በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ወደ ፈተና እንዳትገቡ”

“ወደ ፈተና እንዳትገቡ”

“ወደ ፈተና እንዳትገቡ”

“ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ሳታቋርጡ ጸልዩ።”​—ማቴዎስ 26:41 NW

ከምንጊዜውም ይበልጥ ተጨንቋል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ ሕይወቱ የሚያበቃበት ጊዜ ተቃርቧል። ኢየሱስ የሚያዝበት፣ ሞት የሚፈረድበትና በእንጨት ላይ የሚሰቀልበት ጊዜ እንደተቃረበ አውቋል። እያንዳንዱ የሚያደርገው ውሳኔም ሆነ የሚወስደው እርምጃ በአባቱ ስም ላይ የሚያስከትለው ውጤት እንዳለ ተገንዝቧል። በተጨማሪም የሰው ዘር የወደፊት ተስፋ በእሱ እጅ ላይ እንደወደቀ ያውቃል። ይህ ሁሉ ነገር ሲያስጨንቀው ምን አድርጎ ይሆን?

2 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ሄደ። ይህ የአትክልት ሥፍራ ኢየሱስ አዘውትሮ የሚሄድበት ቦታ ነበር። በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ነጠል ብሎ በመሄድ ሰማያዊ አባቱ ብርታት እንዲሰጠው በመለመን ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረበ። ይህን ጸሎት ያቀረበው አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሦስት ጊዜ ነበር። ፍጹም የነበረ ቢሆንም እንኳ የገጠመውን ፈታኝ ሁኔታ በራሱ እንደሚወጣው አድርጎ አላሰበም።—ማቴዎስ 26:36-44

3 በዛሬው ጊዜ እኛም ብዙ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በዚህ ብሮሹር መግቢያ ላይ እንደተመለከትነው በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ዘመን ላይ ነው። የሰይጣን ዓለም የሚያመጣብን ፈተናና የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። እውነተኛውን አምላክ አገለግላለሁ የሚል ማንኛውም ሰው የሚያደርገው ውሳኔም ሆነ የሚፈጽመው ድርጊት በአምላክ ስም ላይም ሆነ በወደፊት ሕይወት ተስፋው ላይ የሚያስከትለው ውጤት ይኖራል። ይሖዋን እንወደዋለን። በመሆኑም ‘እስከ መጨረሻው መጽናት’ እንፈልጋለን፤ ይህም እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ አሊያም እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 24:13) ይሁንና ሁልጊዜ በጥድፊያ ስሜት ማገልገልና ነቅተን መጠባበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በዚያን ጊዜ የነበሩትም ሆኑ በዛሬው ጊዜ ያሉት ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ተጽዕኖዎች እንደሚገጥሟቸው ስለተገነዘበ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ሳታቋርጡ ጸልዩ” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (ማቴዎስ 26:41 NW) እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ ለእኛ ምን መልእክት አላቸው? ምን ፈተናዎች ያጋጥሙሃል? ‘ነቅተህ መጠበቅ’ የምትችለውስ እንዴት ነው?

ምን ፈተናዎች ያጋጥሙሃል?

5 ሁላችንም በየዕለቱ ‘በዲያብሎስ ወጥመድ’ ውስጥ እንድንወድቅ የሚገፋፉ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:26) ሰይጣን የይሖዋን አገልጋዮች ዋነኛ ዒላማ እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። (1 ጴጥሮስ 5:8፤ ራእይ 12:12, 17) ይህን የሚያደርገው ለምንድን ነው? ዋነኛ ዓላማው እኛን መግደል ላይሆን ይችላል። ለአምላክ ታማኝ ሆነን ብንሞት ሰይጣን እንደ ድል አይቆጥረውም። ምክንያቱም ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በትንሣኤ እንደሚያስነሳን ያውቃል።—ሉቃስ 20:37, 38

6 ሰይጣን ሕይወታችንን ከማጥፋት ይልቅ አምላክን እንድንክድ ቢያደርግ ይበልጥ ይደሰታል። ይሖዋን እንድንተው ማድረግ እንደሚችል ለማሳየት ሲል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። በመሆኑም ምሥራቹን መስበካችንን እንድናቆም ወይም የአምላክን መሥፈርቶች እንድንጥስ ማድረግ ቢችል ለእሱ ትልቅ ድል ነው! (ኤፌሶን 6:11-13) ስለዚህም “ፈታኙ” እኛን ለማጥመድ ሲል የተለያዩ ፈተናዎችን ያቀርባል።—ማቴዎስ 4:3

7 ሰይጣን የተለያዩ “የማታለያ ዘዴዎች” ይጠቀማል። (ኤፌሶን 6:11 ጂውሽ ኒው ቴስታመንት) በፍቅረ ነዋይ ወይም በተድላ እንድንታለል፣ በፍርሃት እንድንሸነፍ አሊያም ጥርጣሬ እንዲያድርብን ለማድረግ ይሞክር ይሆናል። ሆኖም በጣም ውጤታማ ሆነው ካገኛቸው ዘዴዎች አንዱ ተስፋ ማስቆረጥ ነው። የተስፋ መቁረጥ ስሜት በመንፈሳዊ እንድንደክምና በቀላሉ በፈተና እንድንወድቅ ሊያደርገን እንደሚችል ስለሚያውቅ ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም አድብቶ ይጠብቃል። (ምሳሌ 24:10) ስለዚህ ስሜታችን በሚደቆስበት ጊዜ በፈተና እንድንሸነፍና እጅ እንድንሰጥ ለማድረግ ይሞክራል።—መዝሙር 38:8

8 ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየተቃረብን በሄድን መጠን ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች እየጨመሩ ይሄዳሉ። እነዚህ ነገሮች በእኛም ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። (“ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ተስፋ ከቆረጥን ኃይላችን ሊሟጠጥ ይችላል። በአካል፣ በአእምሮም ሆነ በስሜት ከዛልክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በስብከቱ ሥራ ለመካፈልም ሆነ ሌሎች መንፈሳዊ ግዴታዎችን ለማከናወን ‘ጊዜ መዋጀት’ አዳጋች ሊሆንብህ ይችላል። (ኤፌሶን 5:15, 16) ሰይጣን እነዚህን ነገሮች እርግፍ አድርገህ እንድትተው እንደሚፈልግ አትዘንጋ። ይሁን እንጂ ይህ ያለንበት ወቅት ቅንዓትህን የምትቀንስበት ወይም በጥድፊያ ስሜት ከማገልገል ወደኋላ የምትልበት ጊዜ አይደለም! (ሉቃስ 21:34-36) ሰይጣን የሚያቀርባቸውን ፈተናዎች መቋቋምና ነቅተህ መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችልባቸውን አራት መንገዶች ተመልከት።

‘ሳታቋርጥ ጸልይ’

9 ይሖዋ እንደሚረዳህ በመተማመን ወደ እሱ ጸልይ። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ያደረገውን አስታውስ። በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ በገጠመው ጊዜ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ‘ላቡ እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር እስኪፈስ’ ድረስ ወደ ይሖዋ አጥብቆ ጸልዮአል። (ሉቃስ 22:44) እስቲ አስበው። ኢየሱስ ሰይጣንን በሚገባ ያውቀዋል። ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች ለማጥመድ ሲጠቀምባቸው የቆዩትን የማታለያ ዘዴዎች በሙሉ ሰማይ ሆኖ ሲመለከት ኖሯል። ያም ሆኖ ሰይጣን የሚያቀርብለትን ማንኛውንም ፈተና በቀላሉ ልወጣው እችላለሁ ብሎ አላሰበም። ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ እርዳታና ብርታት ለማግኘት ወደ ይሖዋ መጸለይ እንደሚያስፈልገው ከተሰማው እኛማ ምን ያህል መጸለይ እንደሚያስፈልገን መረዳት አያዳግተንም!—1 ጴጥሮስ 2:21

10 በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ‘ሳያቋርጡ እንዲጸልዩ’ ካሳሰባቸው በኋላ “መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው” ሲል እንደተናገረ አስታውስ። (ማቴዎስ 26:41) ኢየሱስ ስለ ማን ሥጋ መናገሩ ነበር? ስለ ራሱ ሥጋ መናገሩ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤ ፍጹም የሆነው ሰብዓዊ ሥጋው ምንም ዓይነት ድክመት የለበትም። (1 ጴጥሮስ 2:22) የደቀ መዛሙርቱ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አለፍጽምናንና የኃጢአት ዝንባሌን የወረሱ በመሆናቸው ፈተናን ለመቋቋም ከኢየሱስ ይበልጥ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ሮሜ 7:21-24) እነሱም ሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ፈተናን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት እንዲጸልዩ አጥብቆ ያሳሰበው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 6:13) ይሖዋ እንዲህ ላሉ ጸሎቶች መልስ ይሰጣል። (መዝሙር 65:2) እንዴት? ቢያንስ ሁለት መንገዶች አሉ።

11 በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ ፈተናዎቹን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። ሰይጣን የሚያቀርባቸው ፈተናዎች በጨለማ ውስጥ በተለያየ ቦታ እንደተቀመጡ ወጥመዶች ናቸው። ካላየሃቸው ድንገት ወጥመዶቹ ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች አማካኝነት የሰይጣንን ወጥመዶች እንድናያቸውና ራሳችንን ከአደጋ እንድንጠብቅ ይረዳናል። ሰውን መፍራት፣ የጾታ ብልግና፣ ፍቅረ ነዋይና ሰይጣን የሚያቀርባቸው ሌሎች ፈተናዎች ወጥመድ እንዳይሆኑብን ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ ጽሑፎችና ትልልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ማሳሰቢያ ሲሰጠን ቆይቷል። (ምሳሌ 29:25፤ 1 ቆሮንቶስ 10:8-11፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ይሖዋ የሰይጣንን ወጥመዶች ለይተህ እንድታውቅ ለሚያደርግልህ እርዳታ አመስጋኝ ነህ? (2 ቆሮንቶስ 2:11) ይህ ሁሉ ማስጠንቀቂያ የሰይጣንን ፈተና ለመቋቋም እንዲረዳህ ለምታቀርበው ጸሎት መልስ ነው።

12 በሁለተኛ ደረጃ ይሖዋ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንድናገኝ በማድረግ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር . . . ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ . . . መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) አምላክ ምንጊዜም በእሱ እስከታመን ድረስ ካለን መንፈሳዊ አቅም በላይ የሆነ ከባድ ፈተና እንዲደርስብን አይፈቅድም። ‘መውጫ መንገዱን የሚያዘጋጅልን’ እንዴት ነው? “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን” ይሰጣል። (ሉቃስ 11:13) ይህ የአምላክ መንፈስ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በወሰድነው ቁርጥ አቋም እንድንጸናና ማስተዋል የተሞላባቸውን ውሳኔዎች ማድረግ እንድንችል የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል። (ዮሐንስ 14:26፤ ያዕቆብ 1:5, 6) መጥፎ ዝንባሌዎችን ማሸነፍ የሚያስችሉ ግሩም ባሕርያትን እንድናንጸባርቅ ሊረዳን ይችላል። (ገላትያ 5:22, 23) አልፎ ተርፎም የአምላክ መንፈስ በሌሎች የእምነት ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ‘ሊያጽናናን’ ወይም ሊያበረታን ይችላል። (ቆላስይስ 4:11) ይሖዋ ለምታቀርበው ጸሎት እንዲህ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መልስ የሚሰጥህ መሆኑ እንድታመሰግነው አይገፋፋህም?

ለጸሎትህ የምትጠብቀው መልስ ምክንያታዊ ይሁን

13 ነቅተን መጠበቅ የምንፈልግ ከሆነ ለጸሎታችን የምንጠብቀው መልስ ምክንያታዊ መሆን አለበት። ማናችንም ብንሆን በኑሮ ተጽዕኖዎች ምክንያት አንዳንድ ጊዜ ልንዝል እንችላለን። ሆኖም አምላክ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት ትኖራላችሁ ብሎ ቃል አልገባልንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች እንኳ ሳይቀሩ ስደትን፣ ድህነትን፣ የመንፈስ ጭንቀትንና በሽታን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ደርሰውባቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 8:1፤ 2 ቆሮንቶስ 8:1, 2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23

14 በዛሬው ጊዜ ያለነው የአምላክ አገልጋዮችም መከራ ይደርስብናል። ስደት ሊደርስብን፣ የገንዘብ ችግር ሊያጋጥመን፣ የመንፈስ ጭንቀት ሊይዘን፣ ልንታመምና ሌሎች ችግሮች ሊደርሱብን ይችላሉ። ይሖዋ ምንም ዓይነት መከራ እንዳይደርስብን በተአምራዊ መንገድ የሚጠብቀን ቢሆን ኖሮ ሰይጣን ላስነሳው ክርክር እንዴት መልስ መስጠት ይቻል ነበር? (ምሳሌ 27:11) ይሖዋ አገልጋዮቹ ፈተና እንዲደርስባቸው ይፈቅዳል፤ እንዲያውም አንዳንዴ በተቃዋሚዎች እጅ እንዲገደሉ ሊፈቅድ ይችላል።—ዮሐንስ 16:2

15 ታዲያ ይሖዋ ቃል የገባልን ምንድን ነው? ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሙሉ በሙሉ በእሱ እስከታመንን ድረስ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። (ምሳሌ 3:5, 6) በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግልናል፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና እስካልተበላሸ ድረስ ብንሞት እንኳ አሸናፊዎች ነን። ምንም ነገር፣ ሞትም እንኳ ቢሆን አምላክ ታማኝ ለሆኑ አገልጋዮቹ ቃል የገባውን ሽልማት እንዳይሰጥ ሊያግደው አይችልም። (ዕብራውያን 11:6) እየቀረበ ባለው አዲስ ዓለም ደግሞ ይሖዋ ለሚወዱት ሁሉ አስደናቂ በረከቶችን ለማፍሰስ የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጽም ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝሙር 145:16

የተነሱትን አከራካሪ ጉዳዮች አስታውስ

16 እስከ መጨረሻው ለመጽናት አምላክ ክፋትን እንዲፈቅድ ምክንያት የሆኑትን አከራካሪ ጉዳዮች ማስታወስ አለብን። አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥሙን ችግሮች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ ሲሰማንና አምላክን ማገልገላችንን እንድንተው ስንፈተን ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት በተመለከተ ያነሳውን ክርክር ማስታወሳችን ይጠቅመናል። በተጨማሪም ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች የታማኝነት አቋም በተመለከተ ጥያቄ አንስቷል። (ኢዮብ 1:8-11፤ 2:3, 4) እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮችና ይሖዋ ለእነዚህ ጉዳዮች እልባት ለማስገኘት የመረጠው መንገድ ከእኛ ደኅንነት የላቀ ግምት የሚሰጣቸው ነገሮች ናቸው። እንዴት?

17 አምላክ ለተወሰነ ጊዜ መከራ እንዲደርስብን በመፍቀዱ ሌሎች እውነትን መስማት የሚችሉበት አጋጣሚ አግኝተዋል። ኢየሱስ መከራ የተቀበለው እኛ ሕይወት እንድናገኝ ብሎ መሆኑን አስታውስ። (ዮሐንስ 3:16) ለዚህ አመስጋኞች አይደለንም? ይሁንና ሌሎችም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ለተወሰነ ጊዜ የሚደርሱብንን ችግሮች ችለን ለመኖር ፈቃደኞች ነን? እስከ መጨረሻው ለመጽናት የይሖዋ ጥበብ ከእኛ ጥበብ የላቀ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። (ኢሳይያስ 55:9) ለእነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ለእኛ ዘላለማዊ ጥቅም የተሻለ ነው ብሎ ባሰበው ጊዜ ክፋትን ከምድር ገጽ ያስወግዳል። ደግሞስ ከዚህ የተሻለ ምን አማራጭ ይኖራል? አምላክ ፈጽሞ ፍትሕን አያጓድልም!—ሮሜ 9:14-24

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ”

18 ምንጊዜም በጥድፊያ ስሜት ለማገልገል ፈጽሞ ከይሖዋ መራቅ የለብንም። ሰይጣን ከይሖዋ ጋር ያለንን ጥሩ ዝምድና ለማበላሸት የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርግ መዘንጋት የለብህም። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ መቼም ቢሆን እንደማይመጣና ምሥራቹን መስበክም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች መጠበቅ ምንም ትርጉም እንደሌለው አድርገን እንድናስብ ለማድረግ ይጥራል። ይሁን እንጂ “ሐሰተኛ፣ የሐሰትም አባት” ነው። (ዮሐንስ 8:44) እስከ መጨረሻው ‘ዲያብሎስን መቃወም’ አለብን። ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና አቅልለን መመልከት የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ሲል ፍቅራዊ የሆነ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 4:7, 8) ወደ ይሖዋ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?

19 በጸሎት ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ ነው። የኑሮ ጫናዎች በጣም ሲከብዱህ ያስጨነቀህን ነገር በሙሉ ለይሖዋ ንገረው። በምትጸልይበት ጊዜ ችግርህን ለይተህ የምትጠቅስ ከሆነ ለጸሎትህ የሚሰጥህን ምላሽ በቀላሉ ማስተዋል ትችላለህ። የሚሰጥህ መልስ ሁልጊዜ አንተ እንደምትጠብቀው ላይሆን ይችላል፤ ይሁንና ፍላጎትህ እሱን ማስከበርና ከእሱ ጎን በታማኝነት መቆም ከሆነ ችግሮችህን በጽናት መቋቋም እንድትችል አስፈላጊውን እርዳታ ይሰጥሃል። (1 ዮሐንስ 5:14) ለሕይወትህ የሚሰጥህን መመሪያ ባስተዋልክ መጠን ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ ትገፋፋለህ። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን የይሖዋ ባሕርያትና መንገዶች ማንበብና በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ ማሰላሰልህ ይሖዋን ይበልጥ እንድታውቀው የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ ለእሱ ያለህ ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል። (መዝሙር 19:14) ፈተናዎችን እንድትቋቋም እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተህ እንድትጠብቅ ከምንም ነገር በላይ የሚረዳህ ይህ ፍቅር ነው።—1 ዮሐንስ 5:3

20 በተጨማሪም ከይሖዋ እንዳንርቅ ከፈለግን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረብ አለብን። ይህ ጉዳይ በዚህ ብሮሹር የመጨረሻ ክፍል ላይ ይብራራል።

ለጥናት የሚረዱ ጥያቄዎች

ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይ በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመው ምን አደረገ? ደቀ መዛሙርቱስ ምን እንዲያደርጉ አሳሰባቸው? (አንቀጽ 1-4)

ሰይጣን የይሖዋን አገልጋዮች ዒላማ ያደረገው ለምንድን ነው? የሚፈትነንስ በምን መንገዶች ነው? (አንቀጽ 5-8)

ፈተናዎችን ለመቋቋም ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን (አንቀጽ 9-12)፣ ለጸሎታችን የምንጠብቀው መልስ ምክንያታዊ መሆን ያለበት (አንቀጽ 13-15)፣ የተነሱትን አከራካሪ ጉዳዮች ማስታወስ ያለብን (አንቀጽ 16-17) እና ‘ወደ እግዚአብሔር መቅረብ’ ያለብን (አንቀጽ 18-20) ለምንድን ነው?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች

ጤና/ዕድሜ። ሥር የሰደደ ሕመም ካለብን ወይም እርጅና ከተጫጫነን በአምላክ አገልግሎት የምንፈልገውን ያህል መሥራት ስለማንችል ስሜታችን ሊደቆስ ይችላል።—ዕብራውያን 6:10

እንደጠበቅነው ሳይሆን ሲቀር። የአምላክን ቃል በምንሰብክበት ጊዜ የጠበቅነውን ያህል ጥሩ ምላሽ ሳናገኝ ስንቀር ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን።—ምሳሌ 13:12

የከንቱነት ስሜት። አንድ ሰው ለብዙ ዓመታት በደረሰበት በደልና ግፍ የተነሳ ማንም ሰው፣ ሌላው ቀርቶ ይሖዋም እንኳ እንደማይወደው ሊሰማው ይችላል።—1 ዮሐንስ 3:19, 20

የስሜት መጎዳት። አንድ ሰው የእምነት ባልንጀራው በፈጸመበት በደል ሳቢያ ስሜቱ በእጅጉ ሊጎዳ ይችላል፤ በዚህም የተነሳ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመቅረትና በስብከቱ ሥራ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማቋረጥ ሊፈተን ይችላል።—ሉቃስ 17:1

ስደት። እምነትህን የማይደግፉ ሰዎች ሊቃወሙህ፣ ሊያሳድዱህ ወይም ሊያፌዙብህ ይችላሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ‘ሳናቋርጥ እንድንጸልይ’ አሳስቦናል