በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 22

“ለአምላክ ስገድ”

“ለአምላክ ስገድ”

ራእይ 22:9

ፍሬ ሐሳብ፦ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ጭብጦች እንዲሁም እነዚህ ጭብጦች ለዘመናችንም ሆነ ለወደፊቱ ጊዜ ያላቸውን ትርጉም መከለስ

1, 2. (ሀ) በሁላችንም ፊት የተደቀነው ምርጫ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ታማኝ መልአክ ዮሐንስ ሊሰግድለት ሲል ምን ምላሽ ሰጠ?

እያንዳንዳችን ለአንድ ወሳኝ ጥያቄ መልስ መስጠት ይኖርብናል። ይህ ጥያቄ “የማመልከው ማንን ነው?” የሚል ነው። ብዙዎች ይህ ጥያቄ በጣም ውስብስብ እንደሆነ ብሎም ያሉት አማራጮች ግራ የሚያጋቡ እንደሆኑ ይሰማቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ያለው ምርጫ ግልጽና የማያሻማ ነው። ልናመልክ የምንችለው ወይ ይሖዋ አምላክን ነው፣ አሊያም ደግሞ ሰይጣንን ነው።

2 ሰይጣን ዲያብሎስ ለመመለክ ይቋምጣል። በተለይ ኢየሱስን በፈተነበት ወቅት ይህ ፍላጎቱ በግልጽ ታይቷል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንደተብራራው ሰይጣን ለኢየሱስ ከፍተኛ ሽልማት ይኸውም የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው ተናግሮ ነበር። ዲያብሎስ በምላሹ የፈለገው ነገር ምን ነበር? ‘አንድ ጊዜ ተደፍቶ እንዲያመልከው’ ኢየሱስን ጠይቆታል። (ማቴ. 4:9) በተቃራኒው ግን ለሐዋርያው ዮሐንስ ራእዩን ያደረሰው መልአክ ለመመለክ ፈቃደኛ አልነበረም። (ራእይ 22:8, 9ን አንብብ።) ዮሐንስ ለመልአኩ ሊሰግድለት በሞከረ ጊዜ ይህ ትሑት የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው!” ብሎታል። መልአኩ ‘እኔን አምልከኝ’ ከማለት ይልቅ “ለአምላክ ስገድ” ሲል ተናግሯል።

3. (ሀ) ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 እኛም ቁርጥ ውሳኔያችን መልአኩ እንደተናገረው ይሖዋ አምላክን ብቻ ማምለክ ነው። እስካሁን እንደተመለከትነው ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀበት ዓላማም ይህን ውሳኔያችንን ማጠናከር ነው። (ዘዳ. 10:20፤ ማቴ. 4:10) ንጹሕ አምልኮን በተመለከተ ከሕዝቅኤል ትንቢቶችና ራእዮች የተማርነውን ነገር እስቲ በአጭሩ እንከልስ። ከዚያም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም፣ በምድር ላይ ለሚኖረው ለእያንዳንዱ ግለሰብ የመጨረሻ ፈተና የሚቀርብበትን ጊዜ አሻግረን እንመለከታለን። ይህ ፈተና የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሙሉ በሙሉ መልሶ ሲቋቋም የማየት መብት የሚያገኘው ማን እንደሆነ የሚወሰንበት ይሆናል።

በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹ ሦስት ጭብጦች

4. የሕዝቅኤል መጽሐፍ ጎላ አድርጎ የሚገልጻቸው ሦስት ጭብጦች የትኞቹ ናቸው?

4 የሕዝቅኤል መጽሐፍ ንጹሕ አምልኮ በዘልማድ የአምልኮ ሥርዓት የመፈጸም ጉዳይ እንዳልሆነ ያስተምረናል። ንጹሕ አምልኮ (1) ይሖዋን ብቻ ማምለክን፣ (2) በአንድነት በንጹሕ አምልኮ መካፈልን እንዲሁም (3) ለሌሎች ፍቅር ማሳየትን ይጠይቃል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተብራሩት ትንቢቶችና ራእዮች እነዚህን ጭብጦች ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የመጀመሪያው ጭብጥ፦ ይሖዋን ብቻ ማምለክ

5-9. ይሖዋን ብቻ ማምለክን በተመለከተ ምን ትምህርት አግኝተናል?

5 ምዕራፍ 3 * ይሖዋ በቀስተ ደመና ተከቦ ኃያላን ከሆኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት በላይ እንደተቀመጠ የሚገልጸው አስደናቂ ራእይ የሚከተለውን መሠረታዊ እውነት ያረጋግጥልናል፦ ሊመለክ የሚገባው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ብቻ ነው።—ሕዝ. 1:4, 15-28

6 ምዕራፍ 5የይሖዋ ቤተ መቅደስ እንደረከሰ የሚያሳየውን ራእይ መመልከት በእርግጥም በጣም አስደንጋጭ ነበር! ይህ ራእይ ከይሖዋ የተሰወረ ምንም ነገር እንደሌለ ያሳያል። ይሖዋ ሕዝቦቹ ከሰው እይታ ተሰውረውም ቢሆን ጣዖት አምልኮን ጨምሮ የተለያዩ የክህደት ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ይመለከታል። እንደነዚህ ያሉት ድርጊቶች በእጅጉ ስለሚያሳዝኑት እንዲህ ያለ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሰዎች ይቀጣቸዋል።—ሕዝ. 8:1-18

7 ምዕራፍ 7እስራኤልን “በንቀት” በተመለከቱት አጎራባች ብሔራት ላይ የተነገሩት ፍርዶች ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ በደል የሚያደርሱ ሰዎችን ከተጠያቂነት ነፃ እንደማያደርጋቸው ያረጋግጣሉ። (ሕዝ. 25:6) ይሁን እንጂ እስራኤል ከእነዚህ ብሔራት ጋር ከነበራት ግንኙነት የምናገኘው ሌላም ትምህርት አለ፦ ከምንም ነገር በላይ ለይሖዋ ታማኝ መሆን ይኖርብናል። ከማያምኑ ዘመዶቻችን ጋር ለመመሳሰል ብለን ላቅ ካሉት የይሖዋ መሥፈርቶች ውልፍት አንልም፤ ሀብትን መታመኛችን አናደርግም ወይም ለይሖዋ ብቻ ታማኝ መሆን ሲገባን ሰብዓዊ መንግሥታትን በመደገፍ የገለልተኝነት አቋማችንን አናላላም።

8 ምዕራፍ 13 እና 14በትልቅ ተራራ ላይ ስለሚገኝ ቤተ መቅደስ የሚገልጸው ራእይ፣ ይሖዋ ከሌሎች አማልክት ሁሉ የበላይ መሆኑን በመገንዘብ ከፍ ካሉት የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር እንደሚገባን ያስተምረናል።—ሕዝ. 40:1 እስከ 48:35

9 ምዕራፍ 15እስራኤልንና ይሁዳን ከዝሙት አዳሪዎች ጋር የሚያወዳድሩት ትንቢታዊ መግለጫዎች፣ መንፈሳዊ ምንዝር በይሖዋ ፊት ምን ያህል አስጸያፊ እንደሆነ ያስታውሱናል።—ሕዝ. ምዕ. 16, 23

ሁለተኛው ጭብጥ፦ በአንድነት በንጹሕ አምልኮ መካፈል

10-14. በአንድነት በንጹሕ አምልኮ መካፈል እንዳለብን ጎላ ተደርጎ የተገለጸው እንዴት ነው?

10 ምዕራፍ 8ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንክብካቤ የሚያደርግ “አንድ እረኛ” እንደሚያስነሳ የሚገልጹት ትንቢቶች፣ በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነን በአንድነትና በሰላም መኖር እንደሚገባን ጎላ አድርገው ያሳያሉ።—ሕዝ. 34:23, 24፤ 37:24-28

11 ምዕራፍ 9የአምላክ ሕዝቦች ከባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተው ዳግመኛ በትውልድ አገራቸው እንደሚኖሩ የሚገልጹት የሕዝቅኤል ትንቢቶች በዛሬው ጊዜም ይሖዋን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሰዎች የያዙት መልእክት አለ። ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ማቅረብ የሚፈልጉ ሰዎች በካይ ከሆኑ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ነፃ መውጣትና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ንክኪ እንዳይኖራቸው መጠንቀቅ አለባቸው። ከተለያየ ሃይማኖት፣ የኑሮ ደረጃ ወይም ዘር የመጣን ብንሆንም የአምላክ ሕዝቦች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቀውን አንድነታችንን ጠብቀን መኖር ይገባናል።—ሕዝ. 11:17, 18፤ 12:24፤ ዮሐ. 17:20-23

12 ምዕራፍ 10የደረቁት አጥንቶች ሕያው እንደሆኑ የሚናገረው ራእይ ስለ አንድነት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በመንፈሳዊ ከነጹትና ተመልሰው ከተቋቋሙት እንዲሁም እንደ አንድ ሠራዊት በኅብረት ከሚሠሩት የይሖዋ አምላኪዎች መካከል መሆን መቻላችን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ሕዝ. 37:1-14

13 ምዕራፍ 12ሁለቱ በትሮች አንድ እንደሆኑ የሚገልጸው ትንቢትም አንድነትን ጎላ አድርጎ ያሳያል። ይህ ትንቢት በቅቡዓን ክርስቲያኖችና በሌሎች በጎች ላይ ፍጻሜውን ሲያገኝ መመልከት ምንኛ እምነት የሚያጠናክር ነው! ያለንበት ዓለም በሃይማኖታዊና በፖለቲካዊ ጥላቻ የተከፋፈለ ቢሆንም እኛ ግን በፍቅርና በታማኝነት ተሳስረን በአንድነት እንኖራለን።—ሕዝ. 37:15-23

14 ምዕራፍ 16የጸሐፊ የቀለም ቀንድ ስለያዘው ሰውና የማጥፊያ መሣሪያ ስለያዙት ሰዎች የሚገልጸው ራእይ ከባድ ማስጠንቀቂያ ይዟል፦ ለመዳን የሚያስችለው ምልክት የሚደረግባቸው ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ በፊት ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ሲያቀርቡ የነበሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።—ማቴ. 24:21፤ ሕዝ. 9:1-11

ሦስተኛው ጭብጥ፦ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት

15-18. ለሌሎች ፍቅር ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

15 ምዕራፍ 4ስለ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት የሚናገረው ራእይ ስለ ይሖዋ ባሕርያት አስተምሮናል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ዋነኛው ፍቅር ነው። ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን ፍቅር የሚንጸባረቅበት ከሆነ የይሖዋ አምላኪዎች መሆናችን በግልጽ ይታያል።—ሕዝ. 1:5-14፤ 1 ዮሐ. 4:8

16 ምዕራፍ 6 እና 11አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር እንደ ሕዝቅኤል ያሉ ጠባቂዎችን እንዲሾም አነሳስቶታል። አምላክ ፍቅር ስለሆነ፣ የሰይጣንን ሥርዓት በሚያጠፋበት ወቅት ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) እኛም በዘመናችን የሚገኘው ጠባቂ እያከናወነ ያለውን ሥራ በመደገፍ የአምላክን ፍቅር ማንጸባረቅ የምንችልበት አጋጣሚ ተከፍቶልናል።—ሕዝ. 33:1-9

17 ምዕራፍ 17 እና 18ይሖዋ ብዙ ሰዎች ምሕረቱን ለመቀበል እንቢተኛ እንደሚሆኑና ታማኝ አምላኪዎቹን ለማጥፋት እንደሚሞክሩ ያውቃል። ይሖዋ ለታማኝ ሕዝቦቹ ያለው ፍቅር ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ በእነሱ ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት ሕዝቦቹን እንዲታደግ ያነሳሳዋል። እኛም ለሌሎች ያለን ፍቅር፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚጨቁኑትን ሁሉ እንደሚያጠፋ የሚገልጸውን ማስጠንቀቂያ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች እንድናሰማ ይገፋፋናል።—ሕዝ. 38:1 እስከ 39:20፤ 2 ተሰ. 1:6, 7

18 ምዕራፍ 19, 20 እና 21ይሖዋ ለሰዎች ያለው ፍቅር፣ ሕይወት ሰጪ ስለሆነው ወንዝና ስለ ምድሪቱ አከፋፈል በሚገልጸው ራእይ ላይ በግልጽ ታይቷል። ይህ ራእይ፣ ከሁሉ የላቀው የይሖዋ የፍቅር መግለጫ ማለትም ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልንና የእሱ ቤተሰብ አባላት ሆነን ፍጹም ሕይወት እንድናገኝ ሲል ልጁን መስጠቱ ያስገኛቸውን ውጤቶች ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። እኛም ይሖዋ በልጁ ለሚያምኑ ሁሉ ስላዘጋጀው አስደናቂ የወደፊት ተስፋ በመናገር ለሰዎች ያለንን ፍቅር እናሳያለን።—ሕዝ. 45:1-7፤ 47:1 እስከ 48:35፤ ራእይ 21:1-4፤ 22:17

ከሺው ዓመት ግዛት በኋላ የሚፈጸም ትሕትና የሚንጸባረቅበት ድርጊት

19. ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ምን ያደርጋል? (“የመጨረሻው ፈተና” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

19 ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ‘ጠላት የሆነው ሞት’ ያስከተለውን ቁስል ይፈውሳል። (1 ቆሮ. 15:26፤ ማር. 5:38-42፤ ሥራ 24:15) የሰው ልጅ ታሪክ በሐዘንና በምሬት የተሞላ ነው። ሆኖም ኢየሱስ የሞቱትን ሰዎች ከሞት በማስነሳት አሳዛኝ የነበረውን ታሪክ ፍቆ እነዚህ ሰዎች የተሻለ ታሪክ የሚጽፉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕቱን መሠረት በማድረግ በሽታ፣ ጦርነትና ረሃብ ያስከተሉትን ጉዳት በሙሉ ይሽራል። ከዚህም በላይ የመከራችን ሁሉ መንስኤ የሆነውን ከአዳም የወረስነውን ኃጢአት ከሥር መሠረቱ ነቅሎ ያስወግድልናል። (ሮም 5:18, 19) ኢየሱስ “የዲያብሎስን ሥራ” ሙሉ በሙሉ ያፈርሳል። (1 ዮሐ. 3:8) ከዚያ በኋላስ ምን ይከናወናል?

ከሞት የሚነሱት ሰዎች የተሻለ ታሪክ የሚጽፉበት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል

20. ኢየሱስና 144,000ዎቹ አስደናቂ የሆነ ትሕትና የሚያሳዩት እንዴት ነው? አብራራ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

20 አንደኛ ቆሮንቶስ 15:24-28ን አንብብ። መላው የሰው ዘር ወደ ፍጽምና ደረጃ ከደረሰ እንዲሁም ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ባወጣው ዓላማ መሠረት ምድር ወደ ገነትነት ከተለወጠች በኋላ ኢየሱስና አብረውት የሚገዙት 144,000 ቅቡዓን መንግሥቱን ለይሖዋ መልሰው በማስረከብ አስደናቂ የሆነ ትሕትና ያሳያሉ። ለሺህ ዓመት የነበራቸውን ሥልጣን በፈቃደኝነትና በሰላም ያስረክባሉ። መንግሥቱ ያስገኛቸው በረከቶች በሙሉ ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።

የመጨረሻው ፈተና

21, 22. (ሀ) በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ዓለማችን ምን ዓይነት መልክ ይኖረዋል? (ለ) ይሖዋ ሰይጣንንና አጋንንቱን ከእስር የሚፈታቸው ለምንድን ነው?

21 ከዚያ በኋላ ይሖዋ በምድራዊ ተገዢዎቹ ላይ ያለውን ከፍተኛ እምነት የሚያሳይ አንድ አስደናቂ ነገር ይፈጽማል። ሰይጣንና አጋንንቱ ለሺህ ዓመት እስረኛ ሆነው ከቆዩበት ጥልቅ እንዲወጡ ያደርጋል። (ራእይ 20:1-3ን አንብብ።) በዚያ ወቅት የሚኖረው ዓለም፣ ሰይጣንና አጋንንቱ ወደ ጥልቁ ከመወርወራቸው በፊት ከነበረው ዓለም እጅግ የተለየ ይሆናል። ከአርማጌዶን በፊት አብዛኞቹ ሰዎች በሰይጣን ተታለው የነበረ ሲሆን የሰው ዘር በአድልዎና በጥላቻ ተከፋፍሎ ነበር። (ራእይ 12:9) በሺው ዓመት ፍጻሜ ግን መላው የሰው ዘር አንድነትና ፍቅር ያለው አንድ ቤተሰብ ሆኖ ይሖዋን ያመልካል። ምድር ሰላም የሰፈነባት ገነት ትሆናለች።

22 ታዲያ ይሖዋ እንደ ሰይጣንና አጋንንቱ ያሉትን ወንጀለኞች እንዲህ ወዳለው ከክፋት የጸዳ ዓለም የሚያመጣቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ለይሖዋ ያላቸው ታማኝነት ተፈትኖ አያውቅም። ብዙዎቹ ይሖዋን የማወቅ አጋጣሚ ከማግኘታቸው በፊት የሞቱና ትንሣኤ አግኝተው በገነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ሕይወት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን በሙሉ አሟልቶላቸዋል። ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ ገጥሟቸው አያውቅም። በዙሪያቸው ያሉ ሁሉ ይሖዋን የሚወዱና የሚያገለግሉ ሰዎች ናቸው። ሰይጣን እነዚህ ሰዎች አምላክን የሚያመልኩት እሱ ስለሚጠብቃቸውና ስለሚባርካቸው ብቻ ነው በማለት በኢዮብ ላይ ሰንዝሮ የነበረውን ዓይነት ክስ ሊሰነዝርባቸው ይችላል። (ኢዮብ 1:9, 10) ስለዚህ ይሖዋ ስማችንን በሕይወት መጽሐፍ ላይ በቋሚነት ከመጻፉ በፊት እሱን እንደ አባታችንና እንደ ሉዓላዊ ገዢያችን በመቀበል ከእሱ ጎን በታማኝነት እንደምንቆም የምናረጋግጥበት አጋጣሚ እንድናገኝ ያደርጋል።—ራእይ 20:12, 15

23. እያንዳንዱ ግለሰብ ምን ጥያቄ ሊደቀንበት ይችላል?

23 ሰይጣን፣ የሰው ልጆች አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ መፈተን እንዲችል አጭር ጊዜ ይሰጠዋል። ይህ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል? እያንዳንዱ ግለሰብ አዳምና ሔዋን ተደቅኖባቸው የነበረው ዓይነት ጥያቄ ሊደቀንበት ይችላል፤ የይሖዋን መሥፈርቶች ለመቀበል፣ አገዛዙን ለመደገፍና እሱን ለማምለክ አሊያም ደግሞ በአምላክ ላይ ዓምፆ ሰይጣንን ለመደገፍ መምረጥ ይኖርበታል።

24. በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ የሚያምፁት ሰዎች ‘ጎግና ማጎግ’ ተብለው የተጠሩት ለምንድን ነው?

24 ራእይ 20:7-10ን አንብብ። በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ የሚያምፁት ሰዎች ጎግና ማጎግ ተብለው መጠራታቸው ትኩረት የሚስብ ነው። እነዚህ ሰዎች፣ በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሱት ዓመፀኞች የሚያሳዩትን ዓይነት ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ተብሎ የተጠራው በታላቁ መከራ ወቅት ጥቃት የሚሰነዝረው ሠራዊት የይሖዋን አገዛዝ በሚቃወሙ ብሔራት የተከፋፈለ ነው። (ሕዝ. 38:2) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ላይ የሚያምፁት ሰዎችም በተመሳሳይ “ብሔራት” ተብለው ተጠርተዋል። ይህ አጠራር ትኩረት የሚስብ ነው። ለምን? ምክንያቱም በሺው ዓመት ግዛት ወቅት የትኛውም ዓይነት ብሔራዊ ክፍፍል ይወገዳል፤ ሁሉም ሰዎች የአንድ መንግሥት ማለትም የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ይሆናሉ። ሁላችንም የአንድ መንፈሳዊ ብሔር አባላት እንሆናለን። ትንቢቱ እነዚህን ዓመፀኞች ‘ጎግና ማጎግ’ እንዲሁም “ብሔራት” ብሎ መጥራቱ ሰይጣን በአንዳንድ የአምላክ ሕዝቦች መካከል ክፍፍል በመፍጠር ረገድ እንደሚሳካለት ያመለክታል። ማንኛውንም ሰው ከይሖዋም ሆነ ከሰይጣን ጎን እንዲሰለፍ የሚያስገድደው አይኖርም። እያንዳንዱ ፍጹም ሰው የራሱን ምርጫ ያደርጋል።

የሚያምፁት ሰዎች ጎግና ማጎግ ተብለው ተጠርተዋል (አንቀጽ 24⁠ን ተመልከት)

25, 26. ከሰይጣን ጋር የሚተባበሩት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ይሆናል? በመጨረሻስ ምን ይደርስባቸዋል?

25 ከሰይጣን ጋር የሚተባበሩት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሚያምፁት ሰዎች ቁጥር “በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” እንደሚሆን ይናገራል። ሆኖም ይህ ሲባል አብዛኞቹ ሰዎች ያምፃሉ ማለት አይደለም። ይህን እንዴት እናውቃለን? ይሖዋ ለአብርሃም ምን ተስፋ ሰጥቶት እንደነበር አስታውስ። ይሖዋ የአብርሃም ዘር “በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ” እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 22:17, 18) ሆኖም የአብርሃም ዘር ሆነው የተገኙት ቁጥራቸው 144,001 ነው። (ገላ. 3:16, 29) ይህ ከፍተኛ ቁጥር ቢሆንም ከጠቅላላው የሰው ዘር ብዛት ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። በተመሳሳይም ከሰይጣን ጋር የሚተባበሩት ሰዎች ብዛት ትንሽ ባይሆንም በጣም ብዙ የሚባል አይሆንም። ዓመፀኞቹ ሰዎች የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ አይችሉም።

26 በዓመፁ የሚተባበሩት ሁሉ ወዲያውኑ ተጠራርገው ይጠፋሉ። እንደ ሰይጣንና እንደ አጋንንቱ ሙሉ በሙሉ ከሕልውና ውጭ ይሆናሉ፤ ዳግመኛ ወደ ሕይወት የመመለስ ተስፋም አይኖራቸውም። እነዚህ ሰዎች ያደረጓቸው መጥፎ ውሳኔዎችና ውሳኔዎቹ ያስከተሏቸው ውጤቶች ብቻ ለዘላለም እየታወሱ ይኖራሉ።—ራእይ 20:10

27-29. የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉት ሰዎች ምን ተስፋ ይጠብቃቸዋል?

27 በሌላ በኩል ደግሞ የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉት ሰዎች ስማቸው “በሕይወት መጽሐፍ” ላይ በቋሚነት ይጻፋል። (ራእይ 20:15) ከዚያም ታማኝ የሆኑት የይሖዋ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው ለይሖዋ የሚገባውን አምልኮ ያቀርቡለታል።

28 ያ ጊዜ ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። እርካታ የሚያስገኝ ሥራ እንዲሁም ጥሩ ወዳጆች ይኖሩሃል። አንተም ሆንክ የምትወዳቸው ሰዎች ዳግመኛ መከራ አይደርስባችሁም። ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ስለምትሆን የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሳያስፈልግህ በይሖዋ ፊት መቆም ትችላለህ። ሁሉም ሰው ያለምንም ገደብ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይችላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ሁሉ ፍጹም በሆነ መንገድ ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ያቀርቡለታል። በዚያ ወቅት ንጹሕ አምልኮ ሙሉ በሙሉ መልሶ ይቋቋማል!

ፍጹም በምትሆንበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከኃጢአት ነፃ ስለምትሆን የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሳያስፈልግህ በይሖዋ ፊት መቆም ትችላለህ (አንቀጽ 28⁠ን ተመልከት)

29 አንተም በዚያ ተገኝተህ ይህን ታላቅ ቀን ማየት ትችል ይሆን? ከሕዝቅኤል መጽሐፍ ያገኘናቸውን ሦስት ቁልፍ ትምህርቶች ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ይኸውም ይሖዋን ብቻ የምታመልክ፣ በአንድነት በንጹሕ አምልኮ የምትካፈል እንዲሁም ለሌሎች ፍቅር የምታሳይ ከሆነ በዚያ ወቅት መገኘት ትችላለህ። ከሕዝቅኤል ትንቢት የምናገኘው አንድ የመጨረሻ ትምህርት አለ። ይህ ወሳኝ ትምህርት ምንድን ነው?

በሰማይና በምድር ያሉ ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡበት ጊዜ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን ለመገመት ሞክር (ከአንቀጽ 27-29⁠ን ተመልከት)

“እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ . . . ያውቃሉ”

30, 31. (ሀ) “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ . . . ያውቃሉ” የሚለው መግለጫ ለአምላክ ጠላቶች ምን ትርጉም አለው? (ለ) ይህ መግለጫ ለአምላክ ሕዝቦች ምን ትርጉም አለው?

30 “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ . . . ያውቃሉ” የሚለው መግለጫ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ እንደ አዝማች ይደጋገማል። (ሕዝ. 6:10፤ 39:28) ለአምላክ ጠላቶች፣ ይህ መግለጫ ጦርነት እንደሚታወጅባቸውና ጥፋት እንደሚደርስባቸው የሚያመለክት ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የይሖዋን መኖር አምኖ ከመቀበል ባለፈ ሌላም ነገር ለማወቅ ይገደዳሉ። የሚደርስባቸው ጥፋት፣ “እንዲሆን ያደርጋል” የሚለውን የይሖዋን ታላቅ ስም ትርጉም እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ’ “ኃያል ተዋጊ” በመሆን በእነሱ ላይ እርምጃ ይወስዳል። (1 ሳሙ. 17:45፤ ዘፀ. 15:3) ይሖዋ ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ የአምላክ ጠላቶች ዘግይተውም ቢሆን ይህን ወሳኝ እውነታ ለመገንዘብ ይገደዳሉ።

31 ለአምላክ ሕዝቦች ደግሞ “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ . . . ያውቃሉ” የሚለው መግለጫ ሰላምና ሕይወት እንደሚያገኙ የሚጠቁም ይሆናል። ይሖዋ፣ መጀመሪያ ላይ ባወጣው ዓላማ መሠረት የእሱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ የምናንጸባርቅ ልጆቹ እንድንሆን ያደርጋል። (ዘፍ. 1:26) አሁንም እንኳ ቢሆን ይሖዋ አፍቃሪ አባትና ተንከባካቢ እረኛ ሆኖልናል። በቅርቡ ደግሞ ድል አድራጊ ንጉሥ ይሆንልናል። ያ ቀን ከመምጣቱ በፊት የሕዝቅኤልን መልእክት ልብ እንበል። በእያንዳንዱ ቀን፣ ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን ይሖዋ ማን እንደሆነና ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እንደምናውቅ የሚያሳይ ይሁን። እንዲህ ካደረግን፣ ጥፋት የሚያመጡት የታላቁ መከራ ነፋሳት በሚለቀቁበት ጊዜ የምንፈራበት ምክንያት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ መዳናችን እንደቀረበ ስለምናውቅ ራሳችንን ቀና እናደርጋለን። (ሉቃስ 21:28) እስከዚያው ድረስ ግን በየትኛውም ቦታ ያሉ ሰዎች አምልኮ ሊቀርብለት የሚገባው ብቸኛ አምላክ የሆነውንና ከስሞች ሁሉ የላቀ ታላቅ ስም ያለውን ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።—ሕዝ. 28:26

^ አን.5 የምዕራፎቹ ቁጥሮች የሚያመለክቱት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ምዕራፎች ነው።