በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበላይ አካሉ መልእክት

የበላይ አካሉ መልእክት

ውድ የይሖዋ ወዳጆች፦

ዓመቱ 1971 ነው። በዚያ ዓመት በተደረገው “መለኮታዊው ስም” የተባለ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሰዎች በስብሰባው ላይ በወጡት አዳዲስ ጽሑፎች በእጅጉ ተደንቀውና ተደስተው ነበር። የ1972 የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እነዚህ ጽሑፎች “ከሚጠበቀው በላይ አስደናቂ” እንደነበሩ ተናግሯል። አንድ ወንድም ከእነዚህ አዳዲስ ጽሑፎች ስለ አንዱ ሲናገር “የወደፊቱን ጊዜ የሚያመላክት እንዲህ ዓይነት ጽሑፍ አግኝተን አናውቅም” ብሎ ነበር። ይህ ወንድም የተናገረው ስለ የትኛው ጽሑፍ ነው? “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”—እንዴት? ስለተባለው መጽሐፍ ነው። ወንድሞች ይህን መጽሐፍ በማግኘታቸው የዚህን ያህል የተደሰቱት ለምን ነበር? መጽሐፉ ስለ ሰው ዘር የወደፊት ዕጣ የሚናገሩትን በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ትንቢቶች በተመለከተ ወቅታዊ የሆነ ማብራሪያ ይዞ ስለወጣ ነበር።

‘ይሖዋን ያውቃሉ’ የተባለው መጽሐፍ በወጣበት ወቅት 1.5 ሚሊዮን የነበረው የአምላክ ሕዝቦች ቁጥር በእጅጉ ጨምሮ አሁን ከ8 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። (ኢሳ. 60:22) እነዚህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች ከ900 የሚበልጡ የተለያዩ ቋንቋዎችን ይናገራሉ። (ዘካ. 8:23) ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል በመንፈስ መሪነት የተናገራቸውን ትንቢቶች በዝርዝር የማጥናት አጋጣሚ አግኝተው አያውቁም።

በተጨማሪም ከ1971 ወዲህ ባሉት አሥርተ ዓመታት ብርሃኑ ይበልጥ እየደመቀ በመሄዱ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በተመለከተ የነበረን ግንዛቤ እየጠራ መጥቷል። (ምሳሌ 4:18) ለምሳሌ፣ “ሌሎች በጎች” የአምላክ ወዳጆች በመሆን ጻድቅ ተደርገው የተቆጠሩት እንዴት እንደሆነ ማስተዋል የጀመርነው በ1985 ነው። (ዮሐ. 10:16፤ ሮም 5:18፤ ያዕ. 2:23) ከዚያም በ1995 ‘በጎቹና ፍየሎቹ’ የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጣቸው በመጪው “ታላቅ መከራ” ወቅት እንደሆነ አስተዋልን። (ማቴ. 24:21፤ 25:31, 32) እነዚህ ማስተካከያዎች ስለ ሕዝቅኤል ትንቢቶች በነበረን ግንዛቤ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

“የሰው ልጅ ሆይ፣ በደንብ ተመልከት፤ በጥሞና አዳምጥ፤ የማሳይህንም ሁሉ በትኩረት ተመልከት፤ እዚህ የመጣኸው ለዚህ ነውና።”​—ሕዝቅኤል 40:4

ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ብርሃኑ ይበልጥ እየደመቀ መሄዱን ቀጥሏል። ለምሳሌ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ያገኘናቸውን ትምህርቶች ለማስታወስ ሞክሩ። ስለ እነዚህ ትምህርቶች ያለን ግንዛቤ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የጠራ ሆኗል። ከእነዚህ ምሳሌዎች መካከል ብዙዎቹ በፍጥነት እየቀረበ ባለው ታላቅ መከራ ወቅት ስለሚፈጸሙ ክንውኖች የሚገልጹ ናቸው። በተጨማሪም በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ትንቢቶችን በተመለከተ የነበረን ግንዛቤ እየጠራ ሄዷል። ከእነዚህ መካከል ስለማጎጉ ጎግ (ምዕራፍ 38 እና 39)፣ የጸሐፊ የቀለም ቀንድ የያዘው ሰው ስለሚያከናውነው ሥራ (ምዕራፍ 9)፣ በደረቁ አጥንቶች ስለተሞላው ሸለቆ እንዲሁም ሁለቱ በትሮች አንድ ስለመሆናቸው (ምዕራፍ 37) የሚገልጹት ትንቢቶች ይገኙበታል። ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለን ግንዛቤ እየጠራ በመሄዱ ከበርካታ ዓመታት በፊት በተዘጋጀው ‘ይሖዋን ያውቃሉ’ በተባለው መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ ማስተካከል አስፈላጊ ሆኗል።

በመሆኑም ብዙዎቹ የይሖዋ አገልጋዮች “ስለ ሕዝቅኤል ትንቢቶች ወቅታዊ ማብራሪያ የሚሰጥ መጽሐፍ የምናገኘው መቼ ይሆን?” ብለው ሲጠይቁ መቆየታቸው የሚያስገርም አይደለም። የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ! የተባለው መጽሐፍ የተዘጋጀው ለዚህ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን 22 ምዕራፎች ስታነቡና ውብ በሆኑት ሥዕሎች ላይ ስታሰላስሉ መጽሐፉን ለማዘጋጀት በተደረገው ጥልቅ ምርምር መደነቃችሁ አይቀርም። ይሖዋ አስደናቂ የሆነውን የሕዝቅኤል መጽሐፍ ያስጻፈው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ጸሎት የታከለበት ጥልቅ ጥናት ተደርጓል። በተጨማሪም ለሚከተሉት ጥያቄዎች ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል፦ የሕዝቅኤል መጽሐፍ በሕዝቅኤል ዘመን ይኖሩ ለነበሩት ሰዎችም ሆነ በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛ ምን ትምህርት ያስተላልፋል? ወደፊት ስለሚፈጸሙ ክንውኖች የሚናገሩት ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ጥላነት ያላቸውን ነገሮች መፈለግ ይኖርብናል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይህን ግሩም መጽሐፍ በተመለከተ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የጠራ ግንዛቤ እንድናገኝ አስችሎናል።

የሕዝቅኤልን መጽሐፍ ከዳር እስከ ዳር ስታነቡ በይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል በእጅጉ መደነቃችሁ አይቀርም። በተጨማሪም ይሖዋ እሱን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ ለሚፈልጉ በሰማይም ሆነ በምድር የሚኖሩ ፍጥረታት ያወጣው መሥፈርት ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ስትገነዘቡ በጣም እንደምትገረሙ ጥርጥር የለውም። ንጹሕ አምልኮ የተባለው መጽሐፍ፣ ይሖዋ እስካሁን ድረስ ለሕዝቦቹ ያደረገላቸውን እንዲሁም በቅርቡ የሚያደርግላቸውን ነገር በተመለከተ ያላችሁ አድናቆት እንዲጨምር ይረዳችኋል። ይህ መጽሐፍ ሁለት ጭብጦችን ጎላ አድርጎ እንደሚገልጽ ማስተዋላችሁ አይቀርም። አንደኛ፣ ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን እሱን ማወቅና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን አምነን መቀበል ይኖርብናል። ሁለተኛ፣ ይሖዋን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ እንዲሁም ከፍ ካሉት መሥፈርቶቹ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን መምራት ይገባናል።

ይህ መጽሐፍ የይሖዋን ታላቅና ቅዱስ ስም በሚያስከብር መንገድ እሱን ለማምለክ ያደረጋችሁትን ቁርጥ ውሳኔ እንዲያጠናክርላችሁ ልባዊ ምኞታችን ነው። በተጨማሪም ብሔራት ሁሉ ይሖዋን የሚያውቁበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቃችሁን እንድትቀጥሉ ይረዳችሁ ዘንድ እንመኛለን።—ሕዝ. 36:23፤ 38:23

አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ፣ ሕዝቅኤልን በመንፈሱ በመምራት ያስጻፈውን መጽሐፍ ለመረዳት የምታደርጉትን ጥረት አብዝቶ ይባርክላችሁ።

ወንድሞቻችሁ፣

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል