በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በ1919 የተካሄደው ታሪካዊ ስብሰባ የአምላክ ሕዝቦች በመጨረሻ ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ እንደወጡ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነበር

ሣጥን 9ለ

በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው?

በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው?

የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ የወጡት በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶችና የታሪክ ማስረጃዎችን አጣምረን ስናይ እዚህ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን።

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና የታሪክ ማስረጃዎች ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረው በ1914 እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ያሳያሉ፤ እዚህ ምድር ላይ ያለው የሰይጣን ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት የጀመሩትም በዚህ ጊዜ ነው። ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ምን እርምጃ ወሰደ? በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን ወዲያውኑ ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ አውጥቷቸዋል? በ1914 “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሾም ታላቁን የመከር ሥራ ጀምሯል?—ማቴ. 24:45

እንዲህ እንዳላደረገ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ፍርድ ከአምላክ ቤት እንደሚጀምር’ በመንፈስ መሪነት እንደተናገረ ልብ በል። (1 ጴጥ. 4:17) በተመሳሳይም ነቢዩ ሚልክያስ ይሖዋ “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ከሆነው ከኢየሱስ ጋር ሆኖ ወደ ቤተ መቅደሱ እንደሚመጣ ተንብዮአል። (ሚል. 3:1-5) ያ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች የሚጠሩበትና የሚፈተኑበት ጊዜ ይሆናል። ታዲያ ታሪክ በዚያ ወቅት እንዲህ ዓይነት ነገር እንደተፈጸመ ያሳያል?

አዎ ያሳያል! ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ ያለው ጊዜ፣ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የማጥሪያና የፈተና ጊዜ ነበር። ብዙዎቹ የአምላክ አገልጋዮች፣ ተስፋ አድርገውት እንደነበረው በ1914 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ባለመምጣቱ አዝነው ነበር። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ግንባር ቀደም ሆኖ ሥራውን ይመራ የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በ1916 ሲሞት ደግሞ ይበልጥ ተስፋ ቆረጡ። ለወንድም ራስል ከልክ በላይ ትኩረት ይሰጡ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ራስልን ተክቶ ሥራውን ይመራ የነበረው ጆሴፍ ራዘርፎርድ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በጥብቅ መቃወም ጀመሩ። በ1917 በአምላክ ሕዝቦች መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን ድርጅቱ ለሁለት ሊከፈል ተቃርቦ ነበር። ከዚያም በ1918 ወንድም ራዘርፎርድና ሰባት የሥራ ባልደረቦቹ በቀሳውስት አነሳሽነት ተከሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡና ኢፍትሐዊ ፍርድ ከተፈረደባቸው በኋላ ወደ እስር ቤት ተላኩ። በብሩክሊን የነበረው ዋና መሥሪያ ቤትም ተዘጋ። የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንዳልወጡ ግልጽ ነበር!

ይሁን እንጂ በ1919 ምን ተከሰተ? ሁኔታዎች በቅጽበት ተለዋወጡ! በ1919 መጀመሪያ አካባቢ ራዘርፎርድና የሥራ ባልደረቦቹ ከእስር ተለቀቁ። ወዲያውኑም ሥራቸውን ማከናወን ቀጠሉ! በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ታሪካዊ ስብሰባ ለማካሄድ እቅድ ተያዘ። ከዚህም ሌላ በአሁኑ ጊዜ ንቁ! በመባል የሚጠራው ወርቃማው ዘመን የተባለ አዲስ መጽሔት መዘጋጀት ጀመረ። ይህ አዲስ መጽሔት የተዘጋጀው ለመስክ አገልግሎት እንዲረዳ ታስቦ ነበር። በተጨማሪም በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የመስክ አገልግሎትን የሚያደራጅና ግንባር ቀደም ሆኖ የሚመራ የበላይ ተመልካች ተሾመ። በዚያው ዓመት የስብከቱን ሥራ ለማደራጀት የሚረዳ ቡለቲን (አሁን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ ይባላል) የተባለ ጽሑፍ መታተም ጀመረ።

ይህ ሁሉ ምን ያሳያል? ክርስቶስ ሕዝቦቹን ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ እንዳወጣና ታማኝና ልባም ባሪያን እንደሾመ እንዲሁም የመከሩ ሥራ እንደጀመረ ግልጽ ነበር። በታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከጀመረበት ከዚያ ዓመት ማለትም ከ1919 አንስቶ ሥራው አስደናቂ በሆነ ፍጥነት ወደፊት መገስገሱን ቀጥሏል።