በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት

ክፍል 6

አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት

1, 2. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክ የሰጣቸውን ጥሩ ጅምር ያበላሹት እንዴት ነው?

ታዲያ ምን ችግር ተፈጠረ? አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኤደን ገነት የሰጣቸውን ጥሩ ጅምር የሚያበላሽ ምን ተፈጸመ? በገነቱ ሰላምና ስምምነት ፈንታ ክፋትና ሥቃይ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የሠፈኑት ለምንድን ነው?

2 መንስኤው አዳምና ሔዋን በነፃ ምርጫቸው አለአግባብ መጠቀማቸው ነው። ከአምላክና ከሕጎቹ ተለይተው እንዲሳካላቸው ሆነው እንዳልተፈጠሩ ዘነጉት። ከአምላክ ነፃ ሆነው በራሳቸው ሐሳብ መመራት ሕይወታቸውን የሚያሻሽልላቸው መስሎአቸው ከአምላክ ተነጠሉ። ስለዚህ አምላክ ለነፃ ምርጫ ከደነገገው ገደብ አፈነገጡ።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 3

በጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ላይ የተነሣው ጥያቄ

3-5. አምላክ አዳምንና ሔዋንን አጥፍቶ ሌሎች ሰዎች በመፍጠር ሥራውን እንደገና ያላስጀመረው ለምንድን ነው?

3 ታዲያ አምላክ አዳምንና ሔዋንን አጥፍቶ ሌላ ባልና ሚስት ያልፈጠረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱ ይኸውም የማይገሰሰው የመግዛት መብቱ ግድድር ማለትም ጥያቄ ነተስቶበት ስለነበረ ነው።

4 ጥያቄውም ለመግዛት መብት ያለው ማን ነው? ትክክለኛው አገዛዝስ የማን አገዛዝ ነው? የሚል ነበር። አምላክ ሁሉን ማድረግ የሚችልና የፍጥረታቱ በሙሉ ፈጣሪ መሆኑ በፍጥረታቱ ላይ ለመግዛት የማያጠያይቅ መብት ይሰጠዋል። ከሁሉ የበለጠ ጥበበኛ በመሆኑ ደግሞ ለፍጥረታቱ በሙሉ ከሁሉ የተሻለው አገዛዝ የእርሱ አገዛዝ ነው። ይሁንና አሁን የአምላክ አገዛዝ ጥያቄ ተነሣበት። በተጨማሪም ይህ ሰው የተባለው ፍጥረት በአፈጣጠሩ ላይ እንከን ኖሮት ይሆንን? በነገሩ ጥያቄ ውስጥ የሰው የፍጹም አቋም ጠባቂነት ጉዳይ እንዴት እንደገባ በኋላ እንመረምራለን።

5 ሰው ከአምላክ ተነጥሎ በራሱ ሐሳብ የሚመራ በሆነ ጊዜ ሰዎች ከአምላክ አገዛዝ ቢወጡ ይሻላቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ በተዘዋዋሪ ተነስቷል። ፈጣሪ የጥያቄውን መልስ ጥሩ አድርጎ ያውቅ ነበር፤ ነገር ግን ሰዎች ራሳቸው መልሱን ለማየት እንዲችሉ የፈለጉትን ሙሉ ነፃነት ፈቀደላቸው። በነፃ ምርጫቸው ተጠቅመው ይህ ዓይነቱን አካሄድ መረጡ፤ አምላክም ፈቀደላቸው።

6, 7. አምላክ ለዚህን ያህል ረዥም ጊዜ ለሰዎች ፍጹም ነፃነት የፈቀደላቸው ለምንድን ነው?

6 አምላክ ሰዎች ከእርሱ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነው በመኖር ነገሩን እንዲሞክሩት በቂ ጊዜ በመፍቀዱ ለሰዎች የሚሻለው በአምላክ አስተዳደር ሥር መሆን ይሁን ወይም በራሳቸው፣ ለሁልጊዜው ይረጋገጣል። የሚፈቀደው ጊዜ ርዝማኔም ሰዎች በፖለቲካዊ፣ በኢንዱስትሪ፣ በሳይንሳዊና በሕክምና ግኝቶች ከፍተኛ ነው ብለው የሚያስቡት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚያስችል መሆን ነበረበት።

7 ስለዚህ አምላክ ከእርሱ ውጭ የሆነ የሰው አገዛዝ ይሳካ ወይም አይሳካ እንደሆነ ቁልጭ ብሎ እንዲታይ ሲል ሰው እስከ ዘመናችን ድረስ ከአምላክ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኖ የፈለገውን እንዲያደርግ ፈቅዷል። በመሆኑም ሰው ከደግነትና ከጭካኔ፣ ከፍቅርና ከጥላቻ፣ ከጽድቅና ከኃጢአት መካከል ይሻለኛል ያለውን የፈለገውን ለመምረጥ ችሎአል። ነገር ግን ምርጫው ከሚያስከትለው ውጤት ይኸውም ከመልካምነትና ከሰላም ወይም ከክፋትና ከሥቃይ ለመሸሽ አልቻለም።

የመንፈሳዊ ፍጡራን አመጽ

8, 9. (ሀ) በመንፈሳዊው ዓለም ዓመፅ የፈነዳው እንዴት ነበር? (ለ) ከአዳምና ከሔዋን ሌላ ሰይጣን እንዲያምፁ ያግባባቸው እነማንን ነው?

8 ሊታሰብበት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ። በአምላክ አገዛዝ ላይ ያመፁት የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ብቻ አልነበሩም። ታዲያ በዚያ ጊዜ ከእነርሱ ሌላ የትኞቹ ፍጡራን በሕይወት ነበሩ? መንፈሳዊ ፍጡራን ነበሩ። አምላክ ሰዎችን ከመፍጠሩ በፊት በሰማያዊው ዓለም እንዲኖሩ የፈጠራቸው ከሰው በላይ የሆነ አፈጣጠር ያላቸው ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው መላእክት ነበሩ። እነሱም ጭምር ከነፃ ምርጫ ጋር የተፈጠሩና ለአምላክ አገዛዝ መገዛት የሚያስፈልጋቸው ነበሩ።—ኢዮብ 38:7፤ መዝሙር 104:4፤ ራዕይ 5:11

9 መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፅ በመጀመሪያ የተነሳው በመንፈሳዊው ዓለም እንደነበረ ይገልጻል። አንድ መንፈሳዊ ፍጡር በሁሉም ነገር ፍጹም ነፃነት ፈለገ። አልፎ ተርፎም ሰዎች እንዲያመልኩት ፈለገ። (ማቴዎስ 4:8, 9) ይህ መንፈሳዊ አመጸኛ ፍጡር አምላክ ከአዳምና ከሔዋን የሚጠቅማቸውን ነገር ከልክሏቸዋል ብሎ በሐሰት በመናገር አዳምና ሔዋንም እንዲያምፁ አነሳስቷል። (ዘፍጥረት 3:1–5) ስለዚህ ዲያብሎስ (ስም አጥፊ፣ ሐሜተኛ) እና ሰይጣን (ተቃዋሚ፣ ባላጋራ) ተብሎ ተጠራ። በኋላም ሌሎች መንፈሳዊ ፍጡራንም እንዲያምፁ አግባብቷቸዋል። እነሱም አጋንንት ተባሉ።—ዘዳግም 32:17፤ ራዕይ 12:9፤ 16:14

10. የሰዎችና የመንፈሳዊ ፍጡራን ማመፅ ምን ውጤት አስከተለ?

10 ሰዎች በአምላክ ላይ በማመፃቸው ምክንያት ለሰይጣንና ለአጋንንቱ ተፅዕኖ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የማያምኑትን አሳብ ያሳወረ” “የዚህ ዓለም አምላክ” በማለት የሚጠራው። ስለዚህ የአምላክ ቃል “ዓለሙም በሞላው በክፉው [ኃይል] ተይዟል” ይላል። ኢየሱስ ራሱም ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ጠርቶታል።—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19፤ ዮሐንስ 12:31

ሁለት አከራካሪ ጥያቄዎች

11. ሰይጣን አምላክን የተገዳደረው በሌላ በምን አከራካሪ ጥያቄ ነው?

11 ሰይጣን አምላክን ለመገዳደር ሌላ ጥያቄም አንስቷል። እሱም አምላክ ሰውን የፈጠረበት መንገድ እንከን እንዳለበትና ማንም ሰው ተጽዕኖ ቢደርስበት ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንደማይፈልግ አድርጎ አምላክን ወነጀለው። እንዲያውም ፈተና ቢደርስባቸው አምላክን እንኳን ከመራገም አይመለሱም አለ። (ኢዮብ 2:1–5) በዚህ መንገድም ሰይጣን የሰብአዊ ፍጥረትን ፍጹም የአቋም ጽናት በጥያቄ ላይ ጣለው።

12-14. ሰይጣን ያስነሳቸውን ሁለቱን ጥያቄዎች በተመለከተ ጊዜ እውነቱን የሚገልጠው እንዴት ነው?

12 ስለዚህ አምላክ ይህ ጥያቄም ሆነ በሉዓላዊነቱ ላይ የተነሳው ጥያቄ እንዴት መፍትሔ እንደሚያገኙ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡሮቹ ሁሉ ለማየት እንዲችሉ በቂ ጊዜ ፈቀደ። (ከዘጸአት 9:16 ጋር አወዳድሩ) ውሎ አድሮ የሰው ታሪክ ስለ እነዚህ ጥያቄዎች በመጨረሻው እውነቱ እንዲገለጥ ማድረጉ የማይቀር ነበር።

13 ከሁሉ በፊት በይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ላይ ስለ አገዛዙ ትክክለኛነት በተነሣው ጥያቄ ረገድ የተፈቀደው ጊዜ ምን አሳየ? ሰዎች አምላክ ከሚያስተዳድራቸው በተሻለ ሁኔታ ራሳቸውን ማስተዳደር ችለዋልን? ከአምላክ የራቀ ማንኛውም የሰው የአገዛዝ ሥርዓት ከጦርነት፣ ከወንጀልና ከፍትሕ መዛባት ነፃ የሆነ ደስተኛ ዓለም አምጥቷልን? ድህነትን አጥፍቶ ለሁሉም ሰው ብልጽግናን ያመጣ አገዛዝ አለን? በሽታን፣ እርጅናንና ሞትን ያሸነፈ የሰው አገዛዝ አለን? የአምላክ አገዛዝ ይህን ሁሉ ለማምጣት የታቀደ ነበር።—ዘፍጥረት 1:26–31

14 ሁለተኛውን ጥያቄ በተመለከተስ የተፈቀደው ጊዜ ስለ ሰብአዊው ፍጥረት ዋጋማነት ምን አሳየ? አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር እንከን ባለበት መንገድ ነበርን? ፈተና ሲደርስበት ትክክለኛ ነገር የሚያደርግ ሰው ይገኛልን? ከአምላክ አገዛዝ ከመውጣት ይልቅ የአምላክን አገዛዝ እንደሚመርጡ የሚያሳዩ ሕዝቦች ይገኙ ይሆን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች ወደ መጨረሻው ከፍተኛ የሥልጣኔ ዕድገት ላይ እንዲደርሱ አምላክ ጊዜ ፈቅዶላቸዋል

[ምንጭ]

የሻትል መንኰራኵር—በናሳ ፎቶ ላይ የተመሰረተ