በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሣጥን 15ሀ

ዝሙት አዳሪዎቹ እህትማማቾች

ዝሙት አዳሪዎቹ እህትማማቾች

ሕዝቅኤል ምዕራፍ 23 የአምላክ ሕዝቦች በፈጸሙት ክህደት ምክንያት የተሰነዘረባቸውን ከባድ የውግዘት ቃል ይዟል። ይህ ምዕራፍ፣ ከምዕራፍ 16 ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላል። እንደ ምዕራፍ 16 ሁሉ ምዕራፍ 23ም ዝሙት አዳሪነትን እንደ ምሳሌ ይጠቀማል። ኢየሩሳሌምና ሰማርያ እንደ እህትማማቾች ተደርገው የተገለጹ ሲሆን ኢየሩሳሌም ታናሽ፣ ሰማርያ ደግሞ ታላቅ እንደሆነች ተገልጿል። ሁለቱም ምዕራፎች ታናሽየዋ ታላቅ እህቷን ተከትላ እንዴት ዝሙት አዳሪ እንደሆነች፣ በኋላ ግን ታላቋን በክፋትም ሆነ በብልግና እንዴት እንደበለጠቻት ይናገራሉ። በምዕራፍ 23 ላይ ይሖዋ ለሁለቱም እህትማማቾች ስም አውጥቶላቸዋል። ታላቅየዋ ኦሆላ ተብላ የተጠራች ሲሆን የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ የነበረችውን ሰማርያን ታመለክታለች። ታናሽየዋ ደግሞ ኦሆሊባ የምትባል ሲሆን የይሁዳ ዋና ከተማ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ታመለክታለች። *ሕዝ. 23:1-4

ሁለቱን ምዕራፎች የሚያመሳስሏቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ከእነዚህ መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የሚከተሉት ሳይሆኑ አይቀሩም፦ ዝሙት አዳሪዎቹ መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ሚስቶች የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ከድተውታል። በተጨማሪም በሁለቱም ምዕራፎች ላይ ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት አለ። ምዕራፍ 23 ላይ ይህ ተስፋ በግልጽ የተቀመጠ ባይሆንም ይሖዋ “ጸያፍ [ምግባርሽና] አመንዝራነትሽ እንዲያበቃ አደርጋለሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ከምዕራፍ 16 ጋር ይመሳሰላል።—ሕዝ. 16:16, 20, 21, 37, 38, 41, 42፤ 23:4, 11, 22, 23, 27, 37

ለሕዝበ ክርስትና ጥላ ይሆናሉ?

ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን ሁለቱ እህትማማቾች ኦሆላና ኦሆሊባ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት እምነቶች ለተከፈለችው ሕዝበ ክርስትና ትንቢታዊ ጥላ እንደሆኑ ይናገሩ ነበር። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ የተደረገው ጸሎት የታከለበት ተጨማሪ ጥናትና ምርምር አንዳንድ ጥያቄዎች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል። ሕዝበ ክርስትና የይሖዋ ሚስት ሆና ታውቃለች? ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ተጋብታስ ታውቃለች? እንደማታውቅ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ጋር የተደረገውን “አዲስ ቃል ኪዳን” መካከለኛ ሆኖ ባቋቋመበት ጊዜ ሕዝበ ክርስትና ገና ወደ ሕልውና አልመጣችም፤ በተጨማሪም ሕዝበ ክርስትና ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈው መንፈሳዊ ብሔር ክፍል ሆና አታውቅም። (ኤር. 31:31፤ ሉቃስ 22:20) ሕዝበ ክርስትና ወደ ሕልውና የመጣችው ራሱ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ትንቢት ላይ ‘በእንክርዳድ’ የተመሰሉትን አስመሳይ ክርስቲያኖች ያቀፈች ብልሹና ከሃዲ ድርጅት ሆና ወደ ሕልውና የመጣችው በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ነበር።—ማቴ. 13:24-30

ሌላው ትልቅ ልዩነት ደግሞ የሚከተለው ነው፦ ይሖዋ ከዳተኞቹ ኢየሩሳሌምና ሰማርያ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ሰጥቶ ነበር። (ሕዝ. 16:41, 42, 53-55) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝበ ክርስትና ተመሳሳይ ተስፋ እንዳላት ይናገራል? በፍጹም! የእሷም ዕጣ በታላቂቱ ባቢሎን ሥር ካሉት ከሌሎቹ የሐሰት ሃይማኖቶች የተለየ አይደለም።

ስለዚህ ኦሆላና ኦሆሊባ የሕዝበ ክርስትና ትንቢታዊ ጥላ አይደሉም። ይሁን እንጂ ስለ እነሱ የሚገልጸው ዘገባ አንድን አስፈላጊ እውነታ ይኸውም ይሖዋ የእሱ ሕዝቦች እንደሆኑ እየተናገሩ ቅዱስ ስሙን ለሚያሰድቡና ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት ለማያከብሩ ሁሉ ያለውን አመለካከት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ሕዝበ ክርስትና በዚህ ረገድ በእጅጉ ተጠያቂ ነች፤ ምክንያቱም በሺዎች የሚቆጠሩት አብያተ ክርስቲያናቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነውን አምላክ እንወክላለን ይላሉ። ከዚህም ሌላ የይሖዋ ውድ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መሪያቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስን የሥላሴ አንድ አካል አድርገው ስለሚመለከቱትና ‘የዓለም ክፍል አትሁኑ’ ሲል የሰጠውን ግልጽ ትእዛዝ ስለሚጥሱ ይህን አባባላቸውን መልሰው ይሽሩታል። (ዮሐ. 15:19) ሕዝበ ክርስትና በጣዖት አምልኮና በፖለቲካዊ ጉዳዮች የምትካፈል መሆኑ ‘የታላቂቱ አመንዝራ’ ክፍል መሆኗን በማያሻማ መንገድ ያሳያል። (ራእይ 17:1) በመሆኑም በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ የምትወክለው ታላቂቱ ባቢሎን ከሚደርስባት ዕጣ ተካፋይ እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለውም!

^ አን.3 ስማቸው በራሱ የሚያስተላልፈው ትርጉም አለ። ኦሆላ የሚለው ስም “የእሷ [የአምልኮ] ድንኳን” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህም እስራኤል በኢየሩሳሌም በሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ከመጠቀም ይልቅ የራሷን የአምልኮ ማዕከሎች ማቋቋሟን የሚያመለክት ስያሜ ሳይሆን አይቀርም። ኦሆሊባ ማለት ደግሞ “[የአምልኮ] ድንኳኔ በእሷ ውስጥ ነው” ማለት ነው። ኢየሩሳሌም የይሖዋ የአምልኮ ቤት የሚገኝባት ከተማ ነበረች።