አምላክ ዓላማዎቹን አሳውቆናል
ክፍል 4
አምላክ ዓላማዎቹን አሳውቆናል
1, 2. አምላክ በቅንነት ለሚጠይቁት ሰዎች መልሱን እንደሚሰጥ እንዴት እናውቃለን?
አፍቃሪ የሆነ አምላክ እርሱን ለሚፈልጉት ቅን ሰዎች ሁሉ ዓላማዎቹን ይገልጣል። አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው ለሚለውና ለመሳሰሉት ሰዎች ለሚነሱባቸው ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
2 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን “ብትፈልጉት ይገኝላችኋል።” “ምስጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ።” “በእውነት ጌታ [ይሖዋ አዓት] ምስጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” በማለት ይናገራል። — 1 ዜና መዋዕል 28:9፤ ዳንኤል 2:28፤ አሞጽ 3:7
መልሶቹ የት ይገኛሉ?
3. አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደ መልሱን የምናገኘው የት ነው?
3 አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደና ይህንንም ለማስቆም ምን እንደሚያደርግ ለሚነሱት ጥያቄዎች መልሶቹ የሚገኙት ለጥቅማችን ብሎ በመንፈሱ መሪነት ባስጻፈልን መዝገብ ውስጥ ነው። ይህም መዝገብ ቃሉ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” — 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
4, 5. መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ በእርግጥ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው። የሰውን ታሪክ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በትክክል ይገልጻል። ሰዎች ከመፈጠራቸው በፊት ወደነበረው ጊዜም አልፎ በመሄድ የሚተርክ መጽሐፍ ነው። ትንቢቶቹ የጊዜያችንንና ወደፊት የሚመጣውን ጊዜም የሚመለከቱ ስለሆኑ እኛ ለምንኖርበት ዘመንም የሚሠራ ነው።
5 ታሪክን በሐቅ በመመዝገብ ረገድ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ መረጃ ያለው ሌላ መጽሐፍ የለም። ለምሳሌ ያህል ከጥንቶቹ የዓለማውያን የብራና ጽሑፎች ውስጥ ዛሬ በእጅ ያሉት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ግን አንዳንዶቹ በሙሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ በከፊል የሆኑ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች (39ኙ የ“ብሉይ ኪዳን” መጻሕፍት) 6,000 ያህል የብራና ጽሑፎች፤ ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች (27ቱ የ“አዲስ ኪዳን” መጻሕፍት) ደግሞ 13,000 ያህል ጥንታውያን የብራና ጽሑፎች ይገኛሉ።
6. ዛሬ ያለን መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በመጀመሪያ በመንፈሱ ካስጻፈው ጋር በመሠረቱ አንድ መሆኑን እርግጠኛ ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
6 መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በእነዚህ የብራና ጽሑፎች ውስጥ የበኩረ ጽሑፉ ሐሳብ በትክክል ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ያሉት መጽሐፍ ቅዱሶቻችን በመንፈስ መሪነትና አነሳሽነት ከተጻፉት ከመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ጋር በሐሳብ ይዘታቸው በመሠረቱ አንድ ናቸው። ይህን ለመገንዘብ የሚረዳን ሌላው ነገር አንዳንድ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የብራና ቅጂዎች የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ከተጻፉ በኋላ መቶ ዓመት በማያልፍ ጊዜ ውስጥ የተጻፉ መሆናቸው ነው። እስከ ዛሬ ያሉት የጥንት ዓለማዊ ጸሐፊዎች የጻፉአቸው የብራና ጽሑፍ ቅጂዎች ወደ መጀመሪያዎቹ ጽሑፎች በብዙ መቶ በሚቆጠሩ ዓመታትም የሚጠጉ እንኳን እምብዛም አይገኙም።
የአምላክ ስጦታ
7. የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭት የቱን ያህል ሠፊ ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ በሠፊው በመሰራጨት በኩል ተወዳዳሪ የማይገኝለት መጽሐፍ ነው። ሦስት ቢልዮን የሚያህሉ ቅጂዎች ታትመዋል። ወደዚህ ቁጥር የሚጠጋ ሌላ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ በሞላውም ሆነ በከፊል 2,000 በሚያህሉ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። በመሆኑም 98 በመቶ የሚሆኑት የፕላኔታችን ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱስን ሊያነቡ እንደሚችሉ ተገምቷል።
8-10.መጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምረው የሚገባ መሆኑን የሚያሳዩ አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
* የሕይወትን ዓላማ፣ የዓለምን ሁኔታዎች ትርጉምና የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ እንደሚመጣ ይገልጻል። ይህን ማድረግ የሚችል ሌላ መጽሐፍ የለም።
8 የአምላክ ቃል እንደሆነ የሚናገርና ለእውነተኛነቱም ማንኛውም ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ማስረጃ ያለው መጽሐፍ ልንመረምረው የሚገባ መሆኑ አያጠራጥርም።9 አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰብአዊው ቤተሰብ ሓሳቡን የሚያሳውቅበት መጽሐፍ ነው። መጽሐፉንም 40 የሚያህሉ ሰዎች በአንቀሳቃሽ ኃይሉ ወይም በመንፈሱ ተመርተው እንዲጽፉት አድርጓል። ይህም በመሆኑ አምላክ ለእኛ የሚናገረው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ በእውነት እንዳለ . . . እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ” አልተቀበላችሁትም በማለት ጽፏል። — 1 ተሰሎንቄ 2:13
10 የዩናይትድ እስቴትስ 16ኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን መጽሐፍ ቅዱስን “አምላክ ለሰው ከሰጠው ስጦታ ሁሉ የበለጠው ስጦታ ነው . . . እሱ ባይኖር ኖሮ መልካሙን ከመጥፎ ለይተን አናውቅም ነበር” በማለት ተናግረዋል። አሁን ታዲያ ይህ ከሁሉ የበለጠ የአምላክ ስጦታ መከራ እንዴት እንደጀመረ፣ አምላክ መከራን ለምን እንደፈቀደና እሱን ለማስወገድ ምን እንደሚያደርግ ምን ይነግረናል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ የሚተርከው ሁሉ ትክክለኛ ስለመሆኑ ተጨማሪ ዝርዝር ማስረጃዎችን ለማግኘት በኒውዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ— የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ይመልከቱ።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ዓላማውን ያሳወቀበት መጽሐፍ ነው