በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

“አሁን ፍጻሜሽ ደርሷል”

“አሁን ፍጻሜሽ ደርሷል”

ሕዝቅኤል 7:3

ፍሬ ሐሳብ፦ ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ ያስነገረው ትንቢታዊ ፍርድ ፍጻሜውን ያገኘበት መንገድ

1, 2. (ሀ) ሕዝቅኤል ምን ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አደረገ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) የሕዝቅኤል እንግዳ ድርጊት የትኛውን ነገር የሚተነብይ ነበር?

ነቢዩ ሕዝቅኤል እያደረገ ስላለው እንግዳ ነገር የሚገልጸው ወሬ በባቢሎን ምድር በነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች መካከል በፍጥነት ተሰራጨ። በመጀመሪያ፣ ምንም ሳይናገር ሳይጋገር ፍዝዝ ብሎ በግዞተኞቹ መካከል አንድ ሳምንት ሙሉ ቁጭ አለ፤ ከዚያም ድንገት ብድግ ብሎ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ በሩን ዘግቶ ተቀመጠ። አሁን ደግሞ፣ በሚያደርገው ነገር ግራ የተጋቡት ጎረቤቶቹ እያዩት ከቤቱ ወጣና ጡብ አንስቶ ከፊቱ አስቀመጠ፤ ከዚያም በጡቡ ላይ ሥዕል መቅረጽ ጀመረ። ቀጥሎም አንድም ቃል ሳይተነፍስ በጡቡ ዙሪያ ቅጥር መሥራት ጀመረ።—ሕዝ. 3:10, 11, 15, 24-26፤ 4:1, 2

2 ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ተመልካቾቹ ‘የዚህ ሁሉ ትርጉም ምን ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ግዞተኞቹ አይሁዳውያን የሕዝቅኤል እንግዳ ድርጊት የይሖዋ የጽድቅ ቁጣ መገለጫ የሆነን አንድ አስፈሪ ክንውን የሚተነብይ መሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚገባቸው ገና ወደፊት ነው። ይህ ክንውን ምንድን ነው? በጥንቱ የእስራኤል ብሔር ላይስ ምን ውጤት አስከተለ? ይህ ክንውን በዛሬው ጊዜ ላሉት ንጹሕ አምልኮን የሚከተሉ ሰዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?

አንድ ጡብ ውሰድ፤ ስንዴ ውሰድ፤ ስለታም ሰይፍ ውሰድ’

3, 4. (ሀ) ሕዝቅኤል ያሳየው የትኞቹን የአምላክ ፍርድ ሦስት ገጽታዎች ነው? (ለ) ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን ከበባ በድራማ ያሳየው እንዴት ነው?

3 በ613 ዓ.ዓ. ገደማ ይሖዋ ሕዝቅኤልን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጣውን የአምላክ ፍርድ ሦስት ገጽታዎች በትንቢታዊ ድራማ መልክ እንዲያሳይ አዘዘው። እነዚህ ገጽታዎች የከተማዋ መከበብ፣ የነዋሪዎቿ ለመከራ መዳረግ እንዲሁም የከተማዋና የነዋሪዎቿ መጥፋት ናቸው። * እስቲ እነዚህን ሦስት ገጽታዎች በዝርዝር እንመልከት።

4 የኢየሩሳሌም መከበብ። ይሖዋ ለሕዝቅኤል “አንድ ጡብ ወስደህ በፊትህ አስቀምጥ። በላዩም ላይ የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅረጽበት። ከተማዋን ክበብ” አለው። (ሕዝቅኤል 4:1-3ን አንብብ።) ጡቡ የኢየሩሳሌምን ከተማ የሚያመለክት ሲሆን ሕዝቅኤል ራሱ ደግሞ ይሖዋ እንደ መሣሪያ የሚጠቀምበትን የባቢሎን ሠራዊት ይወክላል። በተጨማሪም ሕዝቅኤል በጡቡ ዙሪያ ቅጥር እንዲሠራ፣ የአፈር ቁልል እንዲደለድልና የመደርመሻ መሣሪያዎችን እንዲደግን ተነግሮታል። እነዚህ ነገሮች የኢየሩሳሌም ጠላቶች ከተማዋን ከበው በሚወጉበት ጊዜ የሚጠቀሙባቸውን የውጊያ መሣሪያዎች የሚያመለክቱ ናቸው። የጠላት ወታደሮች የሚኖራቸውን እንደ ብረት ያለ ጥንካሬ ለማመልከት ሕዝቅኤል በራሱና በከተማዋ መካከል “የብረት ምጣድ” ወይም ጠፍጣፋ ብረት ማስቀመጥ ነበረበት። ከዚያ በኋላ ‘ፊቱን በከተማዋ ላይ እንዲያዞር’ ታዟል። ሕዝቅኤል የፈጸማቸው ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀትን የሚያመለክቱ ድርጊቶች ጨርሶ ያልተጠበቀ ነገር ሊከሰት መሆኑን “ለእስራኤል ቤት” ለማሳየት እንደ “ምልክት” ሆነው አገልግለዋል። ይሖዋ በአንድ የጠላት ሠራዊት ተጠቅሞ የአምላክ ቤተ መቅደስ የሚገኝባት፣ የሕዝቦቹ ዋነኛ ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም እንድትከበብ ሊያደርግ ነው!

5. ሕዝቅኤል በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ነገር እንዴት እንዳሳየ ግለጽ።

5 በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው መከራ። ይሖዋ ሕዝቅኤልን “ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ ማሽላና አጃ ወስደህ . . . ዳቦ ጋግር። . . . በየቀኑ 20 ሰቅል (230 ግራም ገደማ) እየመዘንክ ትበላለህ” ሲል አዘዘው። ከዚያም ይሖዋ “የኢየሩሳሌም የምግብ አቅርቦት እንዲቋረጥ አደርጋለሁ” አለው። (ሕዝ. 4:9-16) በዚህኛው ትእይንት ላይ ሕዝቅኤል የሚያመለክተው የባቢሎንን ሠራዊት ሳይሆን የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ነው። ሕዝቅኤል ያደረገው ነገር በመጪው ከበባ ወቅት በከተማይቱ ውስጥ ያለው የምግብ አቅርቦት እንደሚሟጠጥ የሚጠቁም ነው። በዚያ ጊዜ ዳቦ የሚጋገረው የተለያዩ እህሎችን ባልተለመደ መንገድ በመደባለቅ ይሆናል፤ ይህም ሕዝቡ ያገኘውን ለመብላት እንደሚገደድ ያሳያል። ረሃቡ ምን ያህል የከፋ ይሆናል? ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች በተመለከተ “አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፤ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ” በማለት ተናግሯል። በመጨረሻም ብዙዎቹ ‘ገዳይ በሆኑ የረሃብ ፍላጻዎች’ ስለሚመቱ ‘መንምነው’ ያልቃሉ።—ሕዝ. 4:17፤ 5:10, 16

6. (ሀ) ሕዝቅኤል በአንድ ጊዜ የትኞቹን ሁለት ገጸ ባሕርያት ወክሎ ተጫውቷል? (ለ) ይሖዋ ለሕዝቅኤል ‘ፀጉሩን መዝኖ እንዲከፋፍል’ የሰጠው ትእዛዝ ምን ያመለክታል?

6 የኢየሩሳሌምና የነዋሪዎቿ መጥፋት። በዚህኛው ትንቢታዊ ድራማ ላይ ሕዝቅኤል በአንድ ጊዜ ሁለት ገጸ ባሕርያትን ወክሎ ይጫወታል። በመጀመሪያ ሕዝቅኤል ይሖዋ የሚያደርገውን ነገር በድራማ መልክ ያሳያል። ይሖዋ ሕዝቅኤልን “እንደ ፀጉር አስተካካይ ምላጭ የምትጠቀምበት ስለታም ሰይፍ ውሰድ” አለው። (ሕዝቅኤል 5:1, 2ን አንብብ።) ሰይፉን የጨበጠው የሕዝቅኤል እጅ የይሖዋን እጅ፣ ማለትም በባቢሎን ሠራዊት አማካኝነት የሚፈጸመውን ፍርዱን ያመለክታል። ቀጥሎ ደግሞ ሕዝቅኤል አይሁዳውያን የሚደርስባቸውን ነገር በድራማ መልክ ያሳያል። ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የራስህን ፀጉርና ጢምህን ተላጭ” ብሎታል። የሕዝቅኤል ራስ መላጨት አይሁዳውያን ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸውና ሙሉ በሙሉ እንደሚጠፉ የሚያመለክት ነው። ከዚህም ሌላ “ሚዛን ወስደህ ፀጉሩን መዝነውና ከፋፍለው” መባሉ በኢየሩሳሌም ላይ የሚፈጸመው የይሖዋ ፍርድ በታሰበበትና ሥር ነቀል በሆነ መንገድ የሚፈጸም እንጂ በዘፈቀደ የሚከናወን አለመሆኑን ያመለክታል።

7. ይሖዋ ለሕዝቅኤል ፀጉሩን ሦስት ቦታ እንዲከፋፍለውና በእያንዳንዱ ክፍል ላይ የተለያየ ነገር እንዲያደርግ የነገረው ለምን ነበር?

 7 ይሖዋ ለሕዝቅኤል የተላጨውን ፀጉሩን ሦስት ቦታ እንዲከፋፍለውና በእያንዳንዱ ክፍል ላይ የተለያየ ነገር እንዲያደርግ የነገረው ለምን ነበር? (ሕዝቅኤል 5:7-12ን አንብብ።) ሕዝቅኤል ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች አንዳንዶቹ በከተማዋ ውስጥ እንደሚሞቱ ለማሳየት የፀጉሩን አንድ ክፍል “በከተማዋ ውስጥ” አቃጠለ። ሌሎቹ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከከተማዋ ውጭ እንደሚገደሉ ለማመልከት ደግሞ የፀጉሩን ሌላ ክፍል “በከተማዋ ዙሪያ” በሰይፍ መታ። ከዚያም የቀሩት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ወደተለያዩ ብሔራት እንደሚበተኑ ለማሳየት የመጨረሻውን የፀጉሩን ክፍል ለነፋስ በተነው፤ እነዚህ ሰዎች በሚበተኑበት ቦታ ሁሉ ‘ሰይፍ ያሳድዳቸዋል።’ ይህም ከጥፋቱ በሕይወት የተረፉት ሰዎች የትም ቦታ ቢሄዱ ሰላም እንደማያገኙ ያመለክታል።

8. (ሀ) የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ድራማ ምን የተስፋ ጭላንጭል ይዟል? (ለ) ስለ ‘ጥቂት ፀጉሮች’ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?

8 ይሁን እንጂ የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ድራማ የተስፋ ጭላንጭልም የያዘ ነው። ይሖዋ ሕዝቅኤልን “ከፀጉሮቹ ላይ ጥቂት ወስደህ በልብስህ እጥፋት ቋጥራቸው” ብሎታል። (ሕዝ. 5:3) ይህ ትእዛዝ በብሔራት መካከል ከሚበተኑት አይሁዳውያን መካከል ጥቂቶች በሕይወት እንደሚተርፉ ያመለክታል። ከእነዚህ ‘ጥቂት ፀጉሮች’ ውስጥ አንዳንዶቹ ለ70 ዓመት የሚቆየው የባቢሎን ግዞት ሲያበቃ ወደ ኢየሩሳሌም ከሚመለሱት ግዞተኞች መካከል ይሆናሉ። (ሕዝ. 6:8, 9፤ 11:17) ታዲያ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል? በሚገባ! የባቢሎን ግዞት ካበቃ ከዓመታት በኋላ ነቢዩ ሐጌ ከተበተኑት አይሁዳውያን መካከል አንዳንዶቹ ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ ዘግቧል። “የቀድሞውን ቤት [የሰለሞንን ቤተ መቅደስ] ያዩ ሽማግሌዎች” የተባሉት እነዚህ አይሁዳውያን ናቸው። (ዕዝራ 3:12፤ ሐጌ 2:1-3) ይሖዋ አስቀድሞ በገባው ቃል መሠረት ንጹሕ አምልኮ ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ አድርጓል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ስለተቋቋመበት መንገድ የሚገልጽ ተጨማሪ ማብራሪያ እናገኛለን።—ሕዝ. 11:17-20

ይህ ትንቢት ወደፊት ስለሚፈጸሙ ክንውኖች ምን ይነግረናል?

9, 10. የሕዝቅኤል ትንቢታዊ ድራማዎች የአምላክ ቃል ወደፊት እንደሚፈጸሙ የሚተነብያቸውን የትኞቹን ጉልህ ክንውኖች ያስታውሱናል?

9 ሕዝቅኤል በድራማ መልክ ያሳያቸው ክንውኖች የአምላክ ቃል ወደፊት እንደሚፈጸሙ የሚተነብያቸውን ጉልህ ክንውኖች ያስታውሱናል። ከእነዚህ ክንውኖች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? በጥንቷ የኢየሩሳሌም ከተማ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ወደፊትም ይሖዋ የፖለቲካ ኃይላትን ተጠቅሞ በመላው ምድር ላይ በሚገኙ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጨርሶ ያልታሰበ ነገር ያከናውናል። (ራእይ 17:16-18) በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥፋት” እንደነበረ ሁሉ በአርማጌዶን ጦርነት የሚደመደመው ‘ታላቅ መከራም’ “እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ” ክንውን ይሆናል።—ሕዝ. 5:9፤ 7:5፤ ማቴ. 24:21

10 የአምላክ ቃል ወደፊት የሃይማኖት ተቋማት በሚጠፉበት ወቅት በርካታ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች በሕይወት እንደሚተርፉ ይጠቁማል። በዚያን ጊዜ መሸሸጊያ ለማግኘት እንደሚራወጡት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ እነዚህ ሰዎችም በፍርሃት ተውጠው የሚደበቁበት ቦታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ዘካ. 13:4-6፤ ራእይ 6:15-17) የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ ከጥፋት ከተረፉ በኋላ ‘ለነፋስ የተበተኑትን’ የጥንቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ያስታውሰናል።  በአንቀጽ 7 ላይ እንደተመለከትነው የጥንቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ለጊዜው ሕይወታቸው ቢተርፍም ይሖዋ “እነሱን ለማሳደድ ሰይፍ” መዞባቸዋል። (ሕዝ. 5:2) በተመሳሳይም በሐሰት ሃይማኖት ላይ ከሚደርሰው ጥቃት የሚተርፉት ሰዎች የትም ቦታ ሄደው ለመሸሸግ ቢሞክሩ ከይሖዋ ሰይፍ ማምለጥ አይችሉም። ከሌሎቹ ፍየል መሰል ሰዎች ጋር አብረው በአርማጌዶን ይጠፋሉ።—ሕዝ. 7:4፤ ማቴ. 25:33, 41, 46፤ ራእይ 19:15, 18

ምሥራቹን መናገራችንን ስለምናቆም እንደ “ዱዳ” እንሆናለን

11, 12. (ሀ) ሕዝቅኤል ስለተናገረው ትንቢት ያለን ግንዛቤ ለአገልግሎት ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? (ለ) በስብከት ሥራችን ላይ ምን ለውጥ ሊኖር ይችላል?

11 ስለዚህ ትንቢት ያለን ግንዛቤ ለአገልግሎታችንም ሆነ ለስብከት ሥራው አጣዳፊነት ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ እንደሚያስፈልገን ያስገነዝበናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት” ለማድረግ የቀረን ጊዜ አጭር ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሕዝ. 33:14-16) “በትሩ” (ፖለቲካዊ ኃይላትን ያመለክታል) በሐሰት ሃይማኖት ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምር የመዳን መልእክት መስበካችንን እናቆማለን። (ሕዝ. 7:10) ሕዝቅኤል በአንድ ወቅት መልእክቱን መናገር አቁሞ እንደ “ዱዳ” እንደሆነ ሁሉ እኛም በዚያ ጊዜ ምሥራቹን መናገራችንን ስለምናቆም እንደ “ዱዳ” እንሆናለን። (ሕዝ. 3:26, 27፤ 33:21, 22) እርግጥ ነው፣ የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ሰዎች “ከነቢይ ራእይ” ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉ፤ ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ሕይወት አድን መመሪያ አያገኙም። (ሕዝ. 7:26) እንዲህ ያለውን መመሪያ መቀበልና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚችሉበት ጊዜ አልፎባቸዋል።

12 ይሁን እንጂ መስበካችንን ሙሉ በሙሉ እናቆማለን ማለት አይደለም። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? በታላቁ መከራ ወቅት እንደ በረዶ መቅሰፍት ያለ የፍርድ መልእክት ማወጅ ልንጀምር እንችላለን። ይህ መልእክት የክፉው ዓለም ፍጻሜ እንደደረሰ በግልጽ የሚያመለክት ይሆናል።—ራእይ 16:21

“እነሆ . . . ጥፋት እየመጣ ነው!”

13. ሕዝቅኤል መጀመሪያ በግራ ጎኑ ከዚያም በቀኝ ጎኑ እንዲተኛ የተነገረው ለምን ነበር?

13 ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም የምትጠፋው እንዴት እንደሆነ መተንበይ ብቻ ሳይሆን ከተማይቱ የምትጠፋው መቼ እንደሆነም ጭምር በድራማ መልክ አሳይቷል። ሕዝቅኤል በግራ ጎኑ 390 ቀን፣ በቀኝ ጎኑ ደግሞ 40 ቀን እንዲተኛ ይሖዋ ነግሮታል። እያንዳንዱ ቀን አንድ ዓመትን ያመለክታል። (ሕዝቅኤል 4:4-6ን አንብብ፤ ዘኁ. 14:34) ሕዝቅኤል ይህን ያደርግ የነበረው በቀን ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ መሆን አለበት። ይህ ትንቢታዊ ድራማ ኢየሩሳሌም የጠፋችበትን ትክክለኛ ዓመት ይጠቁማል። የእስራኤል ሕዝብ በደል የፈጸመባቸው 390 ዓመታት የጀመሩት የአሥራ ሁለቱ ነገድ መንግሥት ለሁለት በተከፈለበት በ997 ዓ.ዓ. ሳይሆን አይቀርም። (1 ነገ. 12:12-20) የይሁዳ መንግሥት ኃጢአት የሠራባቸው 40 ዓመታት መቆጠር የጀመሩት ደግሞ ኤርምያስ በይሁዳ መንግሥት ላይ ስለሚመጣው ጥፋት በግልጽ እንዲያስጠነቅቅ የነቢይነት ተልእኮ በተቀበለበት በ647 ዓ.ዓ. መሆን አለበት። (ኤር. 1:1, 2, 17-19፤ 19:3, 4) ሁለቱም ጊዜያት ያበቁት በ607 ዓ.ዓ. ነው፤ ይሖዋ በተነበየው መሠረት ኢየሩሳሌም የወደቀችውና የጠፋችው በዚሁ ዓመት ነበር። *

ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም የምትጠፋበትን ትክክለኛ ዓመት የጠቆመው እንዴት ነው? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

14. (ሀ) ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ከወሰነው ጊዜ ዝንፍ እንደማይል እርግጠኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር? (ለ) ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ምን ነገር ይፈጸማል?

14 ሕዝቅኤል የ390ዎቹንና የ40ዎቹን ቀናት ትንቢታዊ ድራማ ባሳየበት ጊዜ የኢየሩሳሌም ፍጻሜ የሚመጣበት ትክክለኛ ዓመት መቼ እንደሆነ አልገባው ይሆናል። ያም ቢሆን ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታት በሙሉ የይሖዋ ፍርድ የሚመጣበት ጊዜ እንደተቃረበ በተደጋጋሚ አይሁዳውያኑን ያስጠነቅቅ ነበር። “አሁን ፍጻሜሽ ደርሷል” በማለት አውጇል። (ሕዝቅኤል 7:3, 5-10ን አንብብ።) ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ከወሰነው ጊዜ ዝንፍ እንደማይል እርግጠኛ ነበር። (ኢሳ. 46:10) በተጨማሪም ነቢዩ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች በተመለከተ ትንቢት ተናግሯል፤ “በጥፋት ላይ ጥፋት ይመጣል” ብሎ ነበር። እነዚህ አስከፊ ክንውኖች ለማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና መንግሥታዊ ተቋማት መንኮታኮት ምክንያት ይሆናሉ።—ሕዝ. 7:11-13, 25-27

በባቢሎናውያን የተከበበችው ኢየሩሳሌም ‘እሳት ላይ እንደተጣደ ድስት’ ሆና ነበር (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ከ609 ዓ.ዓ. ጀምሮ የትኞቹ የሕዝቅኤል ትንቢት ክፍሎች ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀመሩ?

15 ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን ውድቀት ከተነበየ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ትንቢቱ መፈጸም ጀመረ። በ609 ዓ.ዓ. ሕዝቅኤል ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደጀመሩ ሰማ። በዚያ ጊዜ የከተማይቱ ነዋሪዎች ከተማቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ ጥሪ ለማቅረብ መለከት የተነፋ ቢሆንም ሕዝቅኤል እንደተነበየው “ወደ ውጊያ የሚሄድ አንድም ሰው” አልነበረም። (ሕዝ. 7:14) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ወራሪውን የባቢሎን ሠራዊት መክተው በመመለስ ከተማቸውን ለመታደግ አልወጡም። አንዳንድ አይሁዳውያን ይሖዋ ከተማይቱን ያድናታል ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። ከዚያ ቀደም አሦራውያን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ በተቃረቡበት ወቅት ይሖዋ መልአኩን ልኮ አብዛኞቹን የአሦር ወታደሮች እንዲደመስስ በማድረግ ከተማዋን አድኖ ነበር። (2 ነገ. 19:32) በዚህ ጊዜ ግን ሊያድናቸው የመጣ መልአክ አልነበረም። ብዙም ሳይቆይ፣ የተከበበችው ከተማ “እሳት ላይ” እንደተጣደ “ድስት፣” ነዋሪዎቿ ደግሞ ድስቱ ውስጥ እንደተጨመረ “ሙዳ ሥጋ” ሆነው እዚያው ተያዙ። (ሕዝ. 24:1-10) አሥራ ስምንት ወራት ከፈጀ አስጨናቂ ከበባ በኋላ ኢየሩሳሌም ተደመሰሰች።

“በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ”

16. ይሖዋ ከወሰነው ጊዜ ዝንፍ እንደማይል እርግጠኛ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ከዚህ የሕዝቅኤል ትንቢት ምን ልንማር እንችላለን? ትንቢቱ፣ ከምንሰብከው መልእክትና የምንሰብክላቸው ሰዎች ከሚሰጡት ምላሽ ጋር ተዛማጅነት ይኖረው ይሆን? ይሖዋ የሐሰት ሃይማኖት መቼ እንደሚጠፋ አስቀድሞ ወስኗል፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ ከቀጠረው ጊዜ ዝንፍ እንደማይል የተረጋገጠ ነው። (2 ጴጥ. 3:9, 10፤ ራእይ 7:1-3) እርግጥ ይህ የሚሆንበትን ትክክለኛ ጊዜ አናውቅም። ያም ቢሆን ይሖዋ የሰጠንን መመሪያ በመከተል ሰዎችን ‘አሁን ፍጻሜያችሁ ደርሷል’ ብለን በተደጋጋሚ ማስጠንቀቃችንን እንቀጥላለን። ይህን መልእክት በተደጋጋሚ ማሰማት ያለብን ለምንድን ነው? ሕዝቅኤል ማስጠንቀቂያውን በተደጋጋሚ ማሰማቱ ምን ውጤት እንዳስገኘ ማወቃችን ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል። * ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ የሚገልጸውን ትንቢት ሲያውጅ አብዛኞቹ ሰዎች አላመኑትም ነበር። (ሕዝ. 12:27, 28) ከጊዜ በኋላ ግን በባቢሎን የነበሩ አንዳንድ አይሁዳውያን ግዞተኞች ጥሩ የልብ ዝንባሌ አሳይተዋል፤ በዚህም ምክንያት ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ በቅተዋል። (ኢሳ. 49:8) ዛሬም በተመሳሳይ ብዙ ሰዎች ይህ ዓለም ይጠፋል የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። (2 ጴጥ. 3:3, 4) ያም ቢሆን የሰው ልጆች የአምላክን መልእክት መቀበል የሚችሉበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ወደ ሕይወት የሚመራውን መንገድ እንዲያገኙ መርዳታችንን እንቀጥላለን።—ማቴ. 7:13, 14፤ 2 ቆሮ. 6:2

ምንም እንኳ ብዙዎች መልእክታችንን ባይቀበሉም ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች መፈለጋችንን እንቀጥላለን (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

የጥንቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ‘ብራቸውን በየጎዳናው ላይ የጣሉት’ ለምን ነበር? (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ምን ነገሮች ሲከናወኑ እናያለን?

17 በተጨማሪም የሕዝቅኤል ትንቢት በሃይማኖታዊ ድርጅቶች ላይ ጥቃት በሚሰነዘርበት ጊዜ አባላቱ ሃይማኖትን ለመታደግ ‘ወደ ውጊያ እንደማይሄዱ’ ያስገነዝበናል። ከዚህ ይልቅ “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ” እያሉ የሚያሰሙት የእርዳታ ጩኸት ሰሚ እንዳላገኘ ሲገባቸው “እጃቸው ሁሉ ይዝላል”፤ ‘ብርክም ይይዛቸዋል።’ (ሕዝ. 7:3, 14, 17, 18፤ ማቴ. 7:21-23) እነዚህ ሰዎች ሌላስ ምን ያደርጋሉ? (ሕዝቅኤል 7:19-21ን አንብብ።) ይሖዋ “ብራቸውን በየጎዳናው ይጥላሉ” ብሏል። ስለ ጥንቷ ኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተነገረው ይህ ሐሳብ በታላቁ መከራ ወቅት የሚሆነውን ነገር በግልጽ ያሳያል። በዚያ ጊዜ ሰዎች፣ እየመጣባቸው ካለው ጥፋት ገንዘብ ሊያድናቸው እንደማይችል ይገነዘባሉ።

18. የሕዝቅኤል ትንቢት ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን በተመለከተ ምን ያስተምረናል?

18 ይህ የሕዝቅኤል ትንቢት ለእኛስ ምን ትምህርት ይዞልናል? ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ነገር ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ያስገነዝበናል። የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ለምን ነገር ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ያስተዋሉት በከተማቸውም ሆነ በሕይወታቸው ላይ ጥፋት እንደተደቀነና ቁሳዊ ነገሮች ሊያድኗቸው እንደማይችሉ ከተገነዘቡ በኋላ እንደነበር ልብ በል። በዚህ ጊዜ ንብረታቸውን ሁሉ በመጣል “ከነቢይ ራእይ” መፈለግ ጀመሩ፤ ግን እርምጃ መውሰድ የሚችሉበት ጊዜ አምልጧቸዋል። (ሕዝ. 7:26) እኛ ግን የዚህ ክፉ ዓለም ፍጻሜ እንደቀረበ ገና ከወዲሁ አሳምረን እናውቃለን። ስለሆነም በአምላክ ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ አነሳስቶናል። በዚህም የተነሳ ዘላቂ ጥቅም ያለውንና መቼም ‘በጎዳና ላይ’ የማይጣለውን መንፈሳዊ ሀብት ለማካበት ጥረት እናደርጋለን።—ማቴዎስ 6:19-21, 24ን አንብብ።

19. ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ከተናገራቸው ትንቢቶች ምን ትምህርት እናገኛለን?

19 እስቲ ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ከተናገራቸው ትንቢቶች ያገኘነውን ትምህርት ለመከለስ እንሞክር። እነዚህ ትንቢቶች ሌሎች ሰዎች የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለመርዳት የቀረን ጊዜ በጣም ውስን እንደሆነ ያስታውሱናል። ስለሆነም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በጥድፊያ ስሜት እንካፈላለን። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አባታችንን ይሖዋን ማገልገል ሲጀምሩ በእጅጉ እንደሰታለን። ይሁን እንጂ ይህን እርምጃ ለማይወስዱ ሰዎችም ጭምር ሕዝቅኤል እንዳደረገው ‘አሁን ፍጻሜያችሁ ደርሷል’ በማለት ማስጠንቀቂያ ማሰማታችንን እንቀጥላለን። (ሕዝ. 3:19, 21፤ 7:3) በተጨማሪም እስከ መጨረሻው በይሖዋ ለመታመንና ለእሱ ንጹሕ አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ ለመስጠት ቆርጠናል።—መዝ. 52:7, 8፤ ምሳሌ 11:28፤ ማቴ. 6:33

^ አን.3 ሕዝቅኤል ይህን ሁሉ ትንቢታዊ ድራማ የሠራው ሰዎች እያዩት ነው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ሕዝቅኤልን ከእነዚህ ትንቢታዊ ድራማዎች አንዳንዶቹን፣ ለምሳሌ ዳቦ እንደመጋገርና ጓዝ እንደመሸከም ያሉትን “በፊታቸው” እንዲያሳይ በቀጥታ አዞት ነበር።—ሕዝ. 4:12፤ 12:7

^ አን.13 ይሖዋ ኢየሩሳሌም እንድትጠፋ መፍቀዱ ሁለት ነገዶችን ባቀፈው የይሁዳ መንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን አሥሩን ነገዶች ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ላይም ፍርድ እንዳስተላለፈ ያሳያል። (ኤር. 11:17፤ ሕዝ. 9:9, 10) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ)፣ ጥራዝ 1 ገጽ 462 ላይ የሚገኘውን “የዘመናት ስሌት—ከ997 ዓ.ዓ እስከ ኢየሩሳሌም ጥፋት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.16 በሕዝቅኤል 7:5-7 ላይ በሚገኘው አጭር ምንባብ ውስጥ ይሖዋ “እየመጣ ነው” እና “ይመጣል” እንደሚሉት ያሉ አገላለጾችን በተደጋጋሚ መጠቀሙን ልብ በል።