በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሣጥን 14ሀ

ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ካየው ራእይ የምናገኛቸው ትምህርቶች

ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ካየው ራእይ የምናገኛቸው ትምህርቶች

ንጹሕ አምልኮ ከፍ ከፍ ተደረገ፤ ጥበቃም ተደረገለት

በራእይ የታየው ቤተ መቅደስ የሚገኘው “ትልቅ ተራራ” (1) ላይ ነው። እኛስ ንጹሕ አምልኮን በሕይወታችን ውስጥ በማስቀደም ከፍ ከፍ እንዲል እያደረግነው ነው?

በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለው በቅጥር (2) የታጠረ ሰፊ ቦታ (3) ማንኛውም ነገር ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ እንዲበክልብን መፍቀድ እንደሌለብን ያሳስበናል። ሕዝቅኤል 42:20 ቅጥሩ “ቅዱስ የሆነውንና ቅዱስ ያልሆነውን” ነገር ለመለየት እንደሚያገለግል ይናገራል። እዚህ ላይ “ቅዱስ ያልሆነ” ሲል ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ነገሮች ማመልከቱ ነው። እነዚህን ነገሮች እንኳ ከንጹሑ አምልኮ ማራቅ ካስፈለገ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ርኩስ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ ከሆኑ ድርጊቶች መራቃቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ዘላለማዊ በረከቶች

ቀስ ብሎ የሚፈስ አንድ ምንጭ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ትልቅ ወንዝ በመሆን በምድሪቱ ላይ ልምላሜና ሕይወት ይዘራል (4)። ይህ ወንዝ የሚያመጣቸው በረከቶች በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 19 ላይ ይብራራሉ።

ለሁሉም አንድ ዓይነት መሥፈርት

ረጃጅሞቹ ውጨኛ በሮችና (5) ውስጠኛ በሮች (9) ይሖዋ በንጹሕ አምልኮ ለሚካፈሉ ሁሉ ከፍ ያለ የሥነ ምግባር መሥፈርት እንዳወጣ ያሳስቡናል። ውጨኞቹና ውስጠኞቹ በሮች እኩል መጠን ያላቸው መሆኑን ልብ በል። ይህ መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ አገልጋዮቹ ያላቸው ኃላፊነትም ሆነ የአገልግሎት መብት ምንም ይሁን ምን፣ ለሁሉም ያወጣው የጽድቅ መሥፈርት አንድ ዓይነት ነው።

ከይሖዋ ማዕድ መመገብ

የመመገቢያ ክፍሎቹ (8) በጥንት ጊዜ ሕዝቡ፣ ካመጧቸው መሥዋዕቶች ይበሉ እንደነበር ያስታውሱናል፤ ይህን ሲያደርጉ ከይሖዋ ጋር በአንድ ማዕድ አብረው እንደተመገቡ ይቆጠር ነበር። እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች አምልኮ በሚያቀርቡበት መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው፤ ምክንያቱም “ለሁልጊዜ የሚሆን አንድ መሥዋዕት” አስቀድሞ ቀርቧል። (ዕብ. 10:12) ያም ሆኖ በዛሬው ጊዜም የውዳሴ መሥዋዕት እናቀርባለን።—ዕብ. 13:15

መለኮታዊ ዋስትና

በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የሰፈረው ከልኬት ጋር የተያያዘ ዝርዝር መረጃ ብዛት ግራ ሊያጋባን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ የሚከተለውን ወሳኝ ነጥብ ያስገነዝበናል፦ የእያንዳንዱ ነገር መጠን ተለክቶ በትክክል መጠቀሱ ይሖዋ ንጹሕ አምልኮን መልሶ ለማቋቋም ያለው ዓላማ የተረጋገጠ እንደሆነና ዝንፍ ሳይል በትክክል እንደሚፈጸም ዋስትና ይሰጠናል። ሕዝቅኤል በራእዩ ላይ ምንም ሰብዓዊ ፍጡር እንዳየ ባይገልጽም ይሖዋ ለካህናቱ፣ ለአለቆቹና ለሕዝቡ የሰጠውን ኃይለኛ ምክር አስፍሮልናል። ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የጽድቅ መሥፈርቶቹን መጠበቅ አለባቸው።