በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የፍርዱ ሰዓት” ደርሷል

“የፍርዱ ሰዓት” ደርሷል

“የፍርዱ ሰዓት” ደርሷል

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ‘የዘላለም ወንጌል የያዘ’ አንድ መልአክ በሰማይ መካከል እየበረረ እንዳለ ይገልጻል። መልአኩ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል” በማለት በታላቅ ድምፅ በማወጅ ላይ ነው። (ራእይ 14:6, 7) ይህ ‘የፍርድ ሰዓት’ አዋጁ የሚታወጅበትንም ሆነ አምላክ ፍርዱን የሚያስፈጽምበትን ጊዜ የሚያጠቃልል ነው። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አንድ “ሰዓት” በጣም አጭር ነው። ይሖዋ ፍርዱን የሚያስፈጽመው “በመጨረሻው ዘመን” መደምደሚያ ላይ ሲሆን አሁን እኛ ያለነው ደግሞ በዚህ ዘመን ውስጥ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1

“የፍርዱ ሰዓት” ጽድቅን ለሚወዱ ሰዎች የምሥራች ነው። ይህ ወቅት በዚህ ዓመፀኛና ጨካኝ የሆነ ሥርዓት ሲሰቃዩ የኖሩት የአምላክ አገልጋዮች እፎይታ የሚያገኙበት ነው።

“የፍርዱ ሰዓት” መደምደሚያ የሆነው የዚህ ክፉ ሥርዓት ጥፋት ከመድረሱ በፊት ‘እግዚአብሔርን እንድንፈራና እንድናከብር’ ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ታዲያ አንተ ይህን እያደረግክ ነው? ይህ እንዲሁ “በአምላክ አምናለሁ” ብሎ የመናገር ጉዳይ አይደለም። (ማቴዎስ 7:21-23፤ ያዕቆብ 2:19, 20) ለአምላክ ያለን ትክክለኛ ፍርሃት ጥልቅ አክብሮት እንድናሳየው ሊገፋፋን ይገባል። በተጨማሪም ከክፉ ነገር እንድንርቅ ሊያደርገን ይገባል። (ምሳሌ 8:13) ከዚህም ሌላ መልካም የሆነውን እንድንወድ እና ክፉ የሆነውን እንድንጠላ ሊያነሳሳን ይገባል። (አሞጽ 5:14, 15) አምላክን የምናከብር ከሆነ የሚለንን ሁሉ እንሰማለን። ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማንበብ እስኪሳነን ድረስ በሌሎች ነገሮች ራሳችንን አናስጠምድም። ምንጊዜም በፍጹም ልባችን በእሱ እንታመናለን። (መዝሙር 62:8፤ ምሳሌ 3:5, 6) ለአምላክ ትክክለኛ አክብሮት ያላቸው ሁሉ የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንደሆነ አምነው የሚቀበሉ ከመሆኑም በላይ ሙሉ በሙሉ ለእሱ ይገዛሉ። ለእነዚህ ነገሮች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለብን ከተገነዘብን ይህን ለማድረግ መዘግየት የለብንም።

መልአኩ የጠቀሰው የአምላክ ፍርድ የሚፈጸምበት ጊዜ “የእግዚአብሔር ቀን” ተብሎም ተጠርቷል። የጥንቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሳይሰሙ በመቅረታቸው በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት የይሖዋ “ቀን” ደርሶባቸዋል። የይሖዋን ቀን አቅርበው ባለመመልከታቸው ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። ይሖዋ ይህን ቀን በተመለከተ “ቅርብ ነው ፈጥኖም ይመጣል” ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር። (ሶፎንያስ 1:14) በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት በጥንቷ ባቢሎን ላይም ሌላ “የእግዚአብሔር ቀን” መጥቶ ነበር። (ኢሳይያስ 13:1, 6) ባቢሎናውያን በገነቡት የመከላከያ ግንብና በአማልክቶቻቸው በመታመን የይሖዋ ነቢያት የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ታላቋ ባቢሎን በአንድ ሌሊት በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ ወደቀች።

ዛሬስ ከፊታችን ምን ተደቅኗል? ይበልጥ ታላቅ የሆነ ሌላ ‘የእግዚአብሔር ቀን’ ከፊታችን ተደቅኗል። (2 ጴጥሮስ 3:11-14) ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ መለኮታዊ ፍርድ ተበይኗል። ራእይ 14:8 በሚገልጸው መሠረት አንድ መልአክ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች” ሲል አስታውቋል። መልአኩ የተናገረው ይህ ቃል ፍጻሜውን አግኝቷል። በመሆኑም እንደቀድሞው የይሖዋን ሕዝቦች ለማገድ የሚያስችል ኃይል የላትም። ምግባረ ብልሹነቷና በጦርነት ውስጥ የምታደርገው ተሳትፎ በእጅጉ ተጋልጧል። አሁን ለአንዴና ለመጨረሻ የምትጠፋበት ጊዜ ቀርቧል። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ለሚገኙ ሰዎች “በኀጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፣ ከእርሷ ውጡ፤ ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሮአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሶአል” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል።—ራእይ 18:4, 5

ታላቂቱ ባቢሎን ማን ነች? ከጥንቷ ባቢሎን ጋር ተመሳሳይነት ያለውን ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ሥርዓት የምትወክል ናት። (ራእይ ምዕራፍ 17, 18) በመካከላቸው ያለውን አንዳንድ ተመሳሳይነት እንመልከት:-

በጥንቷ ባቢሎን የነበሩት ካህናት በአገሪቷ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ ይገቡ ነበር። ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ ሃይማኖቶችም እንዲሁ ናቸው።

የባቢሎን ካህናት አገሪቱ በምታካሂዳቸው ውጊያዎች ዋነኛ አራጋቢዎች ነበሩ። በዘመናችን ያሉ ሃይማኖቶችም ብዙውን ጊዜ ብሔራት በሚያደርጉት ውጊያ ወታደሮችን ባርከው ወደ ጦር ግንባር በመላክ ዋነኛ የጦርነት አቀንቃኞች መሆናቸውን አሳይተዋል።

የጥንቷ ባቢሎን ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ልማዶች ነዋሪዎቿ ወራዳ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ አድርገዋል። ዛሬ ያሉ የሃይማኖት መሪዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች ወደ ጎን ገሸሽ ስለሚያደርጉ በቀሳውስቱም ሆነ በምእመኖቻቸው መካከል የጾታ ብልግና የተለመደ ነገር ሆኗል። ታላቂቱ ባቢሎን ከዓለምና ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር የምታመነዝር በመሆኗ የራእይ መጽሐፍ አመንዝራ ሲል ይጠራታል።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ታላቂቱ ባቢሎን ‘እንደምትቀማጠል’ ይገልጻል። የጥንቷ ባቢሎን እምነቶች ሰፋፊ ርስቶች የነበሯቸው ከመሆኑም በላይ ካህናቱም በንግዱ መስክ የጎላ ድርሻ ነበራቸው። በዛሬው ጊዜም ታላቂቱ ባቢሎን የአምልኮ ሥፍራዎች ብቻ ሳይሆን ትልልቅ የንግድ ተቋማትም አሏት። የምታስተምራቸው ትምህርቶችም ሆኑ በዓሎቿ እሷም ሆነች በንግዱ ዓለም የተሰማሩ ሌሎች ድርጅቶች ከፍተኛ ሀብት ማጋበስ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም፣ አስማትና ጥንቆላ በጥንቷ ባቢሎን የተለመዱ ነገሮች እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም በእጅጉ ተስፋፍተው ይገኛሉ። ሞት ወደ ሌላ ሕይወት መሸጋገሪያ ድልድይ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ባቢሎን ለአማልክቷ በተሠሩ ቤተ መቅደሶችና የአምልኮ ሥፍራዎች የተሞላች ነበረች፤ ሆኖም ባቢሎናውያን የይሖዋን አምላኪዎች ይቃወሙ ነበር። ታላቂቱ ባቢሎንም ተመሳሳይ የሆኑ እምነቶችና ልማዶች አሏት።

በጥንት ዘመን ይሖዋ እሱንም ሆነ ዓላማውን የሚቃወሙትን ሁሉ ለመቅጣት ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ኃይል የነበራቸውን ብሔራት መሣሪያ አድርጎ ይጠቀም ነበር። በመሆኑም ሰማርያ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦራውያን ጠፍታለች። ኢየሩሳሌም ደግሞ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎናውያን ከዚያም በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮማውያን ጠፍታለች። ባቢሎንም ብትሆን በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ድል ተመታለች። በዘመናችንም የፖለቲካ መንግሥታት እንደ አውሬ ሆነው ‘በአመንዝራይቱ’ ላይ እንደሚነሱና ዕርቃኗን በማስቀረት ማንነቷን እንደሚያጋልጡ አልፎ ተርፎም ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠፏት መጽሐፍ ቅዱስ ይተነብያል።—ራእይ 17:16

የዓለም መንግሥታት በእርግጥ እንዲህ ያለ እርምጃ ይወስዱ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ‘እግዚአብሔር ይህን ሐሳብ በልባቸው እንደሚያኖር’ ይገልጻል። (ራእይ 17:17) በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚደርሰው ጥፋት አስቀድሞ በግልጽ የሚታይና ቀስ በቀስ የሚከናወን ባለመሆኑ ድንገተኛና እጅግ አስደንጋጭ ይሆናል።

ምን እርምጃ መውሰድ ይኖርብሃል? ‘አሁንም ያለሁት የታላቂቱ ባቢሎን መለያ የሆኑ ትምህርቶችንና ልማዶችን በሚያራምድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ውስጥ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እንዲህ ያለ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል ባትሆንም እንኳ ‘በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ የሚንጸባረቀው መንፈስ አንዳንድ ተጽዕኖዎች እያደረገብኝ ነው?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ ትችላለህ። ይህ መንፈስ ልቅ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖርህ፣ ከአምላክ ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችንና ተድላን እንድትወድ ወይም የይሖዋን ቃል (ትናንሽ በሚመስሉ ጉዳዮችም ቢሆን) ሆን ብለህ ቸል እንድትል ተጽዕኖ እያሳደረብህ ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠውን መልስ በጥሞና አስብበት።

የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ድርጊታችንም ሆነ አስተሳሰባችንና ዝንባሌያችን የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል አለመሆናችንን በግልጽ የሚያሳይ መሆን አለበት። ይህን እርምጃ ለመውሰድ ዛሬ ነገ ማለት የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ድንገት እንደሚመጣ ሲያስጠነቅቅ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን፣ እንዲህ ባለ ኀይል ትወረወራለች፤ ተመልሳም አትገኝም” ይላል።—ራእይ 18:21

ሆኖም ይሖዋ አምላክ ‘በፍርዱ ሰዓት’ የሚያከናውነው ሌላም ነገር አለ። በዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሥርዓትና በገዥዎቹ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራውን ሰማያዊ መንግሥቱን በማይቀበሉ ሁሉ ላይ ይፈርዳል። (ራእይ 13:1, 2፤ 19:19-21) በዳንኤል 2:20-45 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢታዊ ራእይ ከጥንቷ ባቢሎን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ያለውን የፖለቲካ አገዛዝ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከብረትና ከሸክላ በተሠራ አንድ ግዙፍ ምስል ይመስለዋል። ትንቢቱ እኛ ያለንበትን ዘመን አስመልክቶ ሲናገር “የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስ . . . መንግሥት ይመሠርታል” ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ መንግሥት በይሖዋ ‘የፍርድ ሰዓት’ የሚያከናውነውን ነገር በተመለከተ “እነዚያን [ሰብዓዊ] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በማለት ይገልጻል።—ዳንኤል 2:44

መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ‘በዓለም ያለውን ነገር’ ማለትም ከእውነተኛው አምላክ የራቀው ይህ ዓለም የሚከተለውን አኗኗር እንዳይወዱ ያስጠነቅቃል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) የምታደርጋቸው ውሳኔዎችም ሆኑ ድርጊቶችህ ሙሉ በሙሉ ከአምላክ መንግሥት ጎን እንደቆምክ ያሳያሉ? በሕይወትህ ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዘው የአምላክ መንግሥት ነው?—ማቴዎስ 6:33፤ ዮሐንስ 17:16, 17

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጨረሻው የሚመጣው መቼ ነው?

“የሰው ልጅም ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:44

“ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ።”—ማቴዎስ 25:13

“ከቶም አይዘገይም።”—ዕንባቆም 2:3

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቀኑን ብታውቅ ኖሮ በአኗኗርህ ላይ ለውጥ ያመጣ ነበር?

መጪው መለኮታዊ ፍርድ የተወሰኑ ዓመታት እንደሚዘገይ ብታውቅ አኗኗርህን ለመለወጥ ትነሳሳ ነበር? የዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ ከጠበቅከው በላይ እንደዘገየ ሆኖ ተሰምቶህ ለይሖዋ አገልግሎት የነበረህ ቅንዓት ቀንሷል?—ዕብራውያን 10:36-38

ይህ ዓለም የሚጠፋበትን ቀን ለይተን አለማወቃችን አምላክን የምናገለግለው በቅን ልቦና ተነሳስተን እንደሆነ ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። ይሖዋ ልብን የሚያይ አምላክ በመሆኑ በመጨረሻዋ ሰዓት ላይ መንፈሳዊ ቅንዓት በማሳየት በእሱ ፊት ተቀባይነት ማግኘት እችላለሁ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።—ኤርምያስ 17:10፤ ዕብራውያን 4:13

ይሖዋን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ሥፍራ የሚሰጡት ለእሱ ነው። እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ሰብዓዊ ሥራ ይሠራሉ። ሆኖም ግባቸው ሀብት ማካበት ሳይሆን ለራሳቸው የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማግኘትና ሌሎችን መርዳት ነው። (ኤፌሶን 4:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:7-12) በተጨማሪም እረፍት የሚወስዱና ጥሩ በሆኑ መዝናኛዎች የሚካፈሉ ሲሆን ይህንንም የሚያደርጉት ሌላው ያደረገው አይቅርብኝ ብለው ሳይሆን ራሳቸውን ዘና ለማድረግና መንፈሳቸውን ለማደስ ነው። (ማርቆስ 6:31፤ ሮሜ 12:2) እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ እነሱም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስታቸዋል።—መዝሙር 37:4፤ 40:8

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለዘላለም ይሖዋን እያገለገሉ መኖር ይፈልጋሉ። አንዳንዶች ወደፊት የምናገኘው በረከት ካሰቡት በላይ እንደዘገየ ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም ይህ ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼም ይሁን መቼ በተስፋው ዋጋማነት ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሉዓላዊነት ጥያቄ

አምላክ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለመረዳት በቅድሚያ ሉዓላዊነትን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ መመርመር ይኖርብናል። ሉዓላዊነት ምንድን ነው? የሥልጣን የበላይነት ነው።

ይሖዋ ፈጣሪ ስለሆነ ምድርንና በላይዋ የሚኖሩትን ሁሉ የመግዛት መብት አለው። ይሁንና በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በተመለከተ ጥያቄ እንደተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ሰይጣን ዲያብሎስ፣ ይሖዋ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ሕጉን ቢጥሱና በራሳቸው ቢመሩ የሚደርስባቸው ችግር እንዳለ በመግለጽ ዋሽቷቸዋል እንዲሁም አላግባብ ጨቁኗቸዋል ሲል ተከራክሯል። በተጨማሪም ከአምላክ አገዛዝ ተላቅቀው ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ የተሻለ ይሆን ነበር የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ አቅርቧል።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 2, 3

አምላክ ዓመፀኞቹን ወዲያው በማጥፋት ኃይሉን ማሳየት ይችል ነበር፤ ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ለተነሳው አከራካሪ ጉዳይ ትክክለኛ ምላሽ አይሆንም። ይሖዋ ዓመፀኞቹን ወዲያውኑ ከማጥፋት ይልቅ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ይህ ዓመፅ የሚያስከትለውን ውጤት ማየት እንዲችሉ ጊዜ ሰጠ። ይህ ሁኔታ ሥቃይና መከራ ያስከተለ ቢሆንም እኛም ወደ ሕልውና መምጣት የምንችልበትን አጋጣሚ ሰጥቶናል።

ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ እሱን የሚታዘዙና በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምኑ ሰዎች ከኃጢአትና ኃጢአት ከሚያስከትላቸው መዘዞች መላቀቅና በገነት መኖር የሚችሉበትን ዝግጅት ለማድረግ ሲል ትልቅ መሥዋዕትነት ከፍሏል። የሞቱ ሰዎችንም እንኳ በትንሣኤ በማስነሳት በዚህ ዝግጅት እንዲጠቀሙ ያደርጋል።

ከዚህም ሌላ ይሖዋ ይህ አከራካሪ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጊዜ መስጠቱ አገልጋዮቹ ለአምላክ ፍቅር ምላሽ እንደሚሰጡና በማንኛውም ሁኔታ ሥር ከእሱ ጎን በታማኝነት እንደሚቆሙ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ያለው ሕግና ሥርዓት በሚገባ እንዲከበር መለኮታዊ ሉዓላዊነትንና የሰው ልጆች ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት በተመለከተ የተነሱት አከራካሪ ጉዳዮች እልባት ማግኘት አለባቸው። የጽንፈ ዓለሙ ሕግ እስካልተከበረ ድረስ እውነተኛ ሰላም ሊገኝ አይችልም። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.36 እነዚህን አከራካሪ ጉዳዮችና ያላቸውን አንድምታ በተመለከተ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወደ ይሖዋ ቅረብ በተባለው መጽሐፍ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዓለም አቀፉ የፖለቲካ አገዛዝ በቅርቡ ያከትማል