በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 15

“ምንዝርሽንም አስተውሻለሁ”

“ምንዝርሽንም አስተውሻለሁ”

ሕዝቅኤል 16:41

ፍሬ ሐሳብ፦ በሕዝቅኤልና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለተጠቀሱት ዝሙት አዳሪዎች ወይም አመንዝሮች ከተሰጠው መግለጫ የምናገኘው ትምህርት

1, 2. ሰዎች በተለይ ለምን ዓይነት ዝሙት አዳሪ ከፍተኛ ጥላቻ ሊያድርባቸው ይችላል?

ዝሙት አዳሪ ስታይ ምን ይሰማሃል? በጣም ልታዝን ብሎም ‘እንዲህ ላለው ወራዳ ሕይወት የዳረጋት ምን ይሆን?’ ብለህ ልታስብ ትችላለህ። በለጋ ዕድሜዋ ወደ ጎዳና እንድትወጣ ያስገደዳት በቤት ውስጥ የደረሰባት ጥቃት ይሆን? ወይስ የምትኖርበት አስከፊ ድህነት ለባርነት ሕይወት ራሷን እንድትሸጥ አስገድዷት ነው? አሊያም ደግሞ ጨካኝ የትዳር ጓደኛ አስመርሯት ሸሽታ ወጥታ ይሆን? በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እንደዚህ ያሉ አሳዛኝ ታሪኮችን መስማት የተለመደ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም ለአንዳንድ ዝሙት አዳሪዎች ደግነት ያሳየው ለዚህ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ንስሐ ገብተው አኗኗራቸውን የሚለውጡ ዝሙት አዳሪዎች የተሻለ ሕይወት መምራት እንደሚችሉ አበክሮ ተናግሯል።—ማቴ. 21:28-32፤ ሉቃስ 7:36-50

2 እስቲ አሁን ደግሞ ከዚህ ፈጽሞ በተለየ ምክንያት ዝሙት አዳሪ ስለሆነች ሴት ለማሰብ ሞክር። ይህች ሴት እንዲህ ወዳለው ሕይወት የገባችው በራሷ ምርጫ ነው። ይህን ሕይወት እንደሚያዋርድ ሳይሆን እንደሚያኮራ አድርጋ ትመለከተዋለች። ይህ ሥራዋ ገንዘብ ስለሚያስገኝላትና በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ስለሚያስችላት ትወደዋለች። ይባስ ብሎ ደግሞ ይህች ሴት የዝሙት አዳሪነትን ሕይወት የመረጠችው ጥሩና ታማኝ የሆነ ባሏን ከድታ እንደሆነ ብታውቅስ? እንዲህ ላለችው ሴትም ሆነ ለመረጠችው የሕይወት ጎዳና ከፍተኛ ጥላቻ ቢያድርብህ የሚያስገርም አይደለም። ይሖዋ አምላክ ስለ ሐሰት ሃይማኖት ያለውን ስሜት ለመግለጽ ዝሙት አዳሪ ሴትን በተደጋጋሚ እንደ ምሳሌ የሚጠቀመው እንዲህ ዓይነት ስሜት እንደሚሰማን ስለሚያውቅ ነው።

3. በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን የሕዝቅኤል መጽሐፍ ምዕራፎች እንመረምራለን?

3 በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ በእስራኤልና በይሁዳ የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች የፈጸሙትን አስከፊ ክህደት ከዝሙት አዳሪነት ጋር እያወዳደሩ የሚገልጹ ሁለት ምዕራፎች አሉ። (ሕዝ. ምዕራፍ 16 እና 23) እነዚህን ሁለት ምዕራፎች በዝርዝር ከመመርመራችን በፊት ግን ስለ አንዲት ሌላ ምሳሌያዊ ዝሙት አዳሪ የተሰጠውን መግለጫ ብንመለከት ጥሩ ይሆናል። የዚህች ዝሙት አዳሪ ምንዝር የጀመረው ከሕዝቅኤል ዘመን ብዙ ቀደም ብሎ፣ እንዲያውም የእስራኤል ብሔር ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ሲሆን ይህ የምንዝር ድርጊት አሁንም ድረስ በስፋት ቀጥሏል። የዚህች ዝሙት አዳሪ ማንነት የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተገልጿል።

‘የአመንዝሮች እናት’

4, 5. “ታላቂቱ ባቢሎን” ምን ታመለክታለች? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ባየው ራእይ ውስጥ አንዲት አስገራሚ ሴት ተመልክቶ ነበር። ይህች ሴት “ታላቂቱ አመንዝራ” እና “ታላቂቱ ባቢሎን፣ የአመንዝሮች . . . እናት” ተብላ ተጠርታለች። (ራእይ 17:1, 5) የዚህች ሴት ትክክለኛ ማንነት ለበርካታ መቶ ዓመታት ለሃይማኖት መሪዎችና ለመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ሚስጥር ሆኖ ኖሯል። አንዳንዶቹ ባቢሎንን፣ ሌሎቹ ሮምን የቀሩት ደግሞ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንደምታመለክት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የዚህችን ‘ታላቅ አመንዝራ’ ትክክለኛ ማንነት ካወቁ በርካታ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። ይህች ሴት በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ታመለክታለች። ይህን እንዴት እናውቃለን?

5 ይህች ዝሙት አዳሪ ‘ከምድር ነገሥታት’ ወይም ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ምንዝር በመፈጸሟ ተወግዛለች። ስለዚህ እሷ ራሷ አንድን የፖለቲካ ኃይል ወይም መንግሥት ልታመለክት እንደማትችል ግልጽ ነው። በተጨማሪም የዚህን ዓለም የንግድ ሥርዓት የሚያመለክቱት “የምድር ነጋዴዎች” ታላቂቱ ባቢሎን በሚደርስባት ጥፋት እንደሚያዝኑ የራእይ መጽሐፍ ይገልጻል። ስለዚህ ታላቂቱ ባቢሎን የንግዱን ሥርዓት ልታመለክት አትችልም። ታዲያ ታላቂቱ ባቢሎን ማን ነች? ‘መናፍስታዊ ድርጊቶችን’ እንደምትፈጽም፣ ጣዖት አምላኪ እንደሆነች እንዲሁም ሌሎችን እንደምታሳስት ተገልጿል። ታዲያ እነዚህ ድርጊቶች ምግባረ ብልሹ የሆኑት የዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የሚፈጽሟቸው አይደሉም? በተጨማሪም ይህች አመንዝራ በዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ኃይሎች ላይ ተቀምጣ እንደምትጋልብ ማለትም በእነሱ ላይ መጠነኛ ተጽዕኖ እንደምታሳድር መገለጹን ልብ በል። ከዚህም ሌላ የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች ታሳድዳለች። (ራእይ 17:2, 3፤ 18:11, 23, 24) ታዲያ የሐሰት ሃይማኖቶች እስከዚህ ዘመን ድረስ ሲያደርጉ የቆዩት ይህን አይደለም?

ከጊዜ በኋላ ባቢሎን ተብላ የተጠራችው የጥንቷ ባቤል የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች፣ መሠረተ ትምህርቶችና ድርጅቶች መፈልፈያ ነች (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. ታላቂቱ ባቢሎን ‘የአመንዝሮች እናት’ የተባለችው ለምንድን ነው?

6 ይሁን እንጂ ታላቂቱ ባቢሎን “ታላቂቱ አመንዝራ” ብቻ ሳይሆን ‘የአመንዝሮች እናት’ የተባለችው ለምንድን ነው? የሐሰት ሃይማኖት ስፍር ቁጥር በሌላቸው የሃይማኖት ድርጅቶችና ኑፋቄዎች የተከፋፈለ ነው። በጥንቷ ባቤል ወይም ባቢሎን ቋንቋዎች ከተዘበራረቁበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች በመላው ምድር የተሰራጩ ሲሆን በዚህም ምክንያት እጅግ ብዙ ሃይማኖቶች ተመሥርተዋል። “ታላቂቱ ባቢሎን” ስያሜዋን ያገኘችው የሐሰት ሃይማኖት መፈልፈያ ከሆነችው ከባቢሎን ከተማ መሆኑ ምንኛ ተገቢ ነው! (ዘፍ. 11:1-9) ስለዚህ እነዚህ ሃይማኖቶች በሙሉ የአንድ ድርጅት ማለትም የአንዲት ታላቅ አመንዝራ “ልጆች” እንደሆኑ ሊቆጠር ይችላል። ሰይጣን ብዙ ጊዜ እንደነዚህ ያሉትን ሃይማኖቶች ተጠቅሞ ሰዎችን በማታለል ወደ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ወደ ጣዖት አምልኮ እንዲሁም አምላክን ወደሚያዋርዱ ሌሎች እምነቶችና ልማዶች ይመራቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ይህችን ምግባረ ብልሹ የሆነች ዓለም አቀፋዊ ድርጅት በተመለከተ “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉ . . . ከሆነ ከእሷ ውጡ” የሚል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑ በእርግጥም የሚያስገርም አይደለም።—ራእይ 18:4, 5ን አንብብ።

7. ‘ከታላቂቱ ባቢሎን ውጡ’ የሚለውን ማስጠንቀቂያ መስማት የሚኖርብን ለምንድን ነው?

7 አንተስ ይህን ማስጠንቀቂያ ሰምተህ እርምጃ ወስደሃል? የሰው ልጆችን ‘መንፈሳዊ ፍላጎት’ እንዲኖራቸው አድርጎ የፈጠራቸው ይሖዋ ራሱ እንደሆነ አስታውስ። (ማቴ. 5:3 ግርጌ) ስለዚህ ይህ ፍላጎት በትክክለኛው መንገድ ሊሟላ የሚችለው በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ አማካኝነት ብቻ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ከመንፈሳዊ ምንዝር ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። ሰይጣን ዲያብሎስ ግን በተቃራኒ አቅጣጫ ሊመራቸው ይሞክራል። የአምላክን ሕዝቦች አታሎ መንፈሳዊ ምንዝር እንዲፈጽሙ ማድረግ ይፈልጋል። በዚህ ረገድም ብዙ ጊዜ ተሳክቶለታል። ከሕዝቅኤል ዘመን በፊት በነበሩት ረጅም ዘመናት የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምንዝር ሲፈጽሙ ቆይተዋል። ይህን የአምላክ ሕዝቦች ታሪክ መመርመራችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ታሪክ ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች፣ ስለ ፍትሑና ስለ ምሕረቱ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ።

‘ዝሙት አዳሪ ሆንሽ’

8-10. (ሀ) ንጹሕ አምልኮ ሊያሟላ የሚገባው ወሳኝ መሥፈርት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በሐሰት ሃይማኖት ስለመካፈል ምን አመለካከት አለው? በምሳሌ አስረዳ።

8 ይሖዋ የሕዝቦቹ ክህደት ምን ያህል ስሜቱን እንደጎዳው ለመግለጽ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ስለ ዝሙት አዳሪ የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል። ይሖዋ ሕዝቦቹ በፈጸሙት ክህደትና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ምክንያት የተሰማውን ሐዘን ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የሚገልጹ ሁለት ምዕራፎችን እንዲዘግብ ሕዝቅኤልን በመንፈሱ መርቶታል። ይሖዋ ሕዝቦቹን ከዝሙት አዳሪ ወይም አመንዝራ ሴት ጋር ያመሳሰላቸው ለምንድን ነው?

9 መልሱን ለመረዳት በመጀመሪያ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ላይ የተብራራውን፣ ንጹሕ አምልኮ ሊያሟላ የሚገባውን አንድ ወሳኝ መሥፈርት ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ላይ “ከእኔ በቀር [ወይም “እኔን የሚቀናቀኑ” ግርጌ] ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። . . . እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ” ብሎ ነበር። (ዘፀ. 20:3, 5) ከጊዜ በኋላም እንደሚከተለው በማለት ይህንኑ ሐቅ አበክሮ ተናግሯል፦ “ይሖዋ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ በመሆኑ የሚታወቅ ስለሆነ ለሌላ አምላክ አትስገድ። አዎ፣ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።” (ዘፀ. 34:14) ይሖዋ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከዚህ ይበልጥ ግልጽ የሆነ መመሪያ ሊሰጥ አይችልም። ይሖዋን ብቻ እስካላመለክን ድረስ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ አንችልም።

10 ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት አንድን ባልና ሚስት እንውሰድ። ባልም ሆነ ሚስት የትዳር ጓደኛቸው ለትዳሩ ታማኝ እንዲሆን የመጠበቅ መብት አላቸው። ባልም ሆነ ሚስት ከትዳር ጓደኛቸው ውጭ ለሌላ ሰው የፍቅር ወይም የፆታ ስሜት በሚያሳዩበት ጊዜ ታማኝ የሆነው ወገን ቢቀና ወይም እንደተከዳ ቢሰማው አያስገርምም። (ዕብራውያን 13:4ን አንብብ።) በተመሳሳይም ይሖዋ ለእሱ ብቻ የተወሰኑ ሕዝቦቹ እሱን ትተው የሐሰት አማልክትን ባመለኩበት ወቅት ክህደት እንደተፈጸመበት የተሰማው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ይሖዋ ሕዝቦቹ በፈጸሙት ክህደት ምክንያት የተሰማውን ሐዘን በሕዝቅኤል ምዕራፍ 16 ላይ ኃይለኛ በሆነ መንገድ ገልጾታል።

11. ይሖዋ ስለ ኢየሩሳሌምና ከጅምሩ ስለነበረችበት ሁኔታ ምን ገልጿል?

11 ይሖዋ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ከተናገራቸው ንግግሮች መካከል ረጅሙ የሚገኘው በምዕራፍ 16 ላይ ነው፤ በተጨማሪም ይህ ንግግር በመላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይሖዋ ከተናገራቸው ረጅም ትንቢቶች መካከል አንዱ ነው። በዚህ ምዕራፍ ላይ ይሖዋ በዋነኝነት ያተኮረው ከዳተኛ የሆነውን የይሁዳ ብሔር በምትወክለው የኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ነው። ይህ ዘገባ ኢየሩሳሌም ከጅምሩ ስለነበረችበት ሁኔታና ስለፈጸመችው ክህደት የሚገልጸውን አሳዛኝ ታሪክ ይተርካል። ኢየሩሳሌም መጀመሪያ ላይ፣ ሳትታጠብና ምንም እንክብካቤ ሳይደረግላት ተወልዳ እንደተጣለች ሕፃን ነበረች። ወላጆቿ የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑት ጣዖት አምላኪዎቹ ከነዓናውያን ነበሩ። ዳዊት የኢየሩሳሌምን ከተማ ድል አድርጎ እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ኢየሩሳሌም የከነዓናውያን ጎሳ በሆኑት በኢያቡሳውያን ቁጥጥር ሥር ነበረች። ይሖዋ ለዚህች የተጣለች ጨቅላ ሕፃን ስላዘነላት አንስቶ በማጠብ እንክብካቤ አደረገላት። ከጊዜ በኋላም እንደ ሚስቱ ሆነች። በኢየሩሳሌም መኖር የጀመሩት እስራኤላውያን በሙሴ ዘመን በፈቃደኝነት ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ተጋብተው ነበር። (ዘፀ. 24:7, 8) ባለጸጋ የሆነና ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ባል ሚስቱን በሚያማምሩ ጌጣጌጦች እንደሚያስውባት ሁሉ ይሖዋም ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ከሆነች በኋላ በረከቱን በእሷ ላይ በማፍሰስ አበልጽጓታል እንዲሁም አስውቧታል።—ሕዝ. 16:1-14

ሰለሞን የባዕድ አገር ሚስቶቹ ኢየሩሳሌምን በጣዖት አምልኮ እንዲበክሉ ፈቅዷል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. ክህደት ወደ ኢየሩሳሌም ቀስ በቀስ ሰርጎ የገባው እንዴት ነው?

12 እስቲ ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ እንመልከት። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ሆኖም አንቺ በውበትሽ መመካት ጀመርሽ፤ ዝናሽንም ለዝሙት አዳሪነት ተጠቀምሽበት። ከአላፊ አግዳሚው ጋር ያለገደብ አመነዘርሽ፤ ውበትሽንም ለማንም አሳልፈሽ ሰጠሽ።” (ሕዝ. 16:15) በሰለሞን ዘመን ይሖዋ ሕዝቡን እጅግ ባርኮና አበልጽጎ ስለነበር ኢየሩሳሌም በጥንቱ ዓለም ከነበሩት ከተሞች ሁሉ ጎልታ የምትታይ ውብ ከተማ ሆና ነበር ማለት ይቻላል። (1 ነገ. 10:23, 27) ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የሐሰት አምልኮ ወደ ከተማዋ ሰርጎ መግባት ጀመረ። ሰለሞን በርካታ የሆኑትን የባዕድ አገር ሚስቶቹን ለማስደሰት ስለፈለገ ኢየሩሳሌምን በአረማዊ አምልኮ በከላት። (1 ነገ. 11:1-8) ከእሱ በኋላ የተነሱት አንዳንድ ነገሥታት ደግሞ መላው የእስራኤል ምድር በሐሰት አምልኮ እንዲበከል በማድረግ ከእሱ የከፋ ድርጊት ፈጽመዋል። ታዲያ ይሖዋ ሕዝቦቹ የፈጸሙትን ክህደትና ምንዝር ሲመለከት ምን ተሰማው? “እነዚህ ነገሮች መሆን የለባቸውም፤ ጨርሶ ሊፈጸሙም አይገባም” ብሏል። (ሕዝ. 16:16) ዓመፀኛ የሆኑት ሕዝቦቹ ግን ይበልጥ ያዘቀጠ ድርጊት መፈጸማቸውን ቀጠሉ።

አንዳንድ እስራኤላውያን ልጆቻቸውን እንደ ሞሎክ ላሉ የሐሰት አማልክት ይሠዉ ነበር

13. በኢየሩሳሌም የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ምን የክፋት ድርጊት ፈጽመዋል?

13 ይሖዋ ሕዝቦቹ ስለፈጸሙት ክፋት የሚገልጸውን የሚከተለውን ሐሳብ ሲናገር ምን ያህል አዝኖና ተዘግንኖ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፦ “ለእኔ የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ወስደሽ መብል ይሆኑ ዘንድ ለጣዖቶቹ ሠዋሽላቸው፤ የምትፈጽሚው ምንዝር እጅግ አልበዛም? ወንዶች ልጆቼን አረድሽ፤ በእሳትም አሳልፈሽ መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሻቸው።” (ሕዝ. 16:20, 21) የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የፈጸሟቸው አሰቃቂ ድርጊቶች ሰይጣን ምን ያህል ክፉ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው። ሰይጣን የይሖዋን ሕዝቦች አታሎ እንዲህ ያሉትን አስጸያፊ ነገሮች እንዲፈጽሙ ማድረግ እጅግ ያስደስተዋል! ይሁን እንጂ ከይሖዋ ዓይን የተሰወረ ነገር የለም። አምላክ ሰይጣን የፈጸመው የጭካኔ ድርጊት ያስከተለውን መጥፎ ውጤት በሙሉ ያስተካክላል፤ እንዲሁም ፍትሐዊ እርምጃ ይወስዳል።—ኢዮብ 34:24ን አንብብ።

14. ይሖዋ በሰጠው ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት የኢየሩሳሌም ሁለት እህቶች እነማን ናቸው? ከሦስቱ መካከል ይበልጥ ክፉ የነበረችው ማን ነች?

14 ኢየሩሳሌም፣ በፈጸመችው ክፋት ልትዘገነን ይገባ ነበር፤ እሷ ግን አልተዘገነነችም። እንዲያውም በዝሙት አዳሪነቷ ገፋችበት። ይሖዋ ኢየሩሳሌም ከሌሎች ዝሙት አዳሪዎችም ይበልጥ እፍረተ ቢስ እንደሆነች ተናግሯል፤ ምክንያቱም ሌሎች ከእሷ ጋር የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ ገንዘብ የምትከፍላቸው እሷ ራሷ ነች! (ሕዝ. 16:34) አምላክ ቤተሰብን እንደ ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም፣ ኢየሩሳሌም ‘እንደ እናቷ’ ማለትም ቀደም ሲል በውስጧ ይኖሩ እንደነበሩት አረማዊ ሕዝቦች እንደሆነች ተናግሯል። (ሕዝ. 16:44, 45) ይሖዋ በመቀጠል የኢየሩሳሌም ታላቅ እህት ሰማርያ እንደሆነች ተናገረ፤ ሰማርያ ከኢየሩሳሌም አስቀድማ ሃይማኖታዊ ምንዝር መፈጸም ጀምራ ነበር። አምላክ ሰዶምም የኢየሩሳሌም እህት እንደሆነች ተናግሯል፤ በግትርነቷና በብልግናዋ ምክንያት ከበርካታ ዘመናት በፊት የጠፋችው ሰዶም እዚህ ላይ የተጠቀሰችው እንዲህ ላለው ክፉ ምግባር ምሳሌ ስለምትሆን ነው። ይሖዋ ይህን የተናገረው ኢየሩሳሌም በክፋት ረገድ ከሁለቱም እህቶቿ፣ ማለትም ከሰማርያና ሌላው ቀርቶ ከሰዶም ጭምር እንደበለጠች ጎላ አድርጎ መግለጽ ስለፈለገ ነው። (ሕዝ. 16:46-50) የአምላክ ሕዝቦች የተሰጧቸውን በርካታ ማስጠንቀቂያዎች ችላ በማለት አስጸያፊ ድርጊት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

15. ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ የፍርድ ውሳኔ ለማስተላለፍ የተነሳሳበት ዓላማ ምን ነበር? ይህስ ምን ተስፋ ይሰጣል?

15 ታዲያ ይሖዋ ምን ያደርግ ይሆን? ኢየሩሳሌምን “ደስ ያሰኘሻቸውን ፍቅረኞችሽን ሁሉ . . . አንድ ላይ እሰበስባለሁ። . . . በእጃቸው አሳልፌ እሰጥሻለሁ” ብሏታል። ወዳጆቿ የነበሩት አረማዊ ብሔራት ውበቷንና ጌጣጌጦቿን ገፈው ይደመስሷታል። ይሖዋ “በድንጋይም ይወግሩሻል፤ በሰይፋቸውም ያርዱሻል” ብሏል። ይሖዋ ይህን ፍርድ የሚያስፈጽመው ለምንድን ነው? ሕዝቦቹን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ምንዝርሽንም አስተውሻለሁ” በማለት ዓላማው ምን እንደሆነ ግልጽ አድርጓል። አክሎም “በአንቺ ላይ የነበረው ቁጣዬ ይበርዳል፤ ንዴቴም ከአንቺ ይርቃል። እኔም እረጋጋለሁ፤ ከእንግዲህም አልቆጣም” ብሏል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ እንደተብራራው የይሖዋ ዋነኛ ዓላማ ሕዝቡን ከግዞት መልሶ ዳግመኛ ማቋቋም ነበር። ይህን የሚያደርገው ለምንድን ነው? “እኔ ራሴ በልጅነትሽ ጊዜ ከአንቺ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ” ብሏል። (ሕዝ. 16:37-42, 60) ይሖዋ ሕዝቦቹ ቢከዱትም እሱ ግን ለእነሱ ምንጊዜም ታማኝ ነው!—ራእይ 15:4ን አንብብ።

16, 17. (ሀ) አሁን ባለን ግንዛቤ መሠረት፣ ኦሆላና ኦሆሊባ ሕዝበ ክርስትናን የሚያመለክቱ ትንቢታዊ ጥላዎች ናቸው የማንለው ለምንድን ነው? (“ዝሙት አዳሪዎቹ እህትማማቾች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) በሕዝቅኤል ምዕራፍ 16 እና 23 ላይ ከሚገኘው ዘገባ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

16 ይሖዋ በሕዝቅኤል ምዕራፍ 16 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ረጅምና ኃይለኛ ንግግሩ አማካኝነት ስለ ጽድቅ መሥፈርቶቹ፣ ስለ ፍትሑና ስለ ምሕረቱ ብዙ ነገር አስተምሮናል። ስለ ሕዝቅኤል ምዕራፍ ሃያ ሦስትም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ ጥንት የነበሩት ሕዝቦቹ የፈጸሙትን ምንዝር በተመለከተ ለተናገረው ግልጽ መልእክት ትኩረት ይሰጣሉ። ይሁዳና ኢየሩሳሌም እንዳደረጉት ይሖዋን ማሳዘን ፈጽሞ አንፈልግም! በመሆኑም ከማንኛውም ዓይነት ጣዖት አምልኮ ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። ይህም እንደ ጣዖት አምልኮ ከሚቆጠሩት ከስግብግብነትና ከፍቅረ ንዋይ መራቅን ይጨምራል። (ማቴ. 6:24፤ ቆላ. 3:5) ይሖዋ በምሕረቱ ተነሳስቶ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ንጹሕ አምልኮን መልሶ ስላቋቋመልንና ዳግመኛ እንዳይበከል ጥበቃ ስለሚያደርግለት ምንጊዜም አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! ይሖዋ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የገባው “ዘላቂ ቃል ኪዳን” በክህደት ወይም በምንዝር ምክንያት ፈጽሞ አይፈርስም። (ሕዝ. 16:60) እንግዲያው በዛሬው ጊዜ ካሉት የይሖዋ ንጹሕ ሕዝቦች እንደ አንዱ የመቆጠር መብታችንን ከፍ አድርገን እንመልከተው።

17 ይሁንና ይሖዋ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ በተገለጹት ዝሙት አዳሪዎች ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ስለ “ታላቂቱ አመንዝራ” ማለትም ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ምን ያስተምረናል? እስቲ እንመልከት።

“ዳግመኛም አትገኝም”

18, 19. በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሱት አመንዝሮችና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰችው አመንዝራ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

18 ይሖዋ አይለወጥም። (ያዕ. 1:17) ታላቂቱ አመንዝራ በኖረችባቸው ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ለሐሰት ሃይማኖት ያለው አመለካከት አልተለወጠም። በመሆኑም በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ በተገለጹት አመንዝሮች ላይ በተላለፈው ፍርድና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸችው “ታላቂቱ አመንዝራ” በሚደርስባት ዕጣ መካከል በርካታ ተመሳሳይነት ያለ መሆኑ አያስደንቅም።

19 ለምሳሌ ያህል፣ በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ በተገለጹት አመንዝሮች ማለትም በከዳተኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ የደረሰው ቅጣት የመጣው በቀጥታ ከይሖዋ ሳይሆን አብረዋቸው መንፈሳዊ ምንዝር ሲፈጽሙ ከነበሩት ብሔራት መሆኑን ልብ በል። በተመሳሳይም በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ የምታመለክተው ታላቂቱ ባቢሎን ‘ከምድር ነገሥታት’ ጋር ምንዝር በመፈጸሟ ተወግዛለች። በእሷ ላይ የሚደርሰው ቅጣትስ የሚመጣው ከማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች “አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል” በማለት ይናገራል። የዓለም መንግሥታት እንዲህ ያለ ያልተጠበቀ እርምጃ የሚወስዱት ለምንድን ነው? አምላክ “ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ . . . ይህን በልባቸው” ስለሚያኖር ነው።—ራእይ 17:1-3, 15-17

20. በባቢሎን ላይ የሚፈጸመው ፍርድ የማያዳግምና የመጨረሻ እንደሚሆን እንዴት እናውቃለን?

20 ስለዚህ ይሖዋ የዚህን ዓለም ብሔራት በመጠቀም በሕዝበ ክርስትና ሥር ያሉትን በርካታ ሃይማኖቶች ጨምሮ በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ የቅጣት ፍርዱን ያስፈጽማል። ይህ ፍርድ የማያዳግምና የመጨረሻ ይሆናል፤ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ የምትወክለው ታላቂቱ ባቢሎን ምሕረት የማግኘትም ሆነ አካሄዷን የመለወጥ አጋጣሚ አታገኝም። የራእይ መጽሐፍ ባቢሎን ‘ዳግመኛ እንደማትገኝ’ ይናገራል። (ራእይ 18:21) የአምላክ መላእክት “ያህን አወድሱ! ከእሷ የሚወጣው ጭስም ለዘላለም ወደ ላይ ይወጣል” በማለት በታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት የተሰማቸውን ደስታ ይገልጻሉ። (ራእይ 19:3) ይህ ፍርድ ለዘላለም የጸና ይሆናል። ከዚህ በኋላ የትኛውም የሐሰት ሃይማኖት በምድር ላይ እንዲኖርና ንጹሕ አምልኮን እንዲበክል አይፈቀድለትም። በባቢሎን ላይ የሚፈጸመው እሳታማ ፍርድና ጥፋት በምሳሌያዊ ሁኔታ ጭሱ ለዘላለም ሲወጣ ይኖራል።

ታላቂቱ ባቢሎን ስታስታቸውና ተጽዕኖ ስታሳድርባቸው የኖሩት ብሔራት በእሷ ላይ ተነስተው ያጠፏታል (አንቀጽ 19, 20⁠ን ተመልከት)

21. የሐሰት ሃይማኖት መጥፋት ለየትኛው ክንውን መጀመሪያ ይሆናል? ይህ ክንውን የሚቋጨውስ እንዴት ነው?

21 የዚህ ዓለም መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እርምጃ በመውሰድ የአምላክን ፍርድ ያስፈጽማሉ፤ ይህ ፍርድ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ታይቶ የማይታወቅ ሁከት የሚፈጠርበት ታላቁ መከራ የሚጀምረው በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ነው። (ማቴ. 24:21) ይህ መከራ የሚቋጨው ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት በሚያካሂደው ጦርነት ማለትም በአርማጌዶን ይሆናል። (ራእይ 16:14, 16) የዚህ መጽሐፍ ቀጣይ ምዕራፎች እንደሚያሳዩት የሕዝቅኤል መጽሐፍ በታላቁ መከራ ወቅት ስለሚከናወኑት ነገሮች የሚነግረን ብዙ ነገር አለ። ይሁንና በሕዝቅኤል ምዕራፍ 16 እና 23 ላይ ከተገለጹት ነገሮች በሕይወታችን ልንሠራበት የምንችለው ምን ትምህርት እናገኛለን?

የዚህ ዓለም መንግሥታት የአምላክን ፍርድ ለማስፈጸም በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ይነሳሉ (አንቀጽ 21⁠ን ተመልከት)

22, 23. በሕዝቅኤልና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለተገለጹት አመንዝሮች መመርመራችን ከምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ምን ለማድረግ ያነሳሳናል?

22 ሰይጣን ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡ ሰዎችን መበከል ያስደስተዋል። ከንጹሕ አምልኮ ዘወር እንድንልና በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን አመንዝሮች ዓይነት አካሄድ እንድንከተል ማድረግ ቢችል ደስታውን አይችለውም። እንግዲያው ይሖዋ በአምልኮ ረገድ ምንም ተቀናቃኝ እንዲኖረው እንደማይፈቅድም ሆነ ክህደትን መታገሥ እንደማይችል ማስታወስ ይኖርብናል። (ዘኁ. 25:11) በተቻለን መጠን ከሐሰት ሃይማኖት ለመራቅና በአምላክ ዓይን ‘ርኩስ የሆነን ማንኛውንም ነገር ላለመንካት’ ጥንቃቄ እናደርጋለን። (ኢሳ. 52:11) በዚህ የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ባሉት ፖለቲካዊ ግጭቶችና ውዝግቦች እጃችንን ባለማስገባት ገለልተኝነታችንን የምንጠብቀውም ለዚህ ነው። (ዮሐ. 15:19) ብሔራዊ ስሜትን ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው የሐሰት ሃይማኖቶች እንደ አንዱ በመቁጠር ከዚያ እንርቃለን።

23 ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ንጹሕ በሆነው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ማምለክ መቻላችን ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ ምንጊዜም አንዘንጋ። የይሖዋ በረከት የማይለየውን ይህን የአምልኮ ዝግጅት ከፍ አድርገን እንመልከት፤ እንዲሁም ከሐሰት ሃይማኖትም ሆነ እሷ ከምትፈጽመው ምንዝር ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ!