በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በመጨረሻ ቀኖች” እንደምንኖር እንዴት ማወቅ እንችላለን?

“በመጨረሻ ቀኖች” እንደምንኖር እንዴት ማወቅ እንችላለን?

ክፍል 9

“በመጨረሻ ቀኖች” እንደምንኖር እንዴት ማወቅ እንችላለን?

1, 2. በመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖር እንዴት ለማወቅ እንችላለን?

በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት በሰው የአገዛዝ ሥርዓት ላይ እርምጃ ልትወስድ በተቃረበችበት ጊዜ እንደምንኖር እንዴት እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን? አምላክ የማንኛውንም ዓይነት ክፋትና ሥቃይ ፍጻሜ ወደሚያመጣበት ጊዜ በጣም እንደቀረብን ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው?

2 የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይህን ሁሉ ለማወቅ ፈልገው ነበር። በመንግሥታዊ ሥልጣኑ የመገኘቱና “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” “ምልክቱ” ምን እንደሚሆን ጠየቁት። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስም የሰው ልጅ ወደዚህ የነገሮች ሥርዓት “ፍጻሜ ዘመን” ወይም ወደ “መጨረሻ ቀኖች” እንደገባን የሚያሳዩ ዓለምን የሚያናውጡ ጉዳዮችና ሁኔታዎችን አጣምረው የሚይዙ ዝርዝሮችን በመግለጽ ጥያቄያቸውን መለሰላቸው። (ዳንኤል 11:40፤ 2 ጢሞ. 3:1) እኛስ ይህ ጥምር ምልክት በዚህ መቶ ዘመን ሲፈጸም ተመልክተናልን? እንዴታ፣ ያውም በገፍ!

የዓለም ጦርነቶች

3, 4. የዚህ መቶ ዘመን ጦርነቶች ለኢየሱስ ትንቢት ተስማሚ መግለጫ የሆኑት እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ፤ መንግሥትም በመንግሥት ላይ እንደሚነሣ’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) ዓለም በ1914 ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ሕዝቦችና መንግሥታት በተንቀሳቀሱበት ጦርነት ተዋጠች። በወቅቱ የነበሩ ታሪክ ጸሐፊዎች ይህን ሐቅ በመገንዘብ ጦርነቱን ታላቁ ጦርነት በማለት ጠርተውታል። በታሪክ ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ጦርነት ወይም የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ነበር። በጦርነቱ 20,000,000 የሚያህሉ ወታደሮችና ሲቪሎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህም ከዚያ በፊት በተደረገ በማንኛውም ጦርነት ከጠፋው ሕይወት እጅግ የሚበልጥ ነበር።

4 አንደኛው የዓለም ጦርነት የመጨረሻ ቀኖችን መጀመር ለይቶ አመልክቷል። ኢየሱስ ይህና ሌሎችም ሁኔታዎች “የምጥ ጣር መጀመሪያ” እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:8) ይህም በትክክል ተፈጽሟል፤ ምክንያቱም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሪያው የበለጠ ሞት በማስከተል 50,000,000 የሚያህሉ ወታደሮችና ሲቪሎች ሕይወታቸውን ያጡበት ሆኗል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከ100,000,000 በላይ ሰዎች በጦርነቶች ተገድለዋል። ይህም ከዚያ በፊት አስቀድሞ በነበሩት 400 ዓመታት በተደረጉ ጦርነቶች የሞቱት ባንድ ላይ ቢደመሩ ይኸኛው ከአራት እጥፍ በላይ ነው! የሰውን አገዛዝ በከፍተኛ የሚያወግዝ እንዴት ያለ ድርጊት ነው!

ሌሎች ማስረጃዎች

5-7. በመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የምንኖር ለመሆናችን ሌሎች ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?

5 ኢየሱስ የመጨረሻ ቀኖችን ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ገጽታዎችንም ጨምሯል:- “ታላቅም የምድር መናወጥና በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር [ወረርሽኝ] ራብም ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) ከ1914 ወዲህ ከእንዲህ ዓይነቶቹ መቅሠፍቶች የሚመጣው ከፍተኛ ሥቃይ በጣም በመጨመሩ ይህም ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል።

6 ታላላቅ የምድር መናወጦች ዘወትር የሚደርሱ ከመሆናቸውም በላይ ብዙ ሕይወትን እያጠፉ ናቸው። አንደኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የመጣው የኅዳር በሽታ ብቻውን 20,​000,​000 የሚያህሉ ሰዎችን ገድሏል። እንዲያውም አንዳንድ ግምቶች የበሽታው ሰለባዎች ቁጥር ከ30,000,000 ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ ይገልጻሉ። ኤድስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወት ያጠፋ ሲሆን ገና ወደፊትም በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊያጠፋ የሚችል ነው። በያመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በልብ ሕመም፣ በካንሰርና በሌሎችም በሽታዎች ይሞታሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ደግሞ አዝጋሚውን የረሀብ ሞት ይሞታሉ። ‘የራዕይ ፈረሶች’ ከ1914 ወዲህ በጦርነት፣ በምግብ ዕጥረትና በበሽታ ወረርሽኞቻቸው አማካኝነት ሰብአዊውን ቤተሰብ እየቀሰፉ መሆናቸው አሌ የሚባል አይደለም።—ራዕይ 6:3–8

7 ኢየሱስ በተጨማሪም የሁሉም አገሮች ዕለታዊ ተሞክሮ የሆነው ወንጀል እንደሚጨምር ትንቢት ተናግሯል። “ከአመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” ብሏል።—ማቴዎስ 24:12

8. በ2 ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ያለው ትንቢት ከጊዜያችን ጋር የሚስማማው እንዴት ነው?

8 በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በዛሬው ጊዜ በዓለም በሙሉ በግልጽ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የሥነ ምግባር ውድቀት እንደሚከተለው በማለት ተንብዮአል:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል። . . . ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1–13) ይህ ሁሉ በትክክል ሲፈጸም በዓይናችን እያየነው ነው።

ሌላም ነገር አለ

9. በምድር ላይ ከመጨረሻው ቀኖች መጀመር ጋር ተገጣጥሞ በሰማይ ምን ተፈጽሟል?

9 በዚህ መቶ ዘመን በሰው ላይ መከራ እንዲጨምር ያደረገ ሌላም ነገር አለ። በ1914 ከመጨረሻ ቀኖች መጀመር ጋር ተገጣጥሞ የሰው ልጆችን ከዚህ በከፋ አደጋ ላይ የጣለ ሌላ ነገር ተፈጽሟል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በመጨረሻው መጽሐፍ ላይ ያለው ትንቢት እንደሚገልጸው በዚያን ጊዜ “በሰማይ ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና [በሰማይ ሥልጣን የተቀዳጀው ክርስቶስና] የእርሱ መላእክት ከዘንዶውና [ከሰይጣንና] ከመላእክቱ [ከአጋንንት] ጋር ተዋጉ፤ ነገር ግን ዘንዶውና መላእክቱ ተሸነፉ፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም። ታላቁም ዘንዶ ወደታች ተጣለ፤ እርሱ ሰዎችን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው። እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ የእርሱም መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ተጣሉ።”—ራዕይ 12:7–9 (እንደ 1980 እትም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ)

10, 11. ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ወደ ምድር በተጣሉ ጊዜ ሰዎች የተነኩት እንዴት ነው?

10 ይህስ በሰብአዊው ቤተሰብ ላይ ያስከተላቸው ውጤቶች ምን ነበሩ? ትንቢቱ በመቀጠል “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ ዲያብሎስ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአል” ይላል። አዎን፣ ሰይጣን የእርሱ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየቀረበ እንዳለ ያውቃል፤ ስለዚህ እርሱና የእርሱ ዓለም ከመንገድ ላይ ከመገለላቸው በፊት ሰዎችን በአምላክ ላይ በጠላትነት ለማዞር የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ላይ ነው። (ራዕይ 12:12 የ1980 እትም​20:1–3) እነዚያ መንፈሳዊ ፍጡራን በነፃ ምርጫቸው አለአገባብ በመጠቀማቸው ምንኛ ወራዶች ናቸው! በእነርሱ ግፊት ምክንያት በተለይም ከ1914 ወዲህ በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎች ምን ያህል አሰቃቂ ሆነዋል!

11 ኢየሱስ ስለ ዘመናችን “በምድር ላይ አሕዛብ መውጫውን በማጣት በፍርሃት ይጨነቃሉ። . . . በዓለም ላይ የሚመጣውን ነገር በመጠባበቅ ሰዎች በፍርሃት ይሸበራሉ” በማለት ትንቢት መናገሩ ምንም አያስደንቅም።—ሉቃስ 21:​25,26 የ1980 እትም

የሰዎችና የአጋንንት አገዛዝ ማክተሚያ ቀርቦአል

12. ይህ ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት መፈጸም ያለበት ከቀሩት የመጨረሻ ትንቢቶች መካከል አንዱ ምንድን ነው?

12 አምላክ የአሁኑን ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት መፈጸም ያለባቸው የቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስንት ናቸው? በጣም ጥቂቶች ናቸው! ከመጨረሻዎቹ አንዱ “ስለ ሰላምና ደህንነት ሲነጋገሩ ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል” በማለት የሚገልጸው 1 ተሰሎንቄ 5:3 ነው። (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚመጣው ‘ሰላም ሆኗል በማለት ገና እየተናገሩ’ እንዳሉ መሆኑን ይህ ትንቢት ያሳያል። ሰዎች ትኩረታቸውን ተስፋ በተደረገው ሰላምና ደኅንነት ላይ ተክለው እያሉ ዓለም ፈጽሞ ያልተመለከተው፣ ፈጽሞ ሊጠበቅ በማይችልበት ወቅት ላይ፣ ጥፋት ዱብ ይላል።

13, 14. ኢየሱስ ምን ዓይነት የመከራ ጊዜ ይመጣል ብሎ ተናገረ? እርሱስ የሚደመደመው እንዴት ይሆናል?

13 በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ላለው ለዚህ ዓለም ጊዜው እያለቀበት ነው። በቅርቡም ኢየሱስ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል” ብሎ በተናገረለት የመከራ ወቅት ላይ ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ይመጣል።—ማቴዎስ 24:21

14 የአምላክ ጦርነት የሆነው አርማጌዶን የ“ታላቁ መከራ” መደምደሚያ ይሆናል። እሱም በነቢዩ ዳንኤል የተነገረለት አምላክ “እነዚያን መንግሥታት የሚፈጭበት” ጊዜ ነው። ይህም ባሁኑ ጊዜ ያሉት ከአምላክ ውጭ የሆኑ የሰው አገዛዞች በሙሉ ፍጻሜ ማለት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ከሰማይ የምታስተዳድረው የእርሱ መንግሥት በሰው ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ ቁጥጥርን ትረከባለች። የማስተዳደር ሥልጣን ዳግመኛ “ለሌላ ሕዝብ እንደማይሰጥ” ዳንኤል ተንብዮአል።—ዳንኤል 2:44፤ ራዕይ 16:14–16

15. የሰይጣንና የአጋንንቱ ግፊት ምን ይሆናል?

15 በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰይጣናዊና አጋንንታዊ ግፊቶች ያበቃሉ። እነዚያ አመጸኛ መንፈሳዊ ፍጡራን “አሕዛብን ወደፊት እንዳያስቱ” ቦታ ይለቃሉ። (ራዕይ 12:9፤ 20:1–3) ሞት ተፈርዶባቸው ጥፋታቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የሰው ልጅ ወደ ወራዳ ድርጊቶች ከሚመራው ግፊታቸው መገላገል ምንኛ እፎይ ያሰኛል!

ከጥፋቱ የሚተርፉት እነማን ናቸው? የማይተርፉትስ?

16-18. የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የሚያልፉት እነማን ናቸው? የማያልፉትስ?

16 የአምላክ ፍርድ በዚህ ዓለም ላይ በሚፈጸምበት ጊዜ ከጥፋቱ የሚተርፉት እነማን ናቸው? የማይተርፉትስ? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን አገዛዝ የሚፈልጉ ሰዎች ከለላ አግኝተው ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ያሳያል። የአምላክን አገዛዝ የማይፈልጉ ሰዎች ከሰይጣን ዓለም ጋር ይጠፋሉ እንጂ ከለላ አያገኙም።

17 ምሳሌ 2:​21, 22 እንዲህ ይላል:- “ቅኖች [ለአምላክ አገዛዝ የሚገዙ] በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኃጥአን [ለአምላክ አገዛዝ የማይገዙ] ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”

18 በተጨማሪም መዝሙር 37:​10, 11 “ገና ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል” ይላል። ቁጥር 29ም ጨምሮ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።

19. ልብ ልንለው የሚገባን የትኛውን ምክር ነው?

19 “[ይሖዋን (አዓት)] ተስፋ አድርግ፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ” የሚለውን የመዝሙር 37:34ን ምክር ልብ ማለት ይኖርብናል። ቁጥር 37 እና 38 ደግሞ “ደጉን ሰው ተመልከት፤ ቅን የሆነውንም ሰው እይ፤ ሰላም ወዳድ ሰው ዘሩ ለዘላለም ይኖራል። ኃጢአተኞች ግን ፈጽሞ ይደመሰሳሉ፤ ዘራቸውም ይጠፋል” ይላል። (እንደ 1980 እትም የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ)

20. በዚህ ጊዜ መኖር መንፈስን የሚያነቃቃና የሚያስደስት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

20 አምላክ በእርግጥ የሚያስብልን እንደሆነና ክፋትንና መከራን በሙሉ እንደሚያቆማቸው ማወቁ እንዴት የሚያጽናና ነው! አዎን፣ እንዴት መንፈስን የሚያነቃቃ ነው! የእነዚህ ክቡር ትንቢቶች ፍጻሜ ቅርብ መሆኑን መገንዘብስ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ቀኖች “ምልክት” የሚሆኑትን ሁኔታዎች አስቀድሞ ተንብዮአል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክ አገዛዝ የማይገዙ ሰዎች በቅርቡ በአርማጌዶን ጦርነት ላይ ይጠፋሉ። ለአምላክ አገዛዝ የሚገዙ ሰዎች ግን በሕይወት ተርፈው ጽድቅ ወዳለበት አዲስ ዓለም ይገባሉ