በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሁን እየተገነባ ያለው የአዲሲቱ ዓለም መሠረት

አሁን እየተገነባ ያለው የአዲሲቱ ዓለም መሠረት

ክፍል 11

አሁን እየተገነባ ያለው የአዲሲቱ ዓለም መሠረት

1, 2. በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ምን ሲሆን በዓይናችን እያየን ነው?

አስደናቂ የሆነው ሌላ ነገር ደግሞ አሁን የሰይጣን ዓለም በመፈራረስ ላይ ሲሆን የአምላክ አዲስ ዓለም መሠረት ግን እየተገነባ መሆኑ ነው። አምላክ ከአሕዛብ ሁሉ ሰዎችን በማሰባሰብ ዛሬ ያለውን የተከፋፈለ ዓለም በቅርቡ የሚተካ አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ ለመገንባት መሠረት እንዲሆኑ እያዘጋጃቸው መሆኑን በዓይናችን እያየን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጴጥሮስ 3:13 ላይ ይህ አዲስ ኅብረተሰብ “አድስ ምድር” ተብሎ ተጠርቷል።

2 በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “በዘመኑም ፍጻሜ [አሁን በምንኖርበት ጊዜ] . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው :- ኑ፣ ወደ ይሖዋ ተራራ [የእርሱ እውነተኛ አምልኮ] . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ” በማለት ይናገራል።—ኢሳይያስ 2:2, 3

3. (ሀ) የኢሳይያስ ትንቢት እየተፈጸመ ያለው በነማን መካከል ነው? (ለ) የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ የሚሰጠው እንዴት ነው?

3 ዛሬ ይህ ትንቢት ‘ለአምላክ መንገዶች በሚታዘዙና በጎዳናውም በሚሄዱ ሰዎች’ መካከል እየተፈጸመ ነው። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ሰላም ወዳድ ስለሆኑት ስለ እነዚህ ዓለም አቀፍ የሰዎች ኅብረተሰብ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች” በማለት ይናገርላቸዋል። እነሱም አምላክን በአንድነት የሚያገለግሉ እውነተኛ ዓለም አቀፍ ወንድማማቾች ናቸው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው” በማለት ይናገራል። ይህም ማለት ከዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የሚተርፉ ናቸው ማለት ነው።—ራዕይ 7:9, 14፤ ማቴዎስ 24:3

እውነተኛ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት

4, 5. የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ሊያገኙ የቻሉት ለምንድን ነው?

4 በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ መመሪያዎችና መንገዶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። የዘላለም ሕይወት ተስፋቸውን የጣሉት በአምላክ አዲስ ዓለም ላይ ነው። የአምላክን ሕጎች በመታዘዝ ዕለታዊ ኑሮአቸውን በመምራት አሁንም ሆነ በአዲሱ ዓለም የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል ያላቸውን ፈቃደኛነት ያሳያሉ። የየትኛውም አገር ዜጋ ቢሆኑም ወይም የትኛውም ዓይነት የቆዳ ቀለም ያላቸው ቢሆኑም ሁሉም የሚታዘዙት አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር ደረጃዎችን ማለትም አምላክ በቃሉ ውስጥ ያሠፈራቸውን የሥነ ምግባር ደረጃዎችን ነው። እውነተኛ ዓለም አቀፍ ወንድማማቾች የሆኑት ማለትም በአምላክ የተዘጋጀ አንድ አዲስ የዓለም ኅብረተሰብ ለመሆን የበቁት ለዚህ ነው።—ኢሳይያስ 54:13፤ ማቴዎስ 22:37, 38፤ ዮሐንስ 15:​9, 14

5 የይሖዋ ምሥክሮች ልዩ የሆኑ ዓለም አቀፍ ወንድማማቾች ሊሆኑ በመቻላቸው ምስጋናውን ለራሳቸው አይወስዱም። ይህ ሊሆን የቻለው ራሳቸውን ለአምላክ ሕጎች በሚያስገዙ ሰዎች ላይ በሚሠራው በኃያሉ የአምላክ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ሥራ 5:29, 32፤ ገላትያ 5:22, 23) የአምላክ ሥራ ውጤት እንጂ የእነሱ አይደለም። ኢየሱስ እንደተናገረው “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል።” (ሉቃስ 18:27) ስለዚህ ለሁልጊዜ ጸንቶ የሚኖረውን አጽናፈ ዓለም ለመሥራት የቻለው አምላክ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር አዲስ የዓለም ኅብረተሰብ ለማስገኘት ይችላል።

6. የይሖዋ ምሥክሮች ወንድማማችነት ዘመናዊ ተአምር ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

6 በመሆኑም በአዲሲቱ ዓለም የይሖዋ አገዛዝ እንዴት ያለ እንደሚሆን የአዲሲቱ ዓለም መሠረት እንዲሆን ዛሬ እየተቋቋመ ባለው ወንድማማችነት ላይ ባስገኘው ውጤት ላይ ሊታይ ይችላል። በምሥክሮቹ ረገድ ይሖዋ ያደረገው ነገር ዘመናዊ ተአምር ሊባል የሚበቃ ነው። ለምን? ምክንያቱም መከፋፈልን በሚያመጡት የብሔር፣ የቆዳ ቀለም ወይም የሃይማኖት ስሜቶች ሊበጠስ የማይችል አንድ እውነተኛ ምድር አቀፍ ወንድማማችነትን በምሥክሮቹ ስለገነባ ነው። ምሥክሮቹ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቢሆኑና ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች የሚገኙ ቢሆኑም በማይበጠስ ሰንሰለት አንድ ላይ ተሳስረዋል። ይህ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት በታሪክ ዘመናት በሙሉ ታይቶ የማያውቅ ብርቅ የሆነና በእርግጥም አምላክ ያስገኘው ዘመናዊ ተአምር ነው።—ኢሳይያስ 43:10, 11, 21፤ ሥራ 10:34, 35፤ ገላትያ 3:⁠28

የአምላክን ሕዝቦች ለይቶ ማወቅ

7. ኢየሱስ የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ተለይተው የሚታወቁት እንዴት ነው ብሏል?

7 አምላክ የአዲሲቱ ዓለም መሠረት እንዲሆኑ እየተጠቀመባቸው ያሉትን ሕዝቦች ለማወቅ የሚያስችለን ተጨማሪ ነገር ምንድን ነው? መልሱን ለማወቅ ኢየሱስ በዮሐንስ 13:34, 35 ላይ የተናገራቸውን ቃላት የሚፈጽሙት እነማን ናቸው? ብለን መጠየቅ አለብን። ኢየሱስ በዚያ ላይ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ቃላት ያምኑባቸዋል፤ በሥራ ላይም ያውሏቸዋል። የአምላክ ቃል እንደሚያዘው ‘እርስ በርሳቸው አጥብቀው ይዋደዳሉ።’ (1 ጴጥሮስ 4:8) “ፍቅር የአንድነት ፍጹም ማሠሪያ በመሆኑ ይጎናጸፉታል” (ቆላስይስ 3:14 አዓት) ስለዚህ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን አንድ ላይ የሚያጣብቃቸው “ሙጫ” ፍቅር ነው።

8. 1 ዮሐንስ 3:​10-12 የአምላክን ሕዝቦች ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ተጨማሪ ነገሮችን የሚሰጠን እንዴት ነው?

8 በተጨማሪም 1 ዮሐንስ 3:10–12 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት መልእክት እርስ በርሳችን እንዋደድ የምትል ይህች ናትና፤ ከክፉው እንደነበረ ወንድሙንም እንደገደለ እንደ ቃየል አይደለም።” በመሆኑም የአምላክ ሕዝቦች ሰላማዊ የሆኑ ምድር አቀፍ ወንድማማቾች ናቸው።

ሌላ መለያ ምልክት

9, 10. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች በመጨረሻ ቀኖች ተለይተው የሚታወቁት በምን እነርሱ በሚፈጽሙት ሥራ ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ማቴዎስ 24:⁠14ን የፈጸሙት እንዴት ነው?

9 የአምላክ አገልጋዮች ተለይተው የሚታወቁበት ሌላ መንገድም አለ። ኢየሱስ ስለ ዓለም ፍጻሜ በሰጠው ትንቢቱ ላይ ይህ ጊዜ የመጨረሻ ቀን መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁ ብዙ ነገሮችን ተናግሯል። (ክፍል 9ን ተመልከቱ) የዚህ ትንቢት አንዱ መሠረታዊ ገጽታ በማቴዎስ 24:14 ላይ በተመዘገበው ቃሉ ተጠቅሷል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል።”

10 ይህ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክተናልን? አዎ፣ ተመልክተናል። የመጨረሻ ቀኖች በ1914 ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ኢየሱስ ባዘዘው መንገድ ማለትም ወደ ሰዎች ቤት በመሄድ በዓለም በሙሉ ሰብከዋል። (ማቴዎስ 10:7, 12፤ ሥራ 20:20) በሚልዮን የሚቆጠሩ ምሥክሮች በሁሉም አገሮች ላሉ ሰዎች እቤታቸው ድረስ በመሄድ ስለ አዲሲቱ ዓለም ይነግሩአቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹ ጽሑፎችን ማተምንና ማሠራጨትንም ስለሚያጠቃልል ይህ ብሮሹር ሊደርስዎት የቻለው በዚህ ምክንያት ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች በቀር በዓለም በሙሉ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ስለ አምላክ መንግሥት የሚሰብክ ሌላ ሃይማኖት ያውቃሉን? ማርቆስ 13:10 ይህ የስብከትና የማስተማር ሥራ ፍጻሜው ከመምጣቱ “አስቀድሞ” መፈጸም እንዳለበት ይገልጻል።

ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን አረጋግጠዋል

11. የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን አገዛዝ እሺ ብለው በመቀበላቸው የሚያከናውኑት ሌላ ነገር ምንድን ነው?

11 የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ሕጎችና ሥርዓቶች በመገዛታቸው የሚያከናውኑት ሌላ ነገርም አለ። ሰይጣን ሰዎች ፈተና ሲደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ ሆነው አይጸኑም በማለት ላስነሳው የሰዎችን ፍጹም አቋም ጠባቂነት ለሚመለከተው ሁለተኛው ትልቅ አከራካሪ ጥያቄ መልስ በመስጠት ውሸታም መሆኑን ያሳያሉ። (ኢዮብ 2:1–5) ምሥክሮቹ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ ማህበረሰብ በመሆን አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው ለአምላክ አገዛዝ በታማኝነት ይቆማሉ። ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ቢሆኑም የሰይጣንን ተጽዕኖ ተቋቁመው በጽንፈ ዓለማዊው ሉዓላዊነት ላይ በተነሣው ጥያቄ ረገድ ከአምላክ ጎን ይሰለፋሉ።

12. ምሥክሮቹ በእምነታቸው የሚመስሉት እነማንን ነው?

12 በዛሬው ጊዜ እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በቀድሞ ዘመናት ለአምላክ ታማኝነታቸውን ካሳዩት ሌሎች ምሥክሮች ረዥም የሰልፍ መሥመር ላይ ተጨምረው የምሥክርነት ቃላቸውን ይሰጣሉ። ከእነዚያ የቀድሞ ዘመን ታማኝ ምሥክሮች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል አንዳንዶቹ አቤል፣ ኖኅ፣ ኢዮብ፣ አብርሃም፣ ሳራ፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ዲቦራ፣ ሩት፣ ዳዊትና ዳንኤል ይገኛሉ። (ዕብራውያን ምዕራፍ 11) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እነሱ ‘የታማኝ ምሥክሮች ታላቅ ደመና’ ናቸው። (ዕብራውያን 12:1) እነዚህና የኢየሱስን ደቀመዛሙርት ጨምሮ ለአምላክ ፍጹም አቋም ጠብቀዋል። ኢየሱስ ራሱም ፍጹም አቋሙን በመጠበቅ ከሁሉ የበለጠ ምሳሌ ሆኗል።

13. ኢየሱስ ስለ ሰይጣን የተናገራቸው የትኞቹ ቃላት ናቸው እውነት መሆናቸው የተረጋገጠው?

13 ይህም ኢየሱስ ለሃይማኖት መሪዎቹ ስለ ሰይጣን የተናገራቸው የሚቀጥለው ቃል እውነት መሆኑን አረጋግጧል:- “ነገር ግን አሁን ከእግዚአብሔር የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ . . . እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።”—ዮሐንስ 8:​40, 44

የእርስዎስ ምርጫ ምንድን ነው?

14. በዛሬው ጊዜ የአዲሲቱ ዓለም መሠረት ምን እየሆነ ነው?

14 በይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ አምላክ እየገነባው ያለው የአዲሲቱ ዓለም መሠረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መጥቷል። በያመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመርኩዘው ነፃ ምርጫቸውን የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል እየተጠቀሙበት ነው። እነሱም የአዲሲቱ ዓለም ማህበረሰብ ክፍል በመሆን በጽንፈ ዓለማዊው ሉዓላዊነት ጥያቄ ረገድ ከአምላክ ጎን ተሰልፈው ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

15. ኢየሱስ በዘመናችን እየፈጸመ ያለው ምን የመለየት ሥራ ነው?

15 የአምላክን አገዛዝ በመምረጣቸውም ክርስቶስ “በጎቹን” “ከፍየሎች” በሚለይበት ጊዜ “በቀኙ” ለመቆም ብቃት ያገኛሉ። ኢየሱስ ስለ መጨረሻ ቀኖች በተናገረው ትንቢቱ ላይ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል” በማለት ተንብዮአል። በጎቹ የአምላክን አገዛዝ በመቀበል ከክርስቶስ ወንድሞች ጋር የሚተባበሩትና ድጋፍ የሚሰጡአቸው ትሑት ሕዝቦች ናቸው። ፍየሎቹ የክርስቶስን ወንድሞች የማይቀበሉና የአምላክን አገዛዝ ለመደገፍ ምንም ጥረት የማያደርጉ ሐሳበ ግትር የሆኑ ሰዎች ናቸው። ከምንስ ውጤት ጋር? ኢየሱስ “እነዚያም [ፍየሎቹ] ወደ ዘላለም ቅጣት [መቆረጥ]፣ ጽድቃን [በጎቹ] ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” ብሎአል።—ማቴዎስ 25:31–46

16. በመጪዋ ገነት ውስጥ ለመኖር ከፈለጉ ምን ማድረግ አለብዎት?

16 በእውነቱ አምላክ ያስብልናል! በጣም ቅርብ በሆነ ጊዜ አስደሳች ምድራዊ ገነት ይሰጠናል። በዚያ ገነት ውስጥ ለመኖር ይፈልጋሉን? የሚፈልጉ ከሆነ ስለ ይሖዋ በመማርና የሚማሩትንም በተግባር በመግለጽ ለይሖዋ ዝግጅቶች ያለዎትን አድናቆት ያሳዩ። ይሖዋ “በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ [ይሖዋም አዓት] ይመለስ እርሱም ይምረዋል።”—ኢሳይያስ 55:6, 7

17. ማንን ማገልገል እንዲሚፈልጉ ለመምረጥ ጊዜ ማባከን የሌለብዎት ለምንድን ነው?

17 ሊባክን የሚችል ጊዜ የለም። የዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም ቀርቦአል። የአምላክ ቃል “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ . . . ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይመክረናል።—1 ዮሐንስ 2:15–17

18. በአምላክ ዕፁብ ድንቅ አዲስ ዓለም ለመኖር በትምክህት ለመጠባበቅ የሚያስችልዎት ምን እርምጃ ነው?

18 ባሁኑ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች በአዲሲቱ ዓለም ለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ሥልጠና በማግኘት ላይ ናቸው። ገነትን ለማልማት የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊና ሌሎችንም ጥበቦች እየተማሩ ናቸው። አምላክን ገዢ አድርገው እንዲመርጡና ዛሬ በመላው ምድር ላይ እርሱ እያሠራው ያለውን ሕይወት አድን ሥራ እንዲደርጉ አጥብቀን እናሳስበዎታለን። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት በእርግጥ ስለ እርስዎ ስለሚያስበውና መከራን ወደ ፍጻሜው ስለሚያመጣው አምላክ ለማወቅ ይጣጣሩ። እንዲህ በማድረግ እርስዎም የአዲሲቱ ዓለም መሠረት ክፍል ለመሆን ይችላሉ። ከዚያም የአምላክን ሞገስ ለማግኘትና በዚያ ዕፁብ ድንቅ አዲስ ዓለም ለመኖር በትምክህት ሊጠባበቁ ይችላሉ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት አላቸው

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ አዲስ ዓለም መሠረት በአሁኑ ጊዜ እየተገነባ ነው