ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው?
ዓለማችን ወዴት እያመራች ነው?
ከባድ ችግሮችና አስደንጋጭ ክስተቶች የዓለማችን የዕለት ተዕለት ዜናዎች ሆነዋል! ይህ ምን ይጠቁማል?
የሰዎች ደኅንነት:- በገበያ ሥፍራ ቦምብ ፈነዳ። በትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪዎችና ተማሪዎች በጥይት ተደብድበው ተገደሉ። ወላጆች ሳያዩ ሕፃናትን በድንገት አፍኖ መውሰድ የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል። ሴቶችና አረጋውያን በጠራራ ፀሐይ እየተደበደቡና እየተዘረፉ ነው።
ሃይማኖት:- አብያተ ክርስቲያናት እርስ በርስ የሚዋጉ ተቀናቃኝ አንጃዎችን ይደግፋሉ። ቀሳውስት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰሱ። ቄሶች ሕፃናት ልጆችን ያስነውራሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ይህን ወንጀል ለመሸፋፈን ትሞክራለች። ወደ አብያተ ክርስቲያናት የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በመመናመን ላይ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኖችም በመሸጥ ላይ ናቸው።
የአካባቢ ሁኔታ:- ደኖች እየተጨፈጨፉ ለንግድ በመዋል ላይ ናቸው። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ለማገዶ ሲሉ ዛፎችን እያወደሙ ነው። በከርሰ ምድር ውስጥ የሚገኘው ውኃ ስለተበከለ ለመጠጥነት የማይውልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ዝቃጮችና ዘመናዊ የሆኑ አንዳንድ የዓሣ ማስገር ዘዴዎች በዓሣ ዝርያዎች ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ነው። አየሩ በጣም በመበከሉ ለመተንፈስ እንኳ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።
መተዳደሪያ:- ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዓመታዊው የነፍስ ወከፍ ገቢ በጣም ዝቅተኛ ነው። ስግብግብ በሆኑ የሥራ ኃላፊዎች ሳቢያ ብዙ የንግድ ድርጅቶች ለኪሳራ በመዳረጋቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራ አጥ ሆነዋል። ሙስና ብዙ ባለሀብቶች ለረጅም ዓመታት ያጠራቀሙትን ሀብት አጥተው ባዶ እጃቸውን እንዲቀሩ እያደረጋቸው ነው።
የምግብ እጥረት:- በዓለም ዙሪያ 800,000,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በቂ ምግብ አጥተው በረሃብ አለንጋ ይገረፋሉ።
ጦርነት:- በ20ኛው መቶ ዘመን ከ100,000,000 የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሰውን ዘር በሙሉ ደግሞ ደጋግሞ ሊያጠፋ የሚችል ከፍተኛ የኑክሊየር መሣሪያ ክምችት አለ። በተለያዩ የምድር ክፍሎች የእርስ በርስ ጦርነቶች በመካሄድ ላይ ናቸው። ሽብርተኝነት መላውን ዓለም እያናወጠ ነው።
ወረርሽኝና ሌሎች በሽታዎች:- የኅዳር በሽታ ከ1918 አንስቶ 21,000,000 የሚሆኑ ሰዎችን ፈጅቷል። በአሁኑ ጊዜ ኤድስ “በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ አስከፊ ወረርሽኝ” ሆኗል። ካንሰርና የልብ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙዎችን በማስጨነቅ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህን የዜና ዘገባዎች እንዲሁ በተናጠል ከመመልከት ይልቅ ያላቸውን አንድምታ አስብ። እነዚህ ሁኔታዎች ራሳቸውን የቻሉ ክስተቶች ናቸው ወይስ ልዩ ትርጉም ያለው የአንድ ዓለም አቀፋዊ ክስተት ገጽታዎች?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አምላክ በእርግጥ ያስብልናል?
ብዙ ሰዎች አስደንጋጭ ክስተቶች ወይም አሳዛኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው አምላክ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲደርስብን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው? ብለው ይጠይቃሉ።
አምላክ በእርግጥ ያስብልናል። በአሁኑ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ በመስጠት እረፍት እንድናገኝ ይረዳናል። (ማቴዎስ 11:28-30፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ዓመፅን፣ በሽታንና ሞትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። አምላክ ያደረገው ዝግጅት ለአንድ ብሔር ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ብሔርና ዘር እንደሚያስብ ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35
እኛስ ስለ አምላክ ምን ያህል እናስባለን? የሰማይና የምድር ፈጣሪ ማን እንደሆነ ታውቃለህ? ስሙ ማን ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። ዓመፅንም ሆነ በሽታንና ሞትን ለማስወገድ ምን እርምጃዎች እየወሰደ እንዳለም ገልጾልናል። ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚዎች መሆን እንድንችል በእኛ በኩል ምን ይፈለግብናል? ስለ አምላክም ሆነ ስለ ዓላማዎቹ ማወቅ ይኖርብናል። በአምላክ ካላመንን እሱ ባደረጋቸው ዝግጅቶች የመጠቀም መብት ይኖረናል ብለን እንዴት ልንጠብቅ እንችላለን? (ዮሐንስ 3:16፤ ዕብራውያን 11:6) በተጨማሪም ትእዛዛቱን መጠበቅ ይኖርብናል። (1 ዮሐንስ 5:3) ይህ ጉዳይ ምን ያህል ያሳስብሃል?
አምላክ አሁን ያሉት ሁኔታዎች እንዲኖሩ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለመረዳት በቅድሚያ፣ እልባት ማግኘት የሚያሻው አንድ አከራካሪ ጉዳይ እንደተነሳ መገንዘብ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ አከራካሪ ጉዳይ ምን እንደሆነ ይገልጻል። በዚህ ጽሑፍ ገጽ 15 ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ማብራሪያ ተሰጥቷል።