በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ ሁሉ ምን ያመለክታል?

ይህ ሁሉ ምን ያመለክታል?

ይህ ሁሉ ምን ያመለክታል?

ኢየሱስ ክርስቶስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈርና የመሬት መንቀጥቀጥ “የሥርዓቱ መደምደሚያ” [NW] ምልክት እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር።—ማቴዎስ 24:1-8፤ ሉቃስ 21:10, 11

ከ1914 ወዲህ በአብዛኛው በቀሳውስት ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ሳቢያ በብሔራት መካከል በሚካሄዱ ጦርነቶችና በጎሳዎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተስፋፋ በመጣው ሽብርተኝነት ዓለማችን በመታመስ ላይ ትገኛለች።

ሳይንስ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ቢደርስም በዓለም ዙሪያ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አስከፊ ለሆነ ረሃብ ተጋልጠዋል። በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ይሞታሉ።

ቸነፈር ወይም ወረርሽኝ በሽታዎችም ኢየሱስ የጠቀሰው ምልክት ገጽታዎች ናቸው። አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተከሰተው የኅዳር በሽታ ከ21,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ቀደም ባሉት ዘመናት የተከሰቱት ወረርሽኞች የተወሰኑ አካባቢዎችን ብቻ ያጠቁ ሲሆን የኅዳር በሽታ ግን በጣም ርቀው የሚገኙ ደሴቶችን ጨምሮ በምድር ዙሪያ የሚገኙ አገሮችን አዳርሷል። በአሁኑ ጊዜ ኤድስ መላውን ዓለም ያዳረሰ ሲሆን እንደ ሳንባ ነቀርሳና ወባ ያሉ በሽታዎች አሁንም ድረስ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በማጥቃት ላይ ናቸው።

በየዓመቱ የተለያየ ኃይል ያላቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የምድር ነውጦች እንደሚከሰቱ ይነገራል። የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚከሰት የሚጠቁሙ ዘመናዊ መሣሪያዎች ባሉበት በዚህ ዘመን እንኳ ብዙ ሕዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በርካታ ሰዎችን እንደፈጀ የሚገልጹ ዘገባዎችን መስማት እንግዳ ነገር አይደለም።

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል:- “በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው ቢባል አትስማማም?

ሰዎች ከሚገባው በላይ ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱና በትዕቢት የተወጠሩ እንደሆኑ አላስተዋልክም?

ዓለም ራስ ወዳድ በሆኑና በማያመሰግኑ እንዲሁም ዕርቅን በማይሹና ከዳተኞች በሆኑ ሰዎች የተሞላች መሆኗን ማን ሊክድ ይችላል?

በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ለወላጆች ያለመታዘዝ ባሕርይ እየተስፋፋ እንደመጣና የሰዎች ፍቅር በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ እንዳለ አስተውለሃል?

መልካም የሆነውን በማይወድና ተድላን በሚያሳድድ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር ሳትገነዘብ አልቀረህም። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ዘመን” የሚኖረውን የሰዎች አመለካከትና ባሕርይ የገለጸው በዚህ መንገድ ነው።

የምንኖርበትን ዘመን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ተጨማሪ ማስረጃ ያስፈልግ ይሆን? ኢየሱስ በዚሁ ዘመን የአምላክ መንግሥት ምሥራች በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክም ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውና የይሖዋን መንግሥት ምሥራች የሚያስታውቀው መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት በየጊዜው እየታተሙ ከሚወጡ ሌሎች መጽሔቶች ሁሉ ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች እየታተመ ይሰራጫል።

የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በመመሥከር በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ሰዓት በላይ ያሳልፋሉ።

በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ርቀው በሚገኙ የምድር ክፍሎች የሚኖሩ ሕዝቦችና አናሳ ብሔረሰቦች የሚናገሯቸውን ቋንቋዎች ጨምሮ ወደ 400 በሚጠጉ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ ጽሑፎችን እያተሙ ያሰራጫሉ። የሁሉም ብሔራት ሕዝቦች ምሥራቹ እንዲደርሳቸው የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በፖለቲካው ዓለም ከቁጥር በማይገቡ አነስተኛ ደሴቶች ጭምር ሰብከዋል። በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፕሮግራም አላቸው።

በእርግጥም የአምላክ መንግሥት ምሥራች መላውን ዓለም ለመለወጥ ሳይሆን ምሥክርነት ለመስጠት በምድር ዙሪያ በመሰበክ ላይ ነው። ይህ የስብከት ሥራ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች ሰማይና ምድርን ስለፈጠረው አምላክ ምን ያህል እንደሚያስቡ እንዲሁም ለሕጎቹ የቱን ያህል አክብሮት እንዳላቸውና ሌሎች ሰዎችን ምን ያህል እንደሚወዱ ማሳየት የሚችሉበት አጋጣሚ እየከፈተላቸው ነው።—ሉቃስ 10:25-27፤ ራእይ 4:11

በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ክፋትን ጠራርጎ በማስወገድ መላዋን ምድር ወደ ገነትነት ይለውጣታል።—ሉቃስ 23:43

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የምን መጨረሻ?

የሰው ዘር መጨረሻ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዳላቸው ይገልጻል።—ዮሐንስ 3:16, 36፤ 1 ዮሐንስ 2:17

የምድር መጨረሻ ማለትም አይደለም። የአምላክ ቃል ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን የተፈጠረችው ምድር ለዘላለም ጸንታ እንደምትኖር ይናገራል።—መዝሙር 37:29፤ 104:5፤ ኢሳይያስ 45:18

ከዚህ ይልቅ የመጨረሻ ቀን የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው የዚህን ዓመፀኛና ጥላቻ የነገሠበት ሥርዓት እንዲሁም ይህን ሥርዓት የሙጥኝ ያሉትን ሰዎች መጨረሻ ነው።—ምሳሌ 2:21, 22

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት በተደጋጋሚ ጊዜያት “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” ሲሉ ጽፈዋል። (ኢሳይያስ 43:14፤ ኤርምያስ 2:2) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ሳይቀር ‘ከራሱ እንዳልተናገረ’ ገልጿል። (ዮሐንስ 14:10) መጽሐፍ ቅዱስ ራሱም ቢሆን “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው” በማለት በግልጽ ይናገራል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የታተመ መጽሐፍ የለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ኅብረት እንዳወጣው ዘገባ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከ2,200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ታትሟል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት የተሰራጨ መጽሐፍ የለም። በአሁኑ ጊዜ ከአራት ቢሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ተሰራጭቷል። አምላክ ለሰው ልጆች በሙሉ ያስተላለፈውን መልእክት የያዘ መጽሐፍ እንዲህ በብዛት መሰራጨቱ ተገቢ አይመስልህም?

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎች ማግኘት ከፈለግክ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብና የአምላክ ቃል መሆኑን አምነህ የምትቀበል ከሆነ በእጅጉ ትጠቀማለህ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ያቋቋመው ልዩ መስተዳድር ነው።—ኤርምያስ 10:10, 12

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ይህን መንግሥት እንዲያስተዳድር ሥልጣን የሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይገልጻል። (ራእይ 11:15) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንኳ አምላክ ትልቅ ሥልጣን እንደሰጠው የሚያሳዩ ነገሮችን አከናውኗል። ይህ ሥልጣን የተፈጥሮ ኃይሎችን እንዲቆጣጠር፣ ሁሉንም ዓይነት በሽታዎች እንዲፈውስና የሞቱትን እንኳ ሳይቀር እንዲያስነሳ አስችሎታል። (ማቴዎስ 9:2-8፤ ማርቆስ 4:37-41፤ ዮሐንስ 11:11-44) በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት የተነገረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አምላክ “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም” እንደሚሰጠው ይናገራል። (ዳንኤል 7:13, 14 የ1954 ትርጉም) ይህ መስተዳድር የሰማይ መንግሥት በመባል የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ሆኖ በመግዛት ላይ ነው።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በዓለም ዙሪያ በመካሄድ ላይ ያለው የምሥራቹ ስብከት