በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 20

‘ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ ተከፋፈሉ’

‘ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ ተከፋፈሉ’

ሕዝቅኤል 45:1

ፍሬ ሐሳብ፦ የምድሪቱ መከፋፈል ምን ትርጉም አለው?

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቅኤል ምን መመሪያ ሰጠው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?

ሕዝቅኤል አሁን ያየው ራእይ ከ900 ዓመት ገደማ በፊት ይኖሩ በነበሩት በሙሴና በኢያሱ ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንዲያስታውስ አድርጎት መሆን አለበት። በዚያ ወቅት ይሖዋ የተስፋይቱን ምድር ወሰኖች ለሙሴ የነገረው ሲሆን ቆየት ብሎ ደግሞ ምድሪቱ ለእስራኤል ነገዶች እንዴት መከፋፈል እንዳለባት ለኢያሱ ነግሮት ነበር። (ዘኁ. 34:1-15፤ ኢያሱ 13:7፤ 22:4, 9) አሁን ደግሞ በ593 ዓ.ዓ. ይሖዋ ሕዝቅኤልንና ግዞተኛ ወገኖቹን ተስፋይቱን ምድር ዳግመኛ ለእስራኤል ነገዶች እንዲያከፋፍሉ ነገራቸው።—ሕዝ. 45:1፤ 47:14፤ 48:29

2 ይህ ራእይ ለሕዝቅኤልና ለግዞተኛ ወገኖቹ ምን መልእክት ይዟል? ዛሬ ለሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦችስ የብርታት ምንጭ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ ራእይ ወደፊት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን?

አራት ዋስትናዎችን የያዘ ራእይ

3, 4. (ሀ) የሕዝቅኤል የመጨረሻ ራእይ ለግዞተኞቹ የትኞቹን አራት ዋስትናዎች ሰጥቷል? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኛውን ዋስትና እንመረምራለን?

3 ሕዝቅኤል ያየው የመጨረሻ ራእይ በመጽሐፉ የመጨረሻ ዘጠኝ ምዕራፎች ላይ ተገልጿል። (ሕዝ. 40:1 እስከ 48:35) ይህ ራእይ የእስራኤልን ብሔር መልሶ መቋቋም በተመለከተ የተነገሩ አራት አጽናኝ ዋስትናዎችን ይዟል። እነዚህ ዋስትናዎች ምንድን ናቸው? አንደኛ፣ ንጹሕ አምልኮ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ መልሶ ይቋቋማል። ሁለተኛ፣ ጻድቅ የሆኑ ካህናትና እረኞች ተመልሶ ለተቋቋመው ብሔር አመራር ይሰጣሉ። ሦስተኛ፣ ወደ እስራኤል የሚመለሱ ሁሉ ርስት ያገኛሉ። አራተኛ፣ ይሖዋ በድጋሚ ከእነሱ ጋር ይሆናል፤ አብሯቸውም ይኖራል።

4 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ ስለ መጀመሪያዎቹ ሁለት ዋስትናዎች፣ ማለትም ስለ እውነተኛው አምልኮ መልሶ መቋቋም እንዲሁም ጻድቅ የሆኑ እረኞች ስለሚሰጡት አመራር የሚገልጹት ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበት መንገድ ተብራርቷል። በዚህ ምዕራፍ ላይ፣ ምድሪቱ ርስት ሆና እንደምትከፋፈል በሚገልጸው በሦስተኛው ዋስትና ላይ ትኩረት እናደርጋለን። የሚቀጥለው ምዕራፍ ደግሞ ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር እንደሚሆን ስለሚገልጸው ተስፋ የሚያብራራ ይሆናል።—ሕዝ. 47:13-21፤ 48:1-7, 23-29

“ይህች ምድር ርስት ሆና ተሰጥታችኋለች”

5, 6. (ሀ) ለነገዶቹ የሚከፋፈለው ክልል የትኛው ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ስለ ርስት ክፍፍል የሚገልጸው ራእይ ዓላማ ምንድን ነው?

5 ሕዝቅኤል 47:14ን አንብብ። ይሖዋ በራእይ አማካኝነት ሕዝቅኤል ትኩረቱን “እንደ ኤደን የአትክልት ሥፍራ” በምትሆነው ምድር ላይ እንዲያሳርፍ አደረገ። (ሕዝ. 36:35) ከዚያም ይሖዋ “ለ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ርስት አድርጋችሁ የምታከፋፍሏት ክልል ይህች ናት” አለው። (ሕዝ. 47:13) ለነገዶቹ የሚከፋፈለው “ክልል” ግዞተኞቹ ተመልሰው የሚኖሩበት የእስራኤል ምድር ነው። ቀጥሎም በሕዝቅኤል 47:15-21 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ይሖዋ የምድሪቱን ውጫዊ ወሰኖች በዝርዝር ገለጸ።

6 ስለ ርስት ክፍፍል የሚገልጸው የዚህ ራእይ ዓላማ ምንድን ነው? የወሰኖቹ ልክ በዝርዝር መገለጹ ሕዝቅኤልና ግዞተኛ ወገኖቹ የሚወዷት አገራቸው ተመልሳ እንደምትቋቋም እርግጠኛ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ዝርዝር መግለጫ በመጠቀም የሰጣቸው ዋስትና ግዞተኞቹን ምን ያህል አስደስቷቸው እንደሚሆን መገመት እንችላለን። ታዲያ የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች በእርግጥ በምድሪቱ ላይ ርስት ተሰጥቷቸዋል? አዎ፣ ተሰጥቷቸዋል።

7. (ሀ) በ537 ዓ.ዓ. የትኛው ክንውን መፈጸም ጀመረ? ይህስ ምን ያስታውሰናል? (ለ) በመጀመሪያ የትኛውን ጥያቄ እንመለከታለን?

7 ሕዝቅኤል ራእዩን ካየ ከ56 ዓመት ገደማ በኋላ በ537 ዓ.ዓ. በሺዎች የሚቆጠሩ ግዞተኞች ወደ እስራኤል ምድር ተመልሰው ምድሪቱን መውረስ ጀመሩ። ጥንት የተፈጸመው ይህ አስደናቂ ክንውን በዘመናችን በአምላክ ሕዝቦች መካከል የተፈጸመውን ተመሳሳይ ክንውን ያስታውሰናል። በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ርስት ተሰጥቷቸዋል ሊባል ይችላል። እንዴት? ይሖዋ አገልጋዮቹ ወደ አንድ መንፈሳዊ “ምድር” እንዲገቡና ርስታቸው አድርገው እንዲወርሱት ፈቅዶላቸዋል። በመሆኑም በጥንት ዘመን የነበረችው ተስፋይቱ ምድር መልሳ እንደምትቋቋም የሚገልጸው ትንቢት፣ በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች የሚኖሩበት መንፈሳዊ “ምድር” መልሶ ስለተቋቋመበት ሁኔታ ጥሩ ትምህርት ይሰጠናል። ይሁን እንጂ የምናገኘውን ትምህርት ከመመርመራችን በፊት “በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ‘ምድር’ አለ የሚል መደምደሚያ ላይ የደረስነው ለምንድን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንሞክር።

8. (ሀ) ይሖዋ የሥጋዊ እስራኤላውያንን ብሔር በየትኛው ብሔር ተክቶታል? (ለ) መንፈሳዊው “ምድር” ወይም መንፈሳዊው ገነት ምንድን ነው? (ሐ) መንፈሳዊው ገነት ወደ ሕልውና የመጣው መቼ ነው? በዚያ የሚኖሩትስ እነማን ናቸው?

8 ይሖዋ ቀደም ሲል ለሕዝቅኤል ባሳየው ራእይ ላይ፣ እስራኤል መልሳ እንደምትቋቋም የሚናገሩት ትንቢቶች በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ‘አገልጋዩ ዳዊት’ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ በኋላ እንደሆነ አመልክቷል። (ሕዝ. 37:24) ይህ የሆነው በ1914 ዓ.ም. ነው። በዚህ ወቅት የሥጋዊ እስራኤላውያን ብሔር የአምላክ ሕዝብ መሆኑ ቀርቶ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ባቀፈው የመንፈሳዊ እስራኤል ብሔር ከተተካ ብዙ ዘመን አልፏል። (ማቴዎስ 21:43፤ 1 ጴጥሮስ 2:9ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ይሖዋ የሥጋዊ እስራኤላውያንን ብሔር በመንፈሳዊ ብሔር በመተካት ብቻ አልተወሰነም፤ ግዑዙን የእስራኤል አገርም በመንፈሳዊ “ምድር” ማለትም በመንፈሳዊው ገነት ተክቶታል። (ኢሳ. 66:8) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ላይ እንደተመለከትነው መንፈሳዊው ገነት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1919 ጀምሮ ይሖዋን ሲያመልኩ የቆዩበትን ከስጋት ነፃ የሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ ወይም የእንቅስቃሴ ቀጠና ያመለክታል። (“በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን 9ለን ተመልከት።) ከጊዜ በኋላ፣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ‘ሌሎች በጎችም’ በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር ጀምረዋል። (ዮሐ. 10:16) መንፈሳዊው ገነት በዛሬው ጊዜም በማደግና በመስፋፋት ላይ ቢሆንም ይህ ገነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ሙሉ በሙሉ ማጣጣም የሚቻለው ገና ከአርማጌዶን በኋላ ነው።

ምድሪቱን እኩል ማከፋፈል

9. ይሖዋ የምድሪቱን አከፋፈል በተመለከተ ምን ዝርዝር መመሪያ ሰጥቷል?

9 ሕዝቅኤል 48:1, 28ን አንብብ። ይሖዋ የምድሪቱን ወሰኖች ከገለጸ በኋላ ምድሪቱ መከፋፈል ያለባት እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ተናገረ። ይሖዋ ምድሪቱ ለዳን ነገድ ከተሰጠው ሰሜናዊ ወሰን አንስቶ ለጋድ ነገድ እስከተሰጠው ደቡባዊ ወሰን ድረስ ለ12ቱ ነገዶች እኩል ቦታ መከፋፈል እንዳለባት ገለጸ። አሥራ ሁለቱም ነገዶች በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው የምድሪቱ ምሥራቃዊ ወሰን አንስቶ በስተ ምዕራብ እስከሚገኘው ታላቁ ባሕር ወይም ሜድትራንያን ባሕር ድረስ ወደ ጎን የተዘረጋ ርስት ተሰጥቷቸዋል።—ሕዝ. 47:20

10. ይህ ራእይ ለግዞተኞቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል?

10 ይህ ራእይ ለግዞተኞቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል? ሕዝቅኤል ስለ ምድሪቱ አከፋፈል የሰጠው ዝርዝር መግለጫ፣ ግዞተኞቹ ምድሪቱን የማከፋፈሉ ሥራ በተደራጀ መንገድ እንደሚከናወን እርግጠኞች እንዲሆኑ አድርጓቸው መሆን አለበት። ከዚህም ሌላ ምድሪቱ ለ12ቱ ነገዶች በትክክል መከፋፈሏ ከግዞት የሚመለሱት እስራኤላውያን በሙሉ መልሶ በተቋቋመው ምድር ላይ ርስት ማግኘታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ያሳያል። ከግዞት ከሚመለሱት መካከል ቤት ወይም መሬት የማያገኝ ሰው አይኖርም።

11. ስለ ምድሪቱ መከፋፈል ከሚገልጸው ትንቢታዊ ራእይ ምን ትምህርት እናገኛለን? (“የምድሪቱ አከፋፈል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

11 ዛሬስ ከዚህ ራእይ ምን የሚያበረታታ ትምህርት እናገኛለን? ተመልሳ የተቋቋመችው ተስፋይቱ ምድር ለካህናቱ፣ ለሌዋውያኑና ለአለቆቹ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የ12ቱ ነገዶች አባላት የሚበቃ ቦታ ነበራት። (ሕዝ. 45:4, 5, 7, 8) ዛሬም በተመሳሳይ ቅቡዓን ቀሪዎችና ‘ከእጅግ ብዙ ሕዝብ’ መካከል አመራር የመስጠት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ብቻ ሳይሆኑ የቀሩት የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላትም በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ቦታ አላቸው። * (ራእይ 7:9) በድርጅቱ ውስጥ የምናበረክተው አስተዋጽኦ ምንም ያህል አነስተኛ ቢሆን፣ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የተረጋገጠ ቦታና ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው የሥራ ድርሻ አለን። ይህ እንዴት ያለ አስደሳች ዋስትና ነው!

በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለን ኃላፊነት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

ሁለት ጉልህ ልዩነቶች

12, 13. ይሖዋ ምድሪቱ ለ12ቱ ነገዶች የምትከፋፈልበትን መንገድ በተመለከተ ምን መመሪያ ሰጥቷል?

12 ይሖዋ የምድሪቱን አከፋፈል በተመለከተ ለሕዝቅኤል የሰጣቸው አንዳንድ መመሪያዎች ለሙሴ ከሰጣቸው መመሪያዎች የተለዩ በመሆናቸው ሕዝቅኤል ግራ ሳይጋባ አይቀርም። ከእነዚህ ልዩነቶች መካከል ሁለቱን እንመልከት። አንደኛው ከምድሪቱ አከፋፈል ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከምድሪቱ ነዋሪዎች ጋር የተያያዘ ነው።

13 አንደኛ፣ የምድሪቱ አከፋፈል። ሙሴ ብዙ ሕዝብ ላላቸው ነገዶች በዛ ያለ ርስት፣ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ላላቸው ነገዶች ደግሞ አነስ ያለ ርስት እንዲሰጥ ተነግሮት ነበር። (ዘኁ. 26:52-54) ሆኖም ሕዝቅኤል ባየው ራእይ ላይ፣ ይሖዋ ለሁሉም ነገዶች “እኩል ድርሻ [“እያንዳንዱም እንደ ወንድሙ” ግርጌ]” እንዲከፋፈል መመሪያ ሰጥቷል። (ሕዝ. 47:14) በመሆኑም የ12ቱም ነገዶች ርስት ከሰሜን ወሰኑ እስከ ደቡብ ወሰኑ ድረስ ያለው ርቀት እኩል መሆን ነበረበት። የየትኛውም ነገድ አባል የሆኑ እስራኤላውያን፣ ለምለም የሆነችው ተስፋይቱ ምድር ከምታስገኘው የተትረፈረፈ ምርት በእኩል መጠን ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።

14. ይሖዋ ስለ ባዕድ አገር ሰዎች ለሕዝቅኤል የሰጠው መመሪያ በሙሴ ሕግ ውስጥ ከተገለጸው የሚለየው በምን መንገድ ነው?

14 ሁለተኛ፣ የምድሪቱ ነዋሪዎች። የሙሴ ሕግ ለባዕድ አገር ሰዎች ጥበቃ ያደርግ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ አምልኮ እንዲካፈሉ ይፈቅድላቸው ነበር፤ ሆኖም የባዕድ አገር ሰዎች ርስት አያገኙም ነበር። (ዘሌ. 19:33, 34) ይሖዋ ለሕዝቅኤል የሰጠው መመሪያ ግን በሕጉ ውስጥ ከሰፈረው የተለየ ነበር። ይሖዋ “ከባዕድ አገር ለመጣው ሰው በሚኖርበት ነገድ ክልል ውስጥ ርስት ልትሰጡት ይገባል” የሚል መመሪያ ሰጥቷል። ይሖዋ በዚህ ትእዛዝ አማካኝነት ‘የአገሪቱ ተወላጆች በሆኑት እስራኤላውያን’ እና በምድሪቱ በሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎች መካከል የነበረውን መሠረታዊ ልዩነት አስወግዷል። (ሕዝ. 47:22, 23) ሕዝቅኤል በራእይ በተመለከታት ተመልሳ የተቋቋመች ምድር ውስጥ በነዋሪዎቹ መካከል እኩልነትና የአምልኮ አንድነት ሰፍኖ ነበር።—ዘሌ. 25:23

15. ይሖዋ ስለ ምድሪቱ አከፋፈልና ስለ ነዋሪዎቿ የሰጣቸው መመሪያዎች እሱን በተመለከተ የትኛውን የማይለወጥ እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ?

15 ይሖዋ የምድሪቱን አከፋፈልና ነዋሪዎቿን በተመለከተ የሰጣቸው እነዚህ ሁለት አስደናቂ መመሪያዎች ግዞተኞቹን አበረታተዋቸው መሆን አለበት። የእስራኤል ተወላጆችም ሆኑ ይሖዋን የሚያመልኩ የባዕድ አገር ሰዎች፣ ይሖዋ ለእያንዳንዳቸው እኩል ቦታ እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። (ዕዝራ 8:20፤ ነህ. 3:26፤ 7:6, 25፤ ኢሳ. 56:3, 8) በተጨማሪም እነዚህ መመሪያዎች የሚከተለውን አበረታች የሆነና የማይለወጥ እውነታ ጎላ አድርገው ያሳያሉ፦ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በእሱ ፊት በእኩል ደረጃ ውድ ናቸው። (ሐጌ 2:7ን አንብብ።) በዚህ ዘመን የምንኖር የይሖዋ አገልጋዮችም፣ ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ይህን እውነት ማወቃችን በጣም ያስደስተናል።

16, 17. (ሀ) የምድሪቱን አከፋፈልና ነዋሪዎቿን በተመለከተ የተሰጡትን ዝርዝር መግለጫዎች መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?

16 የምድሪቱን አከፋፈልና ነዋሪዎቿን በተመለከተ የተሰጡትን እነዚህን ዝርዝር መግለጫዎች መመርመራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ዋነኛ ገጽታ እኩልነትና አንድነት መሆን እንዳለበት ያስገነዝበናል። ይሖዋ አያዳላም። በመሆኑም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘አድልዎ ባለማድረግ የይሖዋን ባሕርይ አንጸባርቃለሁ? ዘራቸውም ሆነ የኑሮ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ለሁሉም የእምነት ባልንጀሮቼ ልባዊ አክብሮት አሳያለሁ?’ (ሮም 12:10) ይሖዋ በሙሉ ልባችን ቅዱስ አገልግሎት ከምናቀርብበትና የእሱን በረከቶች ከምናገኝበት መንፈሳዊ ገነት ሁላችንም በእኩል ደረጃ ተጠቃሚዎች እንድንሆን ስላስቻለን በጣም ደስተኞች ነን።—ገላ. 3:26-29፤ ራእይ 7:9

አድልዎ ባለማድረግና ለሌሎች ልባዊ አክብሮት በማሳየት የይሖዋን ባሕርይ እናንጸባርቃለን? (አንቀጽ 15, 16⁠ን ተመልከት)

17 አሁን ደግሞ ሕዝቅኤል ባየው የመጨረሻ ራእይ የመደምደሚያ ክፍል ላይ የምናገኘውን አራተኛ ዋስትና ይኸውም ይሖዋ ከግዞተኞቹ ጋር እንደሚሆን የሰጠውን ተስፋ እንመልከት። ከዚህ ተስፋ ምን ትምህርት እናገኛለን? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።

^ አን.11 ይሖዋ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ለካህናቱና ለአለቆቹ ስለሰጠው ልዩ ቦታና የሥራ ድርሻ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ምዕራፍ 14⁠ን ተመልከት።