በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መኖሩን ማወቅ የምንችልበት መንገድ

አምላክ መኖሩን ማወቅ የምንችልበት መንገድ

ክፍል 3

አምላክ መኖሩን ማወቅ የምንችልበት መንገድ

1, 2. አምላክ መኖር አለመኖሩን እንድናውቅ የሚረዳን ደንብ ምንድን ነው?

አምላክ መኖሩን የምናውቅበት አንዱ መንገድ የተሠራ ነገር ሠሪ ያስፈልገዋል በሚለው የታወቀ ደንብ በመጠቀም ነው። የተሠራው ነገር ይበልጥ ውስብስብ በሆነ መጠን ሠሪውም በዚያው ልክ ከፍ ያለ ችሎታ ያለው መሆን አለበት።

2 ለምሳሌ ያህል በቤትዎ ውስጥ ዙሪያውን ይቃኙ። ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮች፣ ዴስኮች፣ አልጋዎች፣ ሸክላዎች፣ መጥበሻዎች፣ ሣህኖችና ሌሎችም የምግብ ማብሰያና ማቅረቢያ ዕቃዎች ሠሪ ያስፈልጋቸዋል። ግድግዳዎች፣ ወለሎችና የቤቱም ጣራ እንደዚሁ ሠሪ ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም እነዚህ ነገሮች ከሌሎች ነገሮች ጋር ሲመዛዘኑ ለመሥራት ቀለል ያሉ ናቸው። ቀላል ነገሮችም እንኳን ሠሪ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ የተወሳሰቡና ረቂቅ የሆኑት ነገሮች የበለጠ የማሰብ ችሎታ ያለው ሠሪ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ አይደለምን?

አስደናቂው ጽንፈ ዓለማችን

3, 4. አጽናፈ ዓለም አምላክ መኖሩን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

3 ሰዓት ሠሪ ያስፈልገዋል። ታዲያ እጅግ በጣም የተወሳሰበው ፀሐይንና ከዘመናት እስከ ዘመናት በሴኮንድ እንኳን ዝንፍ በማይል ከፍተኛ ትክክለኛነት በዙሪያዋ የሚሽከረከሩትን ፕላኔቶቿን የያዘው ሥርዓተ ፀሐይ ሠሪ አያስፈልገውምን? ከ100 ቢልዮን በላይ ከዋክብትን የያዘው ፍኖተሐሊብ (ሚልኪ ዌይ) የተባለው እኛ በውስጡ የምንኖርበት አስደናቂው ጋላክሲ ሠሪ አያስፈልገውምን? ማታ ፍኖተሐሊብን (የወተት ጐዳና) ለመመልከት ቆም ብለው ያውቃሉን? በተመለከቱት ነገር አልተመሰጡምን? እኛ ያለንበትን ፍኖተሐሊብ የመሰሉ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው በቢልዮኖች የሚቆጠሩ የከዋክብት ረጨቶች (ጋላክሲስ) ስለያዘውና ለመገመት አዳጋች የሆነ ስፋት ስላለው አጽናፈ ዓለምም እስቲ ቆም ብለው ያስቡ! ከዚህም ሌላ በሰማይ ያሉት ግዑዛን አካላት እንቅስቃሴአቸው ከዘመን ዘመን ዝንፍ የማይል እጅግ አስተማማኝ ከመሆኑ የተነሣ የጠፈር አካላቱ ከፍተኛ ትክክለኛነትን ከሚጠብቅ የጊዜ መቁጠሪያ ጋር ተወዳድረዋል።

4 ከሌሎች ነገሮች ጋር ሲነፃፀር ውስብስብነት የሌለው ሰዓት እንኳን ሠሪ እንዳለው ካመለከተ እጅግ በጣም የተወሳሰበው አስደናቂ ጽንፈ ዓለም ንድፍ አውጭና ሠሪ እንዳለው እንደሚያመለክት ጥርጥር የለውም። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዓይናችንን ወደላይ አንስተን እንድንመለከት’ ከጋበዘን በኋላ “እነዚህን የፈጠረ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀረበልን። መልሱ “ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ [አምላክ] ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም” የሚል ነው። (ኢሳይያስ 40:26) በመሆኑም አጽናፈ ዓለም ወደ ሕልውና የመጣው የማይታይ ቁጥጥር በሚያደርግና የማሰብ ችሎታ ባለው ኃይል ይኸውም በአምላክ ነው።

ምድር ልዩና ድንቅ ሆና ተሠርታለች

5-7. ምድር ንድፍ አውጪ እንዳላት የሚያሳዩት ምን እውነቶች ናቸው?

5 የሳይንስ ሊቃውንት ስለምድር ማጥናታቸውን በቀጠሉ ቁጥር ለሰው መኖሪያ እንድትሆን ድንቅ አሠራር ያላት መሆኗን ይበልጥ እየተገነዙቡ መጥተዋል። መሬት የምትገኘው ከፀሐይ ትክክለኛ የብርሃንና የሙቀት መጠን ልታገኝ በምትችልበት ትክክለኛ ርቀት ላይ ነው። በዓመት አንድ ጊዜ በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች፤ ይህን ዙረቷንም የምታከናውነው በብዙ የምድር ክፍሎች የወቅቶች መፈራረቅን ሊያስገኝ በሚችል ሁኔታ አስፈላጊ ወደሆነው አቅጣጫ ጋደል በማለት ነው። ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ በ24 ሰዓት ውስጥ አንድ ጊዜ በመሽከርከር ዘወትር የብርሃንና የጨለማ ጊዜያት መፈራረቅን ታስገኛለች። መተንፈስ የምንችልበትና ጠፈርን አቋርጠው ከሚመጡ ጎጂ ጨረሮች መከላከያ የምናገኝበት የተመጣጠነ የጋዞች ቅልቅል አላት። በተጨማሪም ምግብ ለማብቀል የሚያስፈልግ ከፍተኛ የውሃ መጠንና አፈርም አላት።

6 በአንድነት ተቀናጅተው የሚሠሩት እነዚህና ሌሎች ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ ሕይወት ሊኖር አይችልም ነበር። ታዲያ ይህ ሁሉ በአጋጣሚ የሆነ ነውን? ሳይንስ ኒውስ “እንዲህ ዓይነቶቹ ልዩና ትክክለኛ የሆኑ ነገሮች እንዳጋጣሚ ሊመጡ የማይችሉ ይመስላል” ብሏል። በፍጹም በአጋጣሚ ሊመጡ አይችሉም። አንድ ግሩም ንድፍ አውጭ ወይም ቅርጽ ሰጪ በዓላማ እንዲሠራቸው አስፈልጓል።

7 ወደ አንድ ያማረ ቤት ውስጥ ቢገቡና በተትረፈረፈ ምግብ ተሞልቶ ቢያገኙት እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ማሞቂያና የሙቀት ማስተካከያ ያለው፤ እንዲሁም ለውሃ አቅርቦቱ ጥሩ ቧንቧ ተደርጎለት ቢያገኙት ምን ይገነዘቡ ነበር? ይህ ሁሉ በራሱ የመጣ ነው ብለው ያስቡ ነበርን? እንደዚያ ብለው ከማሰብ ይልቅ አንድ የማሰብ ችሎታ ባለው ሰው በከፍተኛ ጥንቃቄ መሠራቱን እንደማይስቱት ጥርጥር የለውም። ምድርም ለነዋሪዎቿ የሚያስፈልገውን ሁሉ መስጠት እንድትችል በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሠራች ናት፤ እሷም ከማንኛውም ቤት ይበልጥ እጅግ የተወሳሰበችና በአስፈላጊው አቅርቦት ሁሉ የተደራጀች ናት።

8. በምድር አዘገጃጀት ረገድ አምላክ ለእኛ ፍቅራዊ አሳቢነት እንዳለው የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 በተጨማሪም ለሕይወታችን ደስታ የሚጨምሩትን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ነገሮች ያስቡ። የተለያዩ ውብ ቀለማትና ሰዎችን የሚያስደስት ማራኪ መዓዛ ያላቸውን ዓይነታቸው የበዛ አበባዎች እስቲ ይመልከቱ። እንዲሁም ዓይነታቸው እጅግ የበዛ ጣፋጭ ምግቦችም አሉ። ለማየት አስደሳች የሆኑ ደኖች፣ ተራሮች፣ ሐይቆችና ሌሎችም ፍጥረታት አሉ። በተጨማሪም ለሕይወት ደስታ የሚጨምረው ውብ የሆነው የፀሐይ መጥለቅስ? በእንስሳት ዓለም የሚታየው ዓይን የሚስብና ደስ የሚለው የቡችሎች፣ የድመት ግልገሎችና የሌሎችም እንስሳት ግልገሎች ጨዋታ አያስደስተንምን? ስለዚህ ምድር ሕይወትን ለማኖር የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ ብዙ አስደሳችና አስገራሚ ነገሮችን ይዛለች። እነዚህ ነገሮች የሚያመለክቱት ምድር የተሠራችው እኛ ሰዎች በሕይወት እንድንኖር ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን እንድንደሰት ታስቦ በፍቅራዊ ጥንቃቄ መሆኑን ነው።

9. ምድርን የሠራት ማን ነው? የሠራትስ ለምን ነበር?

9 ስለዚህ ምክንያታዊው መደምደሚያ “አንተ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል” በማለት ስለ ይሖዋ አምላክ እንደተናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሰጠ አምላክ መኖሩን አምኖ መቀበል ነው። እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራውስ ለምን ዓላማ ነው? ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አምላክ “ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት” መሆኑን በመግለጽ መልሱን ይሰጣል።—ኢሳይያስ 37:16፤ 45:18

አስገራሚው ሕያው ሴል

10, 11. አንድ ሕያው ሴል በጣም አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ሕይወት ያላቸው ነገሮችስ? እነሱም ሠሪ አያስፈልጋቸውምን? ለምሳሌ ያህል የአንድን ሕያው ሴል አስገራሚ ገጽታዎች እንውሰድ። ሚካኤል ዴንተን የተባሉ የሞሌክዩል ባዮሎጂ ሊቅ ዝግመተ ለውጥ:- ለመውደቅ በመንገዳገድ ላይ የሚገኘው ንድፈ ሐሳብ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው አትተዋል:- “ዛሬ በምድር ላይ ካሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ በውስብስብነት ረገድ በጣም አነስተኛ ናቸው የሚባሉት የባክቴሪያ ሴሎች (ረቂቅ ተሕዋስያን) እንኳን አለቅጥ የተወሳሰቡ ነገሮች ናቸው። . . . በጣም ጥቃቅኖቹ የባክቴሪያ ሴሎች ለመግለጽ አዳጋች በሆነ ደረጃ በጣም ትናንሽ ቢሆኑም . . . እያንዳንዱ ሴል በሺህ የሚቆጠሩ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የተሠሩ ውስብስብ የሞሌክዩል ማሺኖችን የያዘ ፋብሪካ ነው . . . በሰው ከተሠራ ከማንኛውም ማሺን ይበልጥ የተወሳሰበና ሕይወት በሌላቸው ነገሮች መካከል ፈጽሞ አምሳያ የሌለው እጅግ በጣም አነስተኛ ፋብሪካ ነው ሊባል ይቻላል።”

11 ከላይ የተጠቀሱት የሳይንስ ሊቅ በእያንዳንዱ ሴል ውስጥ ያለውን የዘሮቹን ባሕርያት የሚወስን ኮድ በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “ዲ ኤን ኤ መረጃ የማስቀመጥ ችሎታው እስከ አሁን ከሚታወቀው መረጃ ለማስቀመጥ ከተሠራ ከማንኛውም ነገር እጅግ የሚበልጥ ነው፤ በመረጃ አያያዙ ከፍተኛ ብቃት ያለው ከመሆኑ የተነሣ ሰውን የሚያክል ፍጡር ለይቶ ለመወሰን የሚያስፈልገው መረጃ በሙሉ ቢመዘን ክብደቱ ከአንድ ግራም ሚልዮን ክፍሎች ውስጥ ጥቂት ሺዎቹን ብቻ የሚያህል ነው። . . . በሞሌክዩላዊው የሕይወት ፋብሪካ ከሚታየው የብልህነትና የውስብስብነት ደረጃ ጋር ሲወዳደሩ በከፍተኛ ደረጃ የተራቀቁ ናቸው የሚባሉት የመሣሪያ ምርቶቻችን እንኳን መናኛ መስለው ይታያሉ። ነገሩ ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ ያስገድደናል።”

12. አንድ የሳይንስ ሊቅ ስለ ሴል አመጣጥ ምን አሉ?

12 ዴንተን ጨምረው ሲናገሩ “ከታወቁት ሴሎች ሁሉ በጣም ያልተወሳሰበ ነው የሚባለው ሴል ውስብስብነቱ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ እንዲህ ዓይነቱ ነገር በአንድ ዓይነት የማይመስል ዱብ ዕዳ አጋጣሚ ተገጣጥሞ ሊገኝ ቻለ ብሎ ማመን የማይቻል ነው” ብለዋል። ንድፍ አውጭና ሠሪ እንዲኖረው አስፈልጓል።

ዕፁብ ድንቅ የሆነው አንጎላችን

13, 14. አንጎል ከአንድ ሕያው ሴል የበለጠ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

13 እኚህ የሳይንስ ሊቅ እንደሚከተለውም ብለዋል:- “በውስብስብነት ረገድ አንድ ቅንጣት ሴል የሰውን አንጎል ከመሰለ ሥርዓት ጋር ሲወዳደር ከምኑም አይደርስም። የሰው አንጎል አሥር ሺህ ሚልዮን የሚያህሉ የነርቭ ሴሎችን ይዟል። እያንዳንዱ የነርቭ ሴል በአንጎል ውስጥ ካሉት ሌሎች የነርቭ ሴሎች ጋር ግንኙነት የሚያደርገው በአሥር ሺህና በመቶ ሺህ በሚቆጠሩ አያያዥ ክር መሰል ነገሮች አማካኝነት ነው። በሰው አንጎል ውስጥ በዚህ ዓይነት አኳኋን የተዘረጉ የመገናኛ አውታሮች ጠቅላላ ቁጥር . . . ሺህ ሚልዮን ጊዜ ሚልዮን ይደርሳል።”

14 ዴንተን በመቀጠል “በአንጎል ውስጥ ካሉት ግንኙነቶች አንድ በመቶኛው ብቻ እንኳን በአንድ ዓይነት መንገድ ቢደራጅ በምድር ላይ ከተዘረጉት ጠቅላላ የመገናኛ አውታሮች በቁጥር እጅግ የሚበልጡ ግንኙነቶችን ያስገኝ ነበር” ብለዋል። ከዚያም “ታዲያ እንዲህ ዓይነቶቹን ሥርዓቶች ያሰባሰባቸው እንዲያው የዘፈቀደ ድልድል ሂደት ሊሆን ይችላልን?” ብለው ጠይቀዋል። መልሱ ሊሆን አይችልም የሚል መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። አንጎል ለሰው የሚያስብ ንድፍ አውጭና ሠሪ ሊኖረው ይገባል።

15. ሌሎች ሰዎች ስለ አንጎል ምን አስተያየት ሰጥተዋል?

15 የሰው አንጎል በጣም የተራቀቁ ናቸው የተባሉትን ኮምፒተሮችም እንኳን አሻንጉሊት አስመስሏቸዋል። የሳይንስ ጸሐፊው ሞርቶን ሐንት “ላይ ላዩን ያለው የማስታወስ ችሎታችን አንድ ትልቅ ዘመናዊ የምርምር ኮምፒተር ሊይዝ ከሚችለው መረጃ በብዙ ቢልዮኖች ጊዜ የሚበልጥ መረጃን ይይዛል” ብለዋል። በመሆኑም የአንጎል ቀዶ ጥገና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሮበርት ጄ ዋይት እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል:- “ከሰው የመረዳት አቅም በላይ ለሆነው ዕፁብ ድንቅ የአንጎልና የሐሳብ ግንኙነት አነዳደፍና አሠራር ምክንያት የሆነ ከፍተኛ ሊቅ መኖሩን አምኜ ከመቀበል ሌላ ምርጫ የለኝም። . . . ይህን ሁሉ ያስጀመረ ብልህ አእምሮ እንዳለና እንዲሆን ያደረገ አንድ ግለሰብ እንዳስፈለገው ማመን አለብኝ።” እሱም ደግሞ ለሰዎች አሳቢ መሆን ይኖርበታል።

አስደናቂው ሥርዓተ ደም

16-18. (ሀ) ሥርዓተ ደም ዕፁብ ድንቅ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ይኖርብናል?

16 በተጨማሪም ምግብና ኦክሲጂን የሚያጓጉዘውንና ከበሽታ የሚከላከልልንን አስደናቂውን ሥርዓተ ደም ይመልከቱ። ከዚህ ሥርዓት ዋና ዋና ክፍሎች አንዱ የሆነውን ቀይ የደም ሴልን በሚመለከት የሰው አካል ሀሁ የተሰኘው መጽሐፍ “አንድ ቅንጣት የደም ጠብታ በውስጡ ከ250 ሚልዮን በላይ የሆኑ ነጠላ የደም ሴሎችን ይይዛል። . . . በሰው አካል ውስጥ ያሉት ቀይ የደም ሴሎች መሬት ላይ ቢነጠፉ ኖሮ አራት የቴኒስ መጫወቻ ሜዳዎችን ሊሸፍኑ የሚችሉ 25 ትሪልዮን የደም ሴሎች ሳይኖሩ አይቀርም። . . . በየሴኮንዱ ሦስት ሚልዮን ያህል አዳዲስ ሴሎች እየተሠሩ የሞቱት ሴሎች ይተካሉ” ብሏል።

17 ይኸው ጽሑፍ የአስደናቂው የደም ሥርዓት ሌላ ክፍል የሆኑትን ነጭ የደም ሴሎች በተመለከተ ደግሞ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ቀይ የደም ሴል አንድ ዓይነት ብቻ ሲሆን ነጭ የደም ሴሎች ግን ሰውነት ከበሽታ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ በተለያየ መንገድ መዋጋት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዓይነት ሴሎች አሉት። ለምሳሌ ያህል አንዱ ዓይነት ነጭ የደም ሴል የሞቱ ሴሎችን የሚያስወግድ ነው። ሌሎቹ ዓይነቶች ደግሞ ከቫይረሶች የሚከላከሉ የሰውነት መከላከያዎችን ያመነጫሉ፣ ለሰውነት ባዕድ የሆኑ ነገሮችን መርዝነት ያስወግዳሉ ወይም ቃል በቃሉ ባክቴሪያዎችን በልተው በመዋጥ ያደቋቸዋል።”

18 እንዴት ያለ አስገራሚና በከፍተኛ ሁኔታ የተደራጀ ሥርዓት ነው! ይህን ያህል በጥሩ ሁኔታ አንድ ላይ የተሰናዳና ኃይለኛ ተከላካይ ነገር በጣም አስተዋይና ለሰው አሳቢ የሆነ አደራጅ ሊኖረው እንደሚገባ አያጠራጥርም። እርሱም አምላክ ነው።

ሌሎች ድንቆች

19. ዐይንን ከሰው ሠራሽ መሣሪያዎች ጋር እያወዳደርህ ሐሳብ ስጥ።

19 በሰው አካል ውስጥ ሌሎች አስደናቂ ነገሮችም አሉ። ከእነዚህም አንዱ የሰው ዐይን ሲሆን እሱም ግሩም በሆነ ሁኔታ ከመሠራቱ የተነሣ ምንም ዓይነት ካሜራ ሊኮርጀው አልቻለም። የከዋክብት ተመራማሪው ሮበርት ጃስትሮ “ዐይን በጥሩ ንድፍ አወጣጥ የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታያል፤ ማንም የቴሌስኮፕ ሠሪ ከዚህ የተሻለ ነገር ሊሠራ ባልቻለም ነበር” ብለዋል። ታዋቂው ካሜራ የተሰኘው ጽሑፍ እንዲህ ብሏል:- “የሰው ዓይኖች ከፊልም ይልቅ እጅግ በጣም በላቀ ስፋት ብዙ ዓይነት ዝርዝሮችን ያያሉ። ነገሮችን የሚያዩት በወርድ፣ በስፋትና በቁመት በፍጹም ቁመናቸውና ያላንዳች መዛባትና በማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው። . . . ካሜራን ከሰው ዓይን ጋር ማመሳሰል ፈጽሞ የማይመጣጠኑ ነገሮችን ማወዳደር ስለሆነ ተገቢ አይደለም። የሰው ዐይን ይበልጥ የሚመሳሰለው ከአርቲፊሻል የማሰብ ችሎታ፣ መረጃ የማዘጋጀት ችሎታ፣ ፍጥነትና ከማንኛውም ሰው ሠራሽ መሣሪያ፣ ኮምፒተር ወይም ካሜራ የላቀ የአሠራር ስልት ካለው ከኮምፒተር በላይ ከሆነ ዕፁብ ድንቅ መሣሪያ ጋር ነው።”

20. ከሰው አካል አስገራሚ ገጽታዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

20 በተጨማሪም የተራቀቁና የተወሳሰቡ የአካል ክፍሎች እኛ ሆን ብለን ሳናስብ እንዴት ተባብረው እንደሚሠሩም አስቡ። ለምሳሌ ያህል ብዙ ዓይነት ምግብና መጠጦችን ወደ ሆዳችን እናስገባለን፣ ሆኖም ሰውነታችን ሁሉንም በየክፍላቸው ይለያያቸውና ኃይልን ይፈጥራሉ። እንዲህ ዓይነቶቹን ብዙ ዓይነት ነገሮች በአውቶሞቢል የነዳጅ ማጠራቀሚያ ታንክ ውስጥ ክተቷቸውና መኪናዋ የቱን ያህል መሄድ እንደምትችል ተመልከቱ! ከዚህም በቀር የወላጆቹ ቅጂ የሆነ ተወዳጅ ህፃንን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ የሚያስገኘው የወሊድ ተአምርም አለ። ልጁ ጥቂት ዓመታት ብቻ ቆይቶ በተራቀቀ ቋንቋ መናገርን ለመማር ያለው ችሎታስ ተአምር አይደለምን?

21. ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች በሰውነት ውስጥ ያሉትን ድንቅ ነገሮች ሲመለከቱ ምን ይላሉ?

21 አዎ፣ በሰው አካል ውስጥ ያሉ ብዙ አስገራሚና የተወሳሰቡ የፍጥረት ሥራዎች በአድናቆት ይሞሉናል። እነዚህን ነገሮች አስመስሎ መሥራት የሚችል መሐንዲስ የለም። ታዲያ የአጋጣሚ ግኝቶች ሊሆኑ ይችላሉን? ሊሆኑ እንደማይችሉ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች የሰውን አካል አስደናቂ ገጽታዎች ሁሉ በሚመለከቱበት ጊዜ እንደ መዝሙራዊው “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው” ይላሉ።—መዝሙር 139:14

ወደር የለሹ አደራጅ

22, 23. (ሀ) የፈጣሪን ሕልውና አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚናገረው ተገቢ የሆነ ነገር ምንድን ነው?

22 መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 3:4) የቱንም ያህል በቀላሉ የተሠራ ቢሆን ማንኛውም ቤት የግዴታ ሠሪ ካስፈለገው እንግዲያውስ እጅግ በጣም የተወሳሰበው አጽናፈ ዓለም በምድር ላይ ካለው ልዩ ልዩ የሕይወት ዓይነት ጋር ሠሪና አዘጋጅ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው። አውሮፕላን፣ ቴሌቪዥንና ኮምፒተሮች የመሳሰሉትን መሣሪያዎች እከሌ ፈለሰፋቸው እያልን እንደምንናገር ሁሉ ሰዎች እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮች እንዲሠሩ አንጎል የሰጣቸው መኖሩንም አምነን መቀበል አይገባንምን?

23 መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፣ ምድርንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ያጸና፣ በእርሷ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፤ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ [ይሖዋ አዓት]” በማለት ለአጽናፈ ዓለማትና በውስጣቸው ላሉት ሁሉ ፈጣሪ እንዳላቸው ያሳያል። (ኢሳይያስ 42:5) መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር፣ ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነው።—ራዕይ 4:11

24. አምላክ መኖሩን እንዴት ለማወቅ እንችላለን?

24 አዎ፣ አምላክ መኖሩን በሠራቸው ነገሮች ለማወቅ እንችላለን። የአምላክ “የማይታየው ባሕርይ” እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል።”—ሮሜ 1:20

25, 26. አንድ ነገር ያላግባብ ቢሠራበት ሠሪ ባይኖረው ነው በማለት ለመከራከር ምክንያት የማይሆነው ለምንድን ነው?

25 አንድን የተሠራ ነገር ሰዎች አላአግባብ ቢጠቀሙበት ያ ነገር ሠሪ የለውም ማለት አይደለም። አንድ አውሮፕላን ለሰላማዊ ዓላማ ይኸውም በአየር ላይ ለመጓጓዝ ሊውል ይችላል። ነገር ግን በቦምብ ጣይነትም ለጥፋት ሊውል ይችላል። ሰውን ለመግደል ማገልገሉ ሠሪ አልነበረውም ማለት አይደለም።

26 በተመሳሳይም ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ መጥፎ መሆናቸው ሠሪ አልነበራቸውም ወይም አምላክ የለም ማለት አይደለም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት በትክክል ተናግሯል:- “ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቆጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን አልሠራኸኝም ይለዋልን? ወይስ የተደረገው አድራጊውን አታስተውልም ይለዋልን?”—ኢሳይያስ 29:16

27. አምላክ ስለ መከራ ለምናነሣቸው ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጠን ልንጠብቅ የምንችለው ለምንድን ነው?

27 ፈጣሪ በሠራቸው ነገሮች አስገራሚነትና ውስብስብነት ጥበቡን አሳይቷል። ምድርን ለመኖር ተስማሚ አድርጎ በማዘጋጀቱ፣ አካላችንንና አእምሮአችንን እንዲህ ድንቅ አድርጎ በመሥራቱና የምንደሰትባቸው ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በማዘጋጀቱ በእርግጥ የሚያስብልን መሆኑን አሳይቷል። ‘አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? መከራን ለማስቀረትስ ምን ያደርግ ይሆን?’ የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ እንድናውቅ በማድረግም ተመሳሳይ ጥበቡንና አሳቢነቱን እንደሚያሳይ የተረጋገጠ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መከላከያ ከሆነው ከባቢ አየር ጋር የተዘጋጀችው ምድር ስለ እኛ አጥብቆ በሚያስብ አምላክ የተሠራች ድንቅ ቤታችን ናት

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምድር ሕይወታችንን በተሟላ መንገድ እንድንደሰትበት ለማስቻል በፍቅራዊ አሳቢነት የተዘጋጀች ናት

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘አንድ አንጎል በምድር ላይ ካሉት የመገናኛ አውታሮች ሁሉ የሚበልጡ መገናኛዎችን ይይዛል—የሞሌክዩል ባዮሎጂ ሊቅ

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ዐይን በጥሩ ንድፍ አወጣጥ የተሠራ መሆኑ በግልጽ ይታያል፤ ማንም የቴሌስኮፕ ሠሪ ከዚህ የተሻለ ሊሠራ አይችልም”—ከዋክብት ተመራማሪ