በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 4

‘አራት ፊት ያላቸው አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት’ ምን ያመለክታሉ?

‘አራት ፊት ያላቸው አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት’ ምን ያመለክታሉ?

ሕዝቅኤል 1:15

ፍሬ ሐሳብ፦ ሕዝቅኤል በራእይ ያያቸው ሕያዋን ፍጥረታት እና ስለ እነሱ በማጥናት የምናገኘው ትምህርት

1, 2. ይሖዋ ምድር ላይ ለሚገኙ አገልጋዮቹ አንዳንድ እውነቶችን ለማስተማር የሚታዩ ነገሮችን የተጠቀመው ለምንድን ነው?

ትናንሽ ልጆች ያሉበት አንድ ቤተሰብ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ይታይህ። አባትየው አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ለልጆቹ ለማስረዳት ሥዕል ሥሎ ያሳያቸዋል። በልጆቹ ፊት ላይ የሚነበበው ፈገግታና የሚሰጡት ሞቅ ያለ ሐሳብ የአባትየው ጥረት መሳካቱን ያሳያል። አባትየው በቃል ከማስረዳት በተጨማሪ ሥዕላዊ መግለጫዎችን መጠቀሙ ልጆቹ ከዕድሜያቸው አንጻር ለመረዳት ሊከብዳቸው የሚችለውን ስለ ይሖዋ የሚገልጽ ትምህርት እንዲረዱት አስችሏቸዋል።

2 በተመሳሳይም ይሖዋ ለመረዳት የሚከብዱ በዓይን የማይታዩ እውነታዎች ለሰብዓዊ ልጆቹ እውን እንዲሆኑላቸው ለማድረግ በሚታዩ ነገሮች ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ራሱ ጥልቀት ያላቸውን እውነታዎች ለማስረዳት ሲል አስገራሚ የሆኑ ምስሎችን የያዘ ራእይ ለሕዝቅኤል አሳይቶታል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ላይ ስለዚህ ራእይ ተመልክተናል። እስቲ አሁን ደግሞ በዚህ አስደናቂ ራእይ አንድ ክፍል ላይ ትኩረት እናድርግና ትርጉሙን መረዳታችን ወደ ይሖዋ ለመቅረብ እንዴት እንደሚረዳን እንመልከት።

የአራት ሕያዋን ፍጥረታትን አምሳያ ተመለከትኩ’

3. (ሀ) ሕዝቅኤል 1:4, 5 እንደሚናገረው ሕዝቅኤል በራእይ ምን ተመለከተ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ሕዝቅኤል ያየውን ነገር ሲጽፍ የተጠቀመባቸው አገላለጾች ምን ያስገነዝቡናል?

3 ሕዝቅኤል 1:4, 5ን አንብብ። ሕዝቅኤል የመልአክ፣ የሰውና የእንስሳ ገጽታ ስላላቸው “አራት ሕያዋን ፍጥረታት አምሳያ” ይናገራል። ሕዝቅኤል የሕያዋን ፍጥረታቱን “አምሳያ” እንደተመለከተ መናገሩን ልብ በል። በሕዝቅኤል ምዕራፍ 1 ላይ የሚገኘውን ሙሉውን ራእይ በምታነብበት ጊዜ ነቢዩ “ይመስላል፣” “የሚመስል፣” “እንደ” እና “ያለ” የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ እንደሚጠቀም ማስተዋልህ አይቀርም። (ሕዝ. 1:13, 24, 26) በእርግጥም ሕዝቅኤል፣ በራእይ የተመለከተው በሰማይ ላይ በእውን ያሉ በዓይን የማይታዩ ነገሮችን ምሳሌ ወይም ምስል እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።

4. (ሀ) ሕዝቅኤል ራእዩን ሲያይ ምን ተሰማው? (ለ) ሕዝቅኤል ስለ ኪሩቦች ምን የሚያውቀው ነገር እንዳለ መገመት ይቻላል?

4 ሕዝቅኤል በራእዩ ላይ ባያቸውና በሰማቸው ነገሮች በእጅጉ ተደንቆ መሆን አለበት። የአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መልክ “የሚነድ የከሰል ፍም” ይመስላል። እንዲሁም “ወዲያና ወዲህ ሲሄዱ እንቅስቃሴያቸው የመብረቅ ብልጭታ ይመስል ነበር።” የክንፎቻቸው ድምፅ “እንደሚጎርፍ ውኃ ድምፅ” ሲሆን ሕያዋን ፍጥረታቱ ሲንቀሳቀሱ የሚሰማው ድምፅ “እንደ ሠራዊት ድምፅ ነበር።” (ሕዝ. 1:13, 14, 24-28ሕያዋን ፍጥረታቱን እየተመለከትኩ ነበር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሕዝቅኤል ቆየት ብሎ ባየው ሌላ ራእይ ላይ እነዚህ ሕያዋን ፍጥረታት ‘ኪሩቦች’ ማለትም ኃያላን መላእክት መሆናቸውን ገልጿል። (ሕዝ. 10:2) ሕዝቅኤል በካህናት ቤተሰብ ውስጥ ያደገ እንደመሆኑ መጠን ኪሩቦች አምላክ በሚገኝበት ቦታ እንደሚገኙና አምላክን በቅርበት እንደሚያገለግሉ ያውቅ እንደነበር አያጠራጥርም።—1 ዜና 28:18፤ መዝ. 18:10

‘እያንዳንዳቸው አራት አራት ፊት ነበራቸው’

5. (ሀ) ኪሩቦቹና አራቱ ፊቶቻቸው የይሖዋን ኃያልነትና ግርማ የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው? (ለ) ይህ የራእዩ ክፍል የይሖዋን ስም ትርጉም እንድናስታውስ ያደርገናል የምንለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

5 ሕዝቅኤል 1:6, 10ን አንብብ። ሕዝቅኤል እያንዳንዱ ኪሩብ አራት ፊት ይኸውም የሰው፣ የአንበሳ፣ የበሬና የንስር ፊት እንደነበረው ተመልክቷል። ሕዝቅኤል እነዚህን አራት ፊቶች ማየቱ የይሖዋን ኃያልነትና ግርማ በተመለከተ ከአእምሮው የማይፋቅ ጥልቅ ስሜት አሳድሮበት መሆን አለበት። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በአራቱም ፊቶች የተወከሉት ፍጥረታት በግርማቸው፣ በጥንካሬያቸውና በኃያልነታቸው የሚታወቁ ናቸው። አንበሳ ታላቅ ግርማ ያለው አውሬ፣ በሬ ግዙፍ የቤት እንስሳ፣ ንስር በጥንካሬው የሚታወቅ ወፍ ሲሆን ሰው ደግሞ የአምላክ ምድራዊ ፍጥረታት ሁሉ የበላይና ገዢ ነው። (መዝ. 8:4-6) ይሁን እንጂ ሕዝቅኤል በኪሩቦቹ አራት ፊቶች የተወከሉት አራቱም ኃያላን ፍጥረታት የሚገኙት የሁሉም የበላይ ገዢ ከሆነው ከይሖዋ ዙፋን ሥር እንደሆነ ተመልክቷል። ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ፍጥረታቱን ሊጠቀም እንደሚችል የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! * በእርግጥም ይሖዋ፣ መዝሙራዊው እንደተናገረው “ግርማው ከምድርና ከሰማይ በላይ ነው።”—መዝ. 148:13

አራቱ ሕያዋን ፍጥረታትና አራቱ ፊቶቻቸው ስለ ይሖዋ ኃያልነት፣ ግርማና ባሕርያት ምን ያሳያሉ? (አንቀጽ 5, 13⁠ን ተመልከት)

6. ሕዝቅኤል አራቱ ፊቶች ሌላም የሚያመለክቱት ነገር እንዳለ እንዲያስተውል የረዳው ምን ሊሆን ይችላል?

6 የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ፣ ሕዝቅኤል ስላየው ነገር ሲያወጣና ሲያወርድ ከእሱ ዘመን በፊት የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች እንስሳትን ለንጽጽር ይጠቀሙ እንደነበር ትዝ ብሎት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያዕቆብ ልጁን ይሁዳን ከአንበሳ፣ ቢንያምን ደግሞ ከተኩላ ጋር በማነጻጸር ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 49:9, 27) ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የአንበሳ ወይም የተኩላ ዓይነት ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ስለዚህ ሕዝቅኤል እነዚህን በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ዘገባዎች አስታውሶ ከነበረ፣ በአራት የተለያዩ ፍጥረታት የተወከሉት የኪሩቦቹ ፊቶች እነዚህ ፍጥረታት የሚያንጸባርቋቸውን ጎላ ያሉ ባሕርያት ያመለክታሉ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

ይሖዋና በሰማይ ያለው ቤተሰቡ የሚያንጸባርቋቸው ባሕርያት

7, 8. የኪሩቦቹ አራት ፊቶች ብዙውን ጊዜ ከየትኞቹ ባሕርያት ጋር ተዛምደው ይገለጻሉ?

7 ከሕዝቅኤል ዘመን በፊት ይኖሩ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንበሳን፣ ንስርንና በሬን ከየትኞቹ ባሕርያት ጋር አዛምደው ገልጸዋቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት፦ “ልቡ እንደ አንበሳ የሆነ ደፋር ሰው።” (2 ሳሙ. 17:10፤ ምሳሌ 28:1) “ንስር ወደ ላይ [ይመጥቃል]”፤ “ዓይኖቹም እጅግ ሩቅ ወደሆነ ቦታ ይመለከታሉ።” (ኢዮብ 39:27, 29) “የበሬ ጉልበት . . . ብዙ ምርት ያስገኛል።” (ምሳሌ 14:4) ከዚህ በፊት በወጡ ጽሑፎቻችን ላይ እነዚህን ጥቅሶች መሠረት በማድረግ በተደጋጋሚ እንደተብራራው የአንበሳው ፊት ድፍረት የተሞላበትን ፍትሕ፣ የንስሩ ፊት አርቆ ተመልካች የሆነውን ጥበብ፣ የበሬው ፊት ደግሞ ማንም ሊቋቋም የማይችለውን ኃይል ያመለክታል።

8 ‘የሰው ፊትስ’ ምን ያመለክታል? (ሕዝ. 10:14) በአምላክ አምሳል ከተፈጠረው ከሰው በስተቀር የትኛውም እንስሳ ሊያሳይ የማይችለውን ባሕርይ የሚያመለክት መሆን አለበት። (ዘፍ. 1:27) “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚሉት የአምላክ ትእዛዛት፣ በምድር ላይ ከሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ የሰው ልጅ ብቻ ሊያንጸባርቀው ስለሚችለው ስለዚህ ባሕርይ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። (ዘዳ. 6:5፤ ዘሌ. 19:18) ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት እነዚህን ትእዛዛት ስንፈጽም የይሖዋ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርን እናንጸባርቃለን። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደጻፈው “እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።” (1 ዮሐ. 4:8, 19) ከዚህ በመነሳት “የሰው ፊት” ፍቅርን እንደሚያመለክት መረዳት እንችላለን።

9. ከኪሩቦቹ ፊቶች ጋር ተያይዘው የሚጠቀሱት ባሕርያት የማን ባሕርያት ናቸው?

9 እነዚህ ባሕርያት የማን ባሕርያት ናቸው? አራቱ ፊቶች የኪሩቦቹ ፊቶች በመሆናቸው ባሕርያቱም የኪሩቦቹ እንደሆኑ ግልጽ ነው፤ በራእዩ ላይ ኪሩቦቹ የይሖዋን ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሙሉ ስለሚወክሉ እነዚህ ባሕርያት የይሖዋ ሰማያዊ ቤተሰብ አባላት የሚያንጸባርቋቸው ባሕርያት ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል። (ራእይ 5:11) ከዚህም ሌላ የኪሩቦቹ ሕይወት ምንጭ ይሖዋ በመሆኑ የባሕርያቸውም ምንጭ እሱ ነው። (መዝ. 36:9) ስለዚህ የኪሩቦቹ ፊቶች ይሖዋ ራሱ የሚያንጸባርቃቸውን ባሕርያት ያመለክታሉ። (ኢዮብ 37:23፤ መዝ. 99:4፤ ምሳሌ 2:6፤ ሚክ. 7:18) ይሖዋ እነዚህን ጎላ ያሉ ባሕርያት የሚያሳይባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

10, 11. ከይሖዋ አራት ዋና ዋና ባሕርያት ጥቅም እያገኘን ያለነው እንዴት ነው?

10 ፍትሕ። ይሖዋ ‘ፍትሕን የሚወድ’ አምላክ ስለሆነ ‘ለማንም አያዳላም’። (መዝ. 37:28፤ ዘዳ. 10:17) በመሆኑም አስተዳደጋችንም ሆነ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለን ቦታ ምንም ይሁን ምን የይሖዋ አገልጋዮች የመሆንና እሱን በቀጣይነት የማገልገል እንዲሁም ዘላለማዊ በረከት የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቶልናል። ጥበብ። ይሖዋ “ጥበበኛ ልብ” ያለው አምላክ እንደመሆኑ መጠን ‘በጥበብ’ የተሞላ መጽሐፍ ሰጥቶናል። (ኢዮብ 9:4፤ ምሳሌ 2:7) ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣትና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት እንችላለን። ኃይል። ይሖዋ ‘ኃይሉ ታላቅ’ የሆነ አምላክ ስለሆነ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል” ይሰጠናል። ይህ ኃይል፣ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ከባድ ፈተና ለመወጣት ያስችለናል።—ናሆም 1:3፤ 2 ቆሮ. 4:7፤ መዝ. 46:1

11 ፍቅር። ይሖዋ “ታማኝ ፍቅሩ የበዛ” አምላክ ስለሆነ ታማኝ አምላኪዎቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም። (መዝ. 103:8፤ 2 ሳሙ. 22:26) በመሆኑም በጤና መታወክ ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት በይሖዋ አገልግሎት የቀድሞውን ያህል ማከናወን ባለመቻላችን ብናዝንም እንኳ ይሖዋ በቀደሙት ጊዜያት በፍቅር ተነሳስተን ያከናወንናቸውን ሥራዎች እንደሚያስታውስ ማወቃችን ያጽናናናል። (ዕብ. 6:10) አሁንም እንኳ ይሖዋ ፍትሑን፣ ጥበቡን፣ ኃይሉንና ፍቅሩን ከገለጸባቸው መንገዶች ብዙ ጥቅም እያገኘን እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ወደፊትም ቢሆን ከእነዚህ አራት ዋና ዋና የአምላክ ባሕርያት ብዙ ጥቅም እናገኛለን።

12. የይሖዋን ባሕርያት የመረዳት አቅማችንን በተመለከተ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

12 እርግጥ ነው፣ እኛ የሰው ልጆች ስለ ይሖዋ ባሕርያት መረዳት የምንችለው ነገር ‘የመንገዱን ዳር ዳር ብቻ’ የማወቅ ያህል እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (ኢዮብ 26:14) ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ “ከመረዳት ችሎታችን በላይ ነው”፤ ምክንያቱም “ታላቅነቱ አይመረመርም።” (ኢዮብ 37:23፤ መዝ. 145:3) ስለሆነም የይሖዋን ባሕርያት በቁጥር መግለጽም ሆነ ነጣጥሎ ማየት እንደማይቻል እንገነዘባለን። (ሮም 11:33, 34ን አንብብ።) የሕዝቅኤል ራእይ ራሱ ይህን እውነታ ያስገነዝበናል። (መዝ. 139:17, 18) ከራእዩ ውስጥ ይህን አስፈላጊ የሆነ እውነታ የሚያጎላው የትኛው ክፍል ነው?

‘አራት ፊቶች፣ አራት ክንፎችና አራት ጎኖች’

13, 14. የኪሩቦቹ አራት ፊቶች ምን ያመለክታሉ? እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደረገን ምንድን ነው?

13 ሕዝቅኤል በራእዩ ላይ እያንዳንዱ ኪሩብ አንድ ብቻ ሳይሆን አራት ፊቶች እንዳሉት ተመልክቷል። ይህ ምን ያመለክታል? በአምላክ ቃል ውስጥ አራት ቁጥር ሁሉን አቀፍ መሆንን ወይም ሙላትን ለማመልከት እንደተሠራበት አስታውስ። (ኢሳ. 11:12፤ ማቴ. 24:31፤ ራእይ 7:1) በዚህ ራእይ ውስጥ ብቻ ሕዝቅኤል አራት ቁጥርን ከአሥር ጊዜ በላይ መጥቀሱ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሕዝ. 1:5-18) ታዲያ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? አራቱ ኪሩቦች ታማኝ የሆኑትን መንፈሳዊ ፍጥረታት በሙሉ እንደሚያመለክቱ ሁሉ የኪሩቦቹ አራት ፊቶች አንድ ላይ ሆነው ሲታዩ ይሖዋ ያሉትን ባሕርያት በሙሉ ይወክላሉ ወይም ያመለክታሉ። *

14 የኪሩቦቹ አራት ፊቶች አራቱን ባሕርያት ብቻ የሚያመለክቱ አይደሉም የምንልበትን ምክንያት ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ሁኔታውን በዚህ ራእይ ላይ ከታዩት አራት መንኮራኩሮች ጋር እናነጻጽር። እያንዳንዱ መንኮራኩር በተናጠል ሲታይ በጣም ግዙፍና አስደናቂ ነው፤ መንኮራኩሮቹ በአንድነት ተቀናጅተው ሲታዩ ግን አራት አስደናቂ መንኮራኩሮች ከመሆን ባለፈ የሠረገላው ወሳኝ ክፍል ይሆናሉ። በተመሳሳይም አራቱ ፊቶች በአንድነት ሲታዩ የሚያመለክቱት አራት የተለያዩ አስደናቂ ባሕርያትን ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ማንነት መገለጫ የሆኑትን ባሕርያቱን በሙሉ ነው።

ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ ቅርብ ነው

15. ሕዝቅኤል፣ ባየው የመጀመሪያ ራእይ አማካኝነት ምን የሚያጽናና እውነት ተምሯል?

15 ሕዝቅኤል፣ ባየው የመጀመሪያ ራእይ አማካኝነት ከይሖዋ ጋር ስላለው ዝምድና አንድ ወሳኝና የሚያጽናና እውነት ተምሯል። ይህ እውነት ምንድን ነው? በሕዝቅኤል መጽሐፍ የመክፈቻ ቃላት ላይ ይህ እውነት ተገልጿል። ሕዝቅኤል “በከለዳውያን ምድር” እንደነበረ ከገለጸ በኋላ “በዚያም የይሖዋ ኃይል በእሱ ላይ [እንደወረደ]” ተናግሯል። (ሕዝ. 1:3) ሕዝቅኤል ራእዩን ያየው በኢየሩሳሌም ሳይሆን እዚያው ባቢሎን እያለ መሆኑን እንደገለጸ ልብ በል። * ታዲያ ይህ ለሕዝቅኤል ምን አስገንዝቦታል? ሕዝቅኤል ከኢየሩሳሌምና ከቤተ መቅደሱ ርቆ የሚኖር ምስኪን ግዞተኛ ቢሆንም ከይሖዋና ከአምልኮው ግን አልተነጠለም። ይሖዋ በባቢሎን ለሕዝቅኤል መገለጡ ሕዝቅኤል የሚያቀርበው ንጹሕ አምልኮ በሚኖርበት ቦታ ወይም በኑሮ ሁኔታው ላይ የተመካ እንዳልሆነ ያሳያል። ዋናው ነገር የሕዝቅኤል የልብ ሁኔታና ይሖዋን ለማገልገል ያለው ፍላጎት ነው።

16. (ሀ) የሕዝቅኤል ራእይ ምን ዋስትና ይሰጠናል? (ለ) ይሖዋን በሙሉ ልብህ እንድታገለግል የሚገፋፋህ ምንድን ነው?

16 ሕዝቅኤል የተማረው እውነት ዛሬ ለምንኖረው ለእኛ ትልቅ ማጽናኛ ይሆነናል የምንለው ለምንድን ነው? የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አሊያም የቱንም ያህል በጭንቀት ብንዋጥ፣ በሙሉ ልባችን ይሖዋን እስካገለገልን ድረስ እሱ ከእኛ እንደማይርቅ ዋስትና ይሰጠናል። (መዝ. 25:14፤ ሥራ 17:27) ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋዩ ያለው ታማኝ ፍቅር እጅግ ብዙ ስለሆነ ቶሎ ተስፋ አይቆርጥብንም። (ዘፀ. 34:6) የትኛውም ነገር ቢሆን ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር ሊለየን አይችልም። (መዝ. 100:5፤ ሮም 8:35-39) ከዚህም ሌላ የይሖዋን ቅድስናና ተወዳዳሪ የሌለውን ኃይሉን ጎላ አድርጎ የሚገልጸው ይህ ራእይ፣ ይሖዋ አምልኮ ልናቀርብለት የሚገባ አምላክ እንደሆነ እንድናስታውስ ያደርገናል። (ራእይ 4:9-11) በእርግጥም ይሖዋ ስለ ራሱና ስለ ባሕርያቱ የሚገልጹ አስፈላጊ እውነቶችን እንድናስተውል ለመርዳት ሲል እንደዚህ ያሉትን ራእዮች በመጠቀሙ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ማራኪ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ጥልቅ ግንዛቤ ማግኘታችን ወደ እሱ እንድንቀርብ እንዲሁም በሙሉ ልባችንና በሙሉ ኃይላችን እንድናወድሰውና እንድናገለግለው ይገፋፋናል።—ሉቃስ 10:27

የትኛውም ነገር ከይሖዋ ታማኝ ፍቅር ሊያርቀን አይችልም (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

17. በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?

17 የሚያሳዝነው ግን በሕዝቅኤል ዘመን ንጹሕ አምልኮ ተበክሎ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋስ ምን ተሰማው? እነዚህ የጥንት ክንውኖች በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ እንመለከታለን።

^ አን.5 ሕዝቅኤል ስለ እነዚህ ፍጥረታት የሰጠው መግለጫ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ያስታውሰናል፤ ይህ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው እንረዳለን። አንደኛው የዚህ ስም ገጽታ፣ ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ይጠቁማል።—በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ መረጃ ሀ4 ተመልከት።

^ አን.13 ባለፉት ዓመታት 50 ስለሚያህሉ የተለያዩ የይሖዋ ባሕርያት የሚገልጽ ማብራሪያ በጽሑፎቻችን ላይ ወጥቷል።—የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች በተባለው ጽሑፍ ላይ “ይሖዋ አምላክ” በሚለው ርዕስ ሥር ያለውን “የይሖዋ ባሕርያት” የሚለውን ንዑስ ርዕስ ተመልከት።

^ አን.15 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ እንደተናገሩት “በዚያም” የሚለው ቃል ‘ሁኔታው ሕዝቅኤልን ምን ያህል እንዳስደነቀው በግልጽ ያሳያል። አምላክ በዚያ በባቢሎንም አለ! ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው!’