ሣጥን 1ለ
የሕዝቅኤል መጽሐፍ አጠቃላይ ይዘት
በጥቅሉ ሲታይ የሕዝቅኤል መጽሐፍ በሚከተለው መንገድ ሊከፋፈል ይችላል፦
ከምዕራፍ 1 እስከ 3
ሕዝቅኤል በ613 ዓ.ዓ. በባቢሎን ከአይሁዳውያን ግዞተኞች ጋር ይኖር በነበረበት ወቅት ይሖዋ ራእይ ያሳየው ሲሆን በኬባር ወንዝ አጠገብ ለሚኖሩ አይሁዳውያን ትንቢት እንዲናገር ተልእኮ ተሰጠው።
ከምዕራፍ 4 እስከ 24
ሕዝቅኤል ከ613 እስከ 609 ዓ.ዓ. ባሉት ዓመታት በዋነኝነት በኢየሩሳሌም እንዲሁም ዓመፀኛና ጣዖት አምላኪ በሆኑት ነዋሪዎቿ ላይ የተላለፈውን ፍርድ የያዙ ትንቢታዊ መልእክቶችን ተናገረ።
ከምዕራፍ 25 እስከ 32
ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ለመጨረሻ ጊዜ ከከበቡበት ከ609 ዓ.ዓ. አንስቶ ሕዝቅኤል በኢየሩሳሌም ላይ የፍርድ መልእክት መናገሩን በመተው ጠላት በሆኑት ብሔራት ማለትም በአሞን፣ በኤዶም፣ በግብፅ፣ በሞዓብ፣ በፍልስጤም፣ በሲዶናና በጢሮስ ላይ የተላለፉትን የፍርድ መልእክቶች ማወጅ ጀመረ።
ከምዕራፍ 33 እስከ 48
ከባቢሎን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኘው ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ የፍርስራሽ ክምር ከሆኑ በኋላ ሕዝቅኤል በ606 ዓ.ዓ. ተስፋ ሰጪ የሆነ መልእክት ማወጅ ጀመረ፤ ይህ አስደሳች መልእክት የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጽ ነበር።
ስለዚህ የሕዝቅኤል መጽሐፍ በጊዜ ቅደም ተከተልና በርዕሰ ጉዳይ የተቀመጠ ነው ማለት ይቻላል። ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጹት ትንቢቶች የሰፈሩት ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ቤተ መቅደሱ መጥፋት ከሚናገሩት ትንቢቶች በኋላ ነው። ደግሞም ይህ መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም ትንቢት መናገር ያስፈለገው በቤተ መቅደሱ ይከናወን የነበረው አምልኮ ተቋርጦ ስለነበረ ነው።
በተጨማሪም በአጎራባች ጠላት ብሔራት ላይ ስለተላለፈው ፍርድ የሚገልጹት ትንቢቶች (ከምዕራፍ 25 እስከ 32) የሚገኙት በኢየሩሳሌም ላይ ስለተላለፈው ፍርድ በሚናገሩትና ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም በሚገልጹት ትንቢቶች መካከል ነው። አንድ ምሁር ሕዝቅኤል በብሔራት ላይ ያስተላለፋቸውን የፍርድ መልእክቶች አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ የፍርድ መልእክቶች አምላክ በሕዝቦቹ ላይ ባስተላለፈው የቁጣ መልእክትና ለሕዝቦቹ ምሕረት እንደሚያሳይ በሚገልጸው መልእክት መካከል እንደ መሸጋገሪያ ሆነው መቀመጣቸው ተስማሚ ነው። ምክንያቱም የእነዚህ ጠላት ብሔራት መቀጣት በራሱ አምላክ ሕዝቡን ነፃ የሚያወጣበት አንዱ መንገድ ነው።”