ማስጠንቀቂያውን መስማታቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል
ማስጠንቀቂያውን መስማታቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል
ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረውን ቤተ መቅደስ ማዕከል ያደረገው የአይሁድ ሥርዓት እንደሚጠፋ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር። ጥፋቱ የሚመጣበትን ቀን ለይቶ አልጠቀሰም። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት መቃረቡን የሚጠቁሙ ክስተቶችን ገልጾ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁኔታ በንቃት እንዲጠባበቁና ከአደጋው ቀጣና እንዲወጡ አሳስቧቸዋል።
ኢየሱስ “ኢየሩሳሌም በጦር ሰራዊት ተከባ በምታዩበት ጊዜ፣ ጥፋቷ መቃረቡን ዕወቁ” ሲል ተንብዮአል። በተጨማሪም “‘የጥፋት ርኩሰት’ በተቀደሰው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ . . . በዚያን ጊዜ በይሁዳ የሚገኙ ወደ ተራራዎች ይሽሹ” ሲል ተናግሯል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ንብረታቸውን ለማዳን ወደኋላ እንዳይመለሱ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከፈለጉ በአፋጣኝ መሸሽ ነበረባቸው።—ሉቃስ 21:20, 21፤ ማቴዎስ 24:15, 16
ሴስትየስ ጋለስ ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የአይሁዶች ዓመፅ ለማዳፈን በ66 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮማን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ አዘመተ። ወደ ከተማዋ ዘልቆ በመግባት ቤተ መቅደሱን እስከ መክበብ ደርሶ ነበር። በከተማዋ ብጥብጥ ነግሦ የነበረ ሲሆን ሁኔታውን በንቃት ይከታተሉ የነበሩት ሰዎች ጥፋት መቃረቡን ማስተዋል ችለዋል። ይሁንና ማምለጥ የሚቻልበት ሁኔታ ነበርን? ሴስትየስ ጋለስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወታደሮቹ ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ዓማፅያን የሮማ ወታደሮችን አሳደዱ። ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ለመሸሽ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።
በቀጣዩ ዓመት በቬስፔዢያን እና በልጁ በቲቶ የሚመራ የሮማ ሠራዊት ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። መላ አገሪቱ በጦርነት ታመሰች። በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጀመሪያ ላይ የሮማ ወታደሮች በኢየሩሳሌም ከተማ ዙሪያ ምሽግ ሠሩ። ከተማዋ ዙሪያዋን በወታደሮች በመታጠሯ ምንም ማምለጫ ቀዳዳ አልነበረም። (ሉቃስ 19:43, 44) በከተማዋ ውስጥ ያሉ የተለያዩ አንጃዎች እርስ በርስ ተጨፋጨፉ። የቀሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ በሮማውያን ወታደሮች ተገድለዋል አሊያም ተማርከዋል። ከተማዋም ሆነች ቤተ መቅደሷ እንዳልነበሩ ሆኑ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንደዘገበው ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያን ተጨፍጭፈዋል። ቤተ መቅደሱም ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አልተገነባም።
በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ክርስቲያኖች በዚያው
በኢየሩሳሌም ውስጥ ቢሆኑ ኖሮ እንደ ሌሎቹ አይሁዳውያን የመገደል ወይም የመማረክ ዕጣ ይገጥማቸው ነበር። ሆኖም የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች እንደዘገቡት ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በመስማት ከኢየሩሳሌምም ሆነ ከመላው የይሁዳ ግዛት በመውጣት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ ወደሚገኙ ተራሮች ሸሽተው ነበር። አንዳንዶቹ በፔሪያ አውራጃ በምትገኘው በፔላ ሰፈሩ። ከይሁዳ ከወጡ በኋላ ፈጽሞ ወደዚያ አልተመለሱም። ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ መስማታቸው ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።ተአማኒነት ያላቸው ምንጮች የሚሰጡትን ማስጠንቀቂያ ሰምተህ እርምጃ ትወስዳለህ?
በየጊዜው ስለተለያዩ ነገሮች የሚሰጡ ማስጠንቀቂያዎች እንደተባለው ሆነው ስለማይገኙ ብዙ ሰዎች ሁሉንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ችላ የማለት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ይሁን እንጂ ማስጠንቀቂያዎችን መስማት ሕይወትህን ሊያተርፍልህ ይችላል።
በ1975 በቻይና የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚከሰት አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር። ባለ ሥልጣናት ሕዝቡ አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ መመሪያ ሰጡ። ሕዝቡ ማስጠንቀቂያውን ሰምቶ እርምጃ በመውሰዱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወት ሊተርፍ ችሏል።
በሚያዝያ 1991 በፊሊፒንስ በፒናቱቦ ተራራ ግርጌ የሚኖሩ ሰዎች ተራራው እንፋሎትና አመድ መትፋት እንደጀመረ አሳወቁ። የፊሊፒንስ የእሳተ ገሞራና የምድር ነውጥ ምርምር ተቋም ለሁለት ወራት ሁኔታውን ሲከታተል ከቆየ በኋላ ከፍተኛ አደጋ እንደሚከሰት ማስጠንቀቂያ ሰጠ። ወዲያውኑ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደረገ። ሰኔ 15 ማለዳ ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ የተከሰተ ሲሆን ከስምንት ክዩቢክ ኪሎ ሜትር የሚበልጥ አመድ ወደ ሰማይ ከተወረወረ በኋላ ተመልሶ አካባቢውን ሁሉ አለበሰው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሰምተው እርምጃ በመውሰዳቸው ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ያለንበት ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ ያስጠነቅቃል። በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን ውስጥ ነው። እየቀረበ ያለውን የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በንቃት እየተከታተልክ ነው? ከአደጋው ቀጣና ለመውጣት እርምጃ በመውሰድ ላይ ነህ? ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ በማሰማት ላይ ነህ?
[ገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፒናቱቦ ተራራ የእሳተ ገሞራ አመድ መትፋት በጀመረበት ጊዜ ብዙዎች የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ በመውሰዳቸው ሕይወታቸውን አትርፈዋል
[ገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ የሰሙ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን አትርፈዋል