በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሰዎች አለባበስና የፀጉር አያያዝ መሰናክል ሆኖብኝ ነበር

የሰዎች አለባበስና የፀጉር አያያዝ መሰናክል ሆኖብኝ ነበር

የሰዎች አለባበስና የፀጉር አያያዝ መሰናክል ሆኖብኝ ነበር

አይሊን ብረምባ እንደተናገረችው

ያደግኩት የጀርመን ባፕቲስት ወንድማማቾች ሃይማኖት ተከታይ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖቱን ወጎች በጥብቅ ይከተል የነበረ ሲሆን ከአሚሽ እና ሜኖናውያን ሃይማኖቶች ጋር ተመሳሳይነት ነበረው። ሃይማኖታዊ ንቅናቄው የጀመረው በ1708 ጀርመን ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃት ለመፍጠር ተብሎ ከተካሄደው ፓየቲዝም ተብሎ የሚጠራ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ነው። ዘ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንደሚለው ፓየቲዝም የተባለው እንቅስቃሴ “የሰው ዘር የክርስቶስ ወንጌል ያስፈልገዋል” የሚለውን አቋም ይዞ የተነሳ ነው። የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች በተለያዩ አገሮች ውጤታማ ሚስዮናዊ ዘመቻዎችን አካሂደዋል።

በ1719 አሌክሳንደር ማክ ተብሎ በሚጠራ ሰው የሚመራ አንድ አነስተኛ ቡድን በአሁኑ ጊዜ ፔንስልቬንያ ተብሎ ወደሚጠራው የዩናይትድ ስቴትስ ክፍል ተዛወረ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ተጨማሪ ቡድኖች ተመሥርተው ራሳቸውን ችለው ወጥተዋል። እያንዳንዱ ቡድን የአሌክሳንደር ማክን ትምህርቶች የሚተረጉምበት መንገድ የተለያየ ነበር። የእኛ ቤተ ክርስቲያን 50 ገደማ አባላት ያሉት አነስተኛ ቡድን ነበር። ቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ያስተላለፉትን ውሳኔ በጥብቅ ይከተል ነበር።

ቤተሰባችን ቢያንስ ለሦስት ትውልድ ያህል ይህን እምነትና የአኗኗር ዘይቤ ሲከተል ቆይቷል። አሥራ ሦስት ዓመት ሲሞላኝ ተጠምቄ የቤተ ክርስቲያኑ አባል ሆንኩ። ከልጅነቴ አንስቶ መኪና፣ ትራክተር፣ ስልክ አልፎ ተርፎም ሬዲዮ ወይም በኤሌክትሪክ የሚሠራን ማንኛውንም መሣሪያ ይዞ መገኘትም ሆነ መጠቀም ስህተት እንደሆነ ተምሬያለሁ። ሴቶች ፀጉራቸውን እንዳይቆረጡ፣ ቀለል ያለ አለባበስ እንዲለብሱና ሁሌም ራሳቸውን እንዲሸፍኑ ይጠበቅባቸው ነበር። ወንዶች ደግሞ ጢማቸውን ያሳድጉ ነበር። በእኛ አስተሳሰብ የዚህ ዓለም ክፍል አለመሆን ተገቢ ያልሆነ ኩራት መገለጫ የሆኑትን ዘመናዊ ልብሶች፣ መኳኳያዎችና ጌጦች ማስወገድን ይጨምራል።

መንፈሳዊ ምግባችን አድርገን ለምንቆጥረው ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረን ተምረናል። በየቀኑ ጠዋት ቁርስ ከመብላታችን በፊት ሳሎን ውስጥ ተሰብስበን አባታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ምዕራፍ አንብቦ ሲያብራራ እናዳምጥ ነበር። ከዚያም ሁላችንም እንንበረከክና አባታችን ይጸልያል። በኋላም እናታችን የጌታን ጸሎት ትደግማለች። መላው ቤተሰባችን ተሰብስቦ መንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩርበትን ይህን ጊዜ በጉጉት እጠብቀው ነበር።

የምንኖረው ዴልፋይ፣ ኢንዲያና አቅራቢያ ባለ አንድ እርሻ ላይ ሲሆን በዚያም የተለያዩ አትክልቶችን እናለማ ነበር። ያመረትነውን አትክልት በፈረስ በሚነዳ ጋሪ ላይ ጭነን መንገድ ላይ ወይም በየቤቱ እየሄድን እንሸጣለን። የጉልበት ሥራ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ክፍል እንደሆነ ይሰማን ነበር። በመሆኑም የጉልበት ሥራ መሥራት ከማይቻልበት ከእሁድ በቀር በሌሎች ቀኖች ሁሉ እንሠራለን። አንዳንድ ጊዜ ግን ቤተሰባችን በእርሻ ሥራ በጣም ከመጠመዱ የተነሳ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ተፈታታኝ ይሆንብን ነበር።

ትዳር እና ቤተሰብ

በ1963 የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ሃይማኖት ያለውን ጄምስ የተባለ ሰው አገባሁ። የጄምስ ቅድመ አያቶች ጭምር የዚህ ሃይማኖት ተከታዮች ነበሩ። ሁለታችንም አምላክን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት የነበረን ሲሆን ብቸኛው እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ እናምን ነበር።

እስከ 1975 ባለው ጊዜ ውስጥ ስድስት ልጆች ወለድን፤ ከዚያም በ1983 ሰባተኛውና የመጨረሻው ልጃችን ተወለደ። ከሁለተኛዋ ልጃችን ከሬቤካ በቀር ሌሎች ልጆቻችን በሙሉ ወንዶች ናቸው። ጠንክረን ለመሥራት፣ ብዙ ገንዘብ ላለማውጣትና ቀላል ሕይወት ለመምራት እንሞክር ነበር። ከወላጆቻችንና ከሌሎች የሃይማኖታችን ተከታዮች የተማርናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ለልጆቻችን ለማስተማር ጥረት እናደርግ ነበር።

ሃይማኖታችን ለአለባበስና ለፀጉር አያያዝ ትልቅ ቦታ ይሰጣል። ልብን ማንበብ የሚችል ሰው ስለሌለ የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ማወቅ የሚቻለው በውጫዊ ገጽታው ነው ብለን እናምን ነበር። በመሆኑም የሃይማኖታችን ተከታይ የሆነች አንዲት ሴት ፀጉሯን በጣም ቡፍ ካደረገች የኩራት ምልክት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በተጨማሪም ልብሳችን የተሰፋበት ጨርቅ ጎላ ብሎ የሚታይ ንድፍ ካለው ይህም የኩራት ምልክት ተደርጎ ይታሰባል። እንዲህ ያሉት ጉዳዮች አንዳንድ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ትኩረት ይሰጣቸው ነበር።

የባለቤቴ ወንድም ታሰረ

ከእኛ ጋር ተመሳሳይ እምነት የነበረው የባለቤቴ ወንድም ጄሲ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በ1960ዎቹ መጨረሻ አካባቢ እስር ቤት ገባ። እስር ቤት ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ፤ ልክ እንደ እኛ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በጦርነት መካፈል ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር እንደሚጋጭ ያምናሉ። (ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:52) ጄሲ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በርካታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የእነሱን ባሕርይ በገዛ ዓይኑ ማየት ችሎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ካጠና በኋላ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ይህን ስናውቅ በጣም ተበሳጨን።

ጄሲ የተማረውን ነገር ለባለቤቴ ነገረው። በተጨማሪም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በቋሚነት እንዲያገኝ ዝግጅት አደረገለት። ጄምስ እነዚህን መጽሔቶች ሲያነብ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎቱ ይበልጥ ጨመረ። ጄምስ ከድሮ ጀምሮ አምላክን የማገልገል ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ወደ አምላክ መቅረብ ከባድ እንደሆነ ይሰማው ነበር፤ በመሆኑም ወደ አምላክ እንዲቀርብ ሊረዳው የሚችልን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር።

ሽማግሌዎቻችን የአሚሾችን፣ የሜኖናውያንን እና ከእኛ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን ሌሎች ሃይማኖቶች መጽሔት እንድናነብ ያበረታቱን ነበር፤ እነዚህን ሃይማኖቶች የዓለም ክፍል እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸው የነበረ ቢሆንም ማለት ነው። በተለይ ግን አባቴ ለይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ጥላቻ ነበረው። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የተባሉትን መጽሔቶች ፈጽሞ ማንበብ እንደሌለብን ይነግረን ነበር። በዚህም ምክንያት ጄምስ እነዚህን መጽሔቶች ሲያነብ ሳይ የሐሰት ትምህርቶችን ሊቀበል ይችላል ብዬ ስለሰጋሁ በጣም ተጨንቄ ነበር።

ጄምስ ከረጅም ጊዜ አንስቶ፣ ቤተ ክርስቲያናችን የሚያስተምራቸው አንዳንድ ትምህርቶች በተለይ እሁድ እሁድ የጉልበት ሥራ መሥራት ኃጢአት እንደሆነ የሚገልጸው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጭ ይሰማው ነበር። ለምሳሌ በእሁድ ቀን እንስሳትን ውኃ ማጠጣት የሚፈቀድ ቢሆንም አረም ማረም ግን ክልክል ነበር። ሽማግሌዎቻችን ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ያለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ለጄምስ ሊነግሩት አልቻሉም። በጊዜ ሂደት እኔም እንዲህ ያሉ ትምህርቶችን መጠራጠር ጀመርኩ።

ዕድሜያችንን በሙሉ ቤተ ክርስቲያናችን በአምላክ የተመረጠ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ እናምን የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከዚያ መልቀቅ ምን ውጤት እንደሚያስከትል አሳምረን እናውቃለን፤ በመሆኑም ከቤተ ክርስቲያኑ መውጣት ከብዶን ነበር። ሆኖም ቤተ ክርስቲያኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ እንደማይመራ እያወቅን እዚያው ለመቀጠል ሕሊናችን ሊፈቅድልን አልቻለም። በመሆኑም በ1983፣ የምንለቅበትን ምክንያት የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈን ደብዳቤው ለጉባኤው እንዲነበብ ጠየቅን። ከዚያም ከቤተ ክርስቲያኑ ተወገድን።

እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ያደረግነው ፍለጋ

ከዚያ በኋላ እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ፍለጋ ማድረግ ጀመርን። ዓላማችን የሚያስተምረውን ነገር ሥራ ላይ የሚያውል ሃይማኖት ማግኘት ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በጦርነት የሚካፈሉ ሃይማኖቶችን በሙሉ ከዝርዝራችን አወጣን። ቀለል ያለ ሕይወት የሚመሩና ትኩረት የማይስብ አለባበስ የሚለብሱ ተከታዮች ያሏቸው ሃይማኖቶች ቀልባችንን ይስቡት ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ሃይማኖቱ የዓለም ክፍል እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶች እንደሆኑ አድርገን እናስብ ነበር። ከ1983 እስከ 1985 ድረስ በመላው አገሪቱ እየተዘዋወርን ሜኖናውያንን ጨምሮ ይህን መሥፈርት የሚያሟሉ ሌሎች ሃይማኖቶችን አንድ በአንድ መረመርን።

በዚህ መሃል የይሖዋ ምሥክሮች በካምደን፣ ኢንዲያና አቅራቢያ ወደሚገኘው እርሻችን መጥተው አነጋገሩን። የኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ተጠቅመው እንዲያወያዩን ነገርናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ከጦርነት ጋር በተያያዘ ያላቸው አቋም አስደስቶኝ ነበር። ሆኖም ቀለል ያለ አለባበስ በመልበስ ከዓለም የተለየ መሆን እንዳለበት የማያምን ሃይማኖት እውነተኛው ሃይማኖት ሊሆን አይችልም ብዬ ስላሰብኩ ውይይቱን መቀጠል ከበደኝ። ሰዎች ከእኛ የተለየ አለባበስ የሚለብሱበት ብቸኛው ምክንያት ኩራት እንደሆነና አንድ ሰው ብዙ ነገሮች በኖሩት መጠን ይበልጥ ኩሩ እንደሚሆን ይሰማኝ ነበር።

ጄምስ ከወንዶች ልጆቻችን መካከል አንዳንዶቹን ይዞ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። ይህ በጣም አበሳጨኝ። ባለቤቴ አብሬው እንድሄድ በተደጋጋሚ ቢጠይቀኝም ፈቃደኛ አልሆንኩም። ከዚያም አንድ ቀን “በሚያስተምሯቸው አንዳንድ ነገሮች ባትስማሚ እንኳ እስቲ ሄደሽ በመካከላቸው ያለውን ፍቅር በገዛ ዓይንሽ ተመልከቺ” አለኝ። ይህ እሱን በጣም አስገርሞት ነበር።

በመጨረሻም፣ ትምህርታቸው ተጽዕኖ እንዳያሳድርብኝ ራሴን በደንብ አዘጋጅቼ በስብሰባቸው ላይ ለመገኘት ተስማማሁ። ወደ ስብሰባ አዳራሹ የሄድኩት ወጥ ቀለም ያለው ቀሚስ ለብሼና ኮፍያ አድርጌ ነበር። ከወንዶች ልጆቻችን አንዳንዶቹ ባዶ እግራቸውን የነበሩ ሲሆን እነሱም ወጥ ቀለም ያለው ልብስ ለብሰው ነበር። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮቹ ወደ እኛ መጥተው ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን። ‘ከእነሱ የተለየን ብንሆንም በጥሩ መንፈስ ነው የተቀበሉን’ ብዬ አሰብኩ።

ባሳዩኝ ፍቅር በጣም ብደነቅም እንዲሁ ከማየት ውጭ ምንም ላለማድረግ ወስኜ ነበር። መዝሙር ሲዘመር ለመነሳትም ሆነ አብሬ ለመዘመር ፈቃደኛ አልነበርኩም። ስብሰባው ካለቀ በኋላ በርካታ ጥያቄዎችን አዥጎደጉድባቸዋለሁ፤ ትክክል እንዳልሆኑ የማስባቸውን ነገሮች ወይም የአንዳንድ ጥቅሶችን ማብራሪያ በተመለከተ እጠይቃቸዋለሁ። ጥያቄዎቹን የማቀርብበት መንገድ ብዙም ዘዴኝነት የሚንጸባረቅበት ባይሆንም የምጠይቃቸው ሰዎች ሁሉ በደግነት መልስ ይሰጡኝ ነበር። የምጠይቀው የተለያዩ ሰዎችን ቢሆንም ሁሉም ተመሳሳይ መልስ የሚሰጡኝ መሆኑ አስገረመኝ። አንዳንድ ጊዜ የሚመልሱልኝ በጽሑፍ ነበር። ይህም በጣም ጠቅሞኛል፤ ምክንያቱም በግሌ ማጥናት የምችልበት አጋጣሚ ሰጥቶኛል።

በ1985 የበጋ ወቅት ቤተሰባችን በይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ሜምፊስ፣ ቴነሲ ተጓዘ፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን ዓላማችን እንዲሁ ማየት ነበር። ጄምስ እንደተለመደው ጢሙን አሳድጎ የነበረ ሲሆን እኛም ወጥ ቀለም ያለው ልብሳችንን ለብሰን ነበር። በእረፍት ሰዓት ላይ፣ ሁሌም ማለት ይቻላል፣ የሆነ ሰው አብሮን ሆኖ ያጫውተን ነበር። ያሳዩን ፍቅር፣ የሰጡን ትኩረትና ያደረጉልን አቀባበል በጣም ማረከን። አንድነታቸውም በጣም አስገረመን፤ የትም ቦታ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ብንገኝ የሚሰጠው ትምህርት ተመሳሳይ ነው።

ጄምስ የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩት ፍቅር ልቡ በጥልቅ ስለተነካ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። የሚማረው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ ይመረምር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 17:11፤ 1 ተሰሎንቄ 5:21) በጊዜ ሂደት ጄምስ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ ሆነ። እኔ ግን ውሳኔ ማድረግ ከብዶኝ ነበር። ትክክል የሆነውን ማድረግ ብፈልግም “ዘመናዊ” መሆንና እንደ “ዓለማዊ ሰው” መቆጠር አልፈለግኩም ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና በአንድ እጄ ኪንግ ጄምስ ቨርዥንን በሌላ እጄ ደግሞ ይበልጥ ዘመናዊ የሆነውን አዲስ ዓለም ትርጉምን ይዤ ነበር። ማንም እንዲያታልለኝ ስላልፈለግኩ እያንዳንዱን ጥቅስ በሁለቱም ትርጉሞች አስተያይ ነበር።

አመለካከቴን እንድለውጥ የረዳኝ ነገር

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናታችንን ስንቀጥል በሰማይ ያለው አባታችን ሥላሴ ሳይሆን አንድ አምላክ እንደሆነ እንዲሁም እኛ የማትሞት ነፍስ ያለን ፍጡራን ሳንሆን ራሳችን ነፍስ እንደሆንን ተማርን። (ዘፍጥረት 2:7፤ ዘዳግም 6:4፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) በተጨማሪም ሲኦል የሞቱ ሰዎች ሁሉ የሚቀበሩበት ቦታ እንጂ በእሳት የምንሠቃይበት ቦታ እንዳልሆነ ተገነዘብን። (ኢዮብ 14:13፤ መዝሙር 16:10፤ መክብብ 9:5, 10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:31) ስለ ሲኦል እውነቱን ማወቄ በአመለካከቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፤ ምክንያቱም ቀድሞ በነበርኩበት ሃይማኖት ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከት ነበር።

ያም ሆኖ የይሖዋ ምሥክሮች በእኔ አመለካከት የዓለም ክፍል ስለነበሩ እውነተኛውን ሃይማኖት ይዘዋል ብሎ ማመን ከብዶኝ ነበር። እኔ ትልቅ ቦታ የምሰጠውን ቀላል የሆነ የአኗኗርና የአለባበስ ዘይቤ አይከተሉም። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ የመንግሥቱን ምሥራች ለሰው ሁሉ እንድንሰብክ የሰጠውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ያሉት እነሱ እንደሆኑ አስተዋልኩ። በጣም ግራ ተጋባሁ!—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

ግራ ተጋብቼ በነበረበት በዚህ ወቅት፣ ምርምር ማድረጌን እንድቀጥል የረዳኝ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩኝ ፍቅር ነው። መላው ጉባኤ ለቤተሰባችን ፍቅር አሳይቶናል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሰዎች፣ አንዳንዴም ወተትና እንቁላል ከእኛ መግዛትን እንደ ሰበብ በመጠቀም መጥተው ይጠይቁን ስለነበር ጥሩ ሰዎች እንደሆኑ ማስተዋል ቻልን። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናን አንድ ሰው ቢሆንም ሌሎቹም ቸል አላሉንም። እንዲያውም ወደ እኛ አካባቢ የሚመጡበት ጉዳይ ካጋጠማቸው ቤታችን ብቅ ሳይሉ አይሄዱም። ይህ አጋጣሚ የይሖዋ ምሥክሮችን በደንብ ለማወቅ እንዲሁም ለእኛ ያላቸውን ከልብ የመነጨ ፍቅር ለማየት አስችሎናል።

እንዲህ ያለ ፍቅር ያሳዩን በአቅራቢያችን ባለ ጉባኤ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አልነበሩም። በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ጉዳይ ግራ ተጋብቼ በነበረበት ወቅት ሌላ ጉባኤ ያለች ኬ ብሪግዝ የተባለች እህት ልትጠይቀኝ መጣች፤ ይህች እህት በራሷ ምርጫ የተነሳ ቀለል ያለ ልብስ ትለብስ የነበረ ከመሆኑም ሌላ መኳኳያ አትጠቀምም ነበር። ከእሷ ጋር በነፃነት ማውራት ቻልኩ። አንድ ቀን ደግሞ ሉዊስ ፍሎራ የተባለ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሃይማኖት ውስጥ ያደገ ሰው ሊጠይቀኝ መጣ። ግራ ተጋብቼ እንደነበር ከፊቴ ገጽታ ማስተዋል ስለቻለ እኔን ለመርዳት ሲል አሥር ገጽ የያዘ ደብዳቤ ጻፈልኝ። ባሳየኝ ደግነት በጣም ስለተነካሁ አለቀስኩ፤ ደብዳቤውን ብዙ ጊዜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ።

ኦዴል የተባለን ተጓዥ የበላይ ተመልካች የሆነ ወንድም ኢሳይያስ 3:18-23⁠ን እና 1 ጴጥሮስ 3:3, 4⁠ን እንዲያብራራልኝ ጠየቅኩት። “እነዚህ ጥቅሶች አምላክን ማስደሰት ከፈለግን ቀለል ያለ አለባበስ መልበስ እንዳለብን የሚጠቁሙ አይደሉም?” አልኩት። እሱም “ኮፍያ ማድረግ ስህተት ነው? ፀጉርን ሹሩባ መሠራትስ ስህተት ይመስልሻል?” ብሎ ጠየቀኝ። በእኛ ሃይማኖት ትናንሽ ሴት ልጆች ፀጉራቸውን ሹሩባ የሚሠሩ ሲሆን ተለቅ ያሉ ሴቶች ደግሞ ኮፍያ ያደርጋሉ። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ያቀረበው ሐሳብ የነበረን አቋም ወጥነት የሌለው እንደሆነ እንዳስተውል ረዳኝ፤ በተጨማሪም በትዕግሥትና በደግነት ያነጋገረኝ መሆኑ በጣም አስገረመኝ።

በጊዜ ሂደት አመለካከቴን እያስተካከልኩ ብሄድም አሁንም መቀበል የከበደኝ ጉዳይ ነበር፤ ይህም ሴቶች ፀጉራቸውን የሚቆረጡ መሆኑ ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች የአንዳንድ ሴቶች ፀጉር በጣም ረጅም ቢሆንም የአንዳንዶቹ ግን ከተወሰነ ርዝመት በላይ እንደማያድግ ከገለጹልኝ በኋላ ይህ መሆኑ የአንዷን ሴት ፀጉር ከሌላዋ የተሻለ እንደማያደርገው እንዳስተውል ረዱኝ። በተጨማሪም በአለባበስና በፀጉር አያያዝ ረገድ ሕሊና የሚጫወተውን ሚና ያብራሩልኝ ሲሆን ቤት ሄጄ የማነበው ነገር ሰጡኝ።

የተማርነውን ነገር ተግባር ላይ ማዋል

በመጨረሻም ስንፈልጋቸው የነበሩትን ጥሩ ፍሬ የሚያፈሩ ሰዎች አገኘን። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ፍቅር የሚያሳዩ ሰዎች እንደሆኑ እርግጠኛ ሆንን። ይሁንና የመጀመሪያው ልጃችን ናታን እና ሁለተኛዋ ልጃችን ሬቤካ የቀድሞውን ሃይማኖታችንን ተቀብለውና በዚያ ሃይማኖት ተጠምቀው ስለነበር ሁኔታው ግራ አጋብቷቸው ነበር። በጊዜ ሂደት ግን በምንነግራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና የይሖዋ ምሥክሮች በሚያሳዩአቸው ፍቅር ልባቸው ይነካ ጀመር።

ሬቤካ ከድሮ ጀምሮ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖራት ትፈልግ ነበር። አምላክ የምናደርገውን ነገር ወይም የወደፊቱን ሕይወታችንን አስቀድሞ እንዳልወሰነ ስታውቅ ወደ እሱ መጸለይ ይበልጥ ቀላል ሆነላት። በተጨማሪም አምላክ ሚስጥራዊ የሆነ ሥላሴ ክፍል ሳይሆን ልትመስለው የምትችል እውን አካል እንደሆነ ማወቋ ወደ እሱ ይበልጥ እንድትቀርብ ረዳት። (ኤፌሶን 5:1) እንዲሁም እሱን ስታነጋግር ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ላይ ያለውን ጥንታዊ አነጋገር መጠቀም እንደማያስፈልጋት ስትማር በጣም ደስ አላት። አምላክ ጸሎትን በተመለከተ ስላወጣው መሥፈርት እንዲሁም የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ስላለው ዓላማ ማወቋ ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ፈጣሪዋ እንድትቀርብ አደረጋት።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4

ያገኘናቸው መብቶች

እኔና ጄምስ እንዲሁም ከፍ ያሉት አምስቱ ልጆቻችን ናታን፣ ሬቤካ፣ ጆርጅ፣ ዳንኤል እና ጆን በ1987 የበጋ ወቅት ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን። ሃርሊ በ1989 የተጠመቀ ሲሆን ሳይመን ደግሞ በ1994 ተጠመቀ። መላው ቤተሰባችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ በሰጠው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ሥራ በትጋት ይካፈላል።

አምስቱ ወንዶች ልጆቻችን ናታን፣ ጆርጅ፣ ዳንኤል፣ ጆን እና ሃርሊ እንዲሁም ሴት ልጃችን ሬቤካ በዩናይትድ ስቴትስ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ አገልግለዋል። ጆርጅ ላለፉት 14 ዓመታት በቅርንጫፍ ቢሮው እያገለገለ ነው፤ ሳይመን ደግሞ በ2001 ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮው ማገልገል ጀምሯል። ሁሉም ወንዶች ልጆቻችን በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም አገልጋይ ናቸው። ባለቤቴ በሚዙሪ ባለው ቴየር ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ሲሆን እኔም በአገልግሎት በትጋት እየተካፈልኩ ነው።

አሁን ጄሲካ፣ ላቲሻ እና ካሌብ የተባሉ ሦስት የልጅ ልጆች አሉን፤ ወላጆቻቸው ከሕፃንነታቸው አንስቶ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያዳብሩ ሲረዷቸው ማየት በጣም ያስደስተናል። ይሖዋ ቤተሰባችንን ወደ እሱ ስለሳበ እንዲሁም በስሙ የሚጠሩትን ሕዝቦቹን በሚያሳዩት ፍቅር አማካኝነት ለይተን እንድናውቃቸው ስለረዳን ከልብ እናመሰግነዋለን።

አምላክን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ሆኖም ሕሊናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ባደጉበት ማኅበረሰብ የተቀረጸ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ ስናስብ በጣም እናዝናለን። እነዚህ ሰዎች እኛ ያገኘነውን ደስታ እንዲያጣጥሙ እንመኛለን። አሁን ቤተሰባችን ከቤት ወደ ቤት የሚሄደው ያመረተውን አትክልት ለመሸጥ ሳይሆን ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ወደፊት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለመናገር ነው። የይሖዋን ስም የተሸከሙት ሰዎች ስላሳዩን ትዕግሥትና ፍቅር ሳስብ ልቤ በአድናቆት ከመሞላቱ የተነሳ እንባ ይተናነቀኛል!

[ሥዕል]

ሰባት ዓመት ገደማ ሳለሁ፣ በኋላም አዋቂ ሆኜ

[ሥዕል]

ጄምስ፣ ጆርጅ፣ ሃርሊ እና ሳይመን ወጥ የሆነ ቀለም ያለው ልብስ ለብሰው

[ሥዕል]

አትክልቶችን ገበያ ወስጄ ስሸጥ የተነሳሁት ይህ ፎቶግራፍ በአካባቢያችን በሚታተም ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር

[ምንጭ]

Journal and Courier, Lafayette, Indiana

[ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከቤተሰባችን ጋር