በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 10

“ሕያው ትሆናላችሁ”

“ሕያው ትሆናላችሁ”

ሕዝቅኤል 37:5

ፍሬ ሐሳብ፦ ‘የደረቁት አጥንቶች’ ሕያው እንደሆኑ የሚገልጸው ራእይና የራእዩ ታላቅ ፍጻሜ

1-3. በባቢሎን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ስሜት እንዲለወጥ ያደረገው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

በባቢሎን የነበሩት አይሁዳውያን ስሜት በአስገራሚ ሁኔታ ተለወጠ። ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ ለአምስት ዓመታት ያህል ትንቢት ሲናገር የቆየ ቢሆንም አይሁዳውያኑ ግን ፈጽሞ አላመኑትም ነበር። ምንም ዓይነት ምልክት ቢያሳይ፣ ምንም ዓይነት ምሳሌ ቢናገር እንዲሁም ምንም ዓይነት መልእክት ቢያውጅ ግዞተኞቹ አይሁዳውያን፣ ይሖዋ ኢየሩሳሌም እንድትወድም ይፈቅዳል ብለው ለማመን አሻፈረን አሉ። እነዚህ ግዞተኞች፣ ኢየሩሳሌም በባቢሎናውያን ሠራዊት እንደተከበበች ከሰሙ በኋላም እንኳ ነዋሪዎቿ ምንም ነገር እንደማይደርስባቸው ተማምነው ነበር።

2 አሁን ግን ከበባው ከጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላ አንድ ስደተኛ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን መጥቶ ‘ከተማዋ እንደተመታች’ ተናገረ። ግዞተኞቹ ይህ ዜና ሲነገራቸው ቅስማቸው ተሰበረ! ተወዳጇ ከተማ፣ ቅዱሱ ቤተ መቅደስና የሚናፍቁት አገራቸው እንዳልነበሩ መሆናቸውን ሲሰሙ ጆሯቸውን ማመን አልቻሉም! ለረጅም ጊዜ የተማመኑበት ተስፋ እንደ ጉም በኖ ጠፋ።—ሕዝ. 21:7፤ 33:21

3 ይሁን እንጂ ተስፋ በቆረጡበት በዚህ ወቅት ሕዝቅኤል ተስፋ የሚፈነጥቅ አንድ ራእይ አየ። ይህ ራእይ ቅስማቸው ለተሰበረው ግዞተኞች ምን መልእክት ይዟል? ራእዩ በዘመናችን ካሉት የአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? እኛስ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ ራእይ ምን ትምህርት እናገኛለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይሖዋ ለሕዝቅኤል የገለጠለትን ራእይ እንመርምር።

“ስለ እነዚህ አጥንቶች ትንቢት ተናገር” እና “ለነፋሱ ትንቢት ተናገር”

4. ሕዝቅኤል ራእዩን ሲመለከት ትኩረቱን የሳበው ነገር ምን ነበር?

4 ሕዝቅኤል 37:1-10ን አንብብ። ሕዝቅኤል በአጥንቶች ወደተሞላ ሸለቋማ ሜዳ በራእይ ተወሰደ። ይሖዋ፣ ሕዝቅኤል የራእዩ መልእክት በደንብ እንዲገባው ስለፈለገ ሳይሆን አይቀርም፣ በተበታተኑት አጥንቶች ‘ዙሪያ እንዲያልፍ’ አዘዘው። ሕዝቅኤል በሸለቋማው ሜዳ ሲዘዋወር በተለይ ትኩረቱን የሳበው የአጥንቶቹ ብዛትና የሚገኙበት ሁኔታ ነበር። “በጣም ብዙ” እንደሆኑና “በጣም ደርቀው” እንደነበር ገልጿል።

5. ይሖዋ ለሕዝቅኤል የትኞቹን ሁለት ትእዛዛት ሰጠው? ሕዝቅኤል ትእዛዛቱን ሲፈጽም ምን ተከሰተ?

5 ከዚያም ይሖዋ አጥንቶቹ ደረጃ በደረጃ ወደ ሕይወት እንዲመለሱ ለማድረግ ለሕዝቅኤል ሁለት ትእዛዛት ሰጠው። የመጀመሪያው ትእዛዝ “ስለ እነዚህ አጥንቶች ትንቢት ተናገር” የሚል ነው፤ ለአጥንቶቹ “ሕያው ትሆናላችሁ” በማለት መናገር ነበረበት። (ሕዝ. 37:4-6) ሕዝቅኤል ትንቢቱን እንደተናገረ ወዲያውኑ “የሚንኮሻኮሽ ድምፅ ተሰማ፤ አጥንቶቹም እርስ በርስ መገጣጠም ጀመሩ። ከዚያም አጥንቶቹ ጅማትና ሥጋ [ለበሱ]፤ በቆዳም ተሸፈኑ።” (ሕዝ. 37:7, 8) ሁለተኛው ትእዛዝ ደግሞ “ለነፋሱ ትንቢት ተናገር። . . . ነፋሱንም እንዲህ በለው፦ . . . ‘በእነዚህ በተገደሉት ሰዎች ላይ ንፈስ’” የሚል ነበር። ሕዝቅኤል ትንቢቱን ሲናገር “[እስትንፋስ] ገባባቸው፤ እነሱም ሕያው ሆነው በእግራቸው ቆሙ፤ እጅግ ታላቅ ሠራዊትም ሆኑ።”—ሕዝ. 37:9, 10

“አጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋችንም ጨልሟል”

6. ይሖዋ ለሕዝቅኤል የራእዩን ትርጉም የገለጠለት ምን በማለት ነበር?

6 ቀጥሎም ይሖዋ የራእዩን ትርጉም ለሕዝቅኤል ገለጠለት፤ “እነዚህ አጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው” አለው። በእርግጥም ግዞተኞቹ፣ ኢየሩሳሌም ፈጽማ መውደሟን ሲሰሙ የሞቱ ያህል ሆኖ ተሰምቷቸው ነበር። በመሆኑም “አጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋችንም ጨልሟል። ከሌሎች ጋር ሙሉ በሙሉ ተቆራርጠናል” በማለት አልቅሰዋል። (ሕዝ. 37:11፤ ኤር. 34:20) ይሖዋ ግን ለቅሷቸውን ሲመለከት ተስፋ አስቆራጭ የሚመስለው ይህ ራእይ ለእስራኤል ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት በውስጡ እንደያዘ ግልጽ አደረገላቸው።

7. ይሖዋ በሕዝቅኤል 37:12-14 ላይ ለሕዝቅኤል ምን ገለጸለት? ይህስ ለግዞተኞቹ ምን ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል?

7 ሕዝቅኤል 37:12-14ን አንብብ። ይሖዋ በዚህ ራእይ አማካኝነት ግዞተኞቹን ዳግም ሕያው እንደሚያደርጋቸው፣ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመልሳቸውና በዚያም እንደሚያሰፍራቸው አረጋግጦላቸዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ በድጋሚ “ሕዝቤ ሆይ” በማለት ጠርቷቸዋል። እነዚህ ቃላት ተስፋ ቆርጠው የነበሩትን ግዞተኞች በጣም አጽናንተዋቸው መሆን አለበት። ግዞተኞቹ ይህ ተስፋ በእርግጥ እንደሚፈጸም መተማመን የሚችሉት ለምን ነበር? ይህን ተስፋ የሰጣቸው ይሖዋ ራሱ ስለሆነ ነው። “እኔ ይሖዋ ራሴ እንደተናገርኩና ይህን እንዳደረግኩ ታውቃላችሁ” ብሏል።

8. (ሀ) “መላው የእስራኤል ቤት” በምሳሌያዊ ሁኔታ የሞተው እንዴት ነው? (ለ) ሕዝቅኤል 37:9 እስራኤላውያን በምሳሌያዊ ሁኔታ እንዲሞቱ ምክንያት የሆነውን ነገር የሚገልጸው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

8 አሳዛኝ የሆነው የዚህ ራእይ ገጽታ በጥንቱ የእስራኤል ብሔር ላይ የተፈጸመው እንዴት ነበር? እስራኤል በምሳሌያዊ ሁኔታ መሞት የጀመረችው በ740 ዓ.ዓ. የአሥሩ ነገድ መንግሥት በወደቀበትና ሕዝቡ በግዞት በተወሰደበት ወቅት ነበር። ከ130 ዓመት ገደማ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በግዞት ሲወሰድ ደግሞ “መላው የእስራኤል ቤት” ግዞተኛ ሆነ። (ሕዝ. 37:11) በዚያ ጊዜ ግዞተኞቹ በሙሉ በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ እንደታዩት አጥንቶች በምሳሌያዊ ሁኔታ ሞተው ነበር። * በተጨማሪም ሕዝቅኤል የተመለከተው እንዲሁ አጥንቶችን ሳይሆን ‘በጣም የደረቁ’ አጥንቶችን እንደሆነ አስታውስ፤ ይህም በምሳሌያዊ ሁኔታ ሞተው የቆዩበት ጊዜ በጣም ረጅም መሆኑን ያመለክታል። እስራኤልና ይሁዳ በግዞት የቆዩት በድምሩ ከ200 ዓመት በላይ ማለትም ከ740 እስከ 537 ዓ.ዓ. ድረስ ስለሆነ በእርግጥም ለረጅም ጊዜ ሞተው ቆይተው ነበር ሊባል ይችላል።—ኤር. 50:33

9. በጥንቶቹ እስራኤላውያን ላይ በደረሰውና “በአምላክ እስራኤል” ላይ በደረሰው ነገር መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

9 የሕዝቅኤልን ትንቢቶች ጨምሮ ስለ እስራኤል መልሶ መቋቋም የሚናገሩት ትንቢቶች በወቅቱ ከነበራቸው ፍጻሜ በተጨማሪ ሌላም የላቀ ፍጻሜ አላቸው። (ሥራ 3:21) በጥንት ጊዜ የእስራኤል ብሔር ‘እንደተገደለና’ በምሳሌያዊ ሁኔታ ለበርካታ ዓመታት በድን ሆኖ እንደቆየ ሁሉ ‘የአምላክ እስራኤል’ የተባለው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤም በምሳሌያዊ ሁኔታ ተገድሎ ለረጅም ዓመታት ከሞት በማይተናነስ ግዞት ሥር ኖሯል። (ገላ. 6:16) የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በምርኮ የቆየበት ጊዜ በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሳ የነበሩበት መንፈሳዊ ሁኔታ ‘በጣም ከደረቁ’ አጥንቶች ጋር የሚመሳሰል ሆኖ ነበር። (ሕዝ. 37:2) ከዚህ በፊት በነበረው ምዕራፍ ላይ እንደተብራራው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በምርኮ የተያዘው በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሲሆን ኢየሱስ ስለ ስንዴውና ስለ እንክርዳዱ የተናገረው ምሳሌ እንደሚያመለክተው ይህ ሁኔታ ለብዙ መቶ ዓመታት ዘልቋል።—ማቴ. 13:24-30

ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከታቸው ‘በጣም የደረቁ’ አጥንቶች ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለረጅም ዘመን እንደ ሞት ባለ ግዞት ውስጥ እንደሚቆዩ ያመለክታሉ (አንቀጽ 8, 9⁠ን ተመልከት)

“አጥንቶቹም እርስ በርስ መገጣጠም ጀመሩ”

10. (ሀ) ሕዝቅኤል 37:7, 8 የአምላክ ሕዝቦች ምን እንደሚሆኑ ይናገራል? (ለ) ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ግዞተኞች እምነታቸው ቀስ በቀስ እንዲያንሰራራ የረዳቸው ምን ሊሆን ይችላል?

10 በጥንት ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹ ደረጃ በደረጃ ተመልሰው ሕያው እንደሚሆኑ ተንብዮ ነበር። (ሕዝ. 37:7, 8) ታዲያ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ግዞተኞች፣ ወደ እስራኤል እንደሚመለሱ የተሰጣቸው ተስፋ እንደሚፈጸም ያላቸው እምነት ቀስ በቀስ እንዲያንሰራራ ያደረጉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ተስፋቸው እንዲያንሰራራ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ ቀደም ሲል የነበሩ ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መሆን አለበት። ለምሳሌ ኢሳይያስ “የተቀደሰ ዘር” ማለትም አይሁዳውያን ቀሪዎችን ያቀፈ ቡድን ወደ ምድሪቱ እንደሚመለስ ተንብዮ ነበር። (ኢሳ. 6:13፤ ኢዮብ 14:7-9) በተጨማሪም ሕዝቅኤል የጻፋቸው ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጹ በርካታ ትንቢቶች ተስፋቸውን አለምልመውላቸው እንደሚሆን አያጠራጥርም። ከዚህም ሌላ እንደ ነቢዩ ዳንኤል ያሉ ታማኝ ሰዎች በባቢሎን መኖራቸውና የባቢሎን ከተማ በ539 ዓ.ዓ. በአስደናቂ ሁኔታ መውደቋ ግዞተኞቹ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የነበራቸውን ተስፋ አጠናክሮት መሆን አለበት።

11, 12. (ሀ) ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀስ በቀስ መልሶ ሕያው የሆነው እንዴት ነበር? (“ንጹሕ አምልኮ ቀስ በቀስ መልሶ ተቋቋመ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) በሕዝቅኤል 37:10 ላይ ከሚገኘው መግለጫ ጋር በተያያዘ ምን ጥያቄ ይነሳል?

11 ‘የአምላክ እስራኤል’ ማለትም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤስ ቀስ በቀስ መልሶ ሕያው የሆነው እንዴት ነው? በሞት የተመሰለው የግዞት ዘመን ከጀመረ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ግለሰቦች ለእውነተኛው አምልኮ ጥብቅና መቆም ሲጀምሩ “የሚንኮሻኮሽ ድምፅ” የተሰማ ያህል ነበር። ለምሳሌ ያህል በ16ኛው መቶ ዘመን ዊልያም ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ ተረጎመ። በዚህ ጊዜ ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚችልበት አጋጣሚ በማግኘቱ የሮም ካቶሊክ ቀሳውስት ተበሳጩ። በመሆኑም ቲንደል ተገደለ። ያም ሆኖ ሌሎች ደፋር ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎማቸውን ቀጠሉ፤ በዚህ መንገድ በጨለማው ዓለም ውስጥ ቀስ በቀስ መንፈሳዊ ብርሃን መፈንጠቅ ጀመረ።

12 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ቻርልስ ቴዝ ራስልና የሥራ ባልደረቦቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመግለጥ በቅንዓት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲጀምሩ አጥንቶቹ “ጅማትና ሥጋ” ለበሱ። የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እና ሌሎች ጽሑፎች ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መንፈሳዊ እውነቶችን እንዲያገኙ ረድተዋል፤ በዚህ የተነሳ እነዚህ ሰዎችም ከአምላክ ቅቡዓን አገልጋዮች ጋር ተቀላቀሉ። በ1900ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለው ፊልም፣ ያለቀለት ሚስጥር የተባለው መጽሐፍና ሌሎችም መሣሪያዎች መዘጋጀታቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ይበልጥ አጠናክሯቸዋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አምላክ ሕዝቦቹን ‘በእግራቸው እንዲቆሙ’ ለማድረግ እርምጃ ወሰደ። (ሕዝ. 37:10) ይህ የሆነው መቼና እንዴት ነው? በጥንቷ ባቢሎን የተከናወኑትን ሁኔታዎች መመልከታችን የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳናል።

“ሕያው ሆነው በእግራቸው ቆሙ”

13. (ሀ) በሕዝቅኤል 37:10, 14 ላይ የሚገኘው ትንቢት ከ537 ዓ.ዓ. ጀምሮ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ከአሥሩ ነገድ ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ ወደ እስራኤል ምድር እንደተመለሱ የሚጠቁሙት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

13 በባቢሎን የነበሩት አይሁዳውያን ከ537 ዓ.ዓ. ጀምሮ ይህ ራእይ ፍጻሜውን ሲያገኝ ተመልክተዋል። እንዴት? ይሖዋ ከግዞት ነፃ ወጥተው ወደ እስራኤል ምድር እንዲመለሱ በማድረግ ‘ሕያው ሆነው በእግራቸው እንዲቆሙ’ አስችሏቸዋል። ቁጥራቸው 42,360 የሚሆን እስራኤላውያንና 7,000 ገደማ የሚሆኑ እስራኤላዊ ያልሆኑ ሰዎች ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን መልሰው ለመገንባት እንዲሁም በእስራኤል ምድር ለመኖር ባቢሎንን ለቀው ወጡ። (ዕዝራ 1:1-4፤ 2:64, 65፤ ሕዝ. 37:14) ከ70 ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ 1,750 የሚያክሉ ግዞተኞች ከዕዝራ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። (ዕዝራ 8:1-20) ስለዚህ በድምሩ ከ44,000 በላይ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፤ በእርግጥም “እጅግ ታላቅ ሠራዊት” ሆነዋል። (ሕዝ. 37:10) በተጨማሪም አሦራውያን በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ከአሥሩ ነገድ መንግሥት በግዞት የወሰዷቸው ሰዎች ዘር የሆኑ እስራኤላውያንም፣ ቤተ መቅደሱን መልሶ በመገንባቱ ሥራ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት ወደ እስራኤል ምድር ተመልሰዋል።—1 ዜና 9:3፤ ዕዝራ 6:17፤ ኤር. 33:7፤ ሕዝ. 36:10

14. (ሀ) በሕዝቅኤል 37:24 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ትንቢቱ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) በ1919 ምን ተከናወነ? (“‘በደረቁት አጥንቶች’ እና ‘በሁለቱ ምሥክሮች’ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

14 ይህ የሕዝቅኤል ትንቢት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? ይሖዋ ከዚህ ጋር ተዛማጅ በሆነ ሌላ ትንቢት ላይ ለሕዝቅኤል እንደገለጠለት፣ ስለ መልሶ መቋቋም የሚገልጸው ይህ ትንቢት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው ታላቁ ዳዊት ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ በኋላ ነው። * (ሕዝ. 37:24) በእርግጥም በ1919 ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንፈሱን ሰጥቷቸዋል። በዚህም የተነሳ “ሕያው ሆነው” ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተዋል። (ኢሳ. 66:8) ከዚያ በኋላ ይሖዋ “በምድራቸው” ማለትም በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ እንዲሰፍሩ ፈቅዶላቸዋል። ታዲያ በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች “ታላቅ ሠራዊት” የሆኑት እንዴት ነው?

15, 16. (ሀ) በዘመናችን ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች “ታላቅ ሠራዊት” የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) ይህ የሕዝቅኤል ትንቢት በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ፈታኝ ሁኔታዎች እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው? (“ተመልሰን በእግራችን እንድንቆም የሚያስችል እርዳታ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ክርስቶስ በ1919 ታማኝና ልባም ባሪያን ከሾመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአምላክ አገልጋዮች፣ ከግዞት በተመለሱት እስራኤላውያን መካከል ነቢይ ሆኖ ያገለግል የነበረው ዘካርያስ የተናገረው የሚከተለው ትንቢት ሲፈጸም ተመልክተዋል፦ “ሕዝቦችና የብዙ ከተማ ነዋሪዎች በእርግጥ ይመጣሉ።” ነቢዩ፣ ይሖዋን የሚፈልጉትን እነዚህን ሰዎች “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች” በማለት ገልጿቸዋል። እነዚህ ሰዎች “አንድን አይሁዳዊ” ማለትም መንፈሳዊ እስራኤላውያንን አጥብቀው በመያዝ “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” ይላሉ።—ዘካ. 8:20-23

16 በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ “እጅግ ታላቅ ሠራዊት” አለ። ይህ ታላቅ ሠራዊት በዋነኝነት መንፈሳዊ እስራኤላውያንን (ቅቡዓን ቀሪዎችን)፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ‘አሥሩን ሰዎች’ (ሌሎች በጎችን) ያቀፈ ነው። (ሕዝ. 37:10) ቁጥሩ እየጨመረ በሚሄደው በዚህ ሠራዊት ውስጥ የታቀፍን የክርስቶስ ወታደሮች እንደመሆናችን መጠን ንጉሣችንን ኢየሱስን በቅርበት እየተከተልን ከፊታችን የሚጠብቀንን በረከት ለማግኘት እንገሰግሳለን።—መዝ. 37:29፤ ሕዝ. 37:24፤ ፊልጵ. 2:25፤ 1 ተሰ. 4:16, 17

17. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ምን እንመረምራለን?

17 ንጹሕ አምልኮ በዚህ መንገድ መልሶ መቋቋሙ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚያስከትለው ከባድ ኃላፊነት አለ። ይህ ኃላፊነት ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ወደ ኋላ መለስ ብለን ሕዝቅኤል ገና ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ተሰጥቶት የነበረውን ሥራ መመርመር ያስፈልገናል። በዚህ መጽሐፍ ቀጣይ ምዕራፍ ላይ ይህን እንመረምራለን።

^ አን.8 ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከታቸው አጥንቶች ‘የተገደሉ ሰዎች’ አጥንቶች እንጂ ተፈጥሯዊ በሆነ ሁኔታ የሞቱ ሰዎች አጥንቶች አልነበሩም። (ሕዝ. 37:9) በመጀመሪያ አሦራውያን አሥሩን ነገድ ያቀፈውን የእስራኤል መንግሥት፣ በኋላ ደግሞ ባቢሎናውያን ሁለቱን ነገድ ያቀፈውን የይሁዳ መንግሥት ድል ነስተው በግዞት በወሰዱበት ወቅት “መላው የእስራኤል ቤት” በምሳሌያዊ ሁኔታ ተገድሏል።

^ አን.14 ስለ መሲሑ የሚናገረው ይህ ትንቢት በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ ተብራርቷል።