በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

“አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ”

“አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ”

ሕዝቅኤል 11:19

ፍሬ ሐሳብ፦ ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገረው ጭብጥና ይህ ጭብጥ በሕዝቅኤል ትንቢቶች ውስጥ የተገለጸበት መንገድ

1-3. ባቢሎናውያን በይሖዋ አምላኪዎች ላይ ምን እያሉ ያፌዙባቸው ነበር? ለምንስ?

በባቢሎን ከተማ የምትኖር ታማኝ አይሁዳዊ ነህ እንበል። የአገርህ ሰዎች የግዞት ኑሮ መግፋት ከጀመሩ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ሆኗቸዋል። እንደ ልማድህ በሰንበት ቀን ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ይሖዋን ለማምለክ እየሄድክ ነው። ትርምስ በበዛባቸው የከተማዋ ጎዳናዎች ስታልፍ ለቁጥር የሚያታክቱ ታላላቅ ቤተ መቅደሶችና የጸሎት ቦታዎች ትመለከታለህ። በርካታ ሰዎች ወደ እነዚህ ስፍራዎች በመጉረፍ እንደ ማርዱክ ላሉ አማልክት መሥዋዕት ያቀርባሉ እንዲሁም መዝሙር ይዘምራሉ።

2 ይህን ሁሉ አልፈህ፣ ገለል ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ ጥቂት ከሆኑ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ተገናኘህ። * ከዚያም አብራችሁ ለመጸለይ፣ ለመዘመርና በአምላክ ቃል ላይ ለመወያየት የሚያስችል ጸጥ ያለ ቦታ በከተማዋ የውኃ መውረጃ ቦዮች አጠገብ አገኛችሁ። አብራችሁ በምትጸልዩበት ጊዜ በውኃ መውረጃ ቦዮቹ ዳርቻ ላይ የታሰሩት የእንጨት ጀልባዎች የሚፈጥሩት ሲጥ ሲጥ የሚል ድምፅ ይሰማል። በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰላማዊ የሆነ ቦታ በማግኘታችሁ ደስ ብሏችኋል። የአካባቢው ሰዎች እንዳያገኟችሁና እንደለመዱት ስብሰባችሁን እንዳይረብሹት ትመኛላችሁ። የሚረብሿችሁ ለምንድን ነው?

3 ባቢሎን ለረጅም ዘመናት በርካታ ጦርነቶችን ስታሸንፍ ኖራለች። ባቢሎናውያን ከተማቸው ይህን ያህል ጠንካራ ልትሆን የቻለችው በሐሰት አማልክታቸው እርዳታ እንደሆነ ያምናሉ። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌም ሙሉ በሙሉ መውደሟ አምላካቸው ማርዱክ ከይሖዋ የበለጠ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በመሆኑም በአምላካችሁና በሕዝቦቹ ላይ ይዘባበታሉ። አንዳንድ ጊዜ ‘እስቲ ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ዘምሩልን’ እያሉ ያፌዙባችኋል። (መዝ. 137:3) ብዙዎቹ መዝሙሮች ጽዮን በይሖዋ ጠላቶች ላይ ስለተቀዳጀቻቸው ድሎች የሚገልጹ ናቸው። ባቢሎናውያኑ በተለይ በእነዚህ መዝሙሮች ማፌዝ ሳያስደስታቸው አይቀርም። ሌሎቹ መዝሙሮች ደግሞ ስለ ራሳቸው ስለ ባቢሎናውያን የሚናገሩ ናቸው። ለምሳሌ አንዱ መዝሙር “ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር አድርገዋታል። . . . በዙሪያችን ያሉትም ያፌዙብናል፤ ደግሞም ይዘብቱብናል” ይላል።—መዝ. 79:1, 3, 4

4, 5. የሕዝቅኤል ትንቢት ምን ተስፋ ይሰጣል? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመረምራለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በይሖዋና በነቢያቱ ላይ እምነት በማሳደርህ ምክንያት የሚያፌዙብህ ከሃዲ አይሁዳውያን አሉ። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ይህ ሁሉ ስድብና ፌዝ ቢደርስባችሁም በንጹሕ አምልኮ መካፈላችሁ ያጽናናችኋል። ከአምላክ ሕዝቦች ጋር አብራችሁ ስትጸልዩና ስትዘምሩ ደስ ይላችኋል። የአምላክን ቃል ማንበባችሁም ያበረታታችኋል። (መዝ. 94:19፤ ሮም 15:4) ዛሬ ደግሞ ከእምነት ባልንጀሮችህ አንዱ ለየት ያለ ነገር ማለትም የሕዝቅኤል ትንቢት የሚገኝበትን ጥቅልል ይዞ መጥቷል። ይሖዋ ሕዝቦቹን ወደ አገራቸው እንደሚመልስ የሚገልጸውን ተስፋ መስማት ያስደስትሃል። እንዲህ ያለው ትንቢት ከፍ ባለ ድምፅ ሲነበብ ስትሰማ ልብህ በደስታ ይሞላል፤ አንድ ቀን አንተና ቤተሰብህ ወደ አገራችሁ ተመልሳችሁ በዚህ አስደሳች የመልሶ ማቋቋም ሥራ ስትካፈሉ ይታይሃል።

5 ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገረው ተስፋ በሕዝቅኤል ትንቢት ውስጥ በተደጋጋሚ ተገልጿል። እስቲ ተስፋ ሰጪ የሆነውን ይህን ርዕሰ ጉዳይ እንመርምር። በግዞት በነበሩት አይሁዳውያን ዘመን እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነበር? በዘመናችንስ ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው? በተጨማሪም አንዳንዶቹ ተስፋዎች ወደፊት የመጨረሻ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

“ተማርከው በግዞት ይወሰዳሉ”

6. አምላክ ዓመፀኛ የሆኑ ሕዝቦቹን በተደጋጋሚ ያስጠነቀቀው እንዴት ነው?

6 ይሖዋ ሕዝቦቹ የዓመፅ ጎዳና በመከተላቸው የተነሳ እንዴት እንደሚቀጣቸው በሕዝቅኤል በኩል በግልጽ ነግሯቸዋል። “ተማርከው በግዞት ይወሰዳሉ” ብሎ ነበር። (ሕዝ. 12:11) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ላይ እንደተመለከትነው ሕዝቅኤል ይህን ፍርድ በድራማ መልክ ጭምር አሳይቶ ነበር። ሆኖም ይህን ማስጠንቀቂያ የተናገረው የመጀመሪያው ሰው ሕዝቅኤል አልነበረም። ይሖዋ ሕዝቦቹ በዓመፀኛ አካሄዳቸው ከቀጠሉ በግዞት እንደሚወሰዱ ከሙሴ ዘመን ማለትም ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት አንስቶ አስጠንቅቋቸዋል። (ዘዳ. 28:36, 37) እንደ ኢሳይያስና ኤርምያስ ያሉት ነቢያትም ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ያስተላልፉ ነበር።—ኢሳ. 39:5-7፤ ኤር. 20:3-6

7. ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ቅጣት ያመጣው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

7 የሚያሳዝነው ግን እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች በአብዛኛው ሰሚ ጆሮ አላገኙም። ይሖዋ ሕዝቦቹ በመጥፎ እረኞች ተጽዕኖ ሥር ሆነው በሚፈጽሙት ዓመፅ፣ ጣዖት አምልኮና ክህደት ምክንያት ልቡ በጣም አዘነ። እንዲህ ላለ የሥነ ምግባር ውድቀት በመዳረጋቸው የተነሳ ይሖዋ በረሃብ እንዲሠቃዩ ፈቀደ። የተሰጠቻቸው ምድር ‘ወተትና ማር የምታፈስ’ ሆና ሳለ ለረሃብ መዳረጋቸው በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነበር። (ሕዝ. 20:6, 7) ከዚያም ይሖዋ፣ ከብዙ ዓመታት በፊት እንደተነበየው ዓመፀኛ የሆኑት ሕዝቦቹ በግዞት እንዲቀጡ ፈቀደ። በ607 ዓ.ዓ. ደግሞ የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን በማውደም የመጨረሻውን የቅጣት እርምጃ ወሰደ። ከጥፋቱ የተረፉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን ተማርከው ተወሰዱ። በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተገለጸው ዓይነት ፌዝና ተቃውሞ የደረሰባቸው በዚያ ወቅት ነበር።

8, 9. አምላክ ክህደትን በተመለከተ ለክርስቲያን ጉባኤ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር?

8 የክርስቲያን ጉባኤስ ከባቢሎን ግዞት ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? አዎ። እንደ ጥንቶቹ አይሁዳውያን ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮችም አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። ኢየሱስ ገና አገልግሎቱን እንደጀመረ አካባቢ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 7:15) ከዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ እንደሚከተለው በማለት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ ተኩላዎች በመካከላችሁ እንደሚገቡና መንጋውን በርኅራኄ እንደማይዙ አውቃለሁ፤ ከእናንተ መካከል እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር የሚናገሩ ሰዎች ይነሳሉ።”—ሥራ 20:29, 30

9 ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉትን አደገኛ ሰዎች መለየትና ከእነሱ መራቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተምረዋል። ክርስቲያን ሽማግሌዎችም ከሃዲዎችን ከጉባኤው እንዲያስወግዱ መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። (1 ጢሞ. 1:19፤ 2 ጢሞ. 2:16-19፤ 2 ጴጥ. 2:1-3፤ 2 ዮሐ. 10) ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች እንደ ጥንቶቹ እስራኤላውያን የተሰጣቸውን ፍቅራዊ ማስጠንቀቂያ መስማት አቆሙ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ክህደት በጉባኤው ውስጥ ሥር ሰዶ ነበር። እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ድረስ በሕይወት የቆየው የመጨረሻው ሐዋርያ የሆነው ዮሐንስ፣ ጉባኤው እንደተበከለና በውስጡ ዓመፅ እንደተስፋፋ አስተውሎ ነበር። ይህ የክፋት አካሄድ ይበልጥ እንዳይስፋፋ አግዶት የነበረው ብቸኛ ነገር የእሱ መኖር ነበር። (2 ተሰ. 2:6-8፤ 1 ዮሐ. 2:18) ታዲያ ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ምን ተከሰተ?

10, 11. ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ጀምሮ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

10 ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ ፍጻሜውን ማግኘት ጀመረ። (ማቴዎስ 13:24-30ን አንብብ።) ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ሰይጣን በጉባኤው ውስጥ “እንክርዳድ” ወይም አስመሳይ ክርስቲያኖችን ዘራ፤ ይህም ጉባኤው ከቀድሞው በበለጠ ፍጥነት እንዲበከል አደረገ። ይሖዋ፣ ልጁ ያቋቋመው ጉባኤ በጣዖት አምልኮ፣ በአረማዊ በዓላትና ልማዶች እንዲሁም ከአምላክ የለሽ ፈላስፎችና ከሰይጣናዊ ሃይማኖቶች በተወሰዱ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶች ተበክሎ ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? በከሃዲዋ እስራኤል ላይ እንዳደረገው ሁሉ ሕዝቡ በግዞት እንዲወሰድ ፈቀደ። ከሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ፣ በስንዴ የተመሰሉት እውነተኛ ክርስቲያኖች በአስመሳይ ክርስቲያኖች ተዋጡ። በወቅቱ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በምትወክለው በታላቂቱ ባቢሎን በምርኮ የተያዘ ያህል ሆኖ ነበር፤ አስመሳይ ክርስቲያኖች ደግሞ ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ተቀላቀሉ። አስመሳይ ክርስቲያኖች እየተስፋፉ ሲሄዱ ሕዝበ ክርስትና ወደ ሕልውና መጣች።

11 ሕዝበ ክርስትና እንደ ልቧ በፈነጨችባቸው የጨለማ ዘመናት ሁሉ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ በጠቀሰው “ስንዴ” የተመሰሉ የተወሰኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች ነበሩ። በሕዝቅኤል 6:9 ላይ እንደተገለጹት አይሁዳውያን ግዞተኞች ሁሉ እነዚህ ክርስቲያኖችም እውነተኛውን አምላክ አስታውሰዋል። አንዳንዶቹ፣ የሕዝበ ክርስትናን የሐሰት መሠረተ ትምህርቶች በድፍረት ተቃውመዋል። በዚህም ምክንያት ለፌዝና ለስደት ተዳርገዋል። ታዲያ ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዲህ ባለው መንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እስከ ወዲያኛው ይተዋቸው ይሆን? በፍጹም! በጥንቷ እስራኤል እንደሆነው ሁሉ የይሖዋ ቁጣ የተገለጸው በተገቢው መጠንና ለተገቢው ጊዜ ያህል ነበር። (ኤር. 46:28) በተጨማሪም ይሖዋ ሕዝቡን ያለተስፋ አልተዋቸውም። በጥንቷ ባቢሎን በግዞት ይኖሩ ወደነበሩት አይሁዳውያን መለስ እንበልና ይሖዋ የግዞት ዘመናቸው እንደሚያበቃ ተስፋ የሰጣቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

እውነተኛ ክርስቲያኖች ለበርካታ መቶ ዘመናት ታላቂቱ ባቢሎን የምታደርስባቸውን ስደት መቋቋም አስፈልጓቸዋል (አንቀጽ 10, 11⁠ን ተመልከት)

“ቁጣዬ ይፈጸማል”

12, 13. ይሖዋ በሕዝቅኤል ዘመን በነበሩት ግዞተኛ ሕዝቦቹ ላይ የተሰማው ቁጣ ከጊዜ በኋላ የበረደው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ በሕዝቡ ላይ የተሰማውን ቁጣ ከመግለጽ ወደኋላ አላለም፤ ይሁን እንጂ የጽድቅ ቁጣው ለዘላለም እንደማይቀጥልም አረጋግጦላቸዋል። ለምሳሌ የሚከተሉትን ቃላት ልብ በል፦ “ቁጣዬ ይፈጸማል፤ በእነሱም ላይ የነደደው ቁጣዬ ይበርዳል፤ እኔም እረካለሁ። በእነሱም ላይ ቁጣዬን ፈጽሜ ባወረድኩ ጊዜ፣ እኔ ብቻ መመለክ የምፈልገው፣ እኔ ይሖዋ ይህን እንደተናገርኩ ያውቃሉ።” (ሕዝ. 5:13) ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ቁጣ የሚበርደው ለምንድን ነው?

13 ከግዞተኞቹ መካከል ከሃዲ ከሆኑ ወገኖቻቸው ጋር አብረው የተጋዙ ታማኝ አይሁዳውያንም ይገኙበታል። በተጨማሪም አምላክ ከሕዝቦቹ መካከል አንዳንዶቹ በግዞት ላይ እያሉ ንስሐ እንደሚገቡ በሕዝቅኤል በኩል ተንብዮአል። ንስሐ የገቡት አይሁዳውያን በአምላክ ላይ በማመፅ የፈጸሟቸውን አሳፋሪ ድርጊቶች አስታውሰው ይሖዋ ይቅር እንዲላቸውና ሞገሱን እንዲያሳያቸው ይማጸኑታል። (ሕዝ. 6:8-10፤ 12:16) በግዞት ከተወሰዱት ታማኝ አይሁዳውያን መካከል ሕዝቅኤል እንዲሁም ነቢዩ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ይገኙበታል። እንዲያውም ዳንኤል የግዞት ዘመኑን መጀመሪያና ፍጻሜ ተመልክቷል። ዳንኤል ስለ እስራኤል ኃጢአት ያቀረበው ልባዊ የንስሐ ጸሎት በዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። የእሱ ስሜት፣ ይሖዋ ይቅር እንዲላቸውና በረከቱን መልሶ እንዲያፈስላቸው የሚናፍቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ግዞተኞችን ስሜት የሚያንጸባርቅ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ግዞተኞች ሕዝቅኤል በመንፈስ ተመርቶ የተናገራቸውን ስለ ነፃነትና መልሶ ስለ መቋቋም የሚገልጹ ተስፋዎች ሲሰሙ በጣም ተደስተው መሆን አለበት!

14. ይሖዋ ሕዝቦቹን ወደ ትውልድ አገራቸው የመለሳቸው ለምንድን ነው?

14 ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቦቹን ነፃ እንዲያወጣና መልሶ እንዲያቋቁም ያነሳሳው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ምክንያት አለ። ለረጅም ዓመታት የዘለቀው ግዞት የሚያበቃው አይሁዳውያን ነፃ መውጣት የሚገባቸው ሆነው ስለተገኙ ሳይሆን ይሖዋ በብሔራት ሁሉ ፊት ስሙን ዳግመኛ የሚቀድስበት ጊዜ ስለደረሰ ነው። (ሕዝ. 36:22) እነዚያ ባቢሎናውያን፣ ማርዱክን ጨምሮ የሚያመልኳቸው ክፉ አማልክት በሙሉ ከሉዓላዊው ጌታ ከይሖዋ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማወቅ ይገደዳሉ! ይሖዋ ሕዝቅኤልን በመንፈሱ በመምራት ለግዞተኛ ወገኖቹ እንዲናገር ያደረጋቸውን አምስት ተስፋዎች እስቲ እንመርምር። በመጀመሪያ እያንዳንዱ ተስፋ ከእነዚህ ታማኝ አይሁዳውያን ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነ እናያለን። ከዚያም እነዚህ ተስፋዎች በላቀ መንገድ ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

15. ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን ከሃይማኖታዊ ልማዶች ጋር በተያያዘ ምን ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸዋል?

15 የመጀመሪያው ተስፋ። ጣዖት አምልኮም ሆነ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች አስጸያፊ ልማዶች ይወገዳሉ። (ሕዝቅኤል 11:18፤ 12:24ን አንብብ።) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ላይ እንደተብራራው ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ እንደ ጣዖት አምልኮ ባሉ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ተበክለው ነበር። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ተበላሽቶና ከይሖዋ ርቆ ነበር። ይሖዋ በሕዝቅኤል በኩል ግዞተኞቹ ዳግመኛ ንጹሕ በሆነና ባልረከሰ አምልኮ የሚካፈሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ተንብዮአል። ስለ አምላክ ሕዝቦች መልሶ መቋቋም ከሚገልጸው ትንቢት ውስጥ ቁልፍ ቦታ የሚይዘው የንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋም ነው፤ ምክንያቱም ሌሎቹ በረከቶች በሙሉ ፍጻሜያቸውን ሊያገኙ የሚችሉት ንጹሕ አምልኮ መልሶ ከተቋቋመ ብቻ ነው።

16. ይሖዋ የሕዝቦቹን የትውልድ አገር በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቷል?

16 ሁለተኛው ተስፋ። ግዞተኞቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ይመለሳሉ። ይሖዋ ለግዞተኞቹ “የእስራኤልንም ምድር እሰጣችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ሕዝ. 11:17) ይህ አስደናቂ ተስፋ ነበር፤ ምክንያቱም ግዞተኞቹ የአምላክ ሕዝቦች፣ ይሳለቁባቸው በነበሩት ባቢሎናውያን ቁጥጥር ሥር እስከሆኑ ድረስ ወደ አገራቸው ሊመለሱ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ተስፋ አልነበራቸውም። (ኢሳ. 14:4, 17) አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ታማኝነታቸውን ጠብቀው እስከኖሩ ድረስ ምድሪቱ ለምና ፍሬያማ ትሆንላቸዋለች፤ እንዲሁም ለሕዝቡ ምግብና መተዳደሪያ የማቅረብ አቅም ይኖራታል። ረሃብ የሚያስከትለው ጉስቁልናና ውርደት ያለፈ ታሪክ ይሆናል።—ሕዝቅኤል 36:30ን አንብብ።

17. ለይሖዋ ከሚቀርቡ መሥዋዕቶች ጋር በተያያዘ የተሰጠው ተስፋ ምን ነበር?

17 ሦስተኛው ተስፋ። በይሖዋ መሠዊያ ላይ እንደ ቀድሞው መባ ይቀርባል። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተገለጸው በሙሴ ሕግ ሥር መሥዋዕትና መባ ማቅረብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የንጹሕ አምልኮ ክፍል ነበር። ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን ታዛዦች እስከሆኑና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን እስከጠበቁ ድረስ የሚያቀርቡት መባ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል። በመሆኑም ሕዝቡ ለኃጢአታቸው ስርየት ማግኘትና ከአምላካቸው ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት ይችሉ ነበር። ይሖዋ “መላው የእስራኤል ቤት ሰዎች፣ አዎ ሁሉም በዚያ በምድሪቱ ላይ ያገለግሉኛልና። በዚያም በእነሱ ደስ እሰኛለሁ፤ ደግሞም ቅዱስ ከሆኑት ነገሮቻችሁ ሁሉ መዋጮዎቻችሁንና የመባችሁን የፍሬ በኩራት እሻለሁ” ሲል ቃል ገብቶላቸዋል። (ሕዝ. 20:40) በዚያ ጊዜ ንጹሕ አምልኮ መልሶ የሚቋቋም ሲሆን ይህም ለአምላክ ሕዝቦች በረከት ያስገኛል።

18. ይሖዋ በጎቹን የሚንከባከበው እንዴት ነው?

18 አራተኛው ተስፋ። ክፉ እረኞች ይወገዳሉ። የአምላክ ሕዝቦች ከትክክለኛው ጎዳና ይህን ያህል ርቀው እንዲሄዱ ካደረጓቸው ነገሮች ዋነኛው ምግባረ ብልሹ የሆኑት መሪዎቻቸው ያሳደሩባቸው ተጽዕኖ ነበር። ይሖዋ ይህን እንደሚለውጥ ቃል ገብቷል። እነዚህን ክፉ እረኞች በተመለከተ “በጎቼን እንዳያሰማሩም እከለክላቸዋለሁ፤ . . . በጎቼን ከአፋቸው አስጥላለሁ” ሲል ተናግሯል። ለታማኝ ሕዝቦቹ ደግሞ “በጎቼን እንከባከባለሁ” በማለት ዋስትና ሰጥቷቸዋል። (ሕዝ. 34:10, 12) ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ታማኝ የሆኑ ወንዶችን እረኛ አድርጎ በመሾም ነው።

19. ይሖዋ አንድነትን በተመለከተ ምን ተስፋ ሰጥቷል?

19 አምስተኛው ተስፋ። በይሖዋ አምላኪዎች መካከል አንድነት ይኖራል። የግዞት ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት በአምላክ ሕዝቦች መካከል የነበረው መከፋፈል ታማኝ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችን ምን ያህል አሳዝኗቸው ሊሆን እንደሚችል አስብ። ሕዝቡ ሐሰተኛ ነቢያትና ምግባረ ብልሹ የሆኑ እረኞች ባሳደሩባቸው ተጽዕኖ ምክንያት ይሖዋን ይወክሉ በነበሩ ታማኝ ነቢያት ላይ ዓምፀዋል፤ እንዲያውም በየወገኑ ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው መጋጨት ጀምረው ነበር። በመሆኑም ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገረው ተስፋ ያለው አንዱ ማራኪ ገጽታ “አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ አኖራለሁ” የሚለው ነው። (ሕዝ. 11:19) ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን ከይሖዋ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ያላቸውን አንድነት እስከጠበቁ ድረስ የትኛውም ተቃዋሚ ድል ሊነሳቸው አይችልም። ይሖዋን ከማሰደብ ይልቅ በብሔር ደረጃ በድጋሚ ለእሱ ክብር ማምጣት ይችላሉ።

20, 21. አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ከግዞት በተመለሱት አይሁዳውያን ላይ የተፈጸሙት እንዴት ነው?

20 ከግዞት የተመለሱት አይሁዳውያን እነዚህ አምስት ተስፋዎች ሲፈጸሙ ተመልክተዋል? በጥንት ዘመን የኖረው ታማኙ ኢያሱ የተናገራቸውን ቃላት ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። “አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም እንዳልቀረች በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ። ሁሉም ተፈጽሞላችኋል። ከመካከላቸው ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም” ብሎ ነበር። (ኢያሱ 23:14) በኢያሱ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱት ግዞተኞች ዘመንም ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ተፈጽመዋል።

21 አይሁዳውያኑ ከአምላክ እንዲርቁ አድርገዋቸው የነበሩትን፣ ጣዖት አምልኮንና ሌሎቹን አስጸያፊ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች አስወግደዋል። ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ይመስል የነበረው ተስፋ ተፈጽሞላቸው ወደ አገራቸው መመለስና ምድሪቱን እያረሱ አስደሳች ሕይወት መምራት ችለዋል። ወደ አገራቸው ሲመለሱ ከወሰዷቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ በኢየሩሳሌም የነበረውን የይሖዋ መሠዊያ መልሶ መገንባትና በዚያ ላይ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት ማቅረብ ነበር። (ዕዝራ 3:2-6) በተጨማሪም ይሖዋ ጥሩ መንፈሳዊ እረኞች በመስጠት ባርኳቸው ነበር፤ ከእነዚህም መካከል ታማኝ ካህንና ገልባጭ የነበረው ዕዝራ፣ ገዢዎች የነበሩት ነህምያና ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ እንዲሁም እንደ ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ያሉት ደፋር ነቢያት ይገኙበታል። ሕዝቡ ይሖዋ የሚሰጣቸውን አመራር ለመቀበል ፈቃደኛ በሆኑበት ዘመን ሁሉ ለረጅም ጊዜ አጥተውት የነበረውን አንድነት አግኝተው ነበር።—ኢሳ. 61:1-4፤ ኤርምያስ 3:15ን አንብብ።

22. ይሖዋ የተናገራቸው ተስፋዎች የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙበት መንገድ ወደፊት ለሚኖረው የላቀ ፍጻሜ እንደ ቅምሻ ያህል ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

22 ይሖዋ የተናገራቸው ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹት ተስፋዎች የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙበት መንገድ በጣም አበረታች እንደነበረ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ይህ ፍጻሜ ወደፊት ለሚኖረው የላቀ ፍጻሜ እንደ ቅምሻ ያህል ብቻ ነበር። ይህን እንዴት እናውቃለን? እነዚህ ተስፋዎች የሚፈጸሙት አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ ብቻ ነበር። ይሖዋ እነዚህን ተስፋዎች የሚፈጽምላቸው፣ ሕዝቡ ታዛዦች እስከሆኑና የእሱን መመሪያ እስከተቀበሉ ድረስ ብቻ ነበር። አይሁዳውያኑ ግን ከጊዜ በኋላ ዳግመኛ በይሖዋ ላይ ዓመፁ። ይሁን እንጂ ኢያሱ እንደተናገረው የይሖዋ ቃል ምንጊዜም መፈጸሙ አይቀርም። ስለዚህ እነዚህ ተስፋዎች የላቀና ይበልጥ ዘላቂ የሆነ ፍጻሜ ሊኖራቸው ይገባል። ይህ የተፈጸመው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“በእናንተ እረካለሁ”

23, 24. “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” የጀመረው መቼና እንዴት ነው?

23 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን የዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች የጀመሩትና የዓለም ሁኔታ ወደ ፍጻሜው እያሽቆለቆለ መሄድ የጀመረው በ1914 እንደሆነ እናውቃለን። ለይሖዋ አገልጋዮች ግን ይህ ዘመን አሳዛኝ የውድቀት ዘመን አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው 1914 “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት” አስደሳች ዘመን የሚጀምርበት ጊዜ ነው። (ሥራ 3:21) ይህን እንዴት እናውቃለን? በ1914 በሰማይ ምን እንደተከናወነ ታስታውሳለህ? ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ ዙፋኑን ተረከበ። ታዲያ ይህ ክንውን የመልሶ መቋቋሙ ወይም ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን መጀመሪያ የሆነው እንዴት ነው? ይሖዋ ለንጉሥ ዳዊት በእሱ የትውልድ መስመር የሚመጣው ንግሥና ለዘላለም እንደሚጸና ቃል ገብቶለት እንደነበር አስታውስ። (1 ዜና 17:11-14) ባቢሎናውያን በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌምን አጥፍተው የዳዊት ዘሮች ንጉሣዊ አገዛዝ እንዲያበቃ ባደረጉበት ወቅት ይህ ንግሥና ተቋርጦ ነበር።

24 ‘የሰው ልጅ’ የሆነው ኢየሱስ ከዳዊት ዘር የተወለደ እንደመሆኑ መጠን የዳዊት ንግሥና ሕጋዊ ወራሽ ሆኗል። (ማቴ. 1:1፤ 16:13-16፤ ሉቃስ 1:32, 33) በ1914 ይሖዋ ሰማያዊውን ዙፋን ለኢየሱስ ሲሰጠው “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” ጀመረ። አሁን ይሖዋ ይህን ፍጹም የሆነ ንጉሥ ተጠቅሞ የመልሶ መቋቋሙ ወይም የመታደሱ ሥራ እንዲቀጥል ማድረግ ይችላል።

25, 26. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ የወጡት መቼ ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን? (“በ1919 ነው የምንለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።) (ለ) ከ1919 ወዲህ የትኞቹ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀመሩ?

25 ክርስቶስ ንጉሥ ከሆነ በኋላ ከወሰዳቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ ከአባቱ ጋር ሆኖ በምድር ላይ የሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች የሚያቀርቡትን አምልኮ መመርመር ነበር። (ሚል. 3:1-5) ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተነበየው ለረጅም ዓመታት ስንዴውን ከእንክርዳዱ ማለትም እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከአስመሳይ ክርስቲያኖች መለየት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። * በ1914 ግን የመከሩ ወቅት ስለደረሰ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በቀላሉ ማየት ይቻል ነበር። ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሕዝበ ክርስትናን ከባድ ስህተቶች ሲያጋልጡ ቆይተዋል፤ ራሳቸውንም ከዚህች ብልሹ ድርጅት መለየት ጀምረው ነበር። ይሖዋ እነሱን ሙሉ በሙሉ መልሶ የሚያቋቁምበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ስለሆነም በ1919 መጀመሪያ አካባቢ ማለትም ‘የመከሩ ወቅት’ ከጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጡ። (ማቴ. 13:30) የግዞት ዘመን አበቃ!

26 በዚያ ወቅት፣ ሕዝቅኤል የተናገራቸው ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹት ትንቢቶች በጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ዘመን ከነበረው እጅግ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀመሩ። እስቲ አሁን ደግሞ ቀደም ሲል ያየናቸው አምስት ተስፋዎች በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

27. አምላክ ሕዝቦቹን ከጣዖት አምልኮ ያጠራው እንዴት ነው?

27 የመጀመሪያው ተስፋ። ጣዖት አምልኮና ሌሎች አስጸያፊ ሃይማኖታዊ ልማዶች ተወገዱ። በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ታማኝ ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰብና የሐሰት ሃይማኖት ልማዶችን ማስወገድ ጀምረው ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘አምላክ ሥላሴ ነው፣’ ‘ነፍስ አትሞትም’ እንዲሁም ‘ሲኦል የማቃጠያ ቦታ ነው’ የሚሉት ትምህርቶች ከሐሰት ሃይማኖት የመጡ እንደሆኑና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንዳልሆኑ ስለተገነዘቡ እነዚህን ትምህርቶች አስወግደዋል። ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ጣዖት አምልኮ እንደሆነ አጋልጠዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የአምላክ ሕዝቦች መስቀልን ለአምልኮ መጠቀም ከጣዖት አምልኮ ተለይቶ እንደማይታይ ተገነዘቡ።—ሕዝ. 14:6

28. የይሖዋ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ሁኔታ ወደ ምድራቸው የተመለሱት በምን መንገድ ነው?

28 ሁለተኛው ተስፋ። የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ሁኔታ ወደ ምድራቸው ተመለሱ። ታማኝ ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖቶች ከወጡ በኋላ ተስማሚ ወደሆነው መንፈሳዊ ምድራቸው ማለትም ዳግመኛ ለመንፈሳዊ ረሃብ ሊጋለጡ ወደማይችሉበት የተባረከ ቦታ ወይም ሁኔታ ተመልሰዋል። (ሕዝቅኤል 34:13, 14ን አንብብ።) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 19 ላይ በሰፊው እንደምንመለከተው ይሖዋ በዚህ “ምድር” ላይ ታይቶ በማይታወቅ መጠን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንዲኖር በማድረግ ይህን ምድር ባርኮታል።—ሕዝ. 11:17

29. የስብከቱ ሥራ በ1919 የተጠናከረው እንዴት ነው?

29 ሦስተኛው ተስፋ። በይሖዋ መሠዊያ ላይ እንደገና መባ መቅረብ ጀመረ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም.፣ ክርስቲያኖች ለአምላክ የእንስሳት መሥዋዕት ሳይሆን የበለጠ ዋጋ ያለው መባ ማቅረብ እንዳለባቸው ተምረው ነበር። ይህን መባ የሚያቀርቡት ይሖዋን በማወደስና ስለ እሱ ለሌሎች በመናገር ነው። (ዕብ. 13:15) የአምላክ ሕዝቦች በግዞት ሥር በነበሩባቸው በርካታ ምዕተ ዓመታት እንዲህ ያለውን መባ የሚያቀርቡበት የተደራጀ ዝግጅት አልነበረም። ይሁን እንጂ በግዞቱ ማብቂያ አካባቢ እንዲህ ያለውን የውዳሴ መሥዋዕት ማቅረብ ጀምረው ነበር። በስብከቱ ሥራ በቅንዓት ይካፈሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በስብሰባዎቻቸው ላይ በደስታ አምላክን ያወድሱ ነበር። ከ1919 ወዲህ ደግሞ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለስብከቱ ሥራ የበለጠ ትኩረት መስጠት የጀመረ ሲሆን ይህ ሥራ ይበልጥ በተደራጀ ሁኔታ እንዲከናወን ዝግጅት አድርጓል። (ማቴ. 24:45-47) በመሆኑም የይሖዋ መሠዊያ ቅዱስ ስሙን የሚያወድሱ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ብዙ ሰዎች በሚያቀርቡት መሥዋዕት ተሞልቷል።

30. ኢየሱስ ሕዝቦቹ ጥሩ እረኞች እንዲያገኙ ያደረገው እንዴት ነው?

30 አራተኛው ተስፋ። ክፉ እረኞች ተወገዱ። ክርስቶስ የአምላክን ሕዝቦች ጨካኝና ራስ ወዳድ ከሆኑት የሕዝበ ክርስትና የሐሰት እረኞች ነፃ አውጥቷቸዋል። በተጨማሪም እንደ እነዚህ የሐሰት እረኞች ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ እረኞችን ከመንጋው መካከል አስወግዷል። (ሕዝ. 20:38) ጥሩ እረኛ የሆነው ኢየሱስ በጎቹ ተገቢውን እንክብካቤ የሚያገኙበትን ዝግጅት አድርጓል። በ1919 ታማኝና ልባም ባሪያን ሾሟል። ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያቀፈው ይህ ቡድን መንፈሳዊ ምግብ የማቅረቡን ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመምራት የአምላክ ሕዝቦች ጥሩ እንክብካቤ እንዲያገኙ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሽማግሌዎችም ‘የአምላክን መንጋ’ በመንከባከቡ ሥራ እንዲካፈሉ አስፈላጊው ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። (1 ጴጥ. 5:1, 2) በሕዝቅኤል 34:15, 16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሐሳብ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ከክርስቲያን እረኞች ምን እንደሚጠብቁ ለማሳሰብ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል።

31. ይሖዋ በሕዝቅኤል 11:19 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት ነው?

31 አምስተኛው ተስፋ። የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን በአንድነት ማምለክ ጀመሩ። ባለፉት መቶ ዘመናት ሕዝበ ክርስትና እርስ በርስ የሚጋጩ ትምህርቶችን በሚያስተምሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሃይማኖቶችና ኑፋቄዎች ተከፋፍላለች። በአንጻሩ ግን ይሖዋ ተመልሰው ከተቋቋሙት ሕዝቦቹ ጋር በተያያዘ በእርግጥም ተአምራዊ የሆነ ነገር አድርጓል። “እኔም አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ” በማለት በሕዝቅኤል በኩል የሰጠው ተስፋ በአስደናቂ ሁኔታ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሕዝ. 11:19) ክርስቶስ በመላው ዓለም ከተለያየ ዘር፣ ሃይማኖትና የኑሮ ደረጃ የተውጣጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት። ሆኖም ሁሉም ተከታዮቹ አንድ ዓይነት እውነት የተማሩ ሲሆን አስደናቂ በሆነ ኅብረትና ስምምነት አንድ ዓይነት ሥራ ያከናውናሉ። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ተከታዮቹ አንድ እንዲሆኑ ልባዊ ጸሎት አቅርቦ ነበር። (ዮሐንስ 17:11, 20-23ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት በዚህ ዘመን በላቀ መንገድ መልስ እንዲያገኝ አድርጓል።

32. ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹት ትንቢቶች ስላገኙት ፍጻሜ ስታስብ ምን ይሰማሃል? (“ስለ ግዞትና ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹ ትንቢቶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

32 ንጹሕ አምልኮ አስደናቂ በሆነ መንገድ መልሶ በተቋቋመበት በዚህ ዘመን መኖር በመቻልህ ደስ አይልህም? በዛሬው ጊዜ የሕዝቅኤል ትንቢቶች በሁሉም የአምልኳችን ዘርፎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ እየተመለከትን ነው። ይሖዋ “በእናንተ እረካለሁ” ሲል በሕዝቅኤል በኩል በተናገረው ትንቢት መሠረት አሁን ያሉ ሕዝቦቹን በሞገስ ዓይን እያያቸው እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሕዝ. 20:41) ለበርካታ መቶ ዘመናት በመንፈሳዊ ግዞት ከቆዩ በኋላ ነፃ ከወጡትና ግሩም መንፈሳዊ ምግብ እየተመገቡ በአንድነት ይሖዋን ከሚያወድሱት በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦች መካከል እንደ አንዱ መቆጠርህ ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ ትገነዘባለህ? እርግጥ ነው፣ ሕዝቅኤል ከተናገራቸው ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹ ወደፊት ይበልጥ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።

“እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ”

33-35. (ሀ) በሕዝቅኤል 36:35 ላይ የሚገኘው ትንቢት ለግዞተኞቹ አይሁዳውያን ምን ትርጉም ነበረው? (ለ) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች ምን ትርጉም አለው? (“ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

33 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” የጀመረው በ1914 ማለትም ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበትና የዳዊት ዘሮች ንግሥና መልሶ በተቋቋመበት ወቅት ነው። (ሕዝ. 37:24) ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ ለበርካታ ምዕተ ዓመታት በመንፈሳዊ ግዞት ውስጥ በኖሩት ሕዝቦቹ መካከል ንጹሕ አምልኮን መልሶ እንዲያቋቁም ለክርስቶስ ሥልጣን ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ የሚያከናውነው መልሶ የማቋቋም ሥራ በዚሁ ብቻ ያበቃል? በፍጹም! ይህ ሥራ ወደፊትም በአስደናቂ ሁኔታ ይቀጥላል፤ ይህን ጊዜ በተመለከተ የሕዝቅኤል ትንቢት አስደሳች የሆኑ ዝርዝር መግለጫዎችን ይሰጣል።

34 ለምሳሌ የሚከተሉትን በመንፈስ መሪነት የተነገሩ ቃላት ልብ በል፦ “ሰዎችም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ባድማ የነበረው ምድር እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ሆነ።’” (ሕዝ. 36:35) ይህ ተስፋ ለሕዝቅኤልም ሆነ ለግዞተኛ ወገኖቹ ምን ትርጉም ነበረው? ‘ይህ ተስፋ ቃል በቃል ይፈጸማል፤ አገራችን ይሖዋ ራሱ እንዳዘጋጃት እንደ መጀመሪያዋ ገነት ትሆናለች’ ብለው እንዳልጠበቁ የተረጋገጠ ነው። (ዘፍ. 2:8) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የትውልድ አገራቸው ውብና ፍሬያማ እንደምትሆን ዋስትና እየሰጣቸው መሆኑን ተገንዝበው መሆን አለበት።

35 ይህ ተስፋ ዛሬ ለምንኖረው ለእኛስ ምን ትርጉም አለው? በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ይህ ተስፋ ቃል በቃል ፍጻሜውን ያገኛል ብለን አንጠብቅም። ከዚህ ይልቅ ይህ ትንቢት በዘመናችን በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እንገነዘባለን። የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የምንኖረው ውብ በሆነ መንፈሳዊ ምድር ውስጥ ማለትም ፍሬያማ አገልግሎት ማከናወን በምንችልበትና ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ቅድሚያ በምንሰጥበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። ይህ መንፈሳዊ ገነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተዋበ መጥቷል። ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል?

36, 37. ወደፊት በገነት ውስጥ የትኞቹ ተስፋዎች ይፈጸማሉ?

36 ከታላቁ የአርማጌዶን ጦርነት በኋላ ኢየሱስ ግዑዟ ምድርም እንድትታደስ ያደርጋል። ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት በይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት የሰው ልጆች መላዋን ምድር ወደ ገነትነት እንዲለውጡ ያደርጋል። (ሉቃስ 23:43) ያን ጊዜ የሰው ልጆች እርስ በርሳቸውም ሆነ መኖሪያቸው ከሆነችው ምድር ጋር ሙሉ በሙሉ ተስማምተው ይኖራሉ። የትም ቦታ አደጋም ሆነ የሚያስፈራ ነገር አይኖርም። የሚከተለው ተስፋ ቃል በቃል ፍጻሜውን ሲያገኝ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ለማሰብ ሞክር፦ “ከእነሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ አደገኛ የሆኑ የዱር አራዊትንም ከምድሪቱ ላይ አጠፋለሁ፤ በመሆኑም በምድረ በዳ ያለስጋት ይኖራሉ፤ በጫካዎችም ውስጥ ይተኛሉ።”—ሕዝ. 34:25

37 እስቲ የሚከተለውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር! በዚህች ሰፊ ምድር ላይ የሚገኝን የትኛውንም ቦታ ያለምንም ስጋት መጎብኘት ትችላለህ። ጉዳት ሊያደርስብህ የሚችል አንድም እንስሳ አይኖርም። ሰላምህን የሚያውክ አንዳች ነገር አይኖርም። ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ብቻህን እየተዘዋወርክ ታላቅ ግርማ የተላበሰውን ደን ውበት ማድነቅ ትችላለህ። እንዲያውም አንዳች ጉዳት ይደርስብኝ ይሆን ብለህ ሳትሰጋ እዚያው ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶህ አርፈህና ሰውነትህ ታድሶ መነሳት ትችላለህ!

‘በጫካ ውስጥ’ እንኳ ያለምንም ስጋት መተኛት የሚቻልበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር (አንቀጽ 36, 37⁠ን ተመልከት)

38. በሕዝቅኤል 28:26 ላይ የተጠቀሰው ተስፋ ፍጻሜውን ስለሚያገኝበት መንገድ ስታስብ ምን ይሰማሃል?

38 የሚከተለው ተስፋም ሲፈጸም እናያለን፦ “[በምድሪቱ] ላይ ያለስጋት ይቀመጣሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ደግሞም በዙሪያቸው ባሉት በሚንቋቸው ሁሉ ላይ የፍርድ እርምጃ በምወስድበት ጊዜ ያለስጋት ይኖራሉ፤ እኔም አምላካቸው ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።” (ሕዝ. 28:26) የይሖዋ ጠላቶች በሙሉ ተጠራርገው ከጠፉ በኋላ በመላው ምድር ላይ ሰላምና ጸጥታ ይሰፍናል። የምንኖርባቸው ምቹ ቤቶች እንሠራለን እንዲሁም የወይን እርሻ እናለማለን። ያን ጊዜ ምድርን ብቻ ሳይሆን ራሳችንንና ቤተሰባችንንም በሚገባ መንከባከብ እንችላለን።

39. ሕዝቅኤል ስለ ገነት የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

39 እነዚህ ተስፋዎች እንዲሁ ሕልም ብቻ ሆነው የሚቀሩ ይመስልሃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ‘ነገሮች ሁሉ በታደሱበት’ በዚህ ዘመን ምን ክንውኖች ሲፈጸሙ እንደተመለከትክ ለማስታወስ ሞክር። ሰይጣን ኃይለኛ ተቃውሞ ቢሰነዝርም ኢየሱስ ዓለም በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠበት በዚህ ዘመን ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንዲቋቋም ማድረግ ችሏል። ይህም፣ አምላክ በሕዝቅኤል በኩል የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው!

^ አን.2 አብዛኞቹ አይሁዳውያን ግዞተኞች የሚኖሩት ከባቢሎን ከተማ ራቅ ብለው በሚገኙ ሰፈሮች ነበር። ለምሳሌ ሕዝቅኤል ይኖር የነበረው በኬባር ወንዝ አቅራቢያ ከሚኖሩ አይሁዳውያን ጋር ነበር። (ሕዝ. 3:15) ይሁን እንጂ በባቢሎን ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ጥቂት አይሁዳውያን ግዞተኞችም ነበሩ። ከእነሱም መካከል “ከንጉሡና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑ” አይሁዳውያን ይገኙበታል።—ዳን. 1:3, 6፤ 2 ነገ. 24:15

^ አን.25 ለምሳሌ በ16ኛው መቶ ዘመን ከተነሱት የተሃድሶ አራማጆች መካከል የትኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደነበሩ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።