በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የሚያመጣው ግሩም የሆነ አዲስ ዓለም

አምላክ የሚያመጣው ግሩም የሆነ አዲስ ዓለም

ክፍል 10

አምላክ የሚያመጣው ግሩም የሆነ አዲስ ዓለም

1, 2. ከአርማጌዶን የማጽዳት ጦርነት በኋላ ምን ይፈጸማል?

አምላክ በአርማጌዶን የማጽዳት ጦርነት ካደረገ በኋላ ምን ይመጣል? እጅግ ግሩም የሆነ አዲስ ዘመን ይጀምራል። ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች ለአምላክ አገዛዝ ታማኞች መሆናቸውን ያረጋገጡ ስለሚሆኑ ወደ አዲሱ ዓለም ይገባሉ። ለሰብአዊው ቤተሰብ ከአምላክ ዘንድ አስደናቂ ጥቅሞች ስለሚፈሱላቸው ያ ጊዜ ምን ዓይነት አስደሳች አዲስ የታሪክ ወቅት ይሆናል!

2 ከጥፋት የተረፉት ሰዎች የአምላክ መንግሥት የምትሰጣቸውን መመሪያ እየተከተሉ ገነትን ማልማት ይጀምራሉ። ጉልበታቸው በዚያን ጊዜ የሚኖሩትን ሁሉ የሚጠቅም ራስ ወዳድነት የሌለበት ተግባር ለመፈጸም ይውላል። ምድር ውብ፣ ሰላማዊና አስደሳች የሰው መኖሪያ ወደመሆን ትለወጣለች።

ክፋት በጽድቅ ይተካል

3. ከአርማጌዶን በኋላ ወዲያው የሚሰማን እፎይታ ምንድን ነው?

3 የሰይጣን ዓለም መጥፋቱ ለዚህ ሁሉ ለውጥ በር ይከፍታል። ከዚያ ወዲያ መከፋፈልን የሚያስከትሉት የሐሰት ሃይማኖቶች፣ ማኅበራዊ ሥርዓቶች ወይም መስተዳድሮች አይኖሩም። ሰዎችን ለማታለል የሚያገለግል ሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳ አይኖርም፤ ፕሮፓጋንዳውን የሚፈጥሩት ድርጅቶች በሙሉ ከሰይጣን ሥርዓት ጋር ይንኮታኮታሉ። እስቲ አስቡት:- መርዛማው የሰይጣን ዓለም በሙሉ ተገፍፎ ይወገዳል! እንዴት ያለ ግልግል ይሆንልናል!

4. በዚያን ጊዜ በሚካሄደው የትምህርት አሰጣጥ ላይ የሚደረገውን ለውጥ ግለጽ።

4 ከዚያ በኋላ በሰው አገዛዝ ውስጥ ያሉት አጥፊ አስተሳሰቦች ከአምላክ በሚመጣ ገንቢ ትምህርት ይተካሉ። “ልጆችሽም ሁሉ [ከይሖዋ አዓት] የተማሩ ይሆናሉ።” (ኢሳይያስ 54:13) ይህ ጤናማ ትምህርት ከዓመት ዓመት ያለማቋረጥ ሲሰጥ “ውሃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር [ይሖዋን አዓት] በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:9) ሰዎች ዳግመኛ መጥፎ የሆነ ነገርን አይማሩም፤ በዚህ ፈንታ “በዓለም የሚኖሩ ጽድቅን ይማራሉ።” (ኢሳይያስ 26:9) ገንቢ አስተሳሰብና ድርጊት የሰው ዕለታዊ መመሪያ ይሆናል።—ሥራ 17:​31፤ ፊልጵስዩስ 4:8

5. ክፋትና ክፉ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?

5 በመሆኑም ግድያ፣ ዓመጽ፣ በፆታ መደፈር፣ ዝርፊያ፣ ወይም ማንኛውም ዓይነት ሌላ ወንጀል አይኖርም። በሌሎች የክፋት ድርጊት ምክንያት የሚሰቃይ ሰው አይኖርም። ምሳሌ 10:30 “ጻድቃን ለዘላለም አይናወጡም፤ ኃጥአን ግን በምድር ላይ አይቀመጡም” ይላል።

ፍጹም ጤንነት ይመለሳል

6, 7. (ሀ) መንግሥቲቱ የምታስቀረው የትኞቹን አሁን ያሉ ነገሮችን ነው? (ለ) ኢየሱስ በምድር ሳለ ይህን ያሳየው እንዴት ነው?

6 በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ዓመፅ መጥፎ ውጤቶች በሙሉ ተገልፍፈው ይወገዳሉ። ለምሳሌ ያህል የመንግሥቲቱ አገዛዝ በሽታንና እርጅናን ያስወግዳል። ባሁኑ ጊዜ መልካም ጤና ያለን ብንሆንም በመጨረሻው እስክንሞት ድረስ በዕድሜ እየገፋን በሄድን ቁጥር ዐይኖቻችን መፍዘዛቸው፣ የመስማት ችሎታችንም እየደበዘዘ መምጣቱ፣ ቆዳችን መጨማደዱ፣ የውስጥ አካላችንም መፈራረሱ አይቀርም።

7 ይሁን እንጂ እነዚህ ከመጀመሪያ ወላጆቻችን የወረስናቸው አሳዛኝ ውጤቶች በቅርብ ጊዜ ይቀራሉ። ኢየሱስ በምድር ሳለ ጤንነትን በተመለከተ ምን እንዳሳየ ያስታውሳሉን? መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፣ ዕውሮችንም፣ ዲዳዎችንም፣ ጉንድሾችንም፣ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፣ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፣ ጉንድሾችም ሲድኑ፣ አንካሶችም ሲሄዱ፣ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ” ይላል።—ማቴዎስ 15:30, 31

8, 9. በአዲሲቱ ዓለም ፍጹም ጤንነት በሚመለስበት ጊዜ የሚኖረውን ደስታ ግለጽ።

8 በአዲሱ ዓለም ሕመማችን በሙሉ ስለሚወገድ ምን ዓይነት ታላቅ ደስታ ይመጣልናል! በጤና ዕጦት ምክንያት የሚመጣ ሥቃይ ዳግመኛ አናየውም። “በዚያም የሚኖር ‘ታምሜያለሁ’ አይልም።” “በዚያን ጊዜ የዕውሮች ዐይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6

9 በየዕለቱ ጧት ከእንቅልፍህ ስትነሣ ደስ የሚል ጤንነት እንዳገኘህ ሲሰማህ በጣም አስደናቂ አይደለምን? ያረጁ ሰዎች የወጣትነት ብርታታቸው እንደተመለሰላቸውና አዳምና ሔዋን መጀመሪያ የነበሩበትን ፍጽምና እንዳገኙ ማወቃቸው መንፈስን የሚያረካ አይደለምን? መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጉብዝናውም ወራት ይመለሳል” በማለት ቃል ገብቷል። (ኢዮብ 33:25) የዐይን መነፅሮችን፣ መስማት ለተሳናቸው ለመስማት የሚረዱ መሣሪያዎችን፣ ምርኩዞችን፣ ተሽከርካሪ ጋሪዎችንና መድሃኒቶችን መወርወር ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! ከዚያ ወዲያ ሆስፒታሎች፣ ዶክተሮችና የጥርስ ሐኪሞች አያስፈልጉም።

10. ሞት ምን ይሆናል?

10 እንዲህ ዓይነቱን ደስ የሚል ጤንነት ያገኙ ሰዎች ለመሞት አይፈልጉም። የሰው ዘር በተወረሰው አለፍጽምናና ሞት መዳፍ ውስጥ ዳግመኛ ስለማይወድቅ መሞትም አያስፈልጋቸውም። ክርስቶስ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው።” “የእግዚአብሐር የጸጋ ሥጦታ ግን የዘላለም ሕይወት ነው።”—1 ቆሮንቶስ 15:25, 26፤ ሮሜ 6:23፤ ኢሳይያስ 25:8​ንም ተመልከቱ።

11. የራዕይ መጽሐፍ የአዲሲቱን ዓለም በረከቶች አጠቃሎ የሚገልጻቸው እንዴት ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመጨረሻው መጽሐፍ ለሰብአዊው ቤተሰብ ከአሳቢው አምላክ ዘንድ የሚፈሱትን ጥቅሞች ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ “ዕንባዎችንም ሁሉ ከዐይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ይላል።—ራዕይ 21:3, 4

ሙታን ተመልሰው ይመጣሉ

12. ኢየሱስ ከአምላክ የተሰጠውን ሙታንን የማስነሳት ኃይል ያሳየው እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ የታመሙትንና ሽባዎችን ከመፈወስ የበለጠ ነገርም አድርጓል። የሞቱ ሰዎችንም ከመቃብር አስነስቷል። እንዲህ በማድረጉም አምላክ ለእርሱ የሰጠውን ሙታንን የማስነሳት አስደናቂ ኃይል አሳይቷል። ኢየሱስ ሴት ልጁ ወደሞተችበት ሰው ቤት የመጣበትን ጊዜ ያስታውሳሉን? ኢየሱስ ለሞተችው ልጃገረድ “አንቺ ብላቴና ተነሺ እልሻለሁ” አላት። ውጤቱስ ምን ነበር? “ወዲያው ቆማ ተመላለሰች።” በዚያ የነበሩ ሰዎች ይህን ሲመለከቱ “ታላቅ መገረም ተገረሙ።” ደስታቸውን አምቀው መያዝ አልቻሉም ነበር!—ማርቆስ 5:41, 42፤ በተጨማሪም ሉቃስ 7:11–16ንና ዮሐንስ 11:1–45 ይመልከቱ።

13. ትንሣኤ የሚያገኙት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

13 በአዲሲቱ ዓለም “ጻድቃንም አመጸኞችም ከሙታን ይነሣሉ።” (ሥራ 24:15) ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ይሆናል” በማለት ስለተናገረ በዚያን ጊዜ አምላክ የሰጠውን ኃይል ሙታንን ለማስነሣት ይጠቀምበታል። (ዮሐንስ 11:25) በተጨማሪም “በመታሰቢያ መቃብር [በአምላክ ማስታወሻ ውስጥ] ያሉት ሁሉ ድምፁን [የኢየሱስን ድምፅ] ሰምተው የሚወጡበት ጊዜ ይመጣል” ብሏል።—ዮሐንስ 5:28, 29

14. ሞት የማይኖር በመሆኑ ምክንያት ምን ነገሮች ይቀራሉ?

14 የሞቱ ሰዎች ከሚወዷቸው ጋር ለመገናኘት በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ ሕይወት ሲመለሱ በምድር ዙሪያ የሚኖረው ደስታ ታላቅ ይሆናል! ከዚያ ወዲያ በሕይወት ያሉ ሰዎችን የሚያሳዝኑ በጋዜጣ የሚወጡ የመርዶ ዐምዶች አይኖሩም። በዚያ ምትክ የዚህ ቀጥተኛ ተቃራኒ ይኖራል። ይኸውም ለሚወዷቸው ሰዎች ምሥራች የሚያመጡ አዲስ የተነሱ ሰዎችን ስም ዝርዝር የሚገልጹ ማስታወቂያዎች ይኖራሉ። ከዚያ ወዲያ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች፣ የሰውን ሬሳ በእሳት ማቃጠል፣ የሬሳ ማቃጠያ ሥፍራዎች ወይም የመቃብር ቦታዎች አይኖሩም!

እውነተኛ ሰላም የሰፈነበት ዓለም

15. የሚክያስ ትንቢት ሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?

15 በማንኛውም የኑሮ መስክ እውነተኛ ሰላም ይረጋገጣል። ጦርነቶች፣ የጦርነት አስፋፊዎች ወይም ለፋፊዎችና የጦር መሣሪያዎችን ማምረት የቀሩ ነገሮች ይሆናሉ። ለምን? ምክንያቱም ከፋፋይ የሆነው የብሔር፣ የጎሣና የዘር የጥቅም ግጭት አይኖርም። በዚያን ጊዜ በሁሉም አንፃር “ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል።—ሚክያስ 4:3

16. አምላክ ጦርነትን የማይታሰብ ነገር የሚያደርገው እንዴት ነው?

16 ይህም የማያቋርጥ ጦርነት ደም ጥማት ካቃጠለው የሰው ታሪክ አንፃር ሲታይ የሚያስገርም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ያ ሁሉ ደም ማፋሰስ ሊመጣ የቻለው የሰው ልጅ በሰውና በአጋንንት አገዛዝ ሥር ስለነበረ ነው። በአዲሲቱ ዓለም በመንግሥቲቱ አገዛዝ ሥር ግን የሚፈጸመው የሚከተለው ነው:- የይሖዋን “ሥራ በምድር ያደረገውንም ተአምራት እንድታዩ ኑ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።”—መዝሙር 46:8, 9

17, 18. በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ በሰዎችና በእንስሳት መካከል ምን ዓይነት ዝምድና ይኖራል?

17 ሰውና አራዊትም በኤደን ገነት እንደነበሩት ዓይነት በሰላም ይኖራሉ። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:19) አምላክ እንዲህ ብሏል:- “በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ . . . ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ።”—ሆሴዕ 2:18 (በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ 2:​20)

18 ያ ሰላም የቱን ያህል ስፋት ይኖረው ይሆን? “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።” እንስሳት ዳግመኛ ለሰዎችም ሆነ እርስ በርሳቸው የሚያስፈሩ አይሆኑም። ሌላው ቀርቶ “አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል”!—ኢሳይያስ 11:6–9፤ 65:25

ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች

19. ምድር ወደ ምንነት ትለወጣለች?

19 መላዋ ምድር ለሰው ልጆች ወደ ገነትነት የተለወጠች መኖሪያ ትሆንላቸዋለች። ኢየሱስ በእርሱ ላመነው ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት ቃል የገባለት ለዚህ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሃውም ሐሴት ያደርጋል እንደ ጽጌረዳም ያብባል . . . በምድረ በዳ ውሃ፣ በበረሃም ፈሳሽ ይፈልቃልና” በማለት ይናገራል።—ሉቃስ 23:43፤ ኢሳይያስ 35:1, 6

20. ረሀብ ሰዎችን ዳግመኛ የማያጠቃው ለምንድን ነው?

20 በአምላክ መንግሥት ሥር ረሀብ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ማጥቃቱ ዳግመኛ አይመለስም። “በምድር ላይ በቂ እህል ይኖራል፤ ተራሮችም በሰብል ይሸፈናሉ።” “የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ምርቷን ትሰጣለች፤ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ።”—መዝሙር 72:16፤ ሕዝቅኤል 34:⁠27

21. ቤት አጥነት፣ ቆሻሻ ሠፈሮችና ደሳሳ ጎጆዎች እንዲሁም መጥፎ አካባቢዎች ምን ይሆናሉ?

21 ከዚያ ወዲያ ዳግመኛ ድህነት፣ መኖሪያ ቤት እጦት፣ ቆሻሻ ሠፈሮችና ደሳሳ ጎጆዎች ወይም በወንጀል የተወረሩ አካባቢዎች አይኖሩም። “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም።” “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22፤ ሚክያስ 4:4

22. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ አገዛዝ የሚያመጣቸውን በረከቶች የሚገልጸው እንዴት አድርጎ ነው?

22 ሰዎች በገነት ውስጥ በእነዚህና በሌሎችም ነገሮች ይባረካሉ። መዝሙር 145:16 “አንተ [አምላክ] እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” ይላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ብሎ መናገሩ አያስደንቅም።—መዝሙር 37:11, 29

የደረሰውን ጉዳት መጠገን

23. የአምላክ መንግሥት የደረሰብንን መከራ በሙሉ የምታስረሳን እንዴት ነው?

23 የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ባለፉት ስድስት ሺህ ዓመታት በሰብአዊው ቤተሰብ ላይ የደረሰውን ጉዳት በሙሉ ትጠግናለች። በዚያን ጊዜ የሚኖረው ደስታ ሰዎች ከደረሰባቸው ከማንኛውም ስቃይ እጅግ የሚልቅ ይሆናል። በፊት የደረሰው ሥቃይ መጥፎ ትዝታ ሕይወትን የሚረብሽ አይሆንም። በዚያን ጊዜ የሰዎች የዕለታዊ ኑሮ ክፍል የሚሆኑት ገንቢ አስተሳሰቦችና ሥራዎች የሚሰቀጥጡ ትውስታዎችን ቀስ በቀስ ፍቀው ያጠፏቸዋል።

24, 25. (ሀ) ኢሳይያስ የተነበየው ምን ይሆናል ብሎ ነው? (ለ) ያለፈው ሥቃይ ትውስታዎች እንደሚደበዝዙና እንደሚጠፉ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

24 ለሰዎች አሳቢ የሆነው አምላክ “እነሆ አዲስ ሰማይ [በሰው ልጆች ላይ የምትገዛ ሰማያዊት መስተዳድርና] አዲስ ምድር [ጻድቅ ሰብአዊ ህብረተሰብ] እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ” ብሎ ተናግሯል። “ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች።”—ኢሳይያስ 14:7፤ 65:17, 18

25 ስለዚህ አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ይህን ለሚያህል ረዥም ዘመን የቆየውን መጥፎ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በመሻር ተቃራኒ የሆኑ ሁኔታዎችን ያመጣል። ባለፈው ጊዜ የደረሰብንን ጉዳት ከመካስ በላይ የሆኑ በረከቶችን በላያችን በማዝነብ ለእኛ ያለውን ከፍተኛ አሳቢነት ለዘላለም ዓለም ያሳያል። በቀድሞ ጊዜ የደረሱብን መከራዎች በሙሉ በዚያን ጊዜ ልናስታውሳቸው ብንፈልግም እስከማንችል ድረስ ስለእነርሱ ያለን ትውስታ ይደበዝዛል።

26. አምላክ ላለፈ ሥቃያችን የሚክሰን ለምንድን ነው?

26 በዚህ ዓለም ያሳለፍነውን ሥቃይ አምላክ የሚክሰን እንዲህ አድርጎ ነው። ከመጀመሪያ ወላጆቻችን አለፍጽምናን በመውረሳችን ምክንያት ፍጽምና የጎደለን ሆነን የተወለድነው በራሳችን ጥፋት እንዳልሆነ ያውቃል። አዳምና ሔዋን ታማኝነታቸውን ቢጠብቁ ኖሮ በገነት ውስጥ ልንወለድ እንችል ነበር፤ ስለዚህ በሰይጣናዊ ዓለም ውስጥ የተወለድነው በራሳችን ምርጫ ወይም ጥፋት አይደለም። ስለዚህ አምላክ በታላቅ ርኅራኄው ያሳለፍነውን ችግር ከመካስ የበለጠ ነገር ያደርጋል።

27. በአዲሲቱ ዓለም አስደናቂ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ምን ትንቢቶች ናቸው?

27 በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ በሮሜ 8:21, 22 ላይ ይመጣል ተብሎ የተነገረለትን ነፃነት ያገኛል:- “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና።” ያኔ ሰዎች “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” የሚለው ጸሎት ሙሉ በሙሉ ሲፈጸም ያያሉ። (ማቴዎስ 6:10) በገነት ምድር ላይ የሚኖሩት ግሩም ሁኔታዎች በሰማይ ያሉትን ሁኔታዎች የሚያንፀባርቁ ይሆናሉ።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዲሲቱ ዓለም የሸመገሉ ሰዎች ወደ ጉብዝናቸው ብርታት ይመለሳሉ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዲሲቱ ዓለም በሽታና አካለ ስንኩልነት በሙሉ ይቀራል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዲሲቱ ዓለም ሙታን ወደ ሕይወት ይመለሳሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ከዚያ በኋላ የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም’ (የ1980 እትም)

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በገነት ውስጥ ሰዎችና እንስሳት በፍጹም ሰላም አብረው ይኖራሉ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘አምላክ እጁን ከፍቶ ሕይወት ላለው ሁሉ ፍላጎቱን ያሟላለታል’

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት ያሳለፍነውን ሥቃይ በሙሉ በሚያስረሳ ሁኔታ ትክሰናለች