በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

“አንድ ብሔር አደርጋቸዋለሁ”

“አንድ ብሔር አደርጋቸዋለሁ”

ሕዝቅኤል 37:22

ፍሬ ሐሳብ፦ ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚሰበስብ የገባው ቃል፤ ስለ ሁለቱ በትሮች የሚገልጸው ትንቢት

1, 2. (ሀ) ግዞተኞቹ ደንግጠው ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ጨርሶ ያላሰቡት ነገር የተከሰተው እንዴት ነው? (ሐ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

ሕዝቅኤል በባቢሎን ይኖሩ ለነበሩት ግዞተኞች በመለኮታዊ አመራር የተለያዩ ትንቢቶችን በድራማ መልክ አሳይቶ ነበር። ሕዝቅኤል በድራማ መልክ ያሳየው የመጀመሪያ ትንቢት የፍርድ መልእክት የያዘ ነበር፤ ሁለተኛውና ሦስተኛውም እንዲሁ። (ሕዝ. 3:24-26፤ 4:1-7፤ 5:1፤ 12:3-6) እንዲያውም ከዚህ በፊት ያሳያቸው ትንቢታዊ ድራማዎች በሙሉ አይሁዳውያን ከባድ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የሚገልጹ ነበሩ።

2 በመሆኑም ሕዝቅኤል ሌላ ትንቢት በድራማ መልክ ሊያሳያቸው ዳግመኛ ፊታቸው ሲቆም ግዞተኞቹ ምን ያህል ደንግጠው ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ‘አሁን ደግሞ ምን ዓይነት የጥፋት መልእክት ሊነግረን ይሆን?’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ግን የሆነው ጨርሶ ያላሰቡት ነገር ነበር። አሁን ሕዝቅኤል የሚያሳያቸው ትንቢታዊ ድራማ ፈጽሞ የተለየ ነው። መልእክቱ ስለ ጥፋት የሚናገር ሳይሆን ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው። (ሕዝ. 37:23) ሕዝቅኤል ለግዞተኞቹ ያስተላለፈው መልእክት ምን ነበር? ትርጉሙስ ምንድን ነው? ይህ መልእክት በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች የሚነካው እንዴት ነው? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት።

“በእጄ አንድ ይሆናሉ”

3. (ሀ) “ለይሁዳ” ተብሎ የተጻፈበት በትር ምን ያመለክታል? (ለ) አሥሩን ነገድ ያቀፈውን መንግሥት የሚያመለክተው በትር በኤፍሬም ስም የተጠራው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ሕዝቅኤልን ሁለት በትሮች እንዲወስድና በአንዱ ላይ “ለይሁዳ” በሌላው ላይ ደግሞ “ለዮሴፍ ይኸውም ኤፍሬምን ለሚወክለው በትር” ብሎ እንዲጽፍ አዘዘው። (ሕዝቅኤል 37:15, 16ን አንብብ።) እነዚህ ሁለት በትሮች ምን ያመለክታሉ? “ለይሁዳ” ተብሎ የተጻፈበት በትር የይሁዳንና የቢንያምን ነገድ ያቀፈውን ባለሁለት ነገድ መንግሥት ያመለክታል። ከይሁዳ ነገድ የሆኑ ነገሥታት በሁለቱ ነገዶች ላይ ይገዙ ነበር። ካህናቱም ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለግሉ ስለነበር የክህነት ሥርዓቱም ከሁለቱ ነገዶች ጋር የቅርብ ትስስር ነበረው። (2 ዜና 11:13, 14፤ 34:30) በመሆኑም የይሁዳ መንግሥት በዳዊት መስመር በኩል የሚመጣውን ንግሥናና በሌዊ ነገድ ሥር የነበረውን የክህነት አገልግሎት ያቀፈ ነበር። ‘ኤፍሬምን የሚወክለው በትር’ አሥሩን ነገዶች ያቀፈውን የእስራኤል መንግሥት ያመለክታል። ይህ በትር በኤፍሬም ስም የተጠራው ለምንድን ነው? አሥሩን ነገዶች ያቀፈው መንግሥት የመጀመሪያ ንጉሥ የኤፍሬም ነገድ ተወላጅ የሆነው ኢዮርብዓም ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የኤፍሬም ነገድ በእስራኤል ውስጥ ኃያል ነገድ ሆነ። (ዘዳ. 33:17፤ 1 ነገ. 11:26) አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት በዳዊት መስመር በኩል የሚመጣውን ንግሥናም ሆነ በሌዊ ነገድ ሥር የነበረውን የክህነት አገልግሎት እንደማያካትት ልብ በል።

4. ሕዝቅኤል ቀጥሎ በበትሮቹ ላይ ያደረገው ነገር ምን ያመለክታል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 ቀጥሎም ሕዝቅኤል “አንድ በትር ይሆኑ ዘንድ” ሁለቱን በትሮች አንድ ላይ እንዲይዛቸው ተነገረው። ግዞተኞቹ በጭንቀት ተውጠው ሕዝቅኤልን እየተመለከቱት “የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አትነግረንም?” ሲሉ ጠየቁት። እሱም ትንቢታዊ ድራማው ይሖዋ ራሱ የሚያደርገውን ነገር የሚያመለክት እንደሆነ ነገራቸው። ይሖዋ ሁለቱን በትሮች በተመለከተ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፤ እነሱም በእጄ ላይ አንድ በትር ይሆናሉ።”—ሕዝ. 37:17-19

5. ሕዝቅኤል በድራማ መልክ ያሳየው ትንቢት ትርጉሙ ምንድን ነው? (“የሁለቱ በትሮች አንድ መሆን” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

5 ከዚያም ይሖዋ ሁለቱ በትሮች አንድ መሆናቸው ምን ትርጉም እንዳለው ገለጸ። (ሕዝቅኤል 37:21, 22ን አንብብ።) ሁለቱን ነገድ ካቀፈው የይሁዳ መንግሥት የተውጣጡ ግዞተኞችና አሥሩን ነገድ ካቀፈው የእስራኤል መንግሥት (ከኤፍሬም) የተውጣጡ ግዞተኞች ወደ እስራኤል ምድር ተመልሰው በዚያ “አንድ ብሔር” ይሆናሉ።—ኤር. 30:1-3፤ 31:2-9፤ 33:7

6. በሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ላይ የትኞቹ ተዛማጅ የሆኑ ሁለት ትንቢቶች ይገኛሉ?

6 በሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ላይ ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹ ተዛማጅ የሆኑ ሁለት አስደናቂ ትንቢቶች ተመዝግበው ይገኛሉ። ይሖዋ ሕዝቦቹን መልሶ ሕያው ማድረግ ብቻ ሳይሆን (ቁጥር 1-14) በድጋሚ አንድነት እንዲኖራቸው ያደርጋል (ቁጥር 15-28)። እነዚህ ሁለት ትንቢቶች ይሖዋ የሞቱትን ሕያው፣ የተከፋፈሉትን ደግሞ አንድ ማድረግ እንደሚችል የሚያሳይ አጽናኝ መልእክት ይዘዋል።

ይሖዋ ‘የሰበሰባቸው’ እንዴት ነው?

7. በ1 ዜና መዋዕል 9:2, 3 ላይ የሚገኘው ዘገባ ‘በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር እንደሚቻል’ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

7 ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር፣ የግዞተኞቹ ነፃ መውጣትም ሆነ አንድ መሆን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ሊመስል ይችላል። * “በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል።” (ማቴ. 19:26) ይሖዋ፣ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል። የባቢሎን ግዞት በ537 ዓ.ዓ. ያበቃ ሲሆን ከሁለቱም መንግሥታት የተውጣጡ ግለሰቦች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እውነተኛውን አምልኮ መልሶ በማቋቋሙ ሥራ የበኩላቸውን ድጋፍ መስጠት ጀመሩ። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የሚከተለው ዘገባ ይህን ያረጋግጣል፦ “የተወሰኑ የይሁዳ፣ የቢንያም፣ የኤፍሬምና የምናሴ ዘሮች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ።” (1 ዜና 9:2, 3፤ ዕዝራ 6:17) በእርግጥም ልክ ይሖዋ በትንቢት እንደተናገረው አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት አባላት ሁለቱን ነገድ ካቀፈው የይሁዳ መንግሥት አባላት ጋር ተቀላቅለዋል ወይም አንድ ሆነዋል።

8. (ሀ) ኢሳይያስ ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር? (ለ) በሕዝቅኤል 37:21 ላይ ምን ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ይገኛሉ?

8 ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ እስራኤልና ይሁዳ በምርኮ ከተወሰዱ በኋላ ስለሚሆነው ነገር ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይሖዋ “በየቦታው የተሰራጩትን እስራኤላውያን” እና “የተበታተኑትን የይሁዳ ሰዎች ከአራቱም የምድር ማዕዘኖች፣” “ከአሦር” ጭምር እንደሚሰበስብ ተንብዮ ነበር። (ኢሳ. 11:12, 13, 16) በእርግጥም ይሖዋ፣ በትንቢት በተናገረው መሠረት “እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው ብሔራት” አምጥቷቸዋል። (ሕዝ. 37:21) እዚህ ጥቅስ ላይ ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን ልብ ማለት ያስፈልጋል፦ በዚህ ወቅት ይሖዋ ግዞተኞቹን “ይሁዳ” እና “ኤፍሬም” በማለት ፋንታ እንደ አንድ ሕዝብ በመቁጠር “እስራኤላውያን” ብሎ ጠርቷቸዋል። በተጨማሪም እስራኤላውያን ከአንድ ብሔር ማለትም ከባቢሎን ሳይሆን ከተለያዩ ብሔራት እንዲያውም “ከየአቅጣጫው” እንደሚመጡ ተገልጿል።

9. ይሖዋ ከግዞት የተመለሱትን እስራኤላውያን አንድ እንዲሆኑ የረዳቸው እንዴት ነበር?

9 ግዞተኞቹ ወደ እስራኤል ከተመለሱ በኋላ ይሖዋ አንድ እንዲሆኑ የረዳቸው እንዴት ነበር? ለእነዚህ እስራኤላውያን እንደ ዘሩባቤል፣ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ፣ ዕዝራ እና ነህምያ ያሉ መንፈሳዊ እረኞችን ሾሞላቸዋል። ከዚህም ሌላ አምላክ እንደ ሐጌ፣ ዘካርያስና ሚልክያስ ያሉ ነቢያትን አስነሳላቸው። እነዚህ ታማኝ ሰዎች በሙሉ ብሔሩ የአምላክን መመሪያዎች እንዲከተል ለማበረታታት የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። (ነህ. 8:2, 3) በተጨማሪም ይሖዋ የሕዝቦቹ ጠላቶች የጠነሰሱባቸውን ሴራዎች በሙሉ በማክሸፍ የእስራኤልን ብሔር ጠብቋል።—አስ. 9:24, 25፤ ዘካ. 4:6

ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድነት እንዲኖራቸው ለመርዳት መንፈሳዊ እረኞች ሰጥቷቸዋል (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)

10. ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ምን በማድረግ ረገድ ተሳክቶለታል?

10 ይሖዋ ይህን ሁሉ ፍቅራዊ ዝግጅት ቢያደርግላቸውም አብዛኞቹ እስራኤላውያን ንጹሕ አምልኮን በታማኝነት መደገፋቸውን አልቀጠሉም። እነዚህ እስራኤላውያን የፈጸሟቸው ነገሮች ግዞተኞቹ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። (ዕዝራ 9:1-3፤ ነህ. 13:1, 2, 15) እንዲያውም እስራኤላውያን ከተመለሱ በኋላ ባለው አንድ መቶ ዓመት ውስጥ ከንጹሕ አምልኮ በጣም ከመራቃቸው የተነሳ ይሖዋ “ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ ለመማጸን ተገዷል። (ሚል. 3:7) ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት የአይሁድ ሃይማኖት ታማኝ ባልሆኑ እረኞች በሚመሩ በርካታ ኑፋቄዎች ተከፋፍሎ ነበር። (ማቴ. 16:6፤ ማር. 7:5-8) ሰይጣን የተሟላ አንድነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ የወጠነው ተንኮል ተሳክቶለት ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ አይቀርም። እንዴት?

“አገልጋዬ ዳዊት ንጉሣቸው ይሆናል”

11. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ እንደሚሆኑ የተናገረውን ትንቢት በተመለከተ ምን ገለጸ? (ለ) ሰይጣን ከሰማይ ከተባረረ በኋላ ዳግመኛ ምን ለማድረግ ሞክሮ ነበር?

11 ሕዝቅኤል 37:24ን አንብብ። ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው፣ ‘አገልጋዩ ዳዊት’ ማለትም ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ በኋላ እንደሆነ ገልጿል፤ ይህ የሆነው ደግሞ በ1914 ነው። * (2 ሳሙ. 7:16፤ ሉቃስ 1:32) በዚያ ወቅት ሥጋዊ እስራኤል ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በሚያመለክተው መንፈሳዊ እስራኤል ተተክቶ ነበር። (ኤር. 31:33፤ ገላ. 3:29) ሰይጣን፣ በተለይ ከሰማይ ከተባረረ በኋላ በድጋሚ የአምላክን ሕዝቦች አንድነት ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ። (ራእይ 12:7-10) ለምሳሌ በ1916 ወንድም ራስል ከሞተ በኋላ ሰይጣን ከሃዲዎችን በመጠቀም በቅቡዓን መካከል ክፍፍል ለመፍጠር ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ከሃዲዎች ድርጅቱን ለቀው ወጡ። በተጨማሪም ሰይጣን ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ይመሩ የነበሩት ወንድሞች እንዲታሰሩ ማድረግ ችሎ ነበር፤ ነገር ግን ይህም ቢሆን የይሖዋን ሕዝቦች ሊያጠፋቸው አልቻለም። ለይሖዋ ታማኞች ሆነው የጸኑት ቅቡዓን አንድነታቸውን ጠብቀዋል።

12. ሰይጣን መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ለመከፋፈል ያደረገው ጥረት የከሸፈው ለምንድን ነው?

12 በመሆኑም ከሥጋዊ እስራኤላውያን በተቃራኒ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ሰይጣን ክፍፍል ለመፍጠር የወጠናቸውን ሴራዎች ማክሸፍ ችለዋል። የሰይጣን ጥረት ያልተሳካው ለምን ነበር? ምክንያቱም ቅቡዓኑ የይሖዋን መሥፈርቶች አክብረው ለመኖር የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። በዚህም የተነሳ በሰይጣን ላይ ድል እየተቀዳጀ ያለውን የንጉሣቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥበቃ አግኝተዋል።—ራእይ 6:2

ይሖዋ አምላኪዎቹ “አንድ” እንዲሆኑ ያደርጋል

13. ሁለቱ በትሮች አንድ ስለመሆናቸው የሚናገረው ትንቢት ምን አስፈላጊ እውነት ያስተምረናል?

13 ሁለቱ በትሮች አንድ ስለመሆናቸው የሚናገረው ትንቢት በዘመናችን ምን ትርጉም አለው? የዚህ ትንቢት ዓላማ ሁለት ቡድኖች አንድ የሚሆኑበትን መንገድ በምሳሌ ማሳየት እንደሆነ ልብ በል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ትንቢቱ ይህን አንድነት የሚያመጣው ይሖዋ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ታዲያ ሁለቱ በትሮች አንድ ስለመሆናቸው የሚገልጸው ይህ ትንቢታዊ ምሳሌ ስለ ንጹሕ አምልኮ የትኛውን አስፈላጊ እውነት ያጎላል? ትንቢቱ ይሖዋ ራሱ አምላኪዎቹ “አንድ” እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ሕዝ. 37:19

14. ሁለቱ በትሮች አንድ ስለመሆናቸው የሚናገረው ትንቢት ከ1919 አንስቶ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

14 የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ከነጹበትና ወደ መንፈሳዊ ገነት መግባት ከጀመሩበት ከ1919 አንስቶ በትሮቹ አንድ ስለመሆናቸው የሚናገረው ትንቢት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ማግኘት ጀምሯል። በዚያ ወቅት አምላክ አንድ አድርጎ ካሰባሰባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በሰማይ ላይ ነገሥታትና ካህናት የመሆን ተስፋ ነበራቸው። (ራእይ 20:6) እነዚህ ቅቡዓን ‘ይሁዳን’ በሚወክለው በትር ማለትም በዳዊት መስመር በኩል የሚመጡትን ነገሥታትና በሌዊ ነገድ ሥር የነበሩትን ካህናት ባቀፈው ብሔር ተመስለዋል። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ከመንፈሳዊ አይሁዳውያን ጋር ተባበሩ። እነዚህ ደግሞ ‘ኤፍሬምን በሚወክለው በትር’ ማለትም በዳዊት መስመር በኩል የሚመጡትን ነገሥታትና በሌዊ ነገድ ሥር የነበሩትን ካህናት በማያካትተው ብሔር ተመስለዋል። ሁለቱም ቡድኖች በአንዱ ንጉሣቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ሆነው በአንድነት ይሖዋን ያገለግላሉ።—ሕዝ. 37:24

“ሕዝቤ ይሆናሉ”

15. በሕዝቅኤል 37:26, 27 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

15 የሕዝቅኤል ትንቢት ራሱ ብዙ ግለሰቦች ከቅቡዓኑ ጋር በንጹሕ አምልኮ ለመተባበር እንደሚነሳሱ ይጠቁማል። ይሖዋ ሕዝቦቹን በተመለከተ “አበዛቸዋለሁ” እንዲሁም “ድንኳኔ በእነሱ ላይ ይሆናል” በማለት ተናግሯል። (ሕዝ. 37:26, 27 ግርጌ) ይህ አገላለጽ ሕዝቅኤል ከኖረበት ዘመን ከ700 ዓመት ገደማ በኋላ ለሐዋርያው ዮሐንስ የተነገረውን ትንቢት ያስታውሰናል፤ ትንቢቱ ‘በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ድንኳኑን በእጅግ ብዙ ሕዝብ ላይ እንደሚዘረጋ’ ይገልጻል። (ራእይ 7:9, 15) ዛሬ ቅቡዓኑና እጅግ ብዙ ሕዝብ እንደ አንድ ብሔር በመሆን በአምላክ ድንኳን ሥር ተጠልለው ይኖራሉ።

16. ዘካርያስ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ምድራዊ ተስፋ ካላቸው ጋር የሚኖራቸውን አንድነት በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል?

16 ከግዞት ከተመለሱት እስራኤላውያን መካከል አንዱ የሆነው ዘካርያስም መንፈሳዊ አይሁዳውያን ምድራዊ ተስፋ ካላቸው ሰዎች ጋር አንድ እንደሚሆኑ ተንብዮአል። “ከብሔራት . . . ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’” እንደሚሉ ተናግሯል። (ዘካ. 8:23) ‘አንድ አይሁዳዊ’ የሚለው መግለጫ የሚያመለክተው አንድን ግለሰብ ሳይሆን “እናንተ” የተባሉትን ሰዎች ያቀፈውን ቡድን ነው፤ ይህ ቡድን በአሁኑ ጊዜ ቅቡዓን ቀሪዎችን ወይም መንፈሳዊ አይሁዳውያንን ይወክላል። (ሮም 2:28, 29) ‘አሥሩ ሰዎች’ ደግሞ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች ቅቡዓኑን “አጥብቀው በመያዝ” ‘ከእነሱ ጋር ይሄዳሉ።’ (ኢሳ. 2:2, 3፤ ማቴ. 25:40) “አጥብቀው በመያዝ” እና “ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” የሚሉት አገላለጾች እነዚህ ሁለት ቡድኖች ፍጹም አንድነት እንደሚኖራቸው ጎላ አድርገው ይገልጻሉ።

17. ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት የገለጸው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ራሱን ከእረኛ ጋር በማመሳሰል በእሱ አመራር ሥር በጎቹ (ቅቡዓን ክርስቲያኖች) ‘ከሌሎች በጎች’ (ምድራዊ ተስፋ ካላቸው ክርስቲያኖች) ጋር “አንድ መንጋ” እንደሚሆኑ የገለጸው፣ ሕዝቅኤል ስለ አንድነት የተናገረውን ትንቢት በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 10:16፤ ሕዝ. 34:23፤ 37:24, 25) ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብም ሆነ ጥንት የነበሩ ነቢያት የተናገሯቸው ትንቢቶች የወደፊቱ ተስፋችን ምንም ይሁን ምን በመካከላችን አስደናቂ መንፈሳዊ አንድነት እንዳለ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። የሐሰት ሃይማኖት ስፍር ቁጥር በሌላቸው ቡድኖች እየተከፋፈለ ባለበት በዚህ ዘመን እኛ እንደ ተአምር የሚቆጠር አንድነት አለን።

በዛሬው ጊዜ ቅቡዓንና “ሌሎች በጎች” “አንድ መንጋ” ሆነው ይሖዋን በአንድነት ያመልካሉ (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

“መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው” ይሆናል

18. ሕዝቅኤል 37:28 እንደሚጠቁመው የአምላክ ሕዝቦች ‘የዓለም ክፍል አለመሆናቸው’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 ሕዝቅኤል ስለ አንድነት የተናገረው ትንቢት የመጨረሻ ቃላት አንድነታችን እንደተጠበቀ እንዲቆይ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ያጎላሉ። (ሕዝቅኤል 37:28ን አንብብ።) የይሖዋ ሕዝቦች አንድነት ሊኖራቸው የቻለው መቅደሱ ማለትም ንጹሑ አምልኮ “በመካከላቸው” ስላለ ነው። ቅዱስ ሆነው ማለትም ራሳቸውን ከሰይጣን ዓለም ለይተው እስከኖሩ ድረስ መቅደሱ ምንጊዜም በመካከላቸው ይሆናል። (1 ቆሮ. 6:11፤ ራእይ 7:14) ኢየሱስ የዚህ ዓለም ክፍል አለመሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አበክሮ ተናግሯል። ስለ ደቀ መዛሙርቱ ባቀረበው ልባዊ ጸሎት ላይ “ቅዱስ አባት ሆይ፣ . . . አንድ እንዲሆኑ . . . ጠብቃቸው። . . . የዓለም ክፍል አይደሉም። በእውነትህ ቀድሳቸው” ብሏል። (ዮሐ. 17:11, 16, 17) ኢየሱስ ‘አንድ መሆንን’ ‘የዓለም ክፍል ካለመሆን’ ጋር እንዳያያዘው ልብ በል።

19. (ሀ) ‘አምላክን እንደምንመስል’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ አንድነትን በተመለከተ የትኛውን አስፈላጊ እውነት ጎላ አድርጎ ገልጿል?

19 ኢየሱስ አምላክን “ቅዱስ አባት” ብሎ እንደጠራው የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይህ ብቻ ነው። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ንጹሕና ጻድቅ ነው። ይሖዋ የጥንቶቹን እስራኤላውያን “እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን መሆን አለባችሁ” በማለት አዟቸው ነበር። (ዘሌ. 11:45) እኛም ‘አምላክን የምንመስል’ እንደመሆናችን መጠን በምግባራችን ሁሉ ይህን ትእዛዝ መከተል እንፈልጋለን። (ኤፌ. 5:1፤ 1 ጴጥ. 1:14, 15) “ቅዱስ” የሚለው ቃል ከሰዎች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት “የተለየ” የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ ዓለምና በዓለም ላይ ካለው ክፍፍል ራሳቸውን እስከለዩ ድረስ አንድነት እንደሚኖራቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል።

‘ከክፉው ጠብቃቸው’

20, 21. (ሀ) ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ምንድን ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

20 በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚታየው አስደናቂ አንድነት ኢየሱስ ‘ከክፉው ጠብቃቸው’ ሲል ላቀረበው ጸሎት ይሖዋ ምላሽ እንደሰጠ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ዮሐንስ 17:14, 15ን አንብብ።) በእርግጥም ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች አንድነት ማጥፋት አለመቻሉ አምላክ ጥበቃ እንደሚያደርግልን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። ይሖዋ በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ ሁለቱ በትሮች በእጁ ላይ አንድ በትር እንደሚሆኑ ተናግሯል። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ ሕዝቦቹ በእሱ ጥበቃ ሥር ሆነው ተአምራዊ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረገው ይሖዋ ራሱ ነው፤ በመሆኑም ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች አንድነት ሊያጠፋ አይችልም።

21 እንግዲያው ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? በአምላክ ሕዝቦች መካከል ላለው ውድ አንድነት እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። እያንዳንዳችን ይህን ማድረግ የምንችለው በምን መንገድ ነው? በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚከናወነው ንጹሕ አምልኮ አዘውትረን በመካፈል ነው። ይህ አምልኮ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ ይብራራል።

^ አን.7 ሕዝቅኤል ይህን ትንቢት ከመናገሩ ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት አሥሩን ነገድ ያቀፈው መንግሥት ነዋሪዎች (‘ኤፍሬምን የሚወክለው በትር’) በአሦራውያን በግዞት ተወስደው ነበር።—2 ነገ. 17:23

^ አን.11 ይህ ትንቢት በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ በሰፊው ተብራርቷል።