በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሣጥን 19ሀ

የይሖዋን በረከት የሚያስገኙ ወንዞች

የይሖዋን በረከት የሚያስገኙ ወንዞች

“ወንዝ” እና “ውኃ” የሚሉት ቃላት ይሖዋ የሚያፈሳቸውን በረከቶች ለማመልከት እንዴት እንደተሠራባቸው የሚያሳዩ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንመልከት። እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ ይሖዋ እኛን ለመባረክ የሚጠቀምባቸውን መንገዶች በተመለከተ አበረታች ትምህርት እናገኛለን።

ኢዩኤል 3:18 ይህ ትንቢት ከቤተ መቅደሱ ስለሚፈልቅ ምንጭ ይናገራል። ይህ ምንጭ ደረቅ የሆነውን ‘የሺቲምን ሸለቆ’ ያጠጣል። ስለዚህ ኢዩኤልም ሆነ ሕዝቅኤል አንድ ወንዝ ጠፍ የሆነን ምድር ነፍስ ሲዘራበት ተመልክተዋል። በሁለቱም ትንቢቶች ላይ ወንዙ የወጣው ከይሖዋ ቤት ወይም ቤተ መቅደስ እንደሆነ ተገልጿል።

ዘካርያስ 14:8 ነቢዩ ዘካርያስ “ሕያው ውኃዎች” ከኢየሩሳሌም ከተማ ሲወጡ ተመልክቷል። ግማሹ ውኃ የሚፈሰው በስተ ምሥራቅ ወዳለው ባሕር ማለትም ወደ ሙት ባሕር ሲሆን ግማሹ ደግሞ የሚፈሰው በስተ ምዕራብ ወዳለው ባሕር ማለትም ወደ ሜድትራንያን ባሕር ነው። ኢየሩሳሌም “የታላቁ ንጉሥ” የይሖዋ አምላክ ከተማ ነበረች። (ማቴ. 5:35) በመሆኑም ዘካርያስ ይህችን ከተማ መጥቀሱ ወደፊት በመላው ምድር የሚሰፍነውን የይሖዋ አገዛዝ ያስታውሰናል። በዚህ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱት ውኃዎች ይሖዋ በገነት ውስጥ ሁለት ቡድኖችን፣ ማለትም ታላቁን መከራ በሕይወት የሚያልፉትንና ከጊዜ በኋላ ከሞት የሚነሱትን ታማኝ ሰዎች እንደሚባርክ ያመለክታሉ።

ራእይ 22:1, 2 ሐዋርያው ዮሐንስ ሕዝቅኤል ካየው ወንዝ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ምሳሌያዊ ወንዝ ተመልክቶ ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ያየው ወንዝ የሚወጣው ከቤተ መቅደሱ ሳይሆን ከይሖዋ ዙፋን ነበር። ስለዚህ ዘካርያስ እንዳየው ራእይ ሁሉ ይህ ራእይም የሚያጎላው የይሖዋ አገዛዝ በሺው ዓመት ግዛት ወቅት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ሳይሆን አይቀርም።

እርግጥ ነው፣ የይሖዋ አገዛዝ በሚያስገኛቸው በረከቶችና ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ በሚያስገኛቸው በረከቶች መካከል የጎላ ልዩነት የለም። ሁሉም በረከቶች የሚፈስሱት ከይሖዋ ሲሆን የሚፈስሱትም ታማኝ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ነው።

መዝሙር 46:4 ይህ ጥቅስ የይሖዋን በረከት የሚያስገኙትን ሁለቱንም ነገሮች ማለትም አምልኮንና አገዛዝን አጣምሮ እንደያዘ ልብ በል። እዚህ ጥቅስ ላይ መንግሥትንና አገዛዝን ለሚያመለክተው ‘የአምላክ ከተማ’ እንዲሁም ንጹሕ አምልኮን ለሚያመለክተው “የልዑሉ አምላክ የተቀደሰ ታላቅ ማደሪያ” ከፍተኛ ደስታ ስለሚያስገኝ ወንዝ ተገልጿል።

በጥቅሉ ሲታይ እነዚህ ጥቅሶች ይሖዋ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን በሁለት መንገዶች እንደሚባርክ ያረጋግጡልናል። አንደኛ ከይሖዋ አገዛዝ፣ ሁለተኛ ደግሞ ለንጹሕ አምልኮ ካደረገው ዝግጅት ዘላለማዊ ጥቅም እናገኛለን። ስለዚህ ይሖዋ አምላክና ልጁ ከሚሰጡን “ሕያው ውኃ” ለመጠጣት ማለትም የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ባደረጉልን ፍቅራዊ ዝግጅቶች በሚገባ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ኤር. 2:13፤ ዮሐ. 4:10