አስደናቂው ነፃ ምርጫ የማድረግ ስጦታ
ክፍል 5
አስደናቂው ነፃ ምርጫ የማድረግ ስጦታ
1, 2. የአፈጣጠራችን ክፍል የሆነው የትኛው አስደናቂ ስጦታ ነው?
አምላክ መከራ እንዲኖር ለምን እንደፈቀደና እሱን ለማስወገድ ምን እያደረገ እንዳለ እንዲገባን ከተፈለገ እንዴት አድርጎ እንደፈጠረን እንዲገባን ያስፈልጋል። አምላክ ሲፈጥረን የሰጠን ሰውነትና አንጎል ብቻ አይደለም። ልዩ የሆኑ የአእምሮና የስሜት ባሕርያትም ሰጥቶ ፈጥሮናል።
2 የአእምሮአዊና የስሜታዊ አሠራራችን አንዱ ቁልፍ የሆነ ክፍል ነፃ ምርጫ የማድረግ ችሎታ ነው። አዎ፣ አምላክ በውስጣችን የመምረጥ ነፃነትን ቀርጾብናል። እሱም በእርግጥ ከአምላክ የተሰጠ ድንቅ ስጦታ ነው።
እንዴት እንደተሠራን
3-5. ነፃ ምርጫን የምንወደው ለምንድን ነው?
3 አምላክ መከራ እንዲኖር ሲፈቅድ በነገሩ ውስጥ ነፃ ምርጫ እንዴት እንደገባ እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ እስቲ የሚከተለውን አስቡበት:- ምን እንደምትናገር፣ ምን እንደምትበላ ወይም እንደምትለብስ፣ ምን ዓይነት ሥራ እንደምትሠራና የትና እንዴት እንደምትኖር የመምረጥ ነፃነት ያለህ በመሆኑ ደስ ይልሃልን? ወይስ እያንዳንዱን ቃልህንና ተግባርህን በየዕለቱ በግድ ሌላ ሰው እንዲወስንልህ ትፈልጋለህን?
4 ትክክለኛ አእምሮ ያለው ማንም ሰው አኗኗሩ ሙሉ በሙሉ ከራሱ ቁጥጥር ውጭ እንዲደረግበት አይፈልግም። ለምን? ምክንያቱም አምላክ እኛን የፈጠረው በዚያ መንገድ ስላልሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰውን ‘በመልኩና በአምሳሉ’ እንደፈጠረው ይነግረናል፤ ከአምላክ ባሕርያት አንዱ ደግሞ የመምረጥ ነፃነት ነው። (ዘፍጥረት 1:26፤ ዘዳግም 7:6) አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር ያንኑ ድንቅ ባሕሪዩ የሆነውን የነፃ ምርጫ ስጦታ ሰጣቸው። በጨቋኝ ገዢዎች በባርነት መያዝ የሚያበሳጨንም ለዚህ ነው።
5 ስለዚህ አምላክ የነፃነት አምላክ ስለሆነ ነፃነትን ብንመኝ ድንገት የመጣ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “[የይሖዋ አዓት] መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ስለዚህ አምላክ ነፃ ምርጫን የባሕሪያችን ክፍል አድርጎ ሰጥቶናል። የአእምሮአችንንና የስሜታችንን አሠራር ስለሚያውቅም ነፃ ምርጫ ቢኖረን ይበልጥ ደስተኞች እንደምንሆን ያውቅ ነበር።
6. አምላክ አእምሮአችንን ከነፃ ምርጫ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራ አድርጎ የፈጠረው እንዴት ነው?
6 ከነፃ ምርጫ ጋር ጐን ለጎን የሚሄዱትን የማሰብ ችሎታ፣ ማመዛዘን፣ ውሳኔ ማድረግንና ጥሩውን ከመጥፎ ለይቶ ማወቅንም አምላክ ሰጥቶናል። (ዕብራውያን 5:14) በመሆኑም ነፃ ምርጫ አስቦ በሚደረግ ምርጫ ላይ የሚመሠረት ነው። እኛ ሰዎች የራሳቸው ፈቃድ ወይም ምርጫ እንደሌላቸው እንደ ሮቦቶች አእምሮ ቢስ ሆነን አልተፈጠርንም፣ ወይም ደግሞ እንደ እንስሳት በውስጣችን በተቀረጸ ፕሮግራም የምንመራ ሆነን አልተፈጠርንም። ከዚህ ይልቅ አስደናቂው አንጎላችን ከመምረጥ ነፃነታችን ጋር ተቀናጅቶ እንዲሠራ የተፈጠረ ነው።
እንከን የሌለው ጅምር
7, 8. አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ምን ግሩም ጅምር ሰጥቷቸው ነበር?
7 አምላክ ለመጀመሪያ ወላጆቻችን ለአዳምና ለሔዋን ከነፃ ምርጫ ስጦታ በተጨማሪ ማንም ሰው ቢያገኛቸው የሚደሰትባቸውን ነገሮች ሁሉ በመስጠት ምን ያህል አሳቢ እንደሆነ አሳይቷል። አዳምና ሔዋንን በአንድ ትልቅ የመናፈሻ ዓይነት የአትክልት ሥፍራ አስቀመጣቸው። ቁሳዊ ነገሮች ተትረፍርፈውላቸው ነበር። አርጅተው ወይም ታመው እንዳይሞቱ የሚያስችል ፍጹም አእምሮና አካል ስለነበራቸው ለዘላለም ሊኖሩ ይችሉ ነበር። አስደሳች የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት የሚኖራቸው ፍጹማን ልጆችን ሊወልዱ ይችሉ ነበር። ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄደው ሕዝብም መላዋን ምድር ወደ ገነትነት የመለወጥ አርኪ ሥራ ነበረው። — ዘፍጥረት 1:26–30፤ 2:15
8 አምላክ ያዘጋጀውን ነገር ሁሉ በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ይለናል። (ዘፍጥረት 1:31) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ሥራው ፍጹም ነው” በማለት ስለ አምላክ ይናገራል። (ዘዳግም 32:4) አዎ፣ ፈጣሪ ለሰብአዊው ቤተሰብ ፍጹም የሆነ ጅምር ሰጥቶት ነበር። ከዚህ የተሻለ ጅምር ሊኖር አይችልም ነበር። ምን ያህል አሳቢ መሆኑን ያረጋገጠ አምላክ ነው!
ነፃነት በገደብ
9, 10.ነፃ ምርጫ ተገቢ በሆነ መንገድ ገደብ ሊበጅለት የሚገባው ለምንድን ነው?
9 ይሁን እንጂ ነፃ ምርጫ ገደብ የሌለው እንዲሆን የአምላክ ዓላማ ነበርን? ምንም የትራፊክ ሕግ የሌለበትን ሁሉም ሰው በፈለገው አቅጣጫና ፍጥነት መኪና ሊያሽከረክር የሚችልበት መኪናና ሰው የሚበዛበትን ከተማ እስቲ ያስቡ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ባሉበት መኪና መንዳት ይፈልጉ ነበርን? አይፈልጉም። ምክንያቱም ይህ ሁኔታ የትራፊክ ግርግር ፈጥሮ አደጋዎች እንደሚያስከትል የማያጠራጥር ስለሆነ ነው።
10 የአምላክ የነፃ ምርጫ ስጦታም እንዲሁ ነው። ገደብ የሌለው ነፃነት መስጠት በኅብረተሰብ ውስጥ ሥርዓት አልበኛነትን ያመጣል። የሰውን እንቅስቃሴ የሚመሩ ሕጎች መኖር አለባቸው። የአምላክ ቃል “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ (ማሳበቢያ) እንዲሆን አታድርጉ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:16) ለጋራ ደህንነት ሲባል አምላክ ነፃ ምርጫ ደንብና ሥርዓት እንዲኖረው ይፈልጋል። ዓላማው እኛ ፍጹም ነፃነት እንዲኖረን ሳይሆን ለሕግ የበላይነት ተገዥ የሆነ አንፃራዊ ነፃነት እንዲኖረን ነበር።
የማንን ሕጎች?
11.የተፈጠርነው የማንን ሕግ እንድንታዘዝ ሆነን ነው?
11 የማንን ሕጎች ማክበር እንዳለብን ሆነን ተፈጥረናል? በጀሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የ1 ጴጥሮስ ሁለተኛው ክፍል “የአምላክ ባሪያዎች እንጂ የሌላ የማንም ባሪያዎች አይደላችሁም” ይላል። የአምላክ ባሪያዎች መሆን የጭቆና ባርነት ሳይሆን ለአምላክ ሕጎች ስንገዛ ደስተኞች እንድንሆን ተደርገን ተፈጥረናል ማለት ነው። ( 2:16ማቴዎስ 22:35–40) የአምላክ ሕጎች በሰዎች ከተረቀቁት ከማንኛቸውም ሕጎች የተሻለ መምሪያ ይሰጣሉ። “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ [ይሖዋ አዓት] ነኝ።” — ኢሳይያስ 48:17
12. በአምላክ ሕጎች የአጥር ክልል ውስጥ ምን የመምረጥ ነፃነት አለን?
12 የዚያኑ ያህልም የአምላክ ሕጎች በአጥራቸው ክልል ውስጥ ከፍተኛ የምርጫ ነፃነት የሚሰጡ ናቸው። ይህም ልዩ ልዩ ዓይነት ነገር እንዲኖር በማስቻል ሰብአዊውን ቤተሰብ አስደናቂ የሚያደርግ ነው። በመላው ዓለም ላይ ስላሉት ልዩ ልዩ ዓይነት ምግቦች፣ ልብሶች፣ ሙዚቃ፣ ኪነ ጥበብና ቤቶች እስቲ አስቡ። በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ሌላ ሰው ከሚወስንልን ይልቅ ራሳችን መምረጥ እንፈልጋለን።
13. ለራሳችን ጥቅም ስንል ምን የተፈጥሮ ሕጎችን መታዘዝ አለብን?
13 ስለዚህ የተፈጠርነው አምላክ ስለሰው ምግባር ላወጣቸው ሕጎች በምንገዛበት ጊዜ ደስተኞች እንድንሆን ነው። ሁኔታው ለአምላክ የተፈጥሮ ሕጎች ከመገዛት ጋር ይመሳሰላል። ለምሳሌ ያህል የስበትን ሕግ ችላ ብለን ከከፍተኛ ቦታ ላይ ብንዘል እንሰበራለን ወይም እንሞታለን። የሰውነታችንን የውስጥ ሕጎች ችላ ብለን ምግብ መብላትና ውሃ መጠጣት ወይም አየር መተንፈስ ብናቆም እንሞታለን።
14. ሰዎች ከአምላክ ተነጥለው ለመኖር እንዳልተፈጠሩ እንዴት እናውቃለን?
14 ለአምላክ የተፈጥሮ ሕጎች መገዛት እንደሚያስገልገን ሆነን የተፈጠርን መሆናችን የተረጋገጠ የመሆኑን ያህል ለአምላክ የሥነ ምግባርና የማህበራዊ ሕጎችም መገዛት ያስፈልገናል። (ማቴዎስ 4:4) ሰዎች የተፈጠሩት ራሳቸውን ከፈጣሪያቸው ቢለዩ እንደሚቀናቸው ሆነው አይደለም። ነቢዩ ኤርምያስ “አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ። አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። አቤቱ [ይሖዋ አርመኝ አዓት]” ብሏል። (ኤርምያስ 10:23, 24) ስለዚህ ሰዎች በማንኛውም መንገድ የተፈጠሩት በአምላክ አገዛዝ ሥር እንጂ በራሳቸው አገዛዝ ሥር እንዲኖሩ አይደለም።
15. የአምላክ ሕጎች ለአዳምና ለሔዋን ከባድ ሸክም ይሆኑባቸው ነበርን?
15 ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለአምላክ ሕጎች መታዘዝ ከባድ ሸክም አይሆንባቸውም ነበር። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ሕጎች መታዘዙ ለራሳቸውና ለመላው ሰብአዊ ቤተሰብ ደህንነት የሚበጅ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከአምላክ ሕጎች ገደብ ውስጥ ባይወጡ ኖሮ ጥሩ ይሆን ነበር። እንዲያውም አሁን እርስ በርሳችን የምንዋደድና የተባበርን ቤተሰቦች ሆነን ግሩም በሆነች ገነት ውስጥ በመኖር ላይ በሆንን ነበር! ክፋት፣ ሥቃይና ሞት አይኖሩም ነበር።
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈጣሪ ለሰዎች ፍጹም አጀማመር አድርጎላቸዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የትራፊክ ሕግ ባይኖር ኖሮ ተሽከርካሪ በበዛበት መንገድ መንዳት ይፈልጉ ነበርን?