

ሃይማኖትና ጸሎት:- አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በክፍል ውስጥ በሚሰጧቸው ትምህርቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርት ይጨምራሉ። በአንድ ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ ወላጆች ልጆቻቸው ከካቶሊክ፣ ከፕሮቴስታንት ወይም ከአይሁድ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች የትኛውን እንደሚመርጡ ይጠይቁ ነበር። ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመማር ያልተመዘገበ ልጅ ሃይማኖታዊ ትምህርት ከሚሰጥበት ክፍል እንዲወጣና በሌላ ቦታ ሆኖ ዓለማዊ ትምህርት እንዲከታተል ይፈቀድለት ነበር። ይሁን እንጂ በ1948 የአገሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚከተለውን ድንጋጌ አውጥቷል:-

“የመጀመሪያው ማሻሻያ የተመረኰዘው ሃይማኖትና መንግሥት እያንዳንዳቸው ከፍተኛ የሆነውን ዓላማቸውን ለማከናወን የሚችሉት አንዳቸው ከሌላው ሲነጠሉና ነፃ ሲሆኑ ነው በሚለው ሐሳብ ላይ ነው። . . . የመጀመሪያው ማሻሻያ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መሐል ከፍ ያለና ሊጣስ የማይገባው ግድግዳ አቁሟል።” ማክኮለም ቪ. ቦርድ ኦቭ ኤዱኬሽን (1948)

ቆየት ብሎም ሰኔ 17, 1963 የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሕዝብ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይነበብና እንዳይጸለይ ከልክሏል። ጀስቲስ ብሪናን አስተያየታቸውን ሲሰጡ “የፌዴራላዊውና የክልል ሕገ መንግሥታችን መንፈስ ከመጀመሪያው ጀምሮ . . . የልጆችን ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚመለከቱ ውሳኔዎች ለወላጆች እንዲተው ነው” ብለዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ለልጆቻቸው ሃይማኖታዊ ትምህርት መስጠት የወላጆች ኃላፊነት መሆን እንደሚገባው ይስማማሉ። ስለዚህ ምሥክር ወላጆች በክፍል ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ ልጆቻቸው ከክፍሉ እንዲወጡ እንዲፈቀድላቸው ይጠይቃሉ። ሃይማኖታዊ ትምህርቱ በምስሎች ፊት ተንበርክኮ ወይም አጐንብሶ መስገድን የመሳሰሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆኑ የምንቆጥራቸውን የአምልኰ ሥርዓቶች የሚጨምር ከሆነ ምሥክር ወላጆች ይህን ድርጊት በምንም ዓይነት አይፈቅዱም።

በሌላ በኩል ግን በክፍል ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ወደ አንድ ወገን የማያደላና ስለ ተለያዩ ሃይማኖቶች ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚደረግ ጥናት ከሆነ ተቃውሞ የላቸውም። ስለዚህ አንድ ትምህርት ቤት የተማሪዎቹን እምነት ለመለወጥ ሳይሆን ስለዚያ ሃይማኖት ለማሳወቅ የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚወክሉ ሰዎች ንግግር እንዲያደርጉ ዝግጅት ቢያደርግ ምሥክሮች የሆኑ ተማሪዎች በአክብሮት ያዳምጣሉ። የይሖዋ ምሥክሮችም በተመሳሳይ ሁኔታ በትምህርት ቤት ንግግር እንዲያደርጉ ቢጋበዙ በደስታ እምነታቸውን የሚገልጽ ንግግር ይሰጣሉ።

በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የጌታ ጸሎት ወይም አባታችን ሆይ መደበኛ ፕሮግራም ተይዞለት ይደገማል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጸሎት የሚቀበሉት ቢሆንም ጸሎቱ በሚደገምበት የአምልኮ ሥርዓት አይካፈሉም። ምክንያቱም ኢየሱስ ይህንን የናሙና ጸሎት ባስተማረበት ጊዜ “አትድገሙ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ማቴዎስ 6:7, 8) በዚህ የጸሎት ፕሮግራም የማንካፈልበት ሌላው ምክንያት የተለያዩ ሃይማኖቶች በሚያደርጉት ማንኛውም ዓይነት የጋራ ጸሎት ስለማንካፈል ነው።

የጾታ ትምህርት:- የጤናና የንጽሕና አጠባበቅ ትምህርቶች ከቀድሞ ጀምሮ በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ይሰጣሉ። እነዚህ ትምህርቶች ንጽሕና በጣም ጠቃሚ ስለመሆኑ፣ በሽታን ስለመከላከል፣ ስለ ልጆች እንክብካቤ፣ ስለ ቤተሰብ ኃላፊነትና ወዘተ በማስተማር በጣም ጠቃሚ እውቀት የሰጡ መሆናቸውን እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ትምህርት ቤቶች ስለ ፅንስ ቁጥጥር፣ የራስን ብልት በማሻሸት የጾታ እርካታ ስለ ማግኘት፣ ስለ ግብረ ሰዶም፣ ፅንስ ስለ ማስወረድና ስለመሳሰሉት የጾታ ጉዳዮች ግልጽ ትምህርት እየሰጡ ነው።

በአጠቃላይ የጾታ ትምህርት የሚሰጠው ያለምንም የሥነ ምግባር አመራር ነው። እንዲያውም አስተማሪዎቹ ራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደረጃዎች መንቀፋቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። ስለዚህ ምሥክር ወላጆች በጾታ የትምህርት ክፍሎች የሚሰጠው ትምህርት በጣም ያሳስባቸዋል።

አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሚገለገሉበት ድሬንግ ኦግ ፒገ፣ ማንድ ኦግ ክቭንደ (ወንዶች ልጆችና ልጃገረዶች፣ ወንዶችና ሴቶች) የተባለ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ ግለሰብ የሌሎችን መብት እስካልተጋፋ ድረስ ያለምንም የዕድሜና የጾታ ልዩነት፣ በፈለገበት መንገድ የጾታ ፍላጎቱን የማርካት መብት ሊኖረው ይገባል” ይላል። ይኸው መጽሐፍ ከእንስሳት ጋር ሩካቤ ሥጋ ስለ መፈጸም “በዚህ አገር (በዴንማርክ) የጾታ ፍላጎትን በዚህ መንገድ ማርካት ሕጋዊ ነው” ይላል። ሆኖም ለእሥራኤል የተሰጠው የአምላክ ሕግ “ከእንስሳ ጋር የሚተኛ ማንኛውም ሰው ይገደል” ይላል።—ዘጸአት 22:19

ቀደም ሲል ጠበቅ ተደርጎ እንደተገለጸው የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተልና እነዚህንም መሠረታዊ ሥርዓቶች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ ለመትከል ይጥራሉ። ስለዚህ ልጆቻቸው እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከማያከብሩ ሰዎች የጾታ ትምህርት እንዲሰጣቸው አይፈልጉም። በመሆኑም የልጆቻቸው አእምሮ እቤት ውስጥ የሚማሯቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚጻረሩ ሐሳቦች ወይም ሥዕላዊ ትምህርቶች በመታጠብ ላይ እንዳለ ከተሰማቸው የጾታ ትምህርት በሚሰጥባቸው ክፍሎች እንዳይገቡ ሊጠይቁ ይችላሉ።

ሳይንስና ዝግመተ ለውጥ:- የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሳይንስ ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። በዙሪያችን ስላለው ዓለም ያለን ግንዛቤ በጣም እንዲጨምር ላስቻሉን ትጉህ ሳይንቲስቶች አክብሮት አላቸው። ወጣቶቻችን የተለያዩትን የሳይንስ ዘርፎች እንዲማሩ እናበረታታቸዋለን። ምክንያቱም ከዚህ የሚያገኙት እውቀት ለፈጣሪያችን ጥበብና ኃይል ያላቸውን አድናቆት ይጨምርላቸዋል።

ይሁን እንጂ ሳይንስ ነው የሚባለው ሁሉ እውነት ላይሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ እንደ ሳይንሳዊ ሐቅ ተደርገው የሚተላለፉ እንደ ዝግመተ ለውጥ የመሳሰሉ ንድፈ ሐሳቦችም አሉ። ዝግመተ ለውጥ የመጀመሪያው ሕይወት ያለው ነገር የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገር ነው፤ ከዚያም ይህ ሕይወት ያለው ነገር ሲዋለድ ዘሮቹ እየተለወጡ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ሕይወት ያላቸውን ነገሮች አስገኘ ይላል።

የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ንድፈ ሐሳብ እውነት ነው ብለው አያምኑም። ወይም ደግሞ መላው ፍጥረት ቃል በቃል በሰባት ቀናት ብቻ ተፈጥሮ አለቀ የሚል እምነት የለንም። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት እንዲሁም ሌሎቹ ሕያው ፍጥረታት በሙሉ በአምላክ እንደተፈጠሩ እናምናለን። ስለዚህ ሕይወት ስላላቸው ነገሮች አመጣጥ ስለሚገልጹ ንድፈ ሐሳቦች ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ መምህራን የምሥክር ወጣቶቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ቢያከብሩላቸው በጣም ደስ ይለናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ እምነታቸው ከሳይንሳዊ ጭብጦች ጋር እንደሚስማማ እናምናለን። ይህን ለማወቅ ከፈለጋችሁ ምሥክር ወጣቶቻችን ስለ እምነታቸው በደስታ ያስረዷችኋል።

ሙዚቃና የኪነ ጥበብ ትምህርት:- የይሖዋ ምሥክሮች የሙዚቃ ወይም የሥነ ጥበብ ትምህርት ራሱ ስህተት ነው ብለው አያምኑም። ይሁን እንጂ ምሥክር ወጣቶች ከሃይማኖታዊ ወይም የአርበኝነት ስሜት ከሚቀሰቅሱ በዓሎች ጋር ግንኙነት ባለው ማንኛውም ዓይነት ሙዚቃና ኪነ ጥበብ አይሳተፉም። በትምህርት ቤት በሚሰጥ የሙዚቃ ትምህርት በመካፈል ረገድ ግን ምሥክር ወጣቶችና ወላጆቻቸው ከግምት ሊያስገቧቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ።

ለምሳሌ ያህል ትምህርቱ የት፣ በምን ሁኔታ እንደሚሰጥና የሚጫወቱት ሙዚቃ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ያጤናሉ። ትምህርቱ በፖለቲካዊ ወይም በሃይማኖታዊ በዓሎች ላይ በሚጫወት የሙዚቃ ጓድ ውስጥ ማገልገልን የሚጨምር ከሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር ሊሳተፍበት አይችልም። ምሥክሮች የሆኑ ተማሪዎች በልምምድ ክፍለ ጊዜም እንኳን ቢሆን ብሔራዊ መዝሙር ወይም ከሃይማኖት ወይም ከብሔራዊ በዓላት ጋር ግንኙነት ያላቸውን መዝሙሮች አይጫወቱም። ሊታሰብበት የሚገባው ሌላ ጉዳይ የሚወስደው ጊዜና ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለቤተሰብ እንቅስቃሴዎች መሰናክል መሆንና አለመሆኑ ነው።

የጦር ትምህርት:- በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ወታደራዊ ትምህርት ይሰጣቸል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ። ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም። ከእንግዲህ ወዲህ ሰልፍ [ጦርነት አዓት] አይማሩም” ብሎ ከሚናገርላቸው ሰዎች መካከል ለመሆን ይፈልጋሉ። (ኢሳይያስ 2:4) ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በትምህርት ቤት ወታደራዊ ሥልጠና ከሚሰጥባቸው ትምህርቶች ነፃ እንዲሆኑ ይጠይቃሉ።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “በተቻላችሁ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ይላል። (ሮሜ 12:18) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ሥራ ላይ ማዋላችን ስለ ሌላ ዓይነት የውትድርና ጥበቦች ያለንን አመለካከትም ይነካል። እነዚህም እንደ ጁዶ፣ ካራቴና ኬንዶ እንዲሁም እንደ ቦክስና ነፃ ትግል የመሳሰሉት ወታደራዊ ጥበቦች ናቸው። እነዚህ ወታደራዊ ልምምዶች ተራ ስፖርት ናቸው ቢባሉም እንደነዚህ ያሉትን ወታደራዊ ጥበቦች መለማመድ ለውጊያ ወይም በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ መሠልጠን እንደሆነ አድርገን እንመለከታለን። በዚህ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ባሉት የውትድርና እንቅስቃሴዎች አይካፈሉም። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወጣቶች በእነዚህ ከመካፈል ነፃ እንዲሆኑ ቢጠይቁም በሌሎች መደበኛ የትምህርት ጊዜያት በሚሰጡ የአካል ማሠልጠኛ ፕሮግራሞች በተቻለ መጠን በደስታ ይተባበራሉ።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወጣቶቻችን የተለያዩትን የሳይንስ ዘርፎች እንዲማሩ እናበረታታቸዋለን