በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 19

“ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል”

“ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል”

ሕዝቅኤል 47:9

ፍሬ ሐሳብ፦ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ስለሚፈሰው ወንዝ የሚገልጸው ራእይ በጥንት ዘመንና በአሁኑ ጊዜ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ወደፊትስ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

1, 2. በሕዝቅኤል 47:1-12 ላይ እንደተገለጸው ሕዝቅኤል ምን ተመለከተ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ባየው ራእይ ላይ ሌላ አስደናቂ ነገር ተመለከተ፦ አንድ ጅረት ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ይፈስሳል። ሕዝቅኤል ይህን ኩልል ያለ ውኃ ተከትሎ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። (ሕዝቅኤል 47:1-12ን አንብብ።) ውኃው የሚመነጨው ከመቅደሱ ደፍ ሥር ነው፤ ከዚያም ቀስ ብሎ እየፈሰሰ በምሥራቁ በር አቅራቢያ ከቤተ መቅደሱ ግቢ ይወጣል። ሕዝቅኤልን የሚያስጎበኘው መልአክ ሕዝቅኤልን እየመራ ከቤተ መቅደሱ ውጭ ወሰደው፤ በሚሄዱበት ጊዜም ርቀቱን ይለካ ነበር። መልአኩ ሕዝቅኤልን በተደጋጋሚ በውኃው መካከል እንዲያልፍ አደረገው። ነቢዩም የውኃው ጥልቀት በፍጥነት እየጨመረ እንደሄደ አስተዋለ፤ ብዙም ሳይቆይ ውኃው በዋና ካልሆነ በስተቀር በእግር ሊሻገሩት የማይቻል ትልቅ ወንዝ ሆነ!

2 ሕዝቅኤል ወንዙ ወደ ሙት ባሕር እንደሚፈስ ተገነዘበ፤ የወንዙ ውኃ በደረሰበት ቦታ ሁሉ በሙት ባሕር ውስጥ ያለውን ሕይወት አልባና ጨዋማ የሆነ ውኃ በመፈወስ በዓሣዎች እንዲሞላ ያደርጋል። በወንዙ ዳርና ዳር ደግሞ ብዙ ዓይነት ዛፎች ይበቅላሉ። ዛፎቹ ለመብል የሚሆን አዲስ ፍሬ በየወሩ ይሰጣሉ፤ ቅጠላቸውም ለመድኃኒት ይሆናል። ሕዝቅኤል ይህን ሁሉ ሲመለከት ልቡ በሰላምና በተስፋ ተሞልቶ መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ይህ የራእዩ ገጽታ ለእሱና በግዞት ላይ ላሉ ወገኖቹ ምን መልእክት ይዟል? በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛስ ምን መልእክት ያስተላልፋል?

በራእይ የታየው ወንዝ ለግዞተኞቹ ምን መልእክት ይዟል?

3. የጥንቶቹ አይሁዳውያን በራእይ የታየው ወንዝ እውነተኛ ወንዝ ነው ብለው እንዳላሰቡ እንዴት እናውቃለን?

3 የጥንቶቹ አይሁዳውያን በራእይ የታየው ወንዝ እውነተኛ ወንዝ ነው ብለው እንዳላሰቡ ጥያቄ የለውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ራእይ ነቢዩ ኢዩኤል ሁለት መቶ ዓመታት ገደማ አስቀድሞ የጻፈውን፣ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም የሚገልጽ ሌላ ትንቢት አስታውሷቸው ይሆናል። (ኢዩኤል 3:18ን አንብብ።) ግዞተኞቹ አይሁዳውያን በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የኢዩኤል ትንቢት ሲያነቡ ተራሮቹ ቃል በቃል “ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ” ወይም “ኮረብቶቹ ወተት ያፈሳሉ” ብለው እንዳልጠበቁ የታወቀ ነው፤ ልክ እንደዚሁ “ከይሖዋም ቤት ምንጭ ይፈልቃል” ብለው አልጠበቁም። በተመሳሳይም እነዚህ አይሁዳውያን ነቢዩ ሕዝቅኤል ያየው ራእይ ስለ እውነተኛ ወንዝ የሚገልጽ እንዳልሆነ ሳይገነዘቡ አይቀሩም። * ታዲያ ይሖዋ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ምን ነበር? ቅዱሳን መጻሕፍት የዚህን ራእይ አንዳንድ ገጽታዎች ትርጉም እንድንረዳ የሚያስችሉ ፍንጮች ይሰጡናል። በጥቅሉ ሲታይ ግን ይህ ትንቢታዊ መግለጫ የይሖዋን ፍቅር የሚያሳዩ ሦስት ዋስትናዎች ይሰጠናል። እስቲ እነዚህን ዋስትናዎች እንመልከት።

4. (ሀ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ አይሁዳውያን የትኞቹን በረከቶች እንደሚያገኙ አረጋግጦላቸው መሆን አለበት? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ “ወንዝ” እና “ውኃ” የሚሉትን ቃላት የሚጠቀምበት መንገድ ይሖዋ ሕዝቦቹን እንደሚባርክ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው? (“የይሖዋን በረከት የሚያስገኙ ወንዞች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

4 በረከት የሚያስገኝ ወንዝ። አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወንዝና ውኃ፣ ሕይወት ሰጪ የሆኑት የይሖዋ በረከቶች መፍሰሳቸውን ለማመልከት እንደ ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ። ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ይፈስ ነበር፤ በመሆኑም ይህ ራእይ የአምላክ ሕዝቦች ከንጹሕ አምልኮ እስካልራቁ ድረስ ሕይወት ሰጪ የሆኑት የይሖዋ መንፈሳዊ በረከቶች ወደ እነሱ መፍሰሳቸውን እንደማያቆሙ አረጋግጦላቸው መሆን አለበት። እነዚህ በረከቶች ምን ነገሮችን ያካትታሉ? የአምላክ ሕዝቦች እንደ ቀድሞው ከካህናቱ መንፈሳዊ መመሪያ ያገኛሉ። በተጨማሪም በቤተ መቅደሱ ውስጥ መሥዋዕቶች ስለሚቀርቡ ኃጢአታቸው እንደሚሰረይላቸው መተማመን ይችላሉ። (ሕዝ. 44:15, 23፤ 45:17) በዚህ መንገድ ከቤተ መቅደሱ በሚወጣው ንጹሕ ውኃ የታጠቡ ያህል ዳግመኛ ንጹሕ ይሆናሉ።

5. በራእዩ ላይ የታየው ወንዝ ምንጊዜም ለሁሉም የሚበቃ በረከት እንደሚኖር የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

5 ይሁንና ምንጊዜም ለሁሉም የሚበቃ በረከት ይኖራል? ራእዩ፣ ቀስ እያለ የሚፈሰው ውኃ በአስደናቂ ሁኔታ እየጨመረ ሄዶ ሁለት ኪሎ ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ትልቅ ወንዝ እንደሚሆን ስለሚገልጽ በዚህ ረገድ የሚያሳስብ ነገር አይኖርም። (ሕዝ. 47:3-5) አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የሕዝቡ ቁጥር እያደገ ይሄድ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የይሖዋ በረከት እየጨመረ ስለሚሄድ የሁሉንም ፍላጎት ማሟላት ይችላል። በራእዩ ላይ የታየው ወንዝ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚኖር ያመለክታል።

6. (ሀ) ራእዩ ምን አጽናኝ ተስፋ ይዟል? (ለ) ራእዩ ምን ማስጠንቀቂያ ያስተላልፋል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

6 ሕይወት ሰጪ ውኃ። በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ወንዙ ወደ ሙት ባሕር ገብቶ አብዛኛውን የባሕሩን ክፍል እንደፈወሰው ተገልጿል። የሙት ባሕር ውኃ ተፈውሶ እንደ ታላቁ ባሕር ማለትም እንደ ሜድትራንያን ባሕር ብዙ ዓይነት ዓሣዎች የሚርመሰመሱበት ሆኗል። እንዲያውም በሙት ባሕር ዳርቻ “ከኤንገዲ እስከ ኤንዔግላይም ድረስ” ብዙዎች ዓሣ በማጥመድ ሥራ ተሰማርተዋል፤ እነዚህ ከተሞች ተራርቀው የሚገኙ ከተሞች ሳይሆኑ አይቀሩም። መልአኩ “ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት ይኖራል” ብሏል። ይህ ሲባል ታዲያ ከይሖዋ ቤት የወጣው ወንዝ ሙት ባሕርን ሙሉ በሙሉ ያዳርሳል ማለት ነው? አይደለም። መልአኩ ሕይወት ሰጪ የሆነው ውኃ የማይደርስባቸው ረግረጋማ የሆኑ አንዳንድ ቦታዎች እንዳሉ ገልጿል። እነዚህ ቦታዎች “ጨዋማ እንደሆኑ ይቀራሉ።” * (ሕዝ. 47:8-11) ራእዩ፣ ንጹሕ አምልኮ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ሕያው እንዲሆኑና ጥሩ ሕይወት እንዲመሩ እንደሚያስችላቸው የሚገልጽ አጽናኝ ተስፋ ይዟል። ይሁን እንጂ ራእዩ የሚያስተላልፈው ማስጠንቀቂያም አለ፦ የይሖዋን በረከት የሚቀበሉትም ሆነ ፈውስ የሚያገኙት ሁሉም አይደሉም።

7. በወንዙ ዳርና ዳር ስለበቀሉት ዛፎች የሚናገረው መግለጫ ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን ምን ዋስትና ሰጥቷቸዋል?

7 ለመብልና ለመድኃኒት የሚሆኑ ዛፎች። በወንዙ ዳርና ዳር ስላሉት ዛፎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ዛፎች ለራእዩ ውበት ከመስጠት ባለፈ የሚያስተላልፉት መልእክትም አለ። ሕዝቅኤልና ወገኖቹ እነዚህ ዛፎች በየወሩ ስለሚሰጡት ጣፋጭ ፍሬ ማሰባቸው ብቻ እንኳ እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። ይህ አስደሳች መግለጫ ይሖዋ በመንፈሳዊ እንደሚመግባቸው ተጨማሪ ዋስትና ሰጥቷቸዋል። ከዚህም ሌላ የዛፎቹ ቅጠል “ለመድኃኒት” እንደሚሆን ልብ በል። (ሕዝ. 47:12) ይሖዋ ከግዞት የሚመለሱት አይሁዳውያን ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ፈውስ እንደሆነ ያውቃል፤ በመሆኑም በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደሚፈውሳቸው ተስፋ ሰጥቷቸዋል። ይህ ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም በሚገልጹ ሌሎች ትንቢቶች ላይ ተብራርቷል፤ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ ይህን ሐሳብ ተመልክተን ነበር።

8. የሕዝቅኤል ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ የሚጠቁመው ምንድን ነው?

8 ይሁን እንጂ በምዕራፍ 9 ላይ እንደተብራራው እነዚህ ትንቢቶች ከግዞት ከተመለሱት አይሁዳውያን ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ውስን በሆነ መንገድ ብቻ ነው። እርግጥ ትንቢቶቹ ውስን በሆነ መንገድ የተፈጸሙት በሕዝቡ ምክንያት ነው። ሕዝቡ በተደጋጋሚ ወደ መጥፎ ጎዳናቸው ይመለሱ፣ በአምላክ ላይ ያምፁ እንዲሁም ንጹሕ አምልኮን ችላ ይሉ ስለነበር ይሖዋ እንዴት በተሟላ ሁኔታ ሊባርካቸው ይችላል? ታማኝ የሆኑት አይሁዳውያን የወገኖቻቸው ምግባር በጣም አሳዝኗቸው መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ታማኞቹ የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ የገባው ቃል በምንም ዓይነት ሳይፈጸም እንደማይቀር ያውቁ ነበር። (ኢያሱ 23:14ን አንብብ።) ስለዚህ የሕዝቅኤል ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ማግኘቱ አይቀርም። ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው?

ወንዙ በዛሬው ጊዜም እየፈሰሰ ነው!

9. ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው?

9 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ላይ እንደተመለከትነው ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ያየው ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው ንጹሕ አምልኮ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ከፍ ከፍ በሚልበት “በዘመኑ መጨረሻ” ነው። (ኢሳ. 2:2) ታዲያ ስለ ወንዙ የሚገልጸው የራእዩ ክፍል በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው በምን መንገድ ነው?

10, 11. (ሀ) በዛሬው ጊዜ እንደ ወንዝ እየፈሰሱልን ያሉት የትኞቹ በረከቶች ናቸው? (ለ) የይሖዋ በረከት ቁጥራቸው እያደገ የሄደውን ሰዎች ፍላጎት ማርካት በሚያስችል መጠን እየፈሰሰ ያለው እንዴት ነው?

10 በረከት የሚያስገኝ ወንዝ። ከይሖዋ ቤት ስለሚፈሰው ውኃ የሚገልጸው ዘገባ በዘመናችን የትኞቹን በረከቶች ያስታውሰናል? በመንፈሳዊ እንድንመገብና መንፈሳዊ ጤንነታችን እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ነገሮች በሙሉ ያስታውሰናል። ከእነዚህ መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው ለኃጢአታችን ይቅርታ እንድናገኝና እንድንነጻ የሚያስችለን የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ንጹሕ እውነትም ሕይወት ሰጪ በሆነና በሚያነጻ ውኃ ተመስሏል። (ኤፌ. 5:25-27) እነዚህ በረከቶች በዘመናችን የፈሰሱት እንዴት ነው?

11 በ1919 በጥቂት ሺዎች ብቻ የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች የነበሩ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት በመቻላቸው እጅግ ተደስተው ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ግን ቁጥራቸው በጣም ጨምሯል። በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ ሕዝቦች ቁጥራቸው ከስምንት ሚሊዮን ይበልጣል። ታዲያ ንጹሕ የሆነው የእውነት ውኃ የእነሱን ፍላጎት ማሟላት በሚያስችል መጠን እየፈሰሰ ነው? አዎ! መንፈሳዊ እውነት በተትረፈረፈ ሁኔታ እየቀረበልን ነው። ባለፈው መቶ ዘመን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጻሕፍት፣ ብሮሹሮችና ትራክቶች ተዘጋጅተዋል። ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ወንዝ መጠኑ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደሄደ ሁሉ ንጹሕ የሆነው የእውነት ውኃም በመላው ዓለም ቁጥራቸው እያደገ የሄደውን በመንፈሳዊ የተጠሙ ሰዎች ፍላጎት ማርካት በሚያስችል መጠን በብዛት እየፈሰሰ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ለበርካታ ዓመታት ሲታተሙ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ jw.org በተባለው ድረ ገጽ አማካኝነት መንፈሳዊ ትምህርት ከ900 በሚበልጡ ቋንቋዎች በመቅረብ ላይ ይገኛል። ይህ የእውነት ውኃ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ምን ጥቅም አስገኝቷል?

12. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሰዎችን የጠቀማቸው እንዴት ነው? (ለ) ራእዩ ምን ማስጠንቀቂያ ይዞልናል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

12 ሕይወት ሰጪ ውኃ። ሕዝቅኤል “ጅረቱ በሚፈስበት ቦታ ያለው ነገር ሁሉ በሕይወት” እንደሚኖር ተነግሮታል። የእውነት ውኃ ወደ መንፈሳዊው ገነት ለመጡ ሁሉ እንዴት እንደፈሰሰላቸው ለማሰብ ሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመንፈሳዊ ሁኔታ ሕያውና ጤናማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ይሁን እንጂ ራእዩ፣ ለዚህ እውነት ምላሽ መስጠታቸውን የሚቀጥሉት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ የሚያሳይ ማስጠንቀቂያም ይዟል። በሕዝቅኤል ራእይ ላይ በሙት ባሕር ውስጥ ወንዙ ያልፈወሳቸው ረግረጋማና ውኃ ያቆሩ ቦታዎች እንዳሉ ተገልጾ ነበር፤ ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች የሆነ ወቅት ላይ ልባቸው በመደንደኑ ለእውነት በጎ ምላሽ መስጠታቸውን አቁመዋል። * ይህ ሁኔታ ፈጽሞ እኛ ላይ እንዲደርስ አንፈልግም!—ዘዳግም 10:16-18ን አንብብ።

13. በወንዙ ዳርና ዳር ስለሚገኙት ዛፎች የሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ይዞልናል?

13 ለመብልና ለመድኃኒት የሚሆኑ ዛፎች። በወንዙ ዳርና ዳር ስለሚገኙት ዛፎች የሚገልጸው ዘገባ ምን የሚያበረታታ ትምህርት ይዞልናል? ዛፎቹ በየወሩ አዲስ ጣፋጭ ፍሬ እንደሚሰጡ፣ ቅጠላቸው ደግሞ ለመድኃኒት እንደሚሆን መገለጹን ልብ በል። (ሕዝ. 47:12) ይህም የምናገለግለው አምላክ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚሰጠንና ከሁሉ በላቀው መንገድ ማለትም በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደሚፈውሰን ያስታውሰናል። የምንኖርበት ዓለም በመንፈሳዊ ሁኔታ ረሃብተኛና ታማሚ ነው። በተቃራኒው ግን ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዴት እንደሚንከባከባቸው ለማሰብ ሞክር። በጽሑፎቻችን ላይ የወጣ አንድ ርዕስ አንብበህ ስትጨርስ፣ በትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ የመደምደሚያውን መዝሙር ስትዘምር አሊያም አንድ ቪዲዮ ወይም የብሮድካስት ፕሮግራም አይተህ ስታጠናቅቅ ባገኘኸው መንፈሳዊ ምግብ እጅግ እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። በእርግጥም ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። (ኢሳ. 65:13, 14) መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን በመንፈሳዊ ጤናማ እንድንሆን ይረዳናል። በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ምክር ማግኘታችን እንደ ፆታ ብልግና፣ ስግብግብነትና እምነት ማጣት ያሉትን ለመንፈሳዊነታችን ጠንቅ የሆኑ ነገሮች እንድንዋጋ ይረዳናል። በተጨማሪም ይሖዋ ከባድ ኃጢአት በመፈጸማቸው ምክንያት በመንፈሳዊ የታመሙ ክርስቲያኖች ከሕመማቸው እንዲያገግሙ ለመርዳት የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል። (ያዕቆብ 5:14ን አንብብ።) በእርግጥም ሕዝቅኤል ስለ ዛፎቹ ያየው ራእይ እንደሚያመለክተው በእጅጉ ተባርከናል።

14, 15. (ሀ) በወንዙ ስላልተፈወሱት ረግረጋማ ቦታዎች ከሚገልጸው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝ በዛሬው ጊዜ እየፈሰሰ ያለው በምን መንገድ ነው?

14 በወንዙ ስላልተፈወሱት ረግረጋማ ቦታዎች ከሚገልጸው ሐሳብም የምናገኘው ትምህርት አለ። የይሖዋን በረከት እንዳናገኝ እንቅፋት የሚሆን ነገር ፈጽሞ ማድረግ አንፈልግም። በመንፈሳዊ ሁኔታ ታማሚ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ እንዳሉት ብዙ ሰዎች ሳንፈወስ ብንቀር በጣም አሳዛኝ ይሆናል። (ማቴ. 13:15) በራእዩ ላይ ከተገለጸው በረከት የሚያስገኝ ወንዝ ተጠቃሚ በመሆናችን በእጅጉ ደስተኞች ነን። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ንጹሕ የእውነት ውኃ ስንጠጣ፣ በስብከቱ ሥራ አማካኝነት ይህን እውነት ለሌሎች ስናካፍል እንዲሁም ታማኙ ባሪያ ሥልጠና ከሰጣቸው ሽማግሌዎች ፍቅራዊ መመሪያ፣ ማጽናኛና እርዳታ ስናገኝ ሕዝቅኤል በራእይ ያየውን ሕይወት ሰጪና ፈዋሽ የሆነ ወንዝ ማስታወሳችን አይቀርም።

15 ስለ ወንዙ የሚገልጸው ራእይ ወደፊትስ ተጨማሪ ፍጻሜ ይኖረው ይሆን? እንዴታ! ቀጥለን እንደምንመለከተው ወንዙ በመጪው ገነት ውስጥ ከአሁኑ እጅግ በላቀ መጠን መፍሰሱን ይቀጥላል።

ራእዩ በገነት ውስጥ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

16, 17. ወንዙ በገነት ውስጥ ምን በረከቶችን ያስገኛል? ምሳሌ ስጥ።

16 በገነት ውስጥ በወዳጆችህና በቤተሰብህ ተከብበህ አስደሳች ሕይወት ስትመራ ይታይሃል? ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ወንዝ የሚገልጸውን ዘገባ መመርመርህ ይህ ተስፋ ይበልጥ እውን ሆኖ እንዲታይህ ይረዳሃል። እንዴት? የይሖዋን ፍቅር የሚያሳዩትን የራእዩን ሦስት ገጽታዎች እስቲ በድጋሚ እንመልከት።

17 በረከት የሚያስገኝ ወንዝ። ምሳሌያዊው ወንዝ በገነት ውስጥ ከአሁኑ እጅግ በላቀ መጠን ይፈስሳል፤ ምክንያቱም ወንዙ በገነት ውስጥ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊም ጥቅም ያስገኛል። በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የአምላክ መንግሥት፣ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከቤዛው ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እነዚህ ሰዎች ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ! በዚያ ወቅት በሽታ፣ ሐኪም፣ ነርስ፣ ሆስፒታል ወይም የጤና መድን የሚባል ነገር አይኖርም! “ታላቁን መከራ” በሕይወት አልፈው ወደ አዲሱ ዓለም ለሚገቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሕይወት ውኃ ይፈስላቸዋል። (ራእይ 7:9, 14) ይህ ወንዝ በአዲሱ ዓለም መጀመሪያ ላይ በከፍተኛ መጠን የሚፈስ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ከሚመጣው በረከት ጋር ሲነጻጸር ጭል ጭል እንደሚል ውኃ ሊቆጠር ይችላል። በሕዝቅኤል ራእይ ላይ እንደታየው፣ ይህ ወንዝ እየተስፋፋ ሄዶ ተጨማሪ በረከቶችን ያስገኛል።

በረከት የሚያስገኘው ወንዝ በገነት ውስጥ ሁሉም ሰው ወጣትና ጤናማ እንዲሆን ያደርጋል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

18. በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ወቅት “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ትልቅ ወንዝ የሚሆነው ከምን አንጻር ነው?

18 ሕይወት ሰጪ ውኃ። በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ወቅት “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ትልቅ ወንዝ ይሆናል። (ራእይ 22:1) በብዙ ሚሊዮኖች እንዲያውም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት ተነስተው በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ! ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት የሚያፈሰው በረከት፣ ለብዙ ዘመናት አፈር ለብሰው የቆዩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሙታን ዳግመኛ ሕያው እንዲሆኑ ማድረግን ይጨምራል። (ኢሳ. 26:19) ይሁን እንጂ ከሞት የሚነሱት ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ?

19. (ሀ) በገነት ውስጥ የሚገለጡ አዳዲስ መንፈሳዊ መመሪያዎች እንደሚኖሩ የሚያመለክተው ምንድን ነው? (ለ) አንዳንድ ሰዎች ‘ጨዋማ እንደሆኑ የሚቀሩት’ በምን መንገድ ነው?

19 እያንዳንዱ ሰው የራሱን ምርጫ ማድረግ ይኖርበታል። በዚያ ወቅት አዳዲስ የመጽሐፍ ጥቅልሎች ይከፈታሉ። ስለዚህ ከይሖዋ የሚመጣው አርኪ የሆነ ውኃ በዚያን ጊዜ የሚገለጡ እውነቶችን ይኸውም አዳዲስ መንፈሳዊ መመሪያዎችን የሚያካትት ይሆናል። ይህ ተስፋ እጅግ አስደሳች አይደለም? ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን መመሪያዎች ለመቀበል እምቢተኞች በመሆን በይሖዋ ላይ ያምፃሉ። በሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ወቅት የሚያምፁ ሰዎች የገነትን ሰላም እንዲያውኩ አይፈቀድላቸውም። (ኢሳ. 65:20) የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የተጠቀሱትን ‘ጨዋማ እንደሆኑ የሚቀሩ’ ረግረጋማ ቦታዎች ያስታውሰን ይሆናል። ውድ ከሆነው የሕይወት ውኃ ለመጠጣት አሻፈረን ማለታቸው እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! ከሺው ዓመት ግዛት በኋላም ከሰይጣን ጎን ተሰልፈው የሚያምፁ ሰዎች ይኖራሉ። ጻድቅ የሆነውን የይሖዋ አገዛዝ የማይቀበሉ ሁሉ የሚጠብቃቸው ዕጣ ዘላለማዊ ሞት ነው።—ራእይ 20:7-12

20. ሕዝቅኤል በራእይ ያያቸውን ዛፎች የሚያስታውሰን በሺው ዓመት ወቅት የሚኖረው የትኛው ዝግጅት ነው?

20 ለመብልና ለመድኃኒት የሚሆኑ ዛፎች። ይሖዋ በገነት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው የዘላለም ሕይወት እንዲያጣ አይፈልግም። በመሆኑም በሺው ዓመት ግዛት ወቅት፣ ይህን አጋጣሚ እንድናገኝ የሚያስችል ዝግጅት ያደርግልናል፤ ይህ ዝግጅት ሕዝቅኤል በራእይ ያያቸውን ዛፎች ያስታውሰናል። ይሁን እንጂ በገነት ውስጥ ከይሖዋ የምናገኘው በረከት መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ ጥቅሞችንም የሚያካትት ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስና አብረውት የሚገዙት 144,000 ቅቡዓን በሰማይ ለሺህ ዓመት ነገሥታት ሆነው ይገዛሉ። በተጨማሪም 144,000ዎቹ፣ ካህናት እንደመሆናቸው መጠን ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙና ወደ ፍጽምና ደረጃ እንዲደርሱ ይረዳሉ። (ራእይ 20:6) ሕዝቅኤል በወንዙ ዳርና ዳር ስላሉት ለመብል የሚሆን ፍሬ የሚያፈሩና ለመድኃኒት የሚሆን ቅጠል የሚያወጡ ዛፎች ያየው ራእይ ሐዋርያው ዮሐንስ ከመዘገበው ሌላ አስደናቂ ትንቢት ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። (ራእይ 22:1, 2ን አንብብ።) ዮሐንስ የተመለከታቸው ዛፎች “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” ቅጠሎች አሏቸው። በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታማኝ የሰው ልጆች 144,000ዎቹ ከሚሰጡት የክህነት አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

21. (ሀ) ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ወንዝ ስታሰላስል ምን ይሰማሃል? (“ቀስ እያለ የሚፈሰው ውኃ ትልቅ ወንዝ ሆነ!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?

21 ሕዝቅኤል በራእይ ስላየው ወንዝ ስታሰላስል ልብህ በሰላምና በተስፋ አይሞላም? በእርግጥም ከፊታችን እጅግ አስደሳች ጊዜ ይጠብቀናል! ይሖዋ በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናችን መሣል እንድንችል ሲል በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በርካታ ትንቢቶችን አስነግሯል። በተጨማሪም እነዚህ ትንቢቶች በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ማየት እንድንችል በትዕግሥት ግብዣ ሲያቀርብ ቆይቷል። ይሁንና ‘በእርግጥ በገነት ውስጥ መኖር እችል ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። የሕዝቅኤል ትንቢት የመጨረሻ ምዕራፎች ማረጋገጫ የሚሰጡን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

^ አን.3 በተጨማሪም ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ከትውልድ አገራቸው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ይህ ወንዝ እውነተኛ ወንዝ እንዳልሆነ ሳይገነዘቡ አይቀሩም፤ ምክንያቱም ወንዙ የሚፈሰው በትልቅ ተራራ ላይ ከሚገኝ ቤተ መቅደስ ተነስቶ ነው፤ ይህ ቤተ መቅደስ ደግሞ በተጠቀሰው ቦታ ላይ አይገኝም። ከዚህም ሌላ ራእዩ፣ ወንዙ ምንም ነገር ሳያግደው በቀጥታ ወደ ሙት ባሕር እንደፈሰሰ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ ይህም ቢሆን ከአካባቢው መልክዓ ምድር አንጻር ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም።

^ አን.6 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች፣ ይህ አገላለጽ አዎንታዊ ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ይናገራሉ፤ ምክንያቱም ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ለማድረግ የሚያገለግል ጨው ማምረት በሙት ባሕር አካባቢ ለረጅም ዘመን የቆየ አትራፊ ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ጥቅሱ “እነዚህ ቦታዎች አይፈወሱም” በማለት በቀጥታ እንደሚናገር ልብ በል። እነዚህ ቦታዎች ከይሖዋ ቤት የሚመነጨው ሕይወት ሰጪ ውኃ ስለማይደርስባቸው ሳይፈወሱ ሕይወት አልባ እንደሆኑ ይቀራሉ። ስለዚህ በዚህ ራእይ ላይ የተጠቀሱት ረግረጋማ ቦታዎች ጨዋማ ሆነው መቅረታቸው አሉታዊ የሆነ ትርጉም የሚያስተላልፍ ሳይሆን አይቀርም።—መዝ. 107:33, 34፤ ኤር. 17:6

^ አን.12 ኢየሱስ ስለ መረቡ የተናገረው ምሳሌም ተመሳሳይ መልእክት ይዟል። መረቡ ብዙ ዓሣዎችን ቢሰበስብም “ጥሩ” ሆነው የተገኙት ግን ሁሉም ዓሣዎች አይደሉም። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው መጥፎ መጥፎዎቹ ዓሣዎች ይጣላሉ። በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ድርጅት ከሚመጡት ሰዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት ከጊዜ በኋላ ታማኝነታቸውን ሊያጓድሉ እንደሚችሉ ገልጿል።—ማቴ. 13:47-50፤ 2 ጢሞ. 2:20, 21