በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 17

“ጎግ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ተነስቻለሁ”

“ጎግ ሆይ፣ እኔ በአንተ ላይ ተነስቻለሁ”

ሕዝቅኤል 38:3

ፍሬ ሐሳብ፦ “ጎግ” ማን ነው? የሚወረው ‘ምድርስ’ ምንድን ነው?

1, 2. የትኛው ታላቅ ጦርነት ከፊታችን ይጠብቀናል? ከዚህ ጋር በተያያዘስ የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

የምንኖርባት ምድር የሰው ልጆች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ባደረጓቸው ጦርነቶች የተነሳ በፈሰሰው ደም ተበክላለች፤ በሃያኛው መቶ ዘመን የተደረጉትን ሁለት የዓለም ጦርነቶች ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ሆኖም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ጦርነት ገና ከፊታችን ይጠብቀናል። ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት የምድር ብሔራት የራስ ወዳድነት ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ እርስ በርስ ከሚያደርጓቸው ጦርነቶች የተለየ ነው። ይህ ጦርነት “ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን” የሚካሄድ ጦርነት ነው። (ራእይ 16:14) ይህ ጦርነት የሚቀሰቀሰው አንድ እብሪተኛ ጠላት በአምላክ ዓይን በጣም ውድ የሆነን “ምድር” ሲወር ነው፤ ይህ ወረራ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ የማጥፋት ኃይሉን እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ላይ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እንዲጠቀምበት ያነሳሳዋል።

2 ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፦ ይህ ጠላት ማን ነው? የሚወረውስ የትኛውን “ምድር” ነው? ይህን “ምድር” የሚወረው መቼ፣ ለምንና እንዴት ነው? ወደፊት የሚፈጸሙት እነዚህ ክንውኖች ንጹሕ አምልኮን የምንደግፈውን ሰዎች በሙሉ በቀጥታ የሚመለከቱ በመሆናቸው የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ያስፈልገናል። በሕዝቅኤል ምዕራፍ 38 እና 39 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው አስደናቂ ትንቢት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

ጠላት የሆነው የማጎጉ ጎግ

3. ስለማጎጉ ጎግ የሚናገረውን የሕዝቅኤል ትንቢት ፍሬ ሐሳብ ግለጽ።

 3 ሕዝቅኤል 38:1, 2, 8, 18፤ 39:4, 11ን አንብብ። የትንቢቱ ፍሬ ሐሳብ የሚከተለው ነው፦ “በመጨረሻዎቹ ዓመታት” ‘የማጎጉ ጎግ’ የተባለ ጠላት የአምላክን ሕዝቦች “ምድር” ይወራል። ይሁን እንጂ ይህ ከባድ ጥቃት የይሖዋ “ታላቅ ቁጣ” እንዲነድ ስለሚያደርግ ይሖዋ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ በመውሰድ ጎግን ድል ያደርጋል። * ድል አድራጊው ይሖዋ፣ ድል የተመታውን ጠላቱንና ከእሱ ጎን የተሰለፉትን ሁሉ “ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች ሁሉና ለዱር አራዊት መብል” አድርጎ ይሰጣል። በመጨረሻም ይሖዋ ለጎግ “የመቃብር ቦታ” ይሰጠዋል። ይህ ትንቢት በቅርቡ እንዴት እንደሚፈጸም ለመረዳት በመጀመሪያ የጎግን ማንነት ማወቅ ያስፈልገናል።

4. የማጎጉን ጎግ በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?

4 ለመሆኑ የማጎጉ ጎግ ማን ነው? ሕዝቅኤል የሰጠው መግለጫ፣ ጎግ የንጹሕ አምልኮ ደጋፊዎች ጠላት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል። ታዲያ ጎግ የእውነተኛው አምልኮ ቀንደኛ ጠላት ለሆነው ለሰይጣን የተሰጠ ትንቢታዊ ስም ነው? ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ጽሑፎቻችን እንዲህ የሚል ማብራሪያ ሲሰጡ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ የተደረገው ተጨማሪ ምርምር በግንዛቤያችን ላይ ማስተካከያ እንድናደርግ አነሳስቶናል። መጠበቂያ ግንብ፣ የማጎጉ ጎግ የሚለው የማዕረግ ስም የሚያመለክተው የማይታይን መንፈሳዊ ፍጡር ሳይሆን በዓይን የሚታይን ሰብዓዊ ጠላት፣ ማለትም ከንጹሕ አምልኮ ጋር ለመዋጋት ግንባር የፈጠሩ ብሔራትን እንደሆነ ገልጾ ነበር። * እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉንን ምክንያቶች ከመከለሳችን በፊት ጎግ መንፈሳዊ ፍጡር አለመሆኑን የሚጠቁሙ በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ የሚገኙ ሁለት ፍንጮችን እንመርምር።

5, 6. በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ፣ የማጎጉ ጎግ መንፈሳዊ ፍጡር አለመሆኑን የሚያመለክት ምን መረጃ እናገኛለን?

5 “ለተለያዩ አዳኝ አሞሮች ሁሉ . . . መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ።” (ሕዝ. 39:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተጠቀሰው፣ አምላክ ለእስራኤላውያንም ሆነ እስራኤላውያን ላልሆኑ ብሔራት መለኮታዊ ፍርድ እንደሚመጣባቸው ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ሬሳቸው ለሰማይ ወፎች መብል እንደሚሆን ገልጿል። (ዘዳ. 28:26፤ ኤር. 7:33፤ ሕዝ. 29:3, 5) ይሁን እንጂ እነዚህ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎች የተሰጡት ለመንፈሳዊ ፍጥረታት ሳይሆን ሥጋ ለባሽ ለሆኑ ሰዎች መሆኑን ልብ በል። አዳኝ አሞሮችና የዱር አራዊትም ቢሆኑ የሚበሉት ሥጋ እንጂ መንፈስ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ስለዚህ በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ የሚገኘው ይህ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ጎግ መንፈሳዊ ፍጡር አለመሆኑን ያሳያል።

6 “በእስራኤል ምድር . . . ለጎግ የመቃብር ቦታ እሰጠዋለሁ።” (ሕዝ. 39:11) ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈሳዊ ፍጥረታት ምድር ላይ እንደሚቀበሩ አይናገሩም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣንና አጋንንቱ በጥልቁ ውስጥ ለ1,000 ዓመት ታስረው ከቆዩ በኋላ የዘላለም ጥፋትን ወደሚያመለክተው ምሳሌያዊ የእሳት ሐይቅ ይወረወራሉ። (ሉቃስ 8:31፤ ራእይ 20:1-3, 10) ጎግ ምድር ላይ “የመቃብር ቦታ” እንደሚሰጠው መገለጹ መንፈሳዊ ፍጡር አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል።

7, 8. ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ወደ ፍጻሜው የሚመጣው መቼ ነው? ይህስ በማጎጉ ጎግ ላይ ከሚደርሰው ነገር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

7 ንጹሕ አምልኮን በሚደግፉ ሰዎች ላይ የመጨረሻ ጥቃት የሚሰነዝረው ጎግ መንፈሳዊ ፍጡር ካልሆነ ታዲያ ምንድን ነው? የማጎጉን ጎግ ማንነት እንድንለይ የሚረዱ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እስቲ እንመልከት።

8 ‘የሰሜኑ ንጉሥ።’ (ዳንኤል 11:40-45ን አንብብ።) ዳንኤል ከእሱ ዘመን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ስለሚነሱ የተለያዩ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ተንብዮአል። በተጨማሪም ትንቢቱ ‘የሰሜን ንጉሥ’ እና ‘የደቡብ ንጉሥ’ በሚባሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ስለሚኖር ሽኩቻ ይጠቅሳል፤ ባለፉት በርካታ መቶ ዘመናት የተለያዩ ብሔራት የበላይነት ለመጨበጥ ባካሄዱት ትግል የእነዚህ ሁለት ጠላቶች ማንነት ሲለዋወጥ ቆይቷል። ዳንኤል የሰሜኑ ንጉሥ “በፍጻሜው ዘመን” የሚያደርገውን የመጨረሻ ዘመቻ አስመልክቶ ሲናገር “እሱም ለማጥፋትና ብዙዎችን ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል” ብሏል። የሰሜኑ ንጉሥ ዋነኛ የጥቃት ዒላማዎች የይሖዋ አምላኪዎች ናቸው። * ነገር ግን እንደ ማጎጉ ጎግ ሁሉ የሰሜኑ ንጉሥም በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት ከከሸፈበት በኋላ “ወደ ፍጻሜው ይመጣል።”

9. በማጎጉ ጎግ ላይ በሚደርሰው ነገርና ‘በዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ላይ በሚደርሰው ነገር መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

9 ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ።’ (ራእይ 16:14, 16፤ 17:14፤ 19:19, 20ን አንብብ።) የራእይ መጽሐፍ “የምድር ነገሥታት” “የነገሥታት ንጉሥ” በሆነው በኢየሱስ ላይ ስለሚሰነዝሩት ጥቃት ይተነብያል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚገኘው በሰማይ በመሆኑ በእሱ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት መሰንዘር አይችሉም፤ ስለዚህ በምድር ላይ በሚገኙት የመንግሥቱ ደጋፊዎች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ከዚያም የምድር ነገሥታት በአርማጌዶን ጦርነት ይሸነፋሉ። እነዚህ ነገሥታት ወደ ፍጻሜያቸው የሚመጡት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ መሆኑን ልብ በል። ይህ ሐሳብ የማጎጉን ጎግ በተመለከተ ከተነገረው ትንቢት ጋር ተመሳሳይ ነው። *

10. የማጎጉን ጎግ ማንነት በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?

10 እስካሁን ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር የጎግን ማንነት በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? አንደኛ፣ ጎግ መንፈሳዊ ፍጡር አይደለም። ሁለተኛ፣ ጎግ የሚያመለክተው በቅርቡ የአምላክን ሕዝቦች ለማጥቃት የሚነሱትን ብሔራት ነው። እነዚህ ብሔራት በሆነ መልኩ ግንባር እንደሚፈጥሩ ጥያቄ የለውም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የአምላክ ሕዝቦች የሚገኙት በመላው ምድር ስለሆነ ብሔራቱ እነሱን ለማጥቃት በዓላማም ሆነ በተግባር አንድ ሊሆኑ ይገባል። (ማቴ. 24:9) እርግጥ ነው፣ የዚህ ጥቃት ዋነኛ ጠንሳሽ ሰይጣን እንደሆነ አይካድም። ሰይጣን ላለፉት ረጅም ዘመናት፣ ብሔራት እውነተኛውን አምልኮ እንዲቃወሙ ሲያነሳሳቸው ቆይቷል። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:17) ይሁን እንጂ ስለማጎጉ ጎግ የሚናገረው የሕዝቅኤል ትንቢት የሚያተኩረው በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩት ብሔራት በሚኖራቸው ሚና ላይ ነው። *

“ምድር” የተባለው ምንድን ነው?

11. የሕዝቅኤል ትንቢት ጎግ የሚወረውን “ምድር” በተመለከተ ምን መግለጫ ይሰጣል?

11  በአንቀጽ 3 ላይ እንደተመለከትነው የማጎጉ ጎግ በይሖዋ ዓይን ውድ የሆነን “ምድር” በመውረር የይሖዋን ታላቅ ቁጣ ይቀሰቅሳል። ይህ “ምድር” ምንን ያመለክታል? እስቲ መለስ ብለን የሕዝቅኤልን ትንቢት እንመልከት። (ሕዝቅኤል 38:8-12ን አንብብ።) ትንቢቱ ጎግ “ከብሔራት ሁሉ መካከል ዳግመኛ የተሰበሰበውን” እና “የተመለሰውን ሕዝብ ምድር” እንደሚወር ይናገራል። በተጨማሪም ትንቢቱ በዚህ “ምድር” ላይ የሚኖሩትን የይሖዋ አምላኪዎች በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “ያለስጋት ተቀምጠዋል”፤ “የሚኖሩት ቅጥር፣ መቀርቀሪያና በር በሌላቸው ሰፈሮች ነው”፤ እንዲሁም “ሀብትና ንብረት” አከማችተዋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ አምላኪዎች የሚኖሩት እንዲህ ባለው “ምድር” ላይ ነው። የዚህን “ምድር” ምንነት ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12. በጥንት ዘመን በእስራኤል ምድር ንጹሕ አምልኮ መልሶ በተቋቋመበት ወቅት የትኛው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል?

12 የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ለበርካታ መቶ ዓመታት ይኖሩበት፣ ይሠሩበትና ያመልኩበት በነበረው በጥንቱ እስራኤል ንጹሕ አምልኮ መልሶ በተቋቋመበት ወቅት የተፈጸመውን ነገር መመልከታችን ጠቃሚ ይሆናል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ባጓደሉበት ወቅት ምድራቸው እንደምትጠፋና ባድማ እንደምትሆን በሕዝቅኤል በኩል ተንብዮ ነበር። (ሕዝ. 33:27-29) በተጨማሪም ይሖዋ ንስሐ የገቡ እስራኤላውያን ቀሪዎች ከባቢሎን ግዞት እንደሚመለሱና በምድሪቱ ላይ ንጹሕ አምልኮን መልሰው እንደሚያቋቁሙ ተንብዮአል። ያን ጊዜ ይሖዋ በእስራኤል ምድር ላይ በረከቱን ስለሚያፈስ ምድሪቱ ተለውጣ “እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ” ውብ ትሆናለች። (ሕዝ. 36:34-36) ይህ ትንቢት ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በትውልድ አገራቸው ንጹሕ አምልኮን መልሰው ለማቋቋም ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱበት ከ537 ዓ.ዓ. ጀምሮ ፍጻሜውን አግኝቷል።

13, 14. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩበት “ምድር” ምንድን ነው? (ለ) ይህ “ምድር” በይሖዋ ዓይን ውድ የሆነው ለምንድን ነው?

13 በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ንጹሕ አምልኮ መልሶ ሲቋቋም መመልከት ችለዋል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ እንደተመለከትነው፣ ለረጅም ዘመን በታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ሥር የቆዩት የአምላክ ሕዝቦች በ1919 ነፃ ወጥተዋል። በዚያ ዓመት ይሖዋ ሕዝቦቹን ወደ አንድ “ምድር” አምጥቷቸዋል። ይህ “ምድር” መንፈሳዊውን ገነት፣ ማለትም እውነተኛውን አምላክ የምናመልክበትን ከስጋት ነፃ የሆነና በመንፈሳዊ የበለጸገ ሁኔታ ወይም የእንቅስቃሴ ቀጠና ያመለክታል። በዚህ “ምድር” ላይ አእምሯችንና ልባችን ሰላም አግኝቶ ያለስጋት በአንድነት እንኖራለን። (ምሳሌ 1:33) የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን፤ እንዲሁም እውነተኛ እርካታ በሚያስገኘው የአምላክን መንግሥት የማወጁ ሥራ እንካፈላለን። በእርግጥም “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም” የሚለው ምሳሌ እውነት እንደሆነ መመልከት ችለናል። (ምሳሌ 10:22) በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንገኝ፣ ንጹሕ አምልኮን በቃልና በተግባር እስከደገፍን ድረስ የምንኖረው በዚህ “ምድር” ማለትም በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ነው።

14 ይህ መንፈሳዊ ገነት በይሖዋ ዓይን በጣም ውድ ነው። ለምን? ምክንያቱም የዚህ “ምድር” ነዋሪዎች ይሖዋ ወደ ንጹሕ አምልኮ የሳባቸው ‘በብሔራት ሁሉ መካከል ያሉ ውድ ነገሮች’ ናቸው። (ሐጌ 2:7 ግርጌ፤ ዮሐ. 6:44) እነዚህ ሰዎች ግሩም የሆኑትን የአምላክ ባሕርያት የሚያንጸባርቀውን አዲስ ስብዕና ለመልበስ ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 4:23, 24፤ 5:1, 2) ከንጹሕ አምልኮ ጎን የቆሙ እንደመሆናቸው መጠን አምላክን በሚያስከብርና ለእሱ ያላቸውን ፍቅር በሚያሳይ መንገድ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በቅዱስ አገልግሎት ይካፈላሉ። (ሮም 12:1, 2፤ 1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ መንፈሳዊውን ገነት ለማስዋብ የሚያደርጉትን ጥረት ሲመለከት ልቡ ምን ያህል በደስታ እንደሚሞላ መገመት እንችላለን። በሕይወትህ ውስጥ ለንጹሕ አምልኮ ቅድሚያ በመስጠት መንፈሳዊውን ገነት ማስዋብ ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት ትችላለህ፤ ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ምሳሌ 27:11

በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንገኝ፣ ንጹሕ አምልኮን እስከደገፍን ድረስ የምንኖረው በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ነው (አንቀጽ 13, 14⁠ን ተመልከት)

ጎግ ይህን “ምድር” የሚወረው መቼ፣ እንዴትና ለምንድን ነው?

15, 16. የማጎጉ ጎግ መንፈሳዊውን ገነት የሚወረው መቼ ነው?

15 ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በቅርቡ ውድ የሆነውን መንፈሳዊ ገነት የሚወሩ መሆኑን ስናስብ ፍርሃት ያድርብን ይሆናል። በትንቢት የተነገረው ይህ ጥቃት ከንጹሕ አምልኮ ጎን የቆምነውን ሰዎች በሙሉ በቀጥታ የሚመለከት በመሆኑ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ እንደምንፈልግ ጥያቄ የለውም። ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ሦስት ጥያቄዎችን እስቲ እንመልከት።

16 የማጎጉ ጎግ መንፈሳዊውን ገነት የሚወረው መቼ ነው? ትንቢቱ “በመጨረሻዎቹ ዓመታት . . . የተመለሰውን ሕዝብ ምድር ትወራለህ” ይላል። (ሕዝ. 38:8) ይህ ትንቢት ጎግ ይህን “ምድር” የሚወረው በዚህ ሥርዓት መጨረሻ አካባቢ እንደሆነ ይጠቁማል። ታላቁ መከራ የሚጀምረው በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ የምታመለክተው ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ እንደሆነ አስታውስ። የሐሰት ሃይማኖት ተቋማት ከጠፉ በኋላ እና አርማጌዶን ከመጀመሩ በፊት ጎግ ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በቆሙ ሰዎች ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መጠነ ሰፊ ጥቃት ይሰነዝራል።

17, 18. ይሖዋ በታላቁ መከራ ወቅት ሁኔታዎችን የሚያመቻቸው እንዴት ነው?

17 ጎግ ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡ ሰዎችን “ምድር” የሚወረው ለምንድን ነው? የሕዝቅኤል ትንቢት ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ ሁለት ነገሮችን ይገልጻል። አንደኛ፣ ይሖዋ ራሱ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጎግ የክፋት ዓላማውን ለመፈጸም ይነሳሳል።

18 ይሖዋ ራሱ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። (ሕዝቅኤል 38:4, 16ን አንብብ።) ይሖዋ ጎግን “በመንጋጋህም መንጠቆ አስገባለሁ” እንዲሁም “በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ” እንዳለው ልብ በል። ታዲያ ይህ ሐሳብ ይሖዋ ራሱ ብሔራት በአገልጋዮቹ ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ እንደሚያስገድዳቸው የሚጠቁም ነው? በፍጹም! ይሖዋ በምንም ዓይነት በሕዝቦቹ ላይ ክፉ ነገር አያመጣም! (ኢዮብ 34:12) ነገር ግን ይሖዋ ጠላቶቹ ከንጹሕ አምልኮ ጎን የቆሙ ሰዎችን እንደሚጠሉና እነሱን ጠራርጎ ለማጥፋት የሚያስችል አጋጣሚ ቢያገኙ ፈጽሞ ወደኋላ እንደማይሉ ያውቃል። (1 ዮሐ. 3:13) በመሆኑም ይሖዋ የተለያዩ ክንውኖች ከፈቃዱና ከፕሮግራሙ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲፈጸሙ ለማድረግ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ ይህም በጎግ መንጋጋ ውስጥ መንጠቆ አስገብቶ እንደመራው ሊቆጠር ይችላል። ታላቂቱ ባቢሎን ከጠፋች በኋላ ይሖዋ በሆነ መንገድ ብሔራት ቀድሞውንም በልባቸው ውስጥ የነበረውን ነገር ለመፈጸም እንዲነሳሱ ያደርጋል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ጎግ የመጨረሻ ጥቃቱን እንዲሰነዝር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤ ይህም በምድር ላይ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ጦርነት የሆነው አርማጌዶን እንዲጀምር ምክንያት ይሆናል። በዚህ ወቅት ይሖዋ ሕዝቡን ይታደጋል፤ ሉዓላዊነቱን ያስከብራል፤ እንዲሁም ስሙን ያስቀድሳል።—ሕዝ. 38:23

ብሔራት ንጹሕ አምልኮን ለመበዝበዝ የሚነሳሱት ንጹሕ አምልኮንም ሆነ የይሖዋን አምላኪዎች በሙሉ ስለሚጠሉ ነው

19. ጎግ ንጹሕ አምልኮን ለመበዝበዝ የሚነሳሳው ለምንድን ነው?

19 ጎግ የክፋት ዓላማውን ለመፈጸም ይነሳሳል። ግንባር የፈጠሩት ብሔራት “ክፉ ዕቅድ” ያወጣሉ። ለበርካታ ዘመናት በውስጣቸው ታምቆ የቆየውን ጥላቻ ለመግለጽና ንዴታቸውን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ለመወጣት ይነሳሳሉ፤ የይሖዋ ሕዝቦችም “ቅጥር፣ መቀርቀሪያና በር በሌላቸው ሰፈሮች” የሚኖሩ ያህል በቀላሉ ሊጠቁ የሚችሉ መስለው ይታያሉ። በተጨማሪም ብሔራቱ ‘ሀብትና ንብረት ያከማቹትን’ ሕዝቦች ‘ለመበዝበዝና ለመዝረፍ’ ይቋምጣሉ። (ሕዝ. 38:10-12) ይህ “ሀብት” ምንድን ነው? የይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ መንፈሳዊ ሀብት አላቸው፤ ከሁሉ የሚበልጠው ውድ ሀብታችን ለይሖዋ ብቻ የምናቀርበው ንጹሕ አምልኮ ነው። ብሔራት ንጹሕ አምልኮን ለመበዝበዝ የሚነሳሱት ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱት ሳይሆን ንጹሕ አምልኮንም ሆነ የይሖዋን አምላኪዎች በሙሉ ስለሚጠሉ ነው።

ጎግ ንጹሕ አምልኮን ለመደምሰስ “ክፉ ዕቅድ” ያወጣል፤ ሆኖም ዕቅዱ ይከሽፋል (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት)

20. ጎግ መንፈሳዊውን ገነት የሚወረው እንዴት ነው?

20 ጎግ መንፈሳዊውን ገነት የሚወረው እንዴት ነው? ግንባር የፈጠሩት ብሔራት ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን ለማወክና አምልኳችንን እንዳናከናውን ለማገድ ይሞክሩ ይሆናል። ለዚህም ሲሉ መንፈሳዊ ምግብ እንዳናገኝ፣ አብረን እንዳንሰበሰብና የአምላክን መልእክት በቅንዓት ማወጃችንን እንድናቆም ለማድረግ ብሎም አንድነታችንን ለማፍረስ ጥረት ያደርጉ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ የመንፈሳዊው ገነት የተለያዩ ገጽታዎች ናቸው። ብሔራት በሰይጣን አነሳሽነት የይሖዋን አምላኪዎችም ሆነ ንጹሕ አምልኮን ከምድር ገጽ ላይ ጠራርገው ለማጥፋት ይሞክራሉ።

21. ይሖዋ ከፊታችን የሚጠብቀንን ነገር አስቀድሞ ያሳወቀን መሆኑ አመስጋኝ እንድትሆን የሚያነሳሳህ ለምንድን ነው?

21 የማጎጉ ጎግ በቅርቡ የሚሰነዝረው ጥቃት አምላክ በሰጣቸው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የሚኖሩትን የይሖዋ አምላኪዎች በሙሉ ይነካል። ይሖዋ ከፊታችን የሚጠብቀንን ነገር አስቀድሞ ስላሳወቀን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ታላቁ መከራ እስኪመጣ ድረስ ግን ንጹሕ አምልኮን ለመደገፍና በሕይወታችን ውስጥ ለንጹሕ አምልኮ ቅድሚያ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይህን በማድረግ መንፈሳዊውን ገነት ለማስዋብ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። በተጨማሪም በቅርቡ ይሖዋ በአርማጌዶን ለሕዝቦቹና ለቅዱስ ስሙ በመቆም የሚወስደውን አስደናቂ እርምጃ በዓይናችን የማየት አጋጣሚ እናገኛለን። የሚቀጥለው ምዕራፍ ስለዚህ ጉዳይ የሚያብራራ ይሆናል።

^ አን.3 በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የይሖዋ ታላቅ ቁጣ በማጎጉ ጎግ ላይ የሚነደው መቼና እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህ ከንጹሕ አምልኮ ጎን ለቆሙ ሰዎች ምን ትርጉም እንደሚኖረው እንመለከታለን።

^ አን.4 በግንቦት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-30 ላይ የሚገኘውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።

^ አን.8 ዳንኤል 11:45 የሰሜኑ ንጉሥ ‘ንጉሣዊ ድንኳኖቹን በታላቁ ባሕር [ሜድትራንያን ባሕር] እና ቅዱስ በሆነው ውብ ተራራ [የአምላክ ቤተ መቅደስ ይገኝበት የነበረውና የአምላክ ሕዝቦች አምልኮ ያቀርቡበት የነበረው ቦታ] መካከል እንደሚተክል’ ይናገራል፤ ይህ ሐሳብ የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክ ሕዝቦችን የጥቃት ዒላማው እንደሚያደርግ ይጠቁማል።

^ አን.9 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናዊው “አሦራዊ” የአምላክን ሕዝቦች ጠራርጎ ለማጥፋት ስለሚሰነዝረው ጥቃት ይናገራል። (ሚክ. 5:5) በአምላክ ሕዝቦች ላይ እንደሚሰነዘሩ በትንቢት የተነገሩት አራቱ ጥቃቶች፣ ማለትም የማጎጉ ጎግ፣ የሰሜኑ ንጉሥ፣ የምድር ነገሥታትና አሦራዊው የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች አንድን ጥቃት የሚያመለክቱ የተለያዩ ስያሜዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

^ አን.10 በራእይ 20:7-9 ላይ የሚገኘው ‘ጎግና ማጎግ’ የሚለው አገላለጽ ማንን እንደሚያመለክት ለመረዳት ምዕራፍ 22⁠ን ተመልከት።