በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 5

“የሚሠሯቸውን ክፉና አስጸያፊ ነገሮች ተመልከት”

“የሚሠሯቸውን ክፉና አስጸያፊ ነገሮች ተመልከት”

ሕዝቅኤል 8:9

ፍሬ ሐሳብ፦ የከሃዲዋ ይሁዳ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት

1-3. ይሖዋ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ሕዝቅኤልን ሊያሳየው የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ለምንስ? (የክፍል 2⁠ን መግቢያና ሥዕሉን ተመልከት።)

ነቢዩ ሕዝቅኤል የካህን ልጅ እንደመሆኑ መጠን ስለ ሙሴ ሕግ ጥሩ እውቀት ነበረው። በመሆኑም በኢየሩሳሌም ስለነበረው ቤተ መቅደስም ሆነ በዚያ መከናወን ስለሚገባው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ በሚገባ ያውቃል። (ሕዝ. 1:3፤ ሚል. 2:7) አሁን ግን በ612 ዓ.ዓ. በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ እየተከናወነ ያለው ነገር ሕዝቅኤልን ጨምሮ ማንኛውንም ታማኝ አይሁዳዊ የሚያስደነግጥ ነው።

2 ይሖዋ፣ ሕዝቅኤል በቤተ መቅደሱ የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ እንዲመለከትና ያየውንም ነገር ቤቱ ተሰብስበው ለነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች ማለትም ‘ለይሁዳ ሽማግሌዎች’ እንዲናገር ፈልጎ ነበር። (ሕዝቅኤል 8:1-4ን አንብብ፤ ሕዝ. 11:24, 25፤ 20:1-3) ይሖዋ ሕዝቅኤልን በባቢሎን፣ በኬባር ወንዝ አጠገብ በቴልአቢብ ከነበረው ቤቱ በማንሳት በስተ ምዕራብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት (በራእይ) ወሰደው። ይሖዋ ነቢዩን በሰሜን ትይዩ ወደሚገኘው ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ግቢ በር አመጣው። ከዚህ ቦታ አንስቶ ይሖዋ ቤተ መቅደሱን በራእይ ያስጎበኘው ጀመር።

3 አሁን ሕዝቅኤል ብሔሩ አሳዛኝ ለሆነ መንፈሳዊ ውድቀት እንደተዳረገ የሚያሳዩ አራት አስደንጋጭ ትእይንቶችን ሊያይ ነው። የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ምን ሁኔታ ገጥሞት ነበር? በዛሬው ጊዜ የምንገኘው እኛስ ከዚህ ራእይ ምን ትምህርት እናገኛለን? እስቲ ከሕዝቅኤል ጋር አብረን ቤተ መቅደሱን እንጎብኝ። በመጀመሪያ ግን ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ምን እንደሚጠብቅና ይህም ተገቢ የሆነው ለምን እንደሆነ መመርመር ያስፈልገናል።

“እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ”

4. ይሖዋ ከአምላኪዎቹ የሚፈልገው ምንድን ነው?

4 ይሖዋ ሕዝቅኤል ከኖረበት ዘመን ዘጠኝ መቶ ዓመታት ያህል ቀደም ብሎ ከአምላኪዎቹ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ ተናግሮ ነበር። ከአሥሩ ትእዛዛት በሁለተኛው ላይ ለእስራኤላውያን * “እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ” ብሏቸው ነበር። (ዘፀ. 20:5) “እኔ ብቻ እንድመለክ” የሚለው አገላለጽ ይሖዋ ማንኛውም ሌላ አምላክ እንዲመለክ እንደማይፈቅድ ያሳያል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው አምልኮ የሚቀርብለት አካል ይሖዋ መሆን አለበት፤ ይህም ንጹሕ አምልኮ ሊያሟላቸው ከሚገቡ ብቃቶች የመጀመሪያው ነው። ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አንደኛውን ቦታ ለእሱ መስጠት አለባቸው። (ዘፀ. 20:3) በሌላ አባባል ይሖዋ አምላኪዎቹ እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰተኛው ጋር ባለመቀላቀል በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆነው እንዲኖሩ ይጠብቅባቸዋል። እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ወደውና ፈቅደው የሕጉን ቃል ኪዳን ተቀብለዋል። ይህን ማድረጋቸው ይሖዋን ብቻ ለማምለክ እንደተስማሙ ያሳያል። (ዘፀ. 24:3-8) ይሖዋ ለገባቸው ቃል ኪዳኖች ታማኝ ነው፤ ከቃል ኪዳን ሕዝቦቹም ተመሳሳይ ታማኝነት ይጠብቅ ነበር።—ዘዳ. 7:9, 10፤ 2 ሳሙ. 22:26

5, 6. ይሖዋ እስራኤላውያን እሱን ብቻ እንዲያመልኩ መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ እስራኤላውያን እሱን ብቻ እንዲያመልኩ መጠበቁ ምክንያታዊ ነበር? እንዴታ! ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክና የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ከመሆኑም ሌላ የሕይወትም ሆነ ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ነው። (መዝ. 36:9፤ ሥራ 17:28) በተጨማሪም ይሖዋ ለእስራኤላውያን አዳኛቸው ነበር። አሥሩን ትእዛዛት በሰጣቸው ጊዜ “ከግብፅ ምድር፣ ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ” ብሏቸው ነበር። (ዘፀ. 20:2) ይሖዋ በእስራኤላውያን ልብ ውስጥ ማንም የማይጋራው ቦታ ሊያገኝ ይገባ ነበር።

6 ይሖዋ አይለወጥም። (ሚል. 3:6) ጥንትም ሆነ ዛሬ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው። በመሆኑም አሁን ለሕዝቅኤል የሚያሳየውን አራት አስደንጋጭ ትእይንቶች ሲያይ ምን ያህል አዝኖ እንደሚሆን መገመት ትችላለህ።

የመጀመሪያው ትእይንት፦ የቅናት ጣዖት ምልክት

7. (ሀ) ከሃዲ የሆኑ አይሁዳውያን በቤተ መቅደሱ ሰሜናዊ በር ላይ ምን ያደርጉ ነበር? ይሖዋስ ይህን ሲያይ ምን ተሰማው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ይሖዋ ቅናት አደረበት ሲባል ምን ማለት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

7 ሕዝቅኤል 8:5, 6ን አንብብ። ሕዝቅኤል በድንጋጤ ክው ብሎ መሆን አለበት! በቤተ መቅደሱ ሰሜናዊ በር ላይ ከሃዲ የሆኑ አይሁዳውያን ለአንድ ጣዖት ምልክት ወይም ምስል አቁመው እየሰገዱለት ነው። ምናልባትም እነዚህ ሰዎች እያመለኩ የነበሩት ከነዓናውያን የባአል ሚስት እንደሆነች አድርገው ለሚያስቧት ለአሼራህ የቆመውን አምድ ሊሆን ይችላል። ምንም ይሁን ምን፣ ጣዖት አምላኪ የሆኑት እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል። ለይሖዋ ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን አምልኮ ለምስል በመስጠት አምላክን ያስቀኑት ሲሆን በዚህም የጽድቅ ቁጣው እንዲቀሰቀስ አድርገዋል። * (ዘዳ. 32:16፤ ሕዝ. 5:13) እስቲ አስበው፦ ቤተ መቅደሱ 400 ለሚያህሉ ዓመታት ይሖዋ የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ ተደርጎ ሲቆጠር ኖሯል። (1 ነገ. 8:10-13) አሁን ግን እነዚህ ጣዖት አምላኪዎች የጣዖት አምልኮን ወደ ቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ በማስገባት ይሖዋ ‘ከመቅደሱ እንዲርቅ አድርገዋል።’

8. ሕዝቅኤል ስለ ቅናት ምልክት የተመለከተው ራእይ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

8 ሕዝቅኤል ስለ ቅናት ምልክት ያየው ራእይ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው? ከሃዲዋ ይሁዳ ሕዝበ ክርስትናን እንደምታስታውሰን ጥርጥር የለውም። በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የጣዖት አምልኮ በእጅጉ በመስፋፋቱ የአብያተ ክርስቲያናቱ አባላት ለአምላክ እናቀርባለን የሚሉት ማንኛውም አምልኮ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ይሖዋ የማይለወጥ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ልክ እንደ ከሃዲዋ ይሁዳ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም የጽድቅ ቁጣውን እንዳነሳሳችው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ያዕ. 1:17) ይሖዋ እንዲህ ካለው እውነተኛ ያልሆነ ክርስትና እንደሚርቅ ጥያቄ የለውም!

9, 10. በቤተ መቅደሱ ውስጥ ስለነበሩት ጣዖት አምላኪዎች ከሚገልጸው ዘገባ ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት እናገኛለን?

9 በቤተ መቅደሱ ስለነበሩት ጣዖት አምላኪዎች ከሚገልጸው ዘገባ ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? ይሖዋን ብቻ ማምለክ ከፈለግን ‘ከጣዖት አምልኮ መሸሽ’ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 10:14) ‘እኔ መቼም ይሖዋን ለማምለክ በምስሎች ወይም በሥዕሎች ልጠቀም አልችልም’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ የጣዖት አምልኮ የተለያየ መልክ ሊኖረው ይችላል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ስውር ናቸው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ‘ከአምላክ የበለጠ ዋጋ ወይም ግምት የምንሰጠው ማንኛውም ነገር እንደ ጣዖት ሊቆጠር ይችላል።’ ስለሆነም ቁሳዊ ንብረቶችን፣ ገንዘብን፣ የፆታ ስሜትንና መዝናኛን ጨምሮ የትኛውም ነገር በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ በመያዝ ለይሖዋ ብቻ ሊቀርብ የሚገባውን አምልኮ የሚሻማብን ከሆነ እንደ ጣዖት ሊታይ ይችላል። (ማቴ. 6:19-21, 24፤ ኤፌ. 5:5፤ ቆላ. 3:5) ሙሉ ልባችንን ልንሰጠውና አምልኮ ልናቀርብለት የሚገባው አምላክ ይሖዋ ብቻ ስለሆነ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ መራቅ ይኖርብናል።—1 ዮሐ. 5:21

10 ይሖዋ ለሕዝቅኤል ያሳየው የመጀመሪያ ትእይንት “አስከፊና አስጸያፊ ነገሮች” የሞሉበት ነበር። ሆኖም ይሖዋ ገና “ይበልጥ አስከፊ የሆኑ አስጸያፊ ነገሮችን” እንደሚመለከት ነገረው። በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የቅናት ጣዖት ምልክትን ከማምለክ የከፋ ምን ነገር ሊኖር ይችላል?

ሁለተኛው ትእይንት፦ ለሐሰት አማልክት ዕጣን የሚያጥኑ 70 ሽማግሌዎች

11. ሕዝቅኤል በቤተ መቅደሱ መሠዊያ አቅራቢያ ወደነበረው ውስጠኛ ግቢ ሲገባ ምን የሚዘገንን ነገር ተመለከተ?

11 ሕዝቅኤል 8:7-12ን አንብብ። ሕዝቅኤል ግድግዳውን ነድሎ መሠዊያው ወደሚገኝበት ውስጠኛ ግቢ ሲገባ “መሬት ለመሬት የሚሳቡ ፍጥረታትንና የሚያስጠሉ አራዊትን ሁሉ እንዲሁም አስጸያፊ የሆኑ የእስራኤል ቤት ጣዖቶችን ሁሉ ምስል” ተመለከተ። * በግድግዳ ላይ የተቀረጹት እነዚህ ምስሎች የሐሰት አማልክትን የሚያመለክቱ ነበሩ። ቀጥሎ ደግሞ ይበልጥ የሚዘገንን ነገር አየ፤ “70 የሚሆኑ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች” “በጨለማ” ውስጥ ቆመው ለሐሰት አማልክት ዕጣን ያጥናሉ። በሙሴ ሕግ ውስጥ ጣፋጭ መዓዛ ያለው ዕጣን ማጨስ ታማኝ አምላኪዎች የሚያቀርቡትን ተቀባይነት ያለው ጸሎት ያመለክት ነበር። (መዝ. 141:2) እነዚህ 70 ሽማግሌዎች ለሐሰት አማልክት ያቀርቡ የነበረው ዕጣን ግን በይሖዋ ፊት የረከሰና የገማ ነው። ይሖዋ የሚያቀርቡትን ጸሎት እንደ መጥፎ ጠረን ተጸይፎታል። (ምሳሌ 15:8) እነዚህ ሽማግሌዎች “ይሖዋ አያየንም” በማለት ራሳቸውን ያታልሉ ነበር። ይሖዋ ግን አይቷቸዋል፤ እንዲያውም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ምን እየሠሩ እንዳሉ ከራሱ አልፎ ለሕዝቅኤልም አሳይቶታል።

ይሖዋ “በጨለማ” የሚፈጸመውን አስነዋሪ ነገር በሙሉ ያያል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

12. “በጨለማ” ውስጥ ሳይቀር ታማኝነታችንን መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ በተለይ እነማን ጥሩ ምሳሌ መሆን ይኖርባቸዋል?

12 ሕዝቅኤል ለሐሰት አማልክት ያጥኑ ስለነበሩት 70 እስራኤላውያን ሽማግሌዎች ከጻፈው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ጸሎታችን በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እንዲያገኝና የምናቀርበው አምልኮ በእሱ ዓይን ንጹሕ ሆኖ እንዲገኝ ከፈለግን “በጨለማ” ውስጥም ጭምር ታማኝ ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል። (ምሳሌ 15:29) የይሖዋ ዓይኖች የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንደሚያዩ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ እውን ሆኖ የሚታየን ከሆነ ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜም እንኳ፣ እሱን እንደሚያስከፋው የምናውቀውን ነገር አናደርግም። (ዕብ. 4:13) በተለይ የጉባኤ ሽማግሌዎች በክርስቲያናዊ አኗኗር ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2, 3) የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች፣ በፊታቸው ቆሞ በስብሰባ ላይ በአምልኮ የሚመራቸው ሽማግሌ “በጨለማ” ውስጥም ማለትም ከሌሎች እይታ ውጭ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮ ይኖራል ብለው መጠበቃቸው ተገቢ ነው።—መዝ. 101:2, 3

ሦስተኛ ትእይንት፦ ‘ሴቶች ታሙዝ ለተባለው አምላክ ያለቅሳሉ’

13. ሕዝቅኤል በሰሜን በኩል ባለው የቤተ መቅደሱ በር ላይ ከሃዲ የሆኑ ሴቶች ምን ሲያደርጉ ተመለከተ?

13 ሕዝቅኤል 8:13, 14ን አንብብ። ሕዝቅኤል አስጸያፊ ድርጊት ሲፈጸም የሚያሳዩትን ሁለት ትእይንቶች ከተመለከተ በኋላ ይሖዋ “እነሱ የሚሠሯቸውን ይበልጥ አስከፊ የሆኑ አስጸያፊ ነገሮች ታያለህ” አለው። ታዲያ ነቢዩ ቀጥሎ ምን ይመለከት ይሆን? ‘በሰሜን በኩል ባለው የይሖዋ ቤት በር’ “ሴቶች ተቀምጠው ታሙዝ ለተባለው አምላክ ሲያለቅሱ” አየ። የሜሶጶጣሚያ አምላክ የሆነው ታሙዝ በሱሜሪያ ጽሑፍ ላይ ዱሙዚ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን የመራባት እንስት አምላክ የሆነችው የኢሽታር ፍቅረኛ እንደሆነ ይታሰባል። * እስራኤላውያኑ ሴቶች የሚያለቅሱት ከታሙዝ ሞት ጋር ተያያዥነት ያለው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ ሴቶች በይሖዋ መቅደስ ውስጥ ለታሙዝ በማልቀስ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል በሆነው ቦታ ላይ አረማዊ አምልኮ እያካሄዱ ነበር። ይሁን እንጂ የሐሰት አምልኮ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለተከናወነ ብቻ የተቀደሰ ሊሆን አይችልም። እነዚህ ከሃዲ ሴቶች የሚያከናውኑት ነገር በይሖዋ ዓይን “አስጸያፊ” ነበር።

14. ይሖዋ ከሃዲዎቹ ሴቶች ለፈጸሙት ድርጊት የነበረውን አመለካከት ማወቃችን ምን ያስተምረናል?

14 ይሖዋ እነዚህ ሴቶች ለፈጸሙት ድርጊት የነበረውን አመለካከት ማወቃችን ምን ያስተምረናል? አምልኳችን ንጹሕ እንዲሆን ከፈለግን ንጹሑን አምልኮ ርኩስ ከሆኑ አረማዊ ልማዶች ጋር ፈጽሞ መቀላቀል አይኖርብንም። በመሆኑም አረማዊ ምንጭ ካላቸው ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ሙሉ በሙሉ መራቅ ይገባናል። አንድ ክብረ በዓል የመነጨው ከየት ነው የሚለው ጉዳይ ለውጥ ያመጣል? አዎ! ለምሳሌ እንደ ገና እና በዓለ ትንሣኤ ካሉት በዓላት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ልማዶች ምንም ጉዳት የሌላቸው ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁንና ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ከሚከናወኑ ሃይማኖታዊ በዓላት ጋር የተቀላቀሉትን አረማዊ ልማዶች ከጅምሩ አንስቶ እንደተመለከተ ልንዘነጋ አይገባም። ረጅም ዘመን ማለፉ ወይም እነዚህን ልማዶች ከንጹሕ አምልኮ ጋር ለመቀላቀል ጥረት መደረጉ ይሖዋ ለአረማዊ ልማዶች ያለውን አመለካከት አያለዝበውም።—2 ቆሮ. 6:17፤ ራእይ 18:2, 4

አራተኛ ትእይንት፦ 25 ወንዶች “ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር”

15, 16. በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ግቢ 25 ወንዶች ምን ያደርጉ ነበር? ድርጊታቸው ይሖዋን እጅግ ያሳዘነውስ ለምን ነበር?

15 ሕዝቅኤል 8:15-18ን አንብብ። ይሖዋ አራተኛውንና የመጨረሻውን ትእይንት ያስተዋወቀው “ከእነዚህ የባሰ አስከፊ የሆኑ አስጸያፊ ነገሮች ታያለህ” የሚሉትን ቃላት በድጋሚ በመናገር ነው። ነቢዩ ‘እስካሁን ካየኋቸው ነገሮች ይበልጥ አስከፊ የሆነ ምን ነገር ሊኖር ይችላል?’ ብሎ ሳያስብ አይቀርም። አሁን ሕዝቅኤል ያለው በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ግቢ ነው። እዚያም በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ “በምሥራቅ አቅጣጫ ለፀሐይ ይሰግዱ” የነበሩ 25 ወንዶችን ተመለከተ። እነዚህ ወንዶች የፈጸሙት ድርጊት ይሖዋን ከምንም ነገር በላይ የሚያሳዝን ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

16 እስቲ ትእይንቱን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር፦ የቤተ መቅደሱ መግቢያ የሚገኘው በምሥራቅ ትይዩ ነው። ስለዚህ ሰዎች ለአምልኮ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚገቡበት ጊዜ ፊታቸው በምዕራብ ትይዩ ስለሚሆን ጀርባቸውን በስተ ምሥራቅ ላለችው ፀሐይ ይሰጣሉ። በራእዩ ላይ የታዩት 25 ወንዶች ግን “ጀርባቸውን ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ሰጥተው” ፀሐይን ለማምለክ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው ነበር። ቤተ መቅደሱ ‘የይሖዋ ቤት’ እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ ጀርባቸውን ሰጥተዋል ሊባል ይችላል። (1 ነገ. 8:10-13) እነዚያ 25 ወንዶች ከሃዲዎች ናቸው። ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ጀርባቸውን የሰጡ ከመሆኑም ሌላ በዘዳግም 4:15-19 ላይ የሚገኘውን ትእዛዝ በቀጥታ ጥሰዋል። ይህን ማድረጋቸው እሱ ብቻ ሊመለክ የሚገባውን አምላክ ምንኛ የሚያሳዝን ነው!

ይሖዋ ለእሱ ብቻ አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባ አምላክ ነው

17, 18. (ሀ) በቤተ መቅደሱ ውስጥ ፀሐይን ያመልኩ ስለነበሩት ወንዶች ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? (ለ) ከሃዲዎቹ እስራኤላውያን ከማን ጋር የነበራቸውን ዝምድና አበላሽተዋል? እንዴትስ?

17 ፀሐይን ያመልኩ ስለነበሩት ወንዶች ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? አምልኳችን ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ከፈለግን መንፈሳዊ ብርሃን ለማግኘት ጥረት ማድረግ የሚኖርብን ከይሖዋ ብቻ ነው። “ይሖዋ አምላክ ፀሐይ፣” ቃሉም ለመንገዳችን “ብርሃን” እንደሆነ አስታውስ። (መዝ. 84:11፤ 119:105) ይሖዋ በቃሉና ድርጅቱ በሚያወጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች አማካኝነት በአሁኑ ጊዜ አርኪ ሕይወት መምራት፣ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ በማሳየት ልባችንንና አእምሯችንን ያበራልናል። ለሕይወታችን መመሪያ ወይም ብርሃን ለማግኘት ወደዚህ ዓለም ዞር ካልን ግን ለይሖዋ ጀርባችንን እንደሰጠን ይቆጠራል። እንዲህ ያለው አካሄድ የይሖዋን ልብ በእጅጉ ያሳዝነዋል። አምላካችንን ይሖዋን ማሳዘን ደግሞ አንፈልግም። በተጨማሪም የሕዝቅኤል ራእይ ለእውነት ጀርባቸውን ከሚሰጡ ሰዎች ማለትም ከከሃዲዎች እንድንርቅ ማስጠንቀቂያ ይሆነናል።—ምሳሌ 11:9

18 እስካሁን እንደተመለከትነው ሕዝቅኤል ከሃዲዋ ይሁዳ ምን ያህል በመንፈሳዊ እንደቆሸሸች የሚያሳዩ ከጣዖት አምልኮ ጋር የተያያዙ አራት አስደንጋጭ ትእይንቶችን አይቷል። እነዚህ እስራኤላውያን በመንፈሳዊ መርከሳቸው በብሔሩና በአምላክ መካከል የነበረው ዝምድና እንዲበላሽ አድርጓል። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ርኩሰትና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። በመሆኑም ከሃዲ የሆኑት እስራኤላውያን ከአምላካቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች ጋር የነበራቸውን ዝምድናም ጭምር የሚያበላሹ ብዙ ዓይነት መጥፎ ድርጊቶችን መፈጸማቸው አያስደንቅም። እስቲ አሁን ነቢዩ ሕዝቅኤል ከሃዲዋ ይሁዳ የተዘፈቀችበትን የሥነ ምግባር ውድቀት በመንፈስ ተመርቶ እንዴት እንደገለጸ እንመልከት።

ሥነ ምግባራዊ ርኩሰት—“በመካከልሽም ጸያፍ ምግባር ይፈጽማሉ”

19. ሕዝቅኤል የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝቦች የደረሰባቸውን የሥነ ምግባር ውድቀት የገለጸው እንዴት ነው?

19 ሕዝቅኤል 22:3-12ን አንብብ። የእስራኤል ብሔር ከገዢዎቹ አንስቶ እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ በሥነ ምግባር ተበላሽቶ ነበር። ‘አለቆቻቸው’ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ንጹሕ ደም ያፈስሳሉ። ሕዝቡም የመሪዎቹን ፈለግ በመከተል የአምላክን ሕግ ቸል ይላል። በቤተሰብ ውስጥ ልጆች ወላጆቻቸውን “ያቃልላሉ”፤ በቅርብ የሥጋ ዘመዶች መካከል የሚፈጸም የፆታ ብልግና የተለመደ ነገር ሆኗል። ዓመፀኞቹ እስራኤላውያን በመካከላቸው ያሉትን የባዕድ አገር ሰዎች ያጭበረብራሉ እንዲሁም አባት የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን ይበድላሉ። እስራኤላውያን ወንዶች የባልንጀሮቻቸውን ሚስቶች ያስነውራሉ። ነዋሪዎቹ ጉቦ በመብላት፣ ወለድ በመቀበልና ቀማኞች በመሆን በጣም ስግብግቦች መሆናቸውን አሳይተዋል። ይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝቦቹ እሱ ያወጣውን ሕግ ገሸሽ በማድረግና ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን ፍቅር የሚንጸባረቅበት መንፈስ ችላ በማለት እንዲህ ያለ ድርጊት ሲፈጽሙ ማየቱ ምን ዓይነት ስሜት እንዳሳደረበት መገመት አያዳግትም! እስራኤላውያን እንዲህ ላለ የሥነ ምግባር ውድቀት መዳረጋቸው ይሖዋን በጣም አሳዝኖታል። በመሆኑም በሥነ ምግባር ለወደቁት ሕዝቦቹ ‘እኔን ጨርሶ ረስታችሁኛል’ በማለት እንዲነግራቸው ሕዝቅኤልን አዝዞታል።

የሕዝበ ክርስትና ተጽዕኖ ዓለም በደም መፋሰስ የተሞላና በሥነ ምግባር ያዘቀጠ እንዲሆን አድርጓል (አንቀጽ 20⁠ን ተመልከት)

20. ሕዝቅኤል ስለ ይሁዳ የሥነ ምግባር ርኩሰት የተናገረው ሐሳብ ለዘመናችንም ትልቅ ትርጉም አለው የምንለው ለምንድን ነው?

20 ሕዝቅኤል ስለ ይሁዳ የሥነ ምግባር ርኩሰት የተናገረው ሐሳብ ለዘመናችንም ትልቅ ትርጉም አለው የምንለው ለምንድን ነው? ስለ ከሃዲዋ ይሁዳ የሥነ ምግባር ውድቀት የተሰጠው መግለጫ በዛሬው ጊዜ ያለውን በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ዓለም ያስታውሰናል። የፖለቲካ ገዢዎች ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ተራውን ሰው ይጨቁናሉ። በርካታ የሃይማኖት መሪዎች በተለይም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ጦርነቶችን ባርከዋል። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሚናገረውን ንጹሕና ግልጽ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት በርዘዋል። በዚህም የተነሳ በዙሪያችን ያለው ዓለም የሥነ ምግባር መሥፈርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዘቀጠ ሄዷል። በእርግጥም ይሖዋ ለከሃዲዋ ይሁዳ እንዳለው ሁሉ ሕዝበ ክርስትናንም “እኔን ጨርሶ ረስተሻል” ሊላት ይችላል።

21. ስለ ጥንቷ ይሁዳ የሥነ ምግባር ርኩሰት ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

21 እኛ የይሖዋ ሕዝቦች ስለ ጥንቷ ይሁዳ የሥነ ምግባር ርኩሰት ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ ከፈለግን ምግባራችን በሁሉም ረገድ ንጹሕ መሆን ይኖርበታል። እርግጥ ምግባረ ብልሹ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። (2 ጢሞ. 3:1-5) ይሁን እንጂ ይሖዋ ለማንኛውም ዓይነት የሥነ ምግባር ርኩሰት ምን አመለካከት እንዳለው እናውቃለን። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ይሖዋንና ሕጎቹን ስለምንወድ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን እናከብራለን። (መዝ. 119:97፤ 1 ዮሐ. 5:3) በሥነ ምግባር መቆሸሽ፣ ቅዱስና ንጹሕ ለሆነው አምላካችን ፍቅር እንደሚጎድለን የሚያሳይ ነው። ይሖዋ ‘እኔን ጨርሶ ረስታችሁኛል’ እንዲለን የሚያደርገው ምንም ነገር መፈጸም አንፈልግም።

22. (ሀ) ይሖዋ የጥንቷን ይሁዳ እንዴት እንዳጋለጠ መመልከትህ ምን ቁርጥ ውሳኔ ለማድረግ አነሳስቶሃል? (ለ) የሚቀጥለው ምዕራፍ ምን ያብራራል?

22 ይሖዋ የጥንቷ ይሁዳ የደረሰባትን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ውድቀት በማጋለጥ ለሕዝቅኤል ያሳየውን ራእይ መመርመራችን ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶች እንድናገኝ አስችሎናል። ለይሖዋ ብቻ ንጹሕ አምልኮ ለማቅረብ ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ይበልጥ እንደተጠናከረልን ጥርጥር የለውም። ይህን ማድረግ ከፈለግን ደግሞ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ መራቅና የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝነታቸውን ያልጠበቁትን ሕዝቦቹን ሲመለከት ምን አደረገ? ሕዝቅኤል ቤተ መቅደሱን ጎብኝቶ ሲጨርስ፣ ይሖዋ “በቁጣ እርምጃ እወስዳለሁ” በማለት በግልጽ ነግሮታል። (ሕዝ. 8:17, 18) ይሖዋ በከሃዲዋ ይሁዳ ላይ ምን እርምጃ እንደወሰደ ማወቅ እንፈልጋለን፤ ምክንያቱም በዚህ ክፉ ዓለም ላይም ተመሳሳይ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል። የሚቀጥለው ምዕራፍ ይሖዋ በይሁዳ ላይ ያስተላለፈው የቅጣት ፍርድ እንዴት እንደተፈጸመ ያብራራል።

^ አን.4 በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ “እስራኤል” የሚለው ቃል የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ለማመልከት ብዙ ጊዜ ተሠርቶበታል።—ሕዝ. 12:19, 22፤ 18:2፤ 21:2, 3

^ አን.7 “ቅናት” የሚለው ቃል የተሠራበት መንገድ ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የመሆንን ጉዳይ ምን ያህል አክብዶ እንደሚመለከተው ያሳያል። ይህ ቃል አንድ ባል ሚስቱ ለእሱ ያላትን ታማኝነት ብታጓድል ምን ያህል እንደሚቆጣ ሊያስታውሰን ይችላል። (ምሳሌ 6:34) ልክ እንደዚህ ባል ሁሉ ይሖዋም የቃል ኪዳን ሕዝቦቹ ጣዖት በማምለክ ለእሱ የነበራቸውን ታማኝነት ሲያጓድሉ መቆጣቱ የሚያስገርም አይደለም። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ቅናት . . . የሚመነጨው ከቅድስናው ነው። እሱ ብቻ ቅዱስ ስለሆነ . . . ማንም አምልኮውን እንዲቀናቀነው አይፈቅድም።”—ዘፀ. 34:14

^ አን.11 “አስጸያፊ ጣዖቶች” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ተዛማጅነት ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።

^ አን.13 አንዳንዶች ታሙዝ የናምሩድ ሌላ ስም እንደሆነ ይናገራሉ፤ ሆኖም ይህን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ የለም።